ዶ/ር አብይ ተፎካካሪ ፓርቲዎች 3 ወይም 4 እንዲሆኑ ጥሪ አቀረቡ

በርካታ ኢትዮጵያዊያውያን በተስፋ ሲጠብቁት የቆየው የዶ/ር አብይ አህመድ እና የተፎካካሪ ፓርቲዎች ጋር ውይይት በጽህፈት ቤታቸው ተካሄደ:: በውይይቱ ዶ/ር አብይ ተፎካካሪ ፓርቲዎች ሶስት እና አራት ብቻ እንዲሆኑ ጠይቀው እገዛ ለማድረግ ቃል ገብተዋል::
https://www.youtube.com/watch?v=kk-bdasg-qA

“በአጠቃላይ የዛሬው መድረክ የፖለቲካ ፓርቲዎች ውይይት በይፋ መጀመሩን የምናሳውቅበትም ይሆናል” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮችን አሁን ላይ በሀገሪቱ ስለተጀመረው የዴሞክራሲ ለውጥ እና በሚቀጥለው ዓመት የሚደረገውን ሀገራዊ ምርጫ ነፃ እና ፍትሃዊ ለማድረግ ሊወሰዱ በሚገባቸው አስፈላጊ ለውጦች ዙሪያ ውይይት ያካሄዱ ሲሆን ባቀረቡት መነሻ ሃሳብም ከተፎካካሪ ፓርቲዎች ጋር የሚደረገው ውይይት በሶስት ደረጃ ተከፋፍሎ የሚካሄድ መሆኑን ገልጸዋል::

በዚህም መሰረት ደረጃ አንድ የውይይቱ መክፈቻ ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ፤ ደረጃ ሁለት ዋና ዋና የምርጫ ስራዎች ላይ ትኩረት እንደሚያደርግ እና በደረጃ ሶስት ደግሞ ከምርጫ በኋላ በሚሰሩ ስራዎች ላይ የሚያተኩር መሆኑን ጠቅሰው; በመጀመሪያ ደረጃ ውይይት ላይም በቀጣይ የሚከናወኑ የፖለቲካ ፓርቲዎች ውይይት ምን መልክ ይኑረው በሚለው ላይ እንደሚመከር እና መመሪያ እንደሚያዘጋጅ ጠቁመዋል።

እንዲሁም ሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች በውይይቱ ላይ እንዲሳተፉ ማድረግ፣ በአጭር፣ በመካከለኛና በረጅም ጊዜ ሊፈቱ የሚገቡ ችግሮችን መለየት፣ ከዚህ ቀደም በተደረጉ ውይይቶች ያጋጠሙ ችግሮችን መለየትና መፍትሄ ማስቀመጥ፣ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ከህግ ውጪ ሲንቀሳቀሱ መንግስት ከሚሰውደው እርምጃ ውጪ ፓርቲዎች በጋራ የሚወስዱት እርምጃ ላይ መምከርም የመጀመሪያው ደረጃ ውይይት አላማ መሆናቸውንም በመግቢያ ንግግራቸው ጠቅሰዋል::

በሁለተኛ ደረጃ ውይይት ዋና ዋና የምርጫ ስራዎች ላይ ትኩረት እንደሚያደርግ ያስታወቁት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ፥ የዚህ ደረጃ ዋና አላማም ቀጣዩን ምርጫ ነፃ፣ ፍትሃዊ እና ዴሞክራሲያዊ ማድረግ መሆኑን አስረድተዋል። በዚህ ዙር ውይይትም በምርጫ ህግ፣ በምርጫ ቦርድ ስያሜ እና የምርጫ ቦርድ የመስራት አቅም ላይ ውይይት እንደሚደረግ እና ከውጭ የገቡ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባ ላይ በጋራ መስራት እንደተካተተ ጠቅሰዋል::

ተጨማሪ ያንብቡ:  የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ አስተዳደር ከልክሏል! # አረንጓዴ ቢጫ ቀይ ያለው ልብስም ተከልክሏል!

ሚዲያን በተመለከተ ውይይት እንደሚደረግ አያይዘው ያነሱት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ፥ ሚዲያዎች ሙሉ በሙሉ ህጋዊ ሆነው እንዲሰሩ ሁሉም የሚመለከተው አካል ተወያይቶበት የሚዲያ ህጉን መለወጥ እንደሚያስፈለግ አንስተዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር እብይ አህመድ አክለውም “የማህበራዊ ትስስር ድረ ገፆች ከዚህ ቀደም በነበሩ ምርጫዎች ላይ ፈተና አልነበሩም፤ በቀጣይ ምርጫ ግን ይፈታተኑናል:: ለዚህም የሚሰራጩ የሀሰት መረጃዎችን ለመከላከል እንዲቻል ሁሉም የፖለቲካ ፓርቲ የራሱ አርማ ያለበት ይፋዊ የማህበራዊ ሚዲያ አድራሻዎች እና ድረ ገጽ እንዲኖራቸው ይደረጋል” ብለዋል:

በሶስተኛ ደረጃ ውይይት ደግሞ ከምርጫ በኋላ ዘላቂ እና የተረጋጋ የፖለቲካ ምህዳር መፍጠር ላይ ምክክር እንደሚደረግ ነው ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አበይ አህመድ ያስታወቁት። በዚህ የውይይት ምእራፍ ህገ መንግስት ማሻሻያዎችን ጨምሮ በተቋማት ግንባታ እና በሌሎች ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ በትኩረት እንደሚመከርም ገልጸው ይህንን ለማምጣት ጊዜ ሊወስድ ቢችልም ነገር ግን መሰረት እንዲኖረው ከወዲሁ መስራት ያስፈልጋል ሲሉም ተናግረዋል::

“ዛሬ በውይይቱ የሚነሳውንም መነሻ በማድረግ ብሄራዊ የምርጫ ቦርድ የራሱን መርሃ ግብር ያወጣል:: የሚካሄደው ምርጫ ከዚህ በፊት የሚነሳበትን ስሞታ የማያስተናግድ ሊሆን ይገባል” ላሉት ዶ/ር አብይ በመድረኩ ላይ የተሳተፉ የተፎካካሪ ፓርቲ አመራሮችም የምርጫ ጊዜ መራዘም የለበትም፣ ከምርጫ በፊት መደማመጥ፣ መከባበር እና መደማመጥ ያስፈልጋል፣ ከምርጫ በፊት ህገ መንግስቱ መሻሻል አለበት፣ አሁን የተገኘውን ምቹ አጋጣሚ በመጠቀም ስርዓት መዘርጋት ያስፈልጋል፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች 80 ሆነን ከመበታተን ወደ ሶሰት እና አራት በመምጣት መጠንከር አለባቸው የሚሉ ሀሳቦች ተነስተውላቸዋል::

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ በሰጡት ምላሽ እና ማብራሪያም፥ ምርጫ ከሚካሄድበት ጊዜ ጋር ተያይዞ እስካሁን በይፋ ይራዘም የሚል ሀሳብ አልቀረበም፤ ሆኖም ግን የሚፈልግ አካል ካለ ሀሳቡን ማንሳት እና በውይይት ውሳኔ ላይ መድረስ እንደሚቻል; የፓርቲዎች ውህደትን በተመከለተም 70 ሆኖ ከመቅረብ ይልቅ 3 እና 4 ሆኖ መቅረብ የበለጠ እንደሚያጠናክር እንስተው፥ ፓርቲዎቹ ባይዋሃዱ እንኳ ግንባር ቢፈጥሩ መልካም መሆኑን እና በዚህ መልኩ ከተደራጁ መንግስትም ይሁን በግላቸው ቢሮ ከመስጠት ጀምሮ አስፈላጊውን ድጋፍ ሁሉ እንደሚያደርጉ ቃል ገብተዋል::

ተጨማሪ ያንብቡ:  የአብይ መደመር ማለት ይሄ ነው - በቃ እንበል

የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ ሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ በአቶ ክርስቲያን ታደሰ ሕገመንግስቱ እንዲሻሻል ጥያቄ አቅርቦ ነበር::
ከህገ መንግስት ማሻሻያ ጋር ተያይዞ ለተነሳላቸው ጥያቄም፥ ህገ መንግስት ማሻሻያ ለማድረግ መጀመሪያ መወያየት እንደሚያስፈልግና አከራካሪ ካልሆነ ውሳኔ እንደሚሰጥበት በመጠቆም፤ አከራካሪ ከሆነ ግን ከምርጫ በኋላ ህዝቡ ውሳኔ እንዲደረግበት ይደረጋል ሲሉ ዶ/ር አብይ ምላሽ ሰጥተዋል::

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ ጨምረውም መንግሥታቸው ሕግን ለማስከበር እየወሰደ ያለው እርምጃ ብሔር ላይ ያነጣጠረ ነው መባሉ ተገቢ አለመሆኑን ተናግረዋል።
እየተከናወነ ያለው ተግባር የሰብዓዊ መብት ጥሰት የፈፀሙና በተደራጀ ሌብነት ላይ የተሰማሩትን ብቻ ለሕግ ማቅረብ ነው። በዚህም ውስጥ ተሳታፊ የሆኑ ሁሉም ተጠያቂ ስለሚደረጉ ከብሔር ጋር ማያያዘ ተገቢ እንዳልሆነ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገልፀው፤ ጥፋት ሲሰሩ ህዝብን ሳያማክሩ ጥፋተኛ ነህ ሲባሉ ከብሔር ጋር ማያያዝ አደገኛ መሆኑን አስረድተዋል።
“ጥፍር ሲነቅል ሕዝብን ያላማከረ፤ ጥፍር መንቀል ሕጋዊ አይደለም ስንለው ብሔሩ ውስጥ ለመደበቅ ይሞክራል” በማለት ድረጊቶቹ በግለሰቦች የተፈፀሙ መሆናቸውን ገልፀዋል።

Share