‹‹በትምህርት ሥርዓት ላይ መቀለድ በትውልድ ላይ መቀለድ ነው የሚል ስምምነት ያሰፈነ መፍትሔ ያስፈልገናል›› ብርሃኑ ነጋ (ፕሮፌሰር)

ዮናስ አማረ

በፖለቲካው መስክ ባተረፉት ስምና ዝና ቢታወቁም እሳቸው ግን በአገር ቤትም በውጭም ለረዥም ጊዜ የሠሩበትን የመምህርነት ሙያ ከሁሉም እንደሚያስበልጡ ይናገራሉ፡፡ በኢኮኖሚክስ ሙያ እስከ ፕሮፌሰርነት በትምህርት ገፍተዋል፡፡ ከእሳቸው ጋር ለቃለ መጠይቅ ተቃጥሮ በደንብ ስለሚያውቁትና ስለኖሩበት የፖለቲካም ሆነ የምጣኔ ሀብት ጉዳይ አለመነጋገር ቢከብድም፣ ሁለቱም ለሌላ ጊዜ በቀጠሮ ይቆዩና በትምህርት ላይ እንነጋገር ባሉት መሠረት በሚኒስትርነት እየመሩት ያሉትን የትምህርት መስክ የተመለከተ ቆይታ ተደርጓል፡፡ አንጋፋው የፖለቲካና የኢኮኖሚ ምሁር፣ እንዲሁም መጠራት በሚፈልጉበት መምህር ብርሃኑ ነጋ (ፕሮፌሰር) አጋጣሚው በዓል ስለሆነ ስለሕይወትና ስለትምህርት ተሞክሯቸው ከዮናስ አማረ ጋር ያደረጉት ቆይታ እንደሚከተለው ቀርቧል፡፡

ሪፖርተር፡- በቅድሚያ እናመሠግናለን፡፡ ለትንሳዔ በዓል እንኳን አደረሰዎት እያልን፣ የበዓል መልካም ምኞት እንዲያስተላልፉ ዕድል በመስጠት ውይይታችንን እንጀምር?

ፕሮፌሰር ብርሃኑ፡- እናንተንም እንኳን አደረሳችሁ፡፡ ለመላው የክርስትና እምነት ተከታዮች ለፋሲካ በዓል እንኳን አደረሳችሁ ማለት እወዳለሁ፡፡ ኢድም እየደረሰ ነውና በበዓሉ ወቅት ዕድል እንደማገኝ ብገምትም ከወዲሁ ግን መልካም የረመዳን ፆም፣ መልካም የኢድ በዓል እንዲሆን ከወዲሁ እመኛለሁ፡፡

ሪፖርተር፡- በዓላት ሲደርሱ ያለዎት ስሜት ምንድነው? በቤተሰብ ደረጃ፣ በሠፈርም ሆነ በወዳጆችና በሥራ ባልደረቦች አካባቢ ሰብሰብ ብሎ በዓልን ማክበሩና ማኅበራዊ ቅርርቡ አሁንም አለ ወይ?

ፕሮፌሰር ብርሃኑ፡- በቤተሰብ ደረጃ ሠፈር ሆነናል ማለት እችላለሁ፡፡ ልጆች፣ የልጅ ልጆችና ዘመድ አዝማዱን ስትጨማምር እንኳን በበዓሉ በማንኛውም የአዘቦት ዕረፍት ቀን ያለው መሰባሰባችን ከ20 እስከ 30 ሰዎች ልንካፈልበት እንችላለን፡፡ እዚህ ከተማ ውስጥ እስካለሁ ዓመት በዓልን ሁል ጊዜም ከቤተሰብ ጋር ነው የማከብረው፡፡ አብዛኞቹን እሑዶችም ከቤተሰብ ጋር ነኝ፡፡ እንዲህ ያሉ ቀናት ወዲህ ወዲያ የማይባሉ የቤተሰብ ናቸው ለእኔ፡፡ ስላለፈው፣ ስለወደፊቱና ስላለው ነገር ስትጫወትና ስታወራ ታሳልፋለህ፡፡ በዓል በአዘቦት ቀን የማታደርገውን እንድታደርግ ዕድል ይሰጥሃል፡፡ ለብዙ ጊዜ ያላየሃቸውንና የናፈቅካቸውን ዘመዶች ታገኛለህ፡፡ ከሁሉም ጋር ታወራለህ፡፡ ይህ ሁሉ ነው ለእኔ በዓላትን የተለየ አጋጣሚዎች የሚያደርጋቸው፡፡

ሪፖርተር፡- በበዓላት ቀናት የፖለቲካ ወይ የኢኮኖሚ ጉዳይ ላይ ያተኮሩ ወሬዎች አይኖሩም ማለት ነው?

ፕሮፌሰር ብርሃኑ፡- አዎን፡፡ ፖለቲካ በዚያን ቀን አይኖርም፡፡

ሪፖርተር፡- ከዚህ ውጪ በፋሲካ የሚታወስ፣ በዓሉን በተለየ ሁኔታ የሚያስታውሱበት ገጠመኝ ይኖርዎት ይሆን?

ፕሮፌሰር ብርሃኑ፡- የተለየ ገጠመኝ የለኝም፡፡ ሁሉም ፋሲካዎች፣ መስቀሎች፣ ገናዎችም ሆኑ በጥቅሉ በዓላት አዋዋላቸው ለእኔ ተመሳሳይ ናቸው፡፡ በዕለቱ የምትበላው የምግብ ዓይነት ካልሆነ በስተቀር፣ በእኛ ቤት አዋዋሉ የተለመደ የመሰባሰብና አብሮ የመዋል ይዘት ያለው ነው፡፡ ልጆችም ሆነን ሆነ አሁንም ይኼው ነው አከባበራችን፡፡

ሪፖርተር፡- በተለየ ሁኔታ የሚናፍቁት በዓልስ?

ፕሮፌሰር ብርሃኑ፡- በልጅነቴ ፋሲካ በጣም የሚናፍቀኝ ነበር፡፡ የተለየ ሃይማኖት አጥባቂ ሰው ሆኜ ሳይሆን፣ ምሽት ቤተ ክርስቲያን ሄዶ ማስቀደሱና መሰባሰቡን እወደዋለሁ፡፡ ጥምቀትን የመሳሰሉ በዓላት ውጪ ወጥቶ ከጓደኞች ጋር መጫወቱና ማክበሩ የሚወደድ ለዛ ያለው ነው፡፡ ስለዚህ ፋሲካና ጥምቀትን ባላቸው ለየት ያለ አከባበር በጉጉት እጠብቃቸው ነበር፡፡ በተለይ ፋሲካ ለረዥም ጊዜ ተፁሞ መምጣቱን ለየት ያሉ አመጋገቦችም ያሉት በመሆኑ የምወደው ነው፡፡ አንዱን ምረጥ የምባል ከሆነ በልጅነቴ ፋሲካን በተለየ ሁኔታ በአከባበሩ የምወደውና የምናፍቀው በዓል ነበር እላለሁ፡፡

ሪፖርተር፡- ዳግም የመኖር ዕድል ከሚሰጥዎት ወይስ ከጭቆናና በደል ነፃ ወጥተዋል ቢባሉ ከሁለቱ የትኛውን ያስቀድማሉ?

ፕሮፌሰር ብርሃኑ፡- ያለ ነፃነት መኖር፣ መኖር ማለት ነው ወይ ብዬ ነው የጥያቄውን ይዘት የምወስደው፡፡ መኖር ማለት ለእኔ ዝም ብሎ ጊዜ መቁጠር አይደለም፡፡ መኖር ማለት ምን ዓይነት ኑሮ ትኖራለህ የሚል መሠረታዊ ጥያቄ ያለው ነው ለእኔ፡፡ የሰውን ልጅ ሰው ከሚያደርጉት ነገሮች አንዱ ነፃነቱ፣ ማሰቡ፣ ማሰላሰሉ፣ ለማወቅ ጥረት ማድረጉና ያወቀውን በተግባር ለመተርጎም መሞከሩ ሁሉ ናቸው፡፡ እነኚህ ነገሮች በሌሉበት እኮ ኑሮ የቁጥር ጉዳይ ነው የሚሆነው፡፡ ነፃነት ከሌለህ በነፃነት መኖር ካልቻልክ መኖር የቁጥር ጉዳይ ስለሚሆን ይህ ብዙም አይስበኝም፡፡ ከኖርክ በተቻለ መጠን ትርጉም ያለው ኑሮ ነው መኖር ያለብህ፡፡ ባሪያ ለመሆን ከሞት ተነሳና ወይም መልሰህ ተወልደህ መቶ ዓመት ኑር ብትለኝ እኔ ይኼ ለምን እንደሚመረጥ ጨርሶ አይገባኝም፡፡

ሪፖርተር፡- ስለዚህ ምርጫዎ የትኛው ነው የሚሆነው?

ፕሮፌሰር ብርሃኑ፡- ባሪያ ሆኜ ለዘለዓለም ከምኖር እኔ ባልኖር ይሻለኛል የሚል ነው ምርጫዬ፡፡ ምንድነው የመኖር ትርጉሙ?

ሪፖርተር፡- ነፃነትን ነው ትልቅ ቦታ የሚሰጡት ማለት ነው? ለምን?

ፕሮፌሰር ብርሃኑ፡- ነፃነት በጣም ጠቃሚው ጉዳይ ነው፡፡ ሕይወትን በሀብት በረከት የተሞላ የሚያደርገው ገንዘብ አይደለም፣ ብዙ ነገሮች አሉ፡፡ ማወቅ አንዱ ትልቅ ጉዳይ ነው፡፡ ስለዚህች በጣም የምትገርም ውስብስብ ዓለም በየጊዜው የምናውቀውና የምንረዳው አዳዲስ ነገር ብዙ አለ፡፡ የሰው ልጅ ራሱ ከየት መጣ? እንዴት መጣ? ወደ የት እየሄደ ነው? ወደ ጥሩ መንገድ እየሄደ ነው? ወይስ የራሱን እግር እየሰበረ ነው? የሚሉ ጥያቄዎችን ማወቅ ቀላል አይደለም፡፡ የሰው ልጅ ምንም ነገር ለማድረግ የሚያነሳሳው ምክንያት ምንድነው? የሚለው በሙሉ የሰው ልጅን የማወቅ ፍላጎት የሚቀሰቅሱ ናቸው፡፡ ማወቅ ቀዳሚው ሲሆን፣ ካወቁ በኋላ ደግሞ የተሻለውን ወስዶ ትክክል ያልሆነውን ለማስተካከል መሞከር ደግሞ ሌላው የመኖር አካል ሲሆን ትምህርትም፣ ዕውቀትም ሆነ የመኖር ትርጉም የሚሰጥ ጉዳይ ነው፡፡ ሕይወት ማለት ለማወቅ መፈለግና ካወቅክ በኋላ የተበላሸውን ነገር በተቻለ አቅም ለመቀየር መሞከር ነው፡፡ ሕይወት ወይም መኖር ማለት ዝም ብሎ ጥሬ ሥጋ መብላት ብቻ አይደለም፡፡ ይህ ዓይነቱ ሕይወት ያን ያህል አመርቂ አይመስለኝም፡፡

ሪፖርተር፡- አሁን ወደ የሚያገለግሉበት የትምህርት ዘርፍ እናምራ፡፡ የኢትዮጵያን የትምህርት ዘርፍ መምራት ምን ዓይነት ፈተናዎች ያሉት ሥራ ነው?

ፕሮፌሰር ብርሃኑ፡- የምትመራው የትምህርት ዘርፍ በምን ሁኔታ ላይ ነው የሚገኘው የሚለው ጥያቄ በጣም ጠቃሚ ነው፡፡ በግሌ ግን ማንኛውንም የመንግሥት ሥልጣን አንድ ሰው ሲይዝ ሥልጣኑን የሚይዘው ምን ለማድረግ ነው? ሥልጣኑን የምትፈልገውስ ምን ለማድረግ ነው? የሚሉ መሠረታዊ ጥያቄዎች አስቀድሞ መመለስ አለባቸው፡፡ ሥልጣን ለእኔ በያዝክበት የሥራ ዘርፍ ኅብረተሰቡ ምንድነው ያጣው? ምን እንዲሆንለት ነው የሚፈልገው? ፍላጎቱ፣ መጉደሉና ያጣው ምንድነው? ብለህ መጠየቅና ችግር የመፍታት ዕድል የማግኘት አጋጣሚ ነው፡፡ በተሠለፍክበት ዘርፍ ያሉ ሁሉንም ችግሮችን መፍታት ባትችል እንኳን፣ የጎበጠውን ጥቂት ነገር ማቃናትም ትልቅ ነገር ነው፡፡ አንድን ኅብረተሰብ ወዴት እንደሚሄድ አቅጣጫውን ለመወሰን የትምህርት ዘርፍን ያህል አቅም ያለው እንደሌለ አምናለሁ፡፡ ኅብረተሰብ ምን ዓይነት አቅጣጫ ነው የሚከተለው? ወይም ወዴት ነው የሚሄደው? ብሎ የረዥም ጊዜ ዕቅዶችን አስቦ መሥራት የሚያስችል ትምህርት ዘርፍ ነው ብዬ አስባለሁ፡፡ በአንድ ዘርፍ ላይ ስትሰማራ ሥራውን ለመምራት የበለጠ የሚያነሳሳህ ደግሞ ዘርፉ የሚገኝበት ሁኔታ ነው፡፡ ዘርፉ ጥሩ ሁኔታ ላይ ካለ የመሪነት ሚናህ ያለውን የማስቀጠል ነው የሚሆነው፡፡ በጣም የተበላሸ ከሆነ ግን የተበላሸውን የማቃናት ኃላፊነት አንተ ላይ እንደተጫነ አስበህ፣ እሱን ለማቃናት ዕዳ መሸከምህን ተረድተህ ነው ወደ ሥራው የምትገባው፡፡

እኔ ወደ ትምህርት ሚኒስቴር ስገባ ከጎኔ ካሉ አመራሮች ጋር ሆነን ያደረግነው የመጀመርያ ሥራ፣ የኢትዮጵያ ትምህርት ያለበት ሁኔታ ምንድነው የሚለውን ጉዳይ መመዘን ነበር፡፡ በራሱ በትምህርት ሚኒስቴር የተደረጉ ጥናቶችን ጨምሮ የትምህርት ሁኔታው ምን ላይ ይገኛል? የአስተማሪዎች፣ የተማሪዎችና የትምህርት መሠረተ ልማቱ ምን ደረጃ ላይ ነው ያለው የሚለውን ገምግመናል፡፡ የትምህርት ሁኔታችን ከዚያ በመነሳት ክፉኛ እንደተጎዳና እንደወደቀ ድምዳሜ ላይ ደረስን፡፡ ይህንን የትምህርት ሁኔታ በመረዳት ዘርፉን ከወደቀበት ለማንሳት በማኔጅመንት ብቻ ሳይሆን፣ ኅብረተሰቡም ተረድቶ በጋራ መሥራት አስፈላጊ መሆኑን ተገነዘብን፡፡ ኅብረተሰቡን ካላሳተፍን በትንንሽ ለውጦች ዘርፉን መቀየር እንደማይቻል አምነንበት ነው ወደ ሥራ የገባነው፡፡

በአጋጣሚ በትምህርት ሚኒስቴር ከፍተኛ አመራር ቦታዎች ላይ ያለን ሰዎች ደግሞ በቅብብሎሽ ዕድሜ ክልል የምንገኝና የዘርፉን ችግር ተግባብቶ ለመረዳት የማንቸገር በመሆናችን አመቺ ሁኔታን ፈጥሯል፡፡ እኔ በንጉሡ ዘመን የተማርኩ ነኝ፡፡ ከአሜሪካ ቆይታዬ ተመልሼ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በማስተምርበት ወቅት አንደኛውን የሥራ ባልደረባዬና ሚኒስትር ዴኤታ አስተምሬው ነበር፡፡ ሁለተኛው ሚኒስትር ዴኤታ ደግሞ የእኔ ተማሪ የነበረው ሚኒስትር ዴኤታ ያስተምረው ነበር፡፡ ሦስታችንም ዩኒቨርሲቲ ውስጥ ስናስተምር የነበርን ነን፡፡ አንዳችን ሌላችንን አስተምረናል፡፡ ስለዚህ በትምህርት ዘርፉ ውስጥ ስላለው ችግር ለመረዳትም ሆነ ለመግባባት አልተቸገርንም፡፡ ቁጭ ብለን ምን ይደረግ ወደሚለው ወዲያው ተሸጋገርን፡፡

ተጨማሪ ያንብቡ:  በአፋር ክልል የሚገኙት መጋሌ እና አብአላ የተባሉ አካቢዎች በትግራይ ኃይሎች ቁጥጥር ሥር መግባታቸውን የክልሉ መንግሥት አስታወቀ

የትምህርት ዘርፉ እዚህ ደረጃ ላይ ያደረሰው ምንድነው፡፡ እኛ ከምናውቀውም ደረጃ እንዲወርድ የገፋው ምንድነው የሚሉ ጥያቄዎችን ፈተሽን፡፡ እኔ በ1969 ዓ.ም. አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ስገባ በወቅቱና ከዚያም በፊት የነበሩ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ምሩቃን፣ በየትኛውም ዓለም ካሉ ዩኒቨርሲቲዎች ተማሪዎች ጋር መወዳደር የሚችሉ ነበሩ፡፡ ከአብዮቱ በኋላ ብዙዎቹ ተሰደው ሲወጡ፣ በወጡበት አገር አሉ በሚባሉ ዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ ለማስተማር የበቁ ነበሩ፡፡ ጥቁር አንበሳ የተማሩ ሜዲካል ዶክተሮች አሜሪካ ሄደው ዶክተር ለመሆን ይሰጥ የነበረው ፈተና ተፈትነው ያለፉ እንጂ የወደቀ አንድም ሰው አላውቅም፡፡ እንዲህ ዓይነት ምሁራን በመቶዎች የሚቆጠሩ እንደነበሩን ነው የማወራው፡፡ እንዲህ ዓይነት ጥራት ያላቸው ምሁራንን ያፈራ ጥራት ያለው የትምህርት ተቋም እኔ በቅርበት አውቀዋለሁ፣ ያለፍኩበትም ነው፡፡ ትምህርቱ በተፈለገው ልክ ባይዳረስም፣ ነገር ግን በጥራቱ ላይ ምንም ጥያቄ የሚነሳበት አልነበረም፡፡

እኔ ካለፍኩበት በኋላ የመጣው ትውልድ ከዚያ ያነሰ ጥራት የነበረው ትምህርት ነው ያገኘው፡፡ ይህ ደግሞ የሆነው የትምህርት ጥራት መውደቅ የጀመረው በደርግ ዘመን በመሆኑ ነው፡፡ ደርግ የዩኒቨርሲቲ ቆይታን ወደ ሦስት ዓመታት አውርዶ ስለነበር፣ በጊዜው የነበሩ ምሁራን ጭምር ይተቹት ነበር፡፡ ትዝ ይለኛል ፕሮፌሰር መስፍን ወልደ ማሪያም፣ ‹‹ያፀድቅ እንደሆነ እንጂ ዲግሪ በሦስት ዓመታት መስጠት ማስተማር አይደለም፤›› ሲል ነበር የተቸው፡፡ ከዚያን ጊዜ ወዲህ እየወረደ መጥቶ አሁን ላይ በጣም የሚያስደነግጥ ደረጃ ላይ ነው የወደቀው፡፡ ለምሳሌ ከቋንቋ ጀምሮ ብታይ ትምህርት በእንግሊዝኛ ቋንቋ ነው የሚሰጠው ይባላል፡፡ ነገር ግን እንግሊዝኛ መናገርም መስማትም የማይችሉ ተማሪና አስተማሪዎች ናቸው የሞሉት፡፡ በምን እንደሚግባቡ ፈጣሪ ነው የሚያውቀው፡፡

የትምህርት ችግሩ ምን ላይ ነው የሚገኘው ብለን ትንተናውን ስንጀምር ዝም ብለን አልነበረም፣ በመረጃ የተደገፉ መመዘኛዎችን ይዘን ነው የተነሳነው፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ባሉ የመንግሥት ትምህርት ቤቶች ሦስተኛ ክፍል ደርሰው ማንበብ የማይችሉ ተማሪዎች ቁጥር ወደ 69 በመቶ ነው፡፡ በሚያስተምሩበት ትምህርት የምዘና ፈተና ወስደው 50 በመቶ በማምጣት ያለፉ መምህራን ቁጥር ከ30 በመቶ በታች ነው፡፡ የትምህርት አስተዳዳሪ የሚባሉት የትምህርት ቤት ዳይሬክተሮች ለቦታው መመጠናቸውን ለማረጋገጥ በተሰጠ ምዘና ፈተና ያለፉት 30 በመቶ ብቻ ናቸው፡፡ ከኢትዮጵያ አስተማሪዎች ውስጥ 52 በመቶዎቹ በአግባቡ ትምህርት ቤት ወይም ክፍል ተገኝተው አያስተምሩም፡፡

በዚህ ዓይነቱ አካሄድ ትምህርት ተብሎ ደግሞ ዲግሪ በየቦታው እንደ ከረሜላ ታድሏል፡፡ ይህ በጣም የሚያስገርምና አጠቃላይ የዘርፉን አስደንጋጭ ስብራት የሚያሳይ ነው፡፡ የትምህርት ተደራሽነት ማደጉን ሳንረሳ፣ ዘርፉ በእጅጉ በመጎዳቱ ላይ ግን ምንም ክርክር አይኖርም፡፡ አንድ ዩኒቨርሲቲ የነበረው አገር ወደ 47 አድጎለታል፡፡ የዩኒቨርሲቲዎች ቁጥር ማደጉ ጥሩ ነው፡፡ ነገር ግን ዩኒቨርሲቲ በሚያሰኝ ደረጃ ላይ ነው ወይ ያሉት የሚለው፣ እንዲሁም ለተማሪዎች የሚሰጡት ዲግሪ ዩኒቨርሲቲ ተምረዋል የሚያሰኝ ነው የሚለው ጥያቄ ውስጥ የሚወድቅ ነው፡፡

ሁለተኛው ለመረዳት የሞከርነው ደግሞ ምንድነው ይህን ችግር የፈጠረው የሚለውን ነው፡፡ በመሠረታዊነት ትምህርትን ማዳረስ አስፈላጊ ነው ከሚለው ቀና አመለካከት ቢነሳም፣ ነገር ግን በቂ የትምህርት መሣሪያ፣ አስተማሪና የትምህርት አሰጣጥን ሳይፈጥሩ ሕንፃ እየገነቡ ብቻ ተማሪዎችን መሰብሰብ ችግሩን እንደፈጠረው ደረስንበት፡፡ በኢትዮጵያ በየትምህርት ዕርከኑ ትምህርት ለመስጠት የሚያስችል የተሟላላቸው ተማሪ ቤቶች ጥቂት ናቸው፡፡ ትምህርት ሚኒስቴር በዚህ ረገድ ተማሪ ቤቶችን በአራት ምድቦች ከፍሎ የሚያስቀምጣቸው ሲሆን፣ አንደኛና ሁለተኛ ደረጃዎች ላይ ያሉት ትምህርት ቤት መሆን የሌለባቸው ናቸው ብሎ ይደመድማል፡፡ በሦስተኛ ደረጃ ላይ ያሉት በአንፃራዊነት ትምህርት መሠረተ ልማት የተሟላላቸው ሲሆኑ፣ አራተኛ ላይ ያሉት ናቸው የተሻለ ደረጃ ላይ ይገኛሉ ተብለው የሚቀመጡት፡፡

በአገር አቀፍ ደረጃ በተደረገው ጥናት ከ47 ሺሕ ተማሪ ቤቶች አራተኛ ደረጃ ላይ የሚገኙት ስድስት ብቻ መሆናቸው ተረጋግጧል፡፡ ይህ 0.001 በመቶ ተብሎ የሚቀመጥ ነው፡፡ ወደ 90 በመቶዎቹ ትምህርት ቤት ሊባሉ በማይችሉበት አንደኛና ሁለተኛ ደረጃ ላይ የወደቁ ናቸው፡፡ ሽንት ቤት፣ ውኃና መብራት የላቸውም፡፡ አፈር ላይ ተቀምጠው ነው የሚማሩት፡፡ እንዲሁም ሴት ተማሪዎች ለንፅህና እንኳን የሚሄዱበት ቦታ የላቸውም፡፡ ከዚህ መሰሉ ግምገማ በመነሳት ነው የትምህርት ችግራችን ወደ እዚህ ቀውስ የገባው ለምንድነው የሚለውን ለማስቀመጥ የሞከርነው፡፡ በዚህ ረገድ ደግሞ አራት ዋና ዋና ምክንያቶችን አስቀምጠናል፡፡

አንደኛው የትምህርት ማስፋፋት ስኬት የመጣው ጥራቱን በመግደል ነው የሚል መነሻ ምክንያት ነው፡፡ ማስፋፋቱ፣ ተደራሽነቱና የተማሪ ቁጥር መጨመሩ የመጣው ጥራትን በመጉዳት ነው፡፡ የተመረቀና የትምህርት ሰርተፊኬት ያለው፣ ነገር ግን ያልተማረ ብዙ ሰው እየተመረተ ነው ማለት ነው፡፡ ይህ በጣም አደገኛ ሲሆን፣ ሌላ ማኅበራዊ ችግር ይዞ የሚመጣ ነው፡፡ በተለይ እኛ በምንሠራባቸው አምስት ዓመታት ዋና ትኩረታችንን ጥራት ላይ በማድረግ ያሉትን ማብቃት ላይ እንሥራ ወደሚል ድምዳሜ ነው የገባነው፡፡

ሁለተኛው ችግር ብለን የለየነው ጉዳይ ደግሞ የትምህርትና የፖለቲካ መጋባት የፈጠረውን ቀውስ ነው፡፡ አንድ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ መምህራንን ሰብስበን ስናወራ፣ ‹‹ፖለቲካና ትምህርት ዝም ብሎ መጋባት ሳይሆን፣ በተክሊል ነው የተጋቡት፤›› ሲል ነበር አንድ መምህር የችግሩን መልክ የገለጸው፡፡ በትምህርት ዘርፍ ውስጥ ፖለቲካ በሁሉም ጉዳይ በመግባቱ ሰፊና ውስብስብ ችግር የፈጠረ ሆኗል፡፡ ከዳይሬክተሮች ምደባ ጀምሮ በፖለቲካ ታማኝነት ሲሆን፣ የዳይሬክተሮች ዋና ሥራም በትምህርት ቤቶች ዙሪያ ያለውን ፖለቲካ መከታተል ነው፡፡ ይህ ባለፉት ጥቂት ዓመታት በተሞከሩ ማሻሻያዎች መቀየር እየጀመረ ነው፡፡

ዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ የፕሬዚዳንቶች ምደባ ፖለቲካን መሠረት ባደረገ ምዘና ነው፡፡ በካሪኩለም፡፡ በሁሉም ቦታ ፖለቲካ አለ፡፡ በተለይ በከፍተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ውስጥ ችግሩ ይሰፋል፡፡ ዩኒቨርሲቲዎች እውነት ፈላጊዎች፣ ኅብረተሰብን መምራት የሚችሉና ዓለም አቀፋዊ የሆነ ዕውቀት ያላቸው ሰዎች የተሰበሰቡበት ተቋም የፈለገ ፖለቲከኛ እንደፈለገ የሚያደርገው ተቋም ሲሆን ማየት፣ መሠረታዊ መናጋት በዘርፉ መፈጠሩን ያሳያል፡፡ በደርግ ዘመን ጀምሮ ዘርፉን መቆጣጠር አለብን በሚል ዕሳቤ የውይይት ክበብ እየተባለ የዩኒቨርሲቲ ምሁራንን ካድሬ ነበር ላስተምር የሚለው፡፡ በጦሩ ውስጥ ትልልቅ ጄኔራሎችን አንድ የፖለቲካ ካድሬ እንደሚመራው ዓይነት የዩኒቨርሲቲ ምሁራንንም በካድሬ ለመምራት ተሞክሮ ነበር፡፡

በኢሕአዴግ ዘመንም ይኼው ዓይነት ችግር ሲፈጠር አስታውሳለሁ፡፡ ኢሕአዴጎች ወደ ሥልጣን በመጡባቸው የመጀመርያዎቹ ዓመታት አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ በታሪክ ትምህርት ዙሪያ ውይይት ይደረጋል ተብሎ ተሰበሰብን፡፡ በጊዜው ከአሜሪካ መጥቼ ነበር፡፡ ውይይቱ የሚደረገው በኢትዮጵያ ጥናትና ምርምር ተቋም ውስጥ ነበር፡፡ ታደሰ ታምራትን (ፕሮፌሰር) የመሳሰሉ ታላላቅ የታሪክ ምሁራን በተሰባሰቡበት ጉባዔ ስለታሪክ ለማስተማር ከኢሕአዴግ የመጡት በረከት ስምዖንና ተፈራ ዋልዋ ነበሩ፡፡ ይህ እጅግ ኮሚክ የሆነ ገጠመኝ ነበር፡፡ እነዚህ ሰዎች ዩኒቨርሲቲ ስላልገቡ አያውቁም፣ ወይም አላነበቡም አይደለም የምለው፡፡ ነገር ግን ድፍረቱ ያስገርማል፡፡ ነገር ግን ፖለቲካ ትምህርት ውስጥ ገብቶ ዕውቀትም ሆነ አዋቂነትም የእኔው ነው ማለት ሲጀመር መሠረታዊ መናጋት ነው የሚፈጥረው፡፡

ስለዚህ ፖለቲካና ትምህርትን መነጠል አስፈላጊ መሆኑን አስቀምጠናል፡፡ ፖለቲካን በየቀበሌውና በሌሎች መንገዶች ማንም ሰው ያድርግ፡፡ ዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ ፖለቲካዊ ውይይት ከተደረገ ግን የካድሬ መፈንጫ ሳይሆን፣ ቢያንስ በዕውቀት ላይ የተመሠረተ ቢሆን ነው የሚሻለው፡፡ ይህ ስለብልፅግና ወይም ስለሌላ ፓርቲ ተብሎ የሚባል አይደለም፡፡ እነዚህ ቦታዎች የዕውቀት ማመንጫና የሐሳብ መፈለጊያ ቦታዎች እስከሆኑ ግን፣ ይህንኑ መሠረት አድርጎ እንጂ የእከሌ ወይ የዚያ ደጋፊ ስለሆንክ ነው በሚል በፖለቲካ የምትባላባቸው ቦታዎች አይደሉም፡፡ ተማሪዎች ወደ እነዚህ ቦታዎች የሚገቡት በዋናነት ለማወቅ ነው፣ ትምህርት ለመማር፡፡ አውቀው ዓለምን የሚያውቁበትን ዕድል መስጠት ነው፡፡ ስለሆነም የትምህርት ሥርዓቱና ፖለቲካው መነጠል አለበት፡፡

ተጨማሪ ያንብቡ:  ህወሓቶች የመቐለን ሰለማዊ ሰልፍ ለመከልከል ወስነዋል። (አብርሃ ደስታ)

ሦስተኛው መሠረታዊ ችግር ብለን የለየነው ደግሞ የትምህርትና ክልላዊነትን ነው፡፡ ብሔሮችና ብሔረሰቦች ባህላቸውን፣ ማንነታቸውን፣ ወይም ቋንቋቸውን ለማስከበር የሚያደርጉት ጥረት ችግር የለውም፡፡ የልጆቻቸውን ትምህርት የዚያ እስረኛ ካደረጉት ግን ትልቅ ችግር ነው የሚገጥማቸው፡፡ ከክልላዊነት ጋር በተያየዘ የራሳቸውን ጥቅም ለማስጠበቅ ብለው በዘርፉ ላይ መጫወት ከጀመሩ የሚጎዱት የራሳቸውን ልጆች ነው፡፡ ይን ደግሞ በብዙ መንገዶች ችግር ሲፈጥር በትምህርት ውስጥ ታየዋለህ፡፡

በቂ የትምህርት መሣሪያና ቁሳቁስ ሳይዘጋጅ በአፍ ቋንቋ ማስተማር ማለት ብዙ ክልሎችን ችግር ውስጥ ከቷል፡፡ በአፍ ቋንቋ መማር በጣም ጥሩ ነገር ነው፡፡ ነገር ግን መሆን ካለበት ግን ተዘጋጅተህና የመማሪያ መሣሪያዎችን አዘጋጅተህ፣ ተማሪዎቹ እንዲጨብጡ የምትፈልገውን ዕውቀት በቋንቋው የሚጨብጡበትን መንገድ ካልፈጠርክ ልጆቹን ይጎዳል፡፡ ‹በአፍ ቋንቋ ማስተማር ጀመርኩ› ለማለት ብቻ ሥራውን የምትሠራው ከሆነ ልጆቹ ይጎዳሉ፡፡ ስለዚህ በአፍ ቋንቋ መማር በጎ ነገር ሆኖ ሳለ፣ ቋንቋና ባህልን ዕውቀት ማግኛ ማድረግ እየተቻለ ከዕውቀት የተነጠለ ሆኖ ከቀረበ ለልጆች ጎጂ ይሆናል፡፡

በትምህርት ዘርፍ ዕውቀት መቅደም አለበት፡፡ በተለይ በዩኒቨርሲቲ ደረጃ ዓለም አቀፍ ዕውቀት ነው የሚገበየው፡፡ ዕውቀት የተለየ ብሔር፣ ቋንቋም ሆነ ማንነት የለውም፡፡ የኦሮሞ ፊዚክስ ወይም የአማራ ኬሚስትሪ ወይም የጉራጌ ባዮሎጂ የለም፡፡ የሰው ልጆች በረዥም ጊዜ ሒደት በጥረታቸው ያገኙትና በቅብብሎሽ ያካበቱት ዕውቀት በሙሉ የሁላችንም ነው፡፡ እነዚህን የመላው ሰው ልጆች ዕውቀት የምትማርበት ቦታ ላይ የእኔ ብቻ ካልቀረበልኝ የምትል ከሆነ ተማሪውንም ታደነቁረዋለህ፡፡ ጥሩውንም መጥፎውንም ምን እንደነበረ እንዲያውቁት ሁሉንም ዕውቀት ማሳወቅ ይጠበቃል፡፡ ይህ ካልሆነ ግን ተማሪዎች ችግር ይገጥማቸዋል፡፡

አሁን በዩኒቨርሲቲዎቻችን የገጠመን አንዱ ችግር ይኼ ነው፡፡ በየክልሉ ያሉ ዩኒቨርሲቲዎች የፌዴራል ተቋማት ሲሆኑ፣ ከየክልሉ ያሉ ተማሪዎች ተሰባስበው የሚማሩባቸውና ዕውቀት የሚገበይባቸው ቦታዎች መሆን ይገባቸዋል፡፡ ነገር ግን ይህን ገባ ብለህ ስታየው ግን አሁን አሁን ዩኒቨርሲቲዎቻችን ከክልልም ወርደው የዞን ንብረት የሆኑ ይመስል፣ የዞን ሰዎች እንደፈለጉ ሊያደርጓቸው የሚሞክሩ ተቋማት ሆነዋል፡፡ ተወዳድረው በችሎታ ሳይሆን የዞን ሰዎች ናቸው ፕሬዚዳንት የሚሆኑት፡፡ ዩኒቨርሲቲዎች ከክልላዊነት በታች ወርደው በአካባቢ የሚተዳደሩ ሆነዋል፡፡ የጎጃም ዩኒቨርሲቲን ለመምራት የአማራ ተወላጅ መሆን ብቻውን አይበቃም፡፡ የወለጋ ዩኒቨርሲቲን ለማስተዳደር ኦሮሞ መሆን ብቻውን መሥፈርት አይደለም፡፡ ከክልልና ከብሔርም ተወርዶ የአካባቢ ሰው ይፈለጋል፡፡ ይህ ነገር ሁሉም ሊማማርበት የሚችል ዓለም አቀፋዊ ዕውቀት መገብያ ተቋሞቻችንን እያበላሸብን ይገኛል፡፡ በክልል አስተዳደር ስም እያበላሸነው ነው፡፡ ይህንንም ማሻሻል ይኖርብናል፡፡

አራተኛው ችግራችን ደግሞ የሞራል ክስረታችን የፈጠረው ነው፡፡ በትምህርት ሥርዓቱ ውስጥ ጉዳዩ ቢሰፋም ነገር ግን የሞራል ኪሳራ አጠቃላይ በኢትዮጵያ በሁሉም ዘርፍ የሚታይ ችግር እየወለደ ነው ያለው፡፡ የራስን አካባቢ ተማሪ ወይም ሰው ለመጥቀም ሲባል ፈተና መስረቅ፣ የግል ትምህርት ቤት ባለቤት ሆነህ ለነገ ገበያ ብቻ በማሰብ ተማሪዎችን ተኮራርጀው እንዲያልፉ መፍቀድ በመሠረታዊነት የትምህርትን ተዓማኒነት እየገደለ ነው ያለው፡፡ ለውጤት ተብሎ አስተማሪና ተማሪ ጉቦ የሚሰጣጣበትና አስተማሪ ክፍል ውስጥ የማይገባበት ሁሉ የዚህ ቀውስ ማሳያ ናቸው፡፡ የኑሮ ችግር ወይም በቂ ደመወዝ ያለማግኘት ችግር ሊነሳ ይችላል፡፡ ነገር ግን የዩኒቨርሲቲ መምህራን በቂ ጊዜ ሳይሸፍኑ ሁለትና ሦስት ሳምንት ብቻ ክፍል የሚገቡበት ትምህርት አሰጣጥ የዚህ ፈተና አካል ነው፡፡ በሞጁል ትምህርት ብቻ ኖት እየሰጡ መጽሐፍ ማንበብ የቆመበት ትምህርት አሰጣጥም ሌላው የችግሩ ዓይነት ነው፡፡ የአስተማሪነት ዕድገት በችሎታ፣ በጥናትና ለተማሪዎች በምትሰጠው ጊዜ መሆኑ ቀርቶ ባለህ ዲግሪና ባስቆጠርከው ዓመት ሲሆን፣ መሠረታዊው የትምህርት ተዓማኒነት ትልቅ ጥያቄ ውስጥ ይወድቃል፡፡ እነዚህ አራት መሠረታዊ ችግሮች ተለይተው ችግሮቹን ለመፍታትም ማኅበራዊ ንቅናቄ መፍጠር እንዳለብን ተግባብተን ሰፊ ሥራ ለማከናወን ጥረት ጀምረናል፡፡ በትምህርት ላይ የማይመለከተው ስለሌለ ጨዋታው ይብቃ ብሎ ሁሉም እንዲነሳ ጥሪ እናቀርባለን፡፡

ሪፖርተር፡- የዘርፉ ችግር ከፖሊሲ ነው የሚመነጨው ይባላል፡፡ በየዘመናቱ መንግሥት በተለዋወጠ ቁጥር ፖሊሲው መቀያየሩና ወጥነት ማጣቱ ችግር መሆኑን ብዙዎች ይስማሙበታል?

ፕሮፌሰር ብርሃኑ፡- ዝርዝር ጉዳይ ከሆነው የፖሊሲ ችግር በላይ የገዘፉ አንኳር ችግሮች አሉብን፡፡ እነዚህ ችግሮች ወዴት እየወሰዱህ እንደሆነ ሳታውቅና ለመፍታትም ጥረት ሳትጀምር የፖሊሲ ጉዳይን መመለስ አትችልም፡፡ ፖሊሲ እኮ ሊቀያየር የሚችል ጉዳይ ነው፡፡ እንደተባለውም አንዱ መንግሥት ሄዶ ሌላው ሲመጣ ሊቀያየር ይችላል፡፡ አሥር ጊዜ ፖሊሲ ስትቀያይር ብትውል ግን እነዚህን መሠረታዊ ችግሮች አብረህ መቀየር ካልቻልክ የዘርፉን ችግሮች ልትፈታ አትችልም፡፡ የእነ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ መንግሥት ከመጣ ወዲህም ብዙ ጥናት ተደርጎ የትምህርት ጥራት ማሻሻያ ፍኖተ ካርታ ተዘጋጅቷል፡፡ ፖሊሲ ተዘጋጅቶም እንዲፀድቅ ወደ ሚኒስትሮች ምክር ቤት ተመርቷል፡፡ በዘርፉ የትምህርት ሕግ ባለመኖሩ የትምህርት አዋጅ የሚባል ረቂቅ አዋጅ ተዘጋጅቶ፣ በእኛ የአማካሪዎች ምክር ቤት ታይቶ ወደ ሚኒስትሮች ምክር ቤት ለመላክ ተራ እየጠበቀ ነው፡፡

ይህን ሁሉ ሕግና ፖሊሲ ብታወጣ እንኳን፣ በመሠረታዊነት የጠቀስኳቸው ችግሮች አብረው ካልተፈቱ ችግሩ አይቀረፍም፡፡ ፍፁም የሚባል ፖሊሲ እንኳ ብታወጣ ቅድም ባነሳኋቸው ድባቦች ውስጥ ልተተገብረው ከተነሳህ ችግሩን አትፈታውም፡፡ ትምህርትን ፖለቲካው ጣልቃ እየገባ ሊያበላሸው የሚችል ከሆነ፣ ፈተና የሚሰረቅ ከሆነና የትምህርት ቤቶችን ከባቢና ሁኔታ መቀየር ካልቻልክ ፖሊሲ ብቻውን መፍትሔ አይሆንም፡፡ በአሜሪካ በየአራት ዓመቱ አዲስ መንግሥት ይመጣል፡፡ ነገር ግን በፖሊሲ ደረጃ የሚቀየሩ ነገሮች ብዙም የሉም፡፡ አነስተኛ የሚባሉ አካሄዶችን ከመለወጥ በቀር የተለየ አዲስ ነገር እንሥራ አይሉም፡፡

የትምህርት ፖሊሲ ከ10 እስከ 15 ዓመታት እንዳስፈላጊነቱ እየተቀየረ የሚሄድ ሊሆን ይችላል፡፡ ለምሳሌ ላለፉት ሦስት ዓመታት ሲጠናና ሲዘጋጅ የቆየ አዲስ ካሪኩለም እያወጣን ነው ያለነው፡፡ እነዚህን መሰል ነገሮች መደረግ አለባቸው፡፡ ነገር ግን እኛ የደረስንበት ድምዳሜ ትምህርቱ ለዚህ ቀውስ የበቃበት ምክንያቶችን በመለየት ከሥር ከመሠረቱ መቀየር አስፈላጊ ነው የሚል ነው፡፡ ድሮ አራት፣ አራት፣ ሁለት የነበረውን አሁን ስድስት፣ ሁለት፣ አራት፣ ስላደረከው መሠረታዊ የትምህርቱ ችግሮች አልተፈቱም፡፡ የውድቀቱን መሠረታዊ ምንጮች ከሥር ከመሠረቱ ካላደረቅህ ችግሩ አይፈታም ተብሎ ነው የሚታመነው፡፡ በንጉሡ ዘመን የነበረው በደርግ ቢተካም፣ ተመልሶ ደግሞ የቀደመው ይተግበር ሲባል ነበር፡፡ የእነዚህ ነገሮች መቀያየር ችግሩን አልፈታውም፡፡ ከአስተማሪ ሥልጠና ጋር በተያያዘ የሚወጡ ሥልጠና፣ ማሻሻያዎችና ሌሎችም አሠራሮችን የሚቀይሩ ሥራዎች በየጊዜው እየተሻሻሉ መሄድ ይችላሉ፡፡

ሪፖርተር፡- የመምህራንና የትምህርት ቤት ዳይሬክተሮችን ሥልጠናና ምደባ በማሻሻል ብቻ እስከ 55 በመቶ የትምህርት ጥራትን ማስጠበቅ ይቻላል የሚል የሙያተኞች አስተያየት አለ፡፡ ይህን ዓይነቱን ሐሳብ ይጋሩታል?

ፕሮፌሰር ብርሃኑ፡- ምንም ጥያቄ የሌለው፣ ነገር የትምህርትን ጥራት በማስጠበቅ ረገድ የአስተማሪዎችም ሆነ የዳይሬክተሮች ሚና ወሳኝ መሆኑ ነው፡፡ እነሱ ብቻ ሳይሆኑ ለዘርፉ ችግር መቀረፍ ብዙ ግብዓቶች አሉ፡፡ አስተማሪው በካሪክለሙ መሠረት ነው የሚሠራው፡፡ ካሪኩለሙ በጥሩ ሁኔታ ካልተዘጋጀ ግን የመምህሩ መቀየር ብቻ ትርጉም ያለው ለውጥ ላይኖረው ይችላል፡፡ በትምህረት መርጃ መጻሕፍት ዝግጅት ላይ በካሪኩለሙ ላይ ተመሥረቶ ካልተከናወነ ችግሩ ይቀባበላል፡፡ በትምህርት አሰጣጥ ሥርዓት ላይ የዳይሬክተሮች በጎ ሚና ካልታከለበት፣ አስተማሪዎች ትምህርት አሰጣጣቸው ካልተሻሻለ ዘርፉ አይሻሻልም፡፡

ሌላው ቀርቶ የትምህርት ቤቱ ገጽታና የክፍሉ ድባብ ሁሉ ለተማሪዎች ትምህርት መቀበልና አለመቀበል ወሳኝ ተፅዕኖ አላቸው፡፡ አካባቢው ሁኔታ ከደሳሳ ጎጆው የተሻለ፣ የወደፊቱን ተስፋ የሚያመላክተውና መማር የሚያመጣለትን በረከት በትንሹም የሚያመላክተው ካልሆነ፣ ተማሪ ትምህርት ለመቀበል ችግር ሊሆንበት ይችላል፡፡ በልጆች የመማር ፍላጎት መጨመርና መቀነስ ላይ እነኚህ ሁሉ ተፅዕኖ ስለሚኖራቸው፣ ከትምህርት ጥራት ማስጠበቅ ጋር ቢቀርቡ አይገርምም፡፡ ነገር ግን በአንድ አመላካች ብቻ የትምህርት ጥናት 50 በመቶና ከዚያ በላይ ሊሻሻል ይችላል ብሎ መነሳት ጥናቱ የተመሠረተበትን መነሻ ካላወቅኩ መልስ መስጠት እቸገራለሁ፡፡ የትምህርት ጥራት ለመጠበቅ ግን መምህራንና ዳይሬክተሮች ብቻ ብዙ ወሳኝ ድርሻ ያላቸው ጉዳዮች መታየት አለባቸው፡፡

ተጨማሪ ያንብቡ:  የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝ "መንግስት ለኔና ለቤተሰቤ ጥበቃ ያድርግልኝ" ሲሉ ተማጸኑ

ሪፖርተር፡- የፈተና መሰረቅ ችግር በየዓመቱ የሚከሰተው ለምንድነው? መሠረታዊ ምክንያቱና ችግሩ ያደረሰው ጉዳት እንዴት ይገለጻል?

ፕሮፌሰር ብርሃኑ፡- ቅድም ካቀረብኳቸው አራት መሠረታዊ ችግሮች መካከል ሁለቱና ከዚያ በላይ ተሳስረው የፈጠሩት ቀውስ ነው፡፡ የሞራል ክስረታችን፣ ክልላዊነትም ሆነ የትምህርትና የፖለቲካ መጋባት የፈጠሩት ይመስለኛል፡፡ የፈተና መስረቅ ችግር በ2008 ዓ.ም. ይመስለኛል የተጀመረው፡፡ ወደ ስምንት ዓመታት እያስቆጠረ ይገኛል፡፡ ፈተና መስረቅ የመጣበት ምክንያት ደግሞ የፖለቲካ ዓላማ ነው፡፡ አንድን ፈተና ሰርቀህ ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ስታሠራጨው ግን የራስህን ወይም የተወሰነ ቡድንን ሳይሆን፣ እየጠቀምክ ያለኸው አጠቃላይ አገርን ለመጉዳት ብለህ ያደረግከው ነው፡፡ ፈተናውን በማውጣት ትምህርት ሥርዓቱን ተዓማኒነት ማሳጣት ወይም መንግሥትን ተቃውሞ እንዲነሳበት ለማድረግ ትሞክራለህ፡፡ ይህ ደግሞ ፖለቲካዊ ፍላጎት ያለው ነው፡፡ ፈተናው የሚሰረቀው ግን በብሔራዊ ደረጃ ብቻ ሳይሆን፣ በየአካባቢው ጭምር ነው፡፡ ወደ ክልሎች ከተላከ በኋላ በአካባቢ ባለሥልጣናት ጭምር የአካባቢውን ተማሪዎች ለማሳለፍ በሚል ፈተና እንዲሰረቅ ግፊት ይደረጋል፡፡ አንዳንድ ቦታዎች በሬ ታርዶና ድግስ ተደግሶ ጭምር ነው የፈተና ጠባቂዎችን ለመደለል ጥረት የሚደረገው፡፡ ይህ ግን ማንንም ሳይሆን የጠቀመው አጠቃላይ የፈተናን ቅቡልነት በመጉዳት የትምህርት ዘርፉን ችግርም ያባባሰ ነው፡፡ ፈተና እኮ በፖሊስና በወታደር ታጅቦ በልዩ ሁኔታ ነው የሚሠራጨው፡፡ ባለፈው ፈተና አጅበው ከሚሄዱ የፌዴራል ፖሊሶች መካከል ሦስት በታጣቂዎች ተገድለውብናል፡፡ ፈተና ማሠራጨትና ሳይሰረቅ ማስፈተን የሞት የሽረት ጉዳይ እየሆነ ነው፡፡

በዚህ የፈተና ስርቆት አካባቢያቸውን ለመጥቀም የሚያስቡ ነገሩ ትውልድን መግደል መሆኑን መረዳት አለባቸው፡፡ ለፖለቲካ ትርፍ የሚያደርገው ካለም ለጊዜው ፖለቲካዊ ትርፍ ቢያገኝበትም መልሶ ግን አገር መግደሉን መረዳት አለበት፡፡ ተቃዋሚም ሆነ ማንም በትምህርት ሥርዓት ላይ መቀለድ በትውልድ ላይ መቀለድ ነው የሚል ስምምነትን ያሰፈነ መፍትሔ ያስፈልገናል፡፡ በመንግሥት በኩል ፈተናው የማይሰረቅበትን መንገዶች መፈለግ አለበት፡፡ ተማሪዎች ተጣጥረው በሚያገኙት ዕውቀት ማለፍን እንዲያስቀድሙ ካላደረግን ስርቆቱን ማቆም አንችልም፡፡ በዚህ ላይ በሚዲያ ማስተማር እንጀምራለን፡፡ የሚያጠና፣ ታታሪና ውጤታማ ተማሪ ማለፍ አለበት፡፡ በዚህ ሒደት ያለፈ ተማሪ ነው ሥራ ላይ ውጤታማ የሚሆነውና አገር የሚጠቅመው፡፡

ትምህርት በግሉ ዘርፍ ዝም ብሎ የሚሰጥ አገልግሎት አይደለም የሚባለው፣ ለአገር ካለው አስተዋጽኦ የተነሳ ነው፡፡ አሜሪካ ለምሳሌ የግል የምትለው ዩኒቨርሲቲ በጣም ጥቂት ነው፡፡ አንድ ተማሪ ተመርቆ ሥራ በመሥራት ለግሉ ከሚያገኘው ጥቅም በላይ አገሩን ያገለግላል ተብሎ ስለሚታመን ነው ይህ የሚሆነው፡፡ በግል ከፍተኛ ትምህርት ተቋም ተማሪ በመማሩ ሊያገኝ ከሚችለው የግለሰቦች ጥቅም በላይ የአገር ጥቅም ቅድሚያ ይሰጠዋል፡፡ በብዙ አገሮች እስከ 12ኛ ክፍል ትምህርት በነፃ ይሰጥ የሚባለው፣ ዘርፉ ለአገር ባለው አስተዋጽኦ የተነሳ ነው፡፡ በዚህ የተነሳ በትምህርት ዘርፉ የሚደረግ ጨዋታ እንዲቆም ቅድሚያ ሰጥተን እየሠራን ነው፡፡ ፈተናን በዲጂታል ቴክኖሎጂ ከመፈተን ጀምሮ ብዙ አማራጮችን እያማተርን ነው፡፡ ታብሌቶችን በበቂ ሁኔታ ካላገኘን በፌዴራል ተቋማት ውስጥ በሚቀጥለው ዓመት እስከመፈተን ልንሄድ እንችላለን፡፡ ለተማሪዎች የምናስተላልፈው መልዕክት ግን በኩረጃና በስርቆት በሚገኝ ዲግሪ ስኬታማ መሆን አይቻልም የሚል ነው፡፡

ሪፖርተር፡- በግጭት ውስጥ ያለፉ እንደ አፋርና አማራ ክልል ያሉ ተፈታኞችን በልዩ ሁኔታ መመዘን ያልተቻለው ለምንድነው?

ፕሮፌሰር ብርሃኑ፡- ፈተናው ከመሰጠቱ ከጥቂት ሳምንታት በፊት ከክልል ትምህርት ቢሮ ኃላፊዎች፣ ከመከላከያ፣ ከፌዴራል ፖሊስ፣ ከኢንሳና ከሌሎች ዘርፎች በተውጣጡ ሰዎች ኮማንድ ፖስት ተዋቅሮ ፈተናው የሚሰጥበትን መንገድ በተመለከተ ውይይትና ዝግጅት ተድርጓል፡፡ ባለፉት ጥቂት ዓመታትም ይኼው ዓይነት አሠራር ስለተጀመረ በዚያው ነው የቀጠለው፡፡ ነገር ግን ዘንድሮ ግጭት ስላለ አንድ ፈተና ብቻ ሳይሆን፣ ሁለት ፈተና ቢያንስ እንዲዘጋጅ ቀደም ባለ ውይይት መግባባት ላይ ተደርሶ ነበር፡፡ አንደኛው ፈተና በጊዜው ሰላም በሆኑ አካባቢዎች እንዲሰጥ የተወሰነ ሲሆን፣ ግጭቱ ባላባራባቸው አካባቢዎች ደግሞ ግጭቱ ሲያበቃ ሌላ ዙር ፈተና ለመፈተን ስምምነት ላይ ተደርሷል፡፡

ሁለተኛውና ከሁሉም አካላት ጋር መግባባት የተደረሰበት ጉዳይ ደግሞ ግጭት ባለባቸው አካባቢዎች ልጆቹ፣ ‹‹ፈተና ለመፈተን ዘንድሮ አዕምሯችን ዝግጁ አይደለም›› ካሉ ማንም እንዳያስገድዳቸውና በሚቀጥለው ዓመት ይፈተኑ የሚለው ነጥብ ነው፡፡ ይህን አማራጭ ተማሪዎቹ ካልፈለጉና እንፈተን ካሉ ግን ፍላጎታቸው ተጠይቆ እንዲፈተኑ ዕድል ተሰጥቷል፡፡ ይህ ሁሉ የተደረገው በዘፈቀደ ሳይሆን ታስቦበትና በመግባባት ነው፡፡ ግጭት ያለባቸው ወለጋ፣ ቤኒሻንጉል ጉሙዝ፣ አፋርና አማራ አካባቢዎች ፈተናውን ለመስጠት የሚቻልባቸው ምቹ አማራጮች በሙሉ ታይተውና ለውይይት ቀርበው ነው ይህ ሁሉ አማራጭ የቀረበው፡፡

የክልል ትምህርት ቢሮዎች ከወላጆች ጋር ተማክረው የወሰኑት ጉዳይ ነው፡፡ በጦርነት ካሉ አካባቢዎች ወጥተው በግል ወደ ሌሎች አካባቢዎች ሄደው መፈተን እንደሚፈልጉ የገለጹ ተማሪዎች ተፈትነዋል፡፡ አፋር አካባቢ የተወሰኑ ተማሪዎችን ሰላም ወዳለበት አካባቢ በመውሰድ ለመፈተን ተሞክሯል፡፡ ኦሮሚያም ተመሳሳይ ነገር አድርጓል፡፡ በጦርነት አሳልፈው ሥነ ልቦናቸው ከጫና ሳይወጣ ፈተና መፈተናቸው ተፅዕኖ አምጥቷል የሚል መከራከሪያ የቀረበው ግን የፈተናው ውጤት ከታየ በኋላ ነው፡፡

ሆኖም በመጀመርያው ዙር ፈተና ሲሰጥ ፊዚክስ ፈተና ከአንድ ቀን በፊት መውጣቱ ሪፖርት ቀረበ፡፡ ውጤቱ ሲመጣ የሲቪክስ ትምህርት የተማሪዎች ውጤት ከሌሎች ትምህርቶች የተጋነነ ሆኖ መታየቱ የፈተናውን መሰረቅ ያረጋገጠ ሆነ፡፡ ሁሉም ክልል የትኛውም ትምህርት ቤት በአማካኝ ከ80 በላይ የመጣበት በመሆኑ ውጤቱ ለዩኒቨርሲቲ መግቢያነት እንዳይያዝ ተደረገ፡፡ በሌላው ነገር ግን የቅበላውን ፍትሐዊነት የሚያዛባ ችግር አልተፈጠረም፡፡

ከፈተና ዕርማት ጋር በተያያዘ የተነሳው ቅሬታም ቢሆን፣ ሰዎች ቅሬታ ሳያቀርቡ ፈተና ሰጪው ድርጅት ያረጋገጠው ነበር፡፡ አንዳንድ ተማሪዎች ከትምህርት ቤታቸው ውጪ ሄደው መፈተናቸውና የኮድ መቀያየርን ያስከተለ ሲሆን፣ አንዳንድ ተማሪዎችን ደግሞ ሁለቱንም ፈተናዎች እንደወሰዱ ቆጥሮ ማሽኑ ያረመበት ሁኔታ ተፈጥሮ ነበር፡፡ አንድ ግለሰብ አንድ ፈተና ተፈትኖ ሁለት ውጤት የተሰጠው ሊገኝ ችሏል፡፡ የመጀመርያውን ወስዶ ነገር ግን በሁለተኛውም የተፈተነ ነው ተብሎ የታረመም አለ፡፡ ይህን ቁጭ ብሎ በማኑዋል ማስተካከል ይጠይቅ ስለነበር፣ እሱ እየተሠራ ሳለ ውጤት በመውጣቱ የተማሪዎች ቅሬታ ተከተለ፡፡

ወደ 1,700 ችግሮች የተገኙ ሲሆን ከዚያ ውስጥ ውጤታቸው የተዘበራረቀ ደግሞ 297 ነበሩ፡፡ እነዚህ ችግሮች ወዲያው እንዲስተካከሉ ተደረገ፡፡ ነገር ግን ክልሎች የተማሪዎቻችን ውጤት ተበላሽቷል ዕርማቱ ትክክል አይደለም የሚል ቅሬታ አነሱ፡፡ በዚህ መሠረት ውጤታችን ልክ አይደለም ተብሎ ወደ 20 ሺሕ ማመልከቻዎች ቀርበዋል፡፡ ነገር ግን ዳግም ታርሞ በትክክል ስህተት የተገኘበት ከ297 በስተቀር አንድም አለመኖሩን አረጋግጠናል፡፡ በፈተና ስርቆት ምክንያትም ሆነ በዕርማት የተዛባ ውጤት አላገኘንም፡፡ ነገር ግን ጦርነቱ በተማሪዎች ላይ ተፅዕኖ ካስከተለ በልዩ ሁኔታ የተማሪዎች ቅበላ እንዲመቻች ለማድረግ እየተሞከረ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ፖለቲከኛ ባይሆኑ ምን ይሆኑ ነበር? መምህር፣ ደራሲ ወይስ ኢኮኖሚስት?

ፕሮፌሰር ብርሃኑ፡- ፖለቲካ ውስጥ ባልገባ ብዬ ብቻ ሳይሆን፣ ከገባሁም በኋላ ሆነ አሁንም አስተማሪ ነው መሆን የምፈልገው፡፡ አሁንም ቢሆን ትምህርት ሚኒስትር ሆኜ ቢያንስ አንድ ትምህርት ማስተማር አለብኝ በሚል ከራሴ ጋር እየተነጋገርኩ ነው፡፡ ማስተማርን እደሰትበታለሁ፡፡ ዝም ብሎ ሥራ ሳይሆን የምትማርበት፣ የምታነብበት፣ አዲስ ትውልድ የምታስተምርበትና ከእነሱም የምትማርበት ነው፡፡ አስተማሪነት ለገንዘብ ተብሎ የሚሠራ አይደለም፡፡ አሜሪካ አገር ለአንድ አንደኛና ሁለተኛ ደረጃ አስተማሪ በዓመት 42 ሺሕ ዶላር ነው በአማካይ የሚከፈለው፡፡ ሆኖም በተቃራኒው የአሜሪካ መንግሥት ለአንድ እስረኛ መቀለቢያ በዓመት 55 ሺሕ ዶላር ያወጣል፡፡ አስተማሪነት የትም አገር ተገቢውን ክፍያ አግኝቶ አያውቅም፡፡ አስተማሪ ሳይቸገር ይሥራ እንጂ የትም በቂ ደመወዝ ታስቦለት አያውቅም፡፡ ለማንም የምመክረው ለገንዘብ ተብሎ ወደ እዚህ ክቡር ሙያ እንዳይገባ ነው፡፡ ሚኒስትርም ሆኜ ባለኝ ጊዜ የሚቀጥረኝ ካገኘሁ ቢያንስ አንድ ትምህርት ለማስተማር ዝግጁ ነኝ፡፡

ሪፖርተር

2 Comments

  1. ሪፖርተር ዮናስ አማረ….. ጥሩ ስራ ነው የጋዜጠኛነት ሙያ እንዲዝህ ያለ የህብረተሰብ እና አገር ችገር እንዴት ሊወገድ በሚችል ገንቢ መረጃ ፍለጋ ላይ ነው ማነፍነፍ ያለበት፡፡ እንድው አብዛኛው ህብረተሰብ እራሱ ወይም ልጁ ወይም በቅርብ ዘመዱ በኩል በትምህርት ላይ ስለሚያልፍ ይህን የተጣመመ ስርዓት ለማቃናት ልብ ያለው ልብ ሊልበት የሚገባ ጊዜ ስለሆነ ሊታሰብብበት ይገባል፡፡
    ከመጠይቁ አንዳንድ መሰረታዊ ሃሳቦች ብቻ ባተኩር ምንምእንኳን ጥልቅ ጥናት እንደተሰራ መረጃው ቢያመለከትም፡፡ እሰቲ በፕሮፌሰሩ የተነሱትን አንዳንዱን እንይ፣
    “ ………… በተሠለፍክበት ዘርፍ ያሉ ሁሉንም ችግሮችን መፍታት ባትችል እንኳን፣ የጎበጠውን ጥቂት ነገር ማቃናትም ትልቅ ነገር ነው:: …….. አንድን ኅብረተሰብ ወዴት እንደሚሄድ አቅጣጫውን ለመወሰን የትምህርት ዘርፍን ያህል አቅም ያለው እንደሌለ አምናለሁ፡፡ ……… በጣም የተበላሸ ከሆነ ግን የተበላሸውን የማቃናት ኃላፊነት አንተ ላይ እንደተጫነ አስበህ፣ እሱን ለማቃናት ዕዳ መሸከምህን ተረድተህ ነው ወደ ሥራው የምትገባው፡፡ ……… ትዝ ይለኛል ፕሮፌሰር መስፍን ወልደ ማሪያም፣ ‹‹ያፀድቅ እንደሆነ እንጂ ዲግሪ በሦስት ዓመታት መስጠት ማስተማር አይደለም፤›› ሲል ነበር የተቸው፡፡
    ……ከዚያን ጊዜ ወዲህ እየወረደ መጥቶ አሁን ላይ በጣም የሚያስደነግጥ ደረጃ ላይ ነው የወደቀው፡፡ ለምሳሌ ከቋንቋ ጀምሮ ብታይ ትምህርት በእንግሊዝኛ ቋንቋ ነው የሚሰጠው ይባላል፡፡ ነገር ግን እንግሊዝኛ መናገርም መስማትም የማይችሉ ተማሪና አስተማሪዎች ናቸው የሞሉት፡፡ በምን እንደሚግባቡ ፈጣሪ ነው የሚያውቀው፡፡ ….. ኢትዮጵያ ውስጥ ባሉ የመንግሥት ትምህርት ቤቶች ሦስተኛ ክፍል ደርሰው ማንበብ የማይችሉ ተማሪዎች ቁጥር ወደ 69 በመቶ ነው፡፡ በሚያስተምሩበት ትምህርት የምዘና ፈተና ወስደው 50 በመቶ በማምጣት ያለፉ መምህራን ቁጥር ከ30 በመቶ በታች ነው፡ : ……… የትምህርት አስተዳዳሪ የሚባሉት የትምህርት ቤት ዳይሬክተሮች ለቦታው መመጠናቸውን ለማረጋገጥ በተሰጠ ምዘና ፈተና ያለፉት 30 በመቶ ብቻ ናቸው፡፡ ከኢትዮጵያ አስተማሪዎች ውስጥ 52 በመቶዎቹ በአግባቡ ትምህርት ቤት ወይም ክፍል ተገኝተው አያስተምሩም፡፡ ….. በዚህ ዓይነቱ አካሄድ ትምህርት ተብሎ ደግሞ ዲግሪ በየቦታው እንደ ከረሜላ ታድሏል፡፡ …. በአገር አቀፍ ደረጃ በተደረገው ጥናት ከ47 ሺሕ ተማሪ ቤቶች አራተኛ ደረጃ ላይ የሚገኙት ስድስት ብቻ መሆናቸው ተረጋግጧል፡፡ ይህ 0.001 በመቶ ተብሎ የሚቀመጥ ነው፡፡ ወደ 90 በመቶዎቹ ትምህርት ቤት ሊባሉ በማይችሉበት አንደኛና ሁለተኛ ደረጃ ላይ የወደቁ ናቸው፡፡ ሽንት ቤት፣ ውኃና መብራት የላቸውም፡፡ አፈር ላይ ተቀምጠው ነው የሚማሩት፡፡ እንዲሁም ሴት ተማሪዎች ለንፅህና እንኳን የሚሄዱበት ቦታ የላቸውም፡፡ ከዚህ መሰሉ ግምገማ በመነሳት ነው የትምህርት ችግራችን ወደ እዚህ ቀውስ የገባው ለምንድነው የሚለውን ለማስቀመጥ የሞከርነው፡፡ በዚህ ረገድ ደግሞ አራት ዋና ዋና ምክንያቶችን አስቀምጠናል፡፡
    …..‹‹ፖለቲካና ትምህርት ዝም ብሎ መጋባት ሳይሆን፣ በተክሊል ነው የተጋቡት፤›› ሲል ነበር አንድ መምህር የችግሩን መልክ የገለጸው፡፡ በትምህርት ዘርፍ ውስጥ ፖለቲካ በሁሉም ጉዳይ በመግባቱ ሰፊና ውስብስብ ችግር የፈጠረ ሆኗል፡፡ ከዳይሬክተሮች ምደባ ጀምሮ በፖለቲካ ታማኝነት ሲሆን፣ የዳይሬክተሮች ዋና ሥራም በትምህርት ቤቶች ዙሪያ ያለውን ፖለቲካ መከታተል ነው፡፡ ይህ ባለፉት ጥቂት ዓመታት በተሞከሩ ማሻሻያዎች መቀየር እየጀመረ ነው::
    ዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ የፕሬዚዳንቶች ምደባ ፖለቲካን መሠረት ባደረገ ምዘና ነው፡፡ በካሪኩለም፡፡ በሁሉም ቦታ ፖለቲካ አለ፡፡ …. በትምህርት ዘርፍ ዕውቀት መቅደም አለበት፡፡ በተለይ በዩኒቨርሲቲ ደረጃ ዓለም አቀፍ ዕውቀት ነው የሚገበየው፡፡ ዕውቀት የተለየ ብሔር፣ ቋንቋም ሆነ ማንነት የለውም፡፡ የኦሮሞ ፊዚክስ ወይም የአማራ ኬሚስትሪ ወይም የጉራጌ ባዮሎጂ የለም፡፡ …
    የፈተና መስረቅ ችግር በ2008 ዓ.ም. ይመስለኛል የተጀመረው፡፡ ወደ ስምንት ዓመታት እያስቆጠረ ይገኛል፡፡ ፈተና መስረቅ የመጣበት ምክንያት ደግሞ የፖለቲካ ዓላማ ነው፡: ….ፈተናው የሚሰረቀው ግን በብሔራዊ ደረጃ ብቻ ሳይሆን፣ በየአካባቢው ጭምር ነው፡: …. ፈተና ማሠራጨትና ሳይሰረቅ ማስፈተን የሞት የሽረት ጉዳይ እየሆነ ነው፡፡ …. በትምህርት ዘርፉ የሚደረግ ጨዋታ እንዲቆም ቅድሚያ ሰጥተን እየሠራን ነው፡፡ ፈተናን በዲጂታል ቴክኖሎጂ ከመፈተን ጀምሮ ብዙ አማራጮችን እያማተርን ነው፡፡ ……..

    በአጠቃላይ ከመጠይቁና ከትምህርት ዘርፉ የምንረዳው ምን ያህል የወረደ እንደሆነ፣ የተቀለደበት፣ ሳይታለም የተፈታ ነቀርሳ የተተከለበት ነው፡፡ ብዙ ተብሎ ነበር፣ ተተችቶ ነበረ የፖለቲካ ማስፈፀሚያ መሳሪያ ሆኖ ተቀለደበት እንጂ፡፡ በዓለም ላይ በስልጣን ዘመኑ እንደዚህች አገር በትምህርት ስርዓት ላይ የቀለደበት አገር የትም አይገኝም፡፡ አስተማሪው ችግር እያለበት ተማሪውስ እንዴት ነው ቋንቋ ጎበዝ ሊሆን የሚችል አንዳንዱ በራሱ ጥረት ቢያሻሽልም፡፡ ታዲያ እንዲህ ያለ ተማሪ ከኮሌጅ እየወጣ ስራ ለመቀጠር ሲሄድ እንደው ለመግባበያ ያህል Briefly explain about yourself ሲባል ግራ የሚገባው ፡፡ ታዲያ የትውልድ ዝቅጠት ከመጣ ዘመናት ተጥሯል አይደንቅም እኮ፡፡ በነገራችን ላይ ፕሮፌሰሩ እንዳሉት ሳይሆን ይመስለኛል ቢሉም የማትሪክ/12ኛ/ ክፍል መሰረቀ የጀመረው በ2008 ሳይሆን በአገራችን አቆጣጠር ለመጀመሪያ ጊዜ በገሃድ የወጣው በ1980 ዓ.ም. ነው ይህን በወቅቱ የነበሩ ተማሪዎች ሊመሰክሩ ይችላሉ፡፡ ሌላው ያለነሱት ነገር ዲግሪ እንደሚታደል ቢገልፁም ዩኒቨርሲቲ ምደባ ጥቁር አንበሳ ህክምና ለማጥናት ሌላም ቅርብ ቦታ ለማስመደብ ስንት ሻጥርና ሙስና የሚሰራበት ነው እኮ፡፡ ፕሮፌሰር መስፍን በጣም ይታገሉ እንደነበረና ሰሚ አጡ እንጂ ዲግ መስጠት ማፅደቁ ብቻ ሳይሆን በፓርቲ አባልነት ብቻ ዩኒቨርሲቲ እና ኮሌጅ ውስጥ እኮ ግሬድ ስንት ይታደል ነበር እንአረ ስንቱን ማውራ ይቻላል፡፡ ሆኖም አሁን የተጀመረው ሰንቆፍ ከስር መሰረቱ መነቀል አለበት፡፡ የመምህራን የራሱ ምዝና ቢኖርም በደንብ መለኪያ ተበጅቶለት ምሳሌ/KPE/ በማዘጋጀት ለሊካ ይገባል፡፡ በየ ዞኑ ያሉ የወትመ/ትምህርት ቢሮ/ ምን እየሰሩ ነው ሊፈተሸ ይገባል፡፡ በየኒቨሪሲቲና ኮሌጆችም ጭምር፡፡
    አሁን ወሬ ሳይሆን ለውጥ!!!ለውጥ!!! ለውጥ!!! ይፈለጋል በዚህች አገር፡፡ የተጣመመውን ለማቅናት መስራት ብቻ ሳይሆን ግንዱን የሚያጣምመውን ሁሉ ማስወገድ ያስፈልጋል፡፡ ፈተና ዲጅታል ሲስተም ማድረጉ ብቻ ሳይሆን ሰው ሁሉንም ነገር Manipulate ስለሚያደረግ ከባድ ጥንቃቄ ያስፈልጋል፡፡ እሰከ ወረዳ ድረስ ያለውን ችግር ለመቅረፍ የማህረሰብ ንቅናቄ ከመፍጠር ጀምሮ በዚህ ሰንሰለት ላይ የሚሰማሩትን እስከ ከባድ ቅጣት/ሞት ፍርድ ድረስ/ እርምጃ መውስድ ትውልድን ከመግደል ይሻላል፡፡
    የህብረተሰብ ውይይት መድረክ ማዘጋጀት ማንም እኮ ጉዳዩ ያገባዋል፡፡ ሕዝብን ያቀፈ ስራ መስራ፡፡

  2. በአጠቃላይ ከመጠይቁና ከትምህርት ዘርፉ የምንረዳው ምን ያህል የወረደ እንደሆነ፣ የተቀለደበት፣ ሳይታለም የተፈታ ነቀርሳ የተተከለበት ነው፡፡ ብዙ ተብሎ ነበር፣ ተተችቶ ነበረ የፖለቲካ ማስፈፀሚያ መሳሪያ ሆኖ ተቀለደበት እንጂ፡፡ በዓለም ላይ በስልጣን ዘመኑ እንደዚህች አገር በትምህርት ስርዓት ላይ የቀለደበት አገር የትም አይገኝም፡፡ አስተማሪው ችግር እያለበት ተማሪውስ እንዴት ነው ቋንቋ ጎበዝ ሊሆን የሚችል አንዳንዱ በራሱ ጥረት ቢያሻሽልም፡፡ ታዲያ እንዲህ ያለ ተማሪ ከኮሌጅ እየወጣ ስራ ለመቀጠር ሲሄድ እንደው ለመግባበያ ያህል Briefly explain about yourself ሲባል ግራ የሚገባው ፡፡ ታዲያ የትውልድ ዝቅጠት ከመጣ ዘመናት ተጥሯል አይደንቅም እኮ፡፡ በነገራችን ላይ ፕሮፌሰሩ እንዳሉት ሳይሆን ይመስለኛል ቢሉም የማትሪክ/12ኛ/ ክፍል መሰረቀ የጀመረው በ2008 ሳይሆን በአገራችን አቆጣጠር ለመጀመሪያ ጊዜ በገሃድ የወጣው በ1980 ዓ.ም. ነው ይህን በወቅቱ የነበሩ ተማሪዎች ሊመሰክሩ ይችላሉ፡፡ ሌላው ያለነሱት ነገር ዲግሪ እንደሚታደል ቢገልፁም ዩኒቨርሲቲ ምደባ ጥቁር አንበሳ ህክምና ለማጥናት ሌላም ቅርብ ቦታ ለማስመደብ ስንት ሻጥርና ሙስና የሚሰራበት ነው እኮ፡፡ ፕሮፌሰር መስፍን በጣም ይታገሉ እንደነበረና ሰሚ አጡ እንጂ ዲግሪ መስጠት ማፅደቁ ብቻ ሳይሆን በፓርቲ አባልነት ብቻ ዩኒቨርሲቲ እና ኮሌጅ ውስጥ እኮ ግሬድ ስንት ይታደል ነበር እንአረ ስንቱን ማውራ ይቻላል፡፡ ሆኖም አሁን የተጀመረው ሰንቆፍ ከስር መሰረቱ መነቀል አለበት፡፡ የመምህራን የራሱ ምዝና ቢኖርም በደንብ መለኪያ ተበጅቶለት ምሳሌ/KPE/ በማዘጋጀት ለሊካ ይገባል፡፡ በየ ዞኑ ያሉ የወትመ/ትምህርት ቢሮ/ ምን እየሰሩ ነው ሊፈተሸ ይገባል፡፡ በየኒቨሪሲቲና ኮሌጆችም ጭምር፡፡
    አሁን ወሬ ሳይሆን ለውጥ!!!ለውጥ!!! ለውጥ!!! ይፈለጋል በዚህች አገር፡፡ የተጣመመውን ለማቅናት መስራት ብቻ ሳይሆን ግንዱን የሚያጣምመውን ሁሉ ማስወገድ ያስፈልጋል፡፡ ፈተና ዲጅታል ሲስተም ማድረጉ ብቻ ሳይሆን ሰው ሁሉንም ነገር Manipulate ስለሚያደረግ ከባድ ጥንቃቄ ያስፈልጋል፡፡ እሰከ ወረዳ ድረስ ያለውን ችግር ለመቅረፍ የማህረሰብ ንቅናቄ ከመፍጠር ጀምሮ በዚህ ሰንሰለት ላይ የሚሰማሩትን እስከ ከባድ ቅጣት/ሞት ፍርድ ድረስ/ እርምጃ መውስድ ትውልድን ከመግደል ይሻላል፡፡
    የህብረተሰብ ውይይት መድረክ ማዘጋጀት ማንም እኮ ጉዳዩ ያገባዋል፡፡ ሕዝብን ያቀፈ ስራ መስራት፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Share