” እሥቲ ተጠየቁ !?” መኮንን ሻውል ወልደጊዮርጊስ

እናንተ ከጥበብ የራቃችሁ
እስቲ ልጠይቃችሁ ?
እስቲ ተጠየቁ…

ሥለ ሀገር የማታውቁ ።
እስቲ ተጠየቁ …

እናንተም ጠፍታችሁ
ሀገር ያጠፋችሁ ።
ድፍን ኢትዮጵያ…
” ቋንቋ” ነው ያላችሁ።

በዝታችኋል አሉ
ቋንቋዬ ይንገሥ የምትሉ።

በቋንቋ አጥር
ያላችሁ ግትርትር።

ቋንቋዬ እያላችሁ
በቋንቋ የተቦደናችሁ።
በአንደበት ማሌያችሁ
ሰውን ከሰው ለያይታችሁ
የፈጣሪን ምድር የተቀራመታችሁ።
ሀገርን ያህል ነገር በእጅ ጠፍጥፋችሁ
ልክ እንደሸክላ ዕቃ እናንተ እንደሰራችሁ
በጣም ያሥገርማል መመፃደቃችሁ።
…………………………………………………..
ጥጃ የምታሥሩበት” ምድር ” የማን መሰላችሁ?
እናንተ ራቁቶች አትሳቱ እባካችሁ።
ዛሬ ያበቃ ፣ በቋንቋ መቀላመዳችሁ ፡፡
እስከመቼ ዜጋን ይጨርስ የእናንተ ጦሳችሁ ?
እስቲ ተጠየቁ ?
እውነትን የማታውቁ ፡፡
እሥቲ ልጠይቃችሁ ?
የሀገር ትርጉሙ ” ቋንቋ ነው።” ያለችሁ።
እናንተ ከጥበብ የራቃችሁ
እስቲ ልጠይቃችሁ ?
እስቲ ተጠየቅ…
እስቲ ተጠየቂ…
ሥለ ሀገር የማታቅ ፡፡
ስለሀገር የማታውቂ ፡፡
ቋንቋን አምልካችሁ
ሀገርን ክዳችሁ
ታሪኳንና ቅርሷን በማውደም
ኢትዮጵያዊነትን ለመደምደም…
ያልፈጠራችሁትን መሬት
የሰውን ሁሉ እናት
በቋንቋ ከፋፍላችሁ
ሰውን ከሰው አበላልጣችሁ
እናቱን የእጀራናት አደርጋችሁ
እንደሁለተኛ ዜጋ የቆጠራችሁ ፡፤
እስቲ ተጠየቁ ?
ሰው መሆናችሁን የማታውቁ ፡፡
እናንተ ከጥበብ የራቃችሁ
የቋንቋን ሀገርነት ያላወቃችሁ ፡፤
እስቲ ተጠየቁ ?
እውነትን የማታውቁ ፡፡
ቋንቋ ነው እኮ አገር
ሰውን የትም የሚያኖር ፤
የትም ማንንም የሚያግባባ
አዋዶና አፈቃቅዶ ጡት የሚያጠባ ፡፡
እሰቲ ተጠየቁ ?
እስቲ ልጠይቃችሁ
እናንተ ከጥበብ የራቃችሁ ፡፡
የሀገር ዳርድንበር
የኢትዮጵያዊነት ሉአላዊ ምድር
በመሰወትነት አጥር መታጠሩን
የሚሊዮኖችን ህይወት ማስገበሩን
በዚች አገር ሰዎች ደም መታፈሩን
በትላንቶቹ አባቶቻችሁ ዳር ድንበሩ ፣ መከበሩን
ይህንን ፈፅሞ የዘነጋችሁ
ከጥበብ ርቃችሁ
እስቲ ልጠይቃችሁ ?
እስቲ ተጠየቁ ?
እውነትን የማታውቁ ፡፡
መላው እናት ምድር
ከምስራቅ እስከምእራብ
ከሰሜን እስከ ደቡብ…
ያላንዳች ሃይ ባይ የምንቧርቅበት
አገር ማለት አይደል ፣ አጥር የሌለበት ?
የነገድ አፆለሌ የማይሰማበት ?
በቋንቋ ተለያይቶ የማይናቆሩበት ?
ግና አገር ከተከለለ
በክልል ከታጠረ
ምኑን አገር ሆነ ??
ትላንት በአድዋ ላይ አጥንቱን የከሰከሰው
ትላንት ከቀይ ባህር ጋራ ደሙን የቀላቀለው
ትላንት መተማ ላይ ፣ አንገቱ የተቀላው ፡፡
ትላንት በካራማራ በጭንአክሰን
በኡጋዴን ደሙን ያፈሰሰው ፡፡
ያለስስት ለእናት አገሩ የተሰዋው
በአለም ፊት እንድንከበር ያደረገው
አይደል ፤ የዚች አገር የትላንት ሰው ?
ከኢትዮጵያ ማህፀን የተገኘው ?
ይህንን እውነት እንዴት ረሳነው ?
እስቲ ተጠየቁ ?
እውነትን የማታውቁ ፡፡
መላው እናት ምድር …
ከምሥራቅ እሥከ ምዕራብ
ከሰሜን እሥከ ደቡብ
ያለአንዳች ከልካይ የምንቧርቅበት
አደለ አገር ማለት ?
አጥር የሌለበት ?
ግና፣ ከተከለለ ፤ በክልል አጥር…
ምኑን ሀገር ሆነው ???
ትላንት በአደዋ ላይ ፣ አጥንቱን የከሰከሰው…
ትላንት ዶጋሊ ላይ ፣ ደሙን ያፈሰሰው…
ትላንት ከቀይ ባህር ደሙን የቀላቀለው…
ትላንት መተማ ላይ፣አንገቱን የተቀላው…
ትላንት በካራማራ፣በጭናክሰን….
በኦጋዴን ደሙን ያፈሰሰው ፡፡
ያ ዋጋ የማይተመንለት፣” ለኢትዮጵያ ” የተሰዋው
የታፈረች ና የተከበረች ሀገር አለን እንድንል ያደረገው ፡፡
ለሀገሩ ግንባሩን ለጥይት ለመሥጠት ያልሳሳውን ጀግና
የአደዋ ባለታሪኩን፣ ታላቅ ድሉን ለምን እናደርገዋለን መና ?
……………………………..
እናም እናንተ ከጥበብ የራቃችሁ
እስቲ ተጠየቅ…
እስቲ ተጠየቂ…
እስቲ ልጠይቃችሁ ???
እስቲ ተጠየቁ ?
እውነትን የማታውቁ …
አይደል እንዴ፣ ያጋመደን ፣ የአገራችን ውብ ተፈጥሮ
በዘመናት ውስጥ ደማችንን አዋህዶ፣የሚያኖረን አቃብሮ ?
ለም አፈሮ አይደል እንዴ በዘር ሳያዳላ
የሚያተገን…..ሰርተን እንድንበላ ?
አይደል እንዴ ?የዜጎች ሁሉ
የሀገራችን ፣የፈጣሪ መሬት
የተሰጠን ወርቅ እንድናፍሥበት???
………………………..
እናም….
እወቅ ፣ የደቡቡ ሰው
ሰሜኑም ያንተነው።
አትንዘንጋ፣ የሰሜኑ ሰው
ደቡብም ያንተ ነው።
ተገንዘብ፣ የምስራቁ ሰው
ምእራቡም ያንተ ነው።
አትርሳ፣ የምዕራቡ ሰው
ምሥራቁም ያንተ ነው።
ቋንቋህ ቢለያይም
ሌላ ሀገር የለህም።
ግና ……………
እናንተ ከጥበብ የራቃችሁ
እስቲ ልጠይቃችሁ ?
እስቲ ተጠየቁ…
ሥለ ሀገር የማታውቁ
እስቲ ተጠየቁ ?
እውነትን የማታውቁ …
የአገር ወዳዱን መስዋትነት የምታናንቁ
በቴዎድሮስ ፣በምኒልክ ፣ በዮሐንስ የምትሳሳቁ
በለአገሩን በድክመቱ ለከንቱ ዓላማችሁ የምታሰልፉ
ጉዳችሁ ይወጣል በእውነት ተደፍጥጠታችሁ ስታልፉ ፡፡
እናም አስተውል ጦጵያው
የአባቶችህ መስዋትነት ፣ ለአንተ ህልውና ነው ፡፡
በጀግኖቹ ሞት ነው ፣ዛሬ በህይወት ያለኸው።
አገርህ የጀግና አገር እንደሆነ እወቀው
ለአንተ መኖር ሲል ነው ፣ በደር በገደሉ በበረሃ የረገፈው።
በአራቱም መአዘን ደሙ ፈሶ አጥንቱ የተዘራው።
እናም …
አትበል ወንድም ዓለም “የእኔ ሰው፣የእኔ ሰው”
አትበይ እህት ዓለም “የእኔ ሰው የእኔ ሰው”
እንዲህ ሲል የነበረው ፋሺሥት ብቻ ነው።
ሀገር የቆመችው በሁሉም ዜጋ ነው ፡፡
በሁሉም ሰው መሰዋትነት ነው …
ሥልጡኖቹን አውሮፓውያን ያሳፈረ ድል ያገኘነው።
ይህ ድል….
ያንተ ሰው…
የዛም ሰው..
የእሱም ሰው..
ያንቺም ሰው…
የሀሉም ዜጋ ኩራት
አደዋ ነው ::
ግና…………..
እናንተ ከጥበብ የራቃችሁ
እስቲ ልጠይቃችሁ ?
እስቲ ተጠየቁ…
ሥለ ሀገር የማታውቁ
እስቲ እንጠይቃችሁ
እስቲ ተጠየቁ ?
ማነው ከጥበብ አርቆ
በቋንቋ አጥምቆ
በዘር እመኑ ያላችሁ ?
“ሥልቻ ቀንቀሎ
ቀንቀሎ ሥልቻ”
መሆኑን የረሳችሁ ?
አለ በዘር ያገለላችሁ ?
ከሰውነት የሰረዛችሁ?
ዘርህ ሰው ሆኖ
የመግባብያ ቋንቋህን አግኖ
“እናንተ ቋንቋ ናችሁ።” ብሎ
ከሰው ተርታ ሰርዞ …
ሀገር አልባ አድርጎ !
ዜግነታችሁን ገፎ !…
አለ ወይ ዘረኝነትን የስተማራችሁ ?
በእርግጥ ባለፉት ዓመታት
ዘረኝነት ፣ጎጠኝነት ሥር ሰዷል…
እንደ ሰናኦር ግንበኛ
ሆኖል አዳሜ ፣ የቋንቋ ልክፍተኛ
ያለመግባባት ህመምተኛ
የነገድ አብዮተኛ
በመንጋ እየጮኸ…የሚል
“የእኔው ጅብ ይብላኛ !!!”
…………………………..
እናንተ ከጥበብ የራቃችሁ
እስቲ ልጠይቃችሁ ?
እስቲ ተጠየቁ…
ሥለ ሀገር የማታውቁ ።
…………………………….
2011 ተወጠነ
ግንቦት 23 ቀን 2013 ዓ/ም በድጋሚ የተፃፈ ፤፤
መኮንን ሻውል ወልደጊዮርጊስ

ተጨማሪ ያንብቡ:  ለሁሉም ጊዜ አለው! የዓባይ ትንቢቱ ሲፈጸም - በገ/ክርስቶስ ዓባይ

ሀሃሳብ እና አስተያትዎን ይስጡ

Your email address will not be published.