“የሙስሊሙን አቋም ወክለው የሚናገሩት የታሰሩት የእኔ ደንበኞች ናቸው” አቶ ተማም አባቡልጉ

ሃገር ቤት ከሚታተመው ሎሚ መጽሔት ጋር ያደረጉት ቃለ ምልልስ

ሎሚ፡- አሁን በእስር ላይ የሚገኙ የሙስሊም ተወካዮች ጉዳይ እንዴት ነው በጠበቃነት የያዝከው የፍርድ ሂደቱ በምን ጉዳይ ላይ ይገኛል
ተማም፡- የፍርድ ሂደቱ በ5-19 ሰኔ 2005ዓ.ም ምስክር ለመስማት ቀጠሮ ተይዞ ነበር፡፡ በሰኔ 5 አቃቢ ህግ ምስክር ጨረስኩ አለ፡፡ ሰማኒያ ዘጠነኛው ምስክር ለይ ምስክር አልቆብኛል ምስክር አጥቻለሁ ስላለ አሁን የሰው ምስክርነት አብቅቷል፡፡ አቃቢ ህግ የአቃቢ መቶ ሰማኒያ ዘጠኝ ነበረኝ ብሎ ነበር፡፡ ሰማኒያ ዘጠኝ ላይ ግን አበቅቷል፡፡ አሁን ደግሞ በሚቀጥለው ሰኔ 13 ፍርድ ቤቱ ከ5-19 ቀጠሮ ይዞ ነበር የአቃቢ ህግ ምስክርነት ለመስማት፡፡ አሁን አበቃሁ ስላለ ቀጠሮውን ትቶ ሰኔ 13 የፊልም /ኦዲዮ ቪዲዮ/ ማስረጃዎችን ለመስማት /ለማየት/ ቀጥሯል፡፡
ሎሚ፡- የሚቀርቡት ምስክሮች ምን አይነት ምስክርነት ነው የሚሰጡት
ተማም፡- የሚመሰክሩት በዚህ ጉዳይ ላይ ነው ለማለት አይቻልም፡፡ የተለያየ ነገር አለው፡፡ በደንበኞቼ ላይ ሁለት አይነት ክስ ነው የቀረበው፡፡ “መንግስት መገልበጥና ሽብርተኝነት” መንግስት መገልበጥ የሚለው ነገር ቀረና አንዱ ክስ በአንዱ ላይ ተደባልቋል፡፡ እኛም የተደባለቀው ክስ ይቅርና በፅሁፍ ይቅረብ አልን፡፡ “በፅሁፍ አልቀረበም” በፅሁፍ መቅረብ አለበት፡፡ የወንጀለኛ መቅጫ ስነ ስርአት 119 በግልፅ ነው የሚያስቀምጠው፡፡ አሁን በኋላ ላይ ፍርድ ቤቱ ምንድ ነው ያለው ብይኑ እኛ የሰጠነው ብይን እራሱ እንደ ክስ ይወሰዳል ተባለ፡፡ ቀጥሎ ጉዳዩ መስማት ሲጀምር ጭብጥ መያዝ አለበት፡፡ የወንጀለኛ መቅጫ 136 በግድ መያዝ አለበት ይላል፡፡ በምን ላይ እንደሚመሰክሩ ጭብጥም አልተያዘም፡፡ በመሀል ነው የተቋረጠው፡፡ በጣም ብዙ ልዩነቶች አሉበት፡፡ በክሱ አካሄድ ላይና እኛ ብዙውን ጊዜ የሚመጡ ምስክሮች በደንበኞቻቸን ላይ ምንድነው የሚመሰክሩት እከሌ እንዲህ አደረገ … እንደዚህ ወጣ ሣይሆን ተናገረ ነው፡፡ በእኛ ንግግር አመለካከት ነው፡፡ ብዙዎቹ አስተያየቶች ናቸው የተመሰከረባቸው፡፡ ብዙም ጉዳዩ ላይ እኔ እስከነበርኩበት ድረስ ደንበኞቼ ላይ የሚመሰክሩ የነበሩ ሰዎች አንደኛ ደንበኞቼን በአካል የማያውቋቸው ሰዎች ናቸው፡፡ የመሰከሩትም ነገር ደግሞ እንዲህ አደረጉ ተብሎ ሣይሆን እንዲህ ተናገሩ ነው፡፡ እስካሁን የመሰከሩት ምስክሮች እስካሁን ባየሁት በአይን አያውቋቸውም፡፡ እከሌ ማነው ስትላቸው በአይን አያውቋቸውም፡፡ ከተጠየቁት ውስጥ ከመቶ ሰማኔያው መለየት አልቻሉም፡፡
ሎሚ፡- እንደሚታወቀው አንተና ዶ/ር ያዕቆብ በክስ ላይ ለሚገኙት ሰዎች የስምንት ሚሊዮን ብር ካሣ ለማስገኘት ማለት ነው እየተንቀሣቀሳችሁ ነው፡፡ ይሄ የጀመራችሁት ነገር እስከምን ያደርሳል
ተማም፡- አሁን እኛ የጀመርነው ጉዳይ ሁለት አይነት ነው፡፡ ምንድነው አንደኛው ጉዳይ ደንበኞቻችን ላይ ጅሀዳዊ ሀረካት የሚል ፊልም ተሰርቷል፡፡ የማይገናኘውን አገናኝተው ነው የሰሩት፡፡ የማይገናኘው ማለት አሁን እዛ ላይ የምታያቸው ሰዎች የማይተዋወቁ ሰዎችን ግማሹ በወንጀል ተፈርዶባቸው የሄዱ ሰዎች ናቸው፡፡ ግማሾቹ በወንጀል ያልተከሰሱ ሰዎች ናቸው፡፡ ልክ በሚመሳሰል የሚተዋወቁ ሰዎች አድርገው “ሴራ” እየሰሩ እንደሆኑ አድርገው ነው ይህንን ነገር የሰሩት፡፡ እና እሱ ላይ የተሰራውን ነገር ደንበኞቻችን ቶርች ተደርገው ነው፡፡ ቶርች ሁለት አይነት ነው፡፡ አካላዊ ጥቃትና ስነልቦናዊ ጥቃት፡፡ ስነልቦናዊ ጥቃት ማለት እየደረሰ ባለ ማንኛውም ስነልቦናዊ ጫና ስር እንድትገባ ይደረግና ምንም ማምለጫ እንደሌለህ አውቀህ እዛ ስነልቦናዊ ጫና ውስጥ ያስገቡህ ሰዎች የሚፈልጉትን ነገር ካልሰጠሀቸው እንደማትወጣና፣ እንድትቀበል አድርገው የሚያስኬዱበት መንገድ ነው፡፡ እነዚህ ሰዎች ታዲያ በቀጥታ አካላዊም ስነልቦናዊም ጫና ተደርጐባቸው ነው፡፡ እኛ አሁን ምንድነው ያደረግነው ቶርቸር የሚለው ነገር የት ነው የጀመረው ፖሊስ ጣቢያ ውስጥ ነው፡፡ ከተያዙበት ጊዜ ጀምሮ፡፡ ቀጥሎ በቴሌቭዥን የቀረበው ነገር እራሱ ቶርቸር ነው፡፡ ስነልቦናዊ ጥቃት /ቶርቸር/ አካል ነው፡፡ ስለሆነም ያ ነገረ በቴሌቭዥን መተላለፉ፡፡ ደንበኞቻችን የኃይማኖት መምህራን ናቸው ፣ ትላልቅ ሰዎች ናቸው፣ ነጋዴዎች ናቸው፡፡ የራሣቸው ነገሮች ያሏቸው ሰዎች ናቸው፡፡ እና በዛ ደረጃ ስማቸው ጠፍቷል፡፡ መልካም ስማቸውን አጥተዋል ጐድፏል፡፡ ምስላቸው የታየ ሰዎች ያን በሚመለከት እያንዳንዱ የፕሬስ አዋጁ አለ፡፡ በፕሬስ አዋጁ አንቀፅ 43 ስር የተቀመጠ አለ፡፡ አንቀፅ 41 ስር የተቀመጠ አለ፡፡ በእሱ መሠረት እስከ 100 ሺህ ብር ለእያንዳንዳቸው የካሣ ጥያቄ አድርገን ነው ስምንት ሚሊዮን ብር የጠየቅነው፡፡ መልካም ስማቸው ጠፍቷል፡፡ የጠየቅነው ስምንት ሚሊዮን ብር ብቻ አይደለም ስማቸውን ያጠፉት ሰዎች ይቅርታ እንዲጠይቁ በተመሳሳይ መልኩ የስም ማደስ እንዲሰሩ ፣ እኛ የምናወጣውን ነገር እንዲያወጡልን ጭምር ነው ጥያቄ ያቀረብነው፡፡ ያቀረብነው ክስ በነገራችን ላይ ጉዳዩ እግድ ተላልፎ ስላደረጉት አይደለም፡፡ እግድ ተላልፈው የገቡት የጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት ናቸው፡፡ ለምን እግዱ እንዲጣስ ያደረጉት ሁለቱ ስለሆኑ ሆን ብለው እግዱን እራሣቸው ጋር በማስቀረት ያደረጉ ስለሆነ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ቴሌቭዥን ነገሩን እያወቀ ያስተላለፈ ስለሆነ ህጉ ላይ ይላል እነዚህ ነገሮች የሰዎችን መልካም ስም ሊያጠፉ መሆኑን ካወቀ ይላል ያ የፕሬስ አካል፡፡ ያውቃሉ፣ ማስታወቂያ አስነግረዋል፣ ሰዎች ምን ሊባል እንደሚችል ነው ያደረገውና በዛ ላይ ነው ያቀረብነው፡፡ ኢትዮጵያ ትልቅ ሀገር ናት፡፡ ብዙ ታሪክ ያላት ሀገር ናት፡፡ ይህ እውነት ነው በነገራችን ላይ ዝም ብሎ ጉዳይ አይደለም፡፡ ይሄን የሚያክል ትልቅ ሀገር ከፍተኛ ፍርድ ቤት ማለት ትልቅ ፍርድ ቤት ነው፡፡ እኛ መዝገብ ስንወስድ ሬጅስትራሩ ምንድነው ማድረግ ያለበት ፎርም አይቶ ሁለቱን ነገሮች አስተያይቶ ይሄ ነገር ፎርሙን አሟልቷል አላሟላም የሚለውን ነገር ነው መክፈት ያለበት፡፡ ኋላ ተከሣሾቹን በሚያይበት ጊዜ ሬጅስትራር አልከፍትም ነው ያለው፡፡ ኋላ ነገሩ በሬዲዮና፣ በቴሌቭዥን መነገሩ ሲበዛ የከፍተኛ ፍርድ ቤቱ ም/ፕሬዝዳንት መጡና እኛ አንከፍትም አላልንም አሉ፡፡ ኋላ ላይ ፕሬዝዳንቱ ጋር ሄደ ወረቀቱ፡፡ ፕሬዝዳንቱ ጋር እንዴት ነው የሚሄደው መዝገብ /መዝገብ የሚከፍተው ሬጅስትራር ነው/ ዳኛ ይመራል፡፡ አሁን ወደ እነሱ ጋር ሄደ ሲባል እንዴት ነው፡፡ ፕሬዝዳንቱን እኔና ዶ/ር ያዕቆብ ሆነን ነው ለማነጋገር የሞከርነው፡፡ ግን ሊያናግሩን ፈቃደኛ አልሆኑም፡፡ በፀሐፊያቸው በኩል አይቼ እመልሰዋለሁ ማክሰኞ ተመለሱ አሉን፡፡ ማክሰኞ ሄድን ማክሰኞ ዋናው ሬጅስትረር ዳኛው ይምጡ አለች፡፡ እስከ አስር አንድ ሰአት ጠበቀን ረቡዕ፣ ሐሙስ ፣ አርብ እያለ መጣ፡፡አርብ ቀን በአሜሪካ ሬዲዮ ላይ /ቪ.ኦ.ኤ/ ምክትል ፕሬዝዳንቱ ቀርበው “እኛ አንከፍትም አላልንም ዝምብሎ መክፈትም የከፍተኛ ፕሬዝዳንቱን ያስጠይቃል” አሉ፡፡ ኋላ ላይ ግን ማክሰኞ ተከፈተ፡፡ ማክሰኞ ከተከፈተ በኋላ ወደ ዳኛ እንመራችኋለን በሚቀጥለው ቀን ኑ አሉ፡፡ ስንሄድ አልመሩም እራሣቸው ሣይመሩ ነው የዘጉት፡፡
ሎሚ፡- የኢትዮጵያ ቴሌቭዥን ከፍርድ ቤቱ ፕሬዝዳንት ደብዳቤ ስላልደረሰኝ ነው ያስተላለፍኩት ብሏል
ተማም፡- ኢቲቪ ፈርሞ ተቀብሏል፡፡ ከከፍተኛ ፍርድ ቤት ስላልደረሰኝ ነው ያላቀረብኩት አላለም፡፡ የከፍተኛ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት እግዱን ስለወሰዱት ነው ያቀረብኩት ለማለት ነው የፈለጉት፡፡ እግዱን ወሰዱትም አለወሰዱትም እኛ እኮ ክሣችን እግዱን ጥሣችሁ አቀረባችሁ አይደለም፡፡ የኢትዮጵያ ቴሌቭዥን በፍርድ ላይ ያለን ሰው በነገራችን ላይ የኢትዮጵያ ቴሌቭዥን የሁላችንም ሀብት እኮ ነው፡፡ በህገ መንግስቱም የተቀመጠ ነገር ስለሆነ ነው፡፡ 29/5 ላይ የኢትዮጵያ ቴሌቭዥንና በመንግስት የሚተዳደሩ ሚዲያዎች ሕዝቡን በእኩልነት ማገልገል አለባቸው ይላል፡፡ ማለት የእኛ ሚዲያ ስለሆነ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ ሚዲያዎች ናቸው፡፡ በኢትዮጵያ ሕዝብ ገንዘብ ለኢትዮጵያ ሕዝብ ጥቅም የተቋቋሙ በኢትዮጵያ ሕዝብ ገንዘብ የሚደጐሙ ናቸው፡፡ የግል መፅሔትና ጋዜጦች ራሣቸውን ችለው ነው የሚሰሩት፡፡ ህገመንግስት የሁላችንም ሀብት ነው ባለው ቴሌቭዥን የአንድ ሰው ስም ማጥፋት የለብህም፡፡ ማንም ሰው መጥቶ /ደህንነትና ፖሊስ ይህንን ነገር አስተላልፍልኝ ስላለው ብቻ ማስተላለፍ የለበትም/ ጅሀዳዊ ሀረካትን ማስተላለፍ የለበትም፡፡ ጅሀዳዊ ሀረካት ወንጀል ነው፡፡ ጅሀዳዊ ሀረካት ወንጀል የሆነበት ምክንያት ስም ማጥፋት ስለሆነ ነው፡፡ እኛ በወንጀል እንከሣቸዋለን፡፡ የተወሰኑ ሰዎችን በወንጀል የምንከስበት ነገር አለ፡፡ ህግ አዘጋጅተን ከጨረስን በኋላ ደንበኞቻችን እየሆነ ባለው ነገር ተስፋ በመቁረጥ ሣይሆን ለምን ሌላ ነገር ላይ ለማተኮር በመፈለግ ማለት ነው፡፡ ቀጥሎ በስልጣን ያለአግባብ መገልገል ሲመጣ ክሱን እያዘጋጀን ነው፡፡ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጀምሮ የምናቀርባቸው ክሶች አልቀዋል፡፡ አሁን በሆኑ ነገሮች ላይ እንዴት ነው መሄድ ያለበት በሚለው እየተነጋገርን ስለሆነ ያልቀረቡት እንጂ በዛ ላይ አጠቃለን እናቀርባለን፡፡ “ጅሃዳዊ ሀረካት” እኮ ወንጀል ነው፡፡ በሰዎች ላይ የተፈፀሙ ወንጀሎች ናቸው፡፡ የባህሪ ገደላ ይባላል፡፡ የባህሪ ገደላ ነው የተፈፀመው፡፡ ምንድነው የተደረገው ፣ ፖሊስና ደህንነት ቁጭ ብለው ሰዎቻችንን እየደበደቡ አሳምነዋቸዋል፡፡እንዲህ እንዲህ በሉ አድርጉ በማለት፡፡ የፈለጋቸውን ቆርጠው አወጡና በቴሌቭዥን አምጥተው አቀረቡ፡፡ አላቀርብም ማለት ያለበት የኢትዮጵያ ቴሌቭዥን ነው፡፡ ይሄ ወንጀል ነው እነዚህ ሰዎች በፍርድ ሂደት ላይ ነው ያሉት፡፡ ገና በፍርድ ቤት ውሣኔ አልተሰጠውም፡፡ በፍርድ ቤት ውሣኔ ቢሰጥ እንኳን ማቅረብ አይችልም ፍርድ ቤቱ ካላዘዘ በቀር፡፡
ይሄ ለሕዝብ ማስተማሪያ ይሆናል ብሎ ፍርድ ቤት ካላዘዘ በቀር፡፡ ሰው በተፈጥሮ ክቡር ነው፡፡ አንተን እንደ ገበያ ማስታወቂያ ሰው እኮ ፎቶውን ገበያ መስቀል አይችልም ያላንተ ፍቃድ፡፡ አንድ ሰው ልጅ አለው፣ ሚስት አለው የተለያየ የቤተሰብ አካል አለው፡፡ ስለዚህ ተከብረህ ነው መኖር ያለብህ፡፡ እያንዳንዱ ያንተ የሆኑ ነገሮች የግልህ የሆኑ ነገሮች ባህሪዎችህ ምናምን ተደብቀው ነው መኖር ያለባቸው፡፡ ህግ ያንን ነው ጥበቃ የሚያደርገው፡፡ ማንም ሰው ተነስቶ ማንንም ሰው ለማንኛውም ሰው አላማ ብሎ ፊት ለፊት በማስታወቂያ አትም ስላለው ብቻ ማቅረብ ወንጀል ነው፡፡ ስለዚህ ወንጀል የፈፀመባቸው “ጅሀዳዊ ሀረካትን” ማንም አስተላልፍ ቢለው እንኳን ማስተላለፍ የለበትም፡፡ ለምን የኢትዮጵያ ሕዝብ ንብረት ስለሆነ ብቻ ሣይሆን የማንም ኢትዮጵያዊ ንብረት ሰውነቱ የተጠበቁ ናቸው፡፡ ካልተጠበቁማ ምኑን ሀገር ሆነ፡፡ ማንም ሰው እንደፈለገ መንገድ ላይ የሚሰድብህ ከሆነ ፣ ማንም ሣይደርስበት ምንም ነገር ሣይባል፣ ምንም የወንጀል ኃላፊነት ሣይመጣበት እኮ አንድ ሰው በቴሌቭዥን አቅርቦ እሱ እንደዚህ ነው ሊለኝ ቢችል እኮ ኢትዮጵያዊ አይደለሁም ማለት ነው፡፡ የዛ ሰውዬ እቃ ነኝ ማለት ነው፡፡ ያ ነው እየተለመደ የመጣው፡፡ እኛ ሀገር መደረግ የሌለበት ነገር ነው የተደረገው፡፡ የሆነ ሰው እንደዚህ አይነት ነገር ካደረገ ይሄ ህግ ሊሆን አይችልም፡፡ ህገ መንግስቱ የሰውን ክብር ይሰጣል ያን ተከትሎ ነው ህጐች መውጣት ያለባቸው፡፡ ስለዚህ አንድ ሰው ፖሊስ ሊሆን ይችላል ያ ሰው ደህንነትም ሊሆን ይችላል የመንግስት ባለስልጣን ሊሆን ይችላል፣ አንተን ማዋረድ ግን አይችልም፡፡ የኢትዮጵያ ቴሌቭዥንም ሆነ በመንግስት የሚተዳደር ማንኛውም ሚዲያ ይህን ማድረግ አይችልም፡፡ የግሉ ሚዲያ ሰዎችን አዋረዳችሁ ተብለው ይከሰሳሉ፣ እናም እነ ኢቴቪ ደግሞ ድርብ ኃላፊነት ነውያ ለባቸው፡፡ የመንግስት ስለሆኑ ፣ የሕዝብ ስለሆኑ ያንን ነገር ያለማድረግ ግዴታ አለባቸው፡፡ በፕሬስ ህጉም ሆነ በወንጀለኛ መቅጫው ላይ ግዴታ አለባቸው ያንን ማድረግ አይችሉም፡፡
ሎሚ፡-አቶ ሽመልስ ከማል ከወራት በፊት “በኢትዮ ቻናል”ጋዜጣ ላይ ባደረጉት ቃለ መጠይቅ ወቅት በእርስዎ ዙሪያ ሲናገሩ ‹‹አርፎ ካልተቀመጠ ሰውዬው ሊታሰር ይችላል›› ሲሉ ገልፀዋል፤ ይህንን ነገር እንዴት ይመለከቱታል
ተማም፡- እኔ በግ አይደለሁም የምታሰረው፡፡፡ አሳስረዋለሁ እኮ ማለት አቶ ሽመልስ ከማል ሰውን ማሳሰር ይቻላል ማለት ነው፡፡ ኢትዮጵያ የህግ አገር አይደለችም ማለት ነው፡፡ በዚህ አባባል እኔ አሳስረዋለሁ ማለት፡፡ እኔ ሽመልስ ከማል ስልጣናቸው የኮሚኒኬሽን ምክትል ኃላፊ መሆናቸውን እንጂ ሰው አሳሳሪ መሆናቸውን አላውቅም፡፡ ፖሊስ መሆናቸውንም አላውቅም፡፡ በግል የእሣቸውን ስም የነካሁትና ያደረኩት ነገር የለም፡፡እሣቸው ናቸው እንደውም ስሜን ያጠፉት፡፡ እኔም አላሳሰርኳቸውም እንኳን እኔን ሊያሳስሩኝ፡፡ በተረፈ አሳስራቸዋለሁ ማለት በኢትዮጵያ ህግ የለም ማለት ነው፡፡ በቃ ማንም ሰው ማንንም ሰው ማሳሰር ከቻለ አቶ ሽመልስ ከማል ተማምን አሳስራለሁ ካሉ ህግ የለም፡፡ የሰው የበላይነት ነው ያለው ማለት ስለሆን የኢትዮጵያን መንግስት እየሰደቡ ነው ያሉት እሣቸው፡፡
ሎሚ፡- ባለፈው ሰማያዊ ፓርቲ በጠራው ሰልፍ ላይ የወጡት ሙስሊሞችን ጥያቄ በሚመለከት አቶ ሬዱዋን ሁሴን ‹‹ከሽብርተኝነት ጋር መቆራኘታቸውን›› ገልፀዋል፡፡ ይህን አገላለፅ እንዴት አየኸው
ተማም፡- እኔን ይሄን ጥያቄ የምትጠይቀኝ እንደ ሙስሊም ከሆነ ሙስሊም ኢትዮጵያዊ ኢትዮጵያዊ ነው፡፡ እንደ ህግ ባለሙያም እንደሙስሊምነትም ጥሩ አባባል አይደለም፡፡ ለምን መሰለህ ኢትዮጵያ ውስጥ አንድ ነገር መታወቅ አለበት፡፡ ከሁሉ አስቀድሞ እኔ አሁን ተማም እባላለሁ፣ ኢትዮጵያዊ ነኝ፣ ሙስሊም ነኝ፡፡ አንተም ክርስቲያን ነህ ኢትዮጵያዊያን ነን፡፡ አንተ ያለህ መብት አጠቃላይ አለኝ፡፡ ከአንተ ተለይቼ ልታይ አልችልም፡፡ በግሌ፡፡ እንደ መንግስት በተለይ ይሄንን ነገር ማክበር አለበት፡፡ መካ አይደለም ሙስሊሞች ሀገራችን ኢትዮጵያ ነው፡፡ አሁን ይሄ ማለት የሙስሊም ሀገር መካ ነው ከሚለው ለይቼ አላየውም፡፡ በርግጠኝነት ድሮ የሙስሊም ሀገር መካ ነው ከሚለው ጋር ይመሳሰላል፡፡ እኔ እንኳን ሰምቼ አላውቅም፡፡እዛ ጋር ሂጃብ የለበሰች ሴት ሰልፍ ብትወጣና ነጠላ የለበሰች የኦርቶዶክስ ክርስቲያን ሰልፍ ብትወጣ የመንግስት ኃላፊዎች ቀርበው የእከሌ ነው የእከሌ ነው ማለት አይችሉም፡፡ ያ ማለት ልዩነት መፍጠር ማለት ነው፡፡ በኃይማኖት፣ በዘር ልዩነት አይደረግም፡፡ በኢትዮጵያ ህገ መንግስት 21/22 በግልፅ ተቀምጧል፡፡ እዛ ጋር ያሉት ሰዎች አሸባሪ ከሆኑ ለምን አያስሯቸውም ነበር፡፡ የአሸባሪዎች ሰልፍነው ከተባለ እዛ ላይ የነበሩት ሰዎች ወንጀል ፈፅመዋል ከተባለ በነገራችን ላይ ፈፅሞ ከህገ መንግስቱ ጋር ተፃራሪ የሆነ አባባል ነው፡፡ ለምንድን ነው አንድ ሰው ወንጀል ፈፅሞ ከሆነ ይታሰራል፡፡ እነዛ ሰዎች ያን ሣይፈፅሙ ሙስሊም ስለሆኑ ብቻ እንደዛ መባላቸው በየትኛውም መልኩ ልዩነት ያለው አካሄድ ነው፡፡ ህገ መንግስቱንም መጣስ ነው፡፡ ህገ መንግስቱ ልዩነት አይፈጥርም፡፡ በኃይማኖት በምናምን ይላል፡፡ በአመጣጥህ ልዩነት አይደረግብህም ነው፡፡ያንን ነው ያደረጉት፡፡ የሽብርተኞች ሰልፍ ነው የተሰለፉትን ሰዎችን አስመልክቶ ነው የተሰለፉላቸውን አስመልክቶ ደንበኞቼንም አስመልክቶም ቢሆን ማንም ሰው ይፈቱ ብሎ መጠየቅ ይችላል፡፡ የወንጀለኛ መቅጫ ስነ ስርአቱ 122/22 ምን ይላል መንግስት በየትኛውም ጊዜ የትኛውንም ክስ ማንሣት ይችላል ይላል፡፡ ያ ማለት ምንድን ነው ማንኛውም ሰው ክስ ይነሣልኝ ብሎ መጠየቅ ይችላል፡፡ በሰላማዊ ሰልፍ ይሁን ፣በምንም አይነት መልኩ በደብዳቤ ቢሆን ሕዝቡም ያንን አድርጐ ከሆነ ደንበኞቼ ይፈቱ ብሎ ከሆነ እሰየው ነው ጥሩ ነው ያደረገው፡፡ ስለዚህ እዛ ጋር የተሰለፉት ሰዎች ሙስሊም ስለሆኑ ተብሎ የሽብርተኞች ሰልፍነው ፣ ዜጐቹን የሚመለከት የተደረገ ከሆነ ይህ በትክክል ህገ መንግስቱን መጣስ ነው፡፡ የእኛን ጥያቄ አስመልክቶ የተነገር ከሆነ ይህም ህገ ወጥ ነው፡፡ለምን በህጉ የሚቻል ነገር ነው ያደረጉት፡፡ ማንም ሰው በሰልፍም ይሁን በየትኛውም መልኩ ሀሣቡን መግለፅ ይቻላል፡፡ የትኛውንም ሀሣቡን ነው መግለፅ የሚቻለው፡፡ ያ ነገር በራሱ ወንጀልና የሚያመጣ ከሆነ ወንጀል ሊሆን ነው፡፡ ወንጀል ነው ብለህ ትከሣለህ አለቀ፡፡ እዚህ ጋር ግን ህገ መንግስታዊ መብትህን ስለተጠቀምክበት በማንነትህ በዘርህ በኃይማኖትህ በአመጣጥህ ኢኮኖሚ ከጀርባ ተነስተህ እነ እከሌ እንደዚህ ናቸው ብሎ ማለት በራሱ መንግስት ሲያቀርብው ደስ አይልም፡፡ መንግስት በእኩል መልኩ ነው ማየት ያለበት፡፡ ይህን ዜጐች ቢያደርጉት የሆነ ነገር ነው የሚባለው፡፡ የመንግስት ባለስልጣን ግን የመንግስት አቋም ነው፡፡ የመንግስት አቋም ምንድን ነው ሙስሊም ሀገሩ እዚህ አይደለም ነው፡፡ እዛ የተሰለፈው ኢትዮጵያዊ ሙስሊም ሀገሩ እዚህ አይደለም ማለት ነው የሚሆነው፡፡ ስለዚህ ተገቢ አይደለም ነው የምለው መታረምም አለበት፡፡
ሎሚ፡- ሁልጊዜ የሙስሊሞች ጉዳይ በተለይ አሁን ካሉት ሁኔታ አንፃር ተያይዞ በዚህ ጉዳይ ላይ መግለጫ የሚሰጡት አቶ ሽመልስ ከማልና አቶ ሬዱዋን ናቸው፡፡ እነዚህ ሰዎች የሚሰጧቸው መግለጫዎች የሙስሊሙ ሕብረተሰብን የሚወክል ነው ብለህ ታምናለህ?
ተማም፡- የሬዱዋንና የሽመልስ ከማል አባባልማ የመንግስትን ነው የሚወክለው፡፡ ሁለቱም የመንግስት ባለስልጣናት ናቸው፡፡ የአለም አቀፉ ህግ የመንግስት ሚዲያ፣ የመንግስት ባለስልጣናት የሚናገሩት በሙሉ የመንግስት አቋም ነው ይላል፡፡ እነሱ የሙስሊሙን አቋም ሣይሆን የመንግስትን አቋም ነው የሚናገሩት፡፡ የሙስሊሙን አቋም ወክለው የሚናገሩት የታሰሩት የኔ ደንበኞች ናቸው፡፡ የኔ ደንበኞች የሙስሉሙን ሕዝብ ፍላጐት የሚወክሉ ናቸው፡፡ እንደዛ እንደሚወክሉ ሕዝቡ በየቀኑ በየአርቡ በየትኛውም ቦታ ላይ አቋሙን እየገለፀ ያለው የሙስሊሙን ሕብረተሰብ የሚወክሉት የኔ ደንበኞች ናቸው፡፡ ስለዚህ እነሱ ናቸው የሙስሊሙን ፍላጐት ያንፀባርቃሉ ተብለው የሚባሉት፡፡ ለምሣሌ ሙስሊሙን ይወክላል ተብሎ የሚከበረው የኢትዮጵያ እስልምና ጠቅላይ ም/ቤት እንዲፈርስ ጠይቀናል እኛ፡፡ ደንበኞቼ የሙስሊሙን ሕብረተሰብ የሚወክል አይደለም ምርጫ የተደረገበትም አካሄድ ተገቢ አይደለም በማለት ጠቅላይ ፍ/ቤት ሰበር ችሎት አቅርበን ቀጠሮ ላይ ነው ያለው፡፡ ያ ማለት ምንድን ነው በነገራችን ላይ መንግስት የሕዝቡን ፍላጐት ይጠብቃል ተብሎ ነው የሚጠበቀው፡፡ ሕዝቡ ደግሞ እስላምም ክርስቲያንም ነው፡፡ አሁን እነ ሽመልስ ከማል የመንግስትን አቋም እንጂ የሚወክሉት የሙስሊሙን አቋም አይወክሉም ሙስሊም ስለሆኑ፡፡ የኔ ደንበኞች በሙስሊሙ ሕብረተሰብ የተመረጡ ስለሆነ የሙስሊሙ መፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴ ሙስሊሙ ችግር አለበት ያ ችግሩ ለመንግስት መቅረብ አለበት፣ መንግስት ያንን ችግር አይቶ መፍትሄ አልሰጠውም ፣ ስለዚህ መፍትሄውን ለመጠየቅ የተቋቋመው ኮሚቴ ነው ሙስሊሙን የሚወክለው፡፡ለምን አሁን ግማሹ የታሰረው ግማሹ ያልታሰረው ያ ቡድን ነው፡፡ አሁን ሕዝቡ እኮ ያ ቡድን ታሰረብን እያለ ነው ያለው፡፡ ለምን የእሱን ፍላጐት የሚወክል ስለሆነ ነው፡፡ ጥያቄ ከሌላ ሰልፍም የለም፡፡ ቅሬታ ከሌለ ሰልፍ አይኖርም፡፡ቅሬታ ከሌለ ተቃዋሚ ፓርቲ የለም፡፡ ቅሬታ ከሌላ የሙያ ማህበር የለም፡፡ ፍላጐት አስጠባቂዎች ናቸው እነዚህ ፍላጐታቸውን በሆነ መልኩ ያቀርባሉ የቀረበለት አካል መልስ መስጠት ነው ያለበት፡፡ መመለስ እንጂ መፈረጅ አይቻልም ማለት ነው፡፡
ሎሚ፡- የታሰሩት የሙስሊም ተወካዮችን የህግ ጉዳይ ይዛችኋል እና አሁን የያዛችሁት ነገርስ ነፃ ያወጣቸዋል፡፡ ነፃ ይወጣሉ ብለህ ትገምታለህ
ተማም፡- አዎ ነፃ ያወጣቸዋል፡፡ ለምን መሰለህ የማምነው እንደባለሞያ በዚህ ሀገር ጥብቅና እንደሚሰራ ባለሞያ አሁን በርግጥ የህግ ባለሞያ ብትሆን ይሄ ምን ማለት እንደሆነ ይገባሀል በትክክል፡፡ በቀላሉ አንድ የህግ ባለሙያ እኔና እኔን መሰል ጠበቆች ወደ ፍርድ ቤት ስንሄድ ምን እንደሚሰማን እኛ እናውቃለን፡፡ በየቀኑ የምናወራውም ያንን ነው፡፡ ምንድነው ብትለኝ አሁን አልነግርህም፡፡ ሁሉም ሰው ያውቀዋል፡፡ በኔ ነፃ ይወጣሉ ብዬ የማስበው በኔ ነፃ ይዋጣሉ ብቻ ሣይሆን መጀመሪያውኑ የሚያስከስሳቸው ነገር የለም ብዬ ነው የማምነው፡፡ እኔ በግሌ እስከመጨረሻውም ክሱን ካየሁበት ጊዜ ጀምሮ ማስረጃውን ካየሁበት ጊዜ ጀምሮ ደንበኞቼ ምንም የሚያስከስስ ወንጀል አልሰሩም ባይ ነኝ፡፡ ይህንን ርግጠኛ ነኝ፡፡ይሄን በፍ/ቤት በሚደረጉ ሙግቶኝ ትገልፃላችሁ ለሚለው በደንብ እናብራራለን፡፡ በርግጠኝነት የምነግርህ በቀላሉ አቃቢ ህግ እነዚህ ሰዎች ወንጀል መስራታቸውን ያስረዳል ወይ ነው ጥያቄው መሆን ያለበት፡፡ አይችልም፡፡በዚህ ምስክርነት በቀረቡት ማስረጃዎች አስሮ ሊያቀርባቸው አይችልም፡፡ ጥፋተኛ ሌላቸው አይችልም፡፡ እኛ ግን መላ የኢትዮጵያ ሕዝብ ነው የደንበኞቼ ምስክር፡፡ የደንበኞቼ ንፁህነት መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ነው የሚመሰክረው ሙስሊም ብቻ አይደለም፡፡ ሙስሊሙም ክርስቲያኑም ነው የሚናገረው፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ 80 ሚሊዮን ሕዝብ ከሆነ የኔ ደንበኞች ምስክር ነው፡፡ ስለዚህ ይህንን ሁሉ ይዘን እንዴት ነፃ አይወጡም ብለህ ታምናለህ፡፡ ስለዚህ በትክክል ነፃ ይወጣሉ ብዬ አምናለሁ፡፡ ነፃ ይወጣሉ ብቻም አይደለም መጀመሪያም የፈፀሙት ወንጀል የለም ብዬ ነው የማምነው፡፡
ሎሚ፡- አሁን ያሉበት ሁኔታ እንዴት ነው
ተማም፡- አሁን የተያዙበት ወይም ያሉበት ሁኔታ ጥሩ ነው፡፡ ከጀመሪያው ተሻሽሏል በጣም፡፡
ሎሚ፡- መጀመሪያ ጥሩ አልነበረም
ተማም፡- መጀመሪያ ጥሩ አልነበረም፡፡ ፌድራል ፖሊስ በነበረበት ጊዜ የነበረው ጥሩ የሚባል ብቻ ሣይሆን ከፍተኛ የሰብአዊ መብት ጥሰት ነው የተፀመባቸው፡፡ ቶርቸር ተፈፅሞባቸዋል፡፡ ተዋርደዋል፡፡ ብዙ ነገር ነው የሆነው፡፡የአንድ ሀገር ሕዝብ እጣ ፈንታ እኮ አንድ ነው፡፡ ብዙ ሰው ሊገነዘበው የሚገባ አንድ ነገር አለ፡፡ ዛሬ ያሲን ኑሩ ላይ ከሆነ ፣አህመድ ሙስጠፋ ላይ የሆነ ነገር ቢደረግ በቀጣይነት ደግሞ ገ/ሚካኤልም ላይም ይደረጋል፡፡ ጫላም ላይ ይደረጋል፡፡ ማንም ላይ ይደረጋል፡፡ አንድ ሀገር የህግ አገር ከሆነ በህግ የሚሰራ ከሆነ በህግ ነው የሚሰራው፡፡ ህግ የሚጣስ ከሆነ ግን አንድ ላይ ነው የሚጣሰው፡፡ የጊዜ ጉዳይ ነው፡፡ እነ ያሲን ላይ የደረሰው እነ በድሩ ሁሴን ላይ የደረሰው ነገ ሁሉም ላይ ይደርሳል፡፡ እነ በድሩ ላይ ሲደረስ መድረስ የለበትም ብሎ ሁሉም መጮህ ያለበት ለዚህነው፡፡ የጊዜ ጉዳይነው ሁሉም ይሄ ነገር ያጋጥመዋል፡፡ ይሄ ለምን መሰለህ የህግ ባህሪ ነው፡፡ አንድ ነገር በህግ የማይሰራ ከሆነ ህግን መጣስ የሚቻል ከሆነ ቀጥሎ ያለው ሁለተኛ ሰው ላይ ይደረግበታል፡፡ ይደረግብሀል፡፡ በምንድነው የምትከላከለው፡፡ ህጉ ሲጣስ ዝም በማለትህ የመከላከል አቅም የለህም ቀጥሎ አንተ ላይ ሲመጣ፡፡ የአንድ ሀገር ሕዝብ እጣ ፈንታ አንድ ነው፡፡
ሎሚ፡- ተማም ጊዜህን አጣበህ ለዚህ ቃለ መጠይቅ ፈቃደኛ ስለሆንክ አመሰግናለሁ፡፡
ተማም፡-እኔም አመሰግናለሁ፡፡

ተጨማሪ ያንብቡ:  የዐቢይ አህመድ መንግስት ከትግራይ አሽባሪ ኃይሎች ጋር እንደሚደራደር መናገራቸው ተረጋገጠ
Share