June 24, 2013
12 mins read

Sport: ፈርጉሰን ጠንካራ ቡድን ትተው አልፈዋል? እያጠያየቀ ነው

fergusen davids moyes

ሰር አሌክስ ፈርጉሰን ከአሰልጣኝነቱ በጡረታ ሲገለሉ ጠንካራ ቡድን ገንብተው እንዳለፉ ገልፀው ነበር፡፡ በእርግጥ አዲሱ ተሿሚ ዴቪድ ሞዬስ የተረከቡት ቡድን የፕሪሚየር ሊጉ ሻምፒዮን ነው፡፡ በርካታ የእግርኳስ ተንታኞችና ተጫዋቾቸ ማንቸስተር ዩናይትድ በጥሩ ደረጃ ላይ እንደሚገኝ ያምናሉ፡፡ እውነት ሰር አሌክስ ጠንካራ መሰረት ያለው ቡድን ትተው አልፈዋል?

 ፈርጉሰን የሊጉን ክብር ከኤቲሃድ ወደ ኦልድትራፎርድ በመመለስ በአሸናፊነት ግርማ ሞገስ ጡረታ ወጥተዋል፡፡ ስኮትላንዳዊው በ26 ዓመታት የዩናይትድ ቆይታቸው በዋንጫ ፉክክሩ እየተቀያየሩ የሚመጡባቸውን ቡድኖች ተራ በተራ ረትተዋቸዋል፡፡ ሊቨርፑልን በእንግሊዝ ከአንደኝነት ማማው ለማውረድ ተሳክቶላቸዋል፡፡ ሰር አሌክስ የአርሰናልን መውጣትና መውረድ ተመልክተዋል፡፡ ቼልሲና ማንቸስተር ሲቲ ጠንካራ ተፎካካሪ ሆነው ቢመጡባቸውም ፈርጉሰን ግን ዳግም የበላይ እንደሆኑ አሳይተዋል፡፡ ነገር ግን ፈርጉሰን ቡድኑን በጥሩ ሁኔታ ላይ ትተውት አላለፉም፡፡

በመጀመሪያ ዴቪደ ዴ ሂያን እናገኛለን፡፡ ፔተር ሽማይክል ክለቡን ሲለቅ እንደተከሰተው ሁሉ ኤድዊን ቫን ደር ሳር ጓንቱን ሲሰቅልም ዩናይትድ ትክክለኛ ተተኪ ማግኘት አልቻለም፡፡ ከ2011 ጀምሮ ሰር አሌክስ ስፔናዊውን ግብ ጠባቂ ከትችት ሲከላከሉትና ከሁለተኛ በረኛው አንደርስ ሊንደጋርድ ጋር በመቀያየር ሲያጫውቱት ነበር፡፡ በዩናይትድ የግብ ጠባቂ ችግር አሁንም አልተፈታም፡፡ በዴ ሂያ ላይ ጥያቄዎች የሚነሱ ሲሆን በክረምቱ ሞዬስ አዲስ በረኛ ለማምጣት ሊፈልጉ ይችላሉ፡፡

ዩናይትድ በግራ መስመር ተከላካይ ቦታም ክፍተት አለበት፡፡ ፓትሪስ ኤራ ከሁለት ወይም ሶስት ዓመታተ በፊት የነበረው ብቃት ላይ አይገኝም፡፡ ፈረንሳዊው ተጨዋች የቀድሞ አቋሙ አብሮት የለም፡፡ ክለቡም የኤቭራን ተተኪ መፈለግ ይኖርበታል፡፡ ሞዬስ ለረጅም ጊዜ በዩናይትድ የሚፈለገው ሌይተን ቤይንስ ከቀድሞ ክለባቸው በክረምቱ ቢያስፈርሙት አግራሞት የሚፈጥር አይሆንም፡፡

የሪዮ ፈርዲናንድና ኔሚኒያ ቪዲች ጉዳይም ሌላው ትልቅ ጥያቄ የሚነሳበት ነው፡፡ ሁለቱም የመሃል ተከላካዮች ዕድሜያቸው እየገፋ ሲሆን ለጉዳትም ቅርብ ናቸው፡፡ ፈርጉሰን የ34 ዓመቱን ፈርዲናንድና ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ከጉዳት ጋር እየታገለ የሚገኘውን ቪዲች ለሞዬስ አስተላልፈዋል፡፡ ስለዚህ አሰልጣኙ በክረምቱ የመሃል ተከላካይ ለማስፈረም ወደ ገበያ እንዲወጡ ሊገደዱ ይችላሉ፡፡ በእርግጥ ጆኒ ኢንስ ፊል ጆንስና ክሪስ ስሞሊንግ የመሳሰሉ ወጣቶች በቡድኑ ውስጥ ይገኛሉ፡፡ ፈርጉሰን እንደ እአነዚህ አይነት ተተኪ ወጣቶችን እንዳዘጋጁ መግለፅ ተገቢ ነው፡፡ ነገር ግን ጆንስ ከፊቱ ብሩህ ጊዜ ቢጠብቀውም በመሃል ተከላካይነት በቋሚነት ስለመጫወቱ እርግጠኛ መሆን አይቻልም፡፡ ስሞሊንግ በአንፃሩ ሌላው አማራጭ ቢሆንም እንደ ጆንስ አይነት መሻሻል ማሳየት አልቻሉም፡፡ ኢቫንስ ምርጥ ብቃቱ ላይ ስለመድረሱ ወደ ፊት የሚታይ ይሆናል፡፡

የመሃል ሜዳ አማካይ ክፍሉ አፋጣኝ የሆነ መልስ የሚያሻው ቦታ ነው፡፡ ቶም ክሌቨርሲ፣ ሺንጂ ካጋዋና ኒክ ፓዌል የመሳሉት ለወደፊቱ መልካም የሆኑ አማራጮችን ይፈጥራሉ፡፡ አሁን ካለው ስኳድ ውስጥ መተካት ያለባቸው ተጨዋቾች ይገኛሉ፡፡ ፖል ስኮልስ ከተጨዋችነት በመገለሉ ተተኪ የሚያስፈልገው ነው፡፡ ሪያን ጊግስ መጫወቱን ቢቀጥልም ወደ 40ኛ ዓመቱ እየተጠጋ በመሆኑ ጫማውን የመስቀያው ጊዜ ሩቅ አይደለም፡፡ አንደርሰን እና ልዊስ ናኒም ኦልድ ትራፎርድን መልቀቅ እንደሚፈልጉ ግልፅ አድርገዋል፡፡ ሁለቱን ተጨዋቾች እስካሁን እንዳይለቁ ያደረጓቸው ሰር አሌከስ የነበሩ መሆናቸው አሁን በሩ ክፍት ሊሆንላቸው ይችላል፡፡ በ2011/12 ድንቅ የውድድር ዘመን ያሳለፈው አንቶኒዮ ቫሌንሺያ በ2012/13 አቋሙ እጅግ ወርዶ አጠናቅቋል፡፡ ኢኳዶራዊው የክንፍ አማካይ ለዩናትድ ይመጥናል? ሞዬስ ተተኪውን ማምጣት ይኖርባቸዋል? በተለይ ናኒ ከለቀቀ ዩናይትድ በተጠናቀቀው የውድድር ዘመን ደካማ አቋም ያበረከተው አሽሊ ያንግና ወጣቱ ዊልፍሬድ ዛሃ ብቻ በክንፍ አማካይነት ይኖሩታል፡፡ ያንግ ክለቡን ከመልቀቅ ጋር ስሙ ተያይዟል፡፡ ታዲያ ይህ ቡድን በጠንካራ መሰረት ላይ ያለ ነው?

ዳረን ፍሌቸርም ከህመሙ ባለማገገሙ የተጫዋችነት ሕይወቱ አደጋ ውሰጥ ይገኛል፡፡ በዚህ ላይ 29 ዓመቱ ላይ የሚገኝ በመሆኑ ረጅም ጊዜ አልቀረውም፡፡ በሌላ በኩል ማይክል ካሪክ በእግርኳስ ህይወቱ ምርጡ ብቃት ላይ ይገኛል፡፡ ነገር ግን ዕደሜው 31 በመድረሱ በመጪዎቹ ዓመታት ተተኪ ያስፈልገዋል፡፡ ይህ ቢሆንም በዩናይትድ ውስጥ በአማካይ ክፍል ላይ ተጨዋቾች ዕድሜያቸው ገፍቶ የመጫወት ባህል አለ፡፡

በአጥቂ መስመር በኩል ደግሞ ለጊዜው ቡድኑ ጠንካራ ስብስብ አለው፡፡ ዳኒ ዌልቤክ በ2012/13 ጥሩ የውድድር ዘመን ባያሳልፍም ከፊቱ ብሩህ ጊዜ ይጠብቀዋል፡፡ ዌለቤክና ሀቪዬር ሄርናንዴዝ በ2013/14 የውድድር ዘመን ከቀድሞው በበለጠ የመጫወት ዕድል እንዲያገኙ መጠየቃቸው አይቀርም፡፡ ሮቢን ቫን ፔርሲም ዕድሜው ወደ 30 እየጠጋ ይገኛል፡፡ አብዛኞቹ የፊት መስመር ተጨዋቾች ዕድሜያቸው ከ32 ካለፈ እንደቀድሞው ጨራሽ የመሆን አቋማቸው ይቀንሳል፡፡ ስለዚህ ሞዬስ በመጪዎቹ ዓመታት በአጥቂ መስመር ላይ ሌላ ስራ ይጠብቃዋል፡፡ የዌይን ሩኒ ውዝግብም እስካሁን እልባት አላገኘም፡፡ እንግሊዛዊው አጥቂ የመልቀቂያ ጥያቄ ባስገባበት ወቅት ሰር አሌክስ ጡረታ በመውጣታቸው ተጨዋቹ በኦልድትራፎርድ እንዲቆይ ማሳመን በሞዬስ ጫንቃ ላይ ወድቋል፡፡

ሞዬስ በዩናይትድ ከባድ ስራ ይጠብቃዋል፡፡ የግብ ጠባቂ ሁኔታ፣ በግራ መስመር ተከላካይ የኤቭራ ተተኪ፣ ሁለቱን የመሃል ተከላካዮች መተካት፣ በዕድሜ መግፋት የሳሳውን የመሃል ክፈል ማጠናከር፣ በሚለቁት ተጨዋቾች እግር አዲስ ፈራሚዎች ማምጣትና በሩኒ ጉዳይ ላይ መፍትሄ መፈለግ ይኖርባቸዋል፡፡ ስለዚህ ሰር አሌክስ ዩናይትድን በተዳከመ ሁኔታ ለሞዬስ አስተላልፈዋል፡፡ ፈርጉሰን ቡድኑ በሽግግር ውስጥ ለመግባት አንድ ወይም ሁለት የውድድር ዘመን እንደቀረው ቢያውቁም ለሞዬስ ለማስተላለፍ ወስነዋል፡፡ በእርግጥ ዩናይትድ በመጪዎቹ ዓመታት አደጋ ውስጥ ሊገባ እንደሚችል መገመት ይከብዳል፡፡ ነገር ግን የስኳዱን ጥልቀት ከተመለከትን አዲሱ አሰልጣኝ ከባድ ስራ አለባቸው፡፡

ከፈርጉሰን ወደ ዴቪድ የሚደረገውን ሽግግር ማየት ያጓጓል፡፡ የዩናይትድን የአሰልጣኝነት ስራ ሌላ ሰው ይዞት መመልከትም ሰፊ ትኩረት ይስባል፡፡ የስኳዱን ጥልቀት ካየን ግን ስራው ጠጠር ይላል፡፡ ሞዬስ በሁለት ዓመታት ጊዜ ውስጥ አዲስ ግብ ጠባቂ፣ የግራ መስመር ተከላካይ፣ ሁለት የመሃል አማካዮች፣ ሁለት ወይም ሶስት የክንፍ አማካዮችና አንድ አልያም ሁለት አጥቂዎች ሊያስፈርሙ ይችላሉ፡፡ ምርጥ ተጨዋቾች ለማስፈረምና ሽግግሩን ስኬታማ ለማድረግ በተለይ ወቅታዊውን የዝውውር ገበያ ታሳቢ በማድረግ ምናልባት 200 ሚሊዮን ፓውንድ አካባቢ ሊያወጡ ይችላሉ፡፡

ሰር አሌክስ ጠንካራ ስኳድ ጥለው ባያልፉም አሁን ያሉት ተጨዋቾች ግን ቡድኑ መጥፎ ውጤት እንዳያስመዘግብ የማድረግ ብቃት አለው፡፡ ሞዬስ ደግሞ በፈርጉሰን የሰረፀውን የማሸነፍ ባህልና ሁለተኛነትን ያለመቀበል ባህሪይን ማስቀጠል ከቻሉ በስኬት ጎዳና ሊጓዙ ይችላሉ፡፡ ፈርጉሰን ጠንካራ መሰረት ያለው ቡድን ለሞዬስ እንዳላስረከቡ ግን ሊያመልጡት የማይችሉት እውነታ ነው፡፡

 

 

 

ask your doctor
Previous Story

Health: ኮንዶም ስጠቀም በብልቴ ቆዳ ሽፍታ ይወጣብኛል፣ ያቃጥለኛል፤ ኮንዶሙን ትቼስ እንዴት ልሆን ነው?

አሸናፊ እጅጉ
Next Story

የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን አሸናፊ እጅጉን አሰናበተ፤ ም/ል ፕሬዚዳንቱ ራሳቸውን አሰናበቱ

Latest from Blog

አስቸኳይ ህዝባዊ ጥሪ

July 24, 2024 ዓለማቀፍ ትብብር ለኢትዮጵያዊያን መብት Global alliance for the Rights of Ethiopians (GARE) በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ገዜ ጎፋ ወረዳ ኬንቾ ሳቻ ጎዝዲ ቀበሌ በደረሰው የመሬት መንሸራተት የብዙ ወገኖቻችንን ህይዎት ማለፉን
Go toTop