July 2, 2021
22 mins read

ከብሔራዊ ደህንነት ምክር ቤት በወቅታዊ ሀገራዊና ቀጠናዊ፣ የደህንነትና ፀጥታ ጉዳዮች ላይ የተሰጠ መግለጫ

Security Council meeting 2የተከበራችሁ የሀገራችን ሕዝቦች፣

  • ከሦስት ዓመታት በፊት ወደ ለውጥ ጎዳና ገባን። በለውጡ ጎዳና ላይ ብዙ የተወሳሰቡ ችግሮች እንዳሉ ተገንዝበን የጀመርነው ለውጥ ነው።
  • የተወሳሰቡ ሀገራዊና ቀጠናዊ ችግሮች በጥቂት ዓመታት የሚጠፉም አይደሉም።እነዚህ ችግሮችን በሚገባ በማወቅም የሚከፈለውን መስዋእትነት ለመክፈል ቆርጠን ነው የተነሳነው።
  • ሀገራችን ውስጥ ያሉት ችግሮች እንደምድር አሸዋ የበዙ ናቸው።ችግሮቹ እንደ አሸዋ ቢበዙም ከዜጎቿ አቅም በላይ እንደማይሆን ፅኑ ዕምነት ይዘን ነው ለለውጡ የተነሳነው።
  • ችግሮቹ የሚፈቱት ተነጣጥለን ሳይሆን በአንድነትና በትብብር መሆኑን ትግሉን ገና ስንጀምር ለውድ ወገኖቻችን አስታውቀናል። ትግሉን ስንጀምር ያለ ብዙ ፈተና በአንዲት ጀንበር የተለወጠች ኢትይጵያ ትኖራለች ብለው የጠበቁ ሰዎች ነበሩ።ለውጡም ከአንድ አቅጣጫ ይመጣል ብለውም እንደታዛቢ ዳር ቆመው የሚመለከቱም ነበሩ።
  • ለውጡን በጀመርንብት ወቅት ሁሉም ሰው ከፍ ባለ ሞራልና ደስታ ተሞልቶ ነበር፤በዚሁም ሞራልና ደስታ እስከ መጨረሻው ይዘልቃል የሚል እምነት ነበር ማለትም ምኞት ነው።
  • በትግሉ ውስጥ ውጣ ውረዶቹ ፈታኝ በሚሆኑበት ወቅት የሞራልና ደስታ ስሜቶች በየጊዜው እየከሰኑ እንደሚሄዱ ግንዛቤ ነበረን።
  • በለውጡ ጎዳና ላይ የሚገጥሙ እሾህና ጋሬጣዎች ሳያቆስሉን፣ እባብና ጊንጦች ሳይነድፉን፣ የበረሃ ሀሩርና ቃጠሎዎች ሳይለበልቡን የምናለማትን የበለጸገች ሀገር መገንባት አይቻልም።ቢቻልማ ኖሮ ገና ድሮ ባደረግነው ነበር። በረሃውን ሳናቛርጥ፣ባህሩን ሳንሻገር የትግል ጉዞውን ማጠናቀቅ ይቻላል ብሎ ማሰብ ሞኝነት ከመሆኑም ባሻገር ሁኔታን ካለመገንዘብ የሚመጣ ነው። የተዘረጋውን ፈተና በቅድሚያ ባለማየትም እራሳቸውን የሚያስጨንቁት በሌላ አካል ላይ ሳይሆን በራሳቸው የተሳሳተ ግምታቸው መሆኑን ሊገነዘቡ ይገባቸዋል።
  • ተስፋ የሚሰጥ ሂደታችን እየተቃረበ በመጣ ቁጥርም ፈታኝ የሆኑ ችግሮች እየበረቱ የሚመጡ መሆኑን መረዳት ይኖርብናል።
  • በሀገራችን ኢትዮጵያ በተለያዩ ጊዜያት ያየናቸው ግጭቶች፣የሰላም ማጣትና የደህንነት ስጋቶች በለውጥ ጉዟችን እጅግ ፈታኝ ሁኔታዎች ጋራ የሚመደቡ ናቸው።
  • የትግል መንገድ ያሰጀመረንን አንድነት ሊደቁሱ፣እጅ ለእጅ ያስተሳሰረንን ገመድ ሊበጥሱ፣የጋራ ቤታችንን ሊደረምሱ የሚቋምጡ ብርቱ ፈተናዎችን የትግሉን ጉዞ ከመጀመራችን በፊትም ነበሩ፣ አሁንም አሉ።
  • የለውጥ ትግል መንገዳችን ላይ ልዩ ልዩ ጋሬጣዎች እየጣሉ ከለውጥ ትግል ጉዟችን ሊያስቀሩን የሚሹ አካላት ብዙ ናቸው።ፍላጎታቸውን በአግባቡ ተረድተን በጥንቃቄና በጥበብ ወደ ዓለምነው ግባችን መጓዛችንን እንደማናቆም ልናሳያቸው ይገባል።ካላሳየናቸው ደግሞ በቀሩ ምዕራፎቻችንም ላይ ተከትለውን ይመጣሉ።
  • የጠላቶቻችን ፍላጎት በጉዟችን ውስጥ ወድቀን ግባችንን ሳናሳካ እንድንቀር ነው።በጋራ ቆመን ያጸናነው ቤታችን ፈራርሶ ወደ ትቢያነት ሲቀየር ማየት ይሻሉ።እኛ ደግሞ ለዚያ ምኞታቸው የተመቸን ሆነንላቸዋል።
  • አንድ ቤት በሦስት ምክንያቶች ሊፈርስ ይችላል፤ አንደኛበግንባታ ወቅት በገጠሙት ችግሮች፣ ሁለተኛከውስጥ ባሉ ሰዎች፣ ሦስተኛከውጭ በሚመጡ ሃይሎች
  • እነዚህ ሦስቱ አውቀውም ይሁን ሳያውቁ የሚተባበሩበት ጊዜ አለ። አንዳንድ ጊዜ በዓላማ፣አንዳንድ ጊዜ በሂደት፣አንዳንድ ጊዜም በውጤት ይተባበራሉ።
  • ከውስጥ ያሉት ሰዎች በውስጥ ጉዳያቸው ሲጣሉ፣ከውጭ ያሉ ሀይሎች ቤትን አፍርሰው ቤቱ የተገባበት ቦታ ወይም በቤቱ ውስጥ ያለውን ሀብት መዝረፍ ሲፈልጉ ቤቱ እንዲፈርስ ተባብረው ሊሰሩ ይችላሉ። ቤቱ ሲገነባ ያጋጠሙት ችግሮች ደግሞ “በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ” ዓይነት ይሆናል።

የተከበራችሁ ኢትዮጵያውያን፣

  • ሁላችንም ልንገነዘበው የሚገባን ሃቅ አለ።ሀገራችን የጋራ ቤታችን ናት።የሁላችንም ቤቶች በዚያች ትልቅ ቤት ውስጥ የሚገኙ የቤቱ ክፍሎች ናቸው።በየክፍሎቻችን ተወሽቀን ያለነው ሁላችንም የጋር ቤታችንን አንጸን በማቆየት ላይ ተመሳሳይ አቅምና ኣቋም የለንም።ቤትን ከውጭ የሚመጣ ሃይል ብቻውን አያፈርሰውም፣የውስጦቹ ካልተባበሩት በስተቀር።
  • የቤቱ ሰዎች ለውጭ አፍራሾች በሦስት መንገዶች አውቀውም ሆነ ሳያውቁ ይተባብሯቸዋል። እነሱም፣ ሀ) ሆን ብለው ለ)ሞኝ ሆነው ሐ)ተኝተው ነው።
  • ከሚፈርስ ቤት እንጠቀማለን የሚሉ ሞኝ የቤት ሰዎች አሉ።ከመሥራትና ከመድከም ዋጋ ማግኘት የሚከብዳቸው የቤቱን ፍርስራሽ ሽጠው ማትረፍ የሚፈልጉ የፍርስራሽ ጌቶች አሉ።እነዚህ ሆን ብለው ቤቱ እንዲፈርስ ይፈልጋሉ።ቤቱ ቶሎ ፈርሶላቸው ፍርስራሹን ለመቸብቸብ ስለሚቸኩሉ ከውጭ ሆነው ቤቱን ከሚነቀንቁት ጋር ተባብረው ያፈርሳሉ።
  • ሌሎቹ ደግሞ በምግቡም፣በልብሱም፣በሳሎን ውስጥና በመኝታ ቤቱም የሚፈጠርባቸውን ቅሬታ የቤት ማፍረሻ ምክንያት የሚያደርጉ የዋሆች ባለቤቶች ናቸው።
  • የላሞች ፀብ በረቱን ለተኩላ፣የውሾች ፀብ መንደሩን ለጅብ ይሰጠዋል እንደሚባለው እነዚህ የቤት ልጆች ከውጭ ያሰፈሰፈውን ጠላት ባለማወቅ የሚያደርጉት ፀብ ከተራ እሰጣገባ አልፎ ሳያስቡት ቤቱን ያፈርሰዋል። ቤት አንዴ ከፈረሰ በኋላ ለውስጦቹ ትርፋቸው ቁጭት ይሆናል።ከመሆኑ በፊት እንጂ ነገሮች ከተበለሻሹ በኋላ መጸጸትና መቆጨቱ ምንም ትርጉም የለውም።
  • እንደገና ሌሎቹ ወይም ሦስተኞቹ ደግሞ ተኝተው ቤት የሚያፈርሱ ናቸው።የቆሸሸውን ማጽዳት፣የተሰነጠቀውን መጠገን፣የጎደለውን ማሟላት፣የጠመመውን ማቃናት ሲገባቸው እእ ምን አገባኝ ብለው ይተኛሉ፤ ችላም ይላሉ።አጥሩ ሲፈርስ፣ሳሎኑ ሲፈርስ፣ መኝታ ቤት እስኪፈርስ ይጠብቃሉ።መኝታ ቤት ሲፈርስ ጓዳ ተደብቀው በመተኛታቸው የሚተርፉ ይመስላቸዋል።ሁሉም ግን የጊዜ ጉዳይ ይሆናል።
  • ዛሬ ታልቋ ቤታችን ኢትዮጵያ በዚህ ሁኔታ ላይ ናት።ሦስቱም አይነት ልጆች አሏት። ከውጭ ጠላት ጋር ይሁነኝ ብለው በዓላማ ለማፍረስ የሚሠሩ በዓላማ ባይገጥሙም በውጤት ከውጭ አፍራሽ ጋር የሚሠሩ፣ቤታቸው ሲቃጠል እያዩ ከመንቃት ይልቅ በሙቀቱ ተከናንበው የተኙ።
  • ይህ ወቅት ለኢትዮጵያ ከወሳኝ ወቅቶች ውስጥ አንዱ ነው።በአንድ በኩል ፍትሓዊ ዲሞክራሲያዊና ተአማኒ ምርጫ አድርገን በሕዝብ ድምጽ የሚጸና መንግሥት ለመመሥረት ሂደት ላይ ነን።
  • በሌላ በኩል ደግሞ የሀገርችንን ከፍታነት አንዱ ማሳያ የሆነውን የሕዳሴ ግድብ ሁለተኛውን ዙር ሙሊት ለማከናወን እየተጋን ነው። ከእነዚህ ጎን ለጎን ግሥጋሴ ከሚያሰጋቸው የውጭና የውስጥ ጠላቶች ጋር በየአቅጣጫው ግንባር ለግንባር ገጥመናል።
  • ኢትዮጵያ እነዚህን ሦስት ፈተናዎች (ዲሞክሪያሲያዊ ምርጫ ማድረግ፣ሕዳሴ ግድቡን ማጠናቀቅና ከውስጥና ከውጭ ጠላቶች ጋር ፍልሚያ) አልፋ ግቦቿን ካሳካች በኋላ ለማንም በቀላሉ እጅ የማትሰጥ የሁላችን መመኪያ ሆና ትወጣለች።
  • ይህ እንዳይሳካ ከምንጩ እናደፍርሰው፣ከአንገታቸው እንሰቅስቀው፣በእሸትነቱ እናጠውልገው የሚሉ የማሰናከያ ድንጋዮች በየአቅጣጫው ተንሥተዋል። ወሳኙ የእነርሱ መነሳት አይደለም፤ የኛ ምላሽ እንጂ።

ውድ የሀገራችን ሕዝቦች፣

  • ከለውጡ ጅማሬ አንስቶ የገዛ ዛፋችንን ከዛፉ በተቆረጠ ጠማማ እንጨት የመቁረጥ አዝማሚያ መኖሩን እየተናገርንም እየታገልንም ነበር።በተለያዩ አቅጣጫዎች የሚወረወሩት ድንጋዮች በቤታችን ላይ የሚያደርሱትን አደጋዎች ለመግታት የፖለቲካ አመራሩና የጽጥታ አካላት መስውእትነት የከፈሉበት ትግል ተካሂዷል።
  • ከጁንታው ጋር የተደረገው ትግል የዚህ አንዱ ማሳያ ነው።የጁንታው አካላት ዛሬም አልጠፉም።የተለያዩ ብሔሮችና ስሞች ይዘው፣ሲመች በሠላም ሳይመች በጠመንጃ የላኪዎቻቸውን ዓላማ ለማሳካት እየሠሩ ነው።
  • የጁንታውን ተልእኮ ያልተረዱ የዋሖች ደግሞ ሀገር እንድትፈርስ ባይፈልጉም ሀገር እንድትፈርስ ግን እየሠሩ ነው።
  • የቤቱ ጥያቄ የሚመለሰው መጀመሪያ ቤቱ ሲኖር ምሆኑን ዘንግተውታል።ቤት እያፈረሱ ስለ ቤት መወያየት ይፈልጋሉ።ላሟ ወተት እንዳላት የሚነሳው ጥያቄ የሚመለሰው ላሟ ስትኖር መሆኑንም ረስተውታል።ከየዋሕነትና ከልጅነት ጨዋታ ያላነሰ ቸልተኝነት ጋር ተደምረው ደግሞ “ምን አገባኝ” የሚሉ ዜጎችም አሉ።ምድር ቤቱ ሲቃጠል እሳቱ ሰባተኛ ፎቅ ላይ የሚደርስ የማይመስላቸው ወይ ለመገንባት ወይም ለመመከት አንዳች ነገር የማያደርጉ እሳቱን ከመከላከል ይልቅ በሙቀቱ ተመቻችተው ያንቀላፉ ጭምር የሀገርችን ችግሮች ናችው።
  • አሁን በአለንበት ጊዜ ሦስት ወሳኝ ዓላማዎቻችንን በጽናት ማሳካት ይኖርብናል፤

መጀመሪያአንድ ወር ያህል ጊዜ የቀረውን ምርጫ ውጤታማ እናድርገው፣በነቂስ ወጥተን ካርድ እንውሰድ።ሁላችንም ይበጀናል ያልነውን እንመረጥ።የፈለግነውን እንዳንመርጥ እንቅፋት የሚሆንብን የትኛውም አካል እርሱ የኢትዮጵያ ጠላት ነው።የሚያጋጥሙ ፈተናዎችን እየተቋቋምን፣ችግሮችን እያረምን፣ጉድለቶችን እየሞላን ምርጫውን ውጤታም እናድርገው።ይሄንን ምርጫ በድል ተወጣነው የምንለው ሂደቱ የሚጠበቅበትን ደረጃ ለማለፍ ከቻለ ብቻ ነው።ለዚህ ደግሞ መራጩ ሕዝብ፣ተመራጮችና የምርጫ ቦርድ ሀገራዊ ኃላፊነታቸሁን እንድትወጡ አደራ እንላለን።

ሁለተኛከምርጫው ጎን ለጎን ግድባችንን ባቀድነው ጊዜ መገንባትና ሁለተኛውን ዙር የውኃ ሙሌት ማከናወን አለብን።የትኛውንም አይነት ጫና ተቋቁመን፣የውስጥና የውጭ ፈተናዎቻችንን አልፈን እንሞላዋለን።ኢትዮጵያን መውደዳችንን የምናሳየው የኢትዮጵያን ጉዞ በማቀላጠፍ እንጂ በማደናቀፍ አይደለም።በእሳት ላንቃ ውስጥ እያለፍንም ቢሆን ማድረግ ያለብንን ማድረግ አለብን።በያዝነው የጊዜ ሰሌዳ መሠረት ግድባችንንን ሞልተን ኃይል ማምረት እንጀምራለን።

ሦስተኛበየአቅጣጫው የምናየው የወገናችን አሰቃቂ ግድያ፣ማፈናቀል፣ቤትና ንብረት ማውደም፣ነውጥና ሸፍጥ ሁሉ በሀገር ውስጥ ብቻ የተመረተ አይደለም።አብዛኛው ጥፋት በውጭ ተመርቶ በሀገር ውስጥ የሚገጣጠም ጥፋት ነው።ግጭቱንና ጥፋቱን ከውጭ አስመጥተው በሀገር ውስጥ የሚገጣጥሙት የእፉኝት ልጆች ናቸው።በዚህ ዓመት መጀመሪያ የእፉኞችን ዋና መፈልፈያ አፍርሰነዋል።ከዚህ በፊት ፈልፍሎ እዚህና እዚያ የጣላችው ግልገሎች ግን አሁንም ይቀራሉ።የትኛውም አይነት የብሔርና የእምነት ስም ቢይዙ ከየትኛውም የውጭ ኃይል የሚረዱትን ገንዘብና መሣሪያ ቢጨብጡ ኢትዮጵያን ይፈትኗት ይሆናል እንጂ አያሸንፏትም።

  • በመጀመሪያ በውስጣችን ያሉ ባለ ሁለት ባላዎችን እናጸዳለን።ቀን ቀን ለኢትዮጵያ የሚሠሩ የሚመስሉ፤ ሌሊት ሌሊት በኢትዮጵያ ላይ የሚዶልቱ አሉ።
  • እነርሱ ከውጭ ጠላቶቻችን በላይ ዋኖቹ ጠላቶቻችን ናቸው።አጥር ላይ ተቀምጠው አሸናፊውን አይተው ከተመቻቸው ሊገቡ፣ካልተመቻቸው ሊሸሹ የሚያስቡ መኖራቸውን አውቀናል።ወቅቱ የምርጫ ጊዜ ነውና መምረጥ አለብን።ወይ እነርሱን እናፀዳለን ወይ ኢትዮጵያን አሳልፈን እንሰጣለን።
  • የኛ ምርጫ ኢትዮጵያን ለእነርሱ ስንል መሠዋት ሳይሆን እነርሱን ለኢትዮጵያ ስንል መሠዋት ነው።በአጠቃላይ ምርጫውን ሰላማዊ፣ዲሞክራሲያዊና ፍትሐዊ ለማድረግ፣ግድባችንን በታቀደለት መንገድ ገንብተን ሁለተኛውን ዙር የውኃ ሙሌት ለማከናወን፣ እንዲሁም ኢትዮጵያን ከውስጥና ከውጭ ጠላቶቿ ታድገን ወደሚገባት ደርጃ ለመውሰድ እንድንችል የኢትዮጵያ ሕዝብ በንቃትና በብስለት ከመንግሥት ጎን እንዲቆም ጥሪ እናደርጋለን።
  • ቆም ብለን እናስብ፤ ከሁሉም በፊት ኢትዮጵያን እናስቀድም።በፌደራልና በክልል የምትገኙ የጸጥታ አካላት ተቀናጅታችሁና ተናብባችሁ በመሥራት የኢትዮጵያንና የኢትዮጵያውያንን ሰላምና ድኅንነት እንድታስጠብቁ እናሳስባለን።
  • የሚደረጉ ማናቸውም የፖለቲካና የመብት እንቅስቃሴዎች ይደገፋሉ።የትግላችን ውጤቶች ናቸውና።እነዚህ የመብትና የፖለቲካ እንቅስቃሴዎች ግን ኢትዮጵያን እንዲያንውጥ አንፈቅድም።
  • ፖለቲካዊ ጨዋታዎችን ከጨዋታ ሜዳ ውጭ ለማድረግ ለሚፈልጉት ኃይሎች ትዕግስታችን ማለቁን በዚሁ አጋጣሚ ልንነግራቸው እንፈልጋለን።ሁሌም እንደምንለው በጽናትም እንደምናምንበት ለኢትዮጵያ ፈተና ብርቋ፣ድል ማድረግም ሰበር ዜናዋ አይደለም።ከነዚህ በላይ አልፋም ዛሬ ላይ ደርሳለች።ይህንን አልፋም ነገ ላይ ትገኛለች።
  • ኢትዮጵያ ማሸነፏ ላይቀር እንዳታሸንፍ ሲታገሉ የኖሩትን ትታዝባቸዋለች፤በታሪክ ሂደትም ትቀጣቸዋለች።እርሷ ግን ወጥመዱን በጣጥሳ፣ሰንኮፏን ነቃቅላ፣አዚሙን አስወግዳ ያሰበችበት ትደርሳለች።
  • ኢትዮጵያ እስካሁን የቆየችው ወደፊትም የምትቆየውም በእኛ በመስዕዋት ልጆቿ ደምና አጥንት ነው።ዛሬ እኛ የምንከፍለው ዋጋ፣ነገና ከነገ ወዲያ ሀገራችን ወደማይቀለበስ የብልጽግና ከፍታ ላይ እንደሚያደርሳት ምንም ጥርጥር የለውም።

የብሄራዊ ደህንነት ምክር ቤት

ሚያዚያ 162013 .

አዲስ አበባ

ከፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን (ኤፍ ቢ ሲ)፤ሚያዚያ 162013፡ የተወሰደና ለማንበብ እንዲቀል የተዘጋጀ (በ ጥበቡ ሞላ)

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Go toTop