October 5, 2013
28 mins read

ግንቦት ሰባት፤ ብርሀኑ፤ አንዳርጋቸው፤ የኤርትራ ነገር? ከተከሌሚካኤል አበበ

ተከሌሚካኤል  አበበ

የኛ ነገር፡ ክፍል 16፤ ከኔ ማእዘን፤

እንደ መግቢያ

  1. ይህ ጽሁፍ ሲታሽ፤ ሲሰቃይ እዚህ የደረሰ የቁጭት ጽሁፍ ነው፡፡ ወዲህም ግንቦት ሰባት የምወደው በሱ ግን ደስ ያላለኝ ፓርቲ ስለሆነና፤ ዲባቶ ብርሀኑ ነጋ ለኢሳት ዝግጅት ወደቶሮንቶ ስለሚዘልቅ፤ ያንዳንዶቻችንን ቁጭትና ጭንቀት ለመገለጽ የተሰናዳ ጽኁፍ ነው። ቀደም ያሉት የራስን የሆነን አካል የተቸሁባቸው ጽሁፎቼ ባንዳንድ ወዳጆቼ ዘንድ ቅሬታ ፈጥረዋል፡፡ በዚህ ጽሁፍ ውስጥ ወዳጅን የሚያስቀይመውን ንጥረ ነገር ለመሽረፍ ጥረት አድርጌያለሁ፡፡ ቀድሞውንስ በግል መንገሩ አይሻልም ወይ ለምን መጸፍ አስፈለገ ለሚሉት መልሱን ወደመጨረሻ እሰጣለሁ፡፡ ደግሞስ ፖለቲከኞች ወደ አደባባይ ሲወጡ ለመተቸት ተዘጋጅተው አይደለምን? ስለዚህ የሌሎችን ሀሳብ እተቻለሁ፤ የእኔም እንዲተች እነሆኝ፡፡

ግንቦት ሰባት፡ ለስልጣን ወይስ?

  1. ብዙ ሰዎች፤ በተለይም የድርጅቱ አመራሮች፤ ግንቦት ሰባት የፖለቲካ ፓርቲ አይደለም፤ ንቅናቄ ነው፤ ለስልጣን አይታገልም፤ ስልጣን የሚያዝበትን መንገድ ለማመቻቸት እንጂ ይላሉ። ይሄ የምንታገለው ለስልጣን አይደለም፡ ለስልጣን ስለማንታገል የውጭ ጉዳይ፤ የኢኮኖሚ፤ የትምህርት፤ የግብርና ፖሊሲ የለንም የሚለው ፍልስፍናቸው ምንም ሊረዳኝ አልቻለም፡፡ የስንፍና ወይንም የግዴለሽነት ወይም የሚሰሩትን የማያውቁ ወይንም የሚሸሹ ሰዎች ፍልስፍና ይመስለኛል፡፡ የስልጣኑን ጉዳይ ከዚህ በፊትም ሞግቻለሁ፡፡ አንዳርጋቸው ጽጌ ሞቶ አዲስ አበባ የሚገባ ብርሀኑ ነጋ፤ ስልጣን ለከማል ገልቹ ሰጥቶ ወደዲሲ ይመለስ፤ ስልጣን ለነጋሶ ጊዳዳ አስረክቦ ሂልተን ሆቴል ተረጋግቶ ይዋኝ፤ ማለት ጅልነት ነው። የማይመስል ነገር ነው፡፡ ሰዎቹ የማይታመኑ ሆነው አይደለም፡፡ ለኢትዮጵያ ከነብርሀኑ ነጋ በላይ የሚታመንና የታመነ ላሳር ነው፡፡ ነገር ግን፤ በፖለቲካ የረዥም ዘመን ታሪክ ውስጥ፤ የፖለቲካ መዝገበ ቃላት ውስጥ ካልገቡ ቃላት አንዱ እመኑኝ የሚለው ነው፡፡ በኢትዮጵያም በዓለምም ፖለቲካ ውስጥ ማመንም መታመንም ውድ ናቸው፡፡ ወይም የሉም፡፡
  2. ስለዚህ ጉዳይ ተጠይቆ ትዝ የሚለኝ ዲባቶ ብርሀኑ ነጋ የሰጠው መልስ ኢህአዴግ እንደወደቀ የግንቦት ሰባት የቡድንና የድርጅት ፖለቲካዊ ተልእኮ ያበቃል የሚል ነው፡፡ ከዚያ በሁዋላ ግለሰቦቹ እንዳሻቸው መሆን ይችላሉ፤ ድርጅቱ ግን ይከስማል አይነት ነገር፡፡ በቅርቡ በጻፈው ጸሁፍ ላይ ዲባቶ ሻውል በትሩ እንደገለጸው፤ የሚናገረውንና የሚጽፈውን በቅጡ የሚያውቀውን ብርሀኑ ነጋንም ይሁን፤ ካሉት ሁሉ የተሻለ ስብስብ ያለበትን ግንቦት ሰባትን በጣም የምንፈልጋቸው ከዚያ በሁዋላ ነው፡፡ ሕዝብም ኢህአዴግን የሚጥልለትን ድርጅት በቀላሉ አይለቀውም፡፡ አንድ ነገር በእምነት እናገራለሁ፤ እንደውም ብርሀኑ ነጋ ጎበዝ የሰላም ጊዜ መሪ ነው። ነበርም፡፡ ትንትም ዛሬም ነፍስ ካወቅኩበት ግዜ ጀምሮ፤ በሰላማዊ ኢትዮጵያ ስልጣን ይዞ ሲመራኝ ማየት የምመኘው ሰው ቢኖር ብርሀኑ ነጋ ነው። ብርሀኑ ስልጣን ስለሚወድ ሳይሆን፤ ብርሀኑ ጎበዝ የሰላም ግዜ መሪ ስለወጣውና ስለሚወጣው፡፡ ስለዚህ ግንቦት ሰባት ኢህአዴግን ጥሎ ስልጣን ይለቃል የሚለው አባባል ተግባራዊነቱ አጠራጣሪ ነው፤ በጎ ሀሳብም አይደለም፡፡

ብርሀኑ ነጋ

  1. ግንቦት ሰባት ኢህአዴግን ጥሎ ስልጣን ካልለቀቀ ደግሞ፤ እንደብርሀኑ ያለ በሳል የሰላም ግዜ መሪ ከቶም አይገኝም፡፡ መቼም ብርሀኑ ሰው፤ ፖለቲካ ደግሞ ሪስክ መውሰድ ነውና፤ ባለፉት አስር የፖለቲካ አመታት ብርሀኑ ነጋ አንዳንድ የፖለቲካ ስህተቶችን ፈጽሞ ሊሆን ይችላል፡፡ ለምሳሌ ብዙ ሰዎች ከቅንጅት አብዮት መክሸፍ ጋር አያይዘው ይከሱታል፡፡ በርግጥ ከስርአቱ ቀጥሎ፤ ብርሀኑም እንደመሪ ከሌሎች መሪዎች ጋር የሚጋራው ሀላፊነት ሊኖር ይችላል፡፡ ነብታሚ መስፍን ወ/ማርያም እንደሚሉት ግን ከቅንጅት መክሸፍም ይሁን መፍረስ ጋር አያይዞ ብርሀኑን ተጠያቂ በማድረጉ አልስማማም፡፡ ከዚያ ይልቅ፤ ባለፉት አስር የፖለቲካ አመታት ታሪኩ ብርሀኑ የፈጸመው ጉልህ የፖለቲካ ስህተት ቢኖር፤ እኛንም ኢትዮጵያንም ለማያዋጡት ሀይሉ ሻውል ሲል፤ እስካሁንም ያልተካነውን ልደቱ አያሌውን መስዋእት/ጭዳ ማድረጉ ነው፡፡ ከዚያ በተረፈ ቢሳካለትም ባይሳካለትም፤ ብርሀኑ የኢትዮጵያን የቅርብ ግዜ ፖለቲካ በዘመናዊ ቅኝት ለመቃኘት የሞከረ ጎበዝ መሪ ነው፡፡ ስለዚህም፤ ግንቦት ሰባት ኢህአዴግን ጥሎ አዲስ አበባ ከገባን፤ ብርሀኑን አንለቀውም፡፡ ብርሀኑ አማራዎች የማይኮሩበት፤ አማራ ያልሆኑ ኢትዮጵያዊያንም ብዙ የማይሰጉበት፤ መሀል ላይ ያለ አማካይ መሪ ነው።
  2. የጋደኞቼ የምጣኔ ሀብት መምህር፤ ዲባቶ ብርሀኑ ነጋ፤ ውጤታማ የአመጽ ወይንም የትጥቅ ትግል መሪ ይሆናል ወይንም ሊሆን ይችላል ወይ የሚለው ገና ወደፊት የምናው ነው። ያለፉት አምስት አመታትና ያለፉት ስድስት ወራት እንቅስቃሴዎች እንደሚያሳዩት ከሆነ ግንቦት ሰባት ብዙ የቤት ስራዎች ይጠብቁታል፡፡ በመሰረቱ፤ የትጥቅ ትግል የሚያራምድ ድርጅት መሪ በየሚዲያውና በየመድረኩ ቃለምልልስና ትንታኔ ካበዛ ጎበዝ መሪ ሳይሆን ጎበዝ ካድሬ ነው የሚሆነው። ጎበዝ ቃል-አቀባይ። ሁለቱንም መሆን የፈለገ ግን ይደበላለቅበታል። ስለዚህም ብርሀኑ ነጋ ፖለቲካዊ ትንታኔ መስጠት ሲያዘወትር ይነደኛል፡፡ ከዚህ ቀደም እንደጻፍኩት፤ የትንታኔ ጋጋት መቀነስ አለበት፡፡

አንዳርጋቸው ጽጌ

  1. በዲባቶ ብርሀኑ ነጋ ላይ ይሄንን ካልኩኝ በሁዋላ፤ ወደ አቶ አንዳርጋቸው ልዝለል፡፡ ልጆቹንና የምእራቡን ዓለም ምቾት ትቶ ወደበረሀ የወረደው ታላቄ አቶ አንዳርጋቸው ከአመት በሁዋላ ነው ወደሚዲያ የመጣው። የአቶ አንዳርጋቸውን የኢሳት ቃለምልልስ አለፍ አለፍ ብዬ ሰምቼዋለሁ። ጨርሼ ላየው አልቻልኩም፡፡ ያበሳጫልና፡፡ ቢሆንም፤ አንድም በስሜ ስለምጽፍ፤ ወዲህም ህይወቱን ለአገሩ እየሰዋ ያለን ሰው ስራ ጨክኜ መተቸት ፍትሀዊ አይደለም በሚል ትችቴን እመጥናለሁ። በጥቅሉ የአንዳርጋቸው ቃለምልልስ የሚያበሳጭ ነው፡፡ የቃለምልልሱ መርዘምም ለአንዳርጋቸው ሀሳቦች ህስተት መብዛትና አበሳጪነት አስተዋጽኦ አድርገዋል፡፡ የኢትዮጵያ ፖለቲከኞቻች ቃለምልልሳቸውን ለምን እንደሚያረዝሙት አይገባኝም፡፡ የስ ኦር ኖ ጥያቄን እንኩዋን፤ ጎትተው ካልመለሱ አይረኩም፡፡ ቃለምልልስ በረዘመ ቁጥር ለስህተትና ለትችት እየተጋለጥን እንሄዳለን፡፡ በአንዳርጋቸው ቃለምልልስ ላይ የተከሰተው ያ ነው፡፡ ባለፈው ሳምንት የቨርጂኒያ የግንቦት ሰባት ስብሰባ ላይም ሊያርመው አልቻለም፡፡
  2. በመሰረቱ፤ በኤርትራና ከኤርትራ ጋር እንስራ የሚለውን ሀሳብ ላለፉት አስር አመታት በቀንደኛነት ባራምድም፤ ሀሳቡን የምደግፈው፤ ኤርትራ ለኢትዮጵያ ቅን የምታስብ በቅኖች የምትመራ ቅድስት አገር ነች በሚል አይደለም። ከ1950ዎቹ መጀመሪያ ጀምሮ፤ የኢትዮጵያ ቁጥር አንድ ጠላት ሻእቢያ ነበር። ሻእቢያ ስልጣን ሲይዝ፤ የኢትዮጵያ ቁጥር አንድ ስጋት ኤርትራ ትሆናለች ማለት ነው። የኤርትራ ቁጥር አንድ ስጋትም ኢትዮጵያ ነች። በኤርትራና በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ ምንም የምንደባበቀው ነገር የለም። አንዳችን የአንዳችን ጠላቶች ነበርን። በተወሰነ መልኩ አሁንም አንዳችን ያንዳችን ስጋት ነን። ማንም የፖለቲካ ሀሁ የገባው ሰው ይሄንን ሀቅ አይስተውም። ኢትዮጵያዊያንና ኤርትራዊያን የፖለቲካ ትምህርት የማያስፈልጋቸው ጉዳይ ቢኖር፤ ይሄ የኤርትራና የኢትዮጵያ የተፈጥሮ ባላንጣነት ነው፡፡ የጥቅምና የታሪክ ባላንጣነት፡፡ ይሄንን የሳተ አንድም ውሸታም ነው አለያም መሀይም ነው። አቶ አንዳርጋቸውን አውቀዋለሁ። መሀይምም ውሸታምም አይደለም። ስለሻእቢያና ስለኤርትራ የተናገረው ግን እምነቴን ሸረሸረው። እውቀቴንም አጠራጠረው። ተመልካቹንና አድማጩን ስቷል ማለት ነው። ስለኤርትራዊያንና ስለኢሳያስ ሲያወራ፤ ትንሽ የኛንም እውቀት ዝቅ አድርጎ ያየው መሰለኝ፡፡
  3. በእውኑ ኤርትራውያን ስለኢትዮጵያ ያለቸውን ስሜት ለመረዳት አስመራና መንደፈራ መሄድ ያስፈልገናልን? በኤርትራ ጦስ ቤታችን ያልተነካ ሰዎች አለንን? በኤርትራና በኢትዮጵያ መካከል ያንን ደም ያፋሰሰ ታሪክ እንዳልተፈጠረ አድርገን መናገር አንችልም፡፡ አንክድም፡፡ የአንዳርጋቸው ትንታኔ፤ ያንን ሁሉ ደምስሶ፤ ኤርትራን በደምና ባጥንት፤ በጦርና በብረት ሳይሆን፤ ልክ እንደጅቡቲ በውል የሄደች አገር ሊያስመስል ነው የጣረው፡፡ ስለሻእቢያና ኤርትራ ክፉ ሳይወጣን፤ ስለኢሳያስ ቅንነትም ብዙ ሳናጋንን፤ ከኤርትራ ጋር ስለመስራት አስፈላጊነት ልንናነገር እንችላለን። ፖለቲካ ሪስክ ነው። የተሰላ ሪስክ እንውሰድ ነው ማለት የነበረበት፤ አንዳርጋቸው። አቶ ይሳያስ አፈወርቂን እላይ መስቀል አልነበረበትም። መለስ የኢትዮጵያ ጠላት ነበር። ህወሀትም ጸረ ኢትዮጵያ ፍላጎት ነበረው። አለውም፡፡ ነገር ግን ከኤርትራም ከባህር በርም ጋር በተያያዘ መለስን ሙሉ ተጠያቂ ማድረግና ኤርትራዊያንን ወይንም ሻእቢያን ነጻ ማድረግ ተጨፈኑ ላሞኛችሁ አይነት ነገር ነው። የሆነው እንዲህ ነው፡፡ ኤርትራውያን 30 አመት ለነጻነታቸው ታገሉ። በዝረራ አሸነፉን። ብዙ ሰዎች በዝረራ መሸነፋችን አይዋጥላቸውም። ባይወጥልንም እውነታው ያ ነው። ተሸነፍን። ሀሰብንም ምጽዋንም ያጣነው ስለተሸነፍን ነው። ከተሸነፍን በሁዋላ መለስ ሊፈይድው የሚችለው ብዙም ነገር አልነበረም። በርግጥም ፈርሞ የኤርትራን አገርነት አጽድቆ ከመገላገል ውጪ።
  4. መለስ ሀሰብን እንኳን ለማስቀረት ይችል ነበር የሚሉ ወገኖች አሉ። ሀሰብና ምጽዋ የታሉና? ገና ጥንት ኢህአዴግ አራት ኪሎ ሳይገባ፤ ኢትዮጵያን ሳያገባ ቀድመው ሄደዋል እኮ፡፡ ኤርትራዊያን ተሰውተው፤ ደማቸውን አፍስሰው በአሸናፊነት ያገኙትን መሬትና ባህር በድርድር ይሰጣሉ ወይ? የማይመስል ነገር ነው። ስለዚህ መለስን በብዙ ነገር ብንከሰውም የባህር በር አሳጣን ብሎ ሙሉ በሙሉ እሱን መክሰስና፤ የመገንጠሉ ሀሳብ ፊታውራሪና ንስሀ አባት የሆኑትን ኢሳያስ አፈወርቂን ነጻ ማድረግ ፍትሀዊ አይደለም። አንዳርጋቸው ያንን ነው ያደረገው፡፡ ኢሳት ይሄንን ቃለምልልስ ለምን እንደለቀቀው ሁሉ ግራ ገብቶኛል፡፡ ለፖለቲካ ፍጆታ ስንል ሁላችንም መለስ ሀሰብንም ኤርትራንም አሳጣን እያልን ስንከስ ቆይተናል። ያ ግን ከፖለቲካ ፍጆታ አልፎ፤ አቶ አንዳርጋቸው እንዳለው፤ እነ አቶ ኢሳያስም፤ ያ አይነት ሀሰብን ለኢትዮጵያ የመስጠት ዝንባሌ እያሳዩ፤ ወይንም ከኢትዮጵያ ጋር መኖር እየፈለጉ መለስ ገፋቸው የሚል ግንዛቤ እንደነበራቸው መናገር ስንጀምር፤ ለፖለቲካ ፍጆታ የተናገርነውን እንደ አውነት እየተቀበልነው እንመጣና የተበረዘ ታሪክ እንጽፋለን። የተሳሳተ ታሪክም እናወርሳለን። እዚህ ጋር ነው የአንዳርጋቸውና የግንቦት ሰባት ስህተት፡፡ ያ ብቻም አይደለም፤ በዚያ ቃለምልልስ ላይ፤ ከኤርትራ ጋር የመስራትን ሀሳብ ለማሳመን ሲል ብቻ አቶ አንዳርጋቸው አቶ ኢሳያስን ያልሆኑትን አድርጎ ሳላቸው። በዚህ የአንዳርጋቸው ቅብ፤ ራሳቸው አቶ ኢሳያስና ኤርትራዊያን የሚከፉ ይመስለኛል፡፡ አፍንጫው ድፍጥጥ የሆነውን ሰው አፍንጫ ሰልካካ፤ አንገቱና ትከሻው የተጣበቀውን የኔቢጤ ጉጣ መለሎ አስመስለው ቢስሉት እንደስድብ ይቆጠራል፡፡

ግንቦት ሰባት፤ ብርሀኑ፤ አንዳርጋቸ፤ የኤርትራ ነገር፡

  1. አቶ አንዳርጋቸውም ይሁን ግንቦት ሰባት ከኤርትራ ጋር መስራታቸውን ከጥንትም ስገፋፋው የነበረ ነገር ነውና ሙሉ በሙሉ እስማማበታለሁ፡፡ ኢትዮጵያም ይሁኑ ኤርትራ አንዳቸው ካንዳቸው ጋር ካልተካካኑ ሁልግዜም ቢሆን የሁለቱም ህልውና ስጋት ውስጥ መውደቁ አይቀርም፡፡ ይሁን እንጂ ግንቦት ሰባት ከብዙዎች ሁሉ የተሻለ ለፖለቲካ መሪነት የቀረበ ፓርቲ ሆኖ ሳለ፤ መሪዎቹ ለምን እየወረዱ፤ ካቅማቸው በታች እንደሚመሩ፤ አንዳንዴ ለምን እንዲህ ኤርትራን የተመለከተ ያለው ደረጃውን ያልጠበቀቀ ስምምነትና ትንተና ውስጥ እንደሚገቡ አልገባኝም። ከምርጫ 97 በሁዋላ፤ ያለውን ግዜ እንኩዋን ብንቆጥር፤ ኢህአዴግ ሌጂቲሜሲውን አጥቶ አገሪቱን ያለምንም ህጋዊ ስልጣን በጉልበት ብቻ የሚመራ ድርጅት ነው። ቅንጅት በ97 ምርጫ አሸንፎ ነበር ካልን፤ በውጭ አገር ካሉት ድርጅቶች ውስጥ፤ በንጽጽር ወደህጋዊ የቅንጅት ወራሽነት የሚጠጋው ፓርቲ ግንቦት ሰባት ነው። ይህ ሊያከራክር ይችላል። ቢያንስ ቢያንስ ግን በተመራጭ ባልንጀሮቹ የአዲስ አበባ ከንቲባ ተደርጎ የተመረጠው ብርሀኑ ነጋ፤ የግንቦት ሰባት መሪ ተደርጎ ሲመረጥ እንደመሪም ባይሆን እንደከንቲባ መተወን ነበረበት። እንግሊዝ ላይቀበለው፤ አሜሪካንም ላይጥመው፤ አውሮፓም ላያምረው ይችላል። ቢያንስ ግን ኤርትራ ትቅበለዋለች። ወደኤርትራ መግባት እንደተማሪ ሳይሆን እንደመሪ ነበር፡፡
  2. የኔ ሀሳብ እንዲህ ነው፡፡ ኢህአዴግን ለመጣል፤ ከነአደጋውም ቢሆን፤ ከኤርትራ ጋር መስራት ምርጫ ሳይሆን ግዴታ ነው፡፡ ግንቦት ሰባት አሁን አንዳርጋቸው እንደደረገው በጓሮ በር ሳይሆን ባደባባይ፤ የስራ አስፈጻሚውንና መገናኛ ብዙሀንን ይዞ፤ በአስመራና በሳዋ፤ በምጽዋና በሀሰብ፤ በቡሬና በሽራሮ፤ የሳምንት ካስፈለገም የወር የስራ ጉብኝት አድርጎ፤ ሌሎች ፓርቲዎችን የሚሰበስብና የሚያስተባብር፤ የሚመራ፤ ጊዜያዊ መንግስት የሚመስል ስብስብ ማቁዋቁዋም አለበት፡፡ ግንቦት ሰባት ለምን በጓሮ መጓዙንና ከአቅሙ በታች ለመተወን እንደመረጠ አልገባኝም። እንደሚመስለኝ፤ ይሄ ችግር የተከሰተው፤ ብርሀኑ ነጋ ከላይ እንዳልኩት ጎበዝ የሰላም ግዜ መሪ እንጂ ውጤታማ የትጥቅ ትግል መሪ መሆን ስላልቻለ ይሆን?

ጠቅላላ ነገሮች

  1. በተረፈ አንዳንድ የቅርብ ወዳጆቼ እኔ የግንቦት ሰባትም የአመራሩም የቅርብ ሰው እንደመሆኔ መጠን ይሄንን አይነት ትችትም ይሁን ሌሎች መሰል አስተያየቶችን ውስጥ ለውስጥ እንጂ በአደባባይ መጻፍ እንደሌለብኝ መክረውኛል። አንዳንዶቹ ገፍተው ሄደውም በጃችን በልተህ ጠጥተህ እንዴት እንዲህ ለውን ስራ ትሰራለህ ብለው ወቅሰውኛል፡፡ በመሰረቱ አንድ ሰው፤ በአባልነት ምክንያት፤ ወይንም ሰዎች አምነው በማቅረብ የነገሩትን ምስጢር፤ ወይንም ምስጥራዊ መረጃ መሰረት አድርጎ አይናገር እንጂ፤ በአደባባይ ላይ ያሉ መረጃዎችን፤ ይፋዊ ቃለምልልሶችን መሰረት አድርጎ መተቸቱ፤ መሪዎችን ለወደፊቱ የበለጠ ሀላፊነት እንዲሰማቸው፤ እንዲጠነቀቁ ያደርጋቸዋል፤ እንጂ ምንም ስህተት የለውም የሚለው አስተምህሮት ተከታይ ነኝ። ያ አካሄድ ዛሬ ትክክል እንደሆነ እርግጠኛ ነኝ፡፡ ነገ ስህተት ሆኖ ቢገኝ፤ ወቅቱ ሲደርስ ለመጸጸት ዝግጁ ነኝ፡፡
  2. በተረፈ፤ ከልምድ እንዳየሁትም፤ ሰዎች ወይም ድርጅቶች ወይም ስብስቦች በአደባባይ ሲነገራቸውና በምስጢር ሲነገራቸው ምላሻቸው አንድ አይደለም። ውስጥ ለውስጥ ሲነገራቸው፤ ቀድሞ ነገር አይመለከቱትምም። ስለዚህ ሰዎቹ እንዲመለከቱት ለማድረግም ጭምር ነው እንዲህ ያለውን ጽሁፍ በአድባባይ መጻፌ። ለመደመጥ፡፡ ትኩረት ለመሳብ፡፡ በርግጥም ከዚህ ቀደም እንደገጽኩት፤ ፖለቲካዊ ጽሁፍ ትኩረት ካልሳበ፤ እንዳልተጻፈ ጽሁፍ ይቆጠራል፡፡ ደግሞስ በክርክርና በትችት ያልፈተነ ሀሳብ ትክክለኛነቱ በምን ይታወቃል? ሀሳብን በነጻነት የመግለጽ መብትስ ዋና ዓላማ ያ አይደለምን? ማለትም፤ የሀሳብን ትክክለኛነት ለመፈተሽ ነው። በርግጥ ሰው ታምኖ የተነገረውን ምስጢር ያባከነ፤ አደባባይ ያወጣ እነደሆነ፤ ያኔ ያ ሰው ጥፋተኛ ነው። ከዚያ መለስ ግን፤ የራስንም ሰው ቢሆን መተቸት መልመድ አለብን፡፡ ተጠያቂነት እንዲሰማቸው ያደርጋቸዋልና፡፡ በስማችን መተቸትም ይልመድብን፡፡ በተለይ ስማቸወንና የቤተሰባቸውን ምቾት ሰውተው አደባባይ የወጡትን ፖለቲከኞች ስንተች፤ ከብእር ስም ጀርባ ተደብቀን መሆን የለበትም፡፡ በብእር ስም ጀርባ ተሰውረው የሚተቹ ፈሪዎች ናቸው፡፡

እሁድ እንገናኝ፡ ኦክቶበር 13፤

  1. ለማንኛውም በመጪው እሁድ፤ ኦክቶበር 13፤ እዚህ ከተማችን ቶሮንቶ የኢሳት የገንዘብ ማሰባሰቢያ ዝግጅት አለ፡፡ ዲባቶ ብርሀኑ ነጋና አቶ አበበ ገላው ወደከተማችን ይመጣሉና፤ 1573 ደንዳስ ዌስት ላይ ወደሚገኘው የሊትዌንያን አዳራሽ ብቅ ይበሉ፡፡ የዚያኑ ቀን ምሽት ላይ አብዱ ኪያር ከወደ ዲሲ መጥቶ ያጫውተናል፡፡ ፖለቲካ የማትወዱ፤ ከእኩለሌሊት በሁዋላ ኑ፡፡ እኛው ነን፡ መስከረም፤ 2006/2013፤ ቶሮንቶ

Latest from Blog

ከሃይለገብርኤል   አያሌው የኦቦ ሲራጅና የወይዘሮ ፉንታዬ ልጅ ጃዋር መሃመድ ትላንትን ዛሬንና ነጋችንን ሊያሳይ የሚችል መጽሃፍ አዘጋጅቶልናል:: በእውነቱ መጽሃፉ ሊነበብ በሚችል የሃሳብ ፍሰት ተቀንብቦ በአነጋጋሪነቱ ቀጥሏል:: ጃዋርን እና የቄሮን ትውልድ በቅጡ ለመረዳት መጽሃፉ ማንበብ

የጃዋር የፖለቲካ ጅዋጅዌ! “ድመት መንኩሳ አመሏን አትረሳ’’

ጥር 2 ቀን 2017 ዓ/ም   January 10, 2025  በኢትዮጵያዊነታችሁ፡ በኦርቶዶክሳዊ እምነታችሁ፡ በአማራነታችሁ፡ በአማረኛተናጋሪነታችሁ፡ በተሰነዘረባችሁ ብትር፡ ቤተ ሰብ፡ ወዳጅ ዘመዶቻችሁን ያጣችሁ: ልጆቻችሁን የቀበራችሁ፡ አካልችሁን ያጣችሁ፡ የተሰነዘረውን ብትር በመከላከል ላይ ያላችሁ፡ያለፈቃዳችሁ በመንግሥት ተጽእኖ ወደመግደልና

በኢትዮጵያዊነታችሁ፡ በኦርቶዶክሳዊ እምነታችሁ፡ በአማራነታችሁ፡ በአማረኛ ተናጋሪነታችሁ፡ በተሰነዘረባችሁ ብትር፡

January 10, 2025
መኮንን ሻውል ወልደጊዮርጊስ ¹⁵ የምድርም ነገሥታትና መኳንንት ሻለቃዎችም ባለ ጠጋዎችም ኃይለኛዎችም ባሪያዎችም ጌቶችም ሁሉ በዋሾችና በተራራዎች ዓለቶች ተሰወሩ ፥ ¹⁶ ተራራዎችንና   በላያችን ውደቁ በዙፋንም ከተቀመጠው ፊት ከበጉም ቍጣ ሰውሩን ፤ ¹⁷ ታላቁ የቁጣው ቀን  መጥቶአልና ፥ ማንስ ሊቆም ይችላል ? አሉአቸው ። ራእይ 6 ፤  15_17 ይኽ የመጽሐፍ ቅዱስ ቃል ። የኢየሱስን ልደት ሰናከብር የየሐንስ ራእይን ማንበብ ጠቃሚ ይመስለኛል ። ምክንያቱም በመጨረሻው ዘመን

ከኢየሱስ የፍርድ ቀን በፊት በህሊናችን ውስጥ ፍቅርን ለማንገስ እንጣር 

የምጣኔ ሀብታዊ ፍጥ፣ የፖለቲካ፣ የእውነትና የሰብአዊ መብት ታጋይ፣ የአመኑበትን ነገር ለመናገር እንደ ፖለቲከኛ በቃላት ሳያሽሞነሙኑ ቀጥታ የሚናገሩት የሀገሬ ኢትዮጵያ ታላቅ ሰው ነበሩ “ዘር ቆጠራውን ተዉት፤ የአባቶቻችሁን ሀገር ኢትዮጵያን አክብሩ!”  አቶ ቡልቻ ደመቅሳ

ሀገር ወዳዱ አቶ ቡልቻ ደመቅሳ ከዚህ አለም በሞት ተለዩ

January 6, 2025
ግን ይህ ሁሉ ወጣት የት ገባ? ግን ይህ ሁሉ ወጣት የት ገባ? ዛሬ፣ 2025 ዓ/ም ላይ ብንገኝም በዝንጋታ ገመድ ወደ ሞት እየተጎተትን እንደሆነ አናውቅም። (ሁል ጊዜ የሚሞተው የገነዝነው ይመስለናል። ) “ገብርዬ ነበረ

ግን ይህ ሁሉ ወጣት የት ገባ?

January 3, 2025
Go toTop