‎የአንድ ጎልማሳ ገንዳ ወግ‎

ከዓለማየሁ ገበየሁ
(በአዲስ አበባ በቁምነገር መጽሔት ላይ ታትሞ የወጣ)

‹‹ እረ ለአንተው ቱ ! ባለጌ ! መተፋት ያለበት ለአንተው ዓይነት ነበር ፡፡ . . . እረ እባክህ አፍንጫህንም መያዝ ትችላለህ እንዴ ? አሁን እንዲህ ለብሰህ ላየህ አዋቂና ጨዋ ትመስላለህ ፤ ይሄኔ ስለ ቆሻሻ ጎጂነት የምታስተምር የሳይንስ መምህር ትሆን ይሆናል . . . ነጭ ጋዋን ለብሰህ ምድረ በሽተኛን የምታመናጭቅ ድሬሰር ወይም ነርስ የማትሆንበትም ምክንያት አይኖርም ፡፡ የዚችን ከተማ ቆሻሻ ነቃቅለን እናጠፋለን ከሚሉ ዲስኩረኛ ፖለቲከኞች ተርታም የምትሰለፍ ቢሆንስ ምን ይገርማል ፡፡ እረ ማዘጋጃ ቤት የጽዳት ፣ ውበትና መናፈሻ ስራ ሂደት መሪም ብትሆን ማን ያውቃል ?

‹‹ እኔ ግን በዚች ሰፈር ካወቅኩህ ስንት ዘመን ተቆጠረ ? ቀን ቀን ‹ ይሄ ገንዳ ሸተተ ! › እያልክ ምራቅህን ትተፋብኛለህ ፤ ገልምጠኀኝ ትሄዳለህ ! አንዳንዴ ደግሞ እንደ ማስቲሽ ንፍጥህ ተጣብቆ አልከፈት በሚለው የተዥጎረጎረ መሀረብህ አፍና አፍንጫህን ለመደበቅ ትጣጣራለህ ፡፡ በል ሲልህ ደግሞ ‹ ቅርናታም ገንዳ ! › እያልክ በብልግና መፈክር ትለማመዳለህ ፡፡ ማታ ማታ ግን ከእኔ በላይ በመጠጥ ቀርንተህ በሁለት እጆችህ ጥርቅም አድርገህ ይዘኀኝ ገላዬ ላይ ስትሸና አንዳችም ነገር አይከረፋህም ፡፡ አስመሳይ – ሰው መሳይ በሸንጎ ! እንዳንተ ዓይነቱን ስንት የሰው ገንዳ ታዝቤያለሁ መሰለህ ?! ይሄኔ የቆለጥህ ማስቀመጫ ጨርቅና ካልሲህን በተናጥልም ሆነ በጥምረት የሚያሸታቸው ቢኖር ‹ እረ ተመስገን ! › የሚባልልኝ እኔ ነበርኩ ፡፡ እውነት እልሃለሁ አንድዬ ለአፍታም ቢሆን እጅ ቢያውሰኝ እንዲህ በነጋ በጠባ ቁጥር ቆሽቴን አታሳርረውም ነበር ፡፡ በሚያምረው ከረባትህ ጎትቼ አስጠጋህና እንደ አርጋው በዳሶ በጭንቅላትህ እቀብርህ ነበር ፡፡ ይሄ የሰው አህያ ! እንደ ወሎ ፈረስ መልክህን ብቻ ከማሳመር ቀፎ ጭንቅላትህ ውስጥ ንቦች ምግብ እንዲሰሩ ምቹ ሁኔታ ብትፈጥርላቸው አይሻላልም ?

‹‹ ጆኒ ቀዌ መጣች ፡፡ ዛሬ ደግሞ እነዚህ የጎዳና ልጆች እያዋከቡት ነው ፡፡ እንደው እኔም ርስት ሆኜ የሰው ዘር በይገባኛል ሲጣላብኝ ያመኛል ፡፡ ይህን ያወኩት እዛ ቆሼ የተባለ ሰፈር ነው ፡፡ ቢያንስ በዓመት ሶስትና አራቴ ቆሼ እንድሄድ ይፈቀድልኛል ፡፡ ለነገሩማ በየሁለት ቀናትና በሳምንት ሂሳብ ነበር ቆሻሻዬ ሊራገፍ የሚገባው ፡፡ አልፎ አልፎ ስሄድ ታዲያ የሰው ልጅ የገንዳ ቆሻሻን የቦሌ – የጉለሌ ፤ የሸራተን – የሂልተን … በሚል ስያሜ ለፍቶ እንዳገኘው ርስት ሲራኮትበት ፤ ጦር ሲማዘዝበት እመለከታለሁ ፡፡ በእውነት ይሄ የዘርና የጎሳ አስተሳሰብ ቆሻሻ ድረስ መዘርጋቱ ያሰቅቃል ፡፡ ማቲው ብቻ ሳይሆን ነፍስ ያወቀው ሁሉ ‹ ምርጥ ምግብና ምርጥ ዕቃ › ለመሰብሰብ ዘወትር ቡጢውን ሌላው ላይ መወርወር ግዴታው ሆኗል ፡፡ አንዱ አገልግሎቱ ስላበቃ ወይም ስለቆሸሸ ብሎ የጣለውን ሌላው እንደ ብርቅ ማዕድን ቆፍሮ ለማውጣት መታከቱ ያስቆዝማል ፡፡

‹‹ ታዲያ ጆኒ የሚገርመኝ የሚፈልገው የብዕር ቀፎና ማስመሪያ መሆኑ ብቻ ነው ፡፡ እነዚህ ኩይሳዎች እንኳ ላዬ ላይ ወጥተው የሚቦጠቡጡት የተራረፈ ምግብ ፍለጋ ነው ፡፡ ታዲያ ለማይገናኘው ፍላጎታቸው ለምን አጉል ይናከሳሉ ? እውነት ይሁን ውሸት ያበደውም ከቆሻሻ ጋር በተያያዘ ምክንያት ነው ይባላል ፡፡ ከቴክኒክና ሙያ ኮሌጅ እንደተመረቀ የከተማው ቆሻሻ እንደ ችግር ሳይሆን እንደ ድሃ አጋር ሊታይ የሚችልበትን ‹ አንድ – በአራት › የተባለ ልዩ የፈጠራ ፕሮጄክት አቅርቦ ነበር ፡፡ ከቆሻሻ አግሮ ስቶን ፣ ነጭ ከሰል ፣ ባዮ ጋዝ እና የካኪ ፌስታል ለመስራት ፡፡ ጉዳዩን ያዳመጡት የሚመለከታቸው ወገኖች ‹ ፕሮጄክትህ ግማሽ እውነት – ግማሽ እብደት የተቀላቀለበት ነው › በማለት አጣጣሉበት ፡፡ እየቆየ ሲሄድ ግን አንዳንድ የፈጠራ ሰዎችና ባለሀብቶች ከጥቅሉ ፕሮጄክት አንድ አንዱን እየመዘዙ ጥቅም አነደዱበት ፡፡ ቀስ በቀስ ደግሞ ‹ ለምን ? እንዴት ? ፍትህ የለም ! › ማለት ያበዛው የጆኒ ጭንቅላት ነደደ አሉ ፡፡ ጆኒ ግን ያሳዝነኛል ፡፡ የጸዳ ነጭ ወረቀት ማለት ነው – ተንኮል ፣ ጥላቻም ሆነ እብሪት አይንጸባረቅበትም ፡፡ በዚህ ለጋ እድሜውም ማበድ አልነበረበትም ፡፡ በርግጥ በሽተኛን ደጋግሞ በማመናጨቅ የሚታወቁት ሀኪሞች በትኩረት ደጋግመው ቢያክሙት ይድናል ፡፡ ጆኒን በትኩረት ቢያጤኑት ሊማሩበትም ይችላሉ ፡፡ ምነው ብትሉ አንድም ቀን ተሳስቶ በአካባቢዬ ሽንቱን ሸንቶ አያውቅም ፡፡

‹‹ ምስኪን ! ከእነዚህ እርጉሞች ጋር ላለመጣላት ነው መሰለኝ አቅጣጫውን ቀየረ ፡፡ መጡ እነዚህ ከፈሳቸው ጋር የተጣሉ ! ዘለው አናቴ ላይ ወጡ ! መነቀሩኝ ! አቤት አስፋልቱ በአንድ አፍታ ቄጤማ ተጎዘጎዘበት ፡፡ ፈንዲሻ ተረጨበት . . . ዕጣን ተለኮሰበት . . . ደስ ይላቸዋል ልበል ?! አልናገርም ፣ አልሰማም ፣ አላይም በሚል ፍልስፍናው የሚታወቀው የአዲስ አበባ ነዋሪም ይፈራቸዋል መሰለኝ አይገስጻቸውም ፡፡

‹‹ ታዲያ ምነው ሮጡ ? . . , አሃ ! ድንጋይ ወርዋሪዋን ወይዘሮ ተካበች አይተው ነው ፡፡ የእኚህ ሴትዮ ልብና በሁለት ገጹ የሚለበስ ጃኬት አንድ ናቸው ፡፡ ሴትየዋ ቀን ቀን ሰው እንዲያያቸው ይህን የመሰለ ልማታዊ ተውኔት ይሰራሉ ፡፡ ሰው አይደለም ውሾች ቆሻሻውን ሲመነቅሩ ዝም አይሉም ፡፡ በጩኀትም ሆነ በፉጨት በል ሲላቸውም ድንጋይ በመወርወር ያካልቧቸዋል ፡፡ ይህ ተግባራቸው ግን አንዳንዴ የከፋ ጉዳት ይዞ ሊመጣ ይችላል ፡፡ አንድ ግዜ የሆነውን ማንሳት ጥሩ ነው ፡፡ የተራቡ ይሁኑ ስሪያ የጨረሱ በርካታ ውሾች ገንዳውን ሲሞነጭሩ በመድረሳቸው ድንጋይ ማዝነብ ጀመሩ ፡፡ ኤፍ ኤም 97.1 ጠዋት ጠዋት ከሳጅን መዝገቡ ጋር አዘውትሮ የሚያሰማውን የትራፊክ ዘገባ ማዳመጥ ከማይመቻቸው ውሾች መካከል ሶስቱ በደመነፍስ ሲካለቡ የትልቅ መኪና ጎማ ደፈጠጣቸው ፡፡ አንድ ቀን ሙሉ ከአስፋልት ማንም ሳያነሳቸው ከተዘረሩ በኃላ መሽተት ሲጀምሩ ወይዘሮ ተካበች የጎዳና ተዳዳሪዎችን አሰባስበው እኔ ጀርባ ላይ እንዲወረወር አደረጉ ፡፡ አቤት ለአንድ ሳምንት የነበረው የአካባቢ ቅርናት ! አቤት ጭንቅላቴን የወረረው የግማት ጥቃት ! ያኔ ጋዜጠኞችን ጠርቼ ጥልቀት ያለው መግለጫ ብሰጥ እደሰት ነበር ፡፡ እረ የሬዲዮ የአየር ሰዓት ገዝቶ የመዘባረቅ ሀሳብ ሁሉ የመጣብኝ ያኔ ነው ፡፡

‹‹ ታዲያ እኚህ ተዋናይ ሴትዮ ዱሪዬዎችንም ሆነ ውሻዎችን ካባረሩ በኃላ ወጪ ወራጁ እንዲሰማቸው የፈጸሙትን ገድል ለደቂቃዎች ይተርካሉ ፡፡ የንግግራቸው ቃናም ሆነ የአካላቸው እንቅስቃሴ ግዜያዊ መድረክ ላይ ያለ አይመስልም ፡፡ በጣም የሚገርመው መነባንቡን የትና መቼ እንደሚያጠኑት ነው ፡፡ ማታ ማታ ሌላ ናቸው ፡፡ የራሳቸውን የጠላ ድፍድፍ ፣ ለሌሎች ተቀጥረው ደግሞ የአትክትልና ፍራፍሬ ልጣጭና ብስባሽ በኔ ዙሪያ ይቆልላሉ ፡፡ ጠዋት ሲነጋ ከሁሉ ቀድመው ‹ አበስኩ ገበርኩ › ን የሚያዜሙት እሳቸው ናቸው ፡፡

‹‹ እኔ የምለው ይህ የከተማ ህዝብ እስከመቼ ነው የምናገባኝ ፖሊሲውን የሚያራምደው ? አንድ ሰሞን በጉንፋንና ኮሌራ ፣ በትውከትና ተቅማጥ ልጆቻችንና እኛ ማለቅ የለብንም ፣ በየአካባቢያችንም በቂ ገንዳ ሊቀመጥ ይገባል በማለት ጩኀቱን አቀለጠ ፡፡ ፊደል የቆጠሩትም ለከተማ እድገት የጽዳት አጠባበቅ አስፈላጊ መሆኑን የሌሎች ሀገሮችን ልምድ በመጠቃቀስ መንግስት ከእንቅልፉ እንዲነቃ ጎተጎቱ ፡፡ የሁሉም ሀሳብ ትክክል ስለነበር እኔና ጓደኞቼ ሰፈር ከተማውን አጥለቀለቅነው ፡፡ ምን ዋጋ አለው ታዲያ ? ጩኀቱ ቆሻሻውን ለመድፋት ብቻ ሆነ ፡፡ ገንዳው ሲሞላ እንዲነሳ ማን ይጩህ ? በግምና ክርፋት አየር ውስጥ ያለመኖር መብታችን ይከበር ! ማን ይበል ?

‹‹ አስተዳዳሪዎቹ በምርጫ ሰሞን ‹ መልካም አስተዳደር እናሰፍናለን ! ህዳሴውን እናረጋግጣለን › ሲሉት ለምን በተጨባጩ ቆሻሻ አያፋጥጣቸውም ፡፡ ሚዛን አትደፋም ተብላ በማትጠቀሰው ቆሻሻ ተግባራዊ ማንነትን መለካት ይቻላል ፡፡ ለምሳሌ አስተዳደሩ የከተማውን ጉድፍ አይደለም በማዘጋጃ ዙሪያ የሚታየውን ሽንትና አይነምድር ማጽዳት አልቻለም ፡፡ የአውሮፓዎችን መንግስታዊ አስተዳደር ቀምሮ ቢያስፋፋ ኖሮ ስንት ግዜ ስልጣኑን በፈቃዱ በለቀቀ ነበር ፡፡

‹‹ ይኀው ስንትና ስንት ዓመት በጀት መመደቢያና መዝጊያ ላይ ፣ የግማሽ ዓመት ስራ አፈጻጸም ላይ አዳዲስ ነገሮች እናዳምጣለን ፡፡ መፍትሄው እጃችን ሊገባ አንድ ሀሙስ ቀርቶታል ይሉናል ፡፡ በምን ይሆን ከተባለ
. የውበትና ጽዳት ተቋም መፈልሰፉ
. የደረቅ ቆሻሻ አስተዳደር መቋቋሙ
. ባለ በርና ባለጎማ ገንዳዎች እየተሰሩ መሆናቸው
. ገንዳ የማንሳት ተግባር 24 ሰዓታት ሙሉ እንደሚከናወን
. ደረቅ ቆሻሻ ወደ ጠቃሚ ግብዓት የሚቀየርበት አሰራር መፈጠሩ
. የደረቅ ቆሻሻ የቆየ ችግር በተደራጁ ማህበራት እንደሚንበረከክ ይነገራል ፡፡ ይህ ዓይነቱ የወረቀት ዲስኩር ከጆኒ ቀዌ ፕሮፖዛል በምን ይሻላል ? አስተዳደሩ ከጆኒ ቀዌ የሚለየው አንደኛውን ጨርቁን ጥሎ አለመታየቱ ነው ፡፡

‹‹ በርግጥ አስተዳደሩ ከተማዋ ለአፍሪካ ህብረት መቀመጫነት አትመጥንም የሚል የሰላ ትችት በውጭ ሰዎች ድንገት ሲቀርብ የሆነ ነገር ለመስራት ተፍ ተፍ ይላል ፡፡ ለልምድና ተሞክሮ ልውውጥ የጽዳት ሰራዊቱን በምድረ አፍሪካ ይበትናል ፡፡ አንድ ሰሞን ኪጋሊ ደርሶ የመጣው ልዑክ ጆሮአችንን አደንቁሮት ነበር ፡፡ ‹ እውነት ሰው በላዋ የሩዋንዳ ከተማ እንደዚህ ውብ ናት ? › የሚለው ግርምት ከልክ በላይ ተጭኖብን ነበር ፡፡ ሰው በጦርነት ሲበላ የከረመ ከተማ የኃላ ኃላ በውበት የሚልቅ እስኪመስል ድረስ ፡፡ እንዲህ ከሆነ ደግሞ አዲስ አበባ የኪጋሊ አቻ ለመሆን የቀረበች ናት ፡፡ የቀይና ነጭ ሽብር ባለታሪክ ናትና ፡፡

‹‹ የጽዳት ሰራዊቱ ግብም በአንድ ተጨባጭ ለውጥ እንደሚደመደም ተገምቶ ነበር ፡፡ ግን የዚህን ሀገር ተግባር አውሎ ንፋስና ማዕበል ሳይሆን ወሬ ነው የሚበላው ፡፡ ይባስ ብሎ በቅርቡ ደግሞ በጥናት ሳይሆን በአውሎ ንፋስ የመጣ የሚመስል ዜና የከተማዋን ኃላፊዎች አሙቋቸዋል ፡፡ ሎንሊ ፕላኔት የተባለ ዓለማቀፍ የጉዞና አስጉበኚ መጽሀፍ ካምፓኒ አ/አ በ2013 ሊጎበኙ ከሚገባቸው አስር የዓለማችን ከተሞች አንደኛዋ ናት በማለት ምስክርነቱን ሰጥቷል ፡፡ ይሄን ያልኩትም ከተማዋ ፈጣን እድገት እያሳየች በመሆኑ ነው ብሏል ፡፡ መቼም ይህ ድርጅት የሀገር ውስጥ ጋዜጣ ቢሆን ኖሮ ሚዛን ያልጠበቀ ዜና በማሰራጨቱ ፍ/ቤት ሊቆም አሊያም ሊታገድ በቻለ ነበር ፡፡ ደግነቱ ስምን መልዓክ ያወጣዋል የሚል አባባል መኖሩ ፡፡ ሎንሊ ወይም ብቸኛው ድርጅት ያወጣውን ዘገባ ሌሎች አልደገፉትም ፡፡ ‹ ብቻህን ተወጣው ! › የተባለ ይመስላል ፡፡ እረ ‹ ፈረንጁ ዋልታ ማዕከል ! › ያሉትም ሳይኖሩ አይቀርም ፡፡ ብቻ ብዙ የሚጋጩ ነገሮች ስላሉ ከእንቅፋቱም ከነገሩም ላለመላተም ግራና ቀኝ እያስተዋሉ መጓዝ ይበጃል ፡፡ ለምሳሌ ባለስልጣኖች የሚፈሩት ፎርበስ / Forbes / አዲስ አበባ የዓለማችን ስድስተኛዋ ቆሻሻ ከተማ መሆኗን ነው በቅደም ተከተሉ የሚያሳየው ፡፡ ይህ አይነቱ መረጃ ከሎንሊ አይደለም ከሞተው ብሩስሊ ጋር ካራቴ አያማዝዝም ?

‹‹ አዲስ አበባ ትንሳኤ ማግኘቷን ታረጋግጥ የነበረው ያ ማነው ; . . . ጉዳዬ ሳይሞላ እያለ ያዜመው . . . እ . ጋሽ አበራ ሞላ እንዳጀማመሩ ቢዘልቅበት ነበር ፡፡ ልብ በሉ ! አበራ ሞላ ሲያንጽ የነበረው ጽዳት ብቻ አልነበረም ፡፡ የአስተሳሰብ ለውጥና ውበትንም ጭምር እንጂ ፡፡ በከተማችን ስንት ሞተው ኀውልት የቆመላቸውን ቦታዎች አይደለ አንዴ እንደ ፈጣሪ . . . ‹ እፍ ተነሱ ብርሃን አግኝታችኃል › እያለ ያነቃቸው ፡፡ ካድሬዎች ግን በግምገማቸው አበራ ሞላ በከተማዋ ያበዛው ማሰሮና መፈክር ነው ማለታቸው ተሰምቷል ፡፡ እረ በሀገራችን ታሪክ መፈክር አብዝቶ የማያውቅ መንግስት ነበር እንዴ ? መፈክሩስ ያን ያህል እየበሉ የተኙ አስተዳዳሪዎችን አብሽቋል ? ግራ የሚያጋባ ነው ፡፡ እስኪ አንድ አራቱን እናስታውስ !
. ቆሻሻ ወዮለት !
. የሸና ይሸነሸናል !
. ጽዳት ሲለካ ስልጣኔ ነው ለካ ?!
. የአበራ ሞላ እንባ ፈሶ አይቀርም !

‹‹ ምናልባት የመጨረሻዋ ?! ድርጅቱ አንደኛ ከሰብዓዊ ሰዎች ይልቅ ግእዙ ግንባር ደምቆ እንዲጠራ ነው የሚፈልገው ፡፡ በግምገማው ላይ ለመሆኑ እንዲህ ከመሬት ተነስቶ የጀገነው አበራ ማነው ? የት ነበር ? የኃላ ታሪኩ ምን ያመለክታል ? እውነተኛ ፍላጎቱ ምንድነው ? የሚሉ ጥያቄዎች በጉልህ ተነስተው የማያዳግም ምላሽ እንዳገኙ ይገመታል ፡፡ ሁለተኛ ጋሽ አበራ የሚዳክረው በሀገር ተቆርቋሪነት እንጂ በድርጅት መስመርና አቅጣጫ አይደለም ፡፡ ታዲያ ይህን በፍትሃዊና ዴሞክራሲያዊ መንገድ በህዝብ ያልተመረጠ ዜጋ ለማድነቅ እንዴት ይመቻል ? ውጤቱስ ከአሳጭነቱ አኳያ እንዴት ይመዘናል ? ጥያቄው እነዚህና የመሳሰሉት ናቸው ፡፡ ግራም ነፈሰ ቀኝ ለበኃላ የተሞክሮ ቅመራ እንዲያመች ሳያደናቅፉት መመልከት አሊያም ቀረብ ብሎ መደገፍ ሲገባ ጠላልፈው ጣሉት ፡፡ የተቀደሰ ሀሳቡን ቀምተውት እንኳ የእሱ ጎዳናን መጨረስ አለመቻል ያሳዝናል ፡፡

‹‹ የከተማው አስተዳደር መቋቋምና ማሸነፍ ካልቻለባቸው ጉዳዮች አንዱ ጽዳት መሆኑ ይታወቃል ፡፡ ብሎ ብሎ ሲያቅተው ደጋግሞ የሚያነሳት ምክንያት ‹ ህዝቡ የአስተሳሰብ ለውጥ ሊያመጣ አልቻለም ! › የምትል ናት ፡፡ የአስተሳሰብ ለውጥ እንዴት ሊመጣ እንደሚችል ግን የጠለቀ ግንዛቤ ያለው መሆኑ ያጠራጥራል ፡፡ ገንዳዎች በየአደባባዩ ከተቀመጡ ሰዎች በአካባቢው ይሸናሉ በሚል ወደ መንደር ማራቅ ተጀምሮ ነበር ፡፡ ግን ገንዳዎች ባይኖሩም የከተማችን ግንቦች ዛሬም በቀንም ሆነ ማታ እንደጉድ ይሸናባቸዋል ፡፡ ይህን ችግር ጠልቆ ያለመረዳት ነው ስንኩልና ፡፡ እንኳን ሽንት ቤት መኖሪያ ቤት የሌለው የከተማ ህዝብ ጭንቀቱን የት ይክፈል ? አስተዳደሩ በየቀበሌውና በየሰፈሩ ደረጃቸውን የጠበቁ መጸዳጃ ቤቶችን መገንባት ቢኖርበትም አላደረገውም ፡፡ ጥቃቅንና አነስተኛ ሱቆችን በየቦታው እንደ አሸን ሲያፈላ ለሽንት ቤት ግን ቦታ የለኝም ይላል ፡፡ ያሉትን ክፍት ቦታዎች በሙሉ በሰብዓዊነት ሳይሆን በገንዘብ ጭንቅላት እያሰበ ግንባታ እንዲጥለቀለቅባቸው ያደርጋል ፡፡ ለልማት ግንባታ የማይደረግ ነገር የለም በሚል ለመንገድ ግንባታ ቤቶችን ያፈርሳል ፡፡ ሽንት ቤት ለመገንባት ለምን ቤቶች እንዲፈርሱ አይደረግም ? ይህ ነው የአስተዳደሩ የአስተሳሰብ ችግር ፡፡ ልማት ማለት አስፓልትና ኮንዶሚኒየም ብቻ ነው ? በአምስት ዓመቱ እቅድ ላይ የጤና ነገር ትልቅ ቦታ እንዳለው ነው የሚታየው ፡፡ በጤና ፖሊሲው ላይ 16 የሚደርሱ ትላልቅ የጤና ፓኬጆች ተቀምጠዋል ፡፡ የግለሰብና የአካባቢ ጤና ጉዳይ ከዚህ ውስጥ በመፍራሙ ደምቆ ይታያል ፡፡ ይህ ማለት ታዲያ በቂ መጸዳጃ ፣ በቂ ገንዳ ፣ በቂ የጽዳት አስተዳደር ማለት አይደለም ፡፡ ይህን ድብቅ ማንነት ሳይገላለጹ ህዝብን በአስተሳሰብ ችግር መገሰጽ የት ያደርሳል ? ይኀው እንደምናየው የትም ! እረ ልማትስ የሚፋጠነው ጤነኛ ዜጋ ሳይፈጠር ነው ? ጽዕዱ ማህበረሰብም በፖለቲካው ረገድ ክብር እንዳለውም መገንዘብ ያስፈልጋል ፡፡

‹‹ ለማንኛውም ገንዳን ለማጽዳት ፍትሃዊ ፣ ግልጽና የጸዳ አስተሳሰብ ያስፈልጋል ፡፡ ይህን ሃሳብ በተጠማዘዘ መንገድ ላስረዳ ፡፡ አስተዳደሩ በስሪቱ ውስጥ የወይዘሮ ተካበች አይነቶችን በብዛት ከመቆለልና ከመካብ ፤ የጆኒ ቀዌ አይነቱን እያከመ ፣ እየደገፈና የስራ ነጻነታቸውን እያረጋገጠ ቢቀጥል ያዋጣዋል ››

Hailu Shwel
Previous Story

“‘አማራ ኬላ’ የሚባሉ አምስት ቦታዎች አሉ፣ የአማራ ተወላጆች በነዚህ ኬላዎች አያልፉም” – ኢንጂነር ኃይሉ ሻውል

eyehealth
Next Story

Health: ጤናማ ሆኖ ለመቆየት 6ቱ ምርጥ ጥቆማዎች

Latest from Blog

ህገ መንግስታዊ ዲዛይን ምርጫዎቻችን የትኞቹ ናቸው?

ኤፍሬም ማዴቦ (emadebo@gmail.com ) እኛ ኢትዮጵያዊያን እራሳችንን ስንገለጽ የረጂም ግዜ ሥልጣኔና ታሪክ ያለን፣በነጭ ያልተገዛን፣ከ2000 አመት በላይ ተከታታይ የመንግስት ሥርዓት ያለን፣የሦስቱ ዘመን ያስቆጠሩ አብርሃማዊ ሃይማኖቶች አገር ነን እያልን ነው። ነገር ግን ባለፉት ሃምሳ አመታት

የኢካን ዓላማ በኔዘርላንድ የሚኖረውን ትውልደ ኢትዮጵያውያንን እና ኢትዮጵያውያንን ኮምዩኒቲይ የማሰባሰብ ሳይሆን የመከፋፋልና የማዳከም ተልኮን ያነገበ ነው።

አገር ! ለየአንድ ሠው ቋንቋው፣ ልማዱ፣ ባሕሉ፣ እምነቱ፣ አስተሳሰቡ፣ ወጉና በአጠቃላይ እሱነቱና ማንነቱ የሚከበርበት ብቸኛ ሥፍራ ነው። ኢትዮጵያውያንም በስደት በሚኖሩባቸው አገራት ሁሉ እነኝህን በስደት ያጧቸውን የግልና የጋራ ማንነቶቻቸውን በአንድ ላይ ሆነው ለመዘከር

ፋኖ ምሽጉን ደረመሰው ድል ተሰማ | ” ስልጣን እለቃለሁ ” ፕረዚዳንቷ | ህዴድ ድብቅ ስብሰባ በአዲስ አበባ | “ተመስገንን በመዳፌ ስር አስገብቼዋለሁ” አብይ

-966+9-የኦህዴድ ድብቅ ስብሰባ በአዲስ አበባ “ተመስገንን በመዳፌ ስር አስገብቼዋለሁ” አብይ – ስልኩ ተጠለፈ “እኛ የምን’ዘጋጀው ለፋኖ ሳይሆን ለኤር-ትራ ነው” አበባው|”በጊዜ ቦታ አዘጋጁልኝ” አረጋ

አንድ በኢኮኖሚና በሌሎች ነገሮች ወደ ኋላ የቀረች አገር አንድን ኃያል መንግስት በመተማመንና ጥገኛ በመሆን ኢኮኖሚያዊ ዕድገትን ማምጣትና የተሟላ ነፃነትን መቀዳጀት ትችላለች ወይ?

ፈቃዱ በቀለ(ዶ/ር) ሰኔ 4፣ 2016 (ሰኔ 11፣ 2024)   በዚህ አርዕስት ላይ እንድጽፍ የገፋፋኝ ዋናው ምክንያት ሰሞኑኑ ዶ/ር ዮናስ ብሩ የቻይንንም ሆነ የቬትናምን በኢኮኖሚ ማደግ አስመልክቶ ሁለቱ አገሮች እዚህ ዐይነቱ የዕድገት ደረጃ ላይ ሊደርሱ የቻሉት ከአሜሪካ ጋር

ፋኖ አንድ ሌሊት አያሳድረንም” የአማራ ብልፅግናየኢሳያስ ግዙፍ ጦር ወደ ወልቃይት

ፋኖ አንድ ሌሊት አያሳድረንም” የአማራ ብልፅግናየኢሳያስ ግዙፍ ጦር ወደ ወልቃይት አብይና ዳንኤል ክብረት ጉድ አሰሙ-|ጀነራሉ በቁ*ጣ ተናገሩ-‘ህዝቡ ጉድ ሰራን’-|“ብልፅግናን ራ*ቁቱን አስቀርተነዋል”-|ታዳሚው ባለስልጣናቱን አፋጠጠ
Go toTop