May 2, 2013
30 mins read

ምርጫ የለም እንጂ ምርጫማ ቢኖር …!

በፍቅር ለይኩን

የዛሬው ጽሑፌን በምርጫ ዙሪያ ካጋጠመኝ ትንሽ ቆየት ካለ ገጠመኜ ልጀምር፡፡ በደቡብ አፍሪካዊቷ ቢዝነስ ከተማ ጆሐንስበርግ፣ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በትውልድ ደቡብ አፍሪካዊ የሆኑ ካህን፣ አባትና አገልጋይ የሆኑ በ60ዎቹ መጨረሻ ዕድሜ ላይ የሚገኙ አንድ አዛውንት አባት አሉ፡፡

እኚህ አዛውንት ካህን ስማቸው ፋዘር ዲሊዛ ኔልሰን ቫሊዛ ሲሆን፤ በኢትዮጵያውያን የቤተ ክርስቲያኒቱ አገልጋዮችና ምእመናን ዘንድ ደግሞ በክህነት የማእረግ ስማቸው መልአከ ሰላም ዲሊዛ ቫሊዛ በመባል ይጠራሉ፡፡ ታዲያ ፋዘር ዲሊዛ ባገኙት አጋጣሚ ሁሉ ስለ ኢትዮጵያ፣ ስለ ኢትዮጵያውያንና ስለ ኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን አውርተው፣ ተናግረው የሚጠግቡ ሰው ዓይነት አይደሉም፡፡

ከኬፕታውን ከትምህርት ቤት በመዘጋቱ ለእረፍት ወደ ጆሐንስበርግ መጥቼ ነበር፡፡ በጆሐንስበርግ መድኃኔ ዓለም ካቴድራል በነበረኝ የመንፈሳዊ አገልግሎት ቆይታዬም ከእኚህ አዛውንት አባት ጋር ከመንፈሳዊና ከሃይማኖታዊ ጉዳዮች ባሻገርም በበርካታ በአገራችንና በደቡብ አፍሪካ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ጉዳዮች ላይ በተለያዩ አጋጣሚዎች አብዝተን እንወያይ ነበር፡፡

ፋዘር ዲሊዛ በየትኛው አጋጣሚ ለሚያገኟቸው ኢትዮጵያውያንም ሆነ የውጭ አገር ዜጎች ሁሉ አዘወትረው የሚናገሩት አንድ ነገር አለ፡፡ ይኸውም ለዛሬው ነፃነታችን፣ ሰላም፣ ዲሞክራሲ፣ የዘረኝነት መድሎ ለሌለበት ፍትሐዊ ሥርዓት እውን መሆን እናንተ ኢትዮጵያውያንና የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ትልቅ ድርሻ አላችሁ በማለት በአድናቆትና በልዩ የደስታ መንፈስ ውስጥ ሆነው ምስክርነታቸውን ባገኙት አጋጣሚ ሁሉ ይሰጣሉ፡፡

በአንድ ወቅት ከፋዘር ዲሊዛ ጋር ባደረግነው ውይይት እኚህ አዛውንት አባት በአገራቸው ደቡብ አፍሪካ ለሚካሄደው የአካባቢ ምርጫ (Local Government Election) ከጆሐንስበርግ ከ1000 ኪ.ሜ. በላይ ወደሚርቀው የውቅያኖስ ጠረፏ የትውልድ አገራቸው ፖርት ኤልዛቤት ለመሄድ በዝግጅት ላይ እንደሆኑ አንዳች ጉጉት በሚንጸባረቅበት ልዩ ስሜት ውስጥ ሆነው አጫወቱኝ፡፡

እኔም በመገረም ሆኜ እንዴ …! ፋዘር እንዴት ለአካባቢ ምርጫ ሲሉ ይህን ያህል ርቀት፣ ይህን ያህል ብዙ ብር የትራንስፖርት ወጪ አውጥተው ይሄዳሉ?! ደግሞስ እርስዎ አሁን አርጅተዋል፣ ለምን እንዲህ በመንገድ ይደክማሉ፤ ባለቤትዎና ልጆችዎ ከመረጡ በቂ አይደለም እንዴ …?! አልኳቸው፡፡

አዛውንቱ ካህን ለምርጫ ወደ ትውልድ መንደራቸው ለመሄድ ጓዛቸውን እየሸከፉ መሆናቸውን መስማቴና እርሳቸውም የጉዞአቸውን ስላረጋገጡልኝ በጣሙን ግርምትም አድናቆትም አጭሮብኝ፡፡ ፋዘር ዲሊዛ ግርምት ለተሞላበት ጥያቄዬና አስተያየቴ ሲመልሱልኝም፡-

አይ ልጄ ይህ የመምረጥም ሆነ የመመረጥ መብቴ በብዙ ዋጋ፣ በእልፎች ክቡር ደምና መሥዋዕትነት የተገኘ ልዩ መብት ነው፡፡ ሌላው ቀርቶ ከእናት ቤተ ክርስቲያናችን ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ጋር ፈጽሞ እንዳንገናኝ ዘረኛው የአፓርታይድ መንግሥት የገነባው የመለያየት ግንብ የተናደው ፓርቲዬ ኤ.ኤን.ሲ፣ በበርካታ የደቡብ አፍሪካውያን የነፃነት ፋኖዎች እና ለሰው ልጆች ነፃነትና እኩልነት ቀናኢ በሆኑ እንደ ኢትዮጵያ ባሉ አገሮችና ሌሎች አጋሮቻችን ጭምር ነው፡፡

እናም ልጄ በዚህ ምርጫ በመምረጥም ሆነ በመመረጥ ለመሳተፍም ሆነ ላለመሳተፍ አንተ እንደምትለው የዕድሜዬ መግፋት፣ በቦታ ርቀት፣ በገንዘብ ወጪ ፈጽሞ የሚተመን አይደለም፡፡ ይህ በምንም በማይተመን በብዙዎች የሕይወት መሥዋዕትነት የተገኘ ልዩና ክቡር መብት/መብቴ ነው፡፡ እናም መብቴን በሕይወት እሳካለሁ መጠቀም አለብኝ፡፡

አየህ አሉኝ ፋዘር ዲሊዛ ንግግራቸውን በመቀጠል በአትኩሮት እየተመለከቱኝ አየህ ልጄ የእኔ አንድ ድምፅ ለፓርቲዬ ድልም ሆነ ሽንፈት ወሳኝነት አለው፤ ስለሆነም ለዘመናት ለታገልንበትና የበርካታ አባቶቻችን ክቡር ሕይወት ተከፍሎበት አገሬ ደቡብ አፍሪካ ዛሬ ለደረሰችበት ሰላም፣ ብልጽግና፣ ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ሂደት እውን መሆን ማረጋገጫው በዚህ ያለማንም አስገዳጅነት በራሴ ፍላጎት፣ ወድጄና ፈቅጄ የምሳተፍበት ይህ ፍትሐዊ የሆነ የአካባቢ ምርጫ አንዱ ነው፡፡

እናም ልጄ ምንም ተአምር ቢፈጠር በሕይወትና በጤና እሳካለሁ ድረስ ለምርጫ ወደ ትውልድ መንደሬ ከመሄድ የሚያግደኝ ነገር አይኖርም በማለት ፈርጠም ብለው መለሱልኝ፡፡ አዛውንቱ ካህን በዚህ የዕድሜያቸው መጨረሻ እንኳን በስስት የሚያዩት የመምረጥና የመመረጥ መብታቸው ላይ ያላቸው ስሱነትና ፖለቲካዊ ንቃታቸው (Sensitivity and political consciousness) በእጅጉ አስገረመኝ፣ አስደመመኝም፡፡

በፋዘር ዲሊዛ ቫሊዛ መልስ የበዛ አድናቆትና ግርምት የተጫረብኝ ኢትዮጵያዊው እኔ ወደኋላ ዘወር ብዬ በበርካታ አፍሪካ አገሮችና በመላው ዓለም የነፃነት ሰንደቅ ተደርጋ በምትታየው ኢትዮጵያ፣ የአገሬን የምርጫ ታሪክና ዲሞክራሲዊ ግንባታ ሂደት ለመታዘብ ይህ ጥቂት የቆየ ገጠመኜ ዕድሉን ፈጠረልኝ፡፡ እናም ከዚህ ገጠመኜ በመነሳት ይህችን አጠር ያለች ትዝብት አዘል ጽሑፍ ባለፉት ሁለት ሳምንታት በተካሄዱት የአካባቢ፣ የቀበሌና የወረዳ ም/ቤቶች ምርጫ ዙሪያ በመመርኮዝ ጥቂት ነግሮችን ለማለት ወደድኩ፡፡

በዘመኔ የደረስኩበት፣ በሙሉ ልቤ የምመሰክርለትና በንቃትም የተከታተልኩት ምርጫ ቢኖር በአገር አቀፍ ደረጃ ተካሄደው የ1997ቱ ምርጫ ነው፡፡ ከዛን በፊት ስለ ምርጫ፣ ስለ መምረጥና ስለ መመረጥ መብት ለማወቅም ሆነ ለማገናዘብ የነበረኝ ፖለቲካዊ ንቃትና ዕድሜዬም ደረጃም ብዙም የሚፈቅድልኝ አልነበረም፡፡ እናም የትዝብቴ ዋና ትኩረት የሚሆነው ምርጫ 97ን ተመርኩዞ ከሰሞኑ በተካሄደው የአካባቢናና የወረዳ ምክር ቤት ምርጫ ላይ ነው፡፡

በዘንድሮው የአካባቢና የወረዳ ምክር ቤት ምርጫ ላይ በጥቂቱ ትዝብቴን ለማካፈል የ1997ቱን ምርጫ እንደ መነሻ ወይም መንደርደሪያ አድርጌ ለመውሰድ የተነሣሁበት የራሴ የሆነ ምክንያት ስላለኝ ነው፡፡ ከላይ ለመጥቀስ እንደሞከርኩት የ1997ቱ ምርጫ በእኔ ብቻ ሳይሆን በብዙ ኢትዮጵውያን ልብ ውስጥ የማይረሳ ውብም አስቀያሚም የሆነ መቼም ማይረሳን ትዝታ ትቶ አልፏል፡፡

1997ቱ ምርጫ ምንም እንኳን ፍጻሜው ባያምርም የምርጫው ጅማሬና ሂደት መላው ኢትዮጵያውያንን ከሊቅ አስከ ደቂቅ፣ ከአፈ ነቢብ እስከ ምሁር፣ አለቃን ከምንዝር ሳይለይ ሁሉንም ኅብረተሰብ ክፍል ያሳተፈ ምድሪቱን ከዳር እስከ ዳር ያነቃነቀና መላውን ዓለም ጭምር ያሰደመመ ነበር፡፡

ሚንጋ ነጋሽ የተባሉ ኢትዮጵያዊ ምሁር Ethiopia’s Post Election Crisis: Institutional Failure and The Role of Mediation በሚል አርዕስት በደቡብ አፍሪካ ጆሐንስበርግ ከተማ በሚገኘው Witwatersrand ዩኒቨርስቲ ባቀረቡት የጥናት ወረቀታቸው፣ ምርጫ 97 በአገራችን ምርጫ ታሪክ ውስጥ ትልቅና ጉልህ የሆነ ታሪካዊ ክስተት ሆኖ ማለፉን እንዲህ በማለት ነው በጥናታዊ ጽሑፋቸው የገለጹት፡-

The 1997 elections marked an historic event in the country, as Ethiopia witnessed its first genuinely competitive campaigns period with multiple parties fielding strong candidates.

 

በወቅቱ ምርጫውን የታዘበው ካርተር ምርጫ ታዛቢ ቡድን ማእክልም ባወጣው ባለ 69 ገጽ ሪፖርቱ እንደገለጸው፣ በምርጫ 97 ወቅት ኢትዮጵያውያን በአጠቃላይ የነበራቸውን ሁሉን አቀፍ ሕዝባዊ ተሳትፎና ትልቅ መነቃቃት በተመለከተ ሲገልጽ፡-

The May 2005 election was started against the backdrop of tensions and unprecented level of public political consciousness. … Voters had a genuine choice in Election Day and responded with enthusiasm and high turnout. 

1997ቱ ምርጫ አንፃር የዘንድሮውን ምርጫ ሂደት የታዘቡ ብዙዎች ዋ ምርጫ!፣ ዋ የምርጫ ፉክክርና ውድድር!፣ ወይ የምርጫ ነገር፣ ወይ ነዶ … በማለት ቁጭታቸውንና ብሶታቸውን የገለጹበትን አጋጣሚ ትቶ ነው ያለፈው፡፡ አንዳንዶችም በማኅበራዊ ድረ ገጾች ባሰነበቡት ምጸትን የተሞላ ሰም-ለበስ ግጥማቸው እንዲህ በማለት ነበር የዘንድሮውን የኢህአዴግን የምረጡኝ አማርጡኝ ደፋ ቀና የአካባቢና የወረዳ ምርጫ ግርግርን እንዲህ የተቀኙበት፡-

ምርጫ የለም እንጂ ምርጫ ቢኖር፣

ኑ ምረጡን የሚለን ‹‹ካድሬ›› ባላሻን ነበር፡፡

 

1997 ምርጫ በኋላ የተካሄደው የ2002ቱ ምርጫ ከ1997ቱ ምርጫ በሁሉ ነገር አንሶና ኮስሶ ነበር የታየው፡፡ በእርግጥ ኢህአዴግ ከ97ቱ ምርጫ ስህተት በወሰደው ትምህርት ራሱን በሚገባ አጠናክሮ፣ ከሕዝቡ ጋር ለመገናኘት ተከታታይ የሆኑ ሰፊ ዘመቻዎችን በማድረግ በፍቅርም በጉልበትም መጪው ዘመን የእርሱና የእርሱ ብቻ እንዲሆን የተለመው እቅዱን ፈጽሟል ማለት ይቻላል፡፡

ይሁን እንጂ በ2002ቱ ምርጫ ላይ የነበረው ሕዝባዊው ተሳትፎው በአብዛኛው የቀዘቀዘ፣ የተቃዋሚ ፓርቲዎች ከገዢው ፓርቲ የተለመደ ወከባና በትር ያላመለጡበት፣ በተሳትፎ ረገድም መሳሳት የታየበት፣ ገዢው ፓርቲ ኢህአዴግም 99.6 በመቶ ምርጫውን ያሸነፈበትን ይህን መሬት አንቀጥቅጥ የሆነ ድሉን ለራሱና ለደጋፊዎቹ የዘከረበትና ያዘከረበት ምርጫ ሆኖ ነበር ያለፈው፡፡

በዘንድሮው 2005 የአዲስ አበባ የአካባቢ፣ የወረዳና የቀበሌ ምክር ቤት ምርጫ ኢህአዴግ በየቤቱ እየዞረና ኑ እባካችሁ ምረጡ እያለ በመቀስቀስ ሕዝቡን ለምርጫ ቢወተውትም የምርጫው ድባብ ከሂደቱ እስከ ፍፃሜው ድረስ ቀዝቃዛና ደብዛዛ ነበር፡፡

አንድ በአነስተኛ የሸቀጥ ሱቅ ውስጥ የሚሰራ ወጣት ስለ መምረጡ ስጠይቀው በሰጠኝ ምላሹ በግርምታ ሆኖ ‹‹እንዴ አዲስ መንግሥት መጥቷል እንዴ!? ትላንትና ዛሬስ ያለው ኢህአዴግ አይደል እንዴ!? ታዲያ የምን ምርጫ ነው የሚሉን እነዚህ ሰዎች በማለት ያስፈገገኝንም ያሳዘነኝንም መለስ ሰጥቶኛል፡፡

ብዙዎች ደግሞ አማራጭ ሲኖር እኮ ነው ምርጫ፣ ለመሆኑ ማንን ከማን ነው የምንመርጠው፣ በእውነት ኢህአዴግ አሁንስ ‹‹ከዝንጀሮ ቆንጆ …›› እንደሚባለው ተረት አደረገው እኮ ይሄን ምርጫ የሚለውን ነገር በማለት፤ ዋ…! ምርጫስ 97 ላይ ቀረ፣ አከተመ፡፡ ሲሉ በትዝታ ሰረገላ የ97ቱን የምርጫ ውድድር ብርቱ መንፈስና ሰፊ ሆነውን ሕዝባዊ ተሳትፎ በሐዘኔታ ውስጥ ሆነው እያስታወሱ፣ ወይ ነዶ፣ ዋ ምርጫ፣ የምርጫስ ነገርስ ይቅርብን ተዉን እባካችሁ … ሲሉ ተደምጠዋል፡፡

በእርግጥ ከ1997 ወዲህ ለተደረጉ አገር አቀፍም ሆነ የክልል ምርጫዎች እንዲህ መቀዛቀዝና ሕዝቡ ለመምረጥም ሆነ ለመመረጥ ያለው ፍላጎትና ስሜት እየወረደና እንደ በረዶ እየቀዘቀዘ መምጣት ገዢው ፓርቲ ብቻውን ተጠያቂ አይሆንም ባይ ነኝ፡፡

በአገራችን የሚገኙ አብዛኛው የተቃዋሚ ፓርቲዎችና አመራሮቻቸው ራእይ አልባነት፣ ቁርጠኝነት ማጣት፣ በሕዝብ ልብ ውስጥ ለመግባት የሚያስችላቸው ፕሮግራምና ፖሊሲ ለመቅረጽ መታከታቸውና ትግሉ የሚጠይቀውን ዋጋ ለመክፈል ያላቸው ዝግጁነት አናሳ መሆኑ አንዳንዶቹን ፓርቲዎችና አመራሮቻቸውን በበቃኝ ከትግሉ መድረክ እንዲያፈገፍጉ እያደረጋቸው እንዳለ እየታዘብን ነው፡፡

እንዲሁም በአገራችን የሚገኙ አብዛኛው የተቃዋሚ ፓርቲዎችና አመራሮቻቸው ከተለያዩ አቅጣጫዎች የሚደርስባቸውን ጫና መቋቋም አቅቷቸው፣ እንደ እሳት ሊፈትናቸው ያለውን መከራ በሩቅ ሸሽተውትና ቀቢጸ ተስፋ ተውጠው፣ ለገዢው ፓርቲ ኢህአዴግ ሜዳውም፣ ፈረሱም ይኸው በማለት ለብቻው ያለአንዳች ከልካይ በአገሪቱ የፖለቲካ ሜዳ ላይ እንደ ልቡና እንዳሻው ይጋልብበት ዘንድ በከፊል ቢሆን ዕድሉን አመቻችተውለታል፡፡

በሌላ በኩል ደግሞ የተቃዋሚ ፓርቲዎች አለመጠናከርና በአመራሮቻቸው መካከል ያለው አምባገነንነት፣ የእርስ በርስ አለመግባባት፣ ሽኩቻ፣ መወጋገዝና መከፋፈል የራሱ ሆነ ትልቅ አስተዋጽኦ እንዳለው ደግሞ ማንም የማይክደው ሐቅ ከሆነ ውሎ አድሯል፡፡

ከምርጫ 97 ማግስት በኋላ እርስ በርሳቸው መካሰስን፣ መወነጃጀልንና መወጋገዝን ሥራዬ ብለው የያዙት የተቀዋሚ ፓርቲ አመራሮች አንዱ የአንዱን ገበና ሳይቀር እንኳን በአደባባይ በማውጣት የገቡበት ቅሌትና የስነ ምግባር ውድቀት፣ አይወርዱ አወራረድ በብዙዎች ዘንድ ለመሆኑ እንደው የሆነስ ሆነና ኢህአዴግ ሥልጣኑን ቢያስረክባቸው ኖሮ ይህችን አገር ሊመሩ የነበሩት እነዚህ ሰዎች ነበሩ እንዴ እስኪሉ ብዙዎች በእፍረት እንዲሸማቀቁና እንዲያንሱ ያደረጉበትን በርካታ አጋጣሚዎችን ታዝበናል፡፡

በአገራችን ያሉ የተቃዋሚ ፓርቲዎችና አመራሮቻቸው በሕዝብ ዘንድ አመኔታን በማጣታቸው የተነሳ አብዛኛው ሕዝብ ‹‹ከማያውቁት መልአክ የሚያውቁት ምንትስ ይሻለናል፡፡››፤ ‹‹ትሻልን ትቼ ትብስን አመጣሁ፡፡›› እንዳይሆን በሚል ስጋት ወዶም ሆኖ ሳይወድ ኢህአዴግን የሙጥኝ እንዲል የተገደደ ነው የሚመስለው፡፡ እናም ዛሬም ድረስ ተቃዋሚ ነን በሚሉ የትላንትናዎቹ አንጋፋ ፓርቲዎች ውስጥ የተከሰተው ታላቅ የሆነ ስብራት ወይም ስንጥቃት የተጠገነ፣ ቁስሉም የተፈወሰ አይመስልም፡፡

የገዢው ፓርቲ የኢህአዴግ ግትርነት፣ ለሕዝቡ ከእኔ በላይ ለአሳር የሚለው አመለካከቱ፣ በአማራጭ መንገዶችን ለማየትና ከሌሎች ጋር ለመነጋገር ያለበት ችግርና በተቃዋሚ ፓርቲዎች መካከል ያሉት ኁልቆ መሣፍርት የሌላቸው ችግሮች ተደራርበው አገራችን የምታልመውን የዲሞክራሲያ ሥርዓት ግንባታን ዕድገት እያጓተተው ነው፡፡

ገዢው ፓርቲ ኢህአዴግና አጋሮቹ የ1997ቱ ዓይነት ሕዝብ አቀፍ የሆነ የዲሞክራሲያዊ እንቅስቃሴ መንፈስና ቅናት ዳግም እንዲፈጠር ከመሥራት ይልቅ ዛሬም በለመደው ሸካራ መንገድ መጓዝን ነው የመረጠው፡፡ ኢህአዴግ ከሌሎች ፓርቲዎች ጋር ተቀራርቦ ለመነጋገር፣ ለመወያየት የጠረቀመውን በሩን በጨዋ መንገድ ለመክፈት ዛሬም ተቸግሮ ያለ ነው የሚመስለው፡፡ እናም በጠላትነት የመተያየት፣ የጥላቻና የጽንፈኝነት ክፉ መንፈስ ዛሬም ድረስ በአገራችን የፖለቲካ ሰማይ ላይ የመጠፋፋትን፣ የመበላላትን ጥቁር ደመና እንዳዘለ ነው፡፡

በዚህ ሁኔታ ደግሞ በፊታችን የሚጠበቀው አገር አቀፉ ምርጫ 2007 የተለየ አንድምታ ሊኖረው አይችልም የሚለው ተስፋ አስቆራጭ የሚመስል ድምፆች ከዚህም ከዚያም እየተሰሙ ናቸው፡፡ ያው እንደተለመደው ምርጫ ሲደርስ ከተደበቁበት ጎሬ ወጥተው አለን አለን የሚሉት የተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮችና ምርጫን ሰበብ አድርገው እንደ እንጉዳይ የሚፈሉትና እዚህም እዛም ብቅ ብቅ የሚሉት የአገራችን ፓርቲዎች እንደልማዳቸው በመጪው ምርጫ ግርግር መፍጠራቸው አይቀር ይሆናል፡፡

ግና ለኢትዮጵያና ለኢትዮጵያውን የሚያስፈልጋቸው ፓርቲና ፖለቲከኛ የምርጫ ሰሞን አለሁ አለሁ የሚል የትርፍ ጊዜ ፓርቲና ፖለቲከኛ አይደለም፡፡ የአገሪቱን የፖለቲካ ታሪክ፣ የተፈጥሮ ሀብቶቿን፣ የሕዝቦቿን ሃይማኖት፣ ታሪክ፣ ባህልና ቅርስ በሚገባና ጠንቅቆ የሚያውቅ፣ በአገሪቱ ብሔራዊ እርቅ፣ መግባባትና አንድነት እንዲመጣ ጠንክሮ የሚሠራ፣ እንደ ማህተመ ጋንዲና እንደ አፍሪካዊው ኔልሰን ማንዴላ የፍቅርን፣ የወንድማማችነትንና የእርቅን ሰንደቅ ዓላማ ከፍ አድርጎ የሚያውለበልብ፣ ቆራጥና የሕዝብ ወገንና አለኝታ የሆነ ፓርቲና ፖለቲከኛ ነው ብዙዎቻችን በእጅጉ የናፈቀን፣ የሚያስፈልገንም፡፡

ጥናቶች እንደሚጠቁሙት በአገራችን የተከሰተው አብዮት ካመጣቸው መዘዞች አንዱ የፖለቲካ ፕሮፌሽናል ደረጃ እየወደቀ መሄድ ነው፡፡ የታሪክ ምሁሩ ፕሮፌሰር ሺፈራው በቀለ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚክስ ባለሙያዎች ማኅበር ባዘጋጀው Vision 2020 የሥራ ባልደረባቸው የሆኑት ፕሮፌሰር ባሕሩ ዘውዴ ‹‹ምን አለምን? የት ደረስን? ወዴትስ እያመራን ይሆን?›› በሚል አርዕስት ባቀረቡት የጥናት ጽሑፍ ላይ ባቀረቡት ለውይይት ማጫሪያና ማዳበሪያ የሚሆን መነሻ ሐሳብ ላይ ሲገልጹ፡-

ፖለቲካ ማለት መቀላመድ፣ ለዘመድ አዝማድ፣ ለአምቻ ለጋብቻ፣ ለዘር፣ ለወገንና ለጎሳ ‹‹ጮማ መቁረጥ ጠጅ ማንቆርቆር›› (በዚህ ዘመን እንኳን ምናልባት ውስኪ ማውረድ ቢባል ይቀላል፡፡) ማለት ሆኗል፡፡ በኢትዮጵያውያን አእምሮ ውስጥ በፖለቲካና በማፈያ መካከል ልዩነቱ እየደበዘዘ ሄዷል ማለት ይቻላል፡፡ በመሠረቱ ግን ፖለቲካ በምዕራቡ ዓለም እጅግ ተከበረ ፕሮፌሽን መሆኑን በመጠቆም የታሪክ ምሁሩ በአገራችንም በጥንት ጊዜ ፖለቲካና ፖለቲከኝነት እንዲሁ እንደነበር ያስረዳሉ፡፡

ፕሮፌሰር ሺፈራው ፖለቲካና ፖለቲሺያኖች የተከበሩ፣ ጨዋ፣ የጨዋ ጨዋ ካልሆኑ፣ የሚናገሩት ከመሬት ጠብ የማይል ካልሆነ ምንም ያህል ውብ ውብ ራእዮች ስንደቀድቅ ብንውል ራእዮቻችን ዋጋ አይኖራቸውም ሲሉ ነው የሚደመድሙት፡፡

በስነ ምግባር የታነጸ፣ ጨዋ፣ ለራሱ ሳይሆን ለሕዝቡ የተሰጠ፣ ልክ እንደ እስራኤላውያኑ መሪ ሙሴ ‹‹ይህን ሕዝብ ከምታጠፋው እኔን ከሕይወት መጽሐፍ ደምስሰኝ፡፡›› የሚል በሕዝብ ፍቅር የሰከረ፣ በሳል ፖለቲከኛ/መሪ፣ ከጽንፈኝነት፣ ከጥላቻና ከጎሰኝነት የጸዳ ጠንካራ ፓርቲና ፖለቲካኞች ለማየት አልናፈቃችሁም ወገኖቼ?!

በትንሹም በትልቁም ዛቻና ማስፈራሪያ እየበረገገ፣ መከራው ሲጸናበትና ቀንበር ሲከብድበት ለሕዝብ የገባውን ቃል አጥፎ፣ ‹‹ሞቴም መቃብሬም እዚሁ ነው፡፡›› ብሎ ምሎ እንዳልተገዘተ ሁሉ ‹‹በቦሌም በባሌም›› ብሎ እግሬ አውጪኝ በማለት ወደ አውሮፓና አሜሪካ የሚሰደድ ሳይሆን፣ እዚሁ በአገሩ ከሕዝቡ ጋር ደጉንም ክፉውንም ተቀብሎ በትዕግሥት፣ በጽናት እና በሰላማዊ መንገድ የሚታገል፣ በሕዝብ ፍቅር የወደቀና የነደደ እንደ ጋንዲ፣ እንደ ማርቲን ሉተር፣ እንደ አፍሪካዊው ኔልሰን ማንዴላ ያለ የሕዝብ የቁርጥ ቀን ልጅ የሆነ ፓርቲና ፖለቲከኛ አልናፈቃችሁም ወገኖቼ!

እንዲህ ዓይነት ከሕዝብ ለሕዝብ የሆኑ ፓርቲዎችና ፖለቲከኞች ሲፈጠሩ ሕዝቦች ያለ ምንም ቀስቃሽና ወትዋች በነቂስ ወጥተው ያገለግለናል፣ ይጠቅመናል የሚሉትን ፓርቲም ሆነ እጩ ለመመረጥ የሌሊቱ ቁር፣ የቀኑ ፀሐይ ሳይበግራቸው መብታቸውን አውቀው ለመጠቀም ይተጋሉ፣ ይሰለፋሉ፡፡ ምርጫ 97 ደግሞ ይህን ሐቅ ለመንግሥት ብቻ ሳይሆን ለዓለም ሕዝብ ሁሉ በይፋ አሳይቷል፣ አስመስክሯል፡፡

ገዢው ፓርቲ ኢህአዴግም ሆነ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ለመቀመጫ ወይም ለስልጣን ከመወዳደራቸው በፊት የሕዝብን ልብ አሸንፈው፣ በሕዝባቸው ልብ ዙፋን ላይ ሊቀመጡ የሚችሉበትን ፍቅርን፣ መፈራትን፣ መወደድንና መከበርን ያገኙ ዘንድ መትጋትና መሥራት ይኖርባቸዋል፡፡ የዛን ጊዜ ምርጫው ምርጫ ይሆናል፤ ሕዝብም ያለ ምንም ቀስቃሽ የመምረጥ መብቱን ለመጠቀም በነቂስ ተጠራርቶ ይወጣል፡፡

ሰላም! ሻሎም!

 

Latest from Blog

መኮንን ሻውል ወልደጊዮርጊስ ¹⁵ የምድርም ነገሥታትና መኳንንት ሻለቃዎችም ባለ ጠጋዎችም ኃይለኛዎችም ባሪያዎችም ጌቶችም ሁሉ በዋሾችና በተራራዎች ዓለቶች ተሰወሩ ፥ ¹⁶ ተራራዎችንና   በላያችን ውደቁ በዙፋንም ከተቀመጠው ፊት ከበጉም ቍጣ ሰውሩን ፤ ¹⁷ ታላቁ የቁጣው ቀን  መጥቶአልና ፥ ማንስ ሊቆም ይችላል ? አሉአቸው ። ራእይ 6 ፤  15_17 ይኽ የመጽሐፍ ቅዱስ ቃል ። የኢየሱስን ልደት ሰናከብር የየሐንስ ራእይን ማንበብ ጠቃሚ ይመስለኛል ። ምክንያቱም በመጨረሻው ዘመን

ከኢየሱስ የፍርድ ቀን በፊት በህሊናችን ውስጥ ፍቅርን ለማንገስ እንጣር 

የምጣኔ ሀብታዊ ፍጥ፣ የፖለቲካ፣ የእውነትና የሰብአዊ መብት ታጋይ፣ የአመኑበትን ነገር ለመናገር እንደ ፖለቲከኛ በቃላት ሳያሽሞነሙኑ ቀጥታ የሚናገሩት የሀገሬ ኢትዮጵያ ታላቅ ሰው ነበሩ “ዘር ቆጠራውን ተዉት፤ የአባቶቻችሁን ሀገር ኢትዮጵያን አክብሩ!”  አቶ ቡልቻ ደመቅሳ

ሀገር ወዳዱ አቶ ቡልቻ ደመቅሳ ከዚህ አለም በሞት ተለዩ

January 6, 2025
ግን ይህ ሁሉ ወጣት የት ገባ? ግን ይህ ሁሉ ወጣት የት ገባ? ዛሬ፣ 2025 ዓ/ም ላይ ብንገኝም በዝንጋታ ገመድ ወደ ሞት እየተጎተትን እንደሆነ አናውቅም። (ሁል ጊዜ የሚሞተው የገነዝነው ይመስለናል። ) “ገብርዬ ነበረ

ግን ይህ ሁሉ ወጣት የት ገባ?

January 3, 2025
መኮንን ሻውል ወልደጊዮርጊስ ዛሬ እንደ አውሮፓዊያኑ አቆጣጠር ጥር 1ቀን 2025 ዓ/ም ነው ። አውሮፓውያኑ አዲስ ዓመትን “ሀ” ብለው ጀምረዋል ። አዲሱን ዓመት ሲጀምሩም ከልክ ባለፈ ፈንጠዚያ ነው ። ርቺቱ ፣ ምጉቡና መጠጡ

ዛሬ፣ 2025 ዓ/ም ላይ ብንገኝም በዝንጋታ ገመድ ወደ ሞት እየተጎተትን እንደሆነ አናውቅም። (ሁል ጊዜ የሚሞተው የገነዝነው ይመስለናል። )

Go toTop