ከሮቤል ሔኖክ
ዛሬ በአዲስ አበባ ታትሞ የወጣውን ሪፖርተር ጋዜጣ ሳነብ ከሰሞኑ ከወረተኛዋ ኢሕአዴግ በፍቅር ሲቆሉ ከከረሙት ባለስልጣናት መካከል አንዱ የሆኑት አቶ መላኩ ፈንታ ታመው እንደነበር የሚገልጽ ዜና አንብቤ በዜናው ቀናሁ። የሙያ ባልደረባችን ርዕዮት ዓለሙ በጡቷ ላይ እብጠት ወጥቶባት ሕክምና ስትፈልግ፤ ለህክምና ራይድ የሚሆን መኪና የለም ተብላ ወራትን ስትጠብቅ ይህን ዜና እንደዘ-ሐበሻ የመሳሰሉ ነፃ ሚድያዎች ሲዘግቡት እነ ሪፖርተር ሆዬ ጆሯችን አልሰማም ብለው አልዘገቡትም። ዛሬ የአቶ መላኩን ዜና ሲጽፉት ትዝ አለኝና ር ዕዮት ዓለሙ ትዝ አለችኝ። የቅናቴ መነሻም ይሄው ነው።
ስለ ር ዕዮት ዓለሙ የጡት ህመም ለመዘገብ አንጀት ያልነበረው ሪፖርተር ስለ መላኩ ፈንታ መታመመ ጠበቃቸውን ጠቅሶ እንዲህ አለ፦
በተጠረጠሩባቸው የተለያዩ የሙስና ወንጀሎች ግንቦት 2 ቀን 2005 ዓ.ም. ከሰዓት በኋላ በቁጥጥር ሥር ውለው በእስር ላይ የሚገኙት በሚኒስትርነት ማዕረግ የኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ መላኩ ፈንታ መታመማቸውን ጠበቃቸው ግንቦት 16 ቀን 2005 ዓ.ም. ፍርድ ቤት ቀርበው አስታወቁ፡፡
ጠበቃው አቶ መላኩ በአስቸኳይ ሕክምና እንዲደረግላቸው ጠይቀው፣ “እኚህ ሰው በጠና ስለታመሙ የታሪክ ተወቃሽ እንዳንሆን፤
የአቶ መላኩን ጤንነት በሚመለከት ጠበቃው በዝርዝር ጠይቀው የሕመማቸው ዓይነትና ደረጃ በምን ሁኔታ ላይ እንደሚገኙ ባይረዱም፣ መልካቸው ቢጫ ሆኖ እንዳዩዋቸው ገልጸዋል፡፡ ለምን እንዳላነጋገሩዋቸው ሲጠየቁ በቂ ጊዜ እንዳልነበራቸው የገለጹት ጠበቃው ከእሳቸውና ከቤተሰቦቻቸው ጋር መገናኘታቸውን፣ ነገር ግን ሆስፒታል ይሂዱ ወይም አይሂዱ አለማወቃቸውንም አስረድተዋል፡፡
በአጃቢ ሆነው ሕክምና እንዲያገኙ ጠበቃው ላነሱት ጥያቄ፣ ስለመታመማቸው የሚገልጽ ማስረጃ ከክሊኒክ ወይም ከሆስፒታል እንደሚያስፈልግ በመግለጽ ያለማስረጃ ትዕዛዝ መስጠት እንደማይቻል ፍርድ ቤቱ አስረድቷል፡፡
አቶ መላኩ መንግሥት የሚያውቀውና በአገር ውስጥ ሕክምና የማይድን ሕመም እንዳለባቸውና በውጭ አገር እየታከሙ እንደነበር፣ ለፍርድ ቤቱ ራሳቸውና ጠበቃቸው ማስረዳታቸው የሚታወስ ነው፡፡ ” ብለዋል
አንድ በሙስና የበሰበሰና የሰዎች ሰብአዊ መብት ሲገፈፍ አቤት ሳይል የከረመ ሆዳም ባለስልጣን ምንስ ቢሆን የምን ታሪክ ይመጣል? ይልቅ የታሪክ ተወቃሽ የሚያደርገን የመናገርና የመጻፍ መብቷን ተገፋ ታስራ ህክምናም እንዳታገኝ በወህኒ የተወረወረችው ር ዕዮት ጉዳይ ነው የታሪክ ተወቃሽ ሊያደርግ የሚችለው።
እኔን የገረመኝ ከሰሞኑ በስርቆት ወንጀል የታሰሩት እነዚህ የወያኔ ተላላኪዎች በፍርድ ቤት ‘ይታዘንልን’ ሲሉ ያቀረቡት ማስተዛዘኛ ሁሉ ህመምን ነው።
– አንዱ የልብ ህመም
– አንዱ መናገር የማልፈልገው በሽታ
– አንዱ ሌላ
– ሌላው ሌላ በሽታ ጠርተዋል: ርዕዮት ዓለሙ ጡቷን ታማ ሲሳለቁ፤ ውስኪያቸውን ሲጨልጡ የነበሩ ተላላኪዎች ይህን “ይታዘንልን?” ምክንያት ሲያቀርቡ እኛ እንቀበል ይሆን?