ከአሰግድ ተፈራ
በመጪው ሚያዝያ ስድስት ቀን 2005ዓ.ም በሚካሄደው የሮተርዳም ማራቶን ውድድር ሁለት ሰዓት ከስድስት ደቂቃ በታች የሆነ ሰዓት ያላቸው ስድስት አትሌቶች የሚሳተፉ ሲሆን ፣ ከእነዚህ መካከል ኢትዮጵያዊው ብርሃኑ ሽፈራው የአሸናፊነት ቅድሚያ ግምት ማግኘቱን የዓለም አቀፉ አትሌቲክስ ፌዴሬሽኖች ማኀበር ድረ ገጽ ዘግቧል።
በፌዴሬሽኑ አንደኛ ደረጃ በተሰጠው በዚህ የማራቶን ውድድር የ19 ዓመቱ ወጣት ብርሃኑ ሽፈራው ፈጣን ሰዓት ካስመዘገቡት አንዱ ሆኗል።
ወጣቱ በርቀቱ ሁለት ሰዓት ከአራት ደቂቃ ከ48 ሰከንድ የሆነ የግሉ ምርጥ ሰአት ያለው ሲሆን፤ይህንን ሰዓት ያስመዘገበው ባለፈው ጥር ወር በዱባይ በተካሄደው ማራቶን ነው። በውድድሩ አትሌቱ ሁለተኛ መውጣቱ ይታወሳል።
የሮተርዳሙ ማራቶን አትሌቱ ለአምስተኛ ጊዜ የሚያደርገው ውድድር መሆኑንም ዘገባው አመልክቷል።
በዚህ ውድድር ላይ ተሳታፊ ከሚሆኑት ኢትዮጵያውያን የማራቶን ሯጮች መካከል በለንደን ኦሊምፒክ የኢትዮጵያ ብሔራዊ አትሌቲክ ቡድን አባል የነበረው ጌቱ ፈለቀ ይገኝበታል።አትሌት ጌቱ ፈለቀ በአውሮፓውያኑ 2012 በስፍራው በተደረገው ተመሳሳይ ውድድር ሁለተኛ መውጣት የቻለ አትሌት ነው።ሁለት ሰዓት ከአራት ደቂቃ ከ50 ሰከንድ የሆነ የግሉ ምርጥ ሰዓት አለው።
ሁለት ሰዓት ከአምስት ደቂቃ ከ25 ሰከንድ የሆነ የግሉን ምርጥ ሰዓት በማስመዝገብ በውድድሩ የሚሳተፈው ሌላው ኢትዮጵያዊ በዙ ወርቁ ነው። አትሌቱ እ.ኤ.አ በ2010 በጀርመን በርሊን በተካሄደው የማራቶን ውድድር ሦስተኛ ሆኖ ማጠናቀቅ መቻሉ ይታወሳል።
ከበዙ ወርቁ በሁለት ሰከንዶች ብቻ የዘገየ ሰዓት ያለውና በሮተርዳም የተሻለ ሰዓት ለማስመዝገብ የሚሮጠው ሌላው ኢተዮጵያዊ ጥላሁን ረጋሳ ነው። አትሌት ጥላሁን የመጀመሪያውን ማራቶን የተወዳደረው ባለፈው ጥቅምት በቺካጎ ማራቶን ነበር።
በሴቶች መካከል በሚደረገው ተመሳሳይ ውድድር ኢትዮጵያዊቷ ምስክር መኮንን እንደምትሳተፍ ዘገባው አስነብቧል። አትሌቷ ርቀቱን በሁለት ሰዓት ከ25 ደቂቃ ከ21 ሰከንድ ያጠናቀቀችበት ሰዓት የግሏ ምርጥ ሰዓት ነው።
የ26 ዓመቷ ምስክር በቅርቡ በሆንግ ኮንግ የተካሄደውን የማራቶን ውድድር በሁለት ሰዓት ከ30 ደቂቃ ከ49 ሰከንድ በሆነ ሰዓት በማጠናቀቅ ለሁለተኛ ጊዜ ማሸነፏ ይታወሳል።
በውድድሩ ከምስክር በተጨማሪ አበበች አፈወርቅ በማራቶን ሁለተኛ ውድድሯን ታደርጋለች ብሏል ዘገባው።
የ22 ዓመቷ አበበች የመጀመሪያዋ የሆነውን የማራቶን ውድድር ያደረገችው በአውሮፓውያኑ 2013 መግቢያ ላይ ሲሆን፤ውድድሩን በሁለት ሰዓት ከ27 ደቂቃ ከስምንት ሰከንድ አጠናቅቃለች።
በውድድሩ የቀድሞ የአይንዶሆቨንና የኮሎኝ ማራቶን ውድድሮች አሸናፊዋ አበሩ መኩሪያም ተሳታፊ እንደምትሆን ዘገባው አመልክቷል።