ማን ቼ ፖለቲካ – ሲና ዘ ሙሴ 

ክልል ቅብርጥስዮ እያላችሁ ጫጫታ አታብዙ ። ጉራጌ ክልል ሆነ ዞን ለጉራጌ ደሃ ጠብ የሚልለት ነገር የለም ። ሌላውም ክልል ልሁን ባይ ፣  የጉራጌን ህዝብ ዓይነት ዕጣ ፈንታ ነው ያለው ። ሺ ቢታለብ ከገሌ አያልፍም እንዳለችው ድመት ነው ነገሩ ። የጉራጌ ደሃ የሚኖረው በአዲስ አበባ ፣ በአዳማ ፣በሃዋሳ፣በሻሸመኔ፣ በድሬደዋ፣ በጅጅጋ፣ ወዘተ ። የኢትዮጵያ ከተሞች  እንደሆነ  ይታወቃል ። ሁለት ሚስት አግብተው አንዷን መሬት ጠባቂ አንዷን የከተማ ዘመናይ አድርገው የሚኖሩም አሉ ። ያም ሆነ ይኽ የጉራጌ አገሩ ከተማ ነው ። ክልል አሜረኝ የሚለው እንደ እርጉዞ ሴት መሆኑ ነው ። አይቅርብኝ ። እኔም ከ60 ዎቹ የደቡብ ጎሳዎች አንዱ ነኝ ባይ ነው  ። ነው ። በቃ ። ግን ፣ ግን  በአዳማ ካሉት ሀብታሞች  የበለጠ ወልቂጤ የጉራጌ ሀብታም እንደሌላት እያወቀ  የኢንጊሊዝ ፕሪመር ሊጋ ይመሥል ” ወያላው ዝምን እየዘፈነ ክልል አማረኝን ምን አመጣው  ? የተኮታኮተው ማንቼ እና የጨሰው አርሴ ጫወታ መሰለ ‘ ኮ ! ፖለቲካው ። በበኩሌ በእንጊሊዝ አፍ “ ማን “ እና በእኛው ቋንቋ “ ቼ “ ለዛሬው የክልል ፖለቲካ የሚመጥን ርዕሥ ነው ። ( ሰው ቼ እየተባለ ለማይረባ ጉዳይ ሁሉ ፣ አደባባይ  መውጣት ብርቁ አይደለም ። በደርግ የተጀመረው የቼ ሰልፍ  በኢህአዴግ እንደቀጠለ አንዘነጋም ።)  ( እግርኳስም የሚያምረው በጥበብ በተሞሉ ተጫዋቾችና በጥበብ በበለፀገ አሠልጣኝ ሲከወን ነው ። አሠልጣኙ ሁሌም ተጨዋቾቹን በጥበብ እየሞላ ሜዳ ካላስገባ በስተቀር ፣ በጫወታ ሂደት   መንጋነት መንፀባረቁና ቡድኑንን   ለሽንፈት መዳረጉ አይቀርም ። የኢትዮጵያ ፖለቲካ ከጥበብ መራቅ የጀመረው ፣  ከቀዳማዊ ኃይለሥላሤ (ቀኃሥ) ውድቀት በኋላ ነው ። በነማን እየተጠመዘዘ ከሁለት ሦሥቴ በላይ አገረ መንግሥቱ  ውድቆ እንደተነሳ ያላሥተዋለ (ጅሌ ) ” ክልል !  ክልል ! ”  እያለ በሞኝነት ይጮኻል ።” መላው ኢትዮጵያ የራሱ መሆኗ እንዴት እንዳልገባው ግርም ይለኛል ።

ተጨማሪ ያንብቡ:  ፍትህና ነጻነት ለጠለምት አማራ

በህዝብ ሥም የተደራጁ  አንዳንድ የፖለቲካ ፖርቲዎች የጥቂቱን ህዝብ ፤ በተለይም በስሜት ፍላሎት የሚነዳውን  ጀብደኛ ወጣት አእምሮ በመኮርኮር ፣ ክልል በመሆኑ ብቻ እንደ ጨው ዘር በመላው ኢትዮጵያ ተመልሶ ወልቂጣ የሚገባ ይመሥል በጣጣ የተሞላውን ክልል ናፋቂአድርገውታል ። እነሱ እንደሚሉት   ከሰልል መሆን ታላቅነት እየመሰለው ፣ ከአገር በፊት ጎሣ ማሥቀደሙ የሚያሥገርም ነው ። ይኽ ድርጊቲ አፐርነሰ አኮስሶ እንደ ማየት ይቆጠራል ።

አገር ከቋንቋ  የምታንሥ ተራ ነገር አየደለችም ። አገር እኮ እንደሰማይ የገዘፈች   ናት ። አገር ከህዝብ ቁመት በላይ ናት ። ልክ እነደ ሰንደቅ ዓላማ ። ለዚህ ነው የአገር ሰንደቅ ዓለማ በከፍታ ላይ የሚውለበለበው ። ትልቅነቷን ለማመልከት ። ደግሞም አገር ታላቅ እንድትሆን የቀደመው ትውልድ የሚከፈለውን መሰዋትነት  መዘንጋት የለብንም ።  አገር ያለመሰዋትነት እንዳልተገነባችም መዘንጋት አልነበረበትም ።

ይኽ ሥህተትህ ነው ፤ ” በዚች አጭር ዕድሜዬ በአገሬ ላይ በነፃነት  እንደ ልቤ ተዘዋውሬ ሳልሳቀቅ  ፤ ሠላሜ ና ደህንነቴ ተጠብቆ ደሥታዬ በዝቶ የምኖርበት የፖለቲካ አውድ ይፈጠር ። ” እንዳትል ያደረገህ ። ለጥቂት የፖለቲካ ቁማርተኞች ብልፅግና አገር ያለ አቅሟ 60 ክልል ይኑራት ማለትህ ልክ አይደለም ።    በትልቋ ጠቃሚዋ ኢትዮጵያሁሉን አሳታፊ የፖለቲካ ሥርዓት ላይ በማተኮር ቢያንሥ ” አገሬ የበለፀጉትን አገራት ፖለቲካ በመከተል ፣ ህዝብ ሰብዓዊ መብቱ ተጠብቆ  ዴሞክራሲያዊ መብቱ በወጉ ተረጋግጦ ፤ መሠረታዊ ፍላጎቶቹ ተሟልተው ፤ አጭር ዕድሜውን በወጉ እንዲኖር ይደረግ  ። ” እንደማለት ፣ ክልል ሲኮን ለምሥኪኑ ገበሬ ና ከተሜ መና ከሰማይ ይወርድለት  ይመሥል ፣ የመከፋፈልን መንገድ መምረጥ በበኩሌ የጥበብን መንገድ አፈርድሜ ማሥበላት ነው ። ይኽንን ወደ አዘቅት ወሳጅ መንገድ ከአንተ ካልባነንከው እየኮረጁ ፣   በየሶሻል ሚዲያው  የሚያራግቡትም  ፣ ፖለቲካ ዛሬም ድረስ ዘልቆ ያልገባቸው  የፖለታካ ማይሞች ናቸው ።  በማጋጨት እና በማባላት ትርፍ ለማግኘት የሚሯሯጡ ሞራለ ቢሶች ። ያም ሆነ ይኽ ዩቲዩብም እንጀራ ያሥገኛል ።

ተጨማሪ ያንብቡ:  አስከፊው አድርባይነት ዛሬም ከዋነኛ የፖለቲካ ደዌዎቻችን አንዱ ሆኖ ቀጥሏል ! - ጠገናው ጎሹ

የጥቂት  ዩቲውበሮች ፣ ጭፍን የመከፋፈል ድጋፍ በድንቁርና የተሞላ ነው ። ለእንጀራ ተብሎ አገርን ለማፈራረስ ቢንዚን ማርከፍከፈ ተገቢ አይደለም ። … ለመሆኑ  ደቡብ ውሥጥ 60 ጎሣዎች ሥላሉ አገሪቱ በሌላት ሀብት 60 ቦታ የቢሮክራሲ መንደላቀቂያ መድረክ ታዘጋጅ ማለት ከድንቁርና የዘለለ ሥም ይሰጠዋል እንዴ ? ወያኔ የሰራውን ሥህተት ለማረም ባልተቻለበት መንገድ ላይ ዛሬም እንጓዝ ማለትሥ በራሱ እብደት አይደለም ወይ ?   በበኩሌ የትላንቱም ሆነ የዛሬው በመንጋነት ላይ የተመሠረተ ጫወታ በቀድሞዎቹ ቅኝ ገዢዎቻችን የሚታገዝ ነው ። ብዬ አምናለሁ ። የፖለቲካ ሥልጣንን በመከላከያቸው ና በደህንነታቸው ኃይለኝነት እንዳይናጋ አድርገው ሲያበቁ ፣ ላወጡት ህግ ተገዢ ሆነው በየአገራቸው በክብር ይኖራሉ ። በእኛ አገር የእነሱን ዓይነት ጠንካራ  የመንግሥት ቅብብሎሸሸ እንዲኖር ሥለማይፈቅዱ አሜሪካኔ አውሮፓ ፣ ትላንት  ኤርትራን አሥገንጥለዋል ። ዛሬም ትግራይን ለማስገንጠል እየሰሩ ነው ።

ኤርትራን ሲያሥገነጥሉ ሥለዴሞክራሲና ሥለ ሰብዓዊ መብት አሰያወሩ ነው ። ኤርትራ ከተገነጠለች በኋላ ግን ለብዝበዛቸው ነው የተጣደፉት ። ይሁን እንጂ ኢሳያስ አልፈቀደላቸውም ። እናም ኢሳያስን ለማሶገድ በብርቱ ጣሩ ። አልተሳካላቸውም ።  ዛሬ ደገሞ ትግራይን ለማሥገንጠል ፣ ትግራይ የሁመራን ኮሪደር እንድታገኝ እየጣሩ ነው ። ለብዝበዛቸው ሲሉም ትግራይን ለማሥገንጠል የማይፈነቅሉት ዲንጋይ የለም ። ቆም ብለን ወያኔ ያቋቋመልንን ከፋፋይ ሥርዓት አደገኝነት አሥተውለን አሽቀንጥረን ካልጣልነው በስተቀር ፣ በመሰዋትነት የሰራነው የአባይ ግድባችን እንኳን ዋሥትና አይኖረውም ። እያደጉ የመጡት ከተሞቻችንም መፈራረሳቸው አይቀርም ። ይኽ እንዳይሆን ጨከን ያለ  የሥርዓት ለውጥ ያሥፈልገናል ።

በበኩሌ ለሥልጣን የቋመጥኩ ፖለቲከኛ ባልሆንም ፣ ” ሥልጣን ለአንድ ቀን ቢሰጥህ ምን ታደርጋለህ ? ” ተብዬ ብጠየቅ ” ሥልጣን ለአንድ ቀን ቢሰጠኝ ክልል የሚባለውን ሥያሜ አፈራርሼ የቀድሞውን ክፍለ አገር አነብር ነበር ። ለሉዩነት ምክንያት የሚሆኑትን እና ለጥቂቶች ብዝበዛ የተሰነዱትን ማዋቅሮች ሁሉ አፈራርሳቸው ነበር ። በቃ ሁሉንም እንደ አገሬ መከላከያ ኢትዮጵያዊ አደረጋቸው ነበር ።   ጎሣ  እንደማትመርጠው ሴቷ ኢትዮጵያ በህዝብ ሥም የሚነግደውን ፖለቲከኛ ተራ ህዝብ ና ሰው እንደሆነ አሳውቀው  ነበር ። ” ከዛሥ  ? ” አትሉኝም ? ” ከዛማ !  በህግ የበላይነት የሚያምን ፤ ፈጣሪን የሚፈራ ፤ በህዝብ ምርጫ ሥልጣንን በየጊዜው ከህዝብ እየተረከበ አገር የሚመራ ፤ የፖለተካ ፓርቲ እንዲኖር አሥፈላጊውን ፖለቲካዊ ምህዳር  እንዲኖር መንገዱን አደላድል ነበር ።   ፈጣሪ በፈጠራት ምድር  በኢትዮጵያ ተወልዶ አየኖረ ፤ ከሥግብግብነቱ የተነሳ ኢትዮጵያን የሚጠላውን ደግሞ  ፣ አይቀጡ ቅጣት እቀጣው ነበር ። ይኽንን  በህግ የበላይነት ሥለማደርገው 90 %  ኢትዮጵያዊ ከጎኔ ሆኖ  ዓላማዬን እንደሚያሳካ አመሰግናለሁ ።

ተጨማሪ ያንብቡ:  ኢትዮጵያዊነት እያበበ ነው ወይስ እየጠወለገ?

እናም ዛሬ በትረ ሥልጣኑንን የያዘው ምን ይጠብቃል ? በከንፈር ሽንገላ ብቻ ከሌባ ካድሬ  ጋር  እየተለማመጠ አገሪቱን ወደ አደጋ የበለጠ እያሥጠጋ መጓዝን ይመርጣል ወይስ የሌቦች እጅ እንዲሰበሰብ ፣ የህዝብን ሀብት በመመዝበር ሺዎችን በርሃብ የቀጡና በመቶ የሚቆጠሩ እንዲሞቱ ያደረጉትን በሥቅላት በመቅጣት አዲስቷን ኢትዮጵያ በጠንካራ አለት ላይ ለመገንባት በብርቱ ይንቀሳቀሳል ? ወይስ “ በሬ ካራጁ  ….” እንዲሉ ዛሬም በያዘው በከፊል ጨለማ መንገድ ይጓዛል  ?  እስከጊዜው …..

 

1 Comment

  1. የብሄር ፓለቲካ ከቁር በማያድን ቡትቶ እንደሚጣሉ የደጀ ሰላም የእኔ ቢጤዎ ነው። ቀደው ሲካፈሉ አንዳቸውንም የተጣሉበት ነገር ከብርድ አያድናቸውም። በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ አሸብራቂ ሥፍራ ያላቸው የጉራጌ ህበረተሰብ የሚታወቁት በሃገር ወዳድነታቸውና በሥራ ባላቸው ትጋት ነው። ወያኔ በዘመኑ ክፋትን ሲዘራ አክ እንትፍ ካሉት ጥቂት ወገኖች መካከል በዋናነት ተጠቃሽ ናቸው። ታዲያ ዛሬ ምን ነክቷቸው ምን ሽተው ነው በክልል የፓለቲካ አዙሪኝ ውስጥ የገቡት? መልሱን ለክልል ጠያቂዎቹ እተዋለሁ።
    ይህ ዓለም አሽሟጣጭ ዓለም ነው። አንድ ለመሞት ሲያጣጥር ሌላዋ ለመውለድ የምጥ ጭኸት ታሰማለች። ከርፋፋው የሃበሻ ፓለቲካ ደግሞ ለዘመናት በዚህም በዚያም ሲያላፋን ያለምንም ትርፍ ጊዜው ያሽቆለቁላል። ተናጋሪና አሽሙረኛ በሞላባት ሃገር ላይ ለችግር መፍትሄ ፈልጎ ህብረ ብሄራዊነትን ለብሶ ኑ፤ ና እኛ ጋ አብረን እንኑር የሚል እንጂ የዘርና የክልል አጥር አጥረው አትድረሱብኝ የሚሉን ሁሉ ራሳቸውን ጭምር ለጥፋት እያዘጋጅ እንደሆነ አይታያቸውም። መለየት ጊዜውና ሰአቱ አልፎበታል። መኖር በዓለም ዙሪያ በአንድነት ነው። የጎሳ ፓለቲከኞች ዝናብ የሌለው ደመና ናቸው። በህዝብ ስም በመነገድ ከኢትዮጵያ የውጭና የውስጥ ጠላቶች ጋር እየተሰለፉ የህዝባችን መከራ ከማባባስ ሌላ ትርፍ አያስገኙም። ለዚህ ነው የድመቷ ተረትን ልክ የሚያደርገው። “ሺህ ቢታለብ ከገሌ አያልፍም”። ግን በዚህ ሁሉ የስካር ፓለቲካ ህዝባችን መቼ ይሆን የሚነቁት? ሃገሪቱስ ከስንት ክልል ነው የምትከፈለው? ማቆሚያውስ የት ድረስ ደርሶ ነው? ግን ገጣሚው ከዘመናት በፊት እንዳለው በዚሁ በዘጋው ይሻላልና በቃኝ።
    እስቲ አንቺ አሞራ ልጠይቅሽ ወሬ
    ተቃጥሏል መሰለኝ ሸተተኝ ሃገሬ።

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Share