እንደ ሰው የሰውነት ግዴታችንን እንደ ትውልድም የትውልድ አደራን እንወጣ!

በላይነህ አባተ (abatebelai@yahoo.com)

ሰውነት ተወልዶ፣ በአካል ማደግ፣ መማር፣ መስራት፣ ገንዘብ ማፍራት፣ መብላት፣ መጠጣትና እድሜን ቆጥሮ ወይም በበሽታ መሞት አይደለም፡፡ ሰውነት ሰው የሆነ ሁሉ የሚለብሰው ቆዳ ነው፡፡ ሰው ተሆን ይህ በጋራ የምንለብሰው ቆዳ ሲሰቃይና ሲታረድ ህመሙ እኩል ሊሰማን ይገባል፡፡
https://youtu.be/1hMVeENjVewi99999999o

 

ሕዝብ ሆይ! ዶሮ ጫጩቶቿን ተጭልፊት ስትጠብቅ፤ በግ ግልግሎቿን ተቀበሮ ለማዳን የሚቻለውን ስታደርግ፣ እኛ ሰዎች የስድስት ቀን ህፃንን በጭራቆች በስድስት ባሩድ ተመደብደብ ለማዳን ምነው አቃተን? ህፃናትን ከታረዱ እናቶቻቸው አስከሬን ውስጥ እንደ ድንች ፈንቅለን ማውጣት ሰልችቶን “ግፍ በቃ!” ብለን በአንድነት ለመነሳት ምነው ዘገየን?

የናዚ ወንጀለኞች እየታደኑ ወህኒ መውረድ በመላው ዓለም አሁንም ቀጥሏል፡፡ በዚህ ሳምንት ብቻ ከሰባ ሰባት ዓመታ በፊት በአይሁዳውያን ጪፍጨፋ የተሰሳተፈ አንድ የሂትለር ጀሌ በ101 ዓመቱ ወህኒ ወርዷል፡፡ [1] በተመሳሳይ መንገድ  በፈረንሳይም ከሰባት ዓመታ በፊት 130 ሰዎችን በመግደል የተሳተፈ ሰው በአገሪቱ ሕግ የመጨራሻ ቅጣት የሆነው እድሜ ልክ እስራት ተፈርዶበታል፡፡ [2]

በእኛ አገር ግን ለሰላሳ ዓመታት በተደጋጋሚ በተፈጠመው የዘር ማጥፋት ወንጅል አንድም ሰው ለፍርድ ቀርቦ እንደማያውቅ እኛ ችላ ብንለው እግዚአብሔርና ታሪክ መዝግበውታል፡፡ እንዲያውም በዘር ማጥፋት ወንጀል የተሳተፉት ጭራቆች በአገር ቤትና በዓለም አቀፍ ድርጅቶች ኢትዮጵያን እየወከሉ ተከፍተኛ ስልጣን ተቀምጠው ሲንፈላሰሱና አለማቸውን ሲቀጩ ይታያል፡፡ ይህ የምድር ግፍ የከበደው የሰማእታት አጥንት “የፍትህ ያለህ!!” እያለ ተመቃብር ይጮኻል! እኛም ይኸንን ጩኸት እየሰማን “ጆሯችን ጥጥ!” እያልን ከርሳችንን እየሞላን እድሜ መቁጠሩን ብልጠት አድርገን ወስደነዋል፡፡

ሌላው ቀርቶ ትናንት ከመስጊዳቸውና ተቤተክርስቲያናቸው የታረዱትንና አይናቸው ያልፈረጠውን ወደ 1600 የሚጠጉ አማራዎችንም ልንዘነጋና እንደ ልማዳችን እሬሳቸውን እየረገጥን ተገዳዮቻቸው ጋር ልንጨፍር ዳር ዳር እያልን ይመስላል፡፡ በአማራ የዘር ፍጅት ችሎት መቅረብ ያለባቸው ገዳይና አስገዳዮችም አንዴ ችግኝ ተከላ፣ ቆይተው የእርቅ ድርድር፣ ሌላ ጊዜም ዓባይ ግድብ እያሉ በተደለመደው ተዶሮ አፍንጫ በማታልፈው ቁማራቸው ያንዘላዝሉናል፡፡

የታረዱት ህፃናት በእናቶቻቸው የሬሳ ክምር ተቀምጠው እያየና እየሰማ ጪጭ ያለ ምሁርም የዓባይ ግድብ፣ የገዳዮችና የቀጣፊዎች እርቅ ሲነሳ ፀሐፊ፣ ተንታኝ፣ በላሙያ፣ ሽማግሌ፣ የሃይማኖት አባት፣ አገር ወዳድና አዋቂ መስሎ ጣቱን እያፍተለተለ ያለምን ሐፍረት ብቅ ይላል፡፡

ይኸንን እየተለመደ የመጣ የሆዳምነት፣ የአድርባይነትና የኢሰብአዊነት ባህሪያችንን ሳስብ ጠቦት ተመካከላቸው ተስቦ ሲታረድ ወይም ግልገል በቀበሮ ሲነጠቅ “ብ ኣ ኣ!” እያሉ ለቀናት የሚያለቅሱት በጎች በአዛኝነታቸውና በበጋዊ የሞራል ብቃታቸው ያስቀኑኛል፡፡

የበጎች መልካም ባህሪ በቅዱሳን መጻሕፍት ተደጋግሞ የተጠቀሰውን ያህል የእንሰሳትን ባህሪ የሚያጠኑ ተመራማሪዎችም አጥንተውታል፡፡ [3-5] በጎች እጅግ የጠነከረ ማህበራዊ ትስስር ያላቸው እንሰሳት ስለሆኑ ተበግ መንጋዎች አንዱ ሲነጠል እጅግ የበረታ ጭንቀት ውስጥ እንደሚገቡ፣ የጭንቀት ፈሳሾች (ሆርሞኖች) በደማቸው እንደሚጨምሩና እንደሚናወጡ በዚህም የተነሳ በጎች በሐዘን ምክንያት የጭንቀት በሽታ እንደሚይዛቸው ተረጋግጧል፡፡

ይህ አድግ የሚባለው እርኩስ አገራችንንና ማህበራዊ ትስስራችንን ባረደበት የቋንቋ ቢለዋ ተቅደም አያቶቻችን የወረስነውን አዛኝ ልባችንና አንጀታችንንም ከታትፎታል፡፡ ይህ አድግ የሚባለው እርኩስ መንፈስ ሳይመጣ እንኳን ሕዝብ ይኸንን ያህል ሲታረድ ወረርሽኝ ከብቶችን ሲገድል ማህበረሰብ ተሰብስቦ ለወራት ያዝን፣ ይጸልይና መፍትሄ ለመፈለግም እንደ ተርብ ይራወጥ ነበር፡፡

በሰፈር ሰው ሲሞት የሥጋ ዝምድና ኖረም አልኖረም ሰርግና ሌላ ሌላም ፌስታ ለዓመት ያህል ይራዘም ነበር፡፡ ባሏ የሞተባት ሴት በቃኝ ብላ ገዳም ትገባ ወይም ሳታገባ ቢያንስ 7 ዓመታት ትቀመጥ ነበር፡፡ ሚስቱ የሞተችበት ባልም እንደዚሁ ያደርግ ነበር፡፡ ዘመድ ሲሞት ከአርባ ከሃምሳ ዓመት በፊት የሞተው ሰው ስም አዲስ ከሞተው ሰው ስም ጋር እየተነሳ የበፊቱ ትውልድ ከአሀኑ የአሁንም ከበፊቱ ያለው ትስስር በሐዘን ወቅትም ይገለጥ ነበር፡

እንደ ሳጥናኤል ደም መጠጣትና አገር እንደ ጨርቅ መቆራረጥ የሚያረካው ይህ አድግ በውጭ ኃይላት ከተጫነብን ወዲህ ግን ልባችንና አንጀታችን እንደ ይህ አድግ ሰዎች አሪዎስ ሆኖ በስድስት ጥይት የተመታውን የስድስት ቀን ህፃንና ከታረደች እናቷ እሬሳ ተደፍታ ስታለቅስ የተገኝችውን የ15 ቀናት ሕፃንም ልንዘነጋ ዳር ዳር ብለናል፡፡

እስከ 1600 የሚደርሱ አማራዎች ታርደው እሬሳቸው ተምድር ተሰጥቶ ደማቸው እየተንደቀደቀ ገዥዎቹ በንቀት ችግኝ እየተከሉ ፎቶግራፍ ሲነሱ አንዳንዶቻችን “በልማታዊነታቸው” እያመሰገን በታረዱት ሰዎች አስከሬን ሌላ ጦር ስንሰድ አብዛኞቻችን ግን ያላዬ ያልሰማ መስለን አፋችንን ተሞሰብ እንጀራ ተክለን የቅንቡርስ ኑሮ መኖሩን ቀጥለናል፡፡

ልብ እንበል! እኛ ሰው ነን ባዮች የታረደ በሬ ፈርስ ሲሸተው የራሱ ወገን መሆኑን አይቶ በሐዘን ተሚቅበዘበዘውና “ቡ ኣ ኣ!’ እያለ ሐዘኑን ተሚገልጠው ከበት፣ ጠቦት ለእርድ ሲጎተት ወይም ግልገል በቀበሮ ሲነጠቅ ሳምንት ሙሉ “ብ ኣ ኣ” እያለ ተሚያዝን የበግ መንጋ አንሰናል፡፡ ጎበዝ! ቤታችሁን ዘግታችሁ ሁኔታችንን በጥሩ ህሊና ብታጤኑት ተሰውነት ብቻ ሳይሆን ተእንሰሳም ዓለም ወጥተናል፣ የሰው ብቻ ሳይሆን የእንሰሳ ባህሪም ተአካላችን ወጥቷል፡፡ በዚህም ምክንያት፦

  1. በወልቃይትናባዶ ስድስት ለአርባ አምስት ዓመታት የተፈፀመውን የዘር ፍጅት አንድም ወንጀለኛ ፍርድ ሳይቀርብ ችላ ብለነዋል፡፡
  2. በራያም በተመሳሳይ ዘመን የተፈፀመውን የዘር ፍጅት አንድም ወንጀለኛ ፍርድ ሳይቀርብ እረስተነዋል፡፡
  3. ጎንደር በአደባባይ እየሱስ የተደረገውን ጪፍጨፋ አንድ ሰው ተችሎት ሳይቀርብ ጭራሽ ዘንግተነዋል፡፡
  4. በደኖ ከእነነፍሳቸው ገደል የተወረወሩትን ሰማእታት አንድ ሰው ለፍርድ ሳይቀርብ በወሬ ብቻ አልፈነዋል፡፡
  5. አርባ ጉጉና አርሲ ነገሌ የታረዱትን አማራዎችና በዚህም ምክንያት አማራን ለማደራጀት ሲጥሩ በወህኒ ማቀውና ሕክምና ተከልክለው ያለፉትን ክቡር ፕሮፌሰር አስራትንና ታፍነው የደረሱበት ያልታወቁት አራት ወንድማማቾችን፣ ተሾመ ቢምረውንና ሌሎችንም ጓዶቻቸውን አንድም ሰው በሕግ ሳይጠየቅ እረስተናቸዋል፡፡
  6. በጋንቤላ ርስታቸውን ለመንጠቅ ሲባል የተጨፈጨፉትን በብዙ መቶዎች የሚቆጠሩ አኝዋኮች አንድም ሰው ክስ ሳይመሰረትበት ዘንግተናቸዋል፡፡
  7. የምርጫ ስርቆትን ሲቃወሙ አዲስ አበባ ላይ የተረሸኑትን ሰማእቶችን ረስተናቸዋል፡፡
  8. ተጉራ ፈረዳ በወረንጦ ተነቅለው እንደ ዘጽአት ሰዎች ጓዛቸውን በራሳቸው ልጆቻቸን በጀርባቸው አዝለው በእግራቸው እየኳተኑ እዲባረሩ የተደረጉ አማራዎችን የአባረራቸው ጭራዎች አሁንም ተስልጣን ተጎልተው ጭጭ ብለናል፡፡
  9. የትግሬ ነፃ አውጪና ሻቢያ በኢትዮጵያ ንብረት ተጣልተው በድንበር አሳባው  በከፈቱትን ጦርነት 70 ሺህ ዜጎችን አስጨርግደው አንድም ባለስልጣን ተጠያቂ ሳይሆን የ70 ሺህ ሰራዊት ደም እርም ውጠን ዝም ብለናል፡፡
  10. በመተከል በጅምላ በጅምላ እየታረዱና አይናቸው ተቆፍሮ እየወጣ ተከብት አስከሬን በከፋ ሁኔታ በግኒደር እየታፈሱ ጉድጓድ ውስጥ የገቡትን አማራዎች አንድም ሰው ወህኒ ሳይገባ ትተነዋል፡፡
  11. ግፍን ሲቃወሙ በባህርዳር፣ በጎንደር፣ በደብርታቦር፣ በዳንግላ፣ በምባ ጊዮርጊስ፣ በቡሬ፣ በደብረ ማርቆስ፣ በወልድያ፣ በማጀቴና ሌሎችም ስፍራዎች ያለቁትን እንደ አበበና ዮሴፍ ያሉ ወጣቶች አንድም ገዳይ ለፍርድ ሳይቀርብ እርማቸውን በልተን ጪጭ ብለናል፡፡
  12. በወለጋ በልጃቸው እሬሳ ላይ እንዲቀመጡ የተደረጉትን እናት ጉዳይ ዜና ብቻ አርገን ትተነዋል፡፡
  13. በአምቦ በተላያዬ ጊዜ የተጨፈጨፉትን ወጣቶች አንድም ሰው ለፍርድ ሳይቀርብ ዘንግተነዋል፡፡
  14. በሻሸመኔ፣ በዝዋይና በአዳሚ ቱሉ ዘሩ እየተለየ ያለቀውን የአማራና የጉራጌ ዘር ፍጅትና የንብረት መውደም አንድም ሰው ተችሎት ሳይቀርብ የአንድ ሰሞን ወሬ አድርገን አልፈነዋል፡፡
  15. በጭራቆች ተጠልፈው የደረሱበት እስካሁን ያልታወቁትን የዩንቨርስቲ ተማሪዎች የአንድ ሰሞን ወሬ አድርገን ትተነዋል፡፡
  16. የትግሬ ነፃ አውጪና ይህ አድግ ቁጥር ሁለት በስልጣን ተጣልተው በፈጠሩት አታካራ በተኛበት ያለቀውን ሰራዊት ሳንቆጥር፣ ሕዝብና ስልታዊ ማፈግፈግ በሚል ቁማር በአፋር፣ በወሎ፣ በጎንደርና በሸዋ የጠፋውን ህልቆ መሳፍርት የሌለው ሕይወትና ሐብት አንድም ባለስልጣን ተጠያቂ ሳይሆን አልፈነዋል፡፡
  17. ያለ ሐጥያታቸው በወህኒ የሚማቅቁ በመቶ ሺሆች የሚደርሱ እስረኞችን ዘንግተናል፡፡
  18. በቅርቡ በጋምቤላ የታረዱትን ማንሳት አቁመናል፡፡
  19. አሁንምወለጋ በጭራቆች ያለቁትን ሴቶች፣ ሕፃናት፣ እናቶች፣ አዛውንቶችና ጎልማሶች አንድም አካል ተጠያቂ ሳይሆን ልንረሳ ጫፍ ላይ ደርሰናል፡፡

የደረስውን ግፍ ዘርዝሮ ከመጨረስ ስንክሳር ወይም ኢሳይክሎፒዲያ መጽሐፍ ይቀላል፡፡

ይኸንን ሁሉ ፍትህ ያለገኘ ግፍ ተሸክመን ትንኝም የሞተብን ሳይመስለን እንደ ቅንቡር ስንበላ ኖረን መቃብር የመግባት ዘዴን ጥበብ አድርገን መያዛችን እንኳን ለፈጣሪ ህሊና ላለው ሰውም ይገርማል፡፡ ማሰብ አይችልም የሚባለው በግ እንኳን ሌላ በግ ተጎኑ ሲጎድል ለቀናት ምርር ብሎ ያለቅሳል፡፡ የሐዘን ሆርሞኑ ይጨምራል፣ ይጨነቃል፣ ይጠበባል፣ ሳሩ አልበላለት ይላል፡፡ እኛ ግን የሰውን ባህሪ ባቻ ሳይሆን ተበግ የምንጋራውንም የእሰሳነት እዝነ ልቡና ፍቀን ተሰው አራጆች ጋር አስረሽ ምቺውን ስንጨፍር፣ ለእኛና ላገራቸው ሲሉ የተሰውትን እረስተን እየጎሰጎስን ስንኖር ሞት ነገ ተእኛ የሚደርስ አልመስለን ብሏል፡፡

ተመኖሪያቸው፣ ተቤተክርስትያንና ተመስጊድ የታረዱትን፣ ስድስት ባሩድ የጨረገደውን የስድስት ቀናት ሕፃንና፣ ከሬሳ ክምር የተለቀሙትን ጨቅላዎች ሰቆቃ ችላ ብለን ለፍትህ ሳንጮህና ፍትህን ሳንተገብር ስንተኛ መኝታው አልቆረቁረን ብሏል፡፡ ተገዳይ አስገዳዮቻቸው ጋር ስንሞዳሞድም የህሊና ልጓም ትንሽም አልስበን ብሏል፡፡

ሕዝብ ሆይ! ንስሐ ልንገባና እንደገና የሰው ባህሪ ልንለብስ ይገባል፡፡ ዶሮ ጫጩቶቿን ተጪልፊት ስትጠብቅ፣ በግ ግልግሎቿን ተቀበሮ ለማዳን የሚቻለውን ስታደርግ፣ እኛ የስድስት ቀን ህፃን በባሩድ ተሚደበድብ ጭራቅ ለማዳን ለምን አቃተን ብለን መጠየቅ ይኖርብናል፡፡ ህፃናትን ከታረዱ እናቶቻቸው አስከሬን ውስጥ እንደ ድንች ፈንቅለን ማውጣት ሰልችቶን “ግፍ በቃን” ብለን በአንድነት ለመነሳት ለምን ዘገየን ብለን ራሳችንን ማፋጠጥ ይኖርብናል!

ሕዝብ ሆይ! ይኸንን ለጀሮ የሚዘገንን፣ እግዚአብሔርን የሚያስቆጣ፣ በታሪክና በትውልድ ሲያስረግም የሚኖር ዘግናኝ ግፍ የፈጠሙ ጭራቆች እንደ ሂትለር ምስለኔዎች በህይወት ያሉት በአካል፤ በህይወት የሌሎትም በስማቸው ክስ ተመስርቶ ለችሎት የማቅረብ ግዴታ በዚህ እስካሁን እርም በበላ ትውልድ ተጥሏል፡፡

ሕዝብ ሆይ! ሰው ሆነን በሰውነታችን ለመኖርና በታሪክም እንደ አምስቱ ዘመን ባንዳዎች ስንረገም እንዳንኖር፣ እግዚአብሔርም እንዳይከፋው፣ ለመጪው ተራፊ ትውልድም የፍትህ ፍለጋ የቤት ሥራ ሰጥተን ላለማለፍ የትውልድ አደራችንና ድርሻችንን ተወጥተን ለማለፍ ቢያንስ የሚከተሉትን ማድረግ ይኖርብናል፡፡

  1. እንደ ሰው ኖሮ እንደ ሰው ለማለፍ ፍትህ በመጠየቁና የዘር ማጥፋት በማስቆም ዘመቻ እያንዳንዱ ዜጋ መሳተፍ ይኖርበታል፡፡ በግ እንኳ ከአጠገቡ ለተነጠቀው በግ ይጮኻል፡፡ ታለገመና ሆዳም ወይም አድር ባይ ታልሆነ በቀር እያንዳንዱ ሰው ማበርከት የሚችለው የታመቀ ኃይል እንዳለው ማወቅ ያስፈልጋል፡፡
  2. ፍትህን ለማስፈንና የሰው ልጅ እንደ ከበት ከመታረድ ለማዳን በሚደረግ ትግል ውስጥ በልሳን፣ በጎጥ፣ በሃይማኖትና በሌሎችም የጅል ዘፈኖች መጠላለፍ በአንገት ላይ ገመድ መሳብ መሆኑን በሚገባ ማጤን ያስፈልጋል፡፡
  3. የቁሳቁስና የሐሳብ እርዳታ እየተደረገላቸው በሙያቸው የተካኑ ሰዎች የሚጠርዙት ማህደር መንገንባት ያስፈልጋል፡፡ በዚህ ማህደር ውስጥ በጅምላ የተጨፈጨፉ፣ ገልደ የተወረወሩ፣ የተገደሉ፣ የደረሱበት ያልታወቁ፣ እንዲመክኑ የተደረጉ፣ የታሰሩ፣ የተገረፉ፣ የተሰደዱ፣ ከሥራ የተባረሩና ሌላም ሌላም ወንጀል የተፈጠመባቸው ዜጎች ዝርዝር በፆታ፣ በእድሜ፣ በሙያ፣ በቦታ ተመዝግቦ ይቀመጣል፡፡
  4. እልቂትን፣ ሰቆቃንና ግፍን ለሕዝብና ለዓለም የሚያሳውቁ ሬዲዮኖች፣ ቴሌቪዥን፣ ዌብ ሳይት፣ ዩ ቱብ ቻናልና ሌላም ሌላም የህዝብ መገናኛ መንገዶችን በጥኑ መሰረት ላይ መጣል ያስፈልጋል፡፡
  5. እንደዚህ አይነቱ ዘግናኝ ወንጀል እንዳይደገም ለማድረግ በበሰሉ ባለሙያዎች የተሞላ የወንጀል መርማሪና ችሎት አቅራቢ አካል በዓለት ላይ መመስረት ያስፈልጋል፡፡
  6. በሙያቸው የተካኑ ሰዎች የሚመሩት ጠንካራ የዲፕሎማሲ ተቋም መመስረት በጣም ያስፈልጋል፡፡
  7. ሕዝብ ጨፍጭፈው ወይም አስጨፍጭፈው፣ አገር ዘርፈውና አዘርፈው በውጪ ተንደላቀው የሚኖሩ አረመኔዎችን በውጪ ፍርድ ቤቶች የሚገትር ተቋም ያስፈልጋል፡፡
  8. በሕዝብ ስም ገነዘብ ሰብስበው ለተሰበሰበለት አላማ ሳያውሉ እንደ ጭልፊት ሞጭልፈው የሚሄዱ ወሮ በሎችን የሚቆጣጠር አካል መፍጠር ያስፈልጋል፡፡
  9. ለአገራቸውና ለሕዝባቸው ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያደርጉትን ጀግኖችት በአንድ በኩል አገራችውን ያወረዱና ሕዝባቸውን ያስፈጁትን ባንዶች በሌላ በኩል ለታሪክ የሚያስቀምጥ ማህደር መገንባት ያስፈልጋል፡፡
  10. በአገር ቤት ለህልውና፣ ለነፃነት፣ ለፍትህና ለአገር ልእዋላዊነት የሚታገሉትን ጀግኖች በቁሳቁስ፣ በሐሳብና በመረጃ የሚያጠናክር ዘላለማዊ ተቋም መገንባት እጅግ በጣም ያስፈልጋል፡፡

ሰውነት ተወልዶ፣ በአካል ማደግ፣ መማር፣ መስራት፣ ገንዘብ ማፍራት፣ መብላት፣ መጠጣትና እድሜን ቆጥሮ ወይም በበሽታ መሞት አይደለም፡፡ ሰውነት ሰው የሆነ ሁሉ የሚለብሰው ቆዳና መንፈስ ነው፡፡ ሰው ተሆን ይህ ቆዳ ሲታረድና ይህ መንፈስ ሲሰቃይ ህመሙ እኩል ሊሰማን ይገባል፡፡

አመሰግናለሁ፡፡

End notes:

1. The New York Times: 101-Year-Old Ex-Guard at Nazi Camp Is Convicted by German Court

https://www.nytimes.com/2022/06/28/world/europe/ex-nazi-guard-convicted-germany.html

  1. TheWall Street Journal: Key Participant in 2015 Paris Terror Attacks Sentenced to Life in Prison, the Harshest Punishment Under French Law https://www.wsj.com/amp/articles/key-participant-in-2015-paris-attacks-convicted-to-life-in-prison-the-harshest-punishment-under-french-law-11656529648
  2. How sheep are like people:
    https://asheeplikefaith.com/2015/03/03/how-sheep-are-like-people-sheep-form-strong-emotional-bonds/
  3. Animals and Grief: https://www.bedlamfarm.com/2014/03/03/kims-lamb-animals-and-grief/
  4. The Truth about Animal Grief: https://www.bbcearth.com/news/the-truth-about-animal-grief

 

ሰኔ ሁለት ሺ አስራ አራት ዓ. .

 

 

 

Leave a Reply

Your email address will not be published.

abiymania 1
Previous Story

አብይ አህመድ በሰይጣን መንፈስ እተመራ አገር መምራት አልቻለም፣ መሄድ አለበት – ግርማ ካሳ

289856109 339987638324698 4353024072721203821 n
Next Story

አምባሳደር ኢንጂነር ስለሺ በቀለ የሹመት ደብዳቤያቸውን ለፕሬዚዳንት ጆ ባይደን አቀረቡ

Go toTop