ግርማ ካሳ
(muziky68@yahoo.com)
ሜይ 20 ቀን 2013
አገር ዉስጥ በሰላም የሚንቀሳቀሰው የሰማያዊ ፓርቲ፣ ግንቦት 17 ቀን 2005 ዓ.ም፣ በአፍሪካ ሕብረት ጽ/ቤት ፊት ለፊት ሰላማዊ ሰልፍ አውጇል። ከግንቦት 15 እስከ 17 ባሉት ቀናት ደግሞ፣ ኢትዮጵያዉያን ጥቁር አልባሳት በመልበስ፣ አገዛዙ በሚያራምዳቸውን ጎጂ ተግባራት ላይ፣ ያላቸውን ተቃዉሞ እንዲገልጹ ጥሪ አስተላልፏል።
ፓርቲዉ በቅርቡ የተመሰረተ፣ ብዙ አገር አቀፍ መዋቅር ገና ያልዘረጋ፣ ተስፋ የሚሰጥና በወጣቶች የተሞላ ለጋ ፓርቲ ነዉ። ጥሪዉ ከቀረበ ገና ሶስት ሳምንት ብቻ እንደመሆኑም፣ ምን ያህል አስቀድሞ ሕዝቡን በማደራጀት አንጻር በቂ ዝግጅት እንደተደረገ ፣ ጥሪው በይፋ ለሕዝብ ከመተላለፉ በፊትም ከሌሎች ድርጅቶች ጋር (እነርሱም ዝግጅት እንዲያደርጉ) ምን ያህል ዉይይት እንደተካሄደ አላውቅም። በመሆኑም በግንቦት 17 ምን ሊፈጠር እንደሚችል ለመተንበይ አስቸጋሪ ነዉ።
እንደዚያም ሆኖ ግን፣ ከወዲሁ በርካታ ድሎችን ተመዝግበዋል ባይ ነኝ። የሰማያዊ ፓርቲ አመራር አባላት፣ ይሄን ጥሪ ሲያቀርቡ፣ ምን ያህል ድፍረትና ጀግንነት እንዳላቸው ለማረጋገጥ ችለዋል። ሊታሰሩ፣ ሊደበደቡ፣ ሊገደሉ እንደሚችሉ ያውቃሉ። እነርሱ መካከል ያሉ፣ ብዙዎቹ ኢንጂነሮች፣ ጠበቃዎች ..ናቸው። የገዢው ፓርቲን ተቀላቅለው፣ የስርዓቱ ተጠቃሚዎች መሆን የሚችሉ ናቸው። ነገር ግን ኢትዮጵያንና ሕዝባቸውን አስቀድመዉ፣ ለፍትህ፣ ለእኩልነት፣ ለዲሞክራሲና ለሕግ የበላይነት በመቆም፣ ከፊት በመቅደም፣ ትግል ምን ማለት እንደሆነ እያሳዩን ነዉ።
በዚህም ምክንያት፣ በፈታኝና ትእግስት አስጨራሽ ሁኔታ ዉስጥ ተኩኖም፣ አገር ቤት የሚደረገዉን የሰላማዊ እንቅስቃሴ፣ መግለጫ ከማዉጣትና ገዢው ፓርቲን ከማውገዝ ያለፈ፣ አንድ ምእራፍ ወደፊት እንዲሄድ፣ የሰማያዊ ፓርቲ ጥሪ አድርጓል። አንድ በሉ።
ለበርካታ አመታት የዳያስፖራዉ ትኩረት አዲስ አበባ ሳይሆን አስመራ ነበር። አገር ቤት ያሉ ወገኖቻችን ምንም እንደማይሰሩ፣ መስራት ቢፈልጉም መስራት እንደማይችሉ፣ አገር ቤት የሚደረገዉ ሰላማዊ ትግል «ቅዠት» እንደሆነ ነበር የሚነገረን። ነገር ግን በቅርቡ በተለያዩ ሜዲያዎች እንዳነበብነው፣ እንደ ኢሕአፓ-ዴሞክራሲያዊና የኢትዮጵያ ሽግግር ምክር ቤት ያሉ አንጋፋ በዉጭ አገር ያሉ ድርጅቶች፣ የሰማያዊ ፓርቲ ላቀረበው ጥሪ ያላቸውን ኢትዮጵያዊና ወቅታዊ አጋርነት ገልጸዋል። በተለያዩ የፓልቶክ ክፍሎች፣ በኢሳት፣ በራዲዮኖች፣ በድህር ገጾች የሰማያዊ ፓርቲ ጥሪ ትልቅ ትኩረት ስቦ ውይይትን ጭሯል። ይሄ ሁሉ እንግዲህ የሚያሳየዉ ዳያስፖራው ትኩረቱን አገር ቤት ወደሚደረገው የሰላማዊ እንቅስቃሴ ላይ እንዲያዞር ማድረጉን ነዉ።
በዉጭ የሚገኘው ወገን ብዙ ሊረዳ፣ ብዙ ሊደግፍ፣ ትልቅም ሚና ሊጫወት የሚችል ነዉ። ይህ ኃይል አገር ቤት ካለው ኃይል ተነጥሎ፣ አገር ቤት ከሚደረገዉ ትግል እራሱን ለይቶ መቆየቱ ብዙ ጉዳት በትግሉ ላይ አምጥቷል። አገዛዙን በእጅጉ ጠቅሟል። በሰማያዊ ፓርቲ ጥሪ ምክንያት፣ አገር ቤት የሚደረገዉን ትግል ለመደገፍ ፣ በዳያስፖራ የሚደረገዉን እንቅሳሴ ማየታችን በራሱ ትልቅ ድል ነው። ብዙዎቻችንን አስደስቶናል። በመካከላችን የነበረዉን መከፋፈል አስወግዶ ከዚህ በፊት በቅንጅት ጊዜ እንደነበረው፣ በአንድነት እንድንሰማራ የማድረግ ትልቅ ኃይል አለዉ። ሁለት በሉ።
በድርጅታዊ መዋቅርና በአባላት ብዛት ከሰማያዊ ፓርቲ እጅግ የላቁ እንደ አንድነት ፓርቲ ያሉ በአገር ዉስጥ የሚንቀሳቀሱ ድርጅቶች አሉ። እነዚህ ድርጅቶች ተመሳሳይ አላማ እንዳላቸው፣ በዚያም ረገድ ሁሉንም አስተባብረው፣ የተጠናና የተደራጀ የሰላማዊ የእምቢተኝነት እንቅስቃሴዎች ለማድረግ እቅድ እንዳወጡ እንሰማለን። የሰማያዊ ፓርቲ ጥሪ፣ በነዚህ ድርጅቶች ዉስጥ በእቅድና በጥናት ደረጃ የተቀመጡ እቅዶች ወደ ተግባራዊነት እንዲሄዱ የሚያበረታታና አሉታዊ አስተዋጾ የሚኖረው ሆኖ ነዉ ያገኘሁት። ሶስት በሉ።
የሰማያዊ ፓርቲን ሰላማዊ ሰልፍ ጥሪን አስከትሎ ገዢዉ ፓርቲ እጅግ በጣም በርካታ ወታደሮች አዲስ አበባ ከተማ ዉስጥ እንዳስገባ እየተዘገበ ነዉ። «ከሕዝብ ሊነሳብኝ የሚችለዉን ዉጥረት እንዴት አድርጌ ነዉ የማከሽፈው?» በሚል አገዛዙ ውጥረት ላይ ሊሆን እንደሚችል አስባለሁ። እንግዲህ የሰማያዊ ፓርቲ ጥሪ፣ ከወዲሁ ለአገዛዙ ትልቅ መልእክት እንዲደርሰው እያደረገ ነዉ። መልእክቱም «ዝም ብለን አንቀመጥም። ለመብታችን፣ ለነጻነታችን እንሞታለን። ከአሁን በኋላ አንፈራችሁም» የሚል ነዉ። ይሄም በራሱ ትልቅ ዉጤት ነዉ። አራት በሉ።
ሁለት ነገር ብዬ ላቁም። የመጀመሪያዉ ሰማያዊ ፓርቲ ያቀረበዉ ጥሪ፣ የሰማያዊ ፓርቲ ቢያቀርበዉም፣ ጉዳዩ ሁላችንምም የሚመለከት እንደሆነ ነው። ሁላችንም የድርሻችንን መወጣት አለብን። በኢሜል፣ በስልክ፣ በኢንተርኔት፣ በቫይበር …ለምናውቃቸው በሙሉ ጥሪ እናስተላልፍ። ሰማያዊዎች ለመታሰር ተዘጋጅተዋል። እኛ ቢያንስ 5፣ 10፣ 20 አገር ቤት ያሉ ኢትዮጵያዉያንን ጥቁር አልባሳት እንዲለብሱ ማበረታት ሊያቅተን አይገባም። እንረባረብ። «አይ እኔ የማደርገዉ ምን ለዉጥ አያመጣም» በጭራሽ አንበል። ግድ የለም ማድረግ የምንችላትን ትንሿን እናድርግ።
ሁለተኛው ነጥብ፣ ይሄ የሰማያዊ ፓርቲ ጥሪ የመጀመሪያዉ እንጂ የመጨረሻዉ እንደማይሆን ነዉ። ከአሁኑ የሰማያዊ ፓርቲ ጥሪ ትምህርት ተወስዶ፣ የሰማያዊ ፓርቲ፣ የአንድነት ፓርቲ፣ መኢአድ፣ አረና ትግራይ፣ የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ ..የመሳሰሉ አገር ቤት ያሉ ድርጅቶች በአንድ በኩል፣ እንደ ኢህአፓ-ዴ፣ የሽግግር ምክር ምክር ቤት፣ ሸንጎ ፣ የኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ግንባር የመሳሰሉ በሌላ በኩል ሆነው፣ ትግሉን በማቀናጀት፣ አገረ ሰፊ፣ ተከታታይ፣ የተቀናጀ፣ በዲፕሎማሲና በሕዝብ ግንኙነት የተደገፈ፣ የተጠና፣ ሰላማዊ የእምቢተኘት ዘመቻዎች መደረግ አለባቸው፤ ይደረጋሉምም። አብረን ተያይዘን እስከሰራን ድረስ፣ ሰላማዊ በሆነ መንገድ ማሸነፋችን አይቀርም።
ሰላማዊ እንቅስቃሴ ማድረጉ የዜጎች ሙሉ አለም አቀፋዊ መብት ነዉ። አሁን ያለው ገዢው ፓርቲ የሚመጻደቅበት ግን እራሱ የማያካብረው ሕገ መንግስት ሁሉ ሳይቀር፣ ሰላማዊ ሰልፍ የማድረግ ሙሉ መብትን ይደነግጋል። በመሆኑም አንዳንድ የገዢዉ ፓርቲ ካድሬዎች የሰማያዊ ፓርቲን እንቅስቅሴ ሊያጣጥሉት ይችላሉ። ጸረ-ልማት፣ ሽብርተኘንት፣ ጽረ-ሕገ መንግስታዊ፣ አመጽ ቀስቃሽ ወዘተ የሚሉ ክሶችን ሊሰነዝሩ ይችላሉ። ነገር ግን ይሄን በማድረጋቸው የሚነገሩን ነገር ቢኖር ዘመናዊ ፖለቲካ ያልገባቸው፣ የኋላ ቀር የጫካ ፖለቲካ የሚያራምዱና በራሳቸው የማይተማመኑ መሆናቸውን ነዉ።
ተቃውሟችን በልማት ላይ አይደለም። ተቃዉሟችን በአባይ ግድብ ላይ አይደለም። ኢሕአዴግን እንደ ድርጅት አንቃወምም። የኢሕአዴግ ደጋፊዎች ኢሕአዴግን የመደገፍ፣ በኢሕአዴግ ፖሊሲ ዙሪያ የመንቀሳቀስና የመደራጀት ሙሉ መብታቸው እንደሆነ እናምናለን። እንደዉም ኢሕአዴግን ከሚደግፉ ፣ ኢሕአዴግ በመልካም አስተዳደርና በደሞክራሲ ረገድ እንዲያሻሻል ከሚፈልጉ ጋር መነጋገር ያስፈልጋል እንላለን። (እንደዉም እንደታዘብነዉ በርካታ የኢሕ፤አዴግ ደጋፊዎች በይፋ የሚደግፉትን ድርጅት እየጠየቁ ያሉበት ወቅት ነዉ)
ነገር ግን የአገዛዙ ባለስልጣናት ሌላዉን የመርገጥ፣ የማሰር፣ የማንገላታት ፣ የማፈናቀልና የመግደል ስልጣን የላቸውም። በዚህ ረግድ የሚፈጽሙትንም እኩይ ተግባራት «ያቁሙ» ብለን ነዉ ተቃዉሞ የምናሰማዉ።
የምንቃወመው፣ ለሕንዶችን ለአረቦች መሬት እየተሰጠ፣ ዜጎችንን ከዚህ ዘር ናቸው በሚል፣ ከቅያቸው በማፈናቀል የሚደረግን አሳዛኝና ጨካኝ የዘር ማጥራት ወንጀልን ነዉ።
የምንቃወመው፣ ድሃዉ ሕዝባችን፣ ታንቆ ከአመት ወደ አመት፣ ለአባይ ገንዘብ እንዲከፍል እየተደረገ፣ ቢሊዮን ዶላሮች ከአገር ቤት መዘረፋቸውን፣ በቱባ የአገዛዙ ጀነራሎችና ባለስልጣናት፣ በአደባባይ ኬት እንዳመጡት በማይታወቅ ገንዘብ የሚሰሩት ፎቆችንና የሚያንቀሳቀሱ ቢዝነሶችን ነዉ።
የምንቃወመው ዜጎች በአገራችን ብእር ስላነሱ ብቻ፣ ወይም «በሃይማኖት ጉዳይ መንግስት ጣልቃ አይገባ» በማለታቸው፣ ሽብርተኞች እየተባሉ በግፍ መታሰራቸውን ነዉ።
እንግዲህ መብቴ ተረገጠ የሚል ኢትዮጵያዊ ካለ ፣ ይነሳ። መብቱንም ያስከብር።