ሰማያዊ ፓርቲ በአዲስ አበባ የጠራው የተቃውሞ ሰልፍ በሰላም ተጠናቀቀ

(ዘ-ሐበሻ) በአዲስ አበባ ዛሬ ግንቦት 25 ቀን 2005 ዓ.ም የተደረገውን የሰማያዊ ፓርቲ የሰላማዊ ሰልፍ ተቃውሞ የኃይለማርያም ደሳለኝ መንግስት ፍቃድ መስጠቱ የሚያስመሰግነው ቢሆንም የሕወሓት/ኢሕአዴግ ወታደሮች በሌላ በኩል ሰልፉ እንዳይካሄድ ሲያውኩ ነበር የከረሙት። ትናንት በአዲስ አበባ 6 የሰማያዊ ፓርቲ አባላት ሾላ የካ ሚካኤል አካባቢ ቅስቀሳ በሚያደርጉበት ወቅት ፖሊስ በቁጥጥር ስር ውለው የነበረ ሲሆን ነገር ግን ፍርሃት የሚባለውን ነገር እያስወገደ የመጣው የኢትዮጵያ ሕዝብ በአካባቢው የሚገኙ ህብረተሰቦች በግምት ወደ 200 የሚጠጉ ልጆቹን ለማስፈታት ባደረጉት ጥረት ከአንድ ሰአት ግርግር በኋላ የታሰሩትን ልጆች ማስፈታት እንደቻሉና፤ ባካባቢው የነበረውም ህብረተሰብ ጭብጨባና ዘፈን በማሰማት ከአካባቢው መበተኑን ሰማያዊ ፓርቲ አስታውቆ ነበር።
መንግስት ይህን የተቃውሞ ሰልፍ በአንድ በኩል ፈቃድ ሰጪ በሌላ በኩል አሰናካይ በመሆን ቢቀርብም ለሰላማዊ ሰልፍ የወጣው በበብዙ ሺዎች የሚቆጠረው ህዝብ ግን ጥያቄው አሁንም ሰላማዊ መሆኑን አሳይቶ ድምጹን በሚገባ በማሰማት በሰላም ወደ መጣበት ተመልሷል።
ከምርጫ 97 በኋላ ሟቹ ጠ/ሚ/ር ከቤት ውጭ የሚደረጉ ማናቸውንም የተቃውሞ ሰልፎች ከከለከሉ ወዲህ ለመጀመሪያ ጊዜ በተደረገው በዚህ የተቃውሞ ሰልፍ ላይ የተገኘው ህዝብ በተለይ የታሰሩ የፖለቲካ፣ የሃይማኖትና ጋዜጠኛ ህሊና እስረኞች እንዲፈቱ፤ በአባይ ስም የሚደረገው ማጭበርበር እንዲቆም፣ የተማረ ቤቱ ቃሊቲ እንዳይሆን፣ የሰብአዊ መብቶች እንዲከበሩ፣ የመናገርና የመጻፍ መብት እንዲከበርና ሌሎችንም ጥያቄዎችን ማንሳታቸውን የዘ-ሐበሻ የአዲስ አበባ ዘጋቢዎች ገልጸዋል።
“በሃገራችን ሰላም አጣን”
“የኑሮ ውድነት ያጎበጠው ትከሻችን እረፍት ይሻል”
“የፖለቲካና የህሊና እስረኞች ይፈቱ”
“መማር ያስከብራል ሃገርን ያኮራል”
“ነፃነት የሌላት ሃገር ጨለማ ናት”
“መማር ያሳስራል፤ ቃሊቲ ያስገባል”
“የመንግስትን በኃይማኖት ጣልቃ ገብነት እናወግዛለን”
“ኮሚቲዎቻችንን ይፈቱ”
“ልማት እያሉ ሙስና ሰሩ”
“ፍትህ! ፍትህ! ፍትህ!”
“መብትን መጠየቅ ወንጀል አይደለም፤ መብትን መጠየቅ ስልጣን አይደለም”
“ዜጎችን ማፈናቀል የዘር ማጥፋት ወንጀል ነው”
“መብትን መጠየቅ አሸባሪነት አይደለም”
“ኢቲቪ ሌባ፤ ውሸት ሰለቸኝ”
“የሙስሊሙ ማህበረሰብ ጥያቄዎች ይመለሱ”
“ህገመንግስቱን የሚጻረሩ ህጎችን እንቃወማለን”
የሚሉና ሌሎችንም መፈክሮችን ያሰሙት ሰላማዊ ሰልፈኞቹ መንግስት በአስቸኳይ ድምጻቸውን እንዲሰማም ጠይቀዋል።
(ተጨማሪ መረጃዎችን ይዘን እስከምንመለስ ከአዲስ አበባ ከተደረገው ሰልፍ በኋላ እዚያው አዲስ አበባ የነበረው ገጣሚ ፋሲል ተካልኝ ስለስልፉ በግጥም የተሰማውን ጽፏል። እናካፍላችሁ)

ተጨማሪ ያንብቡ:  የጠቅላይ ሚኒስትሩ ቅንጡ ፕሮጀክቶችና የኢትዮጵያ የከፋ ድህነት

_ጥቂቶች ስንት ነን?!?___
“ጥቂቶች” አትበሉን..እናንት ብዙኃኑ!
የጊዜ ጉዳይ ነው..እልፍ አዕላፍ መሆኑ::
እናንት ብዙኃኑ!..
ተዉ አታሳንሱን..ተዉ አታንኩዋስሱን..
እናንተም ጥቂቶች..
እንደነበራችሁ.. እኛን አታስታውሱን::
ወር ተራው ደርሷችሁ..
አውነታው ጠፍቷችሁ..
…ዛሬ ስታገሉን
ጥቂት እንኩዋ’ አታፍሩም?!?
…”ጥቂቶች” ስትሉን
እናንተ ብዙኃን..”ጥቂቶች” አትበሉን
ሐቁን ስነግራችሁ..ሐቁን ተቀበሉን::
“…ተባዝቶ..ተባዝቶ..
ዛሬ ምድርን ሞልቶ..
ሰባት ቢሊዮናት..ቁጥሩ የደረሰው
ከጥቂትም..ጥቂት..ከጥቂት እሚያንሰው
የኦሪቱም አዳም..ነበረ’ኮ አንድ ሰው::…”
እናንት ብዙኃኑ!..
ኧረ ለመሆኑ…
እማንታያችሁ..በቁጥራችን ገነን
“ጥቂቶች” ስትሉን..”ጥቂቶች ስንት ነን?!?”
* * *
___ፋሲል ተካልኝ አደሬ___
___________________________________________________
በሌላ በኩል የቀድሞ የኢትኦጵ እና የአዲስ ዜና ዋና አዘጋጅ ወሰን ሰገድ ገ/ኪዳን በፌስቡክ ገጹ ስለዛሬው ሰልፍ የሚከተለውን ጽፏል።
“አሂምሳ!”
ዝምታው ተሰበረ!!!
ሠማያዊ ፓርቲ የጠራው ሰላማዊ ሰልፍ ሰልፈኞች አደባባይ ወጥተው ስለ ፍትህ ዘመሩ፡፡ እጅግ አስደናቂ፣ እጅግ አስገራሚ፣ ፍፁም ሠላማዊ የሆነ ሰልፍ…!!
በግሌ በሠላማዊ ትግል ላይ ያለኝ ጠንካራ ዕምነት የሚያመረቃ ፍሬ ያፈራበት፣ እጅግ በጣም የተደሰትኩበት፣ በተለይ በወጣተ ትውልድ መነቃቃት የኮራሁበት ቀን ነው፡- ዛሬ፡፡
እንደዛሬ “የፎቶ ካሜራ በኖረኝ” ብዬ የተመኘሁበት ቀን የለም፡፡ እንዲያም ሆኖ በሞባይል ካሜራ አስደናቂውን ሰላማዊ ሰልፍ በምስል ላሳያችሁ ሞክሬአለሁ፡፡ እውነት እውነት እጅግ በጣም የሚያኮራ ቀን ነበር ዛሬ፡፡ የሠላማዊ ትግል ትንሳኤ ነበር ማለት ይቻላል፡፡
ጋንዲ ለሚታወቁበት “የጨው አብዮት” ለሠልፍ የወጡት በ20 ሺ የሚቆጠሩ ሰዎች ነበሩ፡፡ ዋናው ግብ ቦታ የደረሱት ግን በቁጥር 193 ሰዎች ነበሩ፡- ታሪክ እንደዲነግረን፡፡

“አሂምሳ” እንዲሉ ማህተመ ጋንዲ ጠንካራ ወኔ መንፈስ የተላበሱ ሠልፈኞች በቸርችል ጎዳና ላይ በእምነት ፈሰሱ፡፡…ያኮራሉ! ኮርቻለሁ!

5 Comments

  1. Ethiopian flag was nt in ze heart of the blue party b/se blue party is mission of Egyptian.

  2. What does this show you people? Don’t you think that the time for the old fashioned politicians has expired? They must stay aside!

    NEW GENERATION=FRESH POLITICAL CONSIOUSNESS=NEW ETHIOPIA!

    Oldies please stay away from this party. Thanks!

  3. people this is the right time to raise up our past flag to see Ethiopia strong,united and stand together for future Ethiopia as before. But this is not time to stand against political parties which are trying to unite people of Ethiopia to express thier buried feelings. However getting in dillema is not bad!!!

  4. medre weyane tenchacha !!! kkkkkkkkkkkkkkkkkkkkkkkk

    viva semayaweeeeee !!!

    bertu Enashenfalen !,, elelelelelelele !!!!!!!!

Comments are closed.

Share