ከፕሮፈሰር ቤካ መገርሳ
በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ፥ አሜን።
“ለፍቅርና ለመልካምም ሥራ እንድንነቃቃ እርስ በእርሳችን እንተያይ፤ በአንዳንዶችም ዘንድ ልማድ እንደ ሆነው፥ መሰብሰባችንን አንተው እርስ በእርሳችን እንመካከር እንጂ ይልቁንም ቀኑ ሲቀርብ እያያችሁ አብልጣችሁ ይህን አድርጉ።” ዕብ ፲፥ ፳፬-፳፭
ክርስቶስ ተንሥአ እሙታን በዐቢይ ኃይል ወሥልጣን አሠሮ ለሰይጣን አግዓዞ ለአዳም ሰላም እምይእዜሰ ኮነ ፍሥሐ ወሰላም
የተወደዳችሁ የእግዚአብሔር ቤተሰቦች እንኳን ለእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በዓል (በደብረ ምጥማቅ የታየችበት ዕለት) በሰላምና በጤና አደረሰን፥ አሜን። ከላይ እንደ መግቢያ የተጠቀምኩት ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ለዕብራውያን ወገኖቹ የጻፈውን መልእክት ነው። ቀለል ባለ አማርኛ ሲተረጎም ‘ቀኑ ሲቀርብ ስታዩ፣ የፍቅርን መቀዝቀዝ ስትመለከቱ፣ የወንድማማችነትና እኅትማማችነትን ጣዕም መቀነስ ስትገነዘቡ ተሰብስባችሁ ተመካከሩ ይህ ለፍቅርና መልካም ሥራ ስለሚያነቃቃችሁ’ እንደማለት ነው። ለመጻፍ ያነሣሣኝ ምክንያት ቢኖር ሰሞኑን ወንድሞችና እኅቶች ስለ ደብረ ሰላም መድኃኔዓለም ቤተ ክርስቲያን የወደፊት ዕጣ የተጻጻፉትን የተለያዩ ሃሳቦች ከተመለከትኩኝ በኋላ ነው።
ታላላቅ ወንድሞችና እኅቶች፣ አባቶችና እናቶች በተለይም ካህናተ ቤተ ክርስቲያን ላለነውም ሆነ ለመጪው ትውልድ ኃላፊነት አለብን። ይህ ኃላፊነታችን ከሁሉም በላይ በተለያዩ ምክንያቶች የመጣነውን በሙሉ በመንፈሳዊ ህይወት አሳድጎ በመልካም ሥነ ምግባር የታነጸ ትውልድን ማፍራት ነው። መንፈሳዊ ህይወት ማለት ደግሞ መመሪያውን መጽሐፍ ቅዱስ በማድረግ ዓለምን ከሁሉ በላይ በሆነው መንፈሳዊ ጥበብ መቃኘትን ያመለክታል። መንፈሳዊ ህይወት እውነት ነው፤ መንፈሳዊ ህይወት ጀግንነት ነው፤ መንፈሳዊ ህይወት መተሳሰብ ነው፤ መንፈሳዊ ህይወት ትዕግሥት ነው፤ መንፈሳዊ ህይወት አርምሞ (ፀጥታ)ነው፤ ከሁሉ በላይ ደግሞ መንፈሳዊ ህይወት በማስተዋል መጓዝ ነው ይህን ካደረግን ነው ለእኛ ሲል የተሰቀለውን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ልንመስለው የምንችለው ይኸውም ፍቅርን እንለብሳለን ማለት ነው።
መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እኛን ለማዳን ሰው የሆነው ስለ ሁለት ዐበይት ነገሮች ነው፤ አንደኛው እኛን ከራሱ ጋር አስታርቆ በኃጢአታችን ምክንያት የተነጠቅነውን ጸጋ ለመመለስ እና ሁለተኛው ምክንያት ደግሞ እርሱን አምነን ለምንጓዝ ምዕመናን በሙሉ ክርስቲያናዊ ህይወት ምን መምሰል እንዳለበት ለማስተማር ነው።
ቤተ ክርስቲያን መመላለስ ክርስቲያናዊ ህይወታችንን ያጠብቀዋል፣ ያለመልመዋል። አእምሮአችን ይሰፋል፣ ጥበብ ሥጋዊና ጥበብ መንፈሳዊ ይሰጠናል። በመንፈሳችንም ሆነ በሥጋችን እንጠቀማለን፤ በመንፈሳችን የምንጠቀመው ሳምንቱን ሙሉ በተለያዩ የዓለም ነገሮች ተይዘን ለጸሎት ጊዜ አጥተን የነበርነው ወይም ከሰዎች ጋር በተለያዩ ምክንያቶች ተጋጭተን የነበርነውን የጸጥታ ወደብ የሆነችው ቤተ ክርስቲያን ስንመጣና ንስሐ ስንገባ፣ ስንጸልይ፣ ስንሰግድ፣ ስናስቀድስ፣ የመድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ቅዱስ ሥጋውን ክቡር ደሙን ስንቀበል ደስ ይለናል ይልቁንም ሐሴትን እናደርጋለን፤ ለበለጠ ሥራ እንነቃቃለን። በሥጋዊ ሕይወታችንም ቢሆን ቤተ ክርስቲያናችን በጣም ትጠቅመናለች። ሌሎች ብዙ እየሰሩ ‘ገንዘብ አይበቃንም’ እያሉ ሲጨነቁ ክርስቲያኖች ግን ‘የምንኖርበት ኑሮ ይበቃናል’ በማለት ከሚያገኙት ደሞዝ አሥራት(አንድ አሥረኛውን)ለቤተ ክርስቲያን አገልግሎት በመሥጠታቸው የተረፋቸውን ገንዘብ እግዚአብሔር አምላክ ሲባርክላቸው እንመለከታለን፣ ጤንነታቸውን ጉልበታቸውን አእምሮአቸውን ሲባርክላቸውና ለማዕረግ ሲያበቃቸው እናያለን አይተናልም።
ይህ ኹኔታ ቤተ ክርስቲያናችንን እስከ መጨረሻው ጊዜ ድረስ እንድንጠብቃት ያደርገናል፣ መንፈሳዊ መጨከንን ያስጨክነናል። ከሁሉ በላይ ቀደም ሲል እንዳልኩት ማስተዋልን የምናገኝባት ቦታ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ናት። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ለቆሮንቶስ ሰዎች በላከው መልእክቱ “መንፈሳዊ ሰው ግን ሁሉን ይመረምራል ራሱ ግን በማንም አይመረመርም።” (፩ ኛ ቆሮ ፪፥፲) ብሎ እንዳስተማረን ከጥበብ ቦታ ጥበብን በደንብ አድርገን መግዛት አለብን፣ ሲያልቅብንም መሙላት አለብን። ክርስቲያኖችን እስከመጨረሻው ድረስ የሚጠብቃቸው የእግዚአብሔር ቸርነት፣ የቅዱሳን አማላጅነት ጥባቆት ነው። እግዚአብሔር ለእኛ ለኃጢአተኞቹ ቸር ነው፤ ይህንንም የምናውቀው እና የምናዳብረው መንፈሳዊ ጥበብን ሊሰጡን የሚችሉ መጻሕፍትን ስናነብ ነው። “የዕለት እንጀራችንን ስጠን ዛሬ” ብለን ስንጸልይ ገንዘብ ብቻ እንድናገኝና እንጀራ እንድንገዛበት ማለቱ አይደለም ምክንያቱም ሰው በእንጀራ ብቻ አይኖርምና ነገር ግን በፈጣሪም ቃል እንጂ። አንድ ሰው ደግሞ ከእግዚአብሔር ቃል ካልተለየ ቢወድቅ አይሰበርም፤ አምላኩ አይለየውምና። እራሱን ደካማ ያደረገ ሰው ኃያሉ መንፈስ ቅዱስ ይቀርበዋል፤ ራሱን አለሁ አለሁ የሚል ግን ደካማው ሰይጣን መሣሪያው ያደርገዋል።
ይህን ለማለት የተገደድኩበት ዋና ጉዳይ ሰሞኑን እየተጻፉ ካሉት አንዳንድ ጽሑፎች በመነሣት ነው። እንደ እኔ እምነት ኢሳት፣ ቪኦኤ፣ ኢትዮ ሚድያ፣ ዘሐበሻ ሌሎችም በሙሉ መረጃ ያቀብላሉ መረጃውን ተቀብሎ እርምጃ መውሰድ የባለቤቱ ድርሻ ነው። እንደ ክርስቲያን ግን እነዚህ በሙሉ መመሪያዎች ሊሆኑ አይገቡም እላለሁ። መመሪያችን መሆን ያለበት መጽሐፍ ቅዱስ ነው። ክርስትናችን የተግባር ክርስትና (applied Christianity) መሆን አለበት። ይህም ማለት የቤተ ክርስቲያን ነገርን በተመለከተ ስንጽፍ መረጃችን መመሪያችን በቅድሚያ መጽሐፍ ቅዱስ መሆን አለበት ማለት ነው። ማንም አስተዋይ ሰው እናት አገሩን የማይወድ የለም፤ በእኔ አመለካከት ደግሞ እናት አገር ማለት አፈር ሸንተረር ወንዝ አየር ብቻ ሳይሆን ከሁሉ በላይ በአገሩ ላይ የሚኖር ማንኛውንም ወገን የሚያጠቃልል ነው። ወገን ሲሰደድ አብሮ መሰደድ፣ ሲያዝን አብሮ ማዘን፣ ሲደሰት አብሮ መደሰት ሰብአዊ ባሕርይ ነው። ከሁሉ በላይ ደግሞ ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን ይህን ነገር በየዕለቱ ታከናውነዋለች (ይህም ይታወቅ ዘንድ በእንተ ቅድሳት የሚባለው ክፍል ላይ ዲያቆኑ የሚያነበውንና እኛም “አሜን አቤቱ ይቅር በለን” እያልን የምንመልሰውን ማስተዋል ይገባል)።
እርግጥ ነው ይህ በቂ ስላልሆነ ካህናተ ቤተ ክርስቲያን ስለ አገር ስለ ወገን መስበክ ይጠበቅባቸዋል፣ በተለያየ ይዘትም ሲያደርጉት እናያለን። ስለዚህ ከቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን በላይ ስለ አገር የሚሰብክና ጠንቅቆ የሚያውቅ የለም ብዬ አምናለሁ። ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ስል ደብረ ሰላምን ብቻ ማለቴ አይደለም በአጠቃላይ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን ማለቴ እንጂ። በዘመናችን የሚድያ ቴክኖሎጂ መስፋፋትን ተከትሎ ስለ ቤተ ክርስቲያናችን ኹኔታ በየቀኑ እንሰማለን፣ እንወያያለን። በአገር ቤት ያሉ ምዕመናን የእኛን ያህል መረጃ የላቸውም ብል ማጋነን አይመስለኝም ምክንያቱም እኔም ራሴ በግሌ አገር ቤት በሄድኩባቸው ወቅቶች ከመረጃ መራቄን ስለማውቅ ማለት ነው።
‘እግዚአብሔር የለም’ ብሎ የሚል አንድ ኢአማኒ (atheist) የእግዚአብሔርን መኖር እንደማያስቀረው ሁሉ አገር ቤት ምንም ዜና አለመሰማቱ ችግር የለም ማለት አይደለም። በእኔ እምነት ቤተ ክርስቲያናችን ላለፉት ሃያ ዓመታት ያሳለፈችው በራሷ ልጆች የመበላትና የመጎዳት ዕጣ መቼም አልታየም። እዚህ ላይ ይህን ስል
ለመታረም ዝግጁ ሆኜ ነው። ቀደም ሲል እንደተናገርኩት መረጃ የማግኘት ዐቅማችን በማደጉ ብዙ የአሁኑ ጊዜ ጥፋቶች ታይተውን ይሆናልና ቀደም ሲል በነበሩ የቤተ ክህነት ሥራዎች ውስጥ ለነበሩና የበለጠ ለሚያስረዱ እተወዋለሁ። ቢሆንም ግን ሰሞኑን ስለ ቤተ ክርስቲያናችን ከተወረወሩት ጽሑፎች እንዳየሁት የመንግሥት ባለሥልጣናት ቤተ ክርስቲያናችንን ለማጥፋት አርፈው የተቀመጡበት ጊዜ የለም ወደፊትም አይኖርም። ይህ በቅጡ የሚወገዝ ተግባር ነው።የቅዱስ አቡነ ጴጥሮስን ስም እያነሡ ቅዱስነታቸው የሠሩትን ሥራ አለመሥራት ግን ጀግና አያስብልም። የመንግሥት ተቃዋሚ መሆን አንድ ሥራ ነው ተቃዋሚ ብቻ ግን መሆን አያስፈልግም ተቃውሞ ጀርባ መሠራት ያለባቸውን ነገሮች መሥራት እንጂ። እንደኔ እምነት በልመና ላይ ያለን ሰው ሁልጊዜ ገንዘብ ከመስጠት ባሻገር ራሱን የሚያሻሻልበትን ኹኔታ መፍጠር ጀግንነት ነው። እንደዛው ሁሉ በአሁኑ ሰዓት ያሉትን የመንግሥት ፖሊሲዎች መቃወም አንድ ነገር ሆኖ ሳለ ባለንበት አገር ውስጥ ተደራጅቶ ድምጽ እንዲሰማ ማድረግ ሌላ ነው። ይህን አመለካከትና አካሄድ ግን ወደ ቤተ ክርስቲያን ለማስገባት ከሞከርን ሌላ መልክና ቅርጽ ይዞ ችግር ይፈጥራል። አገራችን ኢትዮጵያ መልካም አስተዳደር እንዲኖራትና በመንግስትም ሆነ በቤተ ክህነቱ በኩል ቅንና አስተዋይ መሪዎች ታገኝ ዘንድ በየትኛውም ዓለም ያለች ቤተ ክርስቲያን ከመጸለይ ወደ ኋላ አትልም።
፮ኛው ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ብጹእ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ከመሾማቸው በፊት በቅን ወገኖች አማካይነት ዕርቀ ሰላም ተጀምሮ እንደነበር ለሁላችንም ግልጽ ነው። ሁላችንም የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ልጆች በከፍተኛ ጉጉት ላይ በነበርንበት ወቅት ከአንድነት ይልቅ መለያየትን፣ ከፍቅር ይልቅ ጸብን የሚሰብከው ሰይጣን በግብር ልጆቹ አማካይነት አፈረሰብን። ለጊዜው በኹኔታው ያልተናደደ ያልተቆጨ ሰይጣንና ሠራዊቶቹ ብቻ ናቸው ብል ማጋነን አይሆንም። ነገር ግን ….ይህ ኹኔታ ታላቂቱን ደብር ደብረ ሰላምን በመዋቅር ሥር ከመክተት ወደ ኋላ የሚያደርግ አይሆንም። ይህን የምልበት ዋናው ምክንያት ‘የቄሣርን ለቄሣር፣ የእግዚአብሔርን ለእግዚአብሔር’ ከሚል አስተሳሰብ ተነሥቼ ነው። ልክ ነው አንዳንድ ባለጌ የመንግሥት ባለ ሥልጣናት በማያገባቸው ገብተው ቤተ ክርስቲያናችንን ሲሰድቡና ሲሳለቁባት እናያለን፤ እንደውም መናፍቅነታቸውን ባጎላ መልኩ አዳዲስና ባዕድ ባህል እያስገቡ ቤተ ክርሰቲያኒቷ ባለቤት እንደሌላት ሲያድርጉ ይስተዋላሉ። እዚህ ያለንበት አገር መጥተው እንደልባቸው መፈንጨት ስለማይችሉ ያችው ምስኪኗ አገር ቤት ያለችውንና በየዕለቱ የምትሳቀቀው ቤተ ክርስቲያንን ሲላገጡባት እንሰማለን፤ ለእነርሱም የሞተላቸው አምላካችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ልቡና ይስጣቸው እላለሁ እንጂ እነሱ በሚናገሩበት ዝቅ ያለ ቋንቋ እኔ አልናገርም ባህሌም መንፈሳዊ ኑሮዬም አይፈቅድልኝምና። ይህን እየተናገሩ ቤተ ክርስቲያኔን ለመከፋፈል ለሚጥሩ ሐራ ሠገራት ግን እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ እጄን አልሰጥም። ለዚህ ነው በአቋም ደረጃ የቤተ ክርስቲያን መዋቅር ሥር እንሁን የሚል አስተሳሰብ ያለኝ። የደብረ ሰላም መድኃኔዓለም ቤተ ክርስቲያን ወደ መዋቅር ሥር ትግባ ማለት ከወያኔ ጋር ትቀላቀል ማለት አይደለም፤ ከአድርባይ የቤተ ክህነት መሪዎችም ጋር እንተባበር ማለት አይደለም።
የዛሬን ሳይሆን የነገን ሳስብ ግን ምናልባት እግዚአብሔር ቢፈቅድ አንድ እየሆንን ስንሄድ መንፈሳዊ መሪዎቻችን የሆኑት ጳጳሳትም ልቡና ገዝተው ፍርሃትን አርቀው ደፋሮች ጀግኖች ሆነው ቤተ ክርስቲያናችንን ወደ ቀደመ ቅድስናዋ ይወስዷታል ብዬ በማመን ነው። የመጪው ግንቦት ፳፭ (June 2) ስብሰባም መሆን ያለበት የግንዛቤ ማስጨበጫ ስብሰባ እንጂ ልክ ከዚህ በፊት አብረው ሻይ ቡና እንዳልጠጡ ወንድማማች እኅትማማች ሆነን አንደኛው ወገን የቤተ ክርስቲያን ተቆርቋሪ፣ ሌላኛው ወገን ቤተ ክርስቲያንን አሳልፎ ሰጪ ሆኖ መታየት የለበትም። ማንም አሸናፊና ተሸናፊ የለም፤ ሁልጊዜም ቢሆን አሸናፊነታችን ለመድኃኔዓለም ነው። ካለንበት አገር አሜሪካ የምንማረው ነገር ቢኖር ሰዎች የተለያዩ አስተሳሰቦችን ይዘው ቀርበው ሲከራከሩ ውለው የማታ ማታ በሰላም ተለያይተውና ተግባብተው ስናይ እኛ ቤተ ክርስቲያን የምንመላለስ ምዕመናን ከእነርሱ በልጠን መገኘት እንዳለብን ይሰማኛል። ካህናት አባቶቻችንን እናክብር፤ ምንም ይሁን ምን በመንፈስ ቅዱስ ተቀብተው እኛን ሊያስተምሩን ንስሐችንን ሊቀበሉን ለነፍሳችን የሚሆን ሥንቅን ሊሰንቁን ከእግዚአብሔር ተሹመዋልና። እርስ በእርሳችን እንከባበር ብናስተውለውም ባናስተውለውም መድኃኔዓለም ስለሁላችን ነው የተሰቀለው እመቤቴ ቅድስት ድንግል ማርያምም ስለሁላችንም ነው የተሰደደችው። የሰበካ ጉባዔ ሥራ አስፈጻሚ አባላት በሚያወጡልን መመሪያ መሠረት የስብሰባውን መርሐ ግብር እንከታተል እንታዘዛቸውም።በእምነት የጸኑትን እናስባቸው። መከራ ከተለያዩ አቅጣጫዎች ሲደርስባቸው ቤተ ክርስቲያናቸውን ሊያቃጥሉባቸው ሲሹ ታቦተ ህጉን ይዘው ወደ ጫካ የገቡትን፣ ‘ከነታቦቱ ቅበሩን እግዚአብሔር የፈቀደው ትውልድ ይጠቀምበት’ ያሉትን አናስባቸው እንጂ ለንደን እንዲህ ሆነ ዳላስ እንዲህ ሆነ ብለን አንፍራ።
እነርሱ ጋር የደረሰው እኛ ጋር ሊደርስ የሚችለው በጥላቻ መንፈስ ብቻ ተመልተን የምንነጋገር ከሆነ ነው። እኛ ከእነርሱ እንበልጣለን እንሻላለን የሚል መንፈስ ይዤ አልናገርም፤ ሁላችንም ሰዎች ነን እንበድላለን ነገር ግን በማስተዋል ነገሮችን ካደረግን ምናልባት ቅድም የጠቀስኳቸው በመጥፎ ምሳሌ እንደሚነሡ እኛ የመልካም
ነገር ምሳሌ እንሆናለን። እንዴ፥ ምነው በሰላም የተቀላቀሉ አብያተ ክርስቲያናት የሉም ወይ? ምሳሌ ካስፈለገ ምነው የቅርባችን የሳውዝ ዳኮታ ኪዳነ ምሕረት ቤተ ክርስቲያን ስሙ የማይነሣው? በመመካከርና በጥበብ በማድረጋቸው ያለ ምንም ችግር ድምጻቸው ሳይሰማ አይደለም እንዴ በመዋቅር ሥር የገቡት?
ዋናው ነገር፥ ልበ ሰፊ ነገር አላፊ ሆኖ ለመወያየት መቅረብ ነው። ሁሉም ሰው በአንድ ጊዜ አንድ አይነት አስተሳሰብ ያስብ ማለት የዋኅነት ነው፤ ስለሆነም ወደ እናት ቤተ ክርስቲያን እንቀላቀል የሚል ወገንም ሆነ በገለልተኝነት እንፅና የሚል ወገን መንፈሳዊነትን ባልለቀቀና ፕሮፌሽናል በሆነ መንገድ የራስን ስሜት በመገደብ የቆሙበትን ቦታና ዓላማ ባለመዘንጋት በማስተዋል ሃሳብን ማስተላለፍ ተገቢ ነው ብዬ አምናለሁ። በሌላ ወገን ደግሞ በምዕመናን ላይ ጫና ለመፍጠር መሞከርና ስምን በመደበቅ የብዕር ስም እየተጠቀሙ ፍርሃትን ለመልቀቅ መሞከር መልካም ሥነ ምግባር አይደለም። ዝምታም ፈሪነት አይደለም።
የጀግና ስም ከጠሩ ጀግናውን ለመሆን መጣር ያስፈልጋል። ክርስቲያኖች መሠረታችን ፈጣሪያችን አምላካችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። የክርስቶስ ከሆንን ደግሞ አይደለም በዘር ማጥፋትና በመለያየት ሃሳብ ላይ የተሰለፉ ወገኖች ብቻም ሳይሆኑ የገሃነም ደጆች ቤተ ክርስቲያናችንን ሊያናውጡአት አይችሉም፤ እኛ ብናንቀላፋ ፈጣሪያችን አያንቀላፋምና።
ወስብሐት ለእግዚአብሔር ወለወላዲቱ ድንግል ወለመስቀሉ ክቡር
ቤካ መገርሳ
Professor
University of Saint Thomas
Mechanical Engineering Dep’t