ግልጽ መልእክት ለአገራችን የታሪክ ፀሃፊዎችና ፖለቲከኞች !
የታሪክ ተወቃሽነቱን በራሳችን እንጀምር !
(ክፍል 2)
በመንገሻ ሊበን
በዚህ ፅሁፍ የመጀመርያ ክፍል ላይ ፣ ባለፍ ገደም ከተፃፉ ተራ ዘለፋዎች ባሻገር ፣ የብዙ አንባቢዎችን ገንቢ ነቀፌታና አስተያየት ተቀብያለሁ ። በዚህ አጋጣሚ ለሁሉም አስተያየት ሰጭዎችና ነቀፌታ አቅራቢዎች ያለኝን ልባዊ አክብሮት እየገለፅኩ በቀጥታ ወደ ጀመርኩት ርእሰ ጉዳይ አመራለሁ ።
“ የታሪክ ተወቃሽነቱን በራሳችን እንጀምር ” በሚል ርእስ ስር በተከታታይ ክፍሎች የማቀርበው ይህ ጽሁፍ፣ በማንኛውም ወገን ላይ የተነጣጠረ ጥቃት አለመሆኑን ሁሉም አንባቢዎች እንዲገነዘቡልኝ እወዳለሁ ። የፅሁፉ ዋነኛ አላማ “በሃገር ደህንነት ስም” ወይም በሌላ ሽፋን ፣ ከህዝባችን የተደበቁና በታሪክ ፀሃፊዎቻችንና ፖለቲከኞቻችን ብእሮች እምብዛም ያልተዳሰሱ ታሪኮች ይፋ ወጥተው ትውልድ ይማርባቸው ዘንድ እንዲተጉ ጉዳዩ በቀጥታ የሚመለከታቸውን አካላት ማሳስብና ማስገንዘብ ነው።
እርግጥ ነው በቀዳሚው ፅሁፌ መግቢያ ላይ እንዳልኩት ካሁን በፊት ከተፃፉልንና ካነበብናቸው “ወገንተኛ” አልያም “የተዛነፉ” ታሪክ ቀመስ መጣጥፎች አኳያ…በዚህ ርዕስ ስር በንዑስ አቅም የሚቀርቡ ጭብጦች ፣ እንደ እሬት የሚመረን በርካታ ሰዎች መኖራችን የሚጠበቅ ነገር ነው። ይሁን እንጅ የራሳችን ታሪክ የራሳችን ነውና ወደድንም ጠላንም ልንቀበለው የግድ ይለናል !!
ከተወሰኑ የተቃዋሚ ፓርቲዎች የአመራር አባላት ጋር በተለያየ አጋጣሚ አብሬ የሰራሁ ሰው እንደመሆኔ መጠን ፣ አብዛኛዎቹ የተቃዋሚ ፓርቲዎች የአመራር አባላት ፣ በኢትዮጵያ አጠቃላይ ታሪክ ላይ ፣ በተለይም ደግሞ በኤርትራ ጉዳይ ላይ ያላቸውን አቋም በቅርበት የማወቅ እድሉን አግኝቻለሁ ፣፣ በእርግጥ አንዳንድ መሪዎቻችን ለአገራችን ካላቸው ጥልቅ ፍቅር አኳያ፣ የኤርትራ ከኢትዮጵያ መገንጠል በእጅጉ እንደሚያንገበግባቸው ጠንቅቄ ባውቅም …አብዛኛዎቹ መሪዎቻችን ግን በተቃራኒው ፣ የኤርትራን ጉዳይ በተለይም ደግሞ የአሰብን ጉዳይ ከአምባገነኑ የወያኔ መንግስት ጋር ለሚያደርጉት ትንቅንቅ ፣ የህዝባችንን ቀልብ ለመሳብ ሲሉ ብቻ “እንደመጫዎቻ ካርታነት” እንደሚጠቀሙበት አሳምሬ አውቃለሁ። (“አሰብ የማን ነች” በሚል ርእስ ስር ከ2 ዓመታት በፊት ታትሞ ለንባብ በበቃው የዶ/ር ያዕቆብ ኃይለማርያም መፅሃፍ ላይ የቀረቡትን የተዛነፉና የተንጋደዱ ታሪኮችን ልብ ይሏል ። በዚሁ መፃህፍ ላይ የአሰብን ኢትዮጵያዊነት ለማሳመን እንደማስረጃነት የቀረበው የደርግ የራስ–ገዝ ሽንሸና የዶክተሩን “ብስለት–አልባ ፖለቲከኝነት” ወይም “አውቆ አጥፊነት” ያሳበቀ ይመስለኛል) ።ለማንኛውም በዚህ ጉዳይ ላይ ለወደፊቱ ሰፋ ያሉና በማስረጃ ላይ የተደገፉ ፅሁፎችን ለማቅረብ እሞክራለሁ ።
በመሰረቱ እኔ ለኤርትራና ህዝቧ ጥብቅና የመቆም ሃሳብም ምኞትም የለኝም ። ይልቁንም እንደ አንድ አገሩን የሚወድ ኢትዮጵያዊ መጠን የኤርትራዊያን ከኢትዮጵያ መገንጠል በእጅጉ ያንገበግበኛል ። የኢትዮጵያና የኤርትራ ህዝቦች የመጨረሻ እድል በእንዲህ አይነቱ አሳዛኝ ድምዳሜ መቋጨቱም እጅጉን ያሳዝነኛል ።
ነገር ግን ፣ የኤርትራን ህዝብ ከኢትዮጵያ ለመገንጠል ያበቃው ዋነኛ ምክንያት ምንድን ነው ? በእውን ይህ ህዝብ ከኢትዮጵያ ለመገንጠል የወሰነው ፣ አብዛኛዎቻችን እንደምንለው “ ሻእቢያና ወያኔ ባቀነባበሩት ሴራ ብቻ ነው ” ? ወይስ ከኛ የተሰወረ አልያም የተዛነፈ ሌላ ታሪክ አለ…? የሚለው አንኳር ነጥብ ፣ ከትላንቱ የሃቀኛ ታሪካችን ፍፃሜ አኳያ መቃኘት አለበት የሚል የፀና እምነት አለኝ ። ምክንያቱም የዚህ ታሪክ ይፋ መውጣት ፣ ለኢትዮጵያችን የወደፊት ደህንነትና አህዳዊነት የማይናቅ አስተዋፅኦ ይኖረዋልና !! ።
ትላንትና ከትላንት ወዲያ ፣ ኤርትራን ጨምሮ በተለያዩ አገራዊ ጉዳዮች ላይ የተከተልነው አቋም ከእውነተኛ ፍፃሜው በታቃረነ መልኩ እንደተሸፋፈነ አልያም እንደተዛነፈ ይቀጥል ካልን ግን፣ ነገና ከነገ ወድያ የኢትዮጵያን አንድነተት ለሚፈታተኑ ከፍተኛ አደጋዎች ራስን ማጋለጥ ከመሆኑም ባሻገር የወደፊቱ ትውልድ ታሪክም እንዳሳለፍናቸው አሰቃቂ ታሪኮች ሁሉ የጦርነትና የእልቂት እንዲሆን መፍረድ ማለት ነው ። ስለዚህ “ያለፈው ይበቃል ! እውነተኛው ታሪካችን ሳይዛነፍና ወደ የትኛውም ወገን ሳያጋድል ይነገረን ፤ ይፃፍልን ” የምንልበት ወቅት አሁን መሆን አለበት ።
አሁንም ሆነ ወደፊት ደጋግሜ ለመግለፅ የምፈልገው ነገር ቢኖር፣ የታሪክ ድርሳን ማለት አኩሪ ፍፃሜዎች ብቻ እየተመረጡ የታጨቀቡት ተራ መዝገብ አለመሆኑን ነው። ታሪክ ማለት ጣፋጭና መራራው ፤ድክመትና ጥንካሬው በአንድ ላይ ተቀይጦ የሰፈረበት የትላንት እውነተኛ ፍፃሜዎች ሰነድ ነው ። ትላንትና ከትላንት ወዲያ በአያቶቻችንና ቅድመ አያቶቻችን የተፈፀሙ ታሪኮች በሙሉ የተሳሳቱ ናቸው አልያም ደግሞ ከነበሩበት ጊዜና ዘመን አንፃር ፍፃሜዎቻቸው በሙሉ የተወገዙ ናቸው የሚል አቋም የለኝም ። ምክንያቱም አንድ አስተያየት ሰጭ እንዳሉት.. “ የአያቶቻችን ስራ የሚመዘነው በአሁኑ ዘመን ሳይሆን…. እነርሱ በነበሩበት ዘመን ነውና ” ። ይሁን እንጅ በእነርሱ የተፈፀመው የትላንቱ ታሪክ ለኛና ለልጅ ልጆቻችን ትምህርት ይሆነን ዘንድ ሳይዛነፍና ሳይንጋደድ መቅረብ አለበት የሚለው አቋሜ መቼም ቢሆን የሚቀየር አይሆንም ።
በየትኛውም ዘመን የነበሩ መሪዎቻችን፣ ለአገራችን ኢትዮጵያ ያበረከቱት ከፍተኛ አስተዋጽኦና ስራ መቼም ቢሆን የሚረሳ አይደለም። ከሰሯቸው ታሪኮች መካከል ደግሞ አዎንታዊ ስራዎቻቸው ይበልጥ የጎሉ መሆናቸውን ማንም ሊክደውም አይችልም። ግን ደግሞ ታሪካቸው በሙሉ አዎንታዊ ብቻ ነበር ማለት አይደለም፤ አሉታዊ ስራዎቻቸውም የታሪካቸው አካል ነውና። የአፄ ዮሃንስን አንገት ቀንጣሽነት አልያም ደግሞ የአፄ ቴድሮስን እግርና እጅ ቆራጭነት የማያምን ኢትዮጵያዊ ካለ፣ ወደ ወሎ ፤ ወደ ጎጃም አልያም ወደ ሸዋ ጎራ ይበልና ፣ ሆን ተብለው እንዲድበሰበሱ የተደረጉ ታሪኮችን ያፈላልግ ። የአፄ ምኒልክን ጡት ዘልዛይነት ለማጣራት የሚሻ ኢትዮጵያዊ ካለም …. ወደ ኦሮምያ ክልል(አርሲ) ጎራ ይበልና በየስፍራው የሚገኙ እድሜ ጠገብ አዛውንቶችን ይጠይቅ ። ነፍጠኛ የሚለው “የተዛነፈ” ስማችንም መነሻው ምን እንደሆነ ይመርምር ። ይህ ሁሉ ታሪክ የኛ የራሳችን ነው ። ከዚህ ያለፈ ታሪክ ነው መማር ያለብን ። ከዚህ እውነተኛ ታሪክ ስንማር ነው… በወያኔና መሰሎቹ የሚነዛውን የዘረኝነት ፕሮፓጋንዳ ያላንዳች ልዩነት በጋራ ልናመክነው የምንችለው ። ከዚህ ውጭ ግን ሁሉም በየፊናውና በየዘመኑ እየተነሳ፣ ለራሱ እንዲመቸው አድርጎ የሚነግረን የተንጋደደና የተዛነፈ ታሪክ እንዲቀጥል የምንፈቅድ ከሆነ፣ ትውልድን ያሳስታል ብቻ ሳይሆን አገራችንንም ሊያሳጣን ይችላል !!
በእኔ እምነት ዛሬ በአማራ ህዝብ ላይ እየተፈፀመ ላለው የዘር ማጥፋት ዘመቻ መሰረቱ የትላንቱ የተዛባ ታሪክ ነው ። እንደ በርካታ የትግራይ እድሜ ጠገብ አዛውንቶች አባባልና፣ እንደህዝባዊ ወያኔ አርነት ትግራይ መሪዎች እምነት፣ ለአጼ ዮሃንስ በድርቡሾች መገደልና ለትግራይ ስርወ– መንግስት ማክተም ዋነኞቹ ተጠያዎች የአማራ መሳፍንቶች ናቸው። እንደነዚህ ወገኖች እምነት ፣ የአማራ መሳፍንቶች የተለያዩ ሚስጥራዊ መረጃዎችን ለድርቡሾች አሳልፈው ባይሰጡ ኖሮ…አጼ ዮሃንስ ባልተገደሉ፣ ትግራይን ማእከል ያደረገው ስርወ መንግስትም ከትግራይ ወደ ሸዋ ባልጋዘ ነበር ። ይህ እምነታቸው ነው እንግዲህ ከ100 አመታት በኋላ በአማራ ህዝብ ላይ የበቀል ሰይፍ እንዲመዙ ያበቃቸው ።እነ አቶ ስብሃት ነጋ ሳይቀር “ እንደ አያቶቻችሁ አርቀን እንቀብራችኋለን ” እያሉ የሚፎክሩብን፣ ከልጅነታቸው ጀምረው እየተጋቱት ባደጉት በዚህ የተዛባና የተንጋደደ ታሪክ ምክንያት ነው ። የኤርትራም ጉዳይ ከዚህ ተነጥሎ የሚታይ አይደለም ። በኦሮሚያና በሶማሌ አልያም በሌሎች ክልሎች አልፎ አልፎ የሚንጸባረቀው ስሜትም የዚህ መሰሉ ታሪክ አንድ ነፀብራቅ ነው ።ይህን መሰሉን ታሪክ ነው እንግዲህ “ ታሪክ እንደፀሃፊው ነው በሚል ወገንተኛ ስሜት ሳይሆን ፣ በሃቀኛና ሚዛናዊ መልኩ ግልፅ ይሁንና ፣ ሁላችንም እንማማርበት እያልኩ ያለሁት።
ያም ሆነ ይህ በዚህ ጉዳይ ላይ ተጨማሪ ጊዜ ከማባከንና … ለመፃፍ ከተነሳሁበት ርእሰ ጉዳይ ላለማፈንገጥ ስል፣ በእንጥልጥል ወዳቆምኩት ርእሰ ጉዳይ ልመለስ ። እንቀጥል………
በኢትዮጵያና በፋሽስት ጣልያን መካከል ከተደረሱት ሶስት ስምምነቶች (1900፤1902፤1908) በፊትም ሆነ በኋላ ባሉት ረጅም ዓመታት ፣ ኤርትራን አሁን ባላት ቅርፅና ይዞታ ግዛቴ ናት የሚል ጥያቄ በኢትዮጵያ በኩል ስለመቅረቡ ምንም የተገኘ ማስረጃ የለም ። የፋሽስት ሰራዊት በአገራችን ላይ ያካሄደውን ሁለተኛውን ወረራ ተከትሎ በመንግስታቱ ማህበር ስብሰባ ላይ የተቃውሞ ንግግር ያስደመጡት ቀዳማዊ ሃይለስላሴም ቢሆኑ ፣ ታሪካዊ በተባለለት የዚያን ጊዜው ንግግራቸው ላይ አስረግጠው የተቃወሙት የኢትዮጵያን በግፍ መወረር ነው እንጅ ፣ የኤርትራን ለ 60 ዓመታት በጣልያን መገዛት አይደለም ። የኤርትራን መገዛት ለመቃወም ቢፈልጉ ኖሮ፣ መላዋ ኢትዮጵያ እስከምትወረር ድረስ መጠበቅ ባላስፈለጋቸው ነበር ። እንደማንኛውም ተጠቂ አካል በማንኛውም ጊዜ “ ሉዓላዊነቴ ተደፈረ ፤የሰሜኑ ግዛቴ በውጭ ሃይል ተወረረ ፤ የባህር በሬን ተነጠቅሁ” ብሎ ማወጅም በቻሉ ነበር ። ግን አላደረጉትም ! በመንግስታቱ ማህበር ታሪካዊ ዲስኩራቸው ላይም ስለ ኤርትራና ህዝቧ አንድም ቃል አልተነፈሱም ። ለምን……?
ይህንን የተዳፈነ ታሪክ ነው ተመፃዳቂ ፖለቲከኞቻችን ፍርጥርጥ አድርገው እንዲነግሩን የምንጠይቃቸው ። ይህን የተንጋደደ ታሪክ ነው ፀሃፊዎቻችን በሰላ ብእራቸው ግልጥልጥ አድርገው እንዲከትቡልን የምንሻው ። ምክንያቱም በዚህ የተንጋደደ ታሪክ ምክንያት በሽዎች አልያም በመቶ ሽዎች ሳይሆን… በሚልዮን የሚቆጠሩ ልጆቻችንን ከሁለቱም ወገን አጥተናልና..!! እዚህ ላይ ቆም ልበልና…..መቼም ቢሆን ስለማይረዳኝ አንድ አንኳር ነጥብ ላንሳ..!
እንደ ማንኛውም ኢትዮጵያዊ መጠን ፣ አገሬ ኢትዮጵያ በምንም አይነት የባእድ ሃይል ቅኝ እንዳልተገዛችና ፣ አውሮፓዊያን ወራሪዎችን ድባቅ መትታ በማባረር በአፍሪካ ብቸኛዋ የነፃነት ቀንዴል ለመሆን እንደበቃች እየተነገረኝ ያደግኩ ሰው ነኝ ። በእርግጥ ይህን ታሪክ እውነተኛ ታሪክ ነው ብዬ ልቀበለው ። ይሁን እንጅ ምንግዜም ቢሆን ሊገባኝ የማይችል ሌላ ታሪክ አለ ። ይሄውም የኤርትራ “ ክፍለ ሃገር ” ለ 400 አመታት ያህል በቅኝ ግዛት መላሸቅ ነው ። እንግዲህ ዋናውና እርስ በእርሱ የሚጣረሰው ነጥብ ያለው እዚህ ላይ ነው ።
እውን ኤርትራ ከረጅም ጊዜ ጀምሮ አካልነቷ የኢትዮጵያ ከሆነ… ለምን ይሆን ኢትዮጵያ አገራችን በምንም አይነት የባእድ ሃይል አልተገዛችም ብለን ለመመፃደቅ የምንሞክረው ???! የኤርትራ በባእድ ሃይል መገዛት እኛን አይመለከተንምን…? የአንድ አካልህ መጎዳት ወይም መቁሰል… ሌላውን የሰውነት ክፍልህን አይመለከተውምን….? የቀይ ባህርንና የሁለቱንም ወደቦች የማያወላውል ኢትዮጵያዊነት ቋቅ እስኪለን ድረስ የሚነግሩን ፖለቲከኞቻችንና የታሪክ ፀሃፊዎቻችን ፣ ይህን እርስ በእርሱ የሚጣረስ ታሪክ ለምን ይሆን በግልፅ መንፈስ ሊያስረዱን የማይፈልጉት ..? የኢትዮጵያችንን በቅኝ ግዛት አለመያዝ በየሄድንበት በኩራት ስናውጅ… የኛ አካል የምንላት ኤርትራን የምንረሳት ለምን ይሆን…..? ስለዚህ በእኔ እምነት ከሁለቱ አንዱን እንምረጥ !! በኤርትራ የኢትዮጵያ አካልነት አምነን … “ ኢትዮጵያ በውጭ ሃይሎች ቅኝ ተገዝታለች’’ ብሎ አዲስ ታሪክ መፍጠር አንዱ ሲሆን….ሁለተኛው አማራጭ ደግሞ የኢትዮጵያን በማንም የውጭ ሃይል አልተገዛችም ታሪክ ለማስቀጠል፣ ኤርትራን ለቀቅ ማድረግ ነው…!! እንደ እሬት ቢመረንም ምርጫው ይህና ይህ ብቻ ነው !! ከዚህ ውጭ ግን እርስ በእርሱ በተጣረሰ ታሪክ እየተጥመዘመዙ ለዘለቄታው መቀጠል ከቶውንም አይቻለንም !!
ከጊዜ መጥበብ አንፃር እንጅ ሌላም ብዙ…እጅግ ብዙ ጥያቄዎችን መዘርዘር በተቻለ ። ይህን እርስ በርሱ የተጣረሰ ታሪክ ነው ለመጭው ትውልድ ትምህርት ይሆን ዘንድ በግልፅ እንናገረው እያልኩ ያለሁት ። ይህ ታሪክ ወደድንም ጠላንም የኛ የራሳችን ታሪክ ነው ። አዎ ! አሁንም ደግሜ ደጋግሜ የምናገረው ነገር ቢኖር ፣ ይህ ታሪክ የኛ የራሳችን እስከሆነ ድረስ፣ ለመጭው ትውልድና ለልጅ ልጆቻችን ሰላምና እፎይታ ስንል እንደ እሬት ቢመረንም የግድ ልንውጠው ይገባናል ። እኛ ተደናግረን…ልጆቻችንም እንዲደናገሩና ተጨባጭነት በሌለው የታሪክ አዙሪት ውስጥ ገብተው እንዲዋልሉ መፍቀድ የለብንም ።
&n bsp; ይቀጥላል…..
&n bsp; መንገሻ ሊበን