(ከኢየሩሳሌም አርአያ)
በአላሙዲ የገንዘብ ድጋፍ የሚደረግለት፣ በረከት ስምኦን ከጀርባ የሚመሩት እና በአንድ ኤርትራዊ የሚዘጋጀው ጋዜጣ አለም አቀፉን ማህበረሰብ ለማደናገር ሲሞክር መታየቱን ተከትሎ ምስጢሩን የሚያውቁ የቅርብ ምንጮች ጉዳዩን አጋለጡ። « ሰንደቅ» የተባለውና በነፃ ፕሬስ ስም የሚያደናግረው ጋዜጣ ፍሬው አበበ በተባለ ዋና አዘጋጅነት እንዲሁም በኤርትራዊው ፋኑኤል ክንፉ ምክትል ዋና አዘጋጅነት የሚሰናዳ ሳምንታዊ ጋዜጣ ሲሆን ቦሌ አትላስ ሆቴል አካባቢ በውድ ዋጋ ቢሮ ተከራይቶ እንደሚሰራ ያስታወቁት ምንጮቹ አያይዘውም ፍሬው አበበ ከዚህ ቀደም የብአዴን ልሳን በሆነው « ማህቶት» ጋዜጣ ላይ ይሰራ እንደነበረና ከብአዴን አመራር አባላትም ጋር የጠበቀ ግንኙነት እንዳለው አረጋግጠዋል። በፓርቲው ልሳን ለመስራት ደግሞ የድርጅቱ አባል መሆን ግድ እንደሚል የጠቆሙት ምንጮቹ “ጋዜጠኛ” ፍሬው የፓርቲው አባል እንደሆነና በነበረው ታማኝነት በበረከት ስሞን ተመርጦ አሁን ባለበት ጋዜጣ እንዲሰማራ መደረጉን አስታውቀዋል። በተጨማሪ «የኢትዮጲያ ነፃ ጋዜጠኞች ማህበር» ተብሎ በሚጠራውና የገዢው ፓርቲ ተለጣፊ በሆነው “ማህበር” ጋዜጠኛ ፍሬው የቦርድ አባል ሲሆን፣ ይህ ማህበር በሃገሪቱ ነፃ ፕሬስ እንዳይኖር ቀን ከሌሊት የሚተጋ ነው ሲሉ ምንጮቹ በመግለፅ ተከታዩን ማስረጃ ያቀርባሉ። « ማህበር ተብዬው በሚሚ ስብሃቱ ሬዲዮ በኩል « እነእስክንድር ነጋ አሸባሪ ናቸው» ብሎ ተከራክሯል፤ «አዲስ ነገር፣ አውራምባ ታይምስ» ጋዜጦች ሲዘጉ «ከስረው ነው» በማለት የሽመልስ ከማልን መግለጫ የሚያጠናከር መግለጫ በማውጣት ከመንግስት ወግኖ ተሟግቷል፤ እንዲሁም በተመስገን ደሰላኝ ይዘጋጁ የነበሩት «ፍትህ፣አዲስ ታይምስና ልዕልና» ጋዜጦች በነበረከት ቀጭን ትእዛዝ እንዲዘጉ ሲደረግም የነፍሬው ማህበር ተመሳሳይ አቋም በማራመድ መከራከሩን በዋቢነት የጠቆሙት ምንጮቹ አክለውም፥ በአጠቃለይ ጋዜጠኛ ሲታሰር፣ ሲንገላታና ሲሰደድ ልክ መንግስት ተቀጥላ እየፈጠረ ለመወንጀል እንደሚሞክረው ሁሉ ይህም ማህበር ተመሳሳይ አካሄድ የሚከተል ፀረ-ፕሬስ ስብስብ ነው ብለዋል። ከዚህ በተጨማሪ የዚህ ተለጣፊ ማህበር ሊቀመንበር አንተነህ አብርሃም እንደሆነ የጠቆሙት ምንጮቹ የአንተነህ ታላቅ ወንድም አማኑኤል አብርሃ ሲባል የደኢህዴን/ኢህአዴግ ማ/ኮሚቴ አባል መሆኑን አጋልጠዋል።
በሌላም በኩል ምክትል የጋዜጣው አዘጋጅ ኤርትራዊው ፋኑኤል አንድ ሰሞን በኢቲቪ የህትመት ዳሰሳ ላይ ቀርቦ « የኢህአዴግ ደጋፊ ነኝ » ሲል በይፋ መናገሩን ያስታወሱት ምንጮቹ የስርአቱን ትክክለኛነት በመግለፅና በመከራከር የገዢው ፓርቲ «ቋሚ ጠበቃ» ሆኖ መታዩትን ጨምረው ገልፀዋል። (ከዚሁ ጋር በተያያዘ የፍትህ ጋዜጣ አምደኛ የነበረው አቤ ቶክቻው « የኢቲቪ አምደኛ» ሲል በወቅቱ ተሳልቆበታል)..
ምንጮቹ ከጋዜጣው ጋር በተያያዘ ሲቀጥሉ ይህን አሉ፤ የነፃ ፕሬስ ህልውና በአገሪቱ ጨርሶ እንዲጠፋ በተደረገበት ተጨባጭ እውነታ፣ የህትመት ዋጋ ጣራ በነካበት ሁኔታ ..«ሰንደቅ» የተባለው ጋዜጣ የሚያሳትመው ሁለት ሺህ ኮፒ ብቻ መሆኑ፣ ማስታወቂያ የሌለው መሆኑ፣ በተጨማሪ በሃገሪቱ ውድ በሚባለው ብርሃነ ሰላም ማ/ቤት መታተሙ እንዲሁም አዘጋጆቹ ከፍተኛ ደሞዝ የሚከፈላቸው የመሆኑ ምስጢር ሼህ አላሙዲ መሆናቸውን ያስገነዝባሉ። በዚህን ያክል ኮፒ ትርፍ ማሰብ ጨርሶ የማይታሰብ መሆኑን ያመለከቱት ምንጮቹ፣ አላሙዲ የገንዘብ ድጋፍ እንደሚያደርጉና ጋዜጣውም በየሳምንቱ ሼኹን ከፍ-ከፍ አድርገው የሚያሳዩና ድርጅቶቻቸውን የተመለከቱ ዜናዎች እያተሙ የማውጣታቸው ምስጢሩ ከገንዘብ ድጋፉ ጋር የተያያዘ ነው ብለዋል።
በዚሁ ጋዜጣ ላይ በረከት የሚፈልጉትና « ህዝብ ዘንድ መድረስ አለበት» የሚሏቸውን ምስጢራዊ ጉዳዮች ለሁለቱ የጋዜጣው አዘጋጆች የስራ መመሪያ ጭምር ከመስጠት ባለፈ በረከትና ሽመልስ በተለያዩ የብእር ስሞች ፖለቲካዊ ነክ ፅሁፎች እንደሚያወጡ፣ የሚፈልጉትን መረጃ እንደሚያስተላልፉ፣ ምንጮቹ አጋልጠዋል። እንዲህ ሲሉም ያብራራሉ፥ « የእነአበበ በለውና እስክንድር ነጋ ንብረት እንዲወረስ የተለያዩ የብእር ስሞች (ሽመልስና በረከት) በመጠቀም በጋዜጣው ቅስቀሳ ሲካሄድ ከቀየ በኋላ በመጨረሻ በዋና ክስነት ከቀረበው ውጭ «የንብረት ክስ» በሚል ሌላ ክስ ተመስርቶ የንብረት ውርሱ ተግባራዊ እንዲሆን ተደረገ። መንግስት የሰጠውን ግዳጅ በመወጣት፣ ነፃ ፕሬስን ሽፋን አድርጎ የተሰማራው ሰንደቅ ጋዜጣ ከጀርባ ያነገበው «አላማ» እንዲሁም አካሄድ በህዝብ ዘንድ ጥርጣሬ በማስከተሉ የጋዜጣው የኮፒ መጠን ላለፉት አመታት ሊያድግ እንዳልቻ አስታውቀዋል። በተለይ የጋዜጣው ዋና <አላማ> ተቃዋሚዎችን በአለ በሌለ ጉልበቱ ጨፍልቆ በመምታት በይፋ እንደሚታወቅ አመላክተዋል።
ለዚህም ከሁለት ሳምንት በፊት የተፈጠረውን ሁኔታ በአስረጅነት ይጠቅሳሉ ምንጮቹ፤ አብዛኛው አገር ቤት ያሉ ምሁራን አድፍጠው ባሉበት ተጨባጭ ሁኔታ ገዢውን ፓርቲ በአደባባይ ከሚቃወሙና የተለያዩ የመሟገቻ ሃሳቦችን ከሚያቀርቡ በጣት የሚቆጠሩ ምሁራን አንዱ ዶ/ር ዳኛቸው አሰፋ ነው በማለት ይገልፃሉ። ጋዜጣው « ዶ/ር ዳኛቸው የመኢአድ ቀጣዩ ፕሬዝዳንት ለመሆን ከኢ/ር ሃይሉ ጋር መምከራቸውን» በማስቀደም አያያዞም « የብአዴን አባል ነበሩ» ሲል በተቃዋሚ ክፍሎችና በህብረተሰቡ ዘንድ ጥርጣሬን ለመጫር መሞከሩን የገለፁት ምንጮቹ በረከት ስሞኦን ያጠናቀሩት ዘገባ መሆኑን አጋልጠዋል። ይህ ዘገባ ጨርሶ ከእውነት የራቀ መሆኑን የሚገልፅ ማስተባበያ ዶ/ር ዳኛቸው በጋዜጣው እንዲወጣ ከማድረጋቸው ባሻገር በፌስቡክ ባሰፈሩት መልእክት « እኔ የብአዴን አባል ብሆን ኖሮ ወረቀት በታኝ ሆኜ የምቀር ይመስላችኋል?. አባል ሆኜ ድምፄ ሳይሰማ የእነ ህላዌና በረከት ስምኦን ወረቀት በታኝ ሆኜ ልቀር አልችልም!» ብለዋል።
ምንጮቹ በማጠቃለያ ያነሱት፥ ፍሬው አበበ «ተከሰሰ» ተብሎ የተራገበውን ሲሆን፣ ከስምንት ወር በፊት የተዘገበን እና አዜብ በግልፅ ከቤተ መንግስት እንደማይለቁ በተነገረለት፣ሚሚ ስብሃቱ ሳይቀር ጠ/ሚ/ር ሃ/ማሪያምን የሚያኮስሥና በአንፃሩ ለአዜብ የወገነ ዲስኩር ማሰማቷና እርሷ ምንም ሳትባል «ጋዜጠኛው ተከሰሰ » የተባለው በአለም አቀፉ ማህበረሰብ ዘንድ ትኩረት ለመሳብ በነበረከት የተቀናበረ « ድራማ» ነው ሲሊ ያጣጥሉታል። ምክንያቱም ሁለት ነው፤ ቀዳሚው በኢትዮጲያ ነፃ ፕሬስ አለ የሚል ስእል በመስጠት እገረመንገዱን <ፍትህ አለ> በሚል እነእስክንድር ነጋ እንዲፈቱ የሚቀርበውን አለም አቀፍ ጥያቄ አቅጣጫ ለማስለወጥ ብሎም «በእነእስክንድር የተሰጠው ውሳኔ በነፃ የህፍትህ አካላት የተወሰነ ነው» ለማለት እንደሆነ ምንጮቹ ያስረዳሉ።