የ ኢትዮጵያ ዋና ዋና ችግሮች እና መፍትሔዎቻቸው-  በ ዘውዱ ገብረ ሕይወት

በ አሁኑ ጊዜ ኢትዮጵያ ብዙ ማህበራዊ፣ ፖለቲካዊ እና ኤኮኖሚያዊ ችግሮች ውስጥ እንደ አለች እሙን ነው፡፡ ስለዚህ፣ እንደ አንድ ዜጋ፣ የ አለኝን ሃሳብ ለ ማጋራት ወደድኩ፡፡ ምናልባት ባለሥልጣኖች እና ተጽዕኖ አሳዳሪዎች ጠቃሚ መስሎ ከታያቸው አዎንታዊ ውጤት ሊያመጣ ይችል ይሆናል ብዬ በ መገመት ነው፡፡

ችግሮቹን እንደ አስከፊነታቸው ቅደም ተከተል ( በ እኔ አስተያየት ) ለ መዳሰስ ሞክሬያለሁ፡፡
1)  ጸጥታን ማስከበር
በየክልሎቹ የ አነስተኛ ብሄሮች ህልውና እና መብቶች ያለ አንዳች ከልካይ ይጣሳሉ። ለዚህም ምክንያቶቹ ጎጠኞች የ ክልሎቹ መሪዎች ናቸው። ስለዚህ የ ፈደራሉ መንግሥት የ ሁሉንም ዜጎች ማስከበር ይጠበቅበታል፡፡
ከ መብቶች ሁሉ ተቀዳሚው መብት ያለ አንዳች ሥጋት የ መኖር መብት መከበር ነው። ይህ እስካልሆነ ድረስ ፈጽሞ ሰላም እና መረጋጋት ሊኖር አይችልም። ሰላም እና መረጋጋት ከሌለ ደግሞ የ ኤኮኖሚ እንቅስቃሴ ሊኖር አይችልም። ስለዚህ መንግሥት ይህን ጉዳይ ቅድሚያ ሰጥቶት ያለ የሌለ ሃይሉን በመጠቀሞ የ ዜጎችን ህልውና እና መብቶች ማስከበር አለበት።
2)   የ ፖለቲካ ፓርቲዎች
ኢትዮጵያ ውስጥ ከ 100 በላይ የ ፖለቲካ ፓርቲዎች አሉ። ይህ ሁኔታ የ ቀልድ ቀልድ ነው፤ አሳፋሪም ነው።፤ ማመን የሚያቅትም ነው። ስለዚህ ይህን ዕብደት መግታት ያስፈልጋል። የ ፖለቲካ ፓርቲዎቹ ወደዱም ጠሉ ከ አራት በማይበልጡ ፓርቲዎች ውስጥ መጠቃለል አለባቸው። ህዝብ እና መንግስት ተባብረው፣ ህዝባችን በ ሰላም እንዲኖር፣ በ ፌደራልም ሆነ በ ክልል ከ አራት የማይበልጡ ፓርቲዎች ብቻ ዕውቅና እንዲያገኙ መደንገግ ያስፈልጋል።
3)   የ ህዝብ ብዛት
በ 60 አመታት ጊዜ ውስጥ የ ኢትዮጵያ ህዝብ ብዛት ከ 22 ሚልዮን ወደ አሁኑ 115 ሚልዮን አድጓል። በሚቀጥሉት 30 አመታት ደግሞ 205 ሚልዮን እንደሚደርስ ተገምቷል። ህዝባችን በ እዚህ ከፍተኛ ዕድገት ከ ቀጠለ፣ ብዙው ህዝብ በ ምግብ እጥረት እንደሚጎዳ ምንም አያጠራጥርም። ስለዚህ ህዝባችን ከ አሁኑ 2.6% በ አመት ዕድገት በ አነሰ ማደግ አለበት ምክንያቱም እንደ ኢትዮጵያ ኤኮኖሚያቸው በ እርሻ ላይ የተመሰረተ አገሮች ህዝብ እየበዛ ሲሄድ የ ኤኮኖሚ ዕድገት እየቀነሰ ይሄዳልና ነው፤ የ እርሻ መሬት ስለማይሰፋ እና የ ዝናብ ሁኔታ ከ አመት አመት ስለሚለዋወጥም ነው። ስለዚህ ወደፊት በ ህዝብ ብዛት የሚመጣውን ነውጥ ለ መቋቋም እያንዳንዱ ቤተሰብ ከ ሁለት ልጆች በላይ እንዳይወልዱ ህግ ማውጣት፤ የተላለፉትን ደግሞ በ ከፍተኛ የ ገንዘብ ቅጣት  መቅጣት የፖሊሲው አላማ እንዲሳካ ይረዳል።
4)   የ እርሻ መሬቶች
80% የሚሆነው የ ኢትዮጵያ ህዝብ የሚተዳደረው በ ግብርና ነው። የ እርሻ መሬቶች በ እንክብካቤ እንዲያዙ የ መሬት ይዞታው ከ መንግሥት ወደ ገበሬዎች መተላለፍ ይኖርበታል። ለ አርሶ አደር ልጆቻቸው ማውረስ ሊፈቀድላቸው ይገባል። ይህ የሚሆነው ግን ከ ግዴታ ጋር ነው፤ መሬቱን እርካብ በ መሥራት፣ ዛፎች በ መትከል፣ ወዘተ መንከባከብ ይኖርባቸዋል። ያን ካላደረጉ በ ህጋዊ ሂደት መሬቱን ሊነጠቁ ይገባል። መሬቱን የ መሽጥ መብት ግን አይኖራቸውም። ከሚጠብቅባቸው በላይ ከ አመረቱ ደግሞ ትርፉ ላይ ቀረጥ ሊከፍሉ አይገባም። በዚህ ፖሊሲ ብቻ እንግሊዝ በ ንግስት ኤልሳቤጥ ቀዳማዊት ዘመን ምርት በከፍተኛ ደረጃ ሊያድግ እና ከችግር ሊላቀቁ ችለዋል። ኢትዮጵያም የ ምግብ እጥረትን በዚህ ዘዴ መቋቋም ትችላለች።
5)   የ ከተማ ነዋሪዎች
ልክ እንደ ገበሬዎች የ ከተማ ነዋሪዎችም መፈናቀል የለባቸውም። የሚኖሩበት ቤት የተሰራበት መሬት ለ ህንፃ መሥሪያ ከተፈለገ ለ ነዋሪዎቹ ህንፃው ላይ ቤት ሊሰጣቸው ይገባል። ለ መኖሪያ ቤት ከ አልሆነ ደግሞ በ አቅራቢያ ሠፈር ቤት ሊሰጣቸው ይገባል። ይህ ፖሊሲ ዜጎች የ ማህበራዊ ቀውስ እንደአያጋጥማቸው ይረዳል። አዲስ ሠፈር ሄዶ ኑሮ መመሥረት ትልቅ ፈተና ነውና።
6)  ከፍተኛ የ ትምህርት ተቋማት
ከፍተኛ ተቋማት መንግሥት የሚያስፈልጉትን የ ሥራ ዘርፎች ቀይሶ የሚያሰናዳበት ማዕከል መሆን አለባቸው፤ እንደ አህኑ ዩኒቨርሲቲዎች የ ንግድ ዘርፍ መሆን የለባቸውም። ለ ሥራ የማያበቁ የ ዲግሪ ኮርሶች ላይ አመታትን ማቃጠል ለ ችግረኛ ልጆች ትልቅ በደል ነው። በዚያም ላይ ዕዳ ተሸክመው ይወጣሉ።
ከፍተኛ ተቋማት የሚገቡት ምርጥ ተማሪዎች ብቻ መሆን አለባቸው። በ ተደጋጋሚ እና የተለያዩ መመዘኛ ፈተናዎች ያለፉት ዩኒቨርሲቲ ሲገቡ ሌሎቹ እንደ አመጡት ውጤት የ ቴክኒክ እና የ እጅ ጥበብ ሙያ ትምህርት ቤቶች ቢማሩ ለ አገር ዕድገት ብዙ አስተውፅኦ ያደርጋሉ።
7)   ጤና አገልግሎት
ጤናማ ዜጎች በ መላ አገራችን እንዲኖሩ የ ገጠሩ ህዝብም የ ጤና አገልግልት እንዲያገኙ ጥረት መደረግ አለበት። ይህን አስፈላጊ ጉዳይ ተግባራዊ ለማድረግ፣ ከየአካባቢው ሃላፊነትን ያሳዩ ወጣቶችን መርጦ ማሰልጠን እና በየአካባቢያቸው መድቦ ማሠራት ጥሩ ውጤት ያስመዘግባል። ለተወሰኑ አመታት በተመደቡበት ቦታ እንዲሰሩ ግዴታ ይኖርባቸዋል።
8)   ለ መንግሥት ሥራ አቀጣጠር
ክፍት የ መንግሥት ሥራ ቦታዎች አቀጣጠር ግልፅ በሆነ መንገድ እና መስፈርት መሆን አለበት። ቅሬታን እና የ ዘመድ መጠቃቀምን ለማስቀረት ችሎታ ያላቸውን ሰዎች ከ መረጡ በኋላ በ አደባባይ ሎተሪ በማውጣት መቅጠር ሁነኛ ዘዴ ነው። ይህ ዘዴ የ ህዝብ አምኔታን ያሳድጋል። ህዝብም ለመንግሥት ድጋፍ ይኖረዋል።
9)   ኑሮን ማሸነፍ
 ከ ዘመነ ኢህአዴግ በፊት ተዘዋውሮ መሥራት ችግር አልነበረም፤ አሁን ግ/ን የማይታሰብ ነው፤ ስለዚህ ዜጎች በ ተወለዱበት አካባቢ ኑሮአቸውን እንዲመሰርቱ ማበረታት እና መርዳት ጥሩ ፖሊሲ ነው፣ ጎሰኝነት እስኪከስም።
10)   መጥፎ ልማዶች
ለጤና ጠንቅ የሆኑ ብዙ ልምዶች ተስፋፍተው በተለይ ወጣቱን ጥሩ ዜጋ እንዳይሆን እያደረጉት ነው። በዚህ ከቀጠለ ትውልድ ጠፋ ማለት ነው። ጫት ካልቃሙ የማያስቡና የማይንቀሳቀሱ ትውልዶች እየተበራከቱ ነው። ስለዚህ አስቸኳይ እርምጃ መውሰድ ያስፈልጋል። ሲጋራ፣ ጫት፣ አልኮሆል እና የ ቅንጦት ዕቃዎች ላይ ከፍተኛ ቀረጥ መደንገግ ተጠቃሚዎችን ይቀንሳል። በተወሰነ እድሜ ክልል ውስጥ ያሉ ወጣቶች በተለይ ሃሺሽ፣ ጋያ፣ ሲጋራ እና ጫት ሲጠቀሙ ቢገኙ በ ወንጀል ሊጠየቁበት ይገባል። ለ ምሳሌ አሁን ከ 16 አመት በታች ያሉ እነዚህን የተከለከሉ ጎጂ ነገሮች ዕድሜ ልካቸውን መጠቀም መከልከል አለባቸው።
11)   ሴትኛ አዳሪነት እና ልመና
እነዚህ ሁለት መተዳዳሪዎች እጅግ በጣም የሰውን ልጆች ስብ/ዕና የሚያዋርዱ ናቸው።  የ አገር መሪዎች እና ፖለቲከኞች ይህን የ አገር ውርደት በ አስቸኳይ መፍትሔ ሊያገኙለት ይገባል። በመጀመሪያ ደረጃ እነዚህ ሁለት መተዳደሪያዎች ከተወሰኑ አመታት በኋላ ወንጀል እንዲሆኑ ህግ ማውጣት እና በዚያን ጊዜ መንግሥት እራሳቸውን እንዲያቋቁሙ መርዳት ያስፈልጋል። ለምሳሌ ያህል ከተሞችን እንዲያጸዱ፣ ዛፎች እንዲተክሉ እና ውሃ እንዲያጠጡ ወዘተ ማድረግ ይቻላል።
12)   ሙስና
ሙስና በ አስፈሪ ሁኔታ እየተስፋፋ ነው፤ አንዳንድ ሰዎች ለሥራ ሲያመለክቱ ተቀዳሚ መመዘኛቸው የመስረቅ ዕድል መኖሩን ማወቅ ሆኗል፤ ይባላል። እንደ ማፍያ ቡድኖች በአገራችንም የቡድን ሌብነት ከተስፋፋ አገር ትጠፋለች/። ስለዚህ መንግሥት ይህን ውንብድና ማጥፋት አለበት/።
ከላይ የተዘረዘሩት ፖሊሲዎች ቢተገበሩ አገር ታድጋለች፤ ጥሩ ዜጎችም ይገነባሉ።
ኢትዮጵያን ፈጣሪ ይጠብቃት። ለ ህዝባችን የሚያስፈልጋቸውን ሁሉ ያድልልን።
ተጨማሪ ያንብቡ:  ከስልጣንዎ ሲባረሩ እውነቱን ይነግሩናል (ከይገርማል)

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Share