November 12, 2020
2 mins read

ታሪክ ሥራ አለብህ (ዘ-ጌርሣም)

ታሪክ ሥራ አለብህ
መስካሪ ነህና ነገ ጧት በተራህ
ይዘጋጅ ብራናው
የገድል መክተቢያው
ሾል ይበል ብዕሩ
ይቀለም መስመሩ
መዝግብ የሆነውን
አገር ያወቀውን
ፀሐይ የሞቀውን
የሰበሰብከውን በገደል በዱሩ
የኢትዮጵያ ጀግኖች እንዴት እንዳደሩ
ታሪክ ሥራ አለብህ
የሰበሰብከውን መዝግበው እባክህ
በጥብጠው ቀለሙን
አሹለው እርሳሱን
መዝግበው ድርጊቱን
አዘጋጅ ጠልሰሙን
ክተበው እልቂቱን
አስቀምጥ ታሪኩን
የተሠራውን ግፍ
የወገንን መርገፍ
በጥይት መደብደብ
ያለምንም ገደብ
በጭካኔ መንፈስ
ሰውን በሚያረክስ
ያገር ሀብት መዘረፍ
የዘር ማፅዳት ግፉን
በየጉራንጉሩ አርበኛ መሞቱን
የሃገር ዋቢውን
መከላከያውን
እንዴት እንዳጠቁት
ያውም ከተኛበት
አንገት ያስደፋውን
ቅስም የሰበረውን
አረመኔ ድርጊት
በዚህ የቅስፈት ወቅት
በአገር ከሃዲዎች
ወጭት ሰባሪዎች
የተሠራውን ግፍ
ለትውልዱ ይትረፍ
ያኑረው በሃፍረት
በማስደፋት አንገት
ታሪክ ሥራ አለብህ
ያዝ ግፉን መዝግበህ
ዕውነት ቢድበሰበስ
በውሸት ቢቸለስ
ሐቅን እትፍ ካልህ
ተጠይቂ አንተ ነህ
ታሪክ ሥራ አለብህ
ስንክሣሩን ያዘው እጅግ ተጠንቅቀህ
የሚተካው ትውልድ ስለሚጠይቅህ
2020-11-11

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Go toTop