ብልህ ከሌላው፣ ሞኝ ከራሱ ይማራል – ማተቤ መለሰ ተሰማ

የታሪክ ድርሳናት እንደሚነግሩን ግብጽ ከዛቻና ከሴራ አልፎ አባይን ከምንጩ ጀምሮ ሙሉ በሙሉ ለመቆጣጠር በዲፕሎማሲ ብቻ ሳይሆን በሃገራችን ላይ በርካታ ወረራዎችን ሞክራለች። ለምሳሌ በእኛ ዘመን አቆጣጥር በ1834 ዓ.ም ከሰላ 1848 ዓ.ም መተማ በ1840 ዓ.ም ደባርቅ ላይ ከአጼ ቲዎድሮስ ጋር ተዋግታለች። 1846 ዓ.ም ምጽዋን ለመያዝ ባደረገችው እንቅስቃሴ ቀላል የማይባል ግብግብ ተካሄዷል። በ1868 ጉንዲትና ጉራህ ላይ ከአጼ ዩሃንስ ጋር ተዋግታለች። በተመሳሳይ አመት ኤርትራ በምትገኘዋ ኩፊት በተባለች ቦታ ላይ ከእራስ አሉላ አባነጋ ጋር ተዋግታለች።

ይህንን ተከትሎ 1869 ዓ.ም ኩናማን 1875 ዓ.ም ሃረርን ለመያዝ ባደርገችው እሩጫ ጅግኖች አባቶቻችን መጠነሰፊ መሷዕትነት ከፍለዋል።ከአንድ መቶ አመት በፊት የነበረው አባይን ከምንጩ ለመቆጣጠር የተደረገው የግብጾቹ ሙከራ በአይበገሪ አባቶቻችን ተጋድሎ መክኗል።

ሁኔታዎቹን በሚገባ ያጤነውና ከ1832 እስከ 1875 ዓ.ም የኢትዩጵያን ሁኔታ ይከታትል የነበርው የስዊዙ ተወላጅ ዋርነር ሙንዚንገር ግብጽ ዳግም በኢትዮጵያ ላይ እጇን ከሰነዘረች ከምትጠብቀው በላይ አድጋ እንደሚደርስባት በማስርግጥ አስጠንቅቋታል።

ግብጽ ኢትዮጵያን በጦር ሃይል ማንበርከክ እንደማትችል ስተረዳ በውስጥ ጉዳያችን ጣልቃ በመግባት ሰላም ማሳጣትን ቀዳሚ ስራዋ በማድርግ መንቀሳቀስ ጀመረች። ለዚህም ግባአት የተጠቀመችው የኤርትራን የመገንጠል ጥያቄ ማቀንቀንና የቀድሞውን የኤርትራ ፓርላማ ፕሪዝዳንት የነበረውን ኢድሪስ ሞሐመድን፣ የእስላማዊ ሊግ ዋና ጽሃፊ የነበረውን ኢብራሄም ሱልጣንን እንዲሁም የኤርትራ ሰራተኛ ማህበር ፕሪዝንዳት የነበረውን ወልደ አብ ወልደ.ማርያምንና ሌሎችንም ወደ  ካይሮ በማጓጓዝ አደራጅታ ማሰማራትን ነው።

እናም ግብጽ የብዙ ሺዎችን ህይወት ለቀጠፈው፣ ለአካለስንኩልነት ለዳረገው፣ ለአፈናቀለው፣ብዙ ሚሊየን ዶላር ለበላውና መጠነሰፊ ንብረት ላወደመው ኢትዮጵያውያንን የማያባራ የእርስ በርስ ጦርነት ውስጥ የከተተውን ትርምስ ፕሮግራም አዘጋጅና ቀዳሚ ተዋናይ በመሆን ያሰበችውን አሳክታለች፣እኛም በቋንቋ ተከፋፍለን እንድንባላ አድርጋናለች።

ተጨማሪ ያንብቡ:  በግልፅና በቀጥታ ካልተነገርን የመከራው ፖለቲካችን ማቆሚያ አይኖረውም  - ጠገናው ጎሹ

ያሽነፈችንና ለወደፊትም እንዳታሽንፈን የምሰጋው አሁንም ሌላ እድሪስ ሞሐመድ፣ ሌላ ኢብራሄም ሱልጣንና ሌላ ወልድ.አብ ወልደ.ማርያምን ከመካከላችን በመመልመል እያደራጀች  ስለሆነ በእነዚህ ካሃዲ ባንዳዎች አማካይነት የእርስ በርስ መተላለቃችንን ቀጣይ እንዳታደርግብን ነው።

እንጅ በአውደ ውጊያ የእኛን የኢትዮጵያውያንን ብቃትና ማንነት ግብጽ ጠንቅቃ ስለምታውቅ በእኔ እምነት ካሁን ወዲያ ከማስፈራራት የዘለለ ጦርነት ውስጥ ትከተናለች የሚል ስጋት የለኝም።

ከእንግዴህ ግብጽ ለኢትዮጵያ ልማት ስጋትና ታሪካዊ ጠላትነቷ ለአንዴና ለምጨረሻ ጊዜ እንዲያከትም ያሁኑ ትውልድ ከአዕምሮና ከጉልበት፣ከጊዜና ከገንዘብ አልፎ የአካልና የህይወት መሷዕትነትን መክፈል ይጠበቅበታል። ከአሁን ወዲያ ግብጽ እያስፍራራችን ሳይሆን እየፈራች፣ እንድትኖር እንዲያውም የጀርመን መንግስት እንዳቀረበው ምክረሃሳብ ለምትጠቀምበት ውሃችን ለኢትይዮጵያ ተመጣጣኝ ገንዘብ እየከፈለች እንድትሮር ማድርግ የግድ ነው።

ግብጽ ይህንን የማትቀበል ከሆነ ደግሞ አባይን ከምንጩ ከግሻባይ ጀምሮ በመጥለፍ ገባርወንዞችንማለትምበለስን፣ብርን፣ብሽሎን፣ወልካን፣ሽንኮራን፣ጀማን፣ሙግርን፣ዳቡስን፣ዴዴሳን፣ፊንጫንና ጉደርን በመጥለፍ ወደ አባይ የሚገባው የውሃ መጠን በእጅጉ እንዲቀንስ ማድርግ ነው። ከእነዚህ የአባይ ገባር ወንዞች ግድቦች ተርፎ የሚፈሰው ውሃ ደግሞ ከታላቁ የእዳሴ ግድብ በማለፍ ወደ ሱዳንና  ግብጽ እንዳይፈስ ማድረግ ነው ያለብን።

ይህ ደግሞ ህልም አይደለም እኛ እርስ በርስ መባላቱን በመተው አንድ ሆነን በእልህ ከተነሳን የሚያቀተን ስራ አይኖርም። ጀግኖች አባቶቻችን የግብጽን ሴራ ቆፍረው ባይቀብሩት እንኳን እየሞቱ ቅኝ ሳያስግዙንና በግብጽ መዳፍ ስር ሳይጥሉን ጠብቀው ኢትዮጵያን ከነ ሙሉ ክብሯ አስረክበውናል። እኛ ደግሞ በድርሻችን ትግሉ የጠየቀውን ሁሉ መሷዕትነት ከፍለን የአባይ ባለቤትነታችንን በማረጋገጥ የበለጽገች ኢትዮጵያን ለልጆቻችን ማስረከብ አልብን።

ብልህ ከሌላው ሞኝ ደግሞ ከእራሱ ይማራል እንዲሉ ግብጽ ከኢጣልያንም ሆነ ከእራሷ ተሞክሮ ባለመማር ኢትዮጵያን በጦር ሃይል አንበርክካለሁ ብላ ይምትሞክር ከሆነ የማያዳግም ትምህርት ሰጥቶ ለመመለስ የጎንዮሽ እርግጫችንን በማቆም ሁላችንም ለግዳጅ ዝግጁ ሆነን በተጠንቀቅ  መጠባበቅ አለብን እላለሁ።

ተጨማሪ ያንብቡ:  ድምፅ አሰጣጣችን በምን ሰሌት ቢሆን ያዋጣል? - ዳዊት ዳባ

ማተቤ መለሰ ተሰማ

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Share