ሁሉንም ነገር ለፖለቲካ ፍጆታ ለማዋል የቆረጠ ፓርቲ የሀገርን ሉዓላዊነት አደጋ ላይ መጣሉ የማይቀር ነው!!! ከአአንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትሕ ፓርቲ (አንድነት) የተሰጠ መግለጫ

June 15, 2013

አንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትሕ ፓርቲ (አንድነት)

UNITY FOR DEMOCRACY AND JUSTICE PARTY (UDJ)

ሀገራችን ኢትዮጵያ በተፈጥሮ ሀብቷ የታደለች፤ በመልክዓ ምድራዊ አቀማመጧ ለብዙ ፈታኝ ሁኔታዎች  የተጋለጠች አገር ናት፡፡ በአንፃራዊነት ሲታይም ምንም እንኳን በተፈጥሮ ሀብት የታደለች ብትሆንም ዜጎቿ በርሃብ የሚሰቃዩባት፤ ከሞት ጋር ተጋፍጠው ስደትን የሚመርጡባት፤ በሙስና ተግጣ ያለቀች፣ መልካም አስተዳደር የናፈቃት የምታስቆጭ ሀገርም ናት፡፡ እንዳለመታደል ሆኖ ከራሱ ስልጣን ይልቅ የህዝብን ጥቅም የሚያስቀድም፣ ለህዝብ ጆሮ የሚሰጥ አስተዋይ መሪ አግኝታ አታውቅም ቢባል ማጋነን አይሆንም፡፡ ለዘመናት ያልተፈቱ ችግሮችና በመሪዎቹ የሚፈጠሩ ችግሮች ትከሻውን ያጎበጡት የኢትዮጵያ ህዝብም ሉዓላዊነቱን ለማንምና ለምንም ሰጥቶ አያውቅም፣ ወደፊትም ሊሰጥ አይችልም፡፡  ይህም ስለሆነ ሀገራችን ሉዓላዊነቷ ሳይደፈር ለብዙ ሺ ዓመታት ቆይታለች፡፡

ከዚህ በፊትም አቶማን ቱርኮች፣ ግብፆች፣ ድርቡሾች፣ ጣሊያኖችና ሶማሊያ ባደረጉት የሉዓላዊነት መድፈር የጨቋኞችን ክፉ ድርጊት ወደ ጎን በማለት፣ ‹‹ጨቋኝ ገዢዎች እንጂ ሀገሬ አይደለችም›› በሚል እሳቤ ደሙን አፍስሷል፡፡ አጥንቱን ከስክሷል፡፡ ለባለፉት ሃያ ሁለት አመታት ግን ብሔርንና ጎሳን መሰረት ባደረገው ከፋፋይ ሥርዓት ኢትዮጵያዊ አንድነትን በማደብዘዝና የጋራ ህብረ ቀለምና እሴቶችን ወደ ቡድን ህብረ ቀለምና እሴት በመቀየር፣ ተከብሮና ታፍሮ የኖረ ሉዓላዊነታችንን ከግራና ከቀኝ እንዲቆረስ በማድረጉ ከቀደሙት አገዛዞች ለየት ያደርገዋል፡፡

በተጨማሪም ይሄን ሥርዓት ከሌሎች የቀደሙ አምባገነን ሥርዓቶች ለየት የሚያደርገው ‹‹ሁሉንም ነገር ለፖለቲካ ሥልጣን መጠቀሚያ ማዋል›› የሚለው ተግባሩ ነው፡፡ ሌላው ሁሉ ቀርቶ የአንድ መንግሥት ግዴታዎች የሆኑት ተግባራት መንገድ፣ መብራት፣ ውሃ፣ ቤት የመሳሰሉት መዳረሻቸው የፖለቲካ ሥልጣንን ማራዘም ነው፡፡ እነዚህንም ስለሞከረ አመስግኑኝ፣ ዘምሩልኝ የሚል መንግሥት የኢህአዴግ መንግሥት ብቻ ነው፡፡ በመሰረቱ መንግሥት አይመሰገንም፡፡ በሰለጠኑት እና እድለኛ በሆኑት ሀገሮች ህዝቡ መንግሥቱን እንዳመሰገነ የሚቆጠረው የምርጫ ካርዱን ሲሰጠው ብቻ ነው፡፡ ከዚያ በኋላ ያለው የመንግሥት ግዴታ ነው፡፡

ፓርቲያችን አጥብቆ እንደሚያምነው ለፖለቲካ ፍጆታ የማይውል ንፁህ ልማት እጅግ አስፈላጊና ወሳኝ ነው፡፡ ለፖለቲካ መጠቀሚያ የማይውል የመሠረተ ልማት ግንባታ እጅግ ጠቃሚ ነው፡፡ ከነዚህም መካከል ትላልቅ ግድቦችን መገንባት፣ ለመስኖና ለተለያዩ ጉዳዮች  መጠቀም እንደ ኢትዮጵያ በርካታ ህዝብ ላለው ሀገር አስፈላጊነቱ ጥያቄ ምልክት ውስጥ የሚገባ አይደለም፡፡ በዚህም ምክንያት ዛሬ ኢህአዴግ እንዳዲስ ያነሳው በአባይ ወንዝ ላይ ግድብ መስራትና የማልማት አስፈላጊነት ለዘመናት ሲነሳ የነበረ ጉዳይ ነው፡፡

አንድነት የኢትዮጵያ ሕዝብ በአባይ ወንዝ ላይ የመጠቀም ተፈጥሮአዊና መብት እንዳለውና ይሄ የኢትዮጵያውያን መብት ለማንም ተላልፎ የሚሰጥ  እንዳልሆነ በጽኑ ያምናል፡፡ በአባይ ላይ በፍትሓዊነት የመጠቀም መብት ከፓርቲዎች ወይም ገዢ ከሆነው ፓርቲ ለህዝቡ የሚሰጥ ሳይሆን የህዝቡና የህዝቡ ነው፡፡ ከዚህ በፊትም በተደጋጋሚ እንዳነሳነው ችግሩ የሚመነጨው ገዥው ፓርቲ አባይ ወንዝ ላይ ግድብ ለመስራት መነሳቱ ሳይሆን የአባይን ጉዳይ የኢህአዴግ ጉዳይ ማድረጉ፣ የአባይን ጉዳይ የአንድ ግለሰብ ራዕይ ማድረጉና ከእለት ጉርሱ ቀንሶ ቦንድ እየገዛ ያለውን ህዝብ የግድቡ ባለቤት ማድረግ አለመቻሉ ነው፡፡ ለዚህ ጥሩ ማሳያ የሚሆነን ግድቡ በጊዜያዊነት አቅጣጫ እንዲቀይር የተደረገበትን ቀን ከግንቦት ሃያ በዓላቸው ጋር ሆን ብለው ለማገጣጠም መፈለጋቸው ነው፡፡ ግድቡ የኢትዮጵያ ህዝብ ግድብ ይሁን የኢህአዴግ በውል አልለዩትም፡፡ ስለዚህ ጉዳዩ የፖለቲካ መጠቀሚያ ጉዳይ ይሆናል ማለት ነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪም በአባይ ላይ ግድብ ከመሰራቱ በፊት ማለቅ የሚገባቸው የዲፕሎማሲ ስራዎችና ሌሎች ጉዳዮች በውል ታይተዋል ወይ የሚል ጥያቄ ማንሳትም ተገቢ ነው፡፡ ምክንያቱም ግድቡ ላይ ከእያንዳንዱ ኪስ የተወሰደ ገንዘብ አለና ነው፡፡

ስለዚህ ገዢው ፓርቲ ሁሉን ነገር ለፖለቲካ ፍጆታ በማዋል ሥልጣንን ማስረዘም በሚል መርህ ተቀይዶ የዘነጋቸው ብዙ ሀገራዊ ተግባራት እንደነበሩና እንዳሉ ለመገመት ይቻላል፡፡ ከነዚህም ዋነኛው በቂ የዲፕሎማሲ ስራ  አለመስራት፤ ከዓባይ ተጋሪ ሀገሮች ጋር በቂና አስተማማኝ ውይይት አድርጎ ስምምነት አለመድረስ፤ በዚህ ረገድ ሀገሪቱ የጦርነት ስጋር ቢገጥማት ለመቋቋም በቂ ዝግጅት አለማድረግ፤ የገንዘብ ቁጥጥርና ሙስና የመሳሳሉት ይጠቀሳሉ፡፡

ሌላው አብይ ጉዳይ ሁሉም ነገር እኔ አውቀዋለሁ በሚል ትእቢት ኢህአዴግ ብሔራዊ መግባባት (National Consensus) እንዲፈጠር ምንም አይነት እንቅስቃሴ ለማድረግ አለመፈለጉ ነው፡፡ ይልቁንም ገዢው አካል ብሔራዊ መግባባት እንዳይፈጠር በመስራት የሚታወቅት ነው፡፡ ሀገራዊ ጉዳይ ያነሱ ፖለቲካኞችንና ጋዜጠኞችንና ባዘጋጀው የማጥቂያ ህግ ‹‹ሽብርተኛ›› በማለት የሚፈርጅ፣ ለመነጋገርና ለመግባባት ዝግጁነት የሌለው፣ በልማት ስም ጭቆና የሚያካሂድ፣ ይቀናቀነኛል የሚላቸውን ኃይሎች ሁሉ ከምድረ ገጽ መጥፋት አለባቸው ብሎ የሚያስብ አምባገነን ሥርዓት ነው፡፡ በኃይማኖት ጉዳይ ጣልቃ በመግባት ብሔራዊ መግባባትን የሚፈታተን በማጥቃት ላይ ብቻ የተመሰረተ አገዛዝ ነው፡፡ ስለዚህ አጣብቂኝ ውስጥ በወደቀበት ጊዜ እንኳን ሀገራዊ አጀንዳ ካላቸው ተቃዋሚዎች ጋር የመመካከር ሃሳብ የለውም፡፡ ይሄም የሆነው ከሀገር ይልቅ ስልጣንንና ለስልጣን ብቻ ከማሰብ የሚመነጭ በመሆኑ ነው፡፡ ታዲያ የታቀደው ትልቅ ፕሮጀክት ያለ ሀገራዊ መግባባት እንዴት ሊሳካ ይችላል?

ከተመረጡ አንድ ዓመት የሚሆናቸው የግብፁ ፕሬዚዳንት መሐመድ ሙርሲ ያቀረቡት ሃሳብ ቅቡልም ሆነ የማይረባ ከተቃዋሚዎች ጋር ተነጋግረዋል፤ የሱዳን መንግሥት የፖለቲካ እስረኞችን በመፍታት የተሻለ ብሔራዊ መግባባት ለመፍጠር እየጣረ ይገኛል፡፡ በአንፃሩ የኢትዮጵያ መንግሥት ግን በግትርነት ማሰርና መፈረጁን በመቀጠል የሀገራዊ መግባባት አደጋ እየሆነ ይገኛል፡፡ በሀገራችን ያሉ ችግሮችን ተነጋግሮ ለመፍታት ፈቃደኛም፣ ቁርጠኛም አይደለም ስለዚህ ራሱ መንግሥት ተጠያቂ የሚሆንበት ጉዳይ ብዙ ነው፡፡

በመዚህም መሠረት የአንድነት አቋም የሚከተለው ነው፡-

1.  የግብጽና የኢትዮጵያ መንግሥት ከፀብ አጫሪ ድርጊት በመቆጠብ፣ የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነትን ከሚያበላሹ ፕሮፓጋንዳዎችን ከመንዛት እንዲታቀቡና ለዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት የጠረጴዛ ዙሪያ ንግግሮች ላይ እንዲያተኩሩ እናሳስባለን፤

2.  አባይን መጠቀም የኢትዮጵያ ተፈጥሮዊ መብት መሆኑ እንዲታወቅ፣

3.  ሁለቱ ሀገሮች የአባይን ጉዳይ የውስጥ ፖለቲካቸው ማብረጃ ከማድረግ እንዲቆጠቡ፣

4.  ሀገራዊ መግባባት አሁኑኑ እንዲፈጠር መንግሥት ኃላፊነቱን እንዲወጣ፣

5.  የአባይ ጉዳይ የፖለቲካ  መጠቀሚያ መሆኑ እንዲያበቃ ጥሪ እናቀርባለን፡፡

አንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትሕ ፓርቲ (አንድነት)

ሰኔ 6 ቀን 2ዐዐ5 ዓ.ም

አዲስ አበባ

2 Comments

  1. አንድነቶች ብራቦ፡፡ ከጫጫታ ነፃ የሆነ ሚዛናዊ መግለጫ ነው፡፡ መለያችሁ የሆነውን ፓርቲዎችን የማሰባሰብ ስራችሁን አጠናክራችሁ ቀጥሉ፡፡

Comments are closed.

Previous Story

አንድነት ፓርቲ ለመድረክ ምላሽ ሰጠ፤ የተደበቀውን አፍረጠረጠው

Next Story

ሰማያዊ ፓርቲ በግብጽ ጉዳይ መግለጫ ሰጠ

Go toTop