January 19, 2020
24 mins read

ሁሉንም መንግሥታዊ ጉዳዮች ከህዝብ እና ከሀገር ጥቅም አንፃር መመልከት ይበጃል። (ትህዳ ኃሣኤ ዘ ኢትዮጵያ)

“…THAT THE PRINCE MUST CONSIDER HOW TO    AVOID THOSE THINGS THAT
WHICH MAKE  HIM HATED OR  DESPISED .  IF HE CAN SUCCEED IN THIS, HE
WILL HAVE DONE  THE BEST HE CAN, AND HE NEED NOT FERE  ANY  DANGER IN
OTHER  CRITICISM    . . . . . ”

(Chapter 19 page 28 & 29

The Prince by Niccole Machiavelli}

(ነፃ ትርጉም። ከፅሁፉ ጭብጥ የተወሰደ)

አንድ መሪ(ልዑል) በሚመራው ህዝብ ዘንድ እንዳይናቅ እና እንዳይጠላ አካሄዱን ወይም እርምጃውን ማሣመርና
ለህዝቡ፣ሰላምና ፍትህ መጠንቀቅ ይኖርበታል። ይህንን ምክር ችላ ካለ እና ህዝብ ከጠላውና ከናቀው የሥልጣን
ጥመኞች በህዝቡ አመካኝተው በቀላሉ ከሥልጣኑ ያወርዱታል።( ከዚህ ሌላ እንዲጠላ እና፣እንዲናቅ የሚያደርገው ነገር
የለም።ግለሰብን፣ቤተሰብን፣የቤተሰብ ፀናሽ የሆኑትን ሴቶችን ፣ቤተሰብን፣ህብረተሰብን ያለ አድሎ ካከበረና  ሀገርን
በእጅጉ ከወደደ ሥለህዝቡ ፍቅር ሢሉ በእሱ ላይ የሚነሱ ሴረኞች አይኖሩም።።)

“አንድ ላይ እሥካሁን አብረንሽን ዘለቅነው

ክፉም አይነካሽም እምነትሽ ትልቅ ነው።

ፍቅር ካለሽ፣እምነት ካለሽ

ሁሉን እግር በእግር ታደርጌለሽ። ”

(ተወዳጁ ድምጻዊ ቴዲ ተደሰ ያንጎራጎረው ውብ እና ግሩም መልዕክት ያለው ግጥም ነው፡፡)

ትልልቆቹ ኃይማኖቶች ክርስትና እና የእስልምና ኃይማኖቶች  በኢትዮጵያ የገዘፈ ቦታ አላቸው።

በእምነት አንፃር ካየነው፣ለፈጣሪ የሚሳነው የለም።እናም ኢትዮጵያ እምነት ካላት(ህዝቧቿ እምነት ካላቸው)
በኢትዮጵያ ላይ ወይም በኢትዮጵያውያን ላይ ክፉ አይከሰትም።

በእርግጠኝነት ይህንን አውቃለሁ። የኢትዮጵያን ህዝብ  ታላቅ ያደረገው እምነቱ እንደሆነ።ኢትዮጵያውያን
የፈጣሪን መኖር የሚያምኑ  በመሆናቸው ብቻ ከ3000 ሺ ዓመት በፊት ታላቅነታቸውን እንዳሥመሰከሩ።በቅዱስ
መፅሐፍትም በተደጋጋሚ ኢትዮጵያ እንደተጠራች።  ኢትዮጵያውያን፣በሀገራቸው፣በማተማቸው ና በእምነታቸው ከቶም
እንደማይደራደሩ።…አዎ ይህንን አውቃለሁ።የአነዋር መስጊድ ገረቤት የራጉኤል ቤተክርስቲያን እንደሆነ አውቃለሁ።
ይህንንም ዋቢ በማደረግም እንደ ቴዲ ታደሰ ሀገሬ በፍፁም አትፈራርስም  እላለሁ። (መልካም የጥምቀት በዓል
ለመላ ኦርቶዶክሳዊያን ።)

ታሪክ   እና የጀግናውን የሀገሬን ህዝብ የአትንኩኝ ባይነት ቁንጥጫ የቀመሱ እንደሚመሰክሩት፣ ይህቺ
ሀገር ፣የሚሞቱላት  በሚሊዮን የሚቆጠሩ ጀግኖች ልጆች ሥላላት  ሊያፈርሷት የተነሱትን ሁሉ አፈራርሳለች እንጂ
አልፈ ረሰችም።

ኢትዮጵያ  ሀገሬ ፣ኢትዮጵያ ተብላ ለዘላለም  ትቀጥል ዘንድ ዛሬም የእምነት ማተቡን አጥብቆ  “እምዬ
ሀገሬ” እያለ   ለአንድነቷ እና ለክብሮ መሥዋት ለመክፈል የተዘጋጀ እልፍ  ኢትዮጵያዊ አለ።

እርግጥ ነው፣ከነዚህ በተቃራኒ ደግሞ፣  ኢትዮጵያን በትልቅ ፈተና ውስጥ እንድትወድቅ  ያደረጓት፣ በማወቅም
ሆነ ባልማወቅ፣ ከራሥ በላይ ነፋሥ የሚሉ ፣ ከፀረ ኢትዮጵያ ኃይሎች  በሚወረወርላቸው ፍርፋሪ የተነሳ ፣ከሆድ
ያልዘለለ ራእይ የሰነቁ ፣ የኢትዮጵያ የእንግዴ ልጆች አሉ።

እነዚህን የእንግዴ ልጆችን በመቅበር ፣በመቃብራቸው ላይ ታላቂቱን ኢትዮጵያ የሚገነቡ ልጆች ግን ይህቺ ሀገር
እንዳላት ወዳጅም ጠላትም ማወቅ አለበት። ዛሬም  በታላቅ ተጋድሏቸው ምንጊዜም ታሪክ የሚዘክረው ድልን ፣ሆዳቸው
አምላካቸው በሆነባቸው ላይ ለመቀዳጀት የተሠናዱ ሚሊዮኖችን ይህቺ ሀገር ማፍራቷን ልብ ያለው ነው ልብ ሊል
የሚችለው።

እኛ ልባሞቹ ፣ለኢትዮጵያ ለውድ እናታቸው   ያለአንዳች ሥሥት፣ህይወታቸውን የሚሰው፣ ዳር ድንበሯ ላይ
አጥንታቸውን የሚከሰክሱ ልበ ሙሉ ፣ ጀግና ልጆች ዛሬም እንዳሉ በተጨባጭ እያየን ነው።ለዚህም ነው፣የኢትዮጵያ
መከላከያ ሠራዊት የሀገሬ ኩራት ነው።በማለት ይህ ፀሐፊ ደጋግሞ  የሚፅፈው።

ትላንት እኮ  በኃያል ሀገሮች የአይዶሎጂ እና የጥቅም ሽኩቻ ነው የገዛ ሀገራችንን ኤርትራን ያጣናት።
በሠራዊቱ ወኔ ቢሥነት እንዳልሆነ ወዳጅም ጠላትም ይመሠክራል።

ትላንት ጀግና ወንድምና እህቶቻችንን ያጣነው በኃያላኖቹ እና በፀረ ኢትዮጵያ ኃይሎች ሴራ ነው።ዛሬም
በነዳጅ የበለፀጉ ሀገሮች ነገ ነዳጃቸው ሲያልቅ ዜጎቻቸው ዘላቂ ጥቅም የሚያገኙበትን መንገድ በዛሬ ሀብታቸው
አማካኝነት፣ በራሳችን ሀገር በሸፍጥ ሲያደራጁ እያሥተዋልን ነው።

ትላንትና ኃያላኑም ሆኑ የፔትሮ ዶላር ከበርቴዎች፣በአይዶሎጂ እና በኃይማኖት ሰበብ ፣ ጥሬ ሀብታችንን
ከመበዝበዝ ውጪ አንዳችም ተጨባጭ የልማት እገዛ አላደረጉልንም።ዛሬም የሚጠጉን በጥቅም እንጂ በወዳጅነት ብቻ
አይደለም።ጥቅም ካላገኙ ጀርባቸውንም አያሳዩንም።

አንዳች የሚነሽጥ ጥቅም ካላገኙም፣ ተጨባጭ የሆነ ወደ ብልፅግና የሚያሸጋግር  ፕሮጀክትን በማገዝ ቢያንስ
ዛሬም ከምንዳክርበት ከሥንዴ ልመና እንድንወጣ  አይረዱንም።

እርግጥ ነው፣ዛሬ ሆንን እንጂ ትላንት በምኒልክ እና በኃይለሥላሴ ዘመነመንግሥት ሥንዴ ለማኝ ወይም
ተመፅዎች አልነበርንም።የሥንዴ ልመና ታሪክ የ43 ዓመት  ታሪክ ነው ።

“ሀገራዊሥንዴ  ልመና” ከ 43 ዓመት በፊት  በዘመነ ደርግ ነው፤የተጀመረው። አምራቹ ኃይል ሀገሩን
ለመከላከል  እና ኤርትራ ከእናት ሀገሯ እንዳትገነጠል በፈቃዱ “ለእናት ሀገር ሁሉም ዜጋ  ሊሞት ይገባዋል”
በሚል የወቅቱ  መፈክር ፤ ወደጦር ግንባር ሥለተጓዘ የብዙ ገበሬዎች ማሳ ፆም በማደሩ የተነሳ ሀገራዊ የሥንዴ
ልመና መጀመሩ ይታወቃል።

ሀገሬን ለልመና የዳረጋት ይህ ችግር  ብቻ አይደለም ። ማባሪያ ባልነበረው የእርስ በእርስ  ጦርነት
ምክንያት ሀብታችንን በሙሉ ለምንተላለቅበት የጦር መሣሪያ  ግዢ ማዋል ግዴታችን ሥለነበር ገጠሩን  ከከተማው ጋር
የሚያሥተሳሥር የልማት ሥራ ባለመሰራቱ ፣በተፈለገው መጠን፣ የተመረተው እንኳ ወደከተማ አይመጣም ነበር።

እንደምታውቁት ሩሲያኖቹ  ወርቅን በክላሽ እና በታላላቅ መድፎች ፣ታንኳች አና አነሥተኛ ሚሣኤሎች (ዙ
ሃያሦሥት) በመቀየር ጥቅማቸውን በርዕዮተ ዓለም እያመካኙ፣ ማሳደድ እና ወርቃችንን መዝረፍ እንጂ ፣የገበሬው
ህይወት የማቀየርበትን፣ከተማና ገጠር የሚተሣሠሩበትን መንገድ ለመቀየሥ አልቻሉም። ይህንን ለመተግበር የሚያሥችል
ነባራዊ ሁኔታ ውሥጥም ባለመሆናቸውና ባለመገኘታቸው በይበልጥ  ደግሞ የጦርነቱ ሁኔታ ፋታ ሥላልሰጣቸው ኢትዮጵያን
ከድርቅ ሰለባነት ሊያተርፎት አልተቻላቸውም።

ከ27 ዓመት በፊት   የኢትዮጵያ መንግሥት፣ በዛ በማያ ባራ ጦርነትም ውሥጥ  ሆኖ እንኳ ፣ የመልካ ዋከና
ኃይድሮ ኤሌትሪክ ማመንጫን ፣  የዲክሲሥን ና የባሌ እርሻዎችን፤ የአጋርፋ  የገበሬዎቸ ማሠልጠኛን…
የአትክልትና ፍራፍሬን እርሻን …የኬሚካል  እና የመጠጥ  ኮርፖሬሽንን በማቋቋም የተሰሩ የመጠጥ ና የኬሚካል
ኢንዱሥትሪዎች (ሀረር ቢራ፣በደሌ ቢራ፣ኮስቲክ ሶዳ አዋሽ መልካሣ ሰልፈሪክ አሲድ ፋብሪካ ) እንዲሁም አዳዲሥ
የጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካዎች እና የሴራሚክ ፋብሪካ ፣  የቡና  እና የሻይ ልማት ወዘተ ኢትዮጵያን ወደብልፅግና
ለመውሰድ ራእይ ወታደራዊው መንግሥት እንዳለው በተጫባጭ አመላካች ነበር።

ወታደራዊው መንግሥት በተጨባጭ ሌብነትን በመጠየፍ፣  በኃቀኝነት የልማት ሥራዎችን ሠርቷል።  ኢትዮጵያን
ለማበልፀግ በቀበሮ ጉድጎድ ውሥጥም ሆኖ  የፈፀመው የልማት ሥራ፣ ሊያሥመሰግነው ይገባል።

ህወሃት መራሹ የኢህአዴግ 26 ዓመት ያለጦርነት የአገዛዝ ዘመን አንፃር የልማት ሥራውን ስናነፃፅረው ደግሞ
ወታደራዊው መንግሥት ለዚች ሀገር ከወያኔ መንግሥት የተሻለ የልማት ሥራ መሥራቱን እንገነዘባለን።

ትላንት (ዛሬ የለም አላልኩም) ከላይ እስከታች የወያኔ መንግሥት ሹመኞች በጨረታ ሥም አይን ያወጣ
ሌብነት እየፈፀሙ ነው፣ከተሞች ለሙ የሚባለው።ከተሟች የለሙት በባለሀብቱ ተሳትፎ እንጂ በማዘጋጃቤቶቹ
ጥረትአይደለም።

ለመሆኑ መንግሥት በልማት ሥም በሚሊዮን የሚቆጠሩ ብሮች ወደግለሰቧች ኪስ እንደሚገባ ያውቃልን?
የየክልል መንግሥታቱ ማዘጋጃ እና የገቢ መ/ቤቶችስ የብዝበዛ ምንጭ መሆናቸውን እና ሥንቶቹሥ በዚህ ብዝበዛ
ሰማይን በእርግጫ እንዳሉ፣ የትላንት ቢቀር የዛሬን አያይምን? ደሞስ ለምን የትላንት ሌባ ይተዋል።የትላንቱን ሌባ
ካመሰገንከው የዛሬውን ማወደሥህ አይቀርምና ይህ ፀረ-ፍትህ አካሄድ የቀበናን ወንዝ እንኳን አያሻግረንም።

ሌባን እና ዘራፊን፤ቅጥር ነፍሰ ገዳይን እና ወሮበላን በማሥታመም መንግሥትም ሀገርን ሊረጋጋ ቀርቶ ራሱ
ለመረጋጋት አይችልም። በታሪክ አጋጣሚ ሥልጣን በመዳፉ የወደቀችው አብይ መራሹ የኢትዮጵያ መንግሥት ይህንን
እውነት  ሊገነዘብ ይገባል። ከላይ በእንጊሊዘኛ የጠቀሥኩት እና በነፃ ትርጉም በአማርኛ የፃፍኩት የማኬቬሊ
የፖለቲካ ማሥጠቀቂያም የዋዛ አይደለም። የህዝብን የእውነትኑሮ በመረዳት ህዝብን በተጨባጭ መርዳት እና ከኑሮ ጫና
ማላቀቅ  እንጂ ለለሆዳቸው ያደሩ አንደበተ ርዕቱዎች ዲንጋዩን ዳቦ ሲሉ ማዳመጥ ለሀገር አይበጅም።

ዛሬ የህዝብን እውነት ሣይሆን ፣የራሥን ሆድ የሚያይ እና በሆዱ፣ለሆዱ ፣ሆዱን እያየ የሚንቀሳቀሥ ፓለቲከኛ
ነው፣በዚች ሀገር የሚበዛው።

ይገርማችኋል እኳ፣ሰው ኤልቲ ቪ ላይ በአማርኛ እየተከራከረ አማርኛ ቋንቋን ሲያጥላላ።እኔ እምለው፣ለምን
በአሥተርጓሚ አይከራከሩም?  ያሳፍራል።ቋንቋ ከመግባቢያነት አልፎ እንዲህ ጣዖት ሲሆን አያሰገርምም?!

እንዲህ ቅጡን አጥቶ፣ እያንዳንዱ ፓለቲከኛ ነኝ ባይ ሲሻኮት ፣ የራሱን ህይወት  ማጣት ብቻ ሳይሆን ሀገርን
አደጋ ላይ መጣሉ አይቀርም።ምድረ ፓለቲከኛ ከአንተ ህይወት ይልቅ የሀገር ህልውና ይበልጣል። ከራሥህ ይልቅ
ለኢትዮጵያ እና ለህዝቦ ብታሥብ ይበጃል።(ሥማ አንተ የዋህ ብረት ለበሥ እንዳልሆንክ እወቅ። ሰው አፈር እንጂ፣
“ዘ አይረን ማን” አይደለም። )

ትላንት  የመግሥት ሹመኛሁሉ ለግል ኪሱ ነበር የሚያሥበው። ሁላችሁም እንደምታውቁት ትላንት ህወሐት መራሹ
የኢትዮጵያ መንግሥት ለ 26 ዓመታት ጠንክሮ ይሰራ የነበረው ለኢትዮጵያ አልነበረም።ለራሱ አውራዎች እና ለዘረፋ
ተባባሪዎቹ ነበር ወጥሮ  ሲሰራ የነበረው ። በዚህ እንቅልፍ ለምኔ ዘረፋውም ለራሱ እና ለግብራአበሮቹ
ብልፅግናን ሲያወርስ ፣መላው የሀገሪቱን ዜጋ  በ50  ዓመት እንኳ ከፍሎ የማይጨርሰው የብድር  ዕዳ ጫንቃው ላይ
ጥ ሎበት ነው ፣በአመፅ  ከሥልጣን አናት ድንገትየተገፈተረው።

የህወሓት ባለሥልጣናት ፣ድንገት ተገፍትረው  ሥልጣን ይጡ እንጂ ዛሬም ቅንጦትን አላጧትም።እነሱ ጮማ
ሲቆርጡ ፣ በውሥኪ ሲራጩ  እና ሌት እና ቀን ” አሸሸ ገዳሜ !” ሲሉ ፣ የትግራይ  ህዝብ የዕርዳታ ሥንዴ
እየቆረጠመ፣ያልተጣራ ውሃ እየጠጣ ፣ ” እህህ ጠዋት ማታን..” እያዜመ ነው የሚኖረው። ” እህህ እሥከመቼ?
እያለ… እሥከመቼ በዳቦ እጦት ኑሮውን ይገፋል  ? እሥከ ዝናባማው የነሐሴ ምርጫ? ወይሥ…

ነሐሴ 10 ቀን ህዝብ ተወካዩን የሚመርጥበት ቀን እንደሚሆን በምርጫ ቦርድ ተገልፆል። ይህ  ሀገር አቀፍ
ምርጫ በዝናብ ወቅት ሥለሚካሄድ የጥቁር ሰማይ ወይም የክረምቱ ምርጫ ቢባል የሚቃወም ይኖራል ብዬ አላሥብም።

በዚህ የክረምት ምርጫ ዕለት ፣ሰማዪ ጠቁሮ ዶፍ ዝናብ ከማለዳው ጀምሮ ሊዘንብ ይችላል።ወይም ላይዘንብ
ይችላል።ወንዞች ሊሞሉ ይችላሉ።ገበሬዎች በነፍስ ውጪ እና ጊቢ ዓይነት የግብርና ሥራ ሊጠመዱም ይችላሉ።በደጋ
ሀገራት መንገዶች እጅግ አሥቸጋሪ ሊሆኑ እና  የምርጫ ጣቢያ ሠራተኞችን እና ታዛቢዎችን ሥራ ሊያከብዱ ይችሉ
ይሆናል።በዚህም ሰበብ ፣ላንቁሶ ታዛቢ ያላቸው ፓርቲዎች፣ ታዛቢዎቻቸው በየምርጫ ጣቢያው በሰዓቱ ላይገኚ ሥለሚችሉ
ያለታዛቢዎቹ ምርጫው ይካሄዳል ማለት ነው።ይህ ከሆነ ደግሞ እነሱ ምርጫው ተአማኒ አይደለም ብለው ይደመድማሉ።

እርግጥ ነው። አንድ ምርጫ ተአማኒ፣ነፃ እና ዴሞክራሲያዊ  የሚሆነው፣በምርጫ ቦርድ የተመዘገቡ ፖርቲዎች
ሁሉ፣ያለአንዳች ተፅእኖ እና አሻጥር በምርጫው ሂደት በመሳተፍ፣በመጨረሻም በየምርጫ ጣቢያዎቹ ታዛቢያቸውን
በማሥቀመጥ ግልፅና ቀጥተኛ ተሳትፎ ማድረጋቸው በተጨባጭ ሲረጋገጥ ነው።ይህ ባልሆነበት ሁኔታ ምርጫ ተካሂዷል
ማለት አይቻልም።ምርጫ በምርጫ ህጉ መሠረት ካልተከናወነ ደግሞ ፣ግርግሮች እና የባህር ማዕበል ዓይነት ህዝባዊ
ተቃውሞዎች ሊነሱ ይችላሉ።እነዚህን ለሀገር ሰላም አሥጊ የሆኑ ማዕበሎችን የነሐሴው ዶፍ ሊያሥቆማቸው ይችላል
ተብሎ ከታመነ እሰየው ነው።መቼም ቢሆን ነሐሴ እንደ ግንቦት ብራ ይሆናል ብለን መጠበቅም ሞኝነት ነው።

በነገራችን ላይ አንድ አንድ ቶካቲቭ ፖለቲከኞችን አትመኗቸው። “ሀገሪቱ ሩጫ ላይ ናት።ቢከፋም፣ቢለማም
ድርጊት።ይህ ትውልድ የድርጊት ትውልድ ነው። …” ብሎ የለ በዓሉ ግርማ። እናንተም ቆመን የምንጠብቀው ቀርፋፋ
ሰው የለም። እኔ የሌለሁበት መንግሥት ይፍረሥ የሚል ጫወታም አይሰራም። ተዱውሏል ወደቅዳሴ ግባ በሉት።  ይህንን
ከመለሥ የባሳ ምላሥም ሁላ።አዳሜ ብሯን ጉያዋ ሸጉጣ ህዝብ ህዝብ ሥትል አትገርምም።ቀዩም ጠይሙም ለእኔ አንድ
ናችሁ።እየተጫወታችሁ ያላችሁትም የፓለቲካ ቁማር ነው።ካርታችሁም የአንዳችሁ ቋንቋ፣ ሲሆን የአንዳችሁ ደግሞ
ጆከር ነው።ጆከሩ ካርታውን የት እንደሚጥለው ተቸግሯል።እናም እንደ ምርጫ ዘጠና ሰባት ምክር ቤት ግቡ አትግቡ
ድራማ ጀምሯል።ይገርማል።

እና ብራ ባይሆንሥ፣ዶፍ ዝናብ ቢጥልሥ? ህልም ተፈርቶ ሳይተኛ ሊታደር ነው እንዴ? አትለኝማ!? ቀልደኛ ነህ
ባክህ። በበረዶ እና በዝናብ ታጅበው የመምረጥ መብታቸውን እነዛ ከተጠቀሙ እኛም በዶፍ ዝናብ ውሥጥም ቢሆን ለምን
መብታችንን አናሥከብርም?እውነተኛው   የምርጫው ሰዓት እኮ ገና ነው።መቼ የፖለቲካ ፓርቲዎችን   ፖሊሢና ክርክር
አዳመጥን?እኔን ግርም የሚለኝ  ሁሉም እየተነሳ ህዝብ ይምረጠው አይምረጠው ሣያቅ  በየሚዲያው አሸንፋለሁ ማለቱ
ነው።ተወኝ ወንድሜ እንደ ዘጠና ሰባቱ ዓይነት  የምርጫ  ሂደት እሥቲ ይኑርና ህዝብ ማንን እንደሚመርጥ
እናያለን።(ከምርጫው በኋላ ከተደረገው ማጭበርበር ውጪ ፣ምርጫው በዓለም ታዛቢዎች ፊት የተካሄደና ክርክሩም
ህዝብን ለምርጫ የረዳ ነበር ።)

በአሥራአደኛው ሰዓት ላይ ብንሆንም  የምርጫውን ጉዳይ ለመራጩ ለኢትዮጵያ ህዝብ እንተውለት።ሁሉንም
የፓለቲካ ጉዳዮች ከዳንዴዎቹ ፓለቲከኞች አንፃር ሳይሆን ከብዙሃኑ ህዝብ ፍላጎትና ጥቅም አንፃር፣ አፅኖት ሰጥተን
በመመልከት ወደሚበጀው መፍትሄ ብንሄድ ይበጀናል። ለዚህም ደግሞ ዛሬም ኳሷ በጠ/ሚ  ዶ/ር አብይ አህመድ እጅ
ናት።

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Go toTop