ሐምሌ 22 ቀን 2014ዓም(29-07-2022)
አገርና ሕዝብ የማይለያዩ የአንድ አካል ሁለት ገጾች ናቸው። ሰው ያላገር ተንቀሳቃሽ እንስሳ(Roving Animal) ነው። አገርም ያለሰው ባዶ መሬት እንጂ አገር አይባልም።አገርን አገር የሚያሰኘው የሰው መኖርና ከባቢውን በአገር ደረጃ ሥርዓትና መልክ አሲዞ ሲመሠርተው ነው።መሬትን ፈጣሪ ሠራት ሲባል አገርን ደግሞ ሰው ሠራ ማለቱ ትክክልና ተገቢ ነው።በውሃ የተከበበችዋን ሆላንድን እንደምሳሌ ብንወስድ ቀድሞ ውሃ የነበሩትን አካባቢዎች ወደመሬት በመለወጥ ሰፋፊ እርሻና መኖሪያ በማድረጋቸው “እግዜር መሬትን ሠራ፣ ደቾች ግን ሆላንድን ሠሩ” የሚል ችሎታን የሚገልጽ የኩራት አባባል እንዳላቸው ይታወቃል።
በሰው ልጆች ወይም በነዋሪው ጥረትና ድካም ባዶና ምድረበዳ የነበረውን መሬት በአገር ደረጃ በመገንባት ብዙ ሥራዎች ተካሂደዋል።መንገዶች ተቀይሰዋል፣ ቤቶችና መንደሮች ከዚያም ከተማዎች ተገንብተዋል፣የእርሻ እንቅስቃሴዎች፣የመአድን ቁፈራዎች ያንንም ተከትሎ ፣የፋብሪካ ተቋማት—ወዘተ ተስፋፍተዋል።የነዋሪው ፍላጎት እዬጨመረ ሲሄድ ለዚያ ፍላጎቱ መሟላት የተለያዩ እንቅስቃሴዎች አድርጓል።ይህንንም ለማድረግ ያስቻለው በአንድ ቦታ ወይም አገር ብሎ በመሠረተው መሬት ላይ የረጋ ኑሮ(Sattled life) ሲጀምር ነው።እነዚህን እንቅስቃሴዎች በተደራጀ መልኩ ለማከናወን ብዙ ደረጃዎችን ያለፈ ሲሆን የህብረተሰብ አስተሳሰብ እያደገና ይበልጥ ቅርጽ እዬያዘ ሲመጣ መንግሥት የሚባል የበላይ አካል ለመፍጠር ቻለ።በመጀመሪያ ደረጃ ላይ ይህንን መንግሥት የተባለ የበላይ አካል ሃብትና ጉልበት ያላቸው ግለሰቦችና ቤተሰቦች የሚቆጣጠሩት ነበር፤አሁንም ድረስ የሚቆጣጠሩ ንጉሶችና ከሊፋዎች አልጠፉም።የነዚህ ፈላጭ ቆራጭነት በጊዜ ሂደት እዬተቀዬረ መጥቶ የሕዝቡን ጥቅምና የበላይነት የሚያስከብሩ የፖለቲካ ድርጅቶችና ከነሱም ተመርጦ በተውጣጣ የሕዝብ ተወካይ ምክር ቤት የአገር ጉዳይ የሚመክርበትና የሚወስንበት ደረጃ ላይ ተደረሰ።ለዚህ ደረጃ መድረስ በጥቂቶች ሥልጣን ላይ ባሉት መልካም ፈቃድና ደግነት ሳይሆን ሕዝቡ ባደረገው ያላሰለሰ ትግልና በከፈለው መስዋእትነት ነው።በዚህ ሂደት የአገር ነክ ጉዳይና ጥቅም ከጥቂት ግለሰቦች ወሳኝነት ተላቆ ሕዝብ የሚሳተፍበትና የሚወስንበት ደረጃ ላይ ለመድረስ ተቻለ።ከዚህም ጋር ተያይዞ ዕቅድና ዘዴ የሚቀይስ፣የሚመራና የሚከታተል ከነዋሪው ሕዝብ የተውጣጣ አመኔታ የሚጣልባቸው፣ችሎታ ያላቸውና ለህሊናቸው ያደሩ ሰዎች የሚካተቱበት መንግሥታዊ ስርዓት በመዘርጋት የነበረውን የአንድ ሰው ወይም ቡድን ፈላጭ ቆራጭነት በሕዝባዊ መንግሥት ለመተካት ተቻለ።ይህ አካል ለሕዝቡ ተጠሪ እንጂ ሕዝቡ ለሱ ተጠሪ አይሆንም።የተጣለበትን አደራና ሃላፊነት ካልተወጣ ይጠዬቅበታል።የተሠጠው ሥልጣን ሊያገለግልበት እንጂ ሊገለገልበት ስላልሆነ ከዚያ ሸብረክ ቢል ፣ለራሱ ጥቅም ካዋለውና ከተጠቀመበት በሕዝቡ ፍላጎት ለረቀቀውና በመተዳደሪያ ደንብ በተሰናዳው ሕግ መሠረት ይጠዬቃል፤ ጥፋቱም ከተረጋገጠ ይቀጣል።ይህም ብቻ አይደለም የመንግሥትን ሥራ የሚከታተሉና የሚያስፈጽሙ የፍትህና የሙያ ተቋማት አሉ።እነዚህ በነጻነት የሚንቀሳቀሱ ተቋማት ለሕዝቡ ዋስትና የሚሰጡ ብቻም ሳይሆኑ የመንግሥትን ምንነት የሚያሳዩ መስተዋቶች ናቸው።መንግሥት የሚመዘንበት ሚዛን በነዚህ ተቋማት ስር የመውደቁ ወይም ተቋማቱ በመንግሥት ባለሥልጣኖች ፍላጎት ስር መውደቃቸው ይሆናል።
ሕዝብ የመንግሥትን ብቻ ሳይሆን የመሪዎቹን የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴ መከታተልና ማወቅም አለበት።ምን እንደሚሠሩ፣ከማን ጋር እንደመከሩ፣ምን እንደተስማሙ፣ምን እንዳገኙ ምንስ እንደሰጡ ሁሉንም ሕዝቡ ሊያውቀው ይገባል።አገርንና ሕዝብን በሚመለከተው ጉዳይ ላይ በስከጀርባ የሚፈጽሙት ነገር አይኖርም።፤ሌላው ቀርቶ በግል ኑሯቸውም ቢሆን ስለቤተሰባቸው ያላቸው ግምትና ግንኙነት ለስብእናቸው መለኪያ ይሆናል።በማህበራዊ ኑሯቸውም የሚያንጸባርቁት ጸባይና ልማድ፣ካያያዝ ይቀደዳል ፣ካነጋገር ይፈረዳል እንዲሉ ከአንደበታቸው የሚወጣው ቃል ሳይቀር ለማንነታቸውና የተጣለባቸውን አደራና ሃላፊነት ለመወጣት መቻል አለመቻላቸውን የሚለኩበት መመዘኛ ነው።
በዚህ አይነት ለተመሠረተ የሕዝብ አገርና መንግሥታዊ ሥርዓት በየብስም በባሕርም አልፎ ተርፎም በአዬር ክልሉም ያለሁሉ፣የዚያ አገር ሕዝብ ሃብትና ንብረት ነው።ለመላው ሕዝብ ጥቅም ይውላል።መንግሥት የተባለው አካል ወይም መሪ ካለሕዝቡ እውቅናና ፈቃድ የሚያዝበትና የሚጠቀምበት የግል ወይም የቡድን ይዞታ አይሆንም።አንድ ግለሰብ ወይም ቡድን የሚያዝበትና የሚቆጣጠረው ከሆነ፣የቡድን ወይም የግለሰብ ፍላጎት የሚከናወንበት አገር ከሆነ ያ አገር የሕዝብ ሳይሆን አምባገነን ወይም አምባገነኖች የሚፈነጩበት ይሆናል ማለት ነው።በሃብቱም በመብቱም ላይ የሚፈርዱት ጥቂቶች ይሆናሉ።በሕዝቡም ኑሮ ብቻ ሳይሆን በእምነቱ፣በባሕሉ ጭምር ጣልቃ እዬገቡ የነሱን ባሕልና እምነት እንዲከተል ያስገድዳሉ።ለሕግ ተጠያቂ ከመሆን አልፈው በሚሠሩት ወንጀል ባለመጠዬቅ ይባስ ብለው ሕዝብ እንዲደግፋቸውና እንዲከተላቸው አስገዳጅ መመሪያ ያወጣሉ።
ጊዜው በተለወጠ ቁጥር መልክና ጸባያቸውን እዬለወጡ ዘመኑ ባስገኘው እውቀትና ችሎታም እዬታገዙ የአምባገነን አገዛዛቸውን ለማርዘም ብዙ ይጥራሉ።በጥቅም የሚደለለውን በጥቅም፣በማንነት የሚደለለውን በጎሳ ማንነቱ፣በሃይማኖት የሚደለለውንም በዚያው መንገድ በደካማ ጎኑ እዬገቡ ለማጭበርበርና ተከታይ ለማድረግ ይሞክራሉ።እምቢ ያለውንም በሚቀልቡት ወታደር ወይም በመደቡት ዳኛ መቀመቅ ይከቱታል፤ይገሉታልም።እዚህ ደረጃ ላይ ሲደረስ ሕዝብ የራሱ አገር ባለቤት ሳይሆን ለአገሩ ባዳ ይሆናል ማለት ነው።
ከላይ የቀረበውን ትንታኔ ይዘን ወደ አገራችን ስንመለስና ያለውን መንግሥትና ስርዓት ስንፈትሸው ሕዝብ የአገሩ ባለቤት አለመሆኑንና አንድ ግለሰብና በዙሪያው የተኮለኮሉ ዘራፊዎች ያሻቸውን የሚያደርጉበት የአምባገነኖች አገር ሆኖ እናገኘዋለን።ኢትዮጵያ ባሳለፈችው የረጅም ጊዜ ታሪኳ ሕዝቡ ያገሩና የመብቱ ባለቤት የሆነበት ወቅት የለም።በዘውዳዊ አገዛዝ፣በወታደራዊ አገዛዝ ከዚያም በጎሳ ፖለቲካ የተበከሉ ቡድኖችና ግለሰቦች የፈነጩባት አገር ነች።በጉልበት በዬተራ የመሪነት ቦታውን የያዙት እነዚህ የመንግሥትን ስልጣን የተቆጣጠሩት ግለሰቦችና ቡድኖች ባገሪቱ ሃብትና ንብረት ብቻም ሳይሆን በዜጎች ህይወት ላይ የመወሰን ስልጣን ነበራቸው ፤አሁንም አላቸው።ሌሎቹን ትተን ከሰላሳ ሁለት ዓመት ወዲህ ያሉትን በጎሳ ፖለቲካ አገር የሚያተራምሱትን ብንመለከት የስብስቡ መሪ የሆነው ግለሰብ ያሻውን ሲያደርግበት የኖረና ያለበት ነው።ከሕዝቡ በኩል ወይም ለሕዝቡ የሚቆረቆሩ ጥያቄ ቢያነሱ የማይደመጡበት አልፎ ተርፎም የበቀል እርምጃ የሚወሰድበት፣የሚታሰሩበት፣ የሚገደሉበት ስርዓት ነው የሰፈነው።
ያለፉትን አራት ዓመታት የመራውን ግለሰብ አብይ አህመድን ብንመለከት በሕዝብና በአገር ስም የሚሰጠውንም ሆነ በብድርና በእርዳታ የሚገኘውን ገንዘብ እንደ ግል ሃብቱ ሲበትን፣ለምን እንዲህ ይሆናል ብለው የጠዬቁትን ምን አገባችሁ እያለ ሲሳደብና ሲያንጓጥጥ ማዬቱ የተለመደ ነው።እስከአሁን ድረስ በአራት ዓመት ውስጥ በእርዳታና በብድር ከ30 ቢሊዮን ዶላር በላይ ቢገኝም እንዴትና ዬት እንደገባና እንደወጣ፣የተፈረመው ውልና ስምምነት፣በምንስ ዋስትና እንደሆነ ሕዝቡ ቀርቶ በዙሪያው ያሉት የፓርላማ ተብዬው አባላትም ሆኑ የተቃዋሚ የፖለቲካ ድርጅት አባላት አያውቁም። አብይ አህመድ ያሻውን ያደርጋል።እሱን መቃወምና መጠዬቅ ሃጢያት ሆኖ የሚቆጠርበት አገር ሆኗል።
የታደሉት አገር ሕዝብ እንኳንስ በስሙ የሚሠራውን ቀርቶ መሪዎቹ የት እንደዋሉና ከማን ጋር እንደተገናኙ ካወሩት ጭምር የማወቅ መብት አለው። መሪው የሚያደርገው ሁሉ ፍለፊትና ይፋ ነው፤ከሕዝቡ ጀርባ የሚከናወን አንዳችም ነገር የለም።ልደብቅ ቢሉት ጎልጉሎ የሚያጋልጥ የፖለቲካ ድርጅት፣ የፍትሕና የዜና አውታር ዝግጁ ነው።ወደ ኢትዮጵያ ስንመጣ ነገሩ ሁሉ የተገላቢጦሽ ነው።እንኳንስ ብድርና እርዳታው፣እንኳንስ የውጭ ግንኙነቱ ቀርቶ ጧት ማታ ደግፉኝ እዬተባለ የሚያስቸግሩት ሕዝብም ሆነ ደጋፊ መሪው ሲጠፋና ሲሰወር የት እንደሆነና ምንስ እንደገጠመው ለማወቅ አልተቻለም።የሰሞኑ የአብይ መሰወር ያመጣው ብዥታና ስጋት ከዚህ የመነጨ ነው።
ለልዩ ልዩ ግምታዊ ወሬዎች ሕዝቡ ሲጋለጥ አንድም የመንግሥት አካል ሃቁን ለመንገር አልደፈረም።ሕዝቡን የማይመለከተው ጉዳይ ሆኖ ተወስዷል።በጥይት ተመቶ ቆስሏል፣አንጎሉ ውስጥ ደም ፈሶ ስቷል፣ሞቷል ፣የሚሉት ወሬዎች እዬተናፈሱ ሕዝቡን ግራ አጋብተውታል።ግራ መጋባት ብቻም ሳይሆን በአንድ ግለሰብ መዳፍ የምትሽከረከር አገር በመሆኗ በዚሪያው ያሉ ጎሰኞች ሥልጣኑን ለመውሰድ የሚያደርጉት የውስጥ ግብግብ ይበልጥ ሽብር ለቆበታል።የውጭ ጠላቶችም እንዲሁ አጋጣሚውን በመጠቀም ያሻቸውን ለማድረግ አሰፍስፈው ይገኛሉ።ድንበር ጥሰው የገቡ የጎረቤት አገር ወራሪዎች እውስጥ ካለው አገር አፍራሽ ሃይል ጋር ተቀናጅተው እዬሠሩ ነው።ትናንት እንኳንስ ድንበር አልፈው ባሉበት ቦታም ሆነው በአንድ ኢትዮጵያዊ ላይ ጥቃት ለመሰንዘር የማይደፍሩት ምናምንቴዎች ዛሬ ውሻ በቀደደው ብለው የጥቃት ክንዳቸውን አንስተዋል።ኢትዮጵያ የዓለም መሳቂያ መሳለቂያ ሆናለች።ሃያላን መንግሥታት የሚፋጩባት የጦርና የፖለቲካ ጉልበት የሚያሳዩባት ባለቤት አልባ አገር ሆናለች።ሕዝቡም ለአገሩ ባዳ ሆኗል።ምን እንደሚካሄድ አያውቅም።ስለሱና ስለሃገሩ አረቦችና ምዕራባውያውያን የበለጠ መረጃ አላቸው። ማወቅ ብቻም ሳይሆን ወሳኞች ሆነዋል።የሚፈልጉትንም ለማድረግ የሕዝቡ በአንድነት አለመቆምና አለመደራጀት ዕድል ሰጥቷቸዋል።
የኢትዮጵያ ሕዝብ በኑሮ መሰቃዬቱ ሳያንሰው በማንነቱ ለያይተው ለመብቱም ላገሩም እንዳይቆም የሚደረገው ሴራ ቀላል አይደለም።እህል እዬለመነ ባለበት ሁኔታ ኢትዮጵያ ሕዝቧን መቀለብ ችላለች፣ሕዝቡ ብዙ ያልነበሩትን አግኝቷል፤ፍትህ ተከብሮለታል፣መብቱ ተረጋግጦለታል፤ለዚያም ለሦስት ቀናት ግራ ደረታችሁን በቀኝ እጃችሁ ደግፋችሁ መንግሥትንና ፈጣሪን አመስግኑ፣የሚል የግዴታ ትዕዛዝ በመንግሥት ቃል አቀባዮችና በአድርባይ ሰባኪዎች በኩል ይተላለፋል።በመሬት ላይ ያለው እውነታ ግን ሕዝብ በማንነቱና በሚከተለው እምነት ከመኖሪያው እዬተፈናቀለ፣እዬተገደለ፣የዳቦ ያለህ እያለ ለልመና እጁን እዬዘረጋ፣ሰላም አጥቶ በስጋት እዬዋለ እያደረ፣መንግሥትን ነቅፈሃል እዬተባለ ያለፍርድ ወህኒ እዬተወረወረና ያለበት ሳይታወቅ ታፍኖ በጨለማ ቤት መከራውን እያዬ ነው።ይህንንና ሌላም ብዙ መከራ ነው ብዙ በጎ ነገር አግኝተሃልና አመስግን የሚባለው። አብይ አህመድ ከእይታ ከተሰወረ ሳምንታት አልፈዋል፤የሚሰጠው ምክንያት ግን እርስ በራሱ የሚጋጭና የተምታታ ነው።ቀደም ሲል በወለጋ ጦሩን እዬመራ ነው ሲባል ቀጥሎም አንድ ጊዜ ቱርክ ሌላ ጊዜ ዱባይ ውስጥ በሕክምና ላይ ነው ይባላል።ምንም እንኳን እንደሰው በሌላው ላይ መጥፎ ነገር መመኘቱ ተገቢ ባይሆንም አብይ አህመድ ተረፈም አልተረፈም ለኢትዮጵያ ሕዝብ ያው በገሌ ነው።ተርፎ የሚያገኘው የለም ሞቶም የሚያጣው የለም።የሱ አለመኖር ለባለተረኞቹ የሥልጣን መሰላል ይሆናል እንጂ ለኢትዮጵያ የሰላም በር አይከፍትም።ለኢትዮጵያና ለሕዝቧ ሰላምና አንድነት ብሎም እድገት አብይና መሰሎቹ የዘረጉት የጎሳ ስርዓትና የሚመሩበት “ሕገመንግሥት” የሚሉት የጥፋት ሰነድ ሲወገድና በሕዝባዊ መንግሥትና እውነተኛ ሕገመንግሥት ሲቀዬር ብቻ ነው። ላለፉት ሰላሳ ሁለት ዓመታት በሕዝቡና በአገሪቱ ላይ ወንጀል የፈጸሙት በሙሉ፣ኢሕአዴግና ብልጽግና ፣የዚህ ጎሳ የዚያ ጎሳ ነጻነት አውጭ ነኝ እያሉ በውጭ ሃይሎች ድጎማ እዚህና እዚያ እዬተቅበዘበዙ ሕዝብን ሰላም የነሱ፣የገደሉ፣ያስገደሉ፣ያፈናቀሉ፣የዘረፉ፣ክልል ብለው ሕዝብን የነጣጠሉ፣ኢትዮጵያን ለመበታተን የቋመጡ በሙል ከፖለቲካው ዓለም ተወግደው በፈጸሙት ወንጀል ሲጠዬቁ ብቻ ነው።በነሱ መካከል የሚደረግ እርቅና ድርድር ለሕዝቡና ለአገሪቱ ዘለቄታዊ ሰላምና አንድነት ብሎም እድገት አያበቃም።በጀመሩት የጥፋት መንገድ እንዲቀጥሉበት ማድረግ ይሆናል።
ሕዝቡ ካለበት ተደጋጋሚ ውድቀትና መከራ አገራችንም ከተጋረጠባት የመበታተን አደጋ ለማዳን በኢትዮጵያዊነታቸው የሚያምኑ፣በጎሳና በሃይማኖት ልዩነት ያልተበከሉ፣በአንድ ኢትዮጵያዊነት እንጂ ክልልና ጎጥ ብለው የማይሰለፉ ዜጎች በአንድ ላይ ተሰባስበው የሚፈለገውን መስዋእትነት ሲከፍሉና ሕዝባዊ መንግሥት ሲያቆሙ ብቻ ነው።
ሕዝብ ያገሩ ባለቤት ይሁን!!ስለሃገሩ የማወቅ መብቱ ይከበር!!ሕዝብ ለአገሩ ባዳ አይሁን!!!
አገሬ አዲስ
እልፍ አእላፋትን በየቀኑ ሊፈጅ አቅም አለው አሁን
ስለዚህ አድበን አሜን እንበለው ጃን መራቂ እንሁን
ብላችሁ ከሆነ ያሁኑ ምስጋና
ሺህ አመት ባላዬ ይንገሥ ብልጽግና
ብዬማ አልጮህም አጽሙ ሳይነሳ
እሱ በላከው ጃርት ተመቶ ወሪሳ
ወለጋ መተከል ዱር የበላው ሬሳ
My dear Brother, Agere,
You are a man of integrity. You struggled for your beloved Country for over 40 years. Despite the genuine sacrifices made, things are now getting from bad to worse. Instead of sitting and clapping hands, I do not see aggressive and convincing struggles today. Our people are falling like litters on a daily basis simply because they are Amharas or Orthodox, etc. The beloved Country that was the symbol of liberty, civilisation and cohabitation is now on the verge of collapse. Can we see that? Would it help anybody?
As you rightly mentioned, let us wake up and struggle to make sure that the divisive ‘constitution is changed and a genuine democratic system established, the system that we have been struggling for decades, The struggle that was hijacked by successive dictatorial regimes.