ሰላማዊ መፍትሔ  ለኢትዮጵያ ሕዝቦች፣ – ሽማግሌው ከሁስተን ቴክሳስ    

የእግዚአብሔር ቃል፣”ሰላምን የሚያወርዱ ብፁዓን ናቸው፣ የእግዚአብሔር ልጆች ተብለው ይጠራሉና።ምሕረትን የሚያደርጉ ብፁዓን ናቸው፣ምሕረትን ያገኛሉና”ይላል። እኛም ይህን የአምላካችንን ቃልና ፈቃድ ተከትለን፣  ስለ አገራችንና ሕዝባችን እውነትን ተነጋግረን፣ ልዩነቶቻችንን በሰላም ብንፈታ፣ አገራችን ሁላችንንም በተድላና በደስታ ለማኖር የምታስችል ናት።

ሰይጣን ግን ክፉ ነው። አንድነታችንና ሰላማችንን ይጠላል።ምክንያት ፈጥሮ አርስ በርስ አጋጭቶ አዋግቶና አፋጅቶ፣ ከፈጣሪ አምላካችን አለያይቶ፣ የጥፋት ግብረ አበሩ በማድረግ ወደ ሲኦል ሊከተን ይሻል።ቀደምት ወላጆቻችን እንደ ሰቱ እኛም ስተናል።ወደንና ፈቅደን የጥፋት ጎዳናውን መርጠን “ሆ !”ብለን እርሱኑ ተከትለናል። የፈጣሪ አምላካችን ፈቃድ ወንድሞቻችንን እንደ ራሳችን እንድንወድ ነው። ወንድሙን የሚጠላ ነፍሰ ገዳይ ነው፣ ነፍሰ ገዳይ ደግሞ መንግሥተ ሰማያት አይገባም።

ኢትዮጵያ አገራችን የብዙ ብሔር ብሔረሰቦች አገር ናት፡፡ ብሔር ደግሞ የራሱ የሆነ ቋንቋና ባህል፣በጂኦግራፊ ተለይቶ የሚታወቅ፣በኢኮኖሚ የተሳሰረ፣ባባህሉ የሚገልጽ ስነሊቦና ዘይቤ ያዳበረ የጸናና የረጋ ማኅበረሰብ  ነው። ስለዚህ ብሔር ከካፒታሊዝም  እድገት ጋር፣በመገናኛ አውታሮች መዝርጋት የተነሳ ፣በሂደት የሚከስት የኅብረተሰብ የእድገት ደረጃ ነው።

ከዚህ የወል የብሔር መለኪያ አንጻር ካየን ፣ ግለሰቦች በአንድ አካባቢ ተሰባስበው ስለኖሩ፣ወይም አንድ ቋንቋ ስለ ተናገሩ ብቻ ብሔር ሊሆኑ አይችሉም።ሁሉንም መለኪያዎች ማሟላት አለባቸው። ስለሆነም  ትግራይ፣አማራ፣ኦሮሞ፣ሱማሌ፣ አፋር፣ ሲዳማ፣ ወለይታ፣ ሐዲያና የመሳሰሉት፣የብዙ ጎሳዎችና ነገዶች ውሁድ ሁነው አንደበታቸውን የፈቱበት የጋራ ቋንቋ አሉዋቸው፣፣በኢኮኖሚ የተሳሰሩና በወሰን ተለይቶ የሚታወቅ የጋራ የመኖሩበት አካባቢ አላቸው።  በተጨማሪም በባህላቸው የሚታይ ሥነሊቡናዊ ዘይቤ ያዳበሩ፣ ጽንተውና ረግተው የኖሩ ብሔሮች ናቸውና፣የፌድራል መንግሥቱ አካል ሁነው፣በብሔራዊ ክልላቸው ያለማንም ጣልቃ ገብነት፣ ራስን በራስ የማስተዳደር ዴሞክራሲያዊ መብታቸው ሊከበርላቸው ይገባል።

ተጨማሪ ያንብቡ:  በማኅበረ ቅዱሳን ጉዳይ፤ የሲኖዶስ ጉባኤ በፓትርያርኩና ጳጳሳቱ ፍጥጫ ተቋጨ - (አዲስ አድማስ ጋዜጣ)

እነዚህ ብሔሮች ደግሞ አብረዋቸው  ለሚኖሩ ነገዶች፣ አናሳ ጎሳዎችና ገለሰቦች ትኩረት በመስጠት፣  መብታቸውን አክብረው ሊያስከብሩላቸው ይጋባል። ምክንያትም እነዚህ አናሳ  ነገዶች፣  ሥርዓት ዘርግተው፣ መከላከያ አደራጅተው መንግስት መስረተው ራስን በራስ ለማስተዳደር አይችሉምና ነው።

ይህ መብት ደግሞ  በተባበሩት መንግሥታት ቻርተር  የተደነገገ፣በአባል አገሮች ፊርማ የጸደቀ፣  በዙዎቹ   አገሮች፣ ከባዕዳን የቅኝ አገዛዝ ነጻ የወጡበት አነቀጽ ነው።    አገራችንም ይህን ድንጋጌ ፈርማ የተቀበለች ስትሆን፣ በመብቱ አከባበር ረገድ ብዙ ጉድለቶች አሉባት፡፡በመሆኑም ነው  በወሰን ግጭትና የዜጎች መፈነቃቀል በመታመስ ላይ የምትገኘው።

ብሔር ብሔረሰቦች መብታቸው ተከብሮ ሁሉም በአካባቢው ራሱን በቋንቋው ቢያስተዳድር፣ከክልላቸው ውጭ የሚኖሩ ዜጎችም መብት በተከበረ ነበር።ትምክህት ጭቆና አፈና፣ ንቀት ባለበት ኅብረተሰብ ውስጥ  ሰላም ሊኖር አይችልም።አመጽ አመጽን፣ በቀልም በቀልን እየወለደ  ችግር ያስከትላልና።

ከዚህ አንጻር ሕዝባችን ከሦስት የፖለቲካና የብሔር አቋዋም ተከፍሎ ይገኛል። ከእነዚህም   የመጀመሪያው፣ በወታደራዊ መንግሥት የተወረሰባቸውን  ርስት ለማስመልሰ የተደራጁ፣  ከኢሕአዴግ ጋርም  ለሃያ ሰባት አመታት የተፈለሙ፣አሁንም በፌድራል መንግሥቱ የበላይነቱን በመጨበጥ፣ ዓላማቸውን ከግብ ለማድረስ የሚታገሉ፣ የነፍጠኛ ሥርዓት ናፋቂዎች ስብስብ ነው።

ሁለተኛው  የብሔርና የአቢዮታዊ ዲሞክራሲ የፖለቲካ አቋዋም አራማጅ የኢሕአዴግ ግምባር  የነበረው ነው።ይህ ግምባር በመጀመሪያ ብሔር ብሔረሰቦችን ከወታደራዊ ደርግ  ጭፍጨፋና ጭቆና ነጻ ለማውጣት የተመሰረተ፣የመንግሥት ሥልጣን ጨብጦ አገሪቱን ለሃያ ሰባት አመት የገዛ፣በዚህም  ጊዜ  ለአገሪቱ ብዙ መልካም ተግባሮችን የፈጸም፣በአነጻሩም ተቃዋሚዎችን ሁሉ በእስር ያማቀቀ፣ቄሮዎችን የጨፈጨፈ፣በመጨረሻም በአገሪቱና በሕዝቡ ላይ በፈጸመው ጥፋትና የአስተዳደር በደል፣ በሕዝብ ቁጣ ተፍረክርኮ ለሁለት የተከፈለና፣አሁን ለሥልጣን እርስ በርስ በመዋጋት ላይ የሚገኝ ነው።

ሦስተኛው፣የፌድራሊስት ጎራ ነው።ይህ ጎራ የአሐዳዊ መንግሥት ተቃዋሚ፣ የሕወሐትንም አቢዮታዊ ዲሞክራሲ የሚጠላ፣የሕወሐት አገዛዙም እንዳይመለስበት የሚታገል፣ለብሔር ብሔረሰቦች መብት የተነሳ  ከብልጽግና  ፓርቲ ጋርም ከቅራኔ ውስጥ የገባ ነው።

ተጨማሪ ያንብቡ:  አንድነት በአዳማ የጠራው ሰልፍ በሰላም ተጠናቀቀ

እንግዲህ አገራችን  በእነዚህ  ቅራኔዎች ታጭቃ የታፈነች በመሆኗ ነው፣ጦርነት፣  የእርስ በርስ ግጭት እና መፈነቃቀል  በዝቶ፣ የብልጽግና ፓርቲን ሚዛን ያሳጣው፡፡ ስለዚህም ነው፣ ሕገ መንግሥትን የሚያከብርና የሚያስከብር የታጣው። የፌድራል መንግሥቱ በክልሎች ሥልጣን ውስጥ፣ ክልሎች ደግሞ በፌድራል መንግሥቱ ሥልጣን ውስጥ ጠልቃ በመግባት፣ ጦርነት በማወጅ፣የመከላከያ ሠራዊቱን አስገድደው በጦርነት በማሰለፍ ችግር እየፈጠሩ ያሉት፡፡ይህ ሥርዓተ አልባኝነት በፍጥነት ካልተገታ፣ ወደ ፋሺሽታዊ የእርስ በርስ ጭፍጨፋ ውስጥ መግባታችን አይቀሬ ነውና፣ አገርን ከጥፋት፣ሕዝብን ከእልቂት ለመታደግ፣የሽምግልናው ወቅት ዛሬ ነው።

ስለሆነም አገራችንን ከጦርነት፣ ሕዝባችንን ከመፈነቃቀል ለመታደግ፣ከሁሉ በፊት  የፌድራል ሕገ መንግሥትን፣ለሁሉም አመቺ በሆነ መልኩ ማሻሻል ያስፈልጋል።ይኸውም የብሔራዊ ክልሎችን ራስን በራስ የማስተዳደር መብት ሳይነካ፣ግለሰቦችም የትም ሄደው  በነፃነትና በእኩልነት ሠርተው የመኖር መብታቸውን የሚያስከብር መሆን አለበት፡፡ በተጨማሪም የፌደራል ሕገ መንግሥቱ፣  በፌድራል ተግባርና ሥልጣን ላይ የሚያተኩር ሁኖ የክልሎችንም  ሕገ መንግሥት የሚያስከብር፣   የመንግሥትና የፓርቲ ሥልጣንና ተግባር በግልጽ የሚለይ፣የሕግ የበላይነትንና  የፍትሕ አካላትን ነጻነት የሚያረጋግጥ፣ከሁሉም በላይ የመንግሥት ሥልጣንን ለሕዝብ የሚመልስ፣ፕሬዚዳንታዊ ቅርጸ መንግሥት  ለመመሥረት የሚያስችል ሊሆን ይገባዋል።ይህ ቢሆን፣መንግሥት የመራጩን ሕዝብ መብት ለማክበር ይገደዳል።ፓርቲዎች የመንግሥት ሥልጣንን ለመያዝ በሕዝብ የደጋፍ ደምጽ እንዲመኩ ያደርጋል።

በዚህ መልኩ የሕዝባችን ጥያቄዎች ከተፈቱና  የመንግሥት ሥልጣን ለባለ መብቱ ሕዝብ ከተመለሰ፤ ከሕዝባችን መካከል ጥላቻ ይወጋዳል።መፈነቃቀሉ ያከትማል። መንግሥትም በሕዝቡ ላይ ፈላጭ ቈራጭ መሆኑ ይቀራል።ኢንቬስተሮችም ከአቢዮታዊ ዲሞክራሲ ፍራቻና ሥጋት በማላቀቅ፣  የውጭ መዋዕለ ነዋይ በመሳብ፤አገራችንን ከኋላ ቀርነትና፣ሕዝባችንን ከሥራ አጥነት የሚያድን ይሆናል።

እንግዲህ  ይህ ያለመድሎ ፤ የሁሉንም ብሔር ብሔረሰብና ግለሰብ መብት በእኩልነት  ለማስከብር  የታቀደ በመሆኑ፣ለአገሩ ሰላምን  የሚሻ ሁሉ፣የክፋት ሁሉ ምንጭ ሰይጣን መሆኑን ተገንዝቦ፣ለፈጣሪ አምላኩ ፈቃድ በመታዘዝ፣ጦርነቱን በማውገዝ፣ ቂም  በቀሉን ለፈጥሪ  አምላኩ በመተው፣አገርን ከውድቀት ትውልዱን ከእልቂት ለማዳን  በንጹህ ልብ  ሊተባበር ይገባል።

ተጨማሪ ያንብቡ:  "የፀጥታ ስጋት ካለብን መንገድ እንዘጋለን" ሽመልስ አብዲሳ | "የታቀደ ፖለቲካ አሻጥር ነው" ዶ/ር ይልቃል ከፍለ | ሰበር መረጃዎች!

ይህ ከሆነ ፈጣሪ አምላካችን ይደሰታል፣የመቃብር ደጆች ይዘጋሉ፣ተምች፣ ኩብኩባና በሽታው ይጠፋል፣ኢትዮጵያም ማቋን አውልቃ፣ በልጆቿ አንድነት አብባ አምራና ደምቃ  ለዘላለም ትኖራለች።

የሰላም መልዕክተኛ የሆነ፣ እናት አገሩን  የሚወድ ሁሉ፣ ይህን መልዕክት ላልሰማ ያሰማ

ሽማግሌው ነኝ ከሁስተን ቴክሳስ

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Share