ሰላማዊ ሰልፉን ከበካዮች (Contaminants) እንጠብቀው! ከግርማ ሞገስ

ግርማ ሞገስ (girmamoges1@gmail.com)

ዐርብ ግንቦት 22 ቀን 2005 ዓ.ም. (Sunday, May 31, 2013)

ግርማ ሞገስ

ሰማያዊ ፓርቲ የጠራው ሰላማዊ ሰልፍ እሁድ ግንቦት 25 ቀን 2005 ይደረጋል የሚል ዜና ዘሃበሻ ድረ ገጽ ላይ ሐሙስ ምሽት ተመለከትኩት። አንድነት ፓርቲ እና መኢአድም ከሰማያዊ ፓርቲ ጋር በአንድነት መቆማቸውን እና መንግስት ሰላማዊ ሰልፉን መፍቀዱን ጨምሮ ይገልጻል ጽሑፉ። ወዲያውኑ ሰላማዊ ሰልፉ እንከን የለሽ እንዲሆን እጅጉን ተመኘሁኝ። የእሁዱ ሰላማዊ ሰልፍ እንደ ኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች ሰላማዊ ተቃውሞ በድስፕሊን የታነጸ እና ክብርን ከመንግስት ሳይቀር የሚጎናጸፍ እንዲሆን እጅጉን ተመኘሁ። የበኩሌንስ ምን አስተዋጽኦ ላድርግ ብዬ ተጨነቅኩ። ይኽን ጽሑፍ በችኮላ እንዳዘጋጅ የገፋፋኝ እሱ ነው።

የሰላም ትግልን ሊበክሉና ለአደጋ ሊያጋልጡት ከሚችሉ ተግባሮች፣ አሰራሮች እና ሁኔታዎች ውስጥ ጥቂቶቹን አንስቼ በአጭር በጭሩ ልበልና ልሰናበት።

(1ኛ) ሰላማዊ ሰልፍ ሲደረግ በመንግስት ወይንም በመንግስት ደጋፊዎች አማካኝነት የሚፈጸምበትን የሽብር ጥቃት ለመመከት ሲል የሚፈጽመው ማንኛውም አይነት የኃይል እርምጃ ሰላማዊ ሰልፉን ሊበክል እና ውድቀት ሊያስከትልበት ይችላል። ስለዚህ የዲሞክራሲ አራማጅ የሆነው ወገን ለሽብር መልሱ ሽብር ነው ከሚለው ፍልስፍና መራቅ አለበት። ሰላማዊ ትግል ወደ ኃይል እርምጃዎች ከተንሸራተተ በሰላማዊ መንገድ ለነፃነት መታገል የጀመረው ህዝብ እምነት ሊተን ይችላል። ህዝብ ሁከት አይወድም። ለሽብር መልሱ አለመሸበር መሆን አለበት።

(2ኛ) የሰላም ትግል አመራር የወጣቶች እንዲሁም በእድሜና በተመክሮ የበሰሉ ሰዎች ቅይጥ ቢሆን ለበካዮች ቀዳዳ ላይከፍት ይችላል። በድስፕሊን የታነጸ ግራና ቀኙን የሚያይ እና ሰላማዊ ሰልፈኛው ውስጥ ጸብ ጫሪ ተግባር እንዳይፈጸም የሚጠብቅ በሰላም ትግል መርሆዎች የሰለጠነ ኃይል መሰማራት አለበት።

ተጨማሪ ያንብቡ:  መግለጫውን የሚመጥን ዝግጅት ተደርጓል ወይ? አብይ ብቻውን ጦርነት አይገጥምም! - አሰፋ በድሉ

(3ኛ) በድርጅቶች ህብረት-አመራር ዘንድ የሚታይ ክፍፍል የሰላም ትግልን ይበክላል። ገዢው ቡድን ደጋፊዎቹን በመላክ ወይንም ከሰላም ትግል አመራር ውስጥ ህሊና ደካሞችን በጥቅም በመግዛት ወሬ እንዲያቀብሉት (informants) ሊያደርግ እንደሚችል ቀደም ተብሎ ሊታሰብበት ይገባል። እነዚህ የመንግስት ወሬ አቀባዮች ለውይይት በሚነሱ ጉዳዮች ላይ ሆን ብለው ስምምነት እንዳይኖር እያደረጉ ዞር ብለው ደግሞ ለሰላማዊ ታጋዩ ህዝቡ ስምምነት ጠፋ ይሉታል። ህዝብ በክፍፍሉ የተነሳ በትግሉ እምነት እንዲያጣ ለማድረግ። ከፍራቻ መውጣት እና መታገል እንዲሳነው ለማድረግ። ስለዚህ የዲሞክራሲ ኃይሎች ህብረትን ማጠናከር እንዳይሳናቸው እና ጸብ ጫሪ ሰርጎ ገቦች (agent provocateurs) ምኞታቸው እንዳይሳካ መደረግ አለበት።

 

(4ኛ) የሲቪክ ድርጅቶች አመራሮች በአምባገነኖች ቁጥጥር ስር ከሆኑ የሰላም ትግል በተወሰነ ደረጃም ቢሆን ተበክሏል ማለት ይቻላል። ለምሳሌ የመምህራን፣ የሰራተኛ፣ የወጣቶች ማህበራት አመራሮች በገዢው ቡድን ቁጥጥር ስር ከሆኑ እነዚህ ተቋሞች የመጨቆኛ አጋዥ ምሶሶዎች ሆነዋል ማለት ነው። ነፃ ማውጣት አሊያም ሊላ ትዩዩ (Parallel) ድርጅቶች መመስረት ያስፈልጋል። እነዚህ ተቋሞች የነፃነት ትግልን ኃላፊነት ለእያንዳንዱ የህብረተሰብ ክፍሎች ለመበትንም ይጠቅማሉ። ወጣቱ ብቻ የሁሉም ህብርተሰብ ነፃ አውጪ ሊሆን አይችልም።

 

(5ኛ) በሰላም ትግል ኃይሎች የሚሰጡ መግለጫዎች አግላይነት ከታየባቸው የተገለለው ወገን ወደ ጸበኛነት እንዲሄድ በማድረግ የሰላም ትግል ሊበከል ይችላል። ለምሳሌ የአንድ ተቃዋሚ ድርጅት አባል ሲታሰር የሁሉም ድርጅቶች ጉዳይ ሊሆን ይገባል። መንግስት ሁሉንም በወዳጅ አይን እንደማያያቸው እና ቢቻል ሁሉም ቢጠፉለት እንደሚፈልግ መዘንጋት የለብንም። ጥቃቱ ተራ ጠብቆ የሚመጣ መሆኑ ታውቆ አንዱ ሲጠቃ ሁሉም እንደተጠቃ በመውሰድ በአንድነት መቆም ጠቃሚ ነው።

ተጨማሪ ያንብቡ:  በማተብዋ ልዳኝ - ወድቃ የተነሳችው - (ከስንሻው ተገኘ)

 

(6ኛ) የመንግስት ወሬ አቀባዮች (informers) ካሉበት የሰላም ትግል የመንግስት መልክተኛ ቆስቋሾች (agent provocateurs) ሰርገው የገቡበት የሰላም ትግል ይበልጥ ተበክሏል (Contaminated) ሊባል ይችላል። የመንግስት ወሬ አቀባዮች (informers) የሰላም ትግልን አቅምን እና እቅዶችን ለመንግስት ይዘግባሉ። የመንግስት መልክተኛ ቆስቋሾች (agent provocateurs) ግን ሆን ብለው የኃይል እርምጃ እንዲወሰድ ያደርጋሉ ወይንም እራሳቸው ድንጋይ ይወረውሩ እና ህግ አክባሪው ሰላማዊ ሰልፈኛ እንዲመታ ያደርጋሉ። በሰላም ትግል ኃይል ውስጥ ብጥብጥ ያነሳሳሉ። ለኃይል መልሱ ኃይል ነው የሚል አዝማሚያ በማራመድ የሰላም ትግል መንግስትን በደካማ ጎኖቹ እንዳይገጥመው ያደርጋሉ።

 

(7ኛ) ፖሊሶች ከከተማው ህዝብ ጋር ተቀላቅለው ስለሚኖሩ ጥሩዎቹን ልናርቃቸው አይገባም። ለምሳሌ ጎረቤቴ የሆነ ፖሊስ እኔ ፍጹም የሰላም ትግል አማኝ መሆኔን እንዲያውቅ አድርጌው ሳለ ድንገት ከፖሊስ ጣቢያ እከሌ ሽብርተኛ ነው እና ይዘህ አምጣ የሚል ትዕዛዝ ቢሰጠው ለአለቃው ሽብርተኛ አለመሆኔን ሊናገር ይችላል።

 

ለራሳችን ጊዜ ሰጥተን ቁጭ ብለን ብናሰላስል ሌሎች በርካታ ብክለት ሊጋብዙ የሚችሉ ሁኔታዎችን ማግኘት እና እንዴት ማስወገድ እንደሚቻል ማስላት እንችላለን።

 

ፍጹም ሰላማዊ እና እንከን የለሽ እንዲሆን ምኞቴ ነው!

 

1 Comment

  1. …ግርማ ሞገስ ያለው ምክር ነው በለው! “አጥብቆ ያሠረ ዘቅዝቆ ይሸከማል”
    ፩) አመራር! አመራር! አመራር! መሪው ውስን ተመሪው ብዙ ሆኖ መሪን ማክበርና መደማመጥ …ለሚነሱ ሠርጎ ብጥበጣና ሽብር እያንዳንዱ በዓላመው ፀንቶ ለድምፅና ምስል ቀረፃ ይዘጋጅ።
    ፪) የተሰባጠረ ፍልጥ ግድግዳ ያጠነክራል ከዕድሜና የልምድ ባለፀጎችም ምክርን ማካፈል ማመዛዘን በተሻለው መጓዝ። ፫) እያንዳንዱ ዜጋ…” አሉ” “ሲሉ ሰምቻለሁ!” ብለው ነጉረኝ !መሰለኝ ፣ጠረጠርኩ በሚለው ማመን ማቆም አለበት። ተገኝቼ፣ተከታትዬ፣አረጋግጫለሁ የሚል የራስ የቁርጠኝነት ውሳኔን መልመድ አለበት። ዴሞክራሲ አመጣን አሉ እንጂ በዲሞክራሲ እየሠራ ለመሆኑ ማረጋገጫ የለም። ይህ ለመናገር ተፈቀደልኝ ያልከው የማታ ማታ ሊሻር ይችላል።
    ፬) ማህበር በጋራ አባላቱን ማወቅ አይቻልም … መሆን አለበት በቡድን የግለሰብ ጥናት ማድረግ (ማ ! ማነው!ከማን ጋር! ገጠሬው ከብዙ በግ መንጋ አንድ ፍየል የሚኖረው ለምንድነው? በድርጅት መቀላቀል ሲመጣ ዝርያው ይበከላል!
    ፮) በሰላማዊ ሠልፍ አካባቢ ባዶ አውቶቡስ የሚያሳልፍ ፀጥታ አስከባሪ ሳይሆን አሸባሪ ነው። ወታደሩን ድንጋይ ወርውርና ምታ ተብሎ የሚቀጠር የፓርቲ ቅጥረኛ (ቆሽቋሾች) አድር ባይ! ሆድአደር! ብቻ ሳይሆን ‘ባንዳ ‘ይባላል። ፯) በማናቸውም ቤተሰብ ሁሉም የራሱ አመለካከት እንዳለው ሁሉ የፓርቲ አባልም ይሁን፣ ተቀጣሪ ወታደር እና ፖሊስ እንደትምህርቱ፣ ቤተሰባዊ ውልደቱና አስተዳደጉ፣ እንደ አለው የሀገር ፍቅርና የገባው ቃለ-መሐላ ሥራውን ማክበርና የማስከበር ግዴታ አለበት። ያ …ማለት ግን በአንድ ሀገር የዜግነት ልዩነት ሳይፈጥር ፣ሥልጣኑን ሳይመካ፣ ሕዝቡን የማገልገል፣ የማክበር፣ የማስከበር፣ ኀላፊነቱም ተግባሩም ግዴታውም ነው።ተቀጣሪነቱ ለግለሰቦች ሳይሆን ለሕዝብ ነውና፣ ስለሆነም በዕለታዊ የግዳጅ ሥራ መደብ ላይ የተሠማሩ ማናቸውም የፀጥታ አስከባሪዎችን እንደራስ ዜጋ ማየትና ማቅረብ ሁሉም ዜጋ ተግባሩ፣ ኅላፊነቱም፣ ግዴታውም ነው። ከመከባበር መቀራረብ፣ ከመቀራረብ መረዳዳት፣ መተማመን፣ መማርና በአንድ ሀገር በተለያየ ብዙ የፖለቲካ አስተሳሰብ ማስተናገድና የተሻለው ተቀባይነትን አግኝቶ የተሻለች ሁሉ ቤት ሆነች ውዲቷን ድንቅ ሀገር በትብስ ትብሽ አብሮ መኖር እንደነበር ፣እንዳለ፣ እንደሚኖር በፀና አቋም አብሮ መሥራትን ማዳበር የዕድገትና የለውጥ ምልክት ነው ውጤቱም ዘላቂና ሠላማዊ ፍትሀዊ ይሆናል በለው!። ከሀገረ ካናዳ በቸር ይግጠመን …ሠላም! ሠላም ! ሠላም!

Comments are closed.

Share