ምነው ይህን ሁሉ???
“ሰካራም” የተባለው የፌደራል ፖሊስ መኮንን አስራ አራት ልጆችሽን ፈጀ። ይህን ሁሉ ግድያ ሲፈፅም (መንግስት ባለበት ሀገር) ሊያስቁመው የቻለ (ወይ የሞከረ) ሃይል እንዳልነበረ ስንሰማ ግራ ገባን። የገዳዩ ማንነት ለተወሰነ ግዜ ሲደበቅብን (የወንጀለኛ ማንነት መደበቅ አስፈላጊ ስላልሆነ) ለተለያዩ መላምቶች ተጋበዝን። (ስሙ ስለተደበቀ ይመስለኛል) ጉዳዩ ከብሄርና ከፖለቲካ ተቀላቀለብን። ‘መንግስት የዜጎችን ደህንነት የመጠበቅ ግዴታ ስላለበት ተጎጂዎቹን ለማዳን መንግስታዊ ሓላፊነቱን አልተወጣም’ ብለን አለፍነው። መንግስት ታጣቂዎችን (ፌደራል ፖሊሶች ጨምሮ) የህዝብ ደህንነት እንዲጠብቁና በህዝብ ጉዳት እንዳያደርሱ የመቆጣጠር ሓላፊነት አለበት።
ሓዘናችን ሳንረሳ የጣና ሃይቅ አደጋ ደረሰ። የአደጋው መንስኤ በትክክል እስካልታወቀ ድረስ ‘የተፈጥሮ አደጋ (ከቁጥጥራችን ውጭ) ነው’ ብለን ለተጎጂዎቹ አፅናንተን ሳንጨረስ ሌላ የእሳት አደጋ መድረሱ እየሰማን ነው። (በጣና ሃይቅ በደረሰው አደጋ የሞቱ ሰዎች አምስት መድረሱ ተነግሮናል)።
በጅንኣድ (በባህርዳር) ያጋጠመ የእሳት አደጋ እስካሁን በቁጥጥር ስር እንዳልዋለና ወደ ሌሎች አከባቢዎች እንዳይዛመት ተሰግቷል። የእሳት አደጋው መንስኤ እስካሁን ካልታወቀ የራሳችን መላምት ብንሰጥ አይከፋም። የአደጋው ምክንያት ይሆናል ብዬ የምገምተው (“ጥያቄ አለኝ ጓዶች” በሚል የፌስቡክ ስም የሚጠቀመው ወዳጄ እንዳስቀመጠው) ሙስና ነው። የድርጅቱ ሰራተኞች ብዙ የመንግስት ሃብት በሙስና ዘርፈው ይሆናል (ወይ እንበል) የድርጅቱ ንብረት ኦዲት ተደርጎ የፈፀሙት ሙስና እንዳይታወቅ ሰነዶችን የሚጠፉበት መንገድ ማመቻቸት ግድ ይላል። ለዚህኛው ጥሩ መፍትሔ ደግሞ ድርጅቱ በእሳት ማቃጠል ነው። (መላምት መሆኑ ነው።)
እንዲህ ዓይነት ሙስናን ለመሸፋፈን የሚወሰድ እርምጃ በትግራይ ክልል በተደጋጋሚ ሲሰራበት ቆይቷል። በትግራይ ትምህርት ቤቶችና ሆስፒታሎች (ሙስናን ለመሸፈን ሲባል) በእሳት ተቃጥለዋል። ሁለት ኪሳራ መሆኑ ነው (1) የመንግስት ገንዘብ በሙስና ይወስዳሉ፣ (2) ይህን ሳያንስ የበሉበት ተቋም በእሳት ያወድማሉ።
It is so!!!