February 17, 2013
18 mins read

ጥያቄዉ የሃይማኖት ሳይሆን የሰብዓዊ መብት ጥያቄ ነዉ ! አማኑኤል ዘሰላም

አማኑኤል ዘሰላም
amanuelzeselam@gmail.com
የካቲት 8  2013
 

ምንጩ ሳዉዲ አረቢያ የሆነው፣ ከነዳጅ በሚገኝ ሚሊዮን ዶላሮች የሚደገፈውና መረቡን በአለም ዙሪያ ሁሉ የዘረጋዉ፣  የዋሃቢዝም የእስልምና አክራሪነት፣ በአለማችን ትልቅ ችግር እየፈጠረ በብዙ አገሮች አለመረጋጋትን ያመጣ እንደሆነ፣ የአለምን ሁኔታ በቅርበት የሚከታታል ያጣዋል ብዬ አላስብም። አል ሻባብ፣ አል ካይዳ፣ አንሳር አሊዝላም ፣ ቦካ ሃራም  የመሳሰሉ ጸረ-ሰላምና ሽብርተኛ ቡድኖች መሰረታቸው፣ ይሄዉ ዋሃቢዝም ነዉ። ዋሃቢስቶች፣ እንኳን ከእስልምና ዉጭ ያሉ እምነቶችን ሊታገሱ ቀርቶ፣ ከነርሱ የቁራን አተረጓገም የተለየ አተረጓገም ዉጭ፣ ቁራንን የሚተረጉሙ ሌሎች ሙስሊሞችን ሳይቀር አይቀበሉም። ከነርሱ አመለካከትና እምነት ዉጭ ያሉ የሌላ እምነት ተከታዮች በሙሉ፣   እነርሱ ትክክለኛ ወደሚሉት እስልምና ካልመጡ በቀር «መጥፋት አለባቸው» ብለዉ የሚያምኑ ናቸዉ።

ሳዉዲ አረቢያ፣  የእስልምና ሁለቱ ታላላቅ ከተሞች (መካና መዲና) ያሉባት አገር ናት። የሳዉዲ ሙፍቲም፣ ፖፑ ለካቶሊኮች እንደሆኑት፣  ለሱኒ ሙስሊሞች መንፈሳዊ አባት ናቸው። በቅርቡ እኝህ ዋሃቢስቱ የሳዉዲ አረቢያዉ ሙፍቲ የተናገሩት፣ ስለዋሃቢዝም ምንነት በግልጽ የሚያመላክት ነዉ። «በአካባቢያችን  ቤተ ክርስቲያን መሰራት የለበትም። የተሰራም ካለ ደግሞ  መፍረስ በማለት ነበር ከዋሃቢዝም እስልምና ዉጭ ሌላ እምነትን ማስተናገድ እንደማይችል በግልጽ ያሳወቁት።

ከሁለት አመታት በፊት በወጣቶች እንቅስቃሴ የተነሳዉ የግብጽ አብዮት፣  ሙባረክ ከስልጣን እንዲነሱ አደረገ። ዋሃቢዝምን መመሪያዉ ያደረገዉ  የሙስሊም ወንድማማቾች ድርጅት፣ በየመስኪዶቹ ስለተደራጀ በቀላሉ ምርጫዉን አሸነፈ። ሞርሲ የአገሪቷ ፕሬዘዳንት ሆኑ። አዲስ ሕገ መንግስት የመጻፍ ስራ ተጀመረ። ሕገ መንግስቱ ከሻሪያ ጋር የተገናኘ እንዲሆን ተደርጎ ተዘጋጀ። ክርስቲያኖችና  አክራሪ ያልሆኑ ሙስሊሞች ተቃወሙ። ሞርሲ ግን እስልምናን  የበላይ የሚያደርግ፣ ለሌሎች እምነቶች እውቅና የማይሰጥ ሕገ መንግስት አስጸደቁ። ቁጥራቸው እጅግ በጣም ብዙ የሆኑ ክርስቲያኖች ባሉባት ግብጽ፣ የእስላማዊ መንግስት ተቋቋመ። ከሙባረክ አምባገነንነት ግብጽ ወደ እስልምና አክራሪነት ተሸጋገረች። የበጋዉ አብዮት ወደ ክረምት ጭጋግ ተቀየረ። ከእሳት ወደ ረመጥ ይሉታል ይሄ ነዉ።

በኢትዮጵያ የእስልምና  መንግስት በኃይል ለማቋቋም የአጭርና ረጅም ጊዜ እቅድ አውጥተዉ፣ በሳዉዲዎችና ግብጾች ተረድተዉ፣ በነርሱም  ሰልጥነዉ፣ ሊንቀሳቀሱ የሚችሉ ዋሃቢስቶች አይኖሩም ብሎ ማሰብ አስቸጋሪ ነዉ። እነዚህን አክራሪዎችን  ተከታትሎ፣ የገንዘብ ምንጫቸዉን አድርቆ፣ አክራሪነት እንዳይስፋፋ የማድረግ ሃላፊነትና ግዴታ መወጣት፣ ከማንም መንግስት የሚጠበቅ ነዉ። በዚህ ረገድ የአገሪቷን  ሕግ ተከትሎ አክራሪነትን ለመከላከል የሚደረግ ማናቸዉም አይነት እርምጃን  አልቃወምም።

ነገር ግን አክራሪነትን ለመዋጋት በሚል ሽፋን፣ የበለጠ አክራሪነትን የሚያስፋፋ፣ ለአገር የማይጠቅም፣ የአገሪቷን ሕግ የማያከብር ተግባራትን  መፈጸም ግን፣  እያንዳንዱን  ዜጋ ሊያሳስብና ሊያስቆጣ የሚገባ ነዉ።

በአገራችን በሙስሊሞች መካከል በተፈጠረው ችግር አማካኝነት፣  የተወሰኑ ወገኖች በሽብርተኝነት ክስ መታሰራቸዉ ይታወቃል።  የነዚህን ወገኖችን መታሰር ተከትሎ ፣ ከዚህ በፊት ለአንባቢያን ባቀረብኩት ጽሑፍ ፣ የሚከተለዉን  ምክር ለኢሕአዴግ አመራር አባላት አቅርቤ ነበር

«በመስኪዶች ሰላማዊ ተቃዉሞ ማሰማት፤ የመጅሊስ አመራሮች እንዲለወጡ መጠየቅ «ሽብርተኛ» ሊያሰኝ አይገባም። በመሆኑም ከሳዉዲ አረቢያ ጋር ግንኙነት የሌላቸው፣ የዋሃቢዝም አክራሪነትን ማስፋፋታቸዉን የሚያሳይ መረጃ ያልተገኘባቸዉ፣ በአዋሊያና በመስኪዶች ሕገ መንግስቱ የሚፈቅድላቸዉን  ተቃዉሞ በማሰማታቸው ብቻ የታሰሩ፣ ሰላማዊ ሙስሊም ወገኖቻችን ያለ አንዳች ቅድመ ሁኔታ መፈታት አለባቸው። እነርሱን በማሰር የሚገኝ አንዳች ጥቅም የለም። ዜጎች ተቃዉሞ ስላሰሙ የሚታሰሩበት አሰራር መቆም አለበት። ኢሕአዴግ በዚህ አንጻር ከኃይል እርምጃዎች ተቆጥቦ ማስተዋል ያለበት እርምጃ እንዲወስድ እመክራለሁ»

በቅርቡ የኢትዮጵያ ቴሌቭዥን አንድ ዘገባ አቀረበ። የቀረበው ዘገባ፣  የኢቲቪ ሪፖርተሮች፣ በታሰሩ ወገኖች ላይ የቀረበዉን  የፍርድ ቤት ሂደት ተከታትለው የዘገቡት ዘገባ አልነበረም። በፍርድ ቤት የቀረቡ ሰነዶችን አላነበቡም። ፍርድ ቤቱ የሰጠዉን ውሳኔ አልገለጹም። ነገር ግን እጆቻቸው በካቴና ከታሰሩ እስረኞች ጋር፣  በእሥር ቤት የተደረጉ ቃለ ምልልሶችን ነዉ ያቀረቡት።

እስረኞቹ ለተጠየቁት ጥያቄ ምላሽ ይሰጣሉ። አስቀድሞ ተጽፎ እንዲናገሩ የተሰጣቸው  ይሁን እዉነቱን  ለማረጋገጥ አይቻልም። በመሆኑም እስረኞቹ የተናገሩትን ይዘን፣  «እንዲህ ነዉ» ወይም «እንደዚያ ነዉ»  ልንል አንችልም።

ይልቅስ ብዙዎቻችንን  ያሳሰበና ያሳዘነ  ጉዳይ ቢኖር እስረኞቹ በመጀመሪያ ደረጃ በቴሌቭዥን እንዲናገሩ መደረጉ ነዉ። ጉዳያቸው በፍርድ ቤት እየታየ ባለበት ወቅት፣  አስቀድሞ በፍርድ ቤት ሊቀርብ የሚገባን  ነገር በሜዲያ ማዉጣት፣  ሂደቱን የፍርድ ሂደት ሳይሆን የፖለቲካ ሂደት አድርጎታል።

የአገሪቷ ሕገ መንግስት ፍርድ ቤቶች  ነጻ እንደሆኑ ይደነግጋል። ነገር ግን ኢቲቪ ያቀረበዉ ፕሮግራም በቀጥታ የፍርድ ሥርዓቱን የሚንድ ሆኖ ነዉ የተገኘዉ። የዜጎችን ሕገ መንግስታዊ መብቶች የሚጋፋ፣ ፍርድ ቤት ዉሳኔ ሳይሰጥ በፍርድ ቤት ሥራ ላይ ጣልቃ የሚገባ ጎጂ ተግባር ነዉ።

የታሰሩ ወገኖች ጥፋተኛ ይሁኑ አይሁኑ ገና ፍርድ ቤት አልወሰነም። ፍርድ ቤት እስካልወሰነ ድረስ ማንም ወንጀለኛ ጥፋተኛ ተደርጎ ሊቆጠር አይችልም። ኢቲቪ እነዚህን ሰዎች አቅርቦ ኑዛዜ ማናዘዙ በሕግም ሆነ በሞራል አንጻር ተቀባይነት የሌለዉ፣  ኢሕአዴግን እንቃወማለን የሚሉ ብቻ ሳይሆን ኢሕአዴግን የሚደግፉ ሁሉ ሊያወግዙት የሚገባ ነዉ። አንድ በሉ።

እነዚህ እስረኞች በኢቲቪ ቀርበዉ ቃለ መጠይቆችን ሲሰጡ፣  ጠበቆቻቸው በአካባቢው አለመኖራቸውን መርሳት የለብንም። ሕገ መንግስቱ ዜጎች የጥብቅና መብት እንዳላቸው በግልጽ ያስቀምጣል። ዜጎች በፍርድ ቤትም ሆነ በፖሊስ ፊት ሲቀርቡ ከጠበቆቻቸው ጋር የመመካከር፣ ጠበቆቻቸውም በነርሱ ስም ምላሽ እንዲሰጡ የማድረግ ሙሉ መብት አላቸዉ። ኢቲቪ ከማረሚያ ቤት ሃላፊዎች ጋር በመነጋገር፣ ጠበቃዎቻቸዉን አልፈው፣ በአቋራጭ እስረኞችን ማናዘዛቸዉ ትልቅ ስህተት ነዉ። ሁለት በሉ።

«እስረኞቹ ቃለ መጠይቆች  ሲሰጡ በዉዴታና ነዉ ወይንስ ተገደው ?» ለሚለው ጥያቄ ግልጽ የሆነ ምላሽ ሊሰጥበት ይገባል። «እስረኞቹ ድብደባና ስቃይ ስለበዛባቸው  ነዉ ባለስልጣናቱ መስማት የሚፈልጉት የተናገሩት» የሚሉ ወገኖች አሉ። እስረኞች መደብደባቸውን የሚያረጋግጥ መረጃ ባይኖርም፣ አለመደብደባቸዉንም የሚያሳይ መረጃ የለም። በመሆኑም በዚህ ረገድ ኢሕአዴግ ግልጽ ምላሽ መስጠት ይጠበቅበታል። ሶስት በሉ።

እንግዲህ ከዚህ በመነሳት ነዉ፣  ኢሕአዴግን እንደግፋለን የሚሉ ወገኖች፣ በሚደግፉት ድርጅት አመራር አባላት ላይ ጫና እንዲያሳድሩ የሚከተሉትን ነጥቦች የማስቀምጠዉ።

  1. በኢቲቪ የተላለፈው ፕሮግራም እንዲቀናበርና እንዲተላለፍ መመሪያ የሰጡ ባለስልጣናት፣ የማስታወቂያ ሚኒስትሩን ጨምሮ ሊጠየቁ ይገባል። ኢሕአዴግ ሃላፊነት የሚሰማዉ እንደሆነ የኢሕአዴግ ደጋፊዎች ሲናገሩ እንሰማለን። እንግዲህ ሃላፊነት ከሚሰማዉ ድርጅት የሚጠበቀዉ ለተሰሩት ስህተቶችና ጥፋቶች የአመራር አባላቱ ተጠያቂ ሲሆኑ ነዉ።
  2. የታሰሩ እስረኞች  በኢቲቪ ሆነ፣ ጠበቆቻቸው በሌሉበት፣ የተናገሩት ሁሉ በፍርድ ቤት እንደ መረጃ እንዳይቀርብ፣  ከጠበቆቻቸው ጋር ያለ አንዳች ገደብ እስረኞቹ መገናኘት እንዲችሉ መደረግ አለበት።
  3. ከሳዉዲ አረቢያ ጋር ግንኙነት የሌላቸው፣ የዋሃቢዝም አክራሪነትን ማስፋፋታቸዉን የሚያሳይ መረጃ ያልተገኘባቸዉ፣ በአዋሊያና በመስኪዶች ሕገ መንግስቱ የሚፈቅድላቸዉን  ተቃዉሞ በማሰማታቸው ብቻ የታሰሩ፣ ሰላማዊ ሙስሊም ወገኖቻችን ያለ አንዳች ቅድመ ሁኔታ እንዲፈቱና ያሉት ችግሮች በሙስሊሞቹ  በራሳቸው እንዲፈታ ማድረግ የሚቻልበት ሁኔታ መፈጠር አለበት። ቅንነት ያለበት ንግግር ብቻ ለችግሮች ዘላቂ መፍትሄ የሚሰጠዉ።

ዜጎችን በማሰር፣ ዜጎችን  በቴሌቭዥኝ በማዋረድና በማሳነስ አገር አትለማም። ዜጎች ጥፋተኛም  ቢሆኑ የሰብአዊ መብታቸው ሊከበር ይገባል። የኢሕአዴግ ደጋፊዎች፣ ከኢሕአዴግ አመራሮች መመሪያ ተቀብለው፣  የሚደግፉት ድርጅታቸው በሚያደርጋቸው መልካም የልማት ተግባራት እንድንተባበር እንደሚገፋፉን ሁሉ፣ ድርጅታቸው የሚያደርጋቸውን ጎጂና አሳዛኝ የሰብአዊ መብት ረገጣን በአስቸኳይ እንዲያቆም በመጠየቅ፣  በአመራር አባላቱ ላይ ግፊት እንዲያደርጉ በአክብሮት እጠይቃለሁ።

በዚህ አጋጣሚ የኢቲቪን አሳዛኝ ዘገባ እንደመሳሪያ በመጠቀም፣ ጉዳዩ የሰብአዊ መብት ጉዳይ ሳይሆን የሃይማኖት ጉዳይ እንደሆነ ለማቅረብ የምንሞክር ካለን፣  ጥንቃቄ ብናደርግ ጥሩ ነዉ እላለሁ። በሃይማኖት ጉዳይ ላይ «እንደዚህ ነዉ እንዲዚያ ነዉ» ብሎ፣  ለጊዚያዊ ትንሽ የፖለቲካ ትርፍ ብለን፣ የሚገነባ፣ የሚያስታርቅና የሚያቀራርብ ሳይሆን፣  ነገሮች የበለጠ ወደ ከረረ ሁኔታ የሚወስድ እንቅስቃሴ ባናደርግ መልካም ነዉ። ከገዢዉ ፓርቲ ጋር ችግር ስላለን ብቻ፣ ከተቀጣጠለ ሊበርድ የማይችልን እሳት ባንለኩስ ይሻላል።

ኢሕአዴግን የምንቃወምበትና የምናወግዝበት ብዙ የተጨበጡ ምክንያቶች አሉ። እስከሚገባኝ ድረስ ግን ላለፉት 20 አመታት ኢሕአዴግ ለሙስሊሙ ማህበረሰብ መልካም በማድረግ እንጂ የእምነት ነጻነትን በመጋፋት አይታማም። ኢሕአዴግ የሃይማኖት ነጻነትን የተጋፋ አይመስለኝም። በኢሕአዴግ ዘመን፣ ሙስሊሙ ማህበረሰብ ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ ነው መስኪዶችን የገነባዉ። ከሃያ አመታት በፊትና እና አሁን በአዲስ አበባ ብቻ ያሉትን የመስኪዶች ቁጥር ማወዳደሩ ብቻ ይበቃል። ሙስሊሞች በታላቁ ስታዲየም በፈለጉበት ወቅት ተሰባስበዉ ለመስገድና ለመጸለይ የተከለከሉበት ጊዜ የለም። የፈረሱ፣  የተቃጠሉ ብዙ አብያተ ክርስቲያናት እንዳሉት፣ የተዘጋ ፣ የፈረሰ ወይንም የተቃጠለ አንድም መስኪድ የለም። ተቃዉሞዎች ስናቀርብ፣ በተቻለ መጠን እዉነትን ይዘን ብንቃወም ጥሩ ነዉ።

በነገራችን ላይ ፣ ኢቲቪ ያቀረበዉ አሳዛኝ ድራማ በሙስሊሙ እስረኞች የተጀመረ አይደለም። ከዚህ በፊትም አኬልዳማ የተሰኘ አሳዛኝ ድራማ ቀርቦ እንደነበረ መዘንጋት የለብንም። ስለዚህ ሃይማኖትን ከዚህ እናዉጣ። ጥያቄዉ የሃይማኖት ጥያቄ አይደለም። ጥያቄዉ የሕግ፣ የሞራልና የሰብዓዊ መብት ጥያቄ ነዉ።

 

Go toTop