ታቸው ለገሰ የካቲት 2013 ዓ.ም.
የታሪክ መበጣጠስ እንዳይኖር ማጋመዱ
የጀግኖችን የሃገር ፍቅር ከማንነታቸው ጋር ማዛመዱ፤
አንድነቷን … በአለም አቀፍ መድረክ ማንነቷን
ለነጻነቷ ቀንአዊ … ለክብሯ ሟችነቷን
ለጥቁር ለነጩ … የትግል ፋና ቀዳጅነቷን፤
የሰውን ዘር ሁሉ እኩልነት
በፈጣሪው አምሳል የመፈጠሩን ሚስጥር አልባ ምንነት
የጥቁርን መናቅና ሰው የመሆኑን ክህደት ዋጋ ያስከፈለበት፤
ኧረ ስንቱ … ኧረ ስንቱ
የአድዋ ድል ግብአቱ ።
የዘመናት አምዳችን … የጥቁርነታችን … የጀግንነታችን
በኢትዮጵያዊነት ህብር መድመቂያችን፤
ይጥፋ … ቢሉት የማይጠፋ
ሲያዳፍኑት…የሚስፋፋ
ጠብበው ሲያጠቡት… የሚሰፋ፤
የማን ሲሉት … የእኛን ይዞ
በአባ ጎራ … በአባ ነፍሶ … በአባ ውርጂ ተጠርዞ፤
ድልብ ታሪክ … ውቅያኖስ … አትጨልፈው አትቆነጥር
በአንድነቱ ተገማምዶ … ተትረፍርፎ የሚመሰክር።
በአንባሰሏ በውጫሌ ተሸርቦ ባርነት
በጣይቱ በምኒልክ ጥበብና ጀግንነት
እንዳይጸና ላይፈረም … መዘዘኛው አስራ ሰባት
የአበሻነት ማንነቴ …ማህተብ ሆኖ እንድኖርባት
የአባት የእናት … ህይወት ግብር … ቃልኪዳናቸው አለባት ።
የአውአሎም ብስለት… የራስ ወሌ ብጡል … የራስ አባተ ቧያለው
የነጻነት ቀንዲል
የአንባላጌ … ወረይሉ… የመቀሌን… የአድዋውን የድሎች ድል
የጣይቱን አልደፈር ባይነት … የምኒልክን የጦር ገድል፤
አላውቅ ያሉ ክደው ያስካዱ የጉድ ጉዶች
ዛሬም እዛው መንደር … እዛው ቀዬ የተፈለፈሉ ባንዳና ሹምባሾች
ለባእድ ደላሎች… ነክሰው አስነከሱሽ … ዙርያ አናካሾች።
ያንዬም በምኒልክ ለሆዱ ያደረ
ባንዳና ሰላዩ በቤቱ ነበረ።
አዎ አፈ ቄሳር አፈወርቅ … ልጅ ጉግሳ… ልጅ ቅጣው
ዛሬም ተክተዋል ከሃዲ የልጅ ልጆች
ካልበላን እንጫረው … ካልገዛን እንናደው … እናፍርሰው ባዮች።
በደም በአጥንት ምድር … አድዋ! ከአንቺው የፈለቁ
ከጣልያን የባሰ ኢትዮጵያን የናቁ
እነሁሉን ለእኔ … ህዝብን እየወጉ በህዝብ የተደቁ
ሲያቅራሩብን ኖረው ገቡት በእንፉቅቁ።
“ጥቁር ሰው አይደለም” … ብለው የፈረጁት
ያንዬ ጣልያኖቹ አጉል በተበቱት
ዛሬም ባንዳዎቹ “ከ እኛ ሌላ …” ያሉት፣
ከሰውም ሰው ሆኖ ዘንድሮም እንደ አምናው
ሲነጋጋ ገጥሞ ረፋፋዱ ላይ ድል በድል የቀናው
ሲያርበደብድ አዩት አይበገር ጀግናው።
አይ አንቺ አድዋ … ስንት ድል አይተሻል?
ከጀግና እስከፈሪ … ከገንቢ እስከ አፍራሹ ስንቱን አብቅለሻል?
ትናንትናም … ዛሬም ስንት ታዝበሻል።
“ነጻነት ተነፍጎ … ከሺህ አመት ኑሮ
ዛሬ ነጻ መውጣት ህይወትን ገብሮ”
እያለ ባዶ እግሩን ምድርን እየናጠው
አንባላጌ ክትቶ አድዋ ብቅ ያለው
የጥቁሮቹ ኩራት… ነጩን አፍ ያስያዘው
በምኒልክ ድግስ የዋለው ጀግና ነው።
አድዋ ነበረች … ዛሬም አድዋ ነች
አድዋም ከበረች … በታሪክ ገነነች
ምኒልክን ጠርታ … ጣይቱንም ብላ መቼም ያላፈረች
የእግር እሳት ሆና ለቤቷ ባንዳዎች
በቃኝ ብላ አምርራ … ዳግም ከመንደሯ ጠራርጋ የቀበረች።
አይ ደደቢት … “መጣሁ” ካለበት እንዳይመለስ አሰናብተሽ
“አንቀጠቀጥኩት” ያለውን ጋራ በላዩ ላይ አንቀጥቅጠሽ ንደሽ
ጉልበቱን ሰብረሽ … ምላሱን ብቻ አስቀርተሽ
ዳግም በምኒልክ…ዛሬም በጣይቱ የልጅ ልጆች አድረሽ
እንዳይነሳ በፍርስራሽሽ ስር ከደንሽ …ቀበርሽ።
በየጋራው ሸንተረሩ ዛሬም ሰንደቅሽ ከፍ ብሎ ተውለበለበ
የልጆችሽ አንድነት ለማንነቱ አብሮ መቆሙ ተጻፈ … ተነበበ ፤
ከአብራክሽ በወጡ ጉዶች ላይ ሊወራ
አድዋ! ዳግም በደም ቀለም ታሪክሽ ተሰራ
125 … “አንድ” ተብሎ እንደ አዲስ ተጠራ፤
አዎ አድዋ … ዛሬም አድዋ አመትሽ እንደገና ሊቆጠር
የልጅ ልጆችሽ ገድል ለመጪው ትውልድ ሊነገር
መቶም አይደለ…. ሃምሳም አልሞላው … “አሃዱ” ብለን ዛሬ እንዲጀመር
ኢትዮጵያዊነት … አንድነታችን… እንዲመሰከር
ንቀው ያስናቁት እንቢኝ ባይነት ከብሮ እንዲከበር
“ሀ”…ተብሎ በአንድነታችን …. አድዋ ዛሬም ይዘከር … ይታወጅ … ይነገር።
ኢትዮጵያችን ለዘላለም ትኑር!!!