የፈጠረን አምላክ ሁላችንንም እኩል ይወደናል።ፈቃዱም እርሱ እንደ ወደደን፣ እኛም እርስ በርስ እንድንዋደድ ነበር።ለዚህ ነው “አትግደል፣ አታመንዝር፣ አትስረቅ፣ በባልጀራህ ላይ በሐሰት አትመስክር፣የባልጀርህን ቤት አትመኝ፣ የባልጀርህን ሚስት፣ወይም የእርሱን ወንድ አገልጋይ ሆነ ሴት አገልጋይ፣ በሬውንም ሆነ አህያውን ወይም የእርሱ የሆነውን ማናቸውም ነገር አትመኝ”በማለት ተከባብረን አብረን እንድንኖር ያዘዘን።
እነዚህ ትዕዛዛት ሁላችንንም የሚመለከቱ ናቸው።ነገር ግን ማንም ይህን የፈጣሪ አምላኩን ትዕዛዝ አክብሮ እንደ ቃሉ የኖረ የለም። እንኳንስ ምዕመናኑ የእምነት መሪዎችም በብሔር ተለያይተው እርስ በርስ በመወጋግገዝ ላይ ናቸውና፡፡ፖለቲካኞቹም እንዲሁ ጀባሃና ሻቢያ፣ ኢሕአፓና መኢሶን፣ወዝ ሊግና አቢዮታዊ ሰደድ፣ ኦነግና፣ ሕወሐት፣ ኢህዴንና ፣ ኦሕዴድ፣ የመሳሰሉት አብረው ለነፃነት ሲታገሉ ቆይተዋል።
የመንግሥት ሥልጣን ግን ታጓጓለች፣ጃንሆይ እንኳን በሰማንያ አመታቸው ሥልጣነ መንግሥታቸውን፣ለአልጋ ወራሻቸው ለመልቀቅ ፈቃደኛ አልነበሩም።ጊዜያዊ ወታደራዊ መንግሥትም፣ ሥልጣነ መንግሥትን ለሕዝብ አልመለሰም፤ መለዮዉን አስቀምጦ ስሙን ቀይሮ በሠራተኛ ፓርቲ ስም ገዛን እንጂ።
ኢሕአዴግም የፌድራል ሕገ መንግሥት የቀረጸው የብሔር ብሄረሰቦችን፣ጥያቄ ለመመለስ አልነበረም፣ በአቢዮታዊ ዲሞክራሲ መሥመር ሕወሐትን በመላ ኢትዮጵያ ላይ ለማንግሥ ነበር እንጂ።ዛሬም ቢሆን እያፋጀን ያለው ይኸው የመንግሥት ሥልጣን ጉዳይ ነው።ለዚህ ነው ዕጩዎቹ ሕግና ሕገ መንግሥትን ተላልፈው፣በግልጽና በስውር ተደራጅተው ማዕከላዊውን መንግሥት በአመጽ ለማፈራረስ፣ በጥሎ ማለፍ ውድድር ላይ የሚገኙት።
ስለሆነም አሁን ጎልቶ የወጣው የመንግሥት ሥልጣን ጥያቄ ባለ ሦስት ፈርጅ ነው።የመጀመሪያውና ከኢሕአዴግ በፊትም የነበረው፣ በኢሕአዴግም ያልተፈታው፣የብሔር ብሔረሰቦች፣ራስን በራስ የማስተዳደር የመብት ጥያቄ ነው።ሁለተኛው በኢሕአዴግ ዘመነ መንግሥት ውስጥ ጎልቶ የወጣው የአሓዳዊ መንግሥት የሥልጣን ጥያቄ ነው።ሦስተኛው በኢሕአዴግ አባል ደርጅቶች ውስጥ ተከስቶ አብጦ የፈንዳው የመንግሥት ሥልጣን ጥያቄ ነው።
ማዕከላዊ መንግሥትም ራሳ የቅራኔዎቹ ምንጭና የመንግሥት ሥልጣን ተወዳዳሪም ስለሆነ፣የሚዲያና የአክቲቪስቶች ተቃውሞውም ከወስጥና ከውጭ፣ከግራና ከቀኝ ስለ በዛበት፣ ሕዝቡን በእኩልነት ወደ ሰላም እንዳይመራ እንቅፋት ሁነውበታል።ስለሆነም ሕዝባችን፣ በፓርቲዎች አማካይነት፣ እየተካሄደ ያለውን የመንግሥት ሥልጣን ጥያቄዎችን፣ በግልጽ መረዳት ይኖርበታል።
በዚህ ረግድ የሕዝባችንን መሠረታዊ ጥያቄዎች በመመለስ ረገድ ሕወሐት ምን አደረገ? በማለት ተግባሩን ብንመረምር፣ በሽግግር መንግሥቱ ምሥረታ የተሰባሰቡትን የብሔር ብሔረሰብ ድርጅቶችን ተራ በተራ አባረረ፣በሁሉም ብሔር ብሔረሰብ የራሱን የብሔር ድርጅት መሰረተ፣ እነርሱንም በድርጅታዊ አሰራር አስመረጠ፣በእነርሱም ድምጽ ተጠቅሞ በጠቅላይ ሚኒስትርነት ተሰየመ፣ በሥልጣኑም ተጠቅሞ፣መብታችንን አፈነ፣ኦነግን በቴረርስትነት አስመዝግቦ ኦሮሞን የጥገኝነት መብት አሳጣ። ይህንን የተቃወሙ ኦሮሞዎችን በአጋዚ አስቀጠቀጠ፣ በወህኒ አመቀቀ፣ ገበሬውንም ከለም መሬቱ አፈናቅሎ ለእንቬስተሮች ሸጠ።የገሪቱን ኅብትና ንብረት ከሽርከኞቹ ጋር ተቃረጠ።በመሆኑም ሕዝባችንን አደኸየ ጥቂት ግብረ አበሮቹን ግን አበለጸገ።
የኦሮማራ የብልጽግና ፓርቲ፣ወይም (ከኢሕአዴግ ሲቀነስ ወያኔ) የሆነ ደርጅት፣ ለአንድ ብሔር ወይም ለአንድ መደብ ጥቅም የቆመ፣ ወጥ ፓርቲ አይድለም።ጠቅላይ ሚኒስትሩም በኢሕአዴግ ድምጽ የተመረጠ፣ ተጠሪነቱም ቀደም ሲል ለኢሕአዴግ፣አሁን ደግሞ ለብልጽግና ፓርቲ የሆነ ነው። ስለሆነም ራሱ የወደደውን የሚያደርግ ንጉስ ወይም በአንድ ብሔር ተመርጦ ለብሔሩ ብቻ የሚሰራ መሪ አይደለም።ከዚህ የተነሳም ነበር ጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ ወደ መደመር ፖሊሲና ወደ ብልጽግና የሚያተኩሩት።
ብልጽግና የብሔር ብሔረሰቦችን መብት በማስከበር ረግድ ከአሓዳዊያን ጋር በመታገል። ሲዳማ በክልል ራሱን በራሱ እንዲያስተዳድር ፈቅደዋል።የወለይታ የብሔር ድርጅቶች ነገሩን ከመንግሥት ሥልጣንና ከኢኮኖሚ ጥቅም አንጻር ብቻ ተመልክተው፣አከረሩት እንጂ፣ የደቡብ ሕዝቦችን የክልልነት ጥያቄ፣ መልስ ለመስጠት ዝግጅት ተገርጎ ነብር። ከዚያም በኋላ የምዕራብ ኦሞ ሕዝብች ያቀረቡትን የክልልነት ጥያቄ አዎንታዊ ምላሽ አግኝቷል።
የኦሮሞ ሕዝብ ጥያቄዎችንም በሚመለከት፣ አፋን ኦሮሞ፣ ትግርኛ፣ አፋርኛና ሱማሊኛ ከአማርኛ ጋር የአገራችን የሥራ ቋንቋ እንዲሆኑ በብልጽግና ፓርቲ ፕሮግራም ላይ አስፍረዋል።የቋንቋዎቹ አጠቃቀምም በባለሙያዎቹ አማካይነት በጥናት ላይ ይገኛል።በዲስ አበባ ከታማም ኦሮሞዎች በቋንቋቸው እንዲማሩ ተደርጓል።ከአዲስ አበባ ከመሬታቸው ለተፈናቀሉ ገበሬዎችም ካሳ የመኖሪያ ቤት ተስጥቷል፣በአዲስ አበባ ዙሪያ ለሚገኙ ገበሬዎች፣ ወደ ስድሳ ሚሊዮን ብር የሚጠጋ የባጀት ድጎማ ተደርጓል።ይህ ሁሉ በብልጽግና ፓርቲ አመራር የተገኘ ውጤት ነው።
ሠፊውን አርሶ አደር ሕዝባችንን ከኋላ ቀርነት ለማላቀቅ፣የመሥኖ እርሻ፣ተስፋፍቷል፣በክላስተር ለተደርጁ ገበሬዎች፣ ትራክተሮች፣ ህርቨስተሮች፣ የውሃ ፓፖች፣ በብዛት አቅርቦላቸዋል። የአቡካዶ፣ የማንጎ፣የሙዝና የፓፓያ ችግኞችን አፍልተው ለገበሬዎቹ በማቅረብ፣የገበሬዎችን ምርትና ምርታማነቱን አሳድገዋል።
የአዲስ አበባን ከተማ ለማስዋብ፣ ጽዳቷንም ለመጠበቅ፣ ምቹ የመዝናኛ ስፍራዎችን በማዘጋጀትም ሆነ፣ የኮሎሮና ቫይረስን በመከላከል፣ የህዳሴ ግድብን ሥራ በማፋጠን፣ከውጭ የሚሰነዘርን ተቃውሞ መክቶ በመመለስ ረገድ፣ በአገራችን እንደ ብልጽግና ፓርቲ የተሳካለት መንግሥት አልነበረም።
ሁለተኛው አንድ አገር፣ አንድ መንግሥት፣አንድ ቋንቋ፣አንድ ስንደቅ ዓላማ በሚል አቋም ሥር የተሰባሰቡ፣ሕገ መንግሥትንና የብሔሮችን መብት የሚቃወሙ፣የዘውድ አገዛዝ ናፋቂዎች ናቸው።እነዚህም ያንኑ ሥርዓት ስም ቀይረው ለመመለስ፣ በአገር ወስጥና ውጭ በብዙ ስሞች የተደራጁ፣እንደ ጋጋኖ በመጮህ ሕዝባችንን ገራ የሚያጋቡ ናቸው።
እንግዲህ ይህ ኃይል ነው፣ምንጩ ከማይታወቅ ገንዘብ ተቃዋሚ ድርጅቶችንና ሚዲያዎችን በመፈልፈል፣በሥልጣን ላይ የሚገኝን መንግሥት በመገዳደር ላይ የሚገኘው።ይህ ድርጅት ነበር በሰላዮቹ በመጠቀም ለማና አቢይን ያለያየው።ኦነግን ወደ አመጽ በመገፍተር፣ ኦሮሞና አማራን ለማለያየት፣የአገር ሽማግሌውች እርቅ በማደናቀፍ፣ ለዚህ የጦርነት እልቂት የዳረገን።
እኛ ግ ን የአንድ አገር ሕዝቦች ነንና፣ እስከ አሁን ክፉም ይሁን ደጉን ዘመን አብረን አሳልፈናል፣ ተዋልደናል ፣በደምም በሥጋም ተዋህደናልና አንለያይም።ወደፊትም አብረን እንኖራለን።ምንም በሰይጣን ተንኮል፣ በእልህና በንዴት ተነሳስተን ብንገዳደል እንኳ ዞሮ ዞሮ መታረቃችን ስለማይቀር፣የዛሬው ድርጊታችን ሲጸጽተን ይኖራል።የምንገድለው የአገራችንን ልጅ፣ ወንድማችንን ነው።የምንተኩሰውም ሆነ የምናወድመው የጦር መሳሪያ፣ ከድሓው ሕዝባችን ጎሮሮ ነጥቀን የገዛነውን ነው።
በመሆኑም ጦርነቱ በቀጠለ ቁጥር በእያንዳንዱ ሰከንድ ከሁለቱም ጎራ ከሲቪልም ሆነ ከሚለተሪ፣ተጨማሪ ሰዎችን እናጋድላለን።ተጨማሪ ንብረት እናወድማለን፣ከፈጣሪ አምላካችን ፊት እየራቅን ከዲያቢሎስ ጎራ እንሰለፋለን።
ስለዚህም ሁላችንም ከጦርነት፣ ጥፋትና እልቂትን እንጂ አንድም ጥቅም አናተርፍም፣በፌድራሊዝም ትግራይ ከሁሉም ይልቅ ተጠቀመች እንጂ አልተበደለችም ነበር።ለሃያ ሰባት አመት በከፍተኛ ሥልጣን ላይ የነበሩት ግን ከእንግዲህ ያንን የሥልጣን ማማ የሚቆናጠጡበት የአቢዮታዊ ዴሞክራሲ መሠላል ስለ ተሸራተተባቸው ቀኑ ጨልሞባቸዋል።ለዚህም ነው ሮኬቶችንና ሚሳይሎቹን ጨብጠው ወደ መንግሥት ሥልጣን የሚመለሱ መስሎአቸው፣ ያአገር መከላከያ ኀይላችንን በጭካኔ የጨፈጨፉት፡፡
ይህ መራራ እውነት ቢሆንም፣ ወደኋላ ልንመልሰው አንችልም።ጦርነቱ ከቀጠለ ጥላቻውም ይቀጥላል።በቀልም በቀልን ይወልዳል።ተግስትም አልቆ ወደ ማይፈለገው ደረጃ ሊያደርስ ይችላል።ስለዚህም ጦርነት፣የሰውን ልጅ ሕይወት የሚቀጥፍ የመጨቆኛ መሣሪያ እንጂ የሕግ ማስከበሪያ መሣሪያ አይደለም።በመሆኑም ሕግም ሆነ ሕገ መንግስት የሚከበረው እኛው ራሳችንን ሕገ መንግሥቱን አክበረና ላማስከበር ስንችል ነው።
ለዚህ ሂደት መስካት የግራና የቀኙን ፈቃደኝነት ይጠይቃል።ይህን ፈቃደኝነትን ማሰገኘት ነው የአባቶች ተልዕኮ።ስለ አገር አንድነትና ስለ ሕዝብ ሰላም ሲባል ሁሉም በቀልን ለፈጣሪው በመተው፣በአገር ሽማግሌዎች ፊት እኩል ራሱን ዝቅ ሊያደርግ ይገባል።
ሽምግልናውም ያገርን ሳርዶ በአገር በሬ እንዲሉ ከግራ ቀኙ በሚመረጡ ያአገር ሽማግሌዎች ሊመራ ይገባዋል።በዚህም ረገድ ሕወሐት ለፌድራል ሕገ መንግሥት ተግዥ መሆኑን ለማመልከት፣እንደ ቀድሞው በቁጥጥሩ ውስጥ በሚገኙ የፌድራል ተቋሟት ሁሉ የፌድራሉን ሰንደቅ ዓላማ እንዲውለብለብ በማድረግ ለእርቁ ፈቃደኝነቱን ማረጋገጥ ይኖርበታል።
ይህ ከሆነ ጊዜ አንስቶ ፌድራል መንግሥቱም የዓየር ድብደባውን በመግታት ፈቃድኝነቱን ማረጋገጥ ይኖርበታል።ይህ ከሆነ የአየር በረራ ተፈቅዶ፣ቀደም ሲል ወደ አዲስ አበባ ተልከው የነበሩት የሕወሐት ሽማግሌዎች፣ወደ አዲስ አበባ በመምጣት፣ከመሐል አገር ወደ መቀሌ ሄደው ከነበሩት ያገር ሽማግሌዎች ጋር በመሆን ለድርድሩ አስፈላጊውን ቅድመ ሁኔታ ሊያመቻቹ ይገባል።ይህ ሲሆን ነው የሁሉም መብት ያለ መድሎ በእኩልነት የሚከበረው።
ይህ ዕድል ድንገት ካመለጠና፣ጦርነቱ ከቁጥጥራችን ወጭ ከሆነ፣ የምንኮራባትንና የምንራራላትን፣ እናት አገር ሊያሳጣን ይችላልና፣ሙፋራት እንዳለችው አሁንም ሰከን ማለት ይገባል።ባለሥልጣኖች ስለሆን ሰውን እንኳን ባይሆን፣ የፈጣሪ አምላካችንን በቀል መፍራት ይገባናል።፣ትውልድና ታሪክም እንደሚፈርድብን ማስተዋል ይገባናል።
ለሁሉም ሥልጣን የሕዝብ በመሆኑ፣ ለሕዝቡ የመወሰን ዕድል እንስጥ። በሚቀጥለው ምርጫ ሕዝቡ በቀጥታ ድምጹ ፕሬዚደንቱን እንዲ መርጥ እናድርግ።የአገራችን መሠረታዊ ችግር የቅርጸ መንግሥቱ ፓርላሜንተራዊ መሆን ነው።ፕሬዚደንቱ በጠቅላላ ሕዝብ የድምጽ ብልጫ የሚመረጥ ከሆነ፣ለሥልጣን የድምጽ ብልጫ ለማግኘት ሲባል የመራጭ ሕዝብ መብት በእኩልነት ይከበራል። መፈነቃቀልም ያከትማል።
እንግዲህ እስከ አሁን በተለያየ ምክንያት ለደረሰው ጥፋትና ጉዳት፣ ይብዛም ይነስ እንጂ፣ የሁላችንም እጅ አለበት።ስለዚህም ላለፈው ጥፋታችን የፈጣሪ አምላካችንን ምሕረት በመማጸን፣ የበደልነውን በመካስ፣ የጠሉንን በመውደድ፣ተጨማሪ ግፍና በደል ከመፈጸም በመቆጠብ፣በሕገ መንግሥቱ መሠረት ተግባብተንና ተስማምተን መኖር ይገባናል። በዚህም ረገድ ያሉንን አባቶች እክብረን ምክራቸውን በመስማት ይቅር መባባል ይጠበቅብናል። በደልን ይቅር የሚል፣ በደሉ ይቅር ይባላልና።
ጆቢር ሔይኢ ከሁስተን ቴክሳስ፣