Sport: ሞዬስ እና ሩኒ ይስማሙ ይሆን? – የማንችስተር ዩናይትድ ውስጣዊ ጉዳይ

ለሊቨርፑሉ አንጋፋ ተከላካይ ጄሚ ካራገር ክብር ከዛሬ ሶስት አመት በፊት የኤቨርተን ምርጥ 11 እና ሊቨርፑል ተጫውተው ነበር፡፡ ለዚያ ጨዋታ የኤቨርተንን ማሊያ የለበሱት ምርጦች ስብስብ ቡድን የሚሰለጥነው በዴቪድ ሞዬስ ነው፡፡ አሰልጣኙ ከዌይን ሩኒ ጥያቄ ቀረበላቸው፡፡ የማንቸስተር ዩናይትዱ አጥቂ በኤቨርተን ደጋፊነት ያደገ የሊቨርፑል ከተማ ተወላጅ መሆኑ ምስጢር አይደለም፡፡ ስለዚህ በዚህ አጋጣሚ የኤቨርተንን ማልያ በድጋሚ ይለብስ ዘንድ እድሉን እንዲሰጡት ሞዬስን ይወተውታቸው ያዘ፡፡ ያሰበው ግን አልተሳካም፡፡ በተጨዋቹና በፕሪሚየር ሊጉ ላይ እንዲጫወት የመጀመሪያውን በር በከፈቱለት አሰልጣኝ መካከል የነበረው መልካም ግንኙነት ይበልጥ ንፋስ የገባው ግን በአዲሱ የፈረንጀች ሚሊኒየም አጋማሽ ላይ በታተመው የሩኒ ግለ ታሪክ (Autobiography) መጽሐፍ ነው፡፡ ‹‹My story so far›› የተሰኘው መፅሐፍ የስነ ፅሑፍ ልምድ ባለው ፀሐፊ እርዳታ የተፃፈ የሩኒ ግለ ታሪክ ነው፡፡ ዌይን የመጽሐፉ በርካታ ገፆች ላይ ስለሞዬስ ተርኳል፡፡ በአሰልጣኙ ላይ ያለውን አሉታዊ አመለካከት የገለፀበት መንገድ ግን ሁለቱን ሰዎች እስከ ችሎት ፊት አድርሷቸዋል፡፡

‹‹ሞዬስን ለመሸሽ ስል (ኤቨርተንን ለቅቄ) ወደየትም ክለብ ለመዛወር ፍቃደኛ ነበርኩ›› ይላል ሩኒ በመጽሐፉ፡፡ ‹‹ኒውካስል ጥያቄ አቅርቦልኝ ቢሆን ኖሮ ወደዚያው ማምራቴ አይቀርም ነበር፡፡ ለእኔ (ሞዬስ) ሌሎችን ሰዎች በመጥፎ አቀራረብ በራሱ ቁጥጥር ስር ለማስገባት የሚሻ ሰው ነው፡፡ እርሱን ለማስቆጣት ወይም ለተናገረው ነገር ምላሽ  ለመስጠት አስቤ አላውቅም ነበር፡፡ እኔ በማደርጋቸው ነገሮች ሁሉ ደስተኛ ያልሆነና የሚበሳጭብኝ ሰው ቢኖር ሞዬስ ብቻ ነው›› ሲል ይቀጥላል፡፡

ሩኒ ይህንን በማድረጉ ብዙዎች ትችት እንጂ ሙገሳን አላጎናፀፉትም፡፡ ይልቅስ መፅሐፉ ከቁም ነገር ይልቅ አንድ ያልበሰለ ታዳጊ በሚሰነዝረው አርቲቡርቲ የተሞላ ነው በሚል ተወርፏል፡፡ መፅሐፉ ለንባብ ሲበቃ ሩኒ ገና የ20 ዓመት ወጣት ነበር፡፡ ‹‹ለሁሉም ነገር የሚደርስበት ሆኖ ሳለ ቸኩሏል›› በሚል ነገሩ የልጅ ነገር… መሆኑን ተቺዎቹ ጠቁመዋል፡፡

ሞዬስ ግን በዚህ አልተከፉም፡፡ ስኮትላንዳዊው በእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ ያሰለጠኑትን ተጫዋች በመክሰስ የመጀመሪያ ያደረጋቸውን እርምጃ የወሰዱት በመፅሐፉ ሌላ ገፅ ላይ የሰፈረው ጉዳይ ነው፡፡ አሰልጣኙ የግል ህይወቴን ምስጢሮች የሚገልፁ መረጃዎችን ‹ሊቨርፑል ኤኮ› ለተባለው የከተማዋ ጋዜጣ ሰጥተዋል ሲል ሩኒ ወቅሷቸዋል፡፡ ሞዬስም ንቀው ሊተውት አልቻሉም፡፡ ይህ ግልፅ ስም የማጥፋት ወንጀል በመሆኑ ጉዳዩን ወደ ፍርድ ቤት ይዘውት ሄዱ፡፡ የሞዬስን ክስ የተመለከተው ፍርድ ቤት አሰልጣኙ በተጨዋቹ ያለአግባብ መወንጀላቸውን ተመልክቶ ፈርዶላቸዋል፡፡ እንደአንዳንድ ዘገባዎች ሞዬስ በስም ማጥፋት ካሳ 500 ሺ ፓውንድ ካሳ ተከፍሏቸዋል፡፡ ገንዘቡንም ለኤቨርተን የቀድሞ ተጨዋቾች ፋውንዴሽን አበርክተውታል፡፡

ዕድሜው እየጨመረ ሲሄድ ጥፋቱ የተሰማው ሩኒ በ2010 ለሞዬስ ደውሎ ይቅርታ ጠይቋቸዋል፡፡ በመጽሐፉ ላይ እርሳቸውን በተመለከተ ያሰፈረው ተገቢ አለመሆኑንና መሳሳቱን አምኖ ይቅር እንዲሉት ተማፅኗቸዋል፡፡ ሞዬስም ይቅርታውን ተቀብለው ከኤቨርተን ጋር መስራትን ቀጠሉ፡፡

ሞዬስ ቆይቶም ቢሆን ሩኒ ይቅርታውን መጠየቁ ተጫዋቹ ዕድሜ ሲጨምር እየበሰለ ለመምጣቱ ማስረጃ መሆኑን ገልፀው እርሳቸውም ይቅር እንዳሉት በሰከነ አንደበት ለሚዲያው ነግረዋል፡፡ ሩኒ በችሎታ እያደገ ሲሄድ መመልከት በጣም እንደሚያስደስታቸው ሞዬስ በወቅቱ ተናግረዋል፡፡

በመገናኛ ብዙሃን ፊት የሚታየውን መከባበር ወደጎን ብንተወው በእውነተኛው የእግርኳስ ህይወታቸው ሞዬስ በኤቨርተን የ16 ዓመቱን ‹‹ጎረምሳ›› መቆጣጠር አስቸግሯቸው ነበር፡፡ ሩኒ ነውጠኛ ሆኖባቸው ሳለ ማንቸስተር ዩናይትድ የከፍተኛ ገንዘብ የዝውውር ጥያቄ አቀረበላቸው፡፡ አጥቂውም ወደ ኦልድትራፎርድ አመራ፡፡ በአዲሱ ክለቡ ውስጥ ግን ቆፍጣና የዲሲፕሊን ሰው

ተጨማሪ ያንብቡ:  ዜጎችን ከስፍራቸው ማፈናቀል አንዱ የኢህአዲግ ማናለብኝ ህገዎጥ ተግባር ነው -(ከሰሜን አሜሪካ አንድነት ድጋፍ ማህበራት የተሰጠ መግለጫ)

ከሆኑት ሰር አሌክስ ፈርጉሰን ጋር ተገናኘ፡፡ የተጨዋቹን እምቅ ብቃት የተረዱት ፈርጊ ሩኒን ፀጥ ለጥ ብሎ እንዲገዛና ለውጤታማነቱ ብቻ እንዲተጋ አደረጉት፡፡

ሰር አሌክስም ቢሆኑ በሩኒ ባህሪይ አልተቸገሩም ብሎ መናገር አይቻልም፡፡ በየወቅቱ አዛውንቱን የሚያስከፋ ባህሪያት እንደነበሩት አይካድም፡፡ ሞዬስም ይህንን ያምናሉ፡፡ በ2010 ላይ የታየው ግን የፈርጉሰንን ትዕግስት እጅጉን የተፈታተነ ነበር፡፡ ወቅቱ ሩኒ ማንቸስተር ዩናይትድን እንደሚለቅ ያስታወቀበት ወቅት ነበር፡፡ ዩናይትድን ቡድኑን በታላላቅ ተጨዋቾች ለማጠናከርና ዋንጫዎችን ለማሸነፍ ያለው ተነሳሽነት ደካማ መሆኑን የገለፀው ሩኒ ይህንን ፍላጎቱን ለማሟላት ሲል ወደ ሌሎች ክለቦች ለመሻገር ማሰቡን ገለፀ፡፡ ድርጊቱ ዲሲፕሊን የአሰልጣኝነታቸው አብይ መሰረት የሆነውን የሰር አሌክስን ቆሽት አሳረረ፡፡ ደጋፊውንም አስቆጣ፡፡ ብዙ ሳይቆይ የኮንትራት ማራዘሚያና ከፍተኛ የደመወዝ ጭማሪ በማግኘቱ ሩኒ ‹‹የእግር ኳስ ህይወቴን በዩናይትድ ማጠናቀቅ እፈልጋለሁ›› የሚል መግለጫ ሰጠ፡፡ ሩኒ በደሉን ቢረሳም፣ ሰር አሌክስ እና ደጋፊዎች ቂም ቋጥረው ቀሩ፡፡

እነዚህ እውነታዎች ባሉበት የ71 ዓመቱ አሰልጣኝ የጡረታ ጊዜያቸው መድረሱን በድንገት ተናገሩ፡፡ ከዚያም ሩኒ የቀድሞ አሰልጣኙና ከሳሹ ሞዬስ ቀጣዩ የማንቸስተር ዩናይትድ አሰልጣኝ እንደሚሆኑ ተገለፀ፡፡

የ50 ዓመቱ አሰልጣኝ በአንድ ወቅት ሩኒን እስከመክሰስ ቢደርሱም ቅሉ በመኖሪያ ቤታቸው በሚገኘው የግል ቢሯቸው ግድግዳ ላይ እስካሁንም ድረስ በኤቨርተን ማሊያ በሊድስ እና በአርሰናል ላይ የማሸነፊያ ጎሎችን ካስቆጠረ በኋላ በደስታ የሚዘለውን ሩኒ ፎቶግራፍ እንደሰቀሉ ይገኛሉ፡፡ ሞዬስ የእንግሊዝ ብሔራዊ ቡድን ቁልፍ እስከመሆን የደረሰውን ተጨዋች በማፍራታቸው ኩራት ይሰማቸዋል፡፡

ሞዬስ በሩኒ መቆየት እንደሚጠቀሙ አይጠረጠርም፡፡ አሁን ጥያቄው በሁለቱ መካከል ከነበረውና እልባት ካገኘው ልዩነት ይልቅ ተጨዋቹ በኦልድ ትራፎርድ ለመቀጠል ደስተኛ አለመሆኑ ይበልጥ ወደ መውጫው በር የሚገፋው ይመስላል፡፡ የሞዬስ ሹመት ወሬ መደመጥ ሳይጀምር ሩኒ ወደሰር አሌክስ ቢሮ ሄዶ በዩናይትድ ደስተኛ ያልሆነባቸው ምክንያቶች መኖራቸውንና የተጨዋችነት ህይወቱን በሌላ ክለብ መቀጠሉ የተሻለ መሆኑን እንደሚያምንበት ነግሯቸዋል፡፡ አሰልጣኙም ወደ ሌላ ክለብ የመዛወሩ ነገር የሚወሰነው በክለቡ ፍላጎት እንጂ በእርሱ ውሳኔ እንዳልሆነ አስረድተውታል፡፡ ሩኒ በመጭውም የውድድር ዘመን የማንቸስተር ዩናይትድ ተጨዋች ሆኖ እንዲቀጥል ለመገናኛ ብዙሃን ከተናገሩ ሰነባብተዋል፡፡

የእንግሊዙ ሻምፒዮን ሩኒን እንደማይረባ ዕቃ የሚጥል ሞኝ አይደለም፡፡ 197 ጎሎችን ያስቆጠረውና በምንጊዜም የክለቡ ታሪካዊ ጎል አስቆጣሪዎች ተርታ አራተኛ ደረጃ ላይ የተቀመጠው፣ ዘንድሮም 31 ጊዜያት በቋሚነት እንዲሁም ሰባት ጊዜ በተጠባባቂነት ተሰልፎ 16 ጎሎችን ያስቆጠረው አጥቂ ጠቃሚ መሆኑን ያውቃል፡፡ ፈርጉሰን ያመፀባቸውን ተጨዋች የማሰናበት ታሪክ ቢኖራቸውም በሩኒ ላይ ጨክነው አላደረጉትም፡፡ ዘንድሮ የሩኒ ጠቃሚነት በአንፃራዊነት ቀደም ካሉት ዓመታት መቀነሱ አይካድም፡፡ ዘንድሮ ሩኒ በሁሉም ውድድሮች 36 ጨዋታዎች ላይ ብቻ ተሳትፏል፡፡ በዘጠኝ ዓመቱ የኦልድትራፎርድ ቆይታው ዝቅተኛ ጨዋታ የተጫወተበት የውድድር ዘመን መሆኑን ነው፡፡ ከፕሪሚየር ሊጉ ስድስት ሃያላን ጋር በተደረጉት ጨዋታዎች ማስቆጠር የቻለው ሁለት ጎሎችን ብቻ ነው፡፡ አምስት ጊዜ ቢጫ ካርድ ተመልክቷል፡፡ ዩናይትድ ባደረጋቸው ስድስት የቻምፒየንስ ሊግ ግጥሚያዎች አንድ ጎል ብቻ (በብራጋ ላይ) ቀንቶታል፡፡ አምና በ44 ጨዋታዎች 34 ጎሎችን ላገባ ተጨዋች ይህ የሚያመረቃ ነው ሊባል አይችልም፡፡ ከጎን ርቆ የተጫወተባቸው ጨዋታዎች በርካታ መሆናቸው በምክንያትነት ቢቀርብ እንኳን የሩኒ የአማካይነት ተፅዕኖ እጅግ የፈዘዘ ነበር፡፡

ተጨማሪ ያንብቡ:  በአማራ ክልል በሚደረገዉ ጦርነት ምክንያት ከ6 ሚሊዮን በላይ ህዝብ ለርሀብ ተጋልጠዋል

የልቀቁኝ ጥያቄውን ካቀረበበት ከኦክቶበር 2010 በኋላ በአሰልጣኙ እና በተጨዋቹ መካከል ያለው ግንኙነት ከመጋረጃ ጀርባ ሻክሯል፡፡ ፈርጉሰንም የቡድኑ ቁልፍ ተጨዋች ሆኖ እንዲቀጥል ፍላጎት ያላቸው አይመስሉም ነበር፡፡ ዘንድሮም የሩኒ ቦታ በሺንጂካጋዋ ብቃት አደጋ እንደተደነቀረበት ለመገናኛ ብዙሃን ሲናገሩ ይደመጡ ነበር፡፡ በመጪው የውድድር ዘመንም የጃፓኑ ኢንተርናሽናል ከዚህም በላይ ብቃቱን እንደሚያጎለብት ሰር አሌክስ ተንብየውለታል፡፡ በሌላ አነጋገር ሩኒ በ2013/14 ሊጫወትበት በሚመርጠው ቦታ ላይ የመሰለፉ ነገር አጠራጣሪ ነው፡፡

ሰር አሌክስን ቅር የሚያሰኛቸው ሌላው አብይ ርዕስ የዘንድሮው የተጫዋቹ አካላዊ ብቃት ደረጃ ነው፡፡ ሩኒ ራሱ ከቅድመ ውድድር ዘመን እረፍት በኋላ ወደ ቡድኑ ሲመለስ ክብደት መጨመሩን አምኗል፡፡ ፈርጊ የሰውነቱን ክብደት እንዲቆጣጠር አጥብቀው አዘውት ነበር፡፡ እርሳቸው ወደሚፈልጉት ደረጃ ዝቅ ሊያደርገው ግን አልቻለም፡፡ ዴቪድ ሞዬስም ይህንን የሩኒ ችግር የተገነዘቡ የመጀመሪያው አሰልጣኝ ናቸው፡፡ ልጁ በኤቨርተን ሳለ ከምሽቱ 3፡00 ሰዓት በኋላ ሳይቀር የመብላት መጥፎ ልምድ እንደነበረበትና ለቋሊማ (sausage) ያለው ፍቅር የሰውነት ክብደቱን ለመቆጣጠር የማያስችል መሆኑን ያውቁት ነበር፡፡ ሞዬስ የሩኒ የጉዲሰን ፓርክ ችግር ወደ ኦልድ ትራፎርድ ተከትሏቸው ሳይመጣ አልቀረም፡፡ ሞዬስ በአዲሱ ስራቸው ከተጨዋቹም ጋር በሚኖራቸው ግንኙነት ለሩኒ ችግር እልባት የማግኘት የቤት ስራ ይጠብቃቸዋል የተባለው ለዚህ ነው፡፡

የአካላዊ ብቃቱን ጉዳይ ደጋግመው በምክንያትነት ሲያነሱ የተደመጡት ፈርጉሰን ሮቢን ቫን ፔርሲን የመሰለ ከፍተኛ ጎል አስቆጣሪ በያዘው የዘንድሮ ቡድናቸው ውስጥ በተለያዩ ቦታዎች እያሰለፉት ታይተዋል፡፡ በጥልቀት ወደኋላ በተሳበ የመሀል አማካይነት ቦታ ሳይቀር እንዲጫወት መደረጉ ሩኒን አስከፍቶታል፡፡ በኦልድ ትራፎርድ የቻምፒየንስ ሊግ ሩብ ፍፃሜ ከሪያል ማድሪድ ጋር ሲጫወቱ ተጠባባቂ በማድረግ በሩኒ ሁኔታ ደስተኛ አለመሆናቸውን ለዓለም አሳይተዋል፡፡

ከሁለት ዓመት ተኩል በፊት ‹‹ልቀቁኝ ወደ ፈለግኩበት ልዛወር›› በሚለው ጥያቄ እንደ ፈርጉሰን ሁሉ የተከፉት የዩናይትድ ደጋፊዎች ቡድናቸው ሩኒን ይዞ እንዲቀጥል አይፈልጉም መባሉ የተጨዋቹን መውጫ የሚያፋጥነው ይመስላል፡፡ ዴይሊ ኤክስፕረስ የተባለው ጋዜጣ ባሳለፍነው ሳምንት እንደዘገበው Red cafe.net በተሰኘው የዩናይትድ ደጋፊዎች የኢንተርኔት መድረክ ላይ ይኸው ፍላጎታቸው በግልፅ ተስተውሏል፡፡ በመድረኩ ላይ የሩኒ ጉዳይ 1.1 ሚሊዮን አንባቢ ያገኘ ሲሆን 10 ሺ ገደማ አስተያየቶች ሰፍረውበታል፡፡ ከተጠቀሱት አስተያየቶች መካከል ሚዛን የሚደፉት ደጋፊዎች በተጨዋቹ ሁኔታ ደስተኛ አለመሆናቸውንና አዲሱ አሰልጣኝም እንዲሸጡት እንደሚፈልጉ የሚገልፁት ናቸው፡፡ ‹‹ዩናይትድ ሩኒን ሊያሰናብት ይገባዋል፡፡ ሩኒን የመሰለ እንደ ልቤ ካልሆንኩ የሚል ተጨዋች አያስፈልገንም፡፡ ከዚህ በኋላም እጅግ ተፈላጊው ተጨዋቻችን አይደለም›› ሲል አንደኛው ደጋፊ ፅፏል፡፡ ሌላኛውም ‹‹ሩኒ እንዲለቅ እመኛለሁ፡፡ በቃ ትክክለኛው ውሳኔ ይኸው ይመስለኛል›› ብሏል፡፡ ‹‹ቫን ፔርሲና ካጋዋን የመሳሰሉ ምርጥ ተጨዋቾች አሉን፡፡ ቢለቅ እርሱ እንጂ፣ እኛ አንፀፀትም፡፡ ከዚህ በኋላ የተለየ ተጨዋች አይደለም›› የሚለው ደግሞ ሌላኛው አስተያየት ሰጪ ነው፡፡ ሩኒ ዘንድሮ ከተጫወተባቸው ጨዋታዎች በግማሽ ያህሉ ለደጋፊዎች ሳያጨበጭብ መውጣቱም እንደ ቂም ተይዞበታል፡፡

ተጨማሪ ያንብቡ:  የ AESA ONE  ፕሬዚዳንት ራሳቸውን ከማህበሩ አገለሉ

‹‹የተለየ ተጨዋች›› ለማምጣት የክለቡ ጥረት መቀጠሉ ደግሞ የሩኒን ተፈላጊነት ይበልጥ ሊቀንሰው ይችላል፡፡ ከሁለት ሳምንት በፊት ቺፍ ኤግዜኪዩቲቭ ዴቪድ ዢል ‹‹ሱፐር ኤጀንት›› በሚል ቅጽል የሚታወቁትን ሆርጌ ሜንዴዝን ለማነጋገር ወደ ማድሪድ ተጉዘው ነበር፡፡ የጉዟቸው ዓላማ በ2009 በዓለም የተጫዋቾች ዝውውር ሪከርድ ዋጋ (80 ሚሊዮን ፓውንድ)  የሸጡትን ክሪስቲያኖ ሮናልዶን መልሶ ማስፈረም ነው፡፡ የሪያል ማድሪዱ ኮከብ ወደ ማንቸስተር ዩናይትድ የመመለስ ፍላጎት እንዳለው በስፋት ሲዘገብ ቆይቷል፡፡ ፈርጉሰንም የሂሳቡ ጉዳይ ውድነት ካላገዳቸው በስተቀር ፖርቹጋላዊውን ተመልሶ ለቀድሞ ክለቡ እንዲጫወት የማድረግ ፍላጎት ለመኖሩ ጥቆማ ሰጥተዋል፡፡ የአሰልጣኙን የጡረታ ስንብት ዜና ተከትሎ በትዊተር ገፁ ላይ ‹‹ስለ ሁሉ ነገር አመሰግናለሁ አለቃዬ›› የሚል አስተያየቱን ያሰፈረው ሮናልዶ ከተሰናባቹ አሰልጣኝ ጋር ያለው ግንኙነት አባታዊና እጅግ በጣም ጥሩ ነው፡፡ ፈርጉሰን ቢለቁም ሮናልዶ በዩናይትድ ማልያ በድጋሚ ለመጫወት ያለው ፍላጎት ይቀዘቅዛል ተብሎ አይታሰብም፡፡ ፈርጉሰን በዕለት ተዕለት ስራ በማይጠምዳቸው የክብር ባለስልጣንነት ቦታ ስለሚያገኙ ለተጨዋቹ መመለስም የጎላ አስተዋፅኦ ሊያበረክቱ ይችላሉ፡፡

የሮናልዶ ‹‹መመለስ›› ሩኒ በክለቡ እንዲቆይ ሊያማልለው ይችላል የሚል ግምት አለ፡፡ ለሪያል ማድሪድ 200ኛ ጎሉን ያስቆጠረው ክሪስቲያኖ ከሩኒ ጋር የፈጠሩት የሜዳ ላይ ቅንጅት ዩናይትድን ለበርካታ ክብሮች እንዳበቃው አይዘነጋም፡፡ የሮናልዶ መምጣት ግን ዘንድሮ በአንድ ቦታ ባልረጋ ሚና በአጥቂ፣ በአማካይ፣ በአጥቂ አማካይና በክንፍ ተጨዋችነት የተጫወተውን ሩኒ ከቡድኑ ቁልፍ ባለተፅዕኖነት ምን ያህል ዝቅ እንደሚያደርገው ገምቱ፡፡

ዩናይትድ ሩኒን እንደማይሸጥ ያለውን አቋም አልቀየረም፡፡ ከሰሞኑ እንኳ የክለቡ ቃል አቀባይ ‹‹ሩኒ አይሸጥም›› የሚል አስተያየት በመስጠት አቋማቸውን አጠናክረዋል፡፡ የተጨዋቹን የመልቀቅ ፍላጎት ተከትለው ለግዢ በኦልድ ትራፎርድ አናት ላይ የሚሽከረከሩ ‹‹ጭልፊቶች›› በርካቶች ናቸው፡፡ ቼልሲ፣ ባየር ሙኒክና ፓሪ-ሰን-ዠርመ ከፈላጊዎቹ ተርታ ተቀምጠዋል፡፡ ሩኒ ከተሸጠ ዩናይትድ ቢያንስ 25 ሚሊዮን ፓውንድ ያገኛል ተብሎ ተገምቷል፡፡ ገንዘቡንም እንደ ሮበርት ሊቫንዶቭስኪ ወይም ራዳሜል ፋልካኦን የመሰሉ አጥቂዎችን ለማስፈረም የግዢ አቅሙን ያሳድግለታል፡፡ መጪዎቹ ወራትም ለሩኒ ጥያቄ ትክክለኛውን መልስ ይሰጡናል፡፡ መልሱ ‹‹እሺ›› ከሆነ ዩናይትድ ለፕሪሚየር ሊጉ ተፎካካሪዎች ይሸጠዋል ብሎ ማሰብ ስለማይቻል የሩኒ መጨረሻ ከፕሪሚየር ሊጉ ውጪ ሊሆን ይችላል፡፡ የጥያቄው ምላሽ ‹‹እምቢ›› ከሆነ ደግሞ ዌይን ሩኒ በፕሮፌሽናል ተጨዋችነቱ የመጀመሪያ አሰልጠኙ ከሆኑት ሞዬስ ጋር ተስማምቶ ከሚደቅንባቸው ፈተና ይልቅ ሊጠናቀቅ ሁለት ዓመት ብቻ የቀረውን ኮንትራት በማራዘሙ ላይ የሚጋረጡትን ጥያቄዎች መመለሱ ከባድ ሊሆንባቸው ይችላል፡፡ ሩኒ በ2010 ያራዘመው ውል በሳምንት እስከ 250 ሺ ፓውንድ ደመወዝ የሚያስገኝለት መሆኑ በስፋት ይነገራል፡፡ (ክለቡ ትክክለኛውን የደመወዝ መጠን በይፋ ባይገልፅም) 30 ዓመት ሊሞላው ገና ሶስት ዓመት የሚቀረውን ኢንተርናሽናል ተጨዋች ኮንትራት ማራዘም ደግሞ የደመወዝ ጭማሪን ያስከትላል፡፡ የሞዬስ ማንቸስተር ዩናይትድ ብቃቱ ላሽቆለቆለው ተጨዋች ከዚህ በላይ ለመክፈል ይስማማ ይሆን? ሞዬስ ምላሹን ለመስጠት በጥሞና ማሰብ ይኖርባቸዋል፡፡S

Share