የሙስና ክተት፤‎ ‎ከታምራት ላይኔ እስከ መላኩ ፈንታ

ከአበባየሁ ገበየሁ
አቶ ታምራት ላይኔብዙዎቹ ቱባ የመንግስት ባለስልጣናት ሙሰኞች መሆናቸው ይታወቃል ፡፡ ይቅርታ በፍርድ ቤት ቋንቋ ‹‹ ተጠርጣሪ ›› ፣ በሰልጣኝነት ቋንቋ ‹‹ ዕጩ ›› ለማለት ስነ ምግባሩ ያስገድደናል ፡፡ አማርኛው ይገጣጠም ከተባለ ተጠርጣሪ ወይም ዕጩ ሌቦች ሊባሉ ነው ፡፡ መቼም ለዚህ አባባል ትክክለኛነት የግድ የባንክ ደብተራቸውን መመልከት አይገባም ፡፡ ባለስልጣናቱ በ 4 እና 6 ሺህ ብር ደመወዛቸው ለፈረንጅ እና ለተቋማት ኪራይ የሚበቃ ግዙፍ ህንጻ በየስርጓጎጡ መገንባታቸውን ፣ ብር በየቀኑ እያጨዱ የሚያቀርቡላቸውን ሱቃቸውንና መኪናዎቻቸውን ፣ በራሳቸውም ሆነ በዘመዶቻቸው ከአዲስ አበባ እስከ ሁሉም ጫፎች ያሰባሰቡትን መሬት ማየት ይበቃል ፡፡
የእድል ጉዳይ ሆኖ ግን እጃቸው ለካቴና የሚበቃው የጥቂቶች ነው፡፡ ነገረ ስራቸውን ሲከታተል የሚቆየው ተዘራፊ ህዝብ የሚበሳጨውም የቅጣቱ መንስኤ ፍትሀዊ ይዘትን መሰረት ባለማድረጉ ነው ፡፡ ለበርካታ አመታት ተቆርቋሪ መስለው እንደሚዘርፉ እየታወቀ በሌብነታቸው ብቻ አይጠየቁም ፡፡ በአንዲት ጠማማ ቀን ሌብነቱ ላይ ፖለቲካ ወይም ያልተገባ ‹‹ ነገር ›› ሲጨምሩ ግን ‹‹ ባቡሩ ›› ወህኒ ቤት ያደርሳቸዋል ፡፡
መቼም ይህ ሀሳብ መላምት አይመስልም ፡፡ ምክንያቱም ፤
‹‹ የታምራት ላይኔ ጦር ግባ ተብለሃል ! ›› ሲባል ሰምተናል ፡፡
አቶ ታምራት ‹‹ እለፍ ተብለሃል ›› ሲባሉ የሚጠበቀውን የጀግንነት ፉከራና ቀረርቶ አላሰሙም ፡፡ ስኳር አብዝተው መላሳቸው በቅኔ ተደጋግሞ ሲነገራቸው ልምዳቸውን ተጠቅመው አሪፍ የመልስ ምት ይመልሳሉ ብሎ የሚጠብቀው ብዙ ነበር ፡፡ ለምሳሌ ያህል ‹‹ የኔ ስኳር መቃም ምን ይደንቃል ፣ ሸንኮራ አገዳውን የሚጨረግደው ሞልቶ ›› የሚል አይነት ፡፡ ሆኖም የማይጠበቀውን እንባ ነበር በፍርድ ቤትም ፣ ከእስር በኃላም በስብከት ግዜ ያንቆረቆሩት ፡፡ የፍርድ ቤቱ ምልልስ ሲበዛባቸው ግን በእሳቸው ፣ በልጃቸውና ባለቤታቸው ላይ የተፈጸመውን ደባ በለሆሳስም ቢሆን አስረድተዋል ፡፡
‹‹ የስዬ አብርሃ ሜካናይዝድ ቀጥል ተብለሃል ! ›› ሲባልም ተገርመናል ፡፡
አቶ ስዬ ግን ዝምታ ለበግም አልበጃት በሚል ሀሳብ ገና ከጠዋቱ ነበር ባለፉበት ችሎት ሁሉ ፉከራና ቀረርቶ የተጠቀሙት ፡፡
‹‹ ዘራፍ ! ስዬ አብርሃ !
የድል የጀግንነት ቀለሃ
ማነው ወንዱ ያለ ግብሩ ስም የሰጠው
ላም ባልዋለበት ኩበት የለቀመው ! ››
አቶ ስዬ ለተከሰሱበት አንድም የሙስና ጉዳይ እውቅና አልሰጡም ነበር ፡፡ ‹ እኔ የታሰርኩት በሌብነት ሳይሆን ከአቶ መለስ ጋር በነበረኝ የፖለቲካ ልዩነት ነው ›› ነበር ያሉት ፡፡ አንዳንድ ተረበኞች ግን ያ ሁሉ ተገዛ የተባለው ትላልቅ መኪና የህወሃት ነው ወይስ የኢፈርት ? ማለታቸው አልቀረም ፡፡
‹‹ የአባተ ኪሾ ሻለቃ እለፍ ተብለሃል ! ›› ሲባል ተደምመናል ፡፡
መላኩ ፈንታ እኚህ ናቸው።ቀስ እያሉ እየጋሉ የመጡት አቶ አባተ አንድ ደፋር ሀሳብ ሰንዝረዋል ይባላል ፡፡ ‹ እኔ በሙስና የምጠየቅ ከሆነ እገሌ / እገሊትም መጠየቅ ይኖርበ / ባታል › የሚል ፡፡ ወሬው በአለ ተባለ ሃዲድ መጥቶ ጆሮአችን የደረሰ በመሆኑ መጠየቅ አለበት የተባለውን ከፍተኛ ባለስልጣን ስም አናነሳም ፡፡
እናም ይህን የመሰለው የክተት ጥሪ ቀላል አልነበረም ፡፡ አቶ ቢተው በላይን ጨምሮ ሌሎች የመንግስት ባለስልጣናትም ጥሪው ደርሷቸው የደንቡን አድርሰው ተመልሰዋል ፡፡ በርግጥ ሊጠሩ ከሚችሉ ‹‹ አዝማቾች ›› መካከል አንዳንዶቹ ከኑግ ጋር እንደተገኘ ሰሊጥ ላለመወቀጥ ፣ ወይም ምን ያለበት ምን አይችልም እንዲሉ… ብቻ በአንድም ሆነ በብዙ ምክንያቶች ከቻሉ በቦሌ ካልቻሉ በሞያሌ ወጥተዋል ፡፡ በዚህ መልኩ መውጣታቸው እንጂ ኢህአዴግ የብዙዎቹን ስም እየጠራ ብዙ ነጋሪት ለመጎሰም በበቃ ነበር ፡፡ በርግጥ ድርጅቱ ከነበሩበት ከፍተኛ ቦታ አውርዶ መሬት ዘጭ የሚያደርጋቸው የተለያየ ታርጋ በመስጠት ነው ፡፡ በችሎታ ማነስ፣ በእድሜ መግፋት፣ ታማኝነት በማጉደል፣ ኔትወርክ በመፍጠር የሚባሉት የተለመዱ ዓይነቶች ናቸው ፡፡
በእውነተኛ ጨዋታ ህዝብና መንግስት ላይ ተገቢ ያልሆነ ፋውል በመስራትም ይሁን ፣ በተለያዩ ጥቅማጥቅሞች አይናቸውን በታወሩ ዳኞች ግፍ ቀይ ካርድ በማየት እስር ቤት ተወርውረው የነበሩት ባለስልጣናት / ታምራት፣ ስዬ፣ አሰፋ፣ ቢተው፣ … / ቅጣታቸውን ጨርሰው ዛሬ በራሳቸው መስመር እየተጓዙ ናቸው ፡፡ በያሉበት ሆነው እንደ አዲስ የተነሳውን የመንግስት ጥሪ ወይም ‹‹ እለፍ ተብለሃል ! ›› ን እንደሚሰሙ አይጠረጠርም ፡፡ ጥሪውንም ሆነ ያሳለፉትን መሪር ቆይታ ሲያስታውሱ ቀረርቶና ፉከራ ሳይሆን አሳዛኝነት ያላትን የጦር ሜዳ መዝሙራቸውን ደጋግመው የሚያንጎራጉሩ ይመስለኛል
‹‹ እንዳያልፉት የለ ያ ሁሉ ታለፈ
ታጋይ የህዝብ ልጅ በደሙ በላቡ ታላቅ ታሪክ ጻፈ ››

በርግጥ የእስር ቤቱ ሰቆቃ ታልፏል ፡፡ ምን አዲስ ነገር ጻፉ ? የሚል ጥያቄ ግን በአሽሙረኞች ተያይዞ መነሳቱ አይቀርም ፡፡ ‹‹ ከፖለቲካ መሪነት ወደ ሃይማኖት ሰባኪነት ! ›› ይሉናል አቶ ታምራት ‹‹ ፈጣሪን ከመክዳት የፈጣሪ ታላቅነትን ወደ መቀበል ! ›› በማለት አስረግጠው ይነግሩናል ፡፡ ‹‹ ከሰው ገዳይነት ወደ ሰው ተንከባካቢነት ! ›› ቢሉ ማን ይከለክላቸዋል ፡፡ ‹‹ በሃይል ተማምኖና በደመ ነፍስ ተናግሮ ህዝብን ከማስቀየም በመጽሀፍ እያመኑ ፍቅርን ማካፈል ›› ቢሉ ከአንደበታቸው ማር ፈሰሰ አይባልም ? ፡፡ በርግጥም ጉዞው ከአንዱ ዋልታ ወደ ሌላኛው ጫፍ በመሆኑ አዲስ ነገር መሆኑ አያጠራጥርም ፡፡
‹‹ ከኢህአዴግነት ወደ ተቃዋሚነት ! ›› ይሉናል አቶ ስዬ በበኩላቸው ‹‹ ከአብዬታዊ ዴሞክራሲ ወደ ሊበራል ›› በማለትም የፕሮግራሙን መሰረታዊ ልዩነት ሊያብራሩ ይችላሉ ፡፡ ነገሩን ላጡዘው ብለው ካሰቡ ደግሞ ‹‹ ከጎጠኝነት ወደ ህብረ ብሄራዊነት … ከገንጣኝነት ወደ አስመላሽነት… ›› በማለት ምርጫ ሳይደርስ የእንካ ሰላንቲያ መድረክ እንዲከፈት ሊያደርጉ ይችላሉ ፡፡ ምናባቸውን ለማስፋትም የእውቀት ትጥቆችን በውጭ ሀገር እየሸማመቱ መሆኑን ቢጠቃቅሱ አዲሱ ሲቪያቸውን አደለቡ ማለት ነው ፡፡ ይሄ ሁሉ ሆኖ የአቶ ስዬ ለውጥ ከፖለቲካ ምህዋር ባለመውጣቱ መሰረታዊ ለውጥ አይደለም ብሎ ለመከራከር መንገድ ይከፍታል ፡፡ እንደውም አንዳንድ ወገኖች አዲስ ወይን ጠጅ በአዲስ አቁማዳ ወይስ አሮጌ ወይን ጠጅ በአዲስ አቁማዳ የሚል ፈታኝ ጥያቄ ይወረውራሉ ፡፡ በሁለቱ ፓርቲዎች መካከል ያለውን ልዩነትና ህዝባዊ ጥቅም ፈትፍቶ ማስረዳት የሚችል ፖለቲከኛ ካለ ግን የጎዳናቸውን ‹‹ አዲስነት ›› ማስረዳት ይችላል ፡፡
ለማንኛውም የኢህአዴግ ባለስልጣናት መዝሙሯንና ጥሪዋን እንደ አንድ ሳንቲም ሁለት ገጽታ መመልከት ይኖርባቸዋል ፡፡ ምክንያቱም የተራ ጉዳይ ካልሆነ በስተቀር ብዙዎቹ ለጥያቄ ትፈለጋለህ መባላቸው አይቀርም ፡፡ ከእስር በኃላ ደግሞ ‹‹ እንዳያልፉት የለ ! ›› የምትለውን መዝሙር ሊደጋግሟት ግድ ይላቸዋል ፡፡ ምነው ቢሉ – ለመጽናናት ፡፡
እናም ጥሪው ቀጥሏል …
‹‹ የመላኩ ፈንታ ብርጌድ እለፍ ተብለሃል ! ›› ተብሏል ሰሞኑን ፡፡
ይህ ጦር በምክትላቸው በአቶ ገ/ዋህድ ገ/ጊዮርጊስና ልማታዊ በነበሩ ቱጃር ነጋዴዎች የተዋቀረ በመሆኑ የክብደቱን ደረጃ ከፍ ያደርገዋል ፡፡ እንደውም አንዳንድ ነገረኞች በኪሳቸው መደለብ ‹ ቼልሲ › በቅርበታቸው ደግሞ ‹ ፋቲክ ያለበሱ አጋዚዎች › ለማለት እየዳዳቸው ይመስላል ፡፡ ይህ ዜና ከተነገረ በኃላ የተደናገጡ ፣ የተደመሙ ፣ የተደሰቱና እስካሁንም እየሆነ ነገር ባለው ጭፍግ ድራማ እየተዝናኑ የሚገኙ የህብረተሰብ ክፍሎች ከኤርትራ ህዝብ ብዛት በሶስት እጥፍ ይበልጣሉ ፡፡
አቶ መላኩ ‹‹ እለፍ ተብለሃል ! ›› ሲባሉ በምላሻቸው የማንን ስልት እንደሚከተሉ ናፋቂ ሁኔታ ፈጥሯል ፡፡ ክሱን አምነው ይቀበላሉ ወይስ በታኮነት ስለሚያገለግለው ፖለቲካና ሌሎች አዳዲስ ጉዳዮች ዘርዘር አድርገው ይነግሩን ይሆን ? አንዳንድ ሚዲያዎች እንደገለጹት በባህርዳሩ ስብሰባ ታክስ የማይከፍሉ በርካታ ‹ ልማታዊ › ካምፓኒዎች መኖራቸውን ጠንከር አድርገው ተችተው ነበር ፡፡ ይህ ማለት ደግሞ ሾርባው ውስጥ ነጭ ሽንኩርትን የሚወክለው ዝርፊያና ጥቁር አዝሙድን የመሰለው ‹‹ ነገር ›› ተደባልቀው ይገኛሉ ማለት ነው ፡፡
ጸረ ሙስና ኮሚሽን የአቶ መላኩን ብርጌድ አንድ ዓመት ከ 8 ወር በፈጀ ጥናት ነው ገቢ ያደረኳቸው ቢልም ኢኮኖሚስቱ አቶ መላኩም ለመንግስታቸው የማይታመን ገቢ መፍጠራቸውን ልብ ይሏል ፡፡ እንደው ለምሳሌ በሙግታቸው ፣
‹‹ ዘራፍ ! መላኩ !
ስራ ነው አምላኩ
አንድ እንጀራ ልኩ
ሳታውቁት አትንኩ … ›› ብለው ከተነሱ በተያዙበት ጉምሩክ ምን ሰርተው ቆዩ የሚለውን ጥያቄ መመለስ ሊገባን ነው ማለት ነው ፡፡ የኢትዮጽያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣን በአዲስ መልክ እአአ በ2008 ሲቋቋም በቦታው የተሾሙት በአቶ መለስ ዜናዊ አማካኝነት ነበር ፡፡ መ/ቤቱን በአዲስ አደረጃጀትና አሰራር በአጭር ግዜ በማዋቀር ፣ የታክስ ከፋዩን ቁጥር በማብዛትና አዳዲስ የታክስ ስርዓቶችን ስራ ላይ በማዋል ባስገኙት ለውጥ ተጨብጭቦላቸዋል ፡፡ ሰውየው ቦታውን ከመያዛቸው በፊት የመንግስት ገቢ 19 ቢሊየን ብር ነበር ፡፡ በእሳቸው የስራ ዘመን ማለትም በ2011/12 የፌዴራል መንግስት ገቢ 71 ቢሊየን ብር መድረስ ችሏል ፡፡ አንዳንዶች የቅጣትና የማስገደድ ስርዓትን በመከተላቸው ያገኙት ውጤት ነው እያሉ ቢያሟቸውም የፈጠሩት ለውጥ ግን ትልቅ ሊባል የሚችል ነው ፡፡
የአቶ መላኩ ክስ ሌላ ጦስ ሊያስከትል ይችላል ብለው የሚያስቡ የህብረተሰብም ክፍሎችም ጥቂቶች አይደሉም ፡፡ ምክንያቱም የሃብት ስር በሆነው ቦታ ላይ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ሲጠቀሙ የነበሩ ባለስልጣናትና ትላልቅ ነጋዴዎች በርካታ በመሆናቸው አንዱ ሌላውን ወደ ጥቁሩ መረብ የማስገባቱ ስራ ሊቀጥል ይችላል በማለት ፡፡ በርግጥ የስነምግባርና ጸረ ሙስና ኮሚሽን በቅርቡ ከ50 በላይ የሚሆኑ የመንግስት ባለስልጣናት፣ ነጋዴዎችና ሌሎች ተጠርጣሪ ሰዎችን መያዙን የመግለጹ ጉዳይ እየተነሳ ያለውን ሀሳብ የሚያጠናክር ይመስላል ፡፡
የሰላም፣ ልማትና እድገት ጸር የሆነውን ሙስና በተደራጀ መልኩ መዋጋት ግድ ነው ፡፡ የሚያሳፍረው ግን ባለስልጣናት ለስርዓቱ ታማኝ እስከሆኑ ድረስ ሀገሪቷን ይጋጡ የሚለው ድሃ አስተሳሰብ ነው ፡፡ ብዙዎቹ መንግስትን የሚጠራጠሩትና አብረው ለመስራት ሙሉ ልብ የማይሰጡት ባለስልጣናትን እየቀጣ የሚገኘው በሚያደርሱት በደልና በንጹህ የሌብነት ተግባራቸው አለመሆኑ ነው ፡፡ ከዘራፊነታቸው ይልቅ የፖለቲካ አለመታመናቸው ነው ሚዛን ደፊ ተደርጎ የሚቆጠረው ፡፡
ከ 176 ሀገሮች የ113ኛ ደረጃ በያዘች ሀገር ሙስናን በርካሽ የፖለቲካ ጥቅም ማስታመም ቀስ በቀስ ሀገርን ለመግደል ምቹ ሁኔታ እየፈጠሩ የመጓዝ ያህል የሚያስቆጥር ነው ፡፡ ታዲያስ መጋዚን Global Financial Integrity የተባለ ድርጅትን ጠቅሶ እንደዘገበው ከ 2001 – 2010 ባለው ግዜ ውስጥ በኢትዮጽያ ባለስልጣናትና በተለያዩ ሰዎች ወደ ውጭ የወጣው ገንዘብ 16 . 5 ቢሊየን ዶላር ነው ፡፡ ይህ መረጃ ሊያሳዝነንም ሊያሳፍረንም ይገባል ፡፡ ይህ ሁሉ ሀገራዊ ሀብት ወደ ውጭ የወጣው በላይኞቹ ባለስልጣናት ቀጥተኛ ተሳትፎና የተዘዋወረ ድጋፍ ጭምር መሆኑ መታወቅ አለበት ፡፡
እንግዲህ አደኔን አጠናክሬ እቀጥላለሁ እያለ የሚፎክረው ጸረ ሙስና ኮሚሽን መረቡን በጣም እየተረተረ ባህሩ ውስጥ በጣለ ቁጥር አዞ አይደለም ሻርክን ሊያጠምድ ይችላል ፡፡ ጉዱ የሚፈላው ያኔ ይሆናል ፡፡ ወይ ከሻርኩ ጋር መጋፈጥ አለበት አሊያም መረቡን ለሻርኩ ጥሎ እግሬ አውጪኝ ይላል ፡፡ ይህን የመሰለ አጋጣሚ ከተፈጠረ እንደ ፉከራው በተግባርም ሩቅ ለመጓዝ የሚያስችል መተማመኛ አይገኝም ፡፡
ስለ Back Fire ወይም ተቃራኒ ውጤት ውስን ምሳሌዎችን ልወርውርና ጽሁፌን ልቋጭ ፡፡
. መንግስት አጋጣሚዎችን በመጠቀም ሙሰኞችን የሚሸከምበት ጫንቃ እንደሌለው ለህዝብ ያስረዳል ፡፡ የሙስናው ስር ሄዶ ሄዶ ጭንቅላት ላይ ከደረሰ ግን ክሱ እንዲለዝብ ወይም እንዲሰረዝ ይደረጋል – Back Fire – 1
. ጸረ ሙስና ኮሚሽን አንድ ሰሞን የጀመረው ዘመቻ እንደጋለ እንዲቀጥል ድጋፍ አድርጉልኝ በማለት ለህዝቡ ጥሪ ያቀርባል ፡፡ የጥቆማው ምንጭ ሄዶ ሄዶ ከትልቅ ባለስልጣናት እልፍኝ ዘው ሲል አብሮ መግባት ይከብዳል ፡፡ ውሻው … ፖሊሱ … ንጉስ አይከሰስ የሚለው ብሂሉ… ለቋጥኙ ዘብ ይቆማሉ ፡፡ ጸረ ሙስና በደከመ ትንፋሽ ‹ ጥርስ የሌለኝ አንበሳ ሆኛለሁ › ሲል ይሰማል – Back Fire – 2
. የአቶ መላኩ መ/ቤት ውስጥ ብዙ ሙሰኞች መኖራቸውን ህዝቡ ይጠቁም ነበር ፡፡ ይህን ሃሳብ በመያዝ ይመስላል ሪፖርተር በአንድ ወቅት ከሚ/ሩ ጋር ቆይታ አድርጎ ነበር ፡፡ ይህ አቤቱታ አውነት ነው ? ሲል ላቀረበው ጥያቄ የሰጡትን ምላሽ እንደወረደ አቅርቤዋለሁ
‹‹ I can not say that our employees do not have problems . For that reason we have put in place special administrative rules . We have applied these rules from hiring to firing . አቶ መላኩም Firing ተደርገዋል … an employee who is unethical and incompetent will have no excuse for coming back . አቶ መላኩም ይቅርታ የማግኘታቸው ጉዳይ የጠበበ ይመስላል … for instance, we have fired fifty employees so far and instituted criminal charges against some of them . አቶ መላኩም ቢያንስ ተጠርጣሪ ወንጀለኛ ተብለዋል … We have managed to have them sentenced up to ten years in prison . አቶ መላኩም በሙግታቸው ካልረቱ በስተቀር ጥቂት የማይባሉ ዓመታትን ወህኒ ቤት ያሳልፋሉ – Back Fire – 3
የተቃራኒው ውጤት / Back Fire / እየበዛ ከሄደስ ? ህዝቡ የነጋሪቱን ጥሪ በሚከተለው መልኩ ለመጎሰም ይገደዳል
‹‹ የኢህአዴግ ፓርቲ ግባ ተብለሃል ! ››

irob ethiopia
Previous Story

ወርሃ ግንቦት ሲታወስ! – (ኢሮብ መብት ተማጓች ማኅበር የበተነው ጽሑፍ)

Next Story

ሸንጎ በአ.አ የተደረገውን ሰልፍ “በሺዎች የተጀመረው እንቅስቃሴ የሚሊዮኖች ይሆናል” አለ

Latest from Blog

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤ/ክ የውጪ ግንኙነት የቤተክርስቲያኒቱን የሺሕ ዘመናት ታሪክ እና እሤቶቿን የሚመጥን መሆን ይኖርባታል!!

በተረፈ ወርቁ (ዲ/ን) (ለሪፖርተር ጋዜጣ እንደጻፈው) እንደመንደርደሪያ ለዛሬው የግል ትዝብቴንና ታሪክን ላዛነቀው ጽሑፌ መነሻ የሆነኝ- ባሳለፍነው ሳምንት በአፍሪካ ኅብረት ኔልሰን ማንዴላ የመሰብሰቢያ አዳራሽ ለአንድ ቀን የተካሄደው፤ ‹‹የአፍሪካ  መንፈሳዊ ቀን/The African Spiritual

የአበባው ታደሰ እና የአረጋ ከበደ ፍርጠጣ | ስለአማራ ክልል ከነዋሪዎች የተሰማው | አበባው ጉ’ድ ሆነ – “አበባውን ሳትይዙ እንዳትመጡ”|“በባህርዳር ተከበናል፣ ከፍተኛ አዛዦች ተመተዋል” | “ፋኖ መንግ’ስት ሆኗል” ጄ/ሉ |

የአበባው ታደሰ እና የአረጋ ከበደ ፍርጠጣ አበባው ጉ’ድ ሆነ – “አበባውን ሳትይዙ እንዳትመጡ”|“በባህርዳር ተከበናል፣ ከፍተኛ አዛዦች ተመተዋል”| “እጅ ከመስጠት ውጭ አማራጭ አይኖረንም” ፊ/ማ “ፋኖ መንግ’ስት ሆኗል” ጄ/ሉ |
Go toTop