ለቸኮለ! ማክሰኞ ጥቅምት 2/2014 ዓ.ም የዋዜማ ዐበይት ዜናዎች

1፤ በኢትዮጵያ የተመድ ዓለማቀፍ ፍልሰተኞች ድርጅት ሃላፊ ማውሪን አቼንግ ከትግራዩ ግጭት ጋር በተያያዘ በሰጡት አስተያየት ለጊዜው የግዳጅ ሥራ ፍቃድ እንዲወስዱ መደረጋቸውን የፈረንሳዩ ዜና ወኪል ዘግቧል። ሃላፊዋ የግዳጅ ፍቃድ የተሰጣቸው፣ ለሕወሃት የወገኑያሏቸው በኒውዮርክ የተመድ ከፍተኛ ሃላፊዎች እርሳቸውን ጨምሮ በኢትዮጵያ የሚገኙ የተመድ ሃላፊዎችን በትግራዩ ግጭት ዙሪያ ከውሳኔ ሰጭነት እና መረጃ ልውውጥ እንዳገለሏቸው ጠቅሰው፣ ለካናዳዊው ጋዜጠኛ ጄፍ ፒርሰ የሰጡት ቃለ ምልልስ የድምጽ ቅጂ ሾልኮ ከወጣ በኋላ ነው። ሃላፊዋ በቃለ ምልልሳቸው ሕወሃት ከሳዑዲ ዐረቢያ የተባረሩ የትግራይ ተወላጅ ፍልሰተኞችን ሩዋንዳ ለማስፈር አሲሮ እንደነበር ጠቅሰዋል። የዓለማቀፉ ፍልሰተኞች ድርጅት ዋና ሃላፊ አንቶኒዮ ቪቶሪኖ የሃላፊዋ አስተያየት ድርጅቱን እንደማይወክል የሚገልጽ ደብዳቤ አሰራጭተዋል።

2፤ መስከረም 20 ምርጫ በተደረገባቸው ሱማሌ፣ ሐረሬ እና የተወሰኑ የደቡብ ክልል ምርጫ ክልሎች አብዛኛውን መቀመጫ ገዥው ብልጽግና ፓርቲ እንዳሸነፈ ምርጫ ቦርድ ዛሬ ባወጣው ውጤት አስታውቋል። ከሦስቱ ክልሎች አንድ የሱማሌ ክልል የግል እጩ ብቻ ለክልሉ ምክር ቤት አሸንፈዋል። በደቡብ ክልል 3 የክልል እና የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ምርጫ ክልሎች እንዲሁም በሱማሌ ክልል 2 የክልል ምክር ቤት ምርጫ ክልሎች ላይ ግን የቅሬታዎች ምርመራ ገና ባለመጠናቀቁ፣ በዛሬው የተረጋገጠ ውጤት አልተካተቱም። በሦስቱ ክልሎች ምርጫ የተካሄደው ለ47 የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እና ለ106 የክልል ምክር ቤት መቀመጫዎች ነው።

3፤ ምርጫ ቦርድ ትናንት ባጸደቀው ሕዝበ ውሳኔ መሠረት አዲሱ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ጥቅምት 29 እንደሚመሠረት የክልሉ ምስረታ ጊዜያዊ አስተባባሪ ጽሕፈት ቤቱ መግለጹን የሀገር ውስጥ ዜና አውታሮች ዘግበዋል። በሕገ መንግሥቱ መሠረት የአዲሱ ክልል ምሥረታ እውን የሚሆነው፣ ከደቡብ ክልል ጋር የሥልጣን ርክክብ ሲያደርግ ነው። አስተባባሪ ጽሕፈት ቤቱ ለአዲሱ ክልል ያዘጋጀውን ረቂቅ ሕገመንግሥት ወደ ሕዝቡ እንዳወረደ ገልጧል። የአዲሱ ክልል መስራቾች ካፋ፣ ቤንች ሸኮ፣ ሸካ፣ ዳውሮ እና ምዕራብ ኦሞ ዞኖች እና ኮንታ ልዩ ወረዳ ናቸው።

ተጨማሪ ያንብቡ:  ቃለ ምልልስ (ነቢዩ ሲራክ)

4፤ የአማጺው ሕወሃት ታጣቂዎች በአማራ ክልል በወረራ በያዟቸው የሰሜን ጎንደር እና ሰሜን ወሎ ዞኖች የአርሶ አደሮችን የኢከኖሚ መሠረት በማውደም ዘመቻ ላይ ተሠማርተዋል ሲል ውጭ ጉዳይ ሚንስቴር ዛሬ ባወጣው መግለጫ ከሷል። አማጺያኑ የአርሶ አደሮችን የደረሱ ሰብሎች እያጋዙ እና ከፍጆታቸው የተረፈውን የአርሶ አደር ጥሪት እያወደሙ እንደሆነ የገለጠው ሚንስቴሩ፣ ዓለማቀፍ ኅብረተሰብ በሕወሃት ወረራ ስር ላለው ዕርዳታ ፈላጊ ሕዝብ ትኩረት እንዲሰጥ ጠይቋል። አማጺዎቹ የአርሶ አደሮችን እንስሳትን በጅምላ እየገደሉ፣ ዕርዳታ እየዘረፉ፣ ትምህርት ቤቶችን፣ ባንኮችንና የሕክምና ተቋማትን እያወደሙና በግንባታ ላይ ባለው የአዋሽወልድያሐራ ገበያ ባቡር ሐዲድ ላይ ጉዳት እያደረሱ እንደሆነ ሚንስቴሩ ጠቁሟል። ሕወሃትን ይህን የሚያደርገው፣ የፖለቲካ ተዋናይ ሆኖ ለመቀጠልእና በትግራይና አማራ ሕዝቦች መካከል ጥላቻ ለመፍጠር ነውብሏል ሚንስቴሩ።

5፤ የኦነግ ሸኔ ታጣቂዎች በኦሮሚያ ክልል ምሥራቅ ወለጋ ዞን ኪራሙ ወረዳ በአማራ ብሄር ተወላጆች ላይ ጥቃት እየፈጸሙ መሆኑን ከጥቃቱ የተረፉ ነዋሪዎችን ለዋዜማ ሪፖርተር ተናግረዋል። ታጣቂዎች ንጹሃን የአማራ ብሄር ተወላጅ ነዋሪዎችን እየገደሉ እና እያሳደዱ ያሉት፣ በኪራሙ ወረዳ የተለያዩ ቀበሌዎች እንዲሁም በሆሮጉድሩ ወለጋ ዞን አቤ ደንጎሮ እና ሆሮ በተባሉ ወረዳዎች በሚገኙ ቀበሌዎች ነው::

6፤ ኢዜማ በኦሮሚያ ክልል ምሥራቅ ወለጋ ዞን ታጣቂዎች በተደጋጋሚ በንጹሃን ዜጎች ላይ የሚፈጽሙትን ጥቃት የክልሉ ፖሊስ እና ፌደራል ፖሊስ ለምን ማስቆም እንዳልቻሉ ማብራሪያ እንዲሰጡ ዛሬ በማህበራዊ ትስስር ገጹ ባወጣው መግለጫ ጠይቋል። የንጹሃን ግድያ ዛሬም መቀጠሉ መንግሥት ለችግሩ በቂ ትኩረት እንዳልሰጠውና ችግሩን ለመቅረፍ አስተዳደራዊና ሕጋዊ ርምጃዎችን እንዳልወሰደ ያሳያልብሏል ኢዜማ። ታጣቂዎች ወደ አጎራባች ወረዳዎች የሚያስወጡ ሁሉንም መንገዶች በመዝጋታቸው፣ በርካታ መውጫ ያጡ ነዋሪዎች በመድሃኒት እና ምግብ እጥረት እየተሰቃዩ መሆኑን ገልጧል።

ተጨማሪ ያንብቡ:  ዶ/ር አብይ ተፎካካሪ ፓርቲዎች 3 ወይም 4 እንዲሆኑ ጥሪ አቀረቡ

7፤ በኦሮሚያ ክልል አርሲ ዞን ለ5 ዓመታት ተዘግቶ የነበረው የአህያ ማረጃ ቄራ እንደገና ሥራ እንደጀመረ ፎርቹን ዘግቧል። በ60 ሚሊዮን ብር ባንድ የቻይና ኩባንያ የተቋቋመው ቄራ፣ ባለፈው ወር 80 ሺህ ዶላር የአህያ ስጋ ለምሥራቅ እስያ ገበያ እንዳቀረበ ዘገባው ጠቅሷል። ቄራው ከ5 ዓመት በፊት የተዘጋው ከኅብረተሰቡ ባሕል እና እምነት ጋር ይጋጫል በሚል ሲሆን፣ አሁን ግን ከከተማዋ አስተዳደር፣ ከሀገር ሽማግሌዎችና ከሐይማኖት አባቶች ጋር በተደረሰ መግባባት እንደገና የአህያ ስጋ ለውጭ ገበያ ማቅረብ ጀምሯል።

8፤ ኬንያ እና ሱማሊያ ከፍተኛ የተፈጥሮ ጋዝ ክምችት ባለበት የሕንድ ውቅያኖስ ግዛት ላይ ያነሱትን የይገባኛል ውዝግብ ሲመለከት የቆየው ዓለማቀፉ ፍርድ ቤት ኬንያ ያቀረበችውን የባሕር ድንበር አከላለል ውድቅ ማድረጉን የሀገሪቱ ዜና ምንጮች ዘግበዋል። ኬንያ በአወዛጋቢው ባሕር ላይ የጋዝ ቁፋሮ በማድረግ ሉዓላዊነቴን ጥሳለች በማለት ሱማሊያ ያቀረበችውን ክስ ችሎቱ አልተቀበለውም። ኬንያ ፍርድ ቤቱ ለውዝግቡ ብይን ለመስጠት አለኝ ለሚለው ሕጋዊ መሠረት እውቅና ነፍጌያለሁ በማለት ብይኑን እንደማትቀበል ባለፈው ሳምንት ማስታወቋ ይታወሳል።

9፤ የኬንያው ፕሬዝዳንት ኡሁሩ ኬንያታ ከተመድ ዋና ጸሃፊ አንቶኒዮ ጉተሬዝ ጋር በኒውዮርክ ተገናኝተው ስለ ትግራይ ግጭት እና ሰብዓዊ ቀውሱ እንደተወያዩ ጽሕፈት ቤታቸው ባሰራጨው መረጃ አስታውቋል። ኬንያታ እና ጉተሬዝ ለትግራዩ ግጭት ሰላማዊ መፍትሄ ለማፈላለግ ከኢትዮጵያ መንግሥት እና ከሌሎች የግጭቱ ተዋናዮች ጋር ውይይት ማድረጋታቸውን እንደሚገፉበት ገልጠዋል። ፕሬዝዳንቱ ዛሬ ጸጥታው ምክር ቤት በብዝሃነት፣ ሀገር ግንባታ እና ጸጥታ ላይ የሚያደርገውን ስብሰባ በሊቀመንበርነት ይመራሉ።

[ዋዜማ ራዲዮ]

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Share