ከብልጠት ወደ ብልህነት – እውነቱ ደሳልኝ

እንደ መነሻ፡
ፊደል የቆጠረው የሞኝ ብልጥ
ረብ የጠፋበት ቅልጥ
እውቀት ለግሞበት ባጅቶ
በለቀመው ሆሄ ተምታቶ፤
ወረደ በክፋት ጎዳና ዘልቆ
ወገን ጥሎ ምድርን ለቆ።
ተመለስ በሉት ንቃ!
ተጠለል በእውቀት ሥር ላንቃ
ሳግ በሉት የእውነትን ሲቃ
ያኔ ነውና ለፅድቅ የሚበቃ።

እንደ ትንታኔ፡

ይህን ፅሁፍ ፈራ ተባ እያልኩ ነው የምፅፈው። ይኸውም በምፅፍበት ርዕስ የጠለቀ እውቀት አልያም ደግሞ አስፈላጊው መረጃና ግብዐት የተሟላ ባለመሆኑ ነው። እንደ እውነቱ ከሆነ አንድን ሐሳብ ወይም ጭብጥ በአግባቡ አስረግጦ ለመፃፍና ሃላፊነት የተሞላው ለማድረግ ዋቢ ጠቅሶ፤ በቂ ጥናት አድርጎ፤ ከሃሳቡ ጋር ቀጥተኛም ሆነ ተዘዋዋሪ ቁርኝት ወይም ተዛማጅነት ያለውን ነገር አስተውሎና መርምሮ ከዚያም በላይ ደግሞ ከስሜታዊነትንና ከወገንተኝነትን ተገልሎ መፃፍ ያስፈልጋል። እነዚህን ሁሉ አሟላለሁ ብዬ ብፎክር መታበይ አልያም ድንቁርና ይሆንብኛል።

ካሰብኩት ጉዳይ እንዳልርቅ ይሁንና፤ በዚህች ቅንጣት ፅሁፍ ልሸፍነው የሻሁት ጉዳይ ምናልባትም ሌሎች ከእኔ እጅግ በተሻለ ሁኔታ ያሰቡበት፤ የተነጋገሩበት፤ የተከራከሩበት እንዲሁም የፃፉበት ጆሮና ብዕር ጠገብ ጉዳይ እንደሚሆን አምናለሁ። ነገር ግን አገራችን አሁን ካለችበት ወይም ከደረሰችበት ሁኔታ ሲታይ የተባለው፤ የተነገረውና የተፃፈው በቂ እንደማይሆንና ገና እጅግ ብዙ ሥራ እንደሚያስፈልግ ፅኑ እምነትም አለኝ። በአንድ ወቅት በሀሳቡ በብዙ እጅ የምስማማውና መሳውን ትንታኔውን የምወድለት ብዕረኛ  ሲናገር እንደሰማሁት “በሐገራችን እውነት እና እውቀት ተመናምኗል” ይላል። ይህ መመናመን ደግም ሐገራችንን በብዙ መልኩ ከማትውጣው አረንቋ እየጨመራት ነው ወይም እንዳትወጣ እየደፈቃት ነው። በሐገራችን ቁጥሩ ቀላል የማይባል ህብረተሰባችን ሐቀኝነትንና ቁምነገርን ዘንግቶ ስርቆትን፤ጉቦኝነትን፤ ጭካኔን፤ ቅጥፈትንና ሥርዐተ አልበኝነትን አንግሷል። ለዚህ ደዌ በጊዜ መላ ካልተፈየደለት የመጥፋታችን ዋዜማና መባቻ ይሆናል።

ተጨማሪ ያንብቡ:  የሕሊና ዳኝነት እና ቀጣዩ ፈተና | ከኤርሚያስ ለገሠ

በዚህ አጭር ፅሁፍ ለማተኮር የወደድኩት የእውቀቱን ጎራ ነው። ሥለምን ቢባል፤ ትክክለኛ እውቀት ካለ በእውቀት ላይ የተመሰረተ እውነት ሊገኝ ይችላልና። እንዲሁም ደግሞ ትክክለኛ እውቀት እውነት ነውና። መቼም እውቀት ብዬ ስል ብዙውቻችሁ እንደምትቀበሉት የችግር መፍቻ የሚሆን እውቀት፤ እውነትን መፈለጊያ የሚሆን እውቀት እንጂ ሰይጣናዊ እውቀት እንዳልሆነ እንደምትረዱልኝ አምናለሁ። ታዲያ ጥያቄው በሐገራችን ይህ እውቀት አለን? እውቀቱስ የተሟላ ነውን? ምሉዕነት የሌለው እንደሁ “ትንሽ እውቀት ለጥፋት”(little knowledge is dangerous) እንደሚሉት ሆኖብን ይሆን? ምሉዕ ከሆነስ ምነው ችግራችንን አይፈታ፣ ደዌያችንን አይፈውስ?

እንደሚመስለኝ ከሆነ ሐገራችን ላለፉት ረጅም ዘመናት ብዙ እጅግ የታፈሩ፤ የተከበሩ፤ አንቱነት የበዛላቸው የተማሩ ሐገርን ያገለገሉ፤ በማገልገል ላይ የሚገኙ፤  ወደፊትም የሚያገለግሉ አያሌ ምሁራን፤ ሊቃውንትና ተመራማሪዎችን አፍርታለች። በአንፃሩ ደግሞ ብዙ የተማሩ ገልቱዎችን እንዳፈራች ጥርጥር የለውም። ከዚህ በበለጠ ደግሞ አብዛኛውን  ጊዜ የተማሩ ገልቱዎች ድምፅ እየናረና ከሌሎች በድንቁርና ከተኮደኮዱ ጋር እየተባበረ የሐገሪቱን ህዝብ የኑሮ አቅጣጫ በአልባሌ መንገድ ሲያስጉዝ ተመልክተናል። ይህም የትዬለሌ ለሚሆኑ ዜጎች መሞትና ከአገር መሰደድ፤ ለንብረት መውደም፤ ለሞራል መውደቅና መጨረሻ ለሌለው ዘርፈ ብዙ የድህነት አዙሪቶሽ ዳርጎናል። በከፊል በአንዳንድ መፅሐፍት እንዳስተዋልኩት (ለምሳሌ የዶ/ር አክሊሉ ሀብቴ “የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ ታሪክ”) እንዲሁም በእድሜዬ እንደታዘብኩት ይህ የተማሩ ገልቱዎች መፈጠር የጀመረው የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ መንግስት የከፍተኛ ትምህርትን ማቋቋም ከጀመረበት ማግስት አንስቶ ይመስለኛል። በወቅቱ የኮሚኒስት አስተሳሰብና ሥርዐት በሌላው ዓለም መሰራጨት የጀመረበት ስለነበረ የሐገራችን የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት መበረዝም በዚሁ ጊዜ እንደሚሆን እገምታልሁ። በማጭበርበር የበላይነተን መቆጣጠር፤ ነውርና የስድብ ቋንቋ መጠቀም፤ መከባበርን፤ መተሳስብንና ጨዋነትን በመተው የቀለም እውቀትን ለእኩይና ለጠማማ ተግባር ማዋልን  ወዘተርፈ መላመድ የተጀመረበት ጊዜ ነው። ከዚህ ሁሉ በላይ ደግሞ “ የጥበብ ሁሉ መጀመሪያ እግዚአብሔርን መፍራት ነው” የሚለውን እንደ እውቀት ተቃራኒና ጅልነት በመቁጠር ፍፁም ግራ የሆነ አቅጣጫ የተጀመረበትና እውቀትና እውነት “ደህና ሰንብት” ጉዞ የትጀመረበት ነው። ከዚያም ይባስ ብሎ በዘመነ ደርግ በጠቅላላው እውቀትና እውነት ከጠለል በታች የዋሉብት ጊዜ ነበር። ውጤቱም ብዙዎቻችን እንዳየነው ሆነ። በመቀጠልም በዘመነ ኢሕአዴግ ይኸው አዝማሚያ ጠልቆና ገዝፎ ይልቁንም በድንቁርና የታጀለውና የእርሱ ውጤት የሆነውን ሳንካ በብሔር ወይም በዘመነ መሳፍንታዊ አስተሳሰብ የሚፈታ ነው በሚል ድኩማን አስተሳሰብ የተማሩ ገልቱዎች ሐሳብ ተጨመረበትና “በቦአ ላይ ቆረቆር” እንዲሉ በድህነት ላይ መበታተንን የሚጨምር፤ ብሄራዊ ስሜት የሌለው በሰፈርና በጎጥ የሚያስብና የሚወሰን መንደርተኛ ትውልድ አፈራን። የተማሩ ገልቱዎች ሀሳብ ገንኖ  ወጣ። ይህ ገንጋኝ ሀሳብ ደግሞ  ብዙ ደጋፊና አራማጅ እንዲኖረው  ትምህርት ቤቶች፤ መገናኛ ብዙሀንና ሌሎችም መዋቅሮች የእውነትና እውቀት ማስፋፊያ ከመሆን ይልቅ መደናቆሪያና የተማሩ ገልቱዎች ሀሳብ መፈንጫ ሆኑ። ይህም እነሆ ለዛሬው እርስ በእርሱ ለማይከባበር፣ የሐገርና የባንዲራ ፍቅር ለጎደለው፤ ዋሾና ቀጣፊ፤ ጉቦኛ፤ አጭበርባሪ ለናኘበት ህብረተስብ ከመዳረጉ ባሻገር እውነተኛትን፤ አዋቂነትን፤ ትህትናን፤ ሰው አክባሪነትን፤ በቃል ፀንቶ መገኘትን፤ ጥዩፍ ሥራ መጥላትንና ሌሎችንም እንደ ሞኝነት፤ ጅልነትና ከንቱነት የሚቆጠሩበት ጊዜ ሆነ። ይህን ስል ጠቅላላውን የኢትዮጵያን ህዝብ አለማለቴን በድርብ እንዲሰመርልኝ እፈልጋለሁ። ከዚህ ዝንባሌ በሌላው ረድፍ የቆሙ ሚሊዮኖች ናቸውና።

ተጨማሪ ያንብቡ:  የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ፣ ‹‹በምርጫ ወይም በጥይት››!!! - ፀ/ት ፂዮን ዘማርያም

እንደ መደምደሚያ፡

እንግዲህ በሙግትና በአተካራ ሳንዋጥ እውቀትና እውነት ለአገር እድገትና ብልፅና እጅግ ከሚያስፈልጉ ዋነኛዎቹ እንደሆኑ ማመን ነው። እውቀት ማለት ደግሞ ወደ እውነት የሚነዳ ሀሳብንና ሂደትን የሚፈጥር፤ የሚያለመልም፤ አርቆ አስተዋይነትን የሚያዳብር፤ ችግርን ከቅርብም ሆነ ከሩቅ ተመልክቶ የመፍትሄ ሀሳብ የሚውልድ ያንንም የሚሞክርና በሂደት የሚያሻሽል ሲሆን በውጤቱም የሰው ልጆችን ደህንነት፤ እድገትና የመኖር ተስፋን የሚያረጋግጡበት ፍቱን መሳሪያ ነው። እውቀት ማለት የሰውን ልጅ ከብልጣብልጥነትና ከእኩይ ተግባር ነፃ አውጥቶ ወደ ጥበበኝነትና አስተዋይነት የሚያደርስ ድልድይ ነው። ይህ ከሆነ ዘንዳ፤ በሀገራችን የተከሰተውን የእውቀትና የእውነት መላላትና ክስረት እንደምን መለወጥ ይቻላል የሚለውን በስፋትና በጥልቀት መወያየትና መፍትሄ መሻት ያስፈልጋል። ለጊዜው ጥቂት ግርድፍ ሀሳቦችን ልወርውርና እንደ እግዚአብሄር ፈቃድ ውደፊት የምመለስበት ይሆናል። ከእሳቤዎቼ መካከልም፡

  • ሥርዓተ ትምህርትን ከልብ ማሻሻል – የትምህርት ይዘትን፤ ጥራትን፤ ስርጭትን፤ መስፋፋትንና ደረጃን መጠበቅ።
  • የትምህርትን ዋጋና ጥቅም በማያወልዳ ሁኔታ ማወቅና ሥራ ላይ ማዋል –  የተማረን ኅይል በአግባቡና በቅጡ መጠቀም፤ ተገቢውን ቦታ መስጠት።
  • ትምህርትና እውቀት ሊያድጉና ሊዳብሩ የሚችሉበትን ሁኔታዎች ማመቻቸትና መፍጠር – ምርምሮችን፣ ትብብሮችንና አለምአቀፋዊ ትሥስሮችን  መፍጠርና ማዳበር።
  • የፖሊሲ አቅጣጫዎችን መንደፍ – ከትምህርት ጋር ተዛማጅነና ተወራራሽነት ያላቸውን መስኮች ማዳበር።
  • ግብረ ገብነት ያለው ማህበረሰብ መፍጠር – ተጓዳኝ ሃይማኖታዊ፤ ማህበራዊ፤ ኢኮኖሚያዊ፤ ባህላዊና ታሪካዊ እውቀቶች የሚዳብሩበትን ዘዴ መሻት።
  • ህጎችንና ድንጋጌዎች ማበጀትና – ህግጋትንና ደንቦችን ማስፈፀሚያና ማስጠበቂያ ዘዴዎችን መቀመር።
  • ወዘተርፈ

 

እውነቱ ደሳልኝ

ሰኔ ፲፬ ፳፻፲፪ ዓ. ም

ሀሃሳብ እና አስተያትዎን ይስጡ

Your email address will not be published.