ብፅዕ ካርዲናል ብርሃነየሱስ የኢትየጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ሊቀጳጳሳት የ2015 ዓ.ም የአዲስ ዘመን መለወጫ በዓልን በማስመልከት ለመላው ምዕመናን ያስተላለፉት መልዕክት

September 7, 2022

ethiopia 1626974390በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!

“በቸርነትህ ዓመታትን ታቀዳጃለህ፤ ምድረ በዳውም ስብን ይጠግባል ፤ የምድረ በዳ ተራሮች ይረካሉ፡፡ ”(መዝ 65፡12-13)

ብፁዓን ጳጳሳት
ክቡራን ካህናት፣ ገዳማውያንና /ገዳማውያት
ክቡራን ምዕመናን
በጎ ፈቃድ ላላቸው ሰዎች ሁሉ
ክቡራትና ክቡራን

ከሁሉ አስቀድሜ ለመላው ኢትዮጵያውያን ትውልደ ኢትዮጵያውያን በሙሉ እንኳን ከዘመነ ማርቆስ ወደ ዘመነ ሉቃስ ለ2015 ዓ.ም የዘመን መለወጫ በዓል በሰላምና በጤና አደረሳችሁ፡፡ የእግዚአብሔር አብ ፍቅር የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ፀጋ የመንፈስ ቅዱስ ኅብረት ከሁላችሁ ጋር ይሁን በማለት በኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያንና በራሴ ስም መልካም ምኞቴን አቀርብላችኋለሁ፡፡

“እኔ ግን አሁን ይህን አላገኘሁትም ወይም አሁን ፍፁም ለመሆን አልበቃሁም፣ ዳሩ ግን ክርስቶስ ኢየሱስ የእራሱ አድርጎኛልና ይህን የራሴ ለማድረግ ወደፊት እሮጣለሁ፡፡ ወንድሞቼ ሆይ! እኔ ግን ይህንን ነገር የራሴ አድርጌዋለሁ ብዬ አላስብም፤ ነገር ግን አንድ ነገር አደርጋለሁ፣ በኋላዬ ያለዉን እየረሳሁ በፊቴ ያለውን ለመያዝ ወደፊት እዘረጋለሁ፡፡” (ፊሊጲ 3፡ 12-13)

የተወደዳችሁ ምዕመናን
ጊዜ የእግዚአብሔር ስጦታ ነው፡፡ በምስጋና መንፈስ እንቀበለው፡፡ ጊዜ ስጦታ መሆኑን ስናስተውል ብዙ እንጠቀማለን፡፡ ያለ ጊዜ ምንም ማድረግ አንችልም፡፡ የጊዜ ባለቤት ደግሞ እራሱ ልዑል እግዚአብሔር ነው፡፡ ዘለዓለማዊ እግዚአብሔር ሲፈጥረን በጊዜና በቦታ ውስጥ እንድንመላለስ አደረገን፣ ጊዜንና ቦታንም ሰጠን፣ ጊዜ አለፈብን ብለን እንጨነቅ ይሆናል፣ ጸሎት ግን ከዚህ ዓይነት ጭንቀት ነፃ ያወጣናል፡፡ ምክንያቱም መጸለይ ማለት ከዘለዓለማዊው ጋር መነጋገር ነውና፡፡ ጊዜንም ማትረፍ ያስችላልና ነው፡፡ ለሰላም ስንሠራም ጊዜን እንቆጥባለን፡፡ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በልደቱ ዘለዓለማዊውንና ጊዜያዊውን አቀራረበ፣ በትንሣኤው የዘለዓለም ሰላምንና እረፍትን እንዲሁም ተስፋን ሰጠን፡፡

አዲሱ ዓመት ለምስጋና እንደሚጋብዘን ሁሉ ለንሰሐም ሊጠራን ይገባል፡፡ ንስሐ ማለት ወደ እግዚአብሔር መመለስ ነው፡፡ ንስሐ አያስፈልገንም ብንል እንሳሳታለን፡፡ ሁላችንም በተገባደደው ዓመት ምን ያህል ተምረናል? ምን ያህልስ በማስተዋል አድገናል? እነዚህን ጥያቄዎች ለመመለስ የኅሊና ምርመራ ያስፈልገናል፡፡ ስለሆነም ከስሜታዊነት ይልቅ በሰከነ አዕምሮ ሕሊናችንን እንመርምር ለማዳመጥና ለመደማመጥ የምንሰጠው ጊዜ የምናስተውልበት የተመረጠ ወቅት ነው፡፡

ጊዜን ተጠቀምንበት የምንለው በኃላፊነት መንፈስ ያለፈውንም ሆነ የአሁኑን መቀበል ስንችል ነው፡፡ ጊዜን ቆጠብን የሚባለዉ የሰላም መሳሪያዎች ስንሆን ነዉ፡፡ የሰላም መሳሪያነት ደግሞ የሚጀምረዉ ከአስተሳሰባችን ነው፡፡ “አትግደል” የሚለው ትዕዛዝ ለሁሉም ነው፡፡ ሁሉንም ይመለከታል፡፡ “አትግደል ” ማለት የሁሉንም ሰው ሕይወት አክብር ማለት ነው፡፡ ይህ ትዕዛዝ የሚመለከተዉ የአንተን ማህበር አባል፣ የአንተን ቤተሰብ አባል፣ የአንተን ክልል አባል ብቻ ሳይሆን የሰው ልጆችን በሙሉ ነው፡፡ ከአንተ የሚለየውንም እንግዳውንም ይመለከታል፡፡

ንግግራችን ወደ ሰላም የሚወስድ ሊሆን ይገበዋል፡፡ ንግግራችን ቁስልን የሚፈውስ፣ ወደ እርቅና አንድነት የሚመራ እንዲሆን ወንጌል ያስተምረናል፡፡ ጥላቻንና አላስፈላጊ ፉክክርን የሚያመጡ ንግግሮች ይጎዱናል፡፡ ወንድምንና እህትን የሚበድሉ ንግግሮች በቤትም፣ በሥራም፣ በትምህርት ቤትም ብሎም በማህበራዊ ሚዲያም ሊወገዱ ይገባል፡፡ ይልቁንም የጋራ ጥቅምን የሚያስቀድሙ ሰላማዊ ንግግሮች ሁላችንንም ይጠቅማሉ፡፡ ንግግር ፍሬያማ የሚሆነው መናገር ከማዳመጥ ጋር ሲቀናጅ ነው፡፡ ማዳመጥ ትልቅ ፀጋ ነው፡፡ ትክክል ነዉ ብለን የያዝነው ነገር ትክክል ላይሆን ይችላል፡፡ ከልጅነታችን ጀምሮ እየሰማን የመጣነው ነገር ጉድለት ሊኖረው ይችላል፣ መሻሻል ያስፈልገዉ ይሆናል፡፡ ለዚህ ፍቱን መድኃኒቱ የማዳመጥ ፀጋ ነው፡፡ አውቃለሁ ከሚለዉ ይልቅ አለማወቁን የሚያውቅ ጠቢብ ነውና መጪው ዘመን በእውቀት የምናድግበት ዘመን እንዲሆን ቆርጠን እንነሳ፡፡

ጊዜ የአምላክ ስጦታ መሆኑን ስንገነዘብ ወደ ትህትና ይወስደናል፡፡ ትህትና የመንፈሳዊነት ንግሥት ናት፡፡ ትሕትና የማይታየውን ታሳየናለች፡፡ ወደ እውነት ትመራናለች እውነት ደግሞ የምትገኘው በትህትናና በጽሞና ነው፡፡ ትህትና ነገሮችን ከተለያዩ አቅጣጫዎች እንድንመለከት ታስችለናለች፡፡ ሰለሆነም እውነት ነፃ እንደምታወጣን በወንጌል ተገልጿል፡፡ (ዮሐ.8፡32)

አዲስ ዓመት የተሰጠን በጎ ነገሮችን እንድንሠራበት ነው፡፡ ለጋራ ጥቅም የሚሆን ሥራን መፈለግ ትልቅ ፀጋ ነው፡፡ የእግዚአብሔርም ትልቅ ስጦታ ነው፡፡ እንዲህ ሲሆን እንኳን የአገራችን ሰው ቀርቶ የአገራችንም ፍጥረታት ይደሰታሉ፡፡ ሁላችንንም ትልቁ ወርቃማው ሕግ ይግዛን፡፡ እሱም “ባንተ ላይ እንዲደረግብህ የማትፈልገዉን አንተም በሌሎች ላይ አታድርግ” (ማቴ.7፡12) የሚለዉ ሕግ ወይም የሕይወት መርህ ነው፡፡ መፈናቀል እንደማንወድ ግልጽ ነው እንግዲውስ ሌሎችም እንዲፈናቀሉ አናድርግ፡፡ መራብ እንደማንፈልግ ግልጽ ነው እንግዲያዉስ ሌሎች እንዲራቡ አናድርግ፡፡ መደኸየት አንፈልግም እንግዲያውስ ሌሎች እንዲደኸዪ አናድርግ፡፡ መገለል አንፈልግም እንግዲውስ ሌሎች እንዲገለሉ አናድርግ፡፡

ወርቃማው ሕግ እንግዲህ በሚከተለው መንገድ ሊገለጽ ይችላል፡፡ እርሱም “ላንተ እንዲደረግልህ የምትፈልገውን ለሌሎች አድርግ” የሚለውን መርኅ ነው፡፡ ይህ ሕግ በፍቅርም ሊተረጎም ይችላል፡፡ ማፍቀር ጊዜን ሃብታም ያደርጋል፡፡ ዘመን ያስውባል በረከትን ይሰጣል፡፡

የተወደዳችሁ ምዕመናን
የተወደዳችሁ የአገራችን ህዝቦች አገራችን በውስጣዊ ጦርነት ላይ የምትገኝ ቢሆንም ጦርነት ለማንም የማይበጅ አጥፊ ስለሆነ በአዲሱ ዓመት ሁሉም ወገኖች ለሰላምና ለእርቅ ቦታ ሰጥተው ወደ ውይይት እንዲቀርቡና እንዲነጋገሩ አገራቸውንና ሕዝባቸውን ከጥፋት እንዲያድኑ ቤተክርስቲያናችን ትማፀናቸዋለች፡፡ ምዕመናንም እግዚአብሔር ሰላሙን እንዲሰጠን በጸሎት እንዲተጉ አደራ እንላለን፡፡ በዘመን መለወጫ በዓላችን ሁላችንም በምንችለውን ዓይነት በችግርና በመከራ በጭንቀት ላይ የሚገኙትን ወገኖች በማሰብ አቅማችን በሚፈቅደዉ መጠን በመተጋገዝና በመረዳዳት በዓሉን እንድናሳልፍ አደራ ማለት እወዳለሁ ፡፡

በመጨረሻም ለመላዉ የአገራችን ሕዝቦች በሙሉ በየሆስፒታሉና በቤታችሁ በህመም ላይ ያላችሁ የእርሱን ምህረትን፣ በየማረሚያ ቤቶች ለምትገኙ የሕግ ታራሚዎች መፈታትን፣ በግጭት ቀጠናዎች ውስጥ ያላችሁ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን እንዲሁም የመንፈስ ልጆቻችን እግዚአብሔር ሰላሙን እንዲያወርድላችሁ፣ በተለያየ ምክንያት በሀገር ውስጥና በውጭ ሀገራት በስደት ላይ የምትገኙ ወገኖቻችን ለአገራችሁና ለአካባቢያችሁ እንዲያበቃችሁ እየተመኘሁ ለሁላችንም አዲሱ ዓመት የሰላም፣ የጤና፣ የፍቅርና የበረከት፣ የመደማመጥ፣ የመወያየት፣ የመተዛዘንና የመተሳሰብ፣ የማስተዋልና የጥበብ ዘመን ይሁንልን፡፡

እግዚአብሔር አምላክ አገራችንን ኢትዮጵያን ይባርካት ይጠብቃት !

† ብፁዕ ካርዲናል ብርሃነየሱስ
ሊቀጳጳሳት ዘካቶሊካውያን
የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን
የጳጳሳት ጉባኤ ፕሬዝዳንት

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Amuru displacement 1536x864.jpg
Previous Story

ኦሮሚያ ክልል፡ በሆሮ ጉዱሩ ወለጋ ዞን ኡሙሩ ወረዳ በታጠቁ ቡድኖች በሲቪል ሰዎች ላይ የተፈጸመ ጥቃት

15a329a0 2df7 11ed 90f6 abf9af5a7e42.jpg
Next Story

ተመድ በሱዳን የስደተኞች መጠለያ ወታደራዊ ምልመላ ይደረግ እንደነበረ መረጃው አለኝ አለ

Go toTop