September 14, 2013
49 mins read

የኢትዮጵያውያን ባህልና የጋብቻ ቅድስና – (ተፈራ ድንበሩ)

ኢትዮጵያ ቅድስት መሆኗን የሚያሳዩ ማስረጃዎች፤
ኢትዮጵያ የሚለው ያገራችን መጠሪያ የተገኘው በካም ወገን ሴማዊ ከሆነውና ከነሙሴና አሮን በፊት ካህን ከነበረው መልከጼዴቅ ከሚባል ኢየሩሳሌምን ከመሠረተው ንጉሥ በተወለደውና ኢትዮጵ ከሚባል በኋላ ኢትዮጲስ ተብሎ የኢትዮጵያ ንጉሠነገሥት ከነበረ ሰው የመጣ ስያሜ መሆኑን የቤተክርስትያን መረጃዎች ያመለክታሉ (ፍቅሬ ቶሎሳ 1-10)። ኢትዮጵያውያን ከሁለቱ የኖህ ልጆች ካም (በኩሽ በኩል) እና ሴም (በአብርሃም በኩል ከእሥራኤላውያን ወገን) የተገኙና ተደባልቀው የተባዙ ዘሮች ሲሆኑ ለምሳሌም አፋር (ከ Ophir) የሴም ወገን ከሆነው ነገደ ዮቅጣን የመጣና በአፍሪካ ቀንድ ከጥንት ጀምሮ የነበረ ሕዝብ ሲሆን የአህጉሩ መጠሪያም ከዚሁ ቃል እንደተገኘ ይነገራል። በአርኪዎሎጂና አንትሮፖሎጂ ጥናት ከመረጋገጡ በፊት ሔሬዶተስና ዲዎዶረስ የተባሉ የጥንት የታሪከ ፀሐፊዎች የመጀመሪያው ሰው የኖረው በኢትዮጵያ እንደነበረ ጽፈዋል (Gates 68)። ኢትዮጵያውያን ዛሬ በቋንቋ ተለያይተው ይታዩ እንጅ፣ የካም፣ የሴም፤ የኦሞቲክና የኒሎቲክ ነገዶች ውሁድ የሆነ አንድነት አላቸው። በባህል ብቻ ሳይሆን በዘርም ተቀላቅለዋል። አሁን ባገራችን ከሚነገሩት ከ፹ በላይ ቋንቋዎቻችን ውስጥም ብዙዎቹ ከጥንቱ ግዕዝ፣ ከሳባ (ሱባ)፣ እብራይስጥ፣ ግሪክና ከሌሎች የሴምና የኩሽ እንዲሁም በአባይ ወንዝና ኦሞ ሐይቅ የተሰየሙ (ኒሎቲክ እና ኦሞቲክ ) አፍሪካዊ ቋንቋዎች ተገኝተውና ተቀያይጠው ትውልዶች እየበዙ ሲሄዱ በተጓዳኝ የተባዙ ናቸው።

መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚያመለክተን ኢትዮጵያ በእግዚአብሄር ዘንድ ከፍተኛ የቅድስና ደረጃ አላት (መዝሙር ፷፰፤፴፩፣ ትንቢተ አሞጽ ፱፡፯)። አገራችን መንፈሳዊነት የሰፈነበት ባህል ያላት ስለሆነች ልዩነቶችን አቻችሎ አብሮ መኖርን፣ ለጋስነትን፣ መረዳዳትንና እንግዳ ተቀባይነትን አዋህዳ ለቤተሰብም ከፍተኛ ክብር በመስጠት የኖረች የጥንት አገር ነች። ሆኖም ትውልድ እየበዛ ሲሄድ ይህች ምድራዊ ገነት የሆነች አገር በየቦታው የተሟላ የተፈጥሮ ሀብትና የአየር ንብረት ስላላት ብዙዎች ሕዝቦቿ በተለያዩ አካባቢዎች በወንዝ፣ ተራራ፣ ወዘተ ተካለውና ራሳቸውን ችለው ለረጅም ዘመናት ሲኖሩ በቋንቋዎቻቸውም እንደዚሁ ተለያይተው ዛሬ የሚታየውን የብሔር-ብሔረሰብ ሰያሜዎች ዝርዝር ሊያስከትል ችሏል (ተፈራ ድንበሩ 59-60) ።

በመዝሙር ፷፰፡፴፩ ላይ “ኢትዮጵያ ታበፅሕ እደዊኃ ሀበ እግዚአብሔር” የተባለችበትም ያለምክንያት አይደለም፤ ከእግዚአብሔር በሲና ተራራ ሕገ-ኦሪትን የተቀበለው ሙሴ የተመላለሰባት፣ ክርስቶስ ከእናቱ ከቅድስት ድንግል ማርያም ጋር በሕፃንነቱ ተሰዶ የሄደባት አገር በመሆኗ ኢትየጵያ ለቅድስት ድንግል ማርያም አሥራት እንደተሰጠችና በሷ አማላጅነት የመዳን ተስፋ እንደተሰጠን ቅዱሳት መጻሕፍት ይናገራሉ። በ፬ኛው መቶ ክፍለ ዘመን በቅዱስ ፍሬምናጦስ/አባሰላማ/ አማካይነት ክርስትና በመንግሥት ደረጃ ቢታወጅም ከዚያ በፊት ሐዋርያው ቅዱስ ማቴዎስ ወንጌልን ያስተማረበት አገር ነበረች፤ ቅዱስ ፊልጶስ ያጠመቀው የቤተመንግሥት ሹም ወደ ኢየሩሳሌም ለአምልኮት መሄድ ቀደም ሲል ኢትዮጵያውያን ከኢየሩሳሌም ጋር የነበራቸውን ሃይማኖታዊ ትሥሥር ያመለክታል (የሐዋርያት ሥራ ፰፡፳፮)። ክርስትና ቀድሞ ከገባባቸው አገሮች አንዷ ኢትየጵያ ስለሆነች ኦሪትንና ሐዲስን አጣምራ የቆየች ብቸኛ አገር ነች። እንዲሁም ፳፻/ ሁለት ሺ/ ዓመታት ከክርስቶስ ልደት በፊት በሥነጽሐፍ ዕድሜው ተወዳዳሪ ያልተገኘለት የግዕዝ ቋንቋችን በጽሐፍ ላይ የነበረ የመንግሥት መገልገያ ቋንቋ ሲሆን መጽሐፍ ቅዱስ መጀመሪያ ከተጻፈባቸው በጣት ከሚቆጠሩ — እብራይስጥ፤ አርማይክ፣ ፅርእ/ግሪክ/፣ ሲራይክ፣ ኮፕቲክ እና ከላቲን ቋንቋ በፊት የነበረ የአገራችን ትልቅ ሰነድ መሆኑ ሊያኮራን ይገባል። በቀደምት ሥነጥበብ ሙያ የሚታወቁት እነሼክስፔር፣ ሚካኤል አንጀሎና ላዎናርድ ዳቪንሲ ከመፈጠራቸው ከ፩ ሺ ዓመት በፊት ዓለም በጭለማ ውስጥ በነበረበት በ፮ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ታላቁ የቤተክርስትያናችን የዜማ አባት ቅዱስ ያሬድ ድጓ፣ ጾመድጓ፣ ምእራፍ፣ ዝማሬና መዋሴትን ደርሶ የግዕዝ፣ እዝልና አራራይን ቅኝት ለዓለም አበርክቷል።
አገራችን የብዙ ጻድቃንና ሰማዕታት አገር ነች፤ ለምሳሌ በ፲፭ኛው መቶ ክፍለ ዘመን የነበረችው ክርስቶስ ሰምራ የኃጢአት ምንጭ የሆነው ሰይጣን ከአምላካችን ይቅርታ ተደርጎለት የሰው ልጅ ሁሉ ሥርየት እንዲያገኝ ቀንና ሌሊት በመፀለይ የቅድስና ሥራ የሠራችና ሌሎች እንደ አቡነ ገብረመንፈስቅዱስ፣ አቡነ ተክለሃይማኖት፣ አቡነ አረጋዊ፣ አባ ሣሙኤል ዘዋልድባ፣… ወዘተ ያሉ የቅድስና ገድሎቻቸው በቤተክርስትያን የሚታወቅላቸው ታላላቅ መንፈሳውያን አገር ነች። እንዲሁም ኢየሱስ ክርስቶስ በቤተልሔም እንደሚወለድ አወቀው ለክብሩ የሚገባውን ስጦታዎች ይዘው በኮከብ እየተመሩ ወደ ኢየሩሳሌም ከሔዱት ሰባሰገል ከሚባሉ አዋቂ ሰዎች መካከል ኢትዮጵያውያን ነበሩበት። ኢትዮጵያ ኦሪትን ከሐዲስ ኪዳን ጋር አስማምታ ፈሪሀ እግዚአብሄር ያደረበትንና የሰውን ልጅ አክብሮ፣ መብቶቹን ጠብቆ ማኅበራዊ አኗኗርን አዋህዶ የተሟላ ባህል ካላቸው ቀደምት አገሮች ውስጥ የሚተካከላት እንደሌለ ያሁኑ ልጆቿ ጠንቅቀው ያውቃሉ?

የሮማው መሪ ጁሊየስ ቄሣርና የአይሁድ መሪ ሄሮድስ ሥልጣናቸውን ለማቆየት የተወለደ ሕፃን ሁሉ ሲገድሉ ኢትዮጵያ ሰብአዊነትን በሚከተሉ የጥበብ ሰዎች ትመራ ነበር (ፍቅሬ ቶሎሳ 29-30)። እንደ ፈረንሳይ፣ ጀርመን፣ እንግሊዝ የመሳሰሉ የአውሮጳ አገሮች ማንበብ መጻፍ በማያውቁባቸውና ያልሠለጠኑ (barbarians) በነበሩባቸው ዘመናት አገራችን በራሷ ፊደል በተጻፈ ሕግና በመንግሥት ትመራ ነበር። በአውሮፓ ሰዎች በባህር ላይ ዘረፋ (piracy) ሲተዳደሩ በነበሩ ጊዜ ኢትዮጵያ ሕግና ሥርዓት የሰፈነባት አገር ነበረች። ሰብአዊ መብት በሌላው ዓለም እየተጣሰ ሰላማዊ ሕዝቦች ሲበደሉ ያገራችን መሪዎች ታድገዋቸዋል። የአይሁድ አክራሪዎች በአረቢያ ናግራን፣ በግብፅ የእስልምና አክራሪዎች በክርስትያኖች ላይ የፈጸሙትን የሰብአዊ መብት ጥሰት ተከላክለዋል፤ ሆኖም በዓለም ላይ በተፈጸመው የሃይማኖት ጦርነት ውስጥ ኢትዮጵያ አልተሳተፈችም። የአገራችን መሪዎች ከ፪፻ በላይ የእስልምና እምነት ተከታዮችን በእምነታቸው ምክንያት ለሕይወታቸው ሲሸሹ በስደት እኤአ በ፮፻፲፫ እና ፮፻፲፭ ዓም ተቀብለው አስተናግደዋቸዋል። ስደተኞቹን እንዲመልሱ የአረቢያው መሪ አቡ ሱፊያን በኃይል ለመጠቀም ቢዝትም የኢትዮጵያ ንጉስ አርማህ (አል አስማሃ ወይም ነጋሽም ይባሉ ነበር) የሚመጣውን ኃይል በኃይል መክቶ ለመመለስ በመወሰን የስደተኞቹን መብት በማስከበር በዓለም የመጀመሪያው መሪ ነበሩ። በዚህ የተነሣ ንጉሡን ነጃሽ በማለት በስማቸው መስጊድ አሠርተው አክብረዋቸዋል፤ ሆኖም አንዳንድ የአሁኑ እስልምና ሃይማኖት ፀሐፊዎች ለክብራቸው የተሠራላቸውን መስጊድ እንደማስረጃ በመውሰድ ንጉሥ አርማህን እስላምናን ተቀብለዋል እስከማለት ደርሰዋል።

ኢትዮጵያ በተለያዩ ጊዜያት በእንግድነት ወይም በጥገኝነት መጥተው በሰላም የሚኖሩ የማናቸውንም የሕዝብ ወገኖች ተቀብላ በማስተናገድ የታወቀች ነች። ማናቸውንም ሃይማኖት የሚከተሉ ኢትዮጵያውያን ሰው በመግደል ጽድቅ አለ ብለው ሳይሆን በመፈቃቀር የሚያምኑ ሲሆን፤ የእስልምና፣ የአይሁድና የክርስትና እምነት ተከታዮች ተከባብረው በሰላም የሚኖሩባት አገር ነች። ኢትዮጵያዊ ስደተኞችን መንገድ በመምራት የምትታወቅ ሲሆን፣ ዛሬ እንደ ሲናይ ባሉ የአረብ በረሀዎች ስደተኞች በእንግድነታቸው መንገድ ሲጠይቁ በአጻፋው በአንድ በኩል ሃይማኖት አለን ብለው በሚመጻደቁ በሌላ በኩል ደግሞ ነፍሰገዳይ በሆኑ ሰዎች ንብረታቸው ተዘርፎ የሚሰጡት ሲያጡ የሰውነት ሕዋሳቶቻቸው ተቆራርጦ የሚሸጥበት ዓይነት ክስተት በኦጋዴን፣ አውሳ፣ ቤኒሻንጉል ጉሙዝ፣ ትግራይ፣ አፋር… ወዘተ በማናቸውም የኢትዮጵያ ክፍለ ሀገር ባላገር ዘንድ እንዲህ ያለ ድርጊት አስነዋሪ ነው።
ኢትዮጵያ ዲፕሎማሲን በማስተማር ቀደምት ከሆኑ አገሮች አንዷ ስትሆን ንግሥት ሳባ ለንጉሥ ሰሎሞን ባበረከተችው ስጦታ በእሥራኤልና ኢትዮጵያ መካከል አንድነት አንዲፈጠር ከማድረጉም በላይ ከንጉሥ ሰሎሞን በተወለደውና በኋላም በኢትዮጵያ በነገሠው ቀዳማዊ ምንሊክ አማካይነት የመጀመሪያው ጽላት ወደ አገራችን ገብቶ ይገኛል። ክርስቶስ የተሰቀለበት ግማደ-መስቀልም እንደዚሁ በአገራችን በግሸን ገዳም የሚገኝ ሲሆን በአገራችን የተፈጸሙ አያሌ መንፈሳዊ ገድሎችን ከቤተክርስትያን መረጃዎች ማግኘት ይቻላል።

ኢትዮጵያ በሕዝቦቿ የተባበረ ኃይል ወራሪዎችን እየመከተች የቆየች እንጂ በቅኝ ያልተያዘች አገር ከመሆኗም በላይ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅትን ቻርተር ካረቀቁት አገሮች አንዷ ነች። በቅኝ ግዛት የተያዙ የአፍሪካ አገሮችን ነፃ እንዲወጡ እንደነ ኔልሰን ማንዴላ ያሉትን በቅርቡም የናሚቢያን የነፃነት ታጋዮችን በማሠልጠንና ሌሎች በቅኝ አገዛዝ ሥር ለነበሩ አገሮች የቁሳቁስና የዲፕሎማሲ እርዳታ በማድረግ በአፍሪካ የፀረ-ቅኝ አገዛዝ ትግል ከፍተኛ ሚና ተጫውታለች። በ፲፱፻፶፭ ዓም የተመሠረተው የአፍሪካ ኅብረት በኢትዮጵያ መሪዎች የተገኘ ውጤት ነው ። እነዚህ አገራችንና ሕዝቦቻችንን ከሚያኮሩ ብዙዎች ነገሮች ጥቂቶች ብቻ ናቸው።

ኢትዮጵያዊ ሥነምግባር እጅግ የሚየኮራ — ሌብነት፣ ቅጥፈት፣ ሰውን በግፍ መግደል በየትኛውም እምነት የተወገዘ (taboo) ነው፤ እንኳንስ በሰው ላይ በእንሰሳት ላይ አንኳ ግፍ መፈጸም ከጥንት ጀምሮ በኢትዮጵያ ውጉዝ ነው። ዛሬ በአገራችን ከአሥራአምሰት እስከ ሃያ ሚሊዮን ሕዝብ ሥራ የሌለውና በአጠቃላይ 80% የሚሆነው ሕዝባችን ከድህነት መሥመር /poverty line/ በታች የሚኖር እንደሆነ የሚታወቅ ሲሆን አንደችግሩ መጠን ቢሆን ኖሮ በሌሎች አገሮች የሚፈጸሙ ወንጀሎች መናኸሪያ በሆነ ነበር፤ ሆኖም በዚህ የኑሮ ደረጃ ላይ ካለው ሕዝባችን ውስጥ እናቶች መቀነታቸውን እየፈቱ ያላቸውን ሲለግሱ ማየት የተለመደ ሲሆን፣ በየትኛውም አካባቢ ያለ ሕዝባችን ያለውን አካፍሎ የመኖር ባህል አለው። በበለፀጉ አገሮች በመንፈስ ጭንቀት ራስን ማጥፋት የተለመደ ሲሆን፣ የአገራችን ደሀ እንኳ በቅድስናው ስለሚያምን በተስፋ የተሞላ ስለሆነ መሬት ራሷ አፏን ከፍታ ካልዋጠችው በስተቀር እጁን ለሞት አይሰጥም።
ኢትዮጵያዊ ባህል በእድር፣ በእቁብ፣ ደቦና ሌሎች ማኅበራዊ ተቋሞች ተባብሮ ተጋግዞ መኖር ነው። ከመልካም ባህሎቿ መገለጫዎች ውስጥ ጋብቻ የተከበረ ተቋም ነው።

ቅዱስ ጋብቻ፤
ጋብቻ በሌላ አገላለጽ ትዳር ይባላል። ትዳር መተዳደር ከሚለው ቃል የተገኘና ኑሮን መሥርቶ በኃላፊነት ባለቤት ሆኖ ቤተሰብ ማስተዳደር ማለት ነው። ስለሆነም አንድ ሰው ትዳር ይዟል ሲባል በመሸበት አዳሪ ከመሆን ወይም ከነጠላነት/ላጤነት/ ወደሰከነና የተከበረ የኅብረተሰብ ሚና ተሸገጋግሮ ቋሚ/ሙሉ/ መተደዳሪያ ይዞ መኖርን ያመለክታል። በጋብቻ ተሳሥሮ ወልዶ ከብዶ መኖር የተቀደሰ ባህላችን ሲሆን በቤተሰብ አባላት መካከል ያለው መደጋገፍና መተሳሰብ በዓለም ላይ ተወዳዳሪ የሌለው ነው፤ ወላጆችን መጦር ወንድምና እህትን ብቻ ሳይሆን ዘመድ አዝማድን ወይም ረዳት የሌለውን የቤተሰብ አካል አድርጎ በሞግዚትነት ማሳደግ፣ ማስተማር ወይም ትዳር ማስያዝ ኢትዮጵያዊ ወግ ነው። ባል (ወንድ) እና ሚስት (ሴት) ተጋብተው ልጆችን በማፍራት የትውልድ ሐረግ የሚፈጠርበት ዓይነተኛ ሥርዓታችን ቤተሰብ ነው።

ጋብቻ ከባህላችን መገለጫዎች ውስጥ መሠረታዊ ሥርዓት ሲሆን በየብሔረሰቡ ያሉትን ዝርዝር የጋብቻ ሥርዓቶች በስፋት ለመግለጽ ጊዜና እቅም የሚጠይቅ ስለሆነ በዚህ ጽሑፍ ትኩረት ለማድረግ የተሞከረው በጋራ ባህሎቿና የኦርቶዶክስ ተዋህዶ እምነትን በሚከተሉት ወገኖች ያለውን ልማድ (tradition) ነው።

ስለጋብቻ መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል፤ “ እግዚአብሔርም ሰውን በመልኩ ፈጠረው፤ በእግዚአብሔር መልክ ፈጠረው፤ ወንድና ሴት አድርጎ ፈጠራቸው፤ እግዚአብሔርም ፣ ባረካቸውም፣ እንዲህም አላቸው፤ ብዙ ተባዙ ምድርንም ሙሉአት ግዟትም፤ የባህርን ዓሣዎች የሰማይን ወፎች በምድር ላይ የሚንቀሳቃሱትንም ሁሉ ግዟቸው” (ኦሪት ዘፍጥረት ፩፡ ፳፯-፳፰)። “እግዚአብሄር አምላክም በአዳም ከባድ እንቀልፍን ጣለበት፤ አንቀላፋም፤ ከጎኑም አንዲት አጥንትን ወስዶ ስፍራውን በሥጋ ዘጋው፤ እግዚአብሔር አምላክም ከአዳም የወሰዳትን አጥንት ሴት አድርጎ ሠራት፤ ወደ አዳምም አመጣት። አደምም አለ፤ ይህች አጥንት ከአጥንቴ ናት፤ ሥጋም ከሥጋዬ ናት፤ እርስዋም ከወንድ ተገኝታለችና ሴት ትባል። ስለዚህ ሰው አባቱንና እናቱን ይተዋል፤ በሚስቱም ይጣበቃል፤ ሁለቱም አንድ ሥጋ ይሆናሉ” ኦሪት ዘፍጥረት ፪፡ ፳፩-፳፬። እንዲሁም በማቴዎስ ወንጌል ፲፱፡ ፬-፮፣ ኦሪት ዘፍጥረት ፪፡ ፳፪-፳፬፣ የሐዋርያው ጳውሎስ መልእክት ወደ ኤፌሶን ሰዎች ም ፭ ቁ ፴፩-፴፪ ሁሉ እንደተገለጸው የእግዚአብሔር ቃል “ሰው አባቱንና እናቱን ይተዋል ከሚስቱም ጋር ይተባበራል፤ ሁለቱም አንድ ይሆናሉ” ይላል።
ዝሙትም ፈጽሞ የተከለከለና ኃጢአት ነው። “አመጸኞች የእግዚአብሔርን መንግሥት እንዳይወርሱ አታውቁምን? አትሳቱ ሴሰኞች ቢሆኑ ወይም ጣኦትን የሚያመልኩ ወይም አመንዝሮች ወይም ቀላጮች ወይም ከወንድ ጋር ዝሙት የሚሠሩ ወይም ሌቦች ወይም ገንዘብን የሚመኙ ወይም ሰካሮች ወይም ተሳዳቢዎች ወይም ነጣቂዎች የእግዚአብሔርን መንግሥት አይወርሱም። (፩ኛ ቆሮንጦስ ፮፡ ፲-፲፩) “ሥጋችሁ የክርስቶስ ብልቶች እንደሆነ አታውቅምን? እንግዲህ የክርስቶስን ብልቶች ወስጄ የጋለሞታ ብልቶች ላደርጋቸውን? አይገባም። ወይስ ከጋለሞታ ጋር የሚተባበር አንድ ሥጋ እንዲሆን አታውቁምን? ሁለቱ አንድ ሥጋ ይሆናል ተብሏልና። ከጌታ ጋር የሚተባበር ግን አንድ መንፈስ ነው። ከዝሙትም ሽሹ። ሰው የሚያደርገው ኃጢአት ሁሉ ከሥጋ ውጪ ነው፤ ዝሙትን የሚሠራ ግን በገዛ ሥጋው ላይ ኃጢአትን ይሠራል (፩ኛ ቆሮንጦስ ፮፡ ፲፭-፲፰)። እንዲሁም በማቴዎስ ወንጌል ፲፱፡ ፲፰-፳ ኢየሱስ ክርስቶስ ለሰዎች በሰጠው ሕግ “አትግደል፤ አታመንዝር፣ አትሥረቅ፣ በሐሰት አትመስክር፣ አባትህንና እናትህን አክብር፤ ባልንጃራችህን እንደራስህ ወደድ” ብሏል። ፩ኛ ቆሮንጦስ ፯፡ ፪-፮ ላይ፣ “ስለዝሙት ጠንቅ ለእያንዳንዱ ለራሱ ሚስት ትኑረው፣ ለእያንድንዲቱ ደግሞ ለራስዋ ባል ይኑራት። ባል ለሚስቱ የሚገባትን ያድርግላት፤ እንደዚሁም ደግሞ ሚስቲቱ ለባልዋ። ሚስት በገዛ ሥጋዋ ላይ ሥልጣን የላትም፤ ሥልጣን ለባልዋ ነው እንጂ፤ እንዲሁም ደግሞ ባል በገዛ ሥጋው ላይ ሥልጣን የለውም ሥልጣን ለሚስቱ ነው እንጂ።…እርስበርሳችሁ አትከላከሉ፤ ራሳችሁን ስለ አለመግዛት ሰይጣን እንዳይፈታተናችሁ ደግሞ አብራችሁ ሁኑ” ይላል።
እግዚአብሔር ጋብቻን የመሠረተው ሰው ብቻውን ከሚሆን ይልቅ ከሚስቱ ጋር እንዲረዳዱ፣ በመንሳዊ አንድነት በፍቅር ተባብረው አንዲኖሩና ዘር እንዲተኩ ነው። ስለሆነም ከዚህ ውጭ የሚደረግ ግንኙነት ሁሉ ሕገወጥና ኃጢአት ነው። ኦሪት ዘሌዋውያን ም ፲፰፡ ፳፫-፳፫ ላይ፣ “ከሴትም ጋር እንደምትተኛ ከወንድ ጋር አትተኛ ጸያፍ ነገር ነውና፤ እንዳትረክስበትም…” ይላል። ኦሪት ዘሌዋውያን ፳፡ ፲-፲፮ እንደተገለጸው የሚያመነዝር ወይም ግብረሰዶም የሚፈጽም ወይም ከእንሳሳ ጋር የሚገናኝ በሞት እንዲቀጣ ያዛል።

ልጅ በወላጆቹና ዘመዶች ታፍሮና ተከብሮ የሚኖርበት ኢትዮጵያዊና ማኅበራዊ ትልቅ እሴት ሲወርድ ሲዋረድ የቆየው ቤተሰብ ሲሆን፣ የመንፈሳዊ መሠረቱ ጥንካሬ በክርስትያኑ ሕዝባችን ብቻ ሳይሆን በሌሎች እምነት ተከታዮች ጭምር ጋብቻ በአገራችን ክቡርና የተቀደሰ ሆኖ ቆይቷል።

ቀደም ሲል ልጅህን ለልጄ እየተባለ ቤተሰቦች የልጆችን ጋብቻ ይወስኑ የነበረው ባህል ዛሬ ኋላ-ቀር ሆኖ ቢታይም በወቅቱ በነበረው ሁኔታ ለቤተሰብ መጠናከር ከፍተኛ አስተዋጽዖ ያደረገና ተቀባይነት የነበረው ባህል ነበር። ለአቅመ አዳምና ሔዋን ያልደረሱ ሕፃናት በቤተሰቦቻቸው ውሳኔ ተጫጭተው አንድ ላይ እንዲያድጉ ከተደረገ በኃላ ዕድሜአቸው ደርሶ በአካል መገናኘት ሲጀምሩ ጋብቻው እውን እየሆነ ይሄድ ነበረ። ሁለቱም ሌላ የሚያውቁት ጓደኛና የፆታ ግነኙነት ስለማይኖራቸው ጋብቻውን ከማክበርና ትዳራቸው እንዲሳካ እንደ አንድ አካል ለአንድ ዓላማ በመቆም ጠንካራ ቤተሰብ ከመገንባት በስተቀር ሌላ ምርጫ አልነበራቸውም፤ ሆኖም ይህ የቆየ ልምድ መሥመሩን ስቶ በተለይ ሴቶች ልጆች ሰብአዊ መብታቸው እየተገፈፈ ቅጥ ያጣ የወንድ ጭቆና እየከፋ ስለሄደ በሕግ የቀረ ሲሆን ሴቷም የመምረጥ ዕድል ልትቀዳጅ ችላለች።

ሆኖም ጋብቻን በነፃ ምርጫ የመፈጸሙ መብት የማያወላዳ ሲሆን ነፃነቱም በአግባቡ ትግባራዊ ካልሆነ የራሱ መዘዝ ሳይኖረው አልቀረም። ዛሬ በሃይማኖት ሥርዓት ካልተገዙ በስተቀር ወንዱም ሆነ ሴቷ ብዙ ጋደኞችን ሲፈትሹ ከቆዩ በኋላ ይጋባሉ፤ በራሳቸው ምርጫ መጋባታቸው በጉልህ የሚታይ የመብት መሻሻል ሲሆን ለወጣቶቹ መሳሳብ ቀጥታና ተዘዋዋሪ ምክንያት (ውበት፣ ሀብት፣ ፀባይ፣ ማህበራዊ ሚና፣ ወዘተ) እንደሚኖር የታወቀ ነው። ሆኖም ሲፈላለጉ የተሳሳቡበት/ የተማረኩበት ነገር ሲለወጥ ወይም ወረቱ ሲያልቅ መውደድ ሚዛኑን ያጣና በሰበብ አስባቡ አለመግባባትና የፍቅር መሻከር ይከተላል። ሲተጫጩ ሊማረኩበት የቻሉበት ነገር የፍቅር መነሻ መሆኑ ባይከፋም በመንፈሳዊ ኃይል ካልተጠናከረ መጀመሪያ ያሳሳባቸው ነገር ቢለወጥ፣ መንፈሳዊ እምነትና የቤተሰብ ጫና በበጎ መልኩ መፍትሔ ሊሰጥ የሚችልበት ኃይል ስለማይኖር የጋብቻው ኅልውና አደጋ ላይ ሊወድቅ ይችላል። ቤተሰብም የመበተን ዕድል ሊያጋጥመው ይችላል። እንዲየውም ሠልጥኗል በሚባለው ዓለም ውስጥ የግለሰብ መብት በከፍተኛ ደረጃ ስሚከበርና ይህም ለማኅበራዊ ፍላጎት ሳይሆን ለግለኝነት የሚያመቻች ስለሆነ በቅዱስነቱ ልጆችን ወልዶ በጋራ በአንድ መንፈስ በማሳደግ ፋንታ ጋብቻ እንደማንኛውም ኮንትራት እየታየ ጥቅሞችን እንደመስጠትና መቀበል ያሉ ቁሳዊ ልውውጥ ተራ ባህርይ ውስጥ ስለሚገባ ማኅበራዊ እሴትነቱና ለዛው ጠፍቶ በሕግ ሽፋን ውስጥ ብቻ እርቃኑን ስለሚቀር ፍቅር አልባ ይሆናል፤ ዓላማውን ለመፈጸም ብቃት ከማጣቱም በላይ ሕልውናውም አስተማማኝ አይሆንም።
በሌላ መልኩ ዛሬ በመብት ስም በተለይም ሠለጠኑ በሚባሉት አገሮች እየተከሠተና አልፎ አልፎም በመንግሥት ደረጃም ዕውቅናን ያገኘው እጅግ አሳፋሪ የሆነው የተመሣሣይ ፆታ ጋብቻ /same sex marriage/ ጉዳይ ሲሆን ኅብረተሰባችን ውስጥ ያልገባ ቢሆንም በተለይ በመደበኛ ትምህርት ቤት በሥነፍጥረት /biological science/ ትምህርት የሰዎች የግል ምርጫ መሆኑን እንዲያይ ተደርጎ የሚማረው ወጣት በማኅበራዊ ኑሮ ላይ የሚያስከትለውን አደገኛነት ጠንቅቆ እንዲያውቀው ማድረግ ያስፈልጋል።

ስለተመሣሣይ ፆታ ግንኙነት ወይም ጋብቻ እግዚአብሔር በሰዶምና ገሞራ ሕዝቦች ላይ ቅጣት በመፈጸም ለዓለም ሕዝብ ትምህርት ሰጥቷል። ይህም በኦሪት ዘፍጥርት ም ፲፰ እና ፲፱ ላይ ተገልጿል። ሰዶምና ገሞራ በሚባሉ በዮርዳኖስ ወንዝ ዳርቻ በሚገኙ ሁለት የጥንት ከተሞች ውስጥ እግዚአብሔር ከፈቀደው የተፈጥሮ የፆታ ግንኙነት ውጭ ወንድ ከወንድ እየተገናኘ ኃጢአት ስለበዛ እግዚአብሔር ከተማውን ከነሕዝቡ ሊያጠፋ እንዳሰበ ለአብርሃም ነገረው። አብርሃምም ጥቂት ንጹሐን ሰዎች ቢገኙ እንዲምርለት ለምኖት ፲ እንኳን ንጹሐን ሰዎች ቢገኙ በነዚያ ምክንያት ሁሉንም እንደሚምርለት እግዚአብሔር ቃል ገባለት። በመሸ ጊዜ ሁለት ሰዎች ወደሰዶም ገቡ፤ ሎጥም በሰዶም በር ተቀምጦ ነበር፤ ሎጥም በእንግድነት ተቀብሎ ያሳድራቸው ዘንድ ለመናቸው፤ በቤቱም አስተናገዳቸው፤ ሆኖም የሰዶም ሰዎች ተሰብስበው እንደተለመደው ሁለቱን ሰዎች በግበረሥጋ ሊደፍሯቸው የቤቱን በር ሰብረው ሊገቡ ሎጥን በታገሉት ጊዜ በሰዎች ተመስለው የመጡት ሁለት እንግዶች መላእክት ስለነበሩ ሕገወጦቹን ሰዎች አሳወሯቸው፤ ሎጥንም አሉት፣ ቤተሰብህን ይዘህ ከዚህ ከተማ ውጣ፤ እኛም ይህን ከተማ እናጠፋዋለን አሉት፤ በዘገየ ጊዜም አዝነውለት እጁን ይዘው አወጡት፤ ወደኋላም እንዳያይ ነገሩት፤ ከነቤተሰቡም ከሰዶም ወጥቶ ከመቅሰፍቱ ሲድን ሰዶምና ገሞራ ከነሕዝቡ ተቃጠሉ፤ ሆኖም የሎጥ ሚስት ወደኋላ ስለተመለከተች የጨው ሀውልት ሆና ቀረች። ከዚህ በኋላ ሕገወጥ የፆታ ግንኙነት ግብረሰዶም ተባለ።

ዛሬ ያለው ችግር በአንዳንድ ማህበረሰቦች ዘንድ እንዲህ ያለ የፆታ ሥርዓት እንደ የግለሰብ ነፃነት ወይም የፆታ ግንኙነት ምርጫ መታየቱ ሲሆን ሊሰመርበት የሚገባው ጉዳዩ በግለሰብ ላይ ብቻ ሳይቆም ቤተሰብን፣ ብዙሓን ሕዝቦችን፣ እንዲሁም አገርን የሚበክል ነገር መሆኑ ነው።
The liberal choice for sexual orientation does not stop on an individual. Homogeneous marriage distorts the basic fabric of the social network reflected in a natural family of parent-offspring relationship by obliterating this human relationship and throwing it into the abyss of mere sexualized instinct.

ባሁኑ ጊዜ በአንዳንድ መንግሥታት የተመሣሣይ ፆታ ጋብቻ መፈቀድ በጥንቃቄ ሊታይ የሚገባው ጉዳይ ነው። ሰዎች በዚያ ባሕርይ በመነደፋቸው ምክንያት ኅብረተሰቡ እየተጸየፋቸው ስላገለላቸው ራሳቸውንም እስከማጥፋት የደረሱ ስላሉ በአብዛኛው መንፈስ መድልዎ /discrimination/ ሳይፈጸምባቸው እንደሌሎች ዜጎች በሰላም የመኖር ነፃነት እንዲኖራቸው ተብሎ አገርን ከማስተዳደር አንፃር እየተወሰደ ያለ እርምጃ ነው አንጂ ትክክል ሆኖ አይደለም ። ለምሳሌ ሲጋራ አጫሾች ሰብአዊ መብት ተጠብቆላቸው በተከለለ ቦታ ማጨሳቸው ምርጫቸው ተቀባይነት አለው ማለት አይለም፤ ሲጋራንም የጤንነት ጠንቅ ከመሆን አያስቀረውም። ከሰብአዊነትና ደህንነት አንፃር የግለሰቦችን ነፃነት ለመጠበቅ የሚወሰደው ሕጋዊ አቋም ወይም አስተዳደራዊ እርምጃ የግለሰቦቹን ጥፋትና ስህተት ትክክለኛ አያደርገውም፣ መቻቻልን /tolerance/ እንጂ። በመንፈሳዊ መንገድም ብናየው እግዚአብሔር ሕግን የሰጠን በፈቃዳችን አንድንፈጽም ሲሆን ሕጉን ባለመከተል ኃጢአት ብንሠራ የምናጣውን ሁሉ ገልጾልናል (፩ኛ ጴጥሮስ ፪፡ ፲፮፣ ገላትያ ፭፡ ፩ የዮሐንስ ወንጌል ፰፡ ፴፩-፴፮)፤ ለመዳን ፈቃደኞች ካልሆንን እና የመዳኛውን ሕግ ትተን የመሞቻውን ነፃነት የምንመርጥ ከሆነ እንጎዳበታለን። ስለሆነም የእግዚአብሔርን ሕግ ከመከተል በስተቅር ሌላ የሚጠቅም አማራጭ እንደሌለ ማውቅ ብልህነት ነው።

የተፈጥሮ ቤተሰብና ሚናው፣
ሰው ሊወለድ የሚችለው ከተፈጥሮ እናትና አባት ብቻ ነው። ሆኖም በማደጎ እጅ ላይ የወደቀ ልጅ የማደጎ ወላጆቹ ምንም ያህል ደጋግ ቢሆኑ የማንነት ጥያቄ ማንሳቱ አይቀርም፤ ይህ ደግሞ የሥነልቡና ችግር ይኖረዋል። ወላጆቻቸው የሞቱባቸው ልጆች እንኳ ከማደጎ ወላጆች ጋር የሚኖራቸው ግንኙነት እስከሞት ድረስ ያደረሰ ቀውስ ማስከተሉ በየጊዜው በዜና ማሠራጫዎች ይሰማል። በአሜሪካን አገር ብቻ ከ፲፱፻፹፱ እስከ ፳፻፲፫ ዓም በማደጎ ከውጭ አገር ከመጡ ሕፃናት ውስጥ ፪፻፺፫ ሞትና ሌላ ከባድ ጉዳት እንደደረሰባቸው ኒጌል ባርበር የተባለ ሳይኮሎጅስት ካቀረበው ስታትስቲከስ ታውቋል።

የተመሣሣይ ፆታ ጋብቻ ብለው ግብረሰዶማውያን የሚጠሩት እውነተኛ ጋብቻ ሳይሆን ሕገወጥ እና በወሲብ ላይ ያተኮረ ግንኙነትና ዝሙት ነው። በአሁኑ ጊዜ ዓለምን እየበከለ ያለው የተመሣሣይ ፆታ ጋብቻ ዓላማው ፍትወተሥጋ (ወሲብ) ብቻ ሲሆን ብዙ ተባዙ ምድርንም ሙሉአት የሚለውን አምላካዊ ቃል የሚፃረር ስለሆነ ልጆች ከወላጆቻቸው ውጭ በእንጀራ እናት ወይም እንጀራ አባት ሥር ስለሚያድጉ የእናት-አባት የወንድም-እህት ወዘተ ቤተሰባዊ ፍቅርና ጣእም ከቶውንም ያጣሉ። ምክንያቱም ከተቃራኒ ፆታዎች (ባልና ሚስት) ውጭ የሚጋቡ ሰዎች ልጅ ለማግኘት በማደጎ ማምጣት አለበለዚያም አመንዝራ የመፈጸም ምርጫ ውስጥ ይገባሉ። እግዚአብሔር ለሰዎች የፈቀደውን የወላጅ-ተወላጅ የተፈጥሮ ሕግ ተከትሎ በቤተሰባዊ ግንኙነት ማኅበራዊ ኑሮ በመኖር ፋንታ እንደ እንሰሳ በዘፈቀደ የመገናኘትና አንደከብት የአባቱን ማንነት ጥያቄ ውስጥ የሚጥል ተወላጅን (offspring) ያስከትላል። በዚህ መልክ ልጆች የተባሉ ተወላጆች ሁሉ እውነተኛ አባትና እናት ሳይሆን በማደጎ ወላጆች ሥር ስለሚያድጉ ይህ የትውልድ ሐረግን ስለሚያጠፋ ሰዎችን በዝምድና ማየት ሳይሆን በአካል ብቻ የመቁጠር ዕድል ስለሚያስከትል ፍቅር፣ ኃላፊነት፣ ሞራል፣ የማንነት ጉዳይ…ወዘተ እየደበዘዙ ሰብአዊነት በእንሰሳዊ ባሕርይ ይዋጣል።

ቤተሰብ ከእግዚአብሔር የተሰጠን በረከትና ልጆች በማኅበራዊ ፍጡርነት ከእግዚአብሔር በተሰጣቸው ፀጋ ፍቅርን የሚያዩበት፣ የሚገልጹበት ትንሹ የኅብረተሰብ ሕዋስ ነው። “ዞሮ ዞሮ ከቤት ኖሮ ኖሮ ከመሬት…” እንደሚባለው ቤተሰብ ተወዳዳሪ በሌለው መስዋዕትነት የተፈጥሮ ፍቅር የሚተገበርበትና ልጅ በወላጁ፣ ወላጅ በልጁ..ወዘተ ፍጹም ተስፋ የሚጥልበትና የሚመካበት የአለኝታነት መገለጫ ነው፤ ቤተሰብ የሰዎች ሰብአዊ ክብርና የትውልድ ሐረግን ተከትሎ የሚመጣ ወግና የማንነት መግለጫ ነው፤ ቤተሰብ በተፈጥሮ የሚተማመኑበት የአንድነትና የባለቤትነት መገለጫ አካል ነው፤ ቤተሰብ የራሴ ከሚሉት አካል ጋር በእውነት ስለ እውነት ከምንም ጋር በማይተካከል ነፃነት የሚገናኙበት በእግዚአብሔር ፀጋ የተገኘ ሕዋስና ርህራሄን፣ ምህረትን፣ ይቅርታንና ልግሰናን የሚያገኙበት ትንሹ መንግሥት ነው፤ ቤተሰብ ተወዳዳሪ በሌለው ቅንነት ኃላፊነት የሚፈጸምበት የኅብረተሰብ አካል ነው። ቤተሰብ ይህን ሁሉ ማኅበራዊ እሴት ተሸክሞ የሚቆም የኅብረተሰብ ምሰሶ ነው። ነገር ግን ከላይ እንደተገለጸው የተመሣሣይ ፆታ ግንኙነት ሕገወጥ ከመሆኑም በላይ ቤተሰብን መሠረት ያሳጣዋል።

መልካም ባህላችንን ጠብቀን ለሌላው ዓለም ማስተማር፣
ምሰሶ ከተዛባ ቤት እንደሚናጋ ሁሉ ቤተሰብም ከእግዚአብሔር የተሰጡትን ማኅበራዊ እሴቶች መሠረት ካጣ ኅብረተሰብ ይናጋል፤ የሰው ልጅም መንፈሳዊ ኃይሉን ስለሚያጣና ለእንሰሳዊ /instinct/ ሥጋዊ ፍላጎት በመገዛት ሙሉ ሰብአዊነቱን ስለሚያጣ የራሱን ክብር ዝቅ ያደርጋል። በዚህ የተነሣ መንፈሳዊ ሙሉነት አይሰማውም። ሰብአዊ ክብሩን የማይጠብቅ ሰው ጥሩ ማኀበራዊ ባህል ሊኖረው አይችልም። ፍቅር፣ ኃላፊነት፣ ይሉኝታ፣ ሞራል በተሞላበት ማኅበራዊ ባህል ያልተገነባ ቤተሰብ ደግሞ ለቁሳቁስና ግብረሥጋ ግንኙነት የሚተባበር ልቅ የሰዎች ስብስብ ስለሚሆን ለማናቸውም ሕገወጥ ተግባሮች የተጋለጠ ነው፤ ምክንያቱም ሥጋዊ ፍላጎቱን ሊገዛ ካልቻለ እንኳንስ ለመንፈሳዊ ሕይወት ቀርቶ ሰው-ሠራሽ ለሆነውም የመንግሥት ሕግ መገዛት አይችልም። ስለዚህም ነው የአመንዝራ ትውልድ እየበዛ የአንድ ወላጅ ልጆች የሚበዙበትና ስብእናቸው ያልተሟላ ስለሚሆን ቁሳዊ ችግር እንኳ ሳያግጥማቸው ሰዎች በመንፈስ ጭንቀት ሐሳርና መቅስፍት የሚደርስባቸው።

ሰው ራሱን መግዛት አቅቶት በሥጋዊ ፍላጎቱ ከተሸነፈ ለእንስሳዊ ባህርይ ስለሚገዛ የራሱን ሰብአዊ ክብር ከማጣቱም በላይ የቤተሰቡን /ዘመዶቹን/ የተፈጥሮ ግንኙነት በጣጥሶ ህልውናቸውን ያጠፋል። ቤተሰብ ጠንካራ ማኅበራዊ መሠረት ከሌለው ደግሞ አንድነት የሌለው በደመነፍስ ፍላጎት የተሞላ የግለሰቦች ጥርቅም ስለሚሆን አጥንት እንደሌለው ሥጋ የመፈራረስ ዕድል ውስጥ ይወድቃል። የቤተሰብ መዳከም ደግሞ የኅብረተሰብን ድርና ማግ ይበጣጥሰዋል፤ ይህም መልካም ሰብእናን የሚያሳሳ ስለሚሆን የአገርን ማኅበራዊ እሴቶች በማጥፋት ዜጎችን ከኅብረተሰቡ ጋር ትሥሥር ሳይኖራቸው የግል ፍላጎታቸውንና ጥቅማቸውን ለማሟላት ብቻ የሚፈልጉ በዘፈቀደ ስሜት የሚመሩ የግለሰቦች ክምችት በማድረግ ሰብአዊነትን ስለሚያጠፋ ለመልካም አስተዳደር መጓደል ከፍተኛ አስተዋፅዖ ሊያደርግ ይችላል።
“እንሰሳ ሰው ሆነ ሰውም እንሰሳ ሆነ” እንደተባለው ከኅብረተሰባችን ውጭ ያሉትም ቢሆኑ በአርዓያሥላሴ የተፈጠሩ ስለሆኑ በዚህ መነሻውም ሆነ መድረሻው ወሲብ ብቻ በሆነ ባህርይ እየተለከፉ ከሄዱ ይህ ልምድ ለሥጋቸውም ሆነ ለነፍሳቸው የዘለቄታ ጥቅም ስለሌለውና በመጨረሻም ትውልዳቸውን ጭምር እያበላሸ ተጨማሪ ማህበረሰቦችንም ሊበክል ስለሚችል ከዚህ ልምድ እግዚአብሔር እንዲያወጣቸው ልንፀልይላቸው ይገባል። ሆኖም በእነዚህ ርካሽ በሆኑና በእንሰሳዊ ደመ-ነፍስ (instinct) ባህርይ በተበረዙ ልማዶች የራሳችንን መልካም ባህል ማዳከም የለብንም፤ የአገራችንን የጋብቻ ሥርዓት በአጠቃላይም በመልካም ባህላችን ውስጥ ያሉ ማኅበራዊ እሴቶቻችንን እያዳበርን ልንጠብቃቸው እና ሌሎችን ኅብረተሰቦች ልናስተምራቸው ይገባናል እንጂ።
ይህ ክስተት ወደ ባህላችን ዘልቆ ስላልገባ አሳሳቢ የማይመስላቸው የዋህ ወገኖች አሉ። ይኽም ራሷን አሸዋ ውስጥ ደብቃ የሚሆነውን ሁሉ አላይም ብላ የቀረውን አካሏን ለአደጋ እንደተወችው እንሰሳ እንደመሆን ነው። ሆኖም ዛሬ ዓለም እየተቀራረበች ባለችበት ዘመን በተለይ ወጣቱን ትውልድ በቅድሚያ በማስተማር በአገሩ ባህል ሙሉ እምነት አድሮበት ከዚህ መጥፎ ባህል ራሱን እንዲጠብቅ በወቅቱ ማስገንዘብ ይመረጣል።

Latest from Blog

ከሃይለገብርኤል   አያሌው የኦቦ ሲራጅና የወይዘሮ ፉንታዬ ልጅ ጃዋር መሃመድ ትላንትን ዛሬንና ነጋችንን ሊያሳይ የሚችል መጽሃፍ አዘጋጅቶልናል:: በእውነቱ መጽሃፉ ሊነበብ በሚችል የሃሳብ ፍሰት ተቀንብቦ በአነጋጋሪነቱ ቀጥሏል:: ጃዋርን እና የቄሮን ትውልድ በቅጡ ለመረዳት መጽሃፉ ማንበብ

የጃዋር የፖለቲካ ጅዋጅዌ! “ድመት መንኩሳ አመሏን አትረሳ’’

ጥር 2 ቀን 2017 ዓ/ም   January 10, 2025  በኢትዮጵያዊነታችሁ፡ በኦርቶዶክሳዊ እምነታችሁ፡ በአማራነታችሁ፡ በአማረኛተናጋሪነታችሁ፡ በተሰነዘረባችሁ ብትር፡ ቤተ ሰብ፡ ወዳጅ ዘመዶቻችሁን ያጣችሁ: ልጆቻችሁን የቀበራችሁ፡ አካልችሁን ያጣችሁ፡ የተሰነዘረውን ብትር በመከላከል ላይ ያላችሁ፡ያለፈቃዳችሁ በመንግሥት ተጽእኖ ወደመግደልና

በኢትዮጵያዊነታችሁ፡ በኦርቶዶክሳዊ እምነታችሁ፡ በአማራነታችሁ፡ በአማረኛ ተናጋሪነታችሁ፡ በተሰነዘረባችሁ ብትር፡

January 10, 2025
መኮንን ሻውል ወልደጊዮርጊስ ¹⁵ የምድርም ነገሥታትና መኳንንት ሻለቃዎችም ባለ ጠጋዎችም ኃይለኛዎችም ባሪያዎችም ጌቶችም ሁሉ በዋሾችና በተራራዎች ዓለቶች ተሰወሩ ፥ ¹⁶ ተራራዎችንና   በላያችን ውደቁ በዙፋንም ከተቀመጠው ፊት ከበጉም ቍጣ ሰውሩን ፤ ¹⁷ ታላቁ የቁጣው ቀን  መጥቶአልና ፥ ማንስ ሊቆም ይችላል ? አሉአቸው ። ራእይ 6 ፤  15_17 ይኽ የመጽሐፍ ቅዱስ ቃል ። የኢየሱስን ልደት ሰናከብር የየሐንስ ራእይን ማንበብ ጠቃሚ ይመስለኛል ። ምክንያቱም በመጨረሻው ዘመን

ከኢየሱስ የፍርድ ቀን በፊት በህሊናችን ውስጥ ፍቅርን ለማንገስ እንጣር 

የምጣኔ ሀብታዊ ፍጥ፣ የፖለቲካ፣ የእውነትና የሰብአዊ መብት ታጋይ፣ የአመኑበትን ነገር ለመናገር እንደ ፖለቲከኛ በቃላት ሳያሽሞነሙኑ ቀጥታ የሚናገሩት የሀገሬ ኢትዮጵያ ታላቅ ሰው ነበሩ “ዘር ቆጠራውን ተዉት፤ የአባቶቻችሁን ሀገር ኢትዮጵያን አክብሩ!”  አቶ ቡልቻ ደመቅሳ

ሀገር ወዳዱ አቶ ቡልቻ ደመቅሳ ከዚህ አለም በሞት ተለዩ

January 6, 2025
ግን ይህ ሁሉ ወጣት የት ገባ? ግን ይህ ሁሉ ወጣት የት ገባ? ዛሬ፣ 2025 ዓ/ም ላይ ብንገኝም በዝንጋታ ገመድ ወደ ሞት እየተጎተትን እንደሆነ አናውቅም። (ሁል ጊዜ የሚሞተው የገነዝነው ይመስለናል። ) “ገብርዬ ነበረ

ግን ይህ ሁሉ ወጣት የት ገባ?

January 3, 2025
Go toTop