ይህ እልቂት በሀገር ውስጥም ሆነ በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚሰሩ የመብት ተሟጋች ነን የሚሉና የሰብአዊ አገልግሎት ድርጅቶች ጆሮ ዳባ ልበስ ያሉበትና የፍጅቱን መኖር እንኳ ለዓለም ህዝብ ለማሳወቅ ዓለምአቀፍ የሚዲያ አካላት ዜና የነፈጉት ሁኗል። ለዚህ የተሰናሰለ ጥቃት መሰረቱ ከፖሊሲ ንድፍ ጀምሮ በእርዳታ ስም መሳሪያዎችን እስከማቅረብ ድረስ ባልተቋረጠው የውጭ ኃይሎች ትብብር እንደሆነ ይታወቃል። ይህም ሀገሬን በምእራባውያን ኃያላን አላስነካም፤ ከቅኝ ግዛት በክብር መሞት ብሎ ታግሎ፤ የሽንፈት ማቅ ያለበሳቸውን እና ያልተንበረከከውን ዐማራ ከራሱ ህዝብ ጋር የሚፋጅበትን ስልት በመንደፍ አማራውንና ጠንካራ የሀገሪቱ ተቋማትን እንዲጠፉና ሀገሪቱ ስትዳከም በሚፈልጉት ጊዜ እንደልባቸው የሚጫወቱበት ሀገር ለማድረግ ነው። ይህንን ፍላጎት ማሳካት የሚያስችላቸውን የሀሰት ትርክቶችን ጎንጉነው ዐማራ ጠልነት ዘመናዊ የኢትዮጵያ ማህበራዊ ፖሊሲ እንዲሆን አስችለዋል። ስለሆነም አሁን የሚካሄደውን የአማራ ዘር ጭፍጨፋ ለዘመናት የደከሙበት ፕሮጀክት ነውና እንደ ምስራች እንጅ አሳዛኝ ክስተት አድርገው ሊመለከቱት አይችሉም።
በመሆኑም ለአለም አቀፍ ማህበረሰቡም ሆነ ሚዲያዎቻቸው ስለአማራው ፍጅት ለማሳወቅ የሚደረገው ጥረት ተሰሚነት ማጣቱ ብቻ ሳይሆን መረጃው ተደራሽ ቢሆንም ለሚጨፈጨፈው ህዝብ ምንም ፋይዳ አይኖረውም። በዚህ ሂደት ምንም ያህል እልቂት ቢፈጠር፤ ምንም ያህል የአማራ አንቂዎች፥ ዳያስፖራውና ጋዜጠኞች ጩኸት ቢያሰሙ፤ አማራውን ለመርዳት የሚራራ የውጭም የውስጥም ወገን ሊገኝ አልቻለም። ይልቁንም የአማራው ጅምላ ግድያ ተለምዶ በየዕለቱ ቀጥሏል። በአጠቃላይ አማራ እንደ አንድ ማህበረሰብ ከራሱ በስተቀር ማንም ከዚህ እልቂት የሚታደገው ኃይል እንደሌለ ያረጋገጠበት ወቅት ነው። ስለሆነም አማራ ህልውናውን ማስቀጠል የሚችልበትን የራሱን ተጋድሎ ስልቶች ነድፎ መነሳትና በራሱ አቅም ብቻ ህልውናውን ማስቀጠል ይጠበቅበታል። የህልውና ተጋድሎው በህዝባዊ አብዮት የሚጀመርና ቀጣይነት ባላቸው አደረጃጀቶች የማህበረሰቡን ህይወት ማሻሻል በሚችሉ ዘዴዎች ተጠናክሮ የሚቀጥል ይሆናል።
ይህ መጽሐፍ ለታለመው የዐማራ ህዝባዊ አብዮት እና የህልውና ተጋድሎ መነሻ የሆኑትን የሀሰት ትርክቶች ከሞላ ጎደል (በአማርኛ ቋንቋ፥ በዐጼ ምኒልክ፥ በኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ላይ የተዘሩትን ስሁት ትርክቶች በማስረጃ) ያቀርብና፤ የገዳይ ኃይሎችን አሰላለፍ በጥልቀት በማሳየት የአማራ አብዮት በምን መንገድ መካሄድ እንደሚችል አቅጣጫ ይጠቁማል።https://www.amazon.com/dp/B0BX5B4JXY?ref_=cm_sw_r_mwn_dp_EJY770BMWSYSF3SY8BBE