ይከበር የአንች ቀን በሆታ በልልታ
ይዘመር ዝማሬ ከበሮ ይመታ
ቢፃፍ ስለማያልቅ የእናቶች ውለታ
ዘጠኝ ወር በሙሉ አንችው ተሸክመሽ
ደምና እስትንፋስሽን ቀንሰሽ አካፍለሽ
ውጋቱን ቁርጠቱን እምቅ አርገሽ ችለሽ
ማሞና ማሚትን በጉያሽ ውስጥ አቅፈሽ
ሽንትና ቅዘኑ ከረፋኝ ሳይወጣሽ
ሰውን ሰው ያረግሽው እናት አንች እኮ ነሽ
ልዩ የዓለም ፀጋ የተፍጥሮ ዉበት
መለኮት የቀባሽ ሰባቱን ቀለማት
ሚስት
እናት
እህት
አክስት
አያት
አይት
ምራት
ተብለሽ እንድትጠሪበት
የሚፈጠሩብሽ አንበሳና አንበሲት
ይከበር ያንች ቀን በሆታ በልልታ
ይዘመር ዝማሬ ከበሮው ይመታ
ቢፃፍ ስለማያልቅ የእናቶች ውለታ
መለኮት ተጠቦ ተጨንቆ ፈጥሮሽ
ምድርን እንድትሞያት አደራ ተብለሽ
ማህፀንን ለብቻሽ መርቆ ሰጠሽ
እናትም አንችው ነሽ እህትም አንች ነሽ
ከደግነት ጋራ ፈትፍተሽ ያጎረስሽ
በምን ቃል ይገለፅ ይዘከር ውለታሽ
የፍቅርን ጎተራ የደግነትን ባንክ
የትዕግሥትን ጋራ የማስተዋልን መስክ
ለእናት ታድሏታል በሰፊው ያለልክ
የቤቱ መሠረት ጉልላቱም አንች
የውስጡን የውጩን የምታመቻች
ሕይወት መና ሁና በቀረች ያለ አንች
ለአያሌ ዘመናት ተጨቁነሽ የኖርሽ
ኋላ ቀር ሥርዓቶች መጠቀሚያው አርገውሽ
በልጆችሽ ትግል ይኸው መድረክ ወጣሽ
በየሥርዓቱ የምትኖሪው እናት
ጭቆናሽ ይለያል በመልክና በዓይነት
አንደኛው ፊትሽን ሸፍኖት ይኖራል
ሌላው በበኩሉ ቤት ቁጭ በይ ይልሻል
ሦስተኛው ትምህርትን ይከለክልሻል
እጥፍ ድርብ በደል ተጭኖሽ ኑረሻል
ዕድሜ ለልጆችሽ ነፃ አውጥተውሻል
አክብሩላት ባዕሏን የእናታችን ቀን
አድምቁላት ባዕሉን የእህታችን ቀን
አደባባይ ወጥታ አብራን መዋሏን
ከድርብ ጭቆና ነፃ እንድትሆንልን
ደመቅ እናድርገው ሆ ! በይው ብለን
ጀግና አይኖርም ነበር አንች ባትወልጅው
ሊቅም አይፈጠር አንች ባታምጭው
ምድር እራቁቷን ነበር የምትቀረው
ጦር ሜዳ ቢልኩሽ ጀግና ታዋጊያለሽ
የፈሪውን ሀሞት ኮስተር ታረጊያለሽ
ከሊቅ ጋር ቢያውሉሽ ታመራምሪያለሽ
ለገበሬውማ አጣማጁ አንችው ነሽ
ወሰኑ አይታይም ሴት ያንች ችሎታሽ
እስኪ ጠቀስ እናርግ ስመ ጥር ሴቶችን
በአድዋ ጣይቱን
የማይጨዋን ነብር ሽዋረግድን
በእስራዔል ማየርን
የእንግሊዟን ታቸር ኢንድራ ጋንዲን
አሁን ካሉት እንኳን አንጀላ መልከርን
አደባባይ ቆመው ደምቀው የታዩትን
የሴትን ችሎታ ያስመስከሩትን
ባሰለፉሽ ቦታ ቀድመሽ ትገኛለሽ
የታመመ አስታመሽ ለዘማች ሰንቀሽ
ፆታሽ ሳይወስንሽ የሴት ወንድ ሁነሽ
በሁሉም ሙያ መስክ ቀድመሽ ትታያለሽ
ይከበር ያንች ቀን በሆታ በልልታ
ይዘመር ዝማሬ ከበሮው ይመታ
ቢፃፍ ስለማያልቅ የሴቶች ዉለታ
እናክብረው በዓሉን የእናትችን ቀን
አደባባይ ወጥታ አብራን መዋሏን
ከድርብ ጭቆና ነፃ መሆኗን
እናድምቀው በዓሉን እልል ሆ ! ብለን
ይበሰር ደስታው ትውልዱም ይወቀው
ስህተት እንዳይሰራ እንዳያስጠይቀው
ታሪክ ተረካቢ ወጣቱ ነውና
አብረነው እንቁም ክንዱ እስከሚጠና