July 20, 2022
9 mins read

በህገ አምላክ! ወይዘሮ አዳነች – ገለታው ዘለቀ

ከአንድ ሁለት ሳምንታት በፊት ወደ ዋሽንግተን ዲሲ አቀናሁ። የጉዞየ አላማ እስክንድር ነጋን ለማግኘት ነበር። ታዲያ በነዚህ ሁለት ሶስት ቀናት ቆይታየ በዲሲ የሚኖሩ ወንድሞች ታክሲ እንድይዝ አይፈቅዱም። ካለሁበት በረው ይመጡና ወደ ፈለኩት ያደርሱኛል። ወንድማችንን እስክንድርን አግኝቼ የሆድ የሆድ ተጫውተን ከጨረስን በሁዋላ መመለሻየ ደረሰና እነዚያው ውለተቸው የበዛብኝ ወገኖቼ ወደ በረራየ ይዘውኝ አንጓዛለን። ወቅቱ ሰመር ስለሆነ ሙቀቱ ፍጥረታትን ሁሉ ያስለከልካል። ያም ሆኖ ግን ግራና ቀኝ የሚታዩት ታሪካዊ ቦታዎችና የሃገሩ ውበት ያማምራል።

ከሜሪ ላንድ ወደ ዋሽንግተን ዲሲ ሬገን አየር ማረፊያ ስንነዳ ሜሪላንድና ዋሽንግተን ዲሲ ወሰን ላይ ደረስን። አብሮኝ ያለው ጓደናየ ኣካባቢውን በሚገባ ያውቃልና ብዙ ነገር ሲገልጽልኝ እየሰማሁ አልፋለሁ። ነገር ግን ከመግለጫዎቹ አንዱ ሙሉ ትኩረቴን ስቦኝ ዛሬ ይሄው ለሃገሬ ሁኔታ አስተማሪ ነገር አገኘሁበትና ልጽፈው ተነሳሁ።
መኪናውን እያሽከረከርን ዲሲና ሜሪላንድ ድንበር ላይ ስንደርስ ይህ ወዳጄ አንዲህ ሲል ጠየቀኝ
ከዚህ ከመጣንበት ሜሪላንድ አካባቢ አንድ ሹፌር በጣም እያበረረ ሲሄድ ፖሊስ ቢያየውና ቢከተለው ይህ ሰው ሳያቆም ዲሲ ቢገባበት ፖሊስ ምን የሚያደርግ ይመስልሃል? ልክ የሜሪላንድ ወሰን ላይ ሲደርስ ፖሊስ ይቆማል። ወደ ዲሲ ተሻግሮ መያዝ ኣይችልም አያለ ያወጋል።። በምንም አይነት ፖሊስ ተሻግሮ ይህንን ሰው ለመያዝ ሙከራ አያደርግም። አንደዚያ ቢያደርግ ወንጀል ፈጸመ ማለት ነው :: ራሱ ፖሊሱ ይታሰራል ማለት ነው። ከባድ ወንጀሎችን በመገናኛ በመነጋገርና በመጠቋቆም ይያዛል አንጂ ፖሊስ ከአንድ ስቴት ወደ ሌላው ተሻግሮ ምንም ነገር የማድረግ መብት የለውም። ሲል ይህ ሰው ያብራራል።
አውነት ነው በተባበረችው አሜሪካ ውስጥ ስቴቶች ሁሉ የየራሳቸው ህገ መንግስት፣ ህጎች፣ ደንቦች ኣላቸው። አነዚህ ህጎች የሚሰሩት በዚያ በስቴቱ ወሰን ሰማይና ምድር ላይ ብቻ ነው። ለምሳሌ ኒው ሃምሸር መኪናችሁ ኢንሹራንስ ባይኖረውም ከመንዳት አትከለከሉም። ማሳቹሴትስ ደግሞ መኪና ለመንዳት መጀመሪያ ኢንሹራንስ ያስፈልጋል። የስቴቶቹ ህገ መንግስታት ልእልና በየስቴቶቹ ብቻ ነው የሚሰራው። የፌደራሉ ህገ መንግስት ደግሞ በሁሉም ስቴቶች ላይ የበላይ ነው።
ይህንን ምሳሌ ያመጣሁት በቅርቡ ወይዘሮ አዳነች አበቤ ለምክር ቤቱ ሲናገሩ የሰማሁትን ነገር ሃይ ለማለት ነው። ወይዘሮ ኣዳነች “ህገ መንግስታችን የኦሮሚያ ዋና ከተማ አዲስ አበባ ናት ይላል” ሲሉ ተደምጠዋል። ይህንን የሚለው የኦሮሚያ ህገ መንግስት መሆኑ ይታወቃል። የፌደራሉ ህገ መንግስት ይህንን ኣይልም። ዋናው ጉዳይ እኒህ ሴት መረዳት ያለባቸው የኦሮሚያ ህገ መንግስት በኣዲስ ኣበባ ላይ ምንም ኣይነት ልእልና እንደሌለው ነው። ክልሎች ያላቸው ህገ መንግስት በራሳቸው ምህዋር ላይ ብቻ ነው የሚሰራው። ስለዚህ ይህንን የኦሮሚያን ህገ መንግስት ኣምጥተው ህገ መንግስታችን አዲስ አበባ የኦሮሚያ ዋና ከተማ ናት ይላልና ይህንን ለመተግበር ይህ ምክር ቤት ይሰራል ማለት የህግ መተላለፍ ነው። ህገ ወጥነት ነው። አዲስ አበባ የኢትዮጵያውያን ሁሉ ዋና ከተማ ስትሆን ሁሉም ክልሎች በዚህች ዋና ከተማቸው ላይ ሙዚየም መክፈት፣ ከተማችን እንድታድግ አስተዋጾ ማድረግ፣ የፌደራል ተቋማቸውን መገንባት ይችላሉ። ከዚህ ውጭ አንድ ክልል ለብቻው አዲስ ኣበባ የኔ ዋና ከተማ ናት ቢል የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ይህንን ተቀብሎ መታገል መስራት የለበትም። ስለሆነም ወይዘሮ አዳነች አበቤ ይህንን በማለታቸው መጠየቅ አለባቸው። የኦሮሚያን ህገ መንግስት አዲስ ኣበባ ላይ አንዲሰራ መፍቀድ ማለት የኦሮሚያ አስፈጻሚ አካል በዚህች ከተማ እንዲቋቋም መፍቀድ ማለት ነው። አዲስ አበባ ውስጥ የኦሮሞ ፖሊስ፣ የኦሮሞ ፍርድ ቤት፣ የኦሮሞ ኣቃቤ ህግ……… አንዲቋቋም ማድረግ ማለት ነው። ይህ ደግሞ ከተማዋን የተከፋፈለች ከተማ ያደርግና ያፈርሳል። ስለዚህ ይህ የአዳነች አበቤ ምክር ቤት የያዘው ጎዳና እጅግ አደገኛ መሆኑን በተግባር ስላሳየ አዲስ አበባ ሆይ ችላ አትበል።
በውነት በውነት ፖለቲከኞች ከዚህ ከብሄር ፖለቲካ መውጣት አለባቸው። የብሄር ፖለቲካ ለማንም አይጠቅምም። የብሄር ፖለቲካ ስናራምድ መጀመሪያ የምናስመታው ቆመንለታል የምንለውን ብሄር ነው። መጀመሪያ የምናስጠላውና በጥላቻ ኢላማ ውስጥ የምናስገባው ያንን የኛ የምንለውን ብሄር ነው። የብሄር ፖለቲካ የራሳችን የምንለውን ብሄር ካስጠቃ በሁዋላ ሌሎችንም ያጠቃል። ለማንም የማይጠቅም ኋላ ቀር ፖለቲካ ነውና በተለይ የአዲስ አበባ አስተዳደር ከዚህ መጽዳት አለበት።
የብሄር ፖለቲካ ዋና አራጋቢ የነበረው ህወሃት በኣንድ ወቅት ብዙ የተኩራራ ቢሆንም ዛሬ የትግራይን ህዝብ ሳይቀር ይዞ መከራ ውስጥ ከቶታል። የጂኖ ሳይድ ዋች ፕሬዝደንት የነበሩት ዶክተር ግሪጎሪ ስታንተን ከብዙ አመታት በፊት የተናገሩት ነገር ይገርመኛል። የዘር ፖለቲካን ክፉነት ሲያስረዱ ምን አሉ? አሁን መለስ ለሚያደርገው ጥፋት ትግራይ ዋጋ ትከፍላለች ብለው ነበር። ቪዲዮውን አዚህ ጋር ማዳመጥ ይቻላል።
ይህንን ያመጣሁት ለምንድን ነው? የብሄር ፖለቲካን የሚያራምድ አስተዳደር በተለይ ደግሞ ለአዲስ አበባ አደጋው ብዙ ነውና የአዳነች አበቤ ካቢኔ ለውጥ ያስፈልገዋል። አንዲህ ያለ የህግ ጥሰት በአደባባይ እያየን ዝም ማለት ተገቢ አይደለም።
 እግዚአብሄር ኢትዮጵያን ይባርክ
 ገለታው ዘለቀ

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Go toTop