ሰኔ ፯ ቀን ፳፻፭ ዓመተ ምህረት
ከአንዱ ዓለም ተፈራ – የእስከመቼ አዘጋጅ
የአንድነት ፓርቲ ግምገማዉንና የመድረክ አመራር መልሱን በአደባባይ ማቅረባቸው ታላቅ በር ከፋች ጥረት ነው። አንድነት መድረክን ብቻ ሳይሆን፤ የራሱን አመራር አካላትም ገምግሞ ለኢትዮጵያዊያን ማሳየቱ፤ ብስለቱንና ጥንካሬውን አመልካች ነው። ከመድረክ በኩል የተሠጠውም መልስ፤ በድብቅ ሳይሆን በአደባባይ መውጣቱ የሚያኮራ ነው። እዚህ ላይ አንዱም ሆነ ሁለቱ ትክክል ናቸው ወይንም ስህተተኞች ናቸው ማለቴ አይደለም። ጥረታቸው የሚያኮራ መሆኑን ለመጠቆም ነው። በዴሞክራሲያዊ ማዕከልነት ስምና በፓርቲ አባልነት ግዴታ ማነቆ ልሳናቸው ሳይዘጋ የተጻጻፉበት ምልልስ፤ ትልቅ ትምህርት ለሁላችን ሠጥቷል። እስከዛሬ ያልተለመደው ግልፅነት በሩ ተከፈተለት። ራሳችንን መገምገም ራሳችንን ዝቅ እንደማድረግ ስለሚወሰድና ይኼን ማድረግ እንደተቸናፊነት ስለሚወሰድ፤ ከትናንት ትምህርት የመውሰዱ ሂደት በሩ ዝግ ነበር። አሁን በሩ ተከፈተ። ሀቅ ይረዳል እንጂ ማንንም አይጎዳም። ይኼ ግን ባህላችን አልነበረም። ጥሩ ነገር ስናይ ደግሞ፤ ማንም ይሥራው ማንም ይበል ማለት ተገቢ ነው።
ጉዳዩ የሁላችን ነው
የተወያዩባቸው ጉዳዮች የግላቸው ሳይሆኑ፤ ሁላችን ኢትዮጵያዊያንን የሚነኩና እኩል እንደነሱ ልንወያይባቸው የሚገባ ነው። ትኩረቱ እከሌ እንዲህ አለ፤ ሌላው ደግሞ ይኼን መለሰለት ለማለት ሳይሆን፤ ባደረጉት ምልልስ የተነሱት ነጥቦች በሁላችንም ዘንድ መልስ ፈላጊ በመሆናቸው፤ በየበኩላችን እንድንወያይበት ይገፋናልና የበኩሌን ለመለገስ ነው። አሁንም እንደገና፤ ግልፅ ውይይት ማድረግ በማንኛውም ወቅት የጥንካሬ፣ በተጨማሪም ራስን ደግሞ ደጋግሞ በየደረሱበት ደረጃ መመርመር፤ ለትግሉ ውጤት ያለንን ቁርጠኝነት መለኪያ መሣሪያዎች ናቸው።
ጉዳዩ እንዲህ ነው። መድረክ በሀገር አቀፍ ደረጃ የተዋቀረ የፖለቲካ ድርጅት ነው። የሀገሪቱን ተጨባጭ ሁኔታ ተንትነው አንድ መፍትሔ በማቅረብ፤ የርዕዩተ ዓለም አመለካከታቸው አንድ የሆነ አባላት ያሉበት ድርጅት ነው። በሌላው በኩል በአካባቢ ወገኖቻቸውን በማሰባሰብ የተዋቀሩ ድርጅቶች አሉ። እኒህ ድርጅቶች የአካባቢያቸው ተቆርቋሪ በመሆን አጀንዳቸውን ያማከሉ ድርጅቶች ናቸው። መድረክን ለመፍጠር በሁለቱ ወገን ያሉ ክፍሎች ወይይት አድርገው፤ በኢትዮጵያ በነበረው ሀቅ ተገደው፤ የተወሰነ ስምምነት ላይ ደረሱ። ይህ መድረክ ወደፊት ምን ሊሆን እንደሚችል ያኔ በደንብ ያጤኑት ላለመሆኑ፤ የአንድነት ፓርቲ ግምገማ ግልፅ አድርጎልናል። አሁን ዕድገታቸውን አስመልክቶ ወደፊት ሲሉ፤ በወቅቱ ያልተመለሱ ጥያቄዎች አስረው ያዟቸውና፤ ከፊታችን ለተደቀነው ውይይት በቁ። ታዲያ ከዚህ ምን እንማራለን?
እውነት ስትፈተን
እያንዳንዳችን መብትና ግዴታችን የሚመነጨው ከኢትዮጵያዊነታችን ነው። መብታችን ሊከበር፣ ኃላፊነታችን ሊጠየቅ የሚገባው፤ በኢትዮጵያዊነታችን ነው። ከሌሎች ኢትዮጵያዊያን ጋር በምንኖርባት ኢትዮጵያ፤ ከኢትዮጵያዊነት የተለዬ መብትና ግዴታ የለንም። አማራ ሆኜ በአማራነቴ መብቴና ግዴታዬ፤ በኢትዮጵያ፤ እንደ ትግሬ ወይንም እንደ ኦሮሞ ወይንም እንደ ሶማሌ ሳይሆን እንደ አማራ ይከበርልኝ ብል፤ የምናገረውን የማላውቅ መብት ፈላጊ እሆናለሁ። አማራ መሆኔ የኔ ጉዳይ ነው። ከአማራና ከኦሮሞ መወለዴ የራሴ ቤተሰብ ጉዳይ ነው። በኢትዮጵያ ስኖር፤ አማራ ወይንም ኦሮሞ፣ ሶማሌ ወይንም አፋር፣ ትግሬ ወይንም ወላይታ መሆን የለብኝም። ኢትዮጵያዊ ብቻ መሆኔ ነው መለኪያው። ከአንዱ ወይንም ከአንዱ በላይ ከሆኑ ቤተሰብ መወለዱ፤ የግለሰቡ የቤተሰብ ትስስር ጉዳይ ነው። ይህ ከማንኛውም ኢትዮጵያዊ መብቱ ሊጨምርለት ወይንም ሊያስቀርበት አይችልም። ታዲያ ምኑ ላይ ነው ችግሩ? ችግሩ የተከሰተው፤ ከዚህ ወይንም ከዚያ በመወለዴ የቀረብኝ ወይንም የደረሰብኝ ወይንም የሚቀርብኝ ወይንም የሚደርስብኝ ጥቅም ወይንም በደል ነው። ይህ ያለአንዳች ጥያቄ በሀገራችን የተከሰተ ችግር ነው። መለያየት የሚመጣው መፍትሔ ሲታሰብ ነው። መፍትሔው ደግሞ፤ ላንድ ወቅት ወይንም ላንድ ክፍል የሚሰራ ሳይሆን፤ ሁሌም ለሁሉም የሚሠራ መሆን አለበት። ይህ ደግሞ፤ በሕገ-መንግሥቱ፣ በመንግሥቱና በያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ሊከበርና ሊጠበቅ የሚገባው መሆኑ ነው። በዚህ ላይ በአንድነት መነሳት አለብን። በውጭ ሀገር በየተሰደድንበት ቦታ፤ መብታችን በሀገሩ ካሉ ነዋሪዎች በአንዲት ጠብታ ሳታንስ እንዲከበርልን ሽንጣችንን ገትረን እንቆማለን። የሀገሩን ዜግነት ተቀበልንም አልተቀበልንም ልዩነት አናይበትም። ታዲያ ኢትዮጵያ ላይ ምን ልዩነት ተፈጠረ? የሀገሩ ዜጋ በሙሉ እኩልነታቸው የሚመዘገበው፤ የሀገሩ ዜጎች በመሆናቸው ብቻ ነው።
የትግላችን ግብ
ኢትዮጵያዊያን ከትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባር መንግሥት ጋር የምናደርገው ትግል፤ ይኼን በጉልበቱ በሥልጣን ላይ ያለን ቡድን ስሙን ስለጠላን ለማስወገድና ሌላ ስም ያለው በቦታው ለመተካት አይደለም። መሠረታዊ የትግሉ መነሻው የዚህ የትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባር መንግሥት የፖለቲካ ፍልስፍናውና የአስተዳደር መመሪያው ናቸው። እኒህ የፖለቲካ ፍልስፍናና የአስተዳደር መመሪያዎቹ በሀገራችን ተዘርፍጠው መቀመጥ ቀርቶ ባንዣበቡበት ሁኔታ፤ ወደፊት መሄድ የሚባል ጉዳይ የለም። የትግል እሽክርክሪቱ ተወግዶ ወደፊት እንድንሄድ ከተፈለገ፤ ግልፅ የሆነ ውይይት ማድረግ አለብን። በአሥራ ዘጠኝ መቶ ስድሳዎቹ የነበረው የተማሪዎች እንቅስቃሴ ዋናው የትግል መስመሩ፤ በገዢዎችና በተገዢዎች መካከል የነበረው ቅራኔ ነበር። በዚህ የተጠቃለሉት የዴሞክራሲያ ጥያቄዎች፤ መሬት ላራሹ፣ የትምህርት ዕድል ለብዙኀኑ፤ ሕክምና ለገጠሬው፣ ኃላፊነት ለፓርላማው፣ የሴቶች እኩልነት፣ በወቅቱ ትክክለኛ ትኩረት ያልተደረገበትና የዘመኑ የሶቪየት ኅብረት ሶሺያሊዝምን መስመር ያንፀባረቀው የብሔሮች እኩልነት ነበሩ ከሞላ ጎደል ሰንደቆቻቸው። በመደብ ትግሉ ጠንካራ አቋም ከነበረው የተማሪዎች እንቅስቃሴ ተገንጥለው፤ “በኢትዮጵያ የብሔሮች ነፃ መውጣት ነው ቅድሚያ ያለው” ብለው የተነሱ ጥቂት ቡድኖች ነበሩ። በዚህ የተመሩ የብሔር ነፃ አውጪ ቡድኖች በሀገራችን ግራ ቀኙን ተሯሯጡበት። ተጨባጭ የነበረው የአድልዖና የጭቆና ክስተት፤ ለትንንሽ መንግሥታት መፍጠሪያ መንገዱን ከፈተ። ለነበረው ሀቅ አንድ ብቻ መፍትሔ ሳይሆን ብዙ መንገዶች ቀረቡ። አንድ ሀገር የሚለው ጉዳይ በአንዳንዶች ዘንድ ተቀባይነት አጣ። በዕርግጥ አብዛኛው ኢትዮጵያዊ መፍትሔ የፈለገው በሀገራችን ውስጥ የነበረውን የገዢዎችና የተገዢዎች ቅራኔ መፍታት ሲሆን፤ ጥቂቶች ደግሞ የተለዬ መፍትሔ ብለው የያዙት የራሳቸውን ሀገር የመመሥረት አጀንዳ ነበር።
አጀንዳ ያልለወጠ ነፃ አውጪ
ይኼን የመጨረሻውን መንገድ የመረጡት የነፃ አውጪ ግንባሮችን በመመሥረት ጠመጃቸውን አነሱ። በባንዳነት ጣሊያንን በማገልገል የታወቁ የትግራይና የኤርትራ ተወላጆች ልጆች፤ ጠንካራ የሆነ ፀረ-ኢትዮጵያ መርኀ-ግብር ይዘው፤ ኢትዮጵያን የማፈራረስ አጀንዳቸውን በራሳቸውና በሌሎች የሀገራችን ክፍሎች መመሪያቸው አደረጉ። በከፍተኛ ደረጃ ለዚህ የረዳው ደግሞ፤ የደርግ ደርጋማ ማንነትና የተከተለው መመሪያ ነበር። ሥልጣን ለብቻው መያዝ ዋናው ዓላማው ያደረገው የመንግሥቱ ኃይለማርያም አረመኔ ደርግ፤ ወጣቶችን በመጨፍጨፍ፤ በእውነትና በሕልሙ ጠላቶቼ ናቸው ብሎ የፈረጃቸውን በማሳደድና የራሱ ሰው በላ ቡችሎችን በከፍተኛ ቦታ በማስቀመጥ፤ ሀገራችንን ወደ አዘቅት ከተታት። የዚህ ውጤቱ ለትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባር መንግሥት ሀገሪቱን ወለል አድርጎ ከፍቶ ሀገር ለቆ መሽምጠጥ ሆኗል። ታዲያ የብሔሮች ነፃ መውጣትን ያነገበው ይኼ የትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባር፤ ትግራይን ነፃ ከማውጣት ይልቅ፤ በተፈጠረለት ቀዳዳ ገብቶ ሀገሪቱን ተቆጣጠረ። አጀንዳውን ሳይለውጥ፤ አሁንም የትግሬዎች ነፃ አውጪ ሆኖ አዲስ አበባ ተዘርፍጧል። ባለበት ቦታ ደግሞ የሚሠራው ሀገራችንን መበጣጠስ ነው። ሀገራችንን ሀገር የሚባል ነገር ጠፍቶ፤ የየራሳቸው ብሔር የሚኖራቸው ሕዝቦች ያሉበት ቦታ አድርጓታል። ይህ ነው የትግሬዎች ነፃ አውጪ አጀንዳ። ይኼን ነው የኢትዮጵያ ሕዝብ የሚታገለው። ታዲያ በየአካባቢያቸው የተዳራጁት የፖለቲካ ድርጅቶች ዓላማቸው ምንድን ነው? የትግራይ ነፃ አውጪ ግንባር መንግሥት የሚከተለውን ዓላማ ማራመድ ነው ወይንስ መለወጥ? ሀገራችንን በጋራ ነፃ አውጥተን ለእያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ እኩል የምትሆን ሀገር ማድረግ ነው? ይህ ነው መሠረታዊው የመድረክ ምስቅልቅል።
“አትከፋፍሉን። አንድ ነን።”
አንድነት የፖለቲካ ግኘታ ቋምጦ ነበር ከአካባቢ የፖለቲካ ድርጅቶች ጋር የተቧደነው። አሁን ጠዘጠዘው። የግድ ከዚህ መላቀቅ አለበት። በአዲስ አበባ የተደረገው ሰላማዊ ሰልፍ፤ “አትከፋፍሉን። አንድ ነን።” ነበር ያለው። የኢትዮጵያ የወደፊት ዕድል በሰማያዊ ፓርቲና በመሰሎቹ ወደፊት መጪ ፓርቲዎች እንጂ፤ በነበሩት የነፃ አውጪና የማያፈሩ የቆዩ ፓርቲዎች እጅ አይደለም። የአካባቢ የፖለቲካ ድርጅቶችን ከሀገር አቀፍ የፖለቲካ ድርጅቶች በዋናነት የሚለያቸው፤ የአካባቢ የፖለቲካ ድርጅቶች ሌሎችን አግላይ መሆናቸው ነው። በነዚህ ድርጅቶች ውስጥ፤ በሌሎች አካባቢ የሚኖሩ የሀገሪቱ ዜጎች፤ አባል ሊሆኑ አይችሉም። ስለዚህ ዴሞክራሲያዊም ሆነ ኢትዮጵያዊ አይደሉም ማለት ነው። ከዚህ ተነስተውም፤ እንንቀሳቀስበታለን በሚሉት የራሳቸው ክልል፤ የሀገር አቀፍ የፖለቲካ ድርጅቶችን መንቀሳቀስ በድፍኑ ይቃወማሉ። የርዕዩተ ዓለም ልዩነት ሳይሆን፤ የዚህ አካባቢ ሕጋዊ ተወካዮች እኛ ብቻ ነን ስለሚሉ፤ ከነዚህ ድርጅቶች ጋር ማንኛውንም ዓይነት ስምምነት ለመድረስ፤ በነሱ አካባቢ የፖለቲካ እንቅስቃሴ ያለማድረግ ቅድመ-ግዴታ ይሆናል። ይኼን የተቀበለ ሀገር አቀፍ ድርጅት፤ አንድም በነዚህ አካባቢ ያሉትን ደጋፊዎቹ የሀገሪቱ ነዋሪዎች ሸጧል ማለት ነው፤ አለያም የሚያደርገውን የማያውቅ ድርጅት ነው። በኢትዮጵያ የፖለቲካ ማኅደር፤ በአካባቢ በተደራጁ የፖለቲካ ድርጅቶችና በሀገር አቀፍ በተደራጁ የፖለቲካ ድርጅቶች መካከል ቅንጣት ታክል ፍቅር የለም። ግንባርማ ቅዠት ነው። ኢሕአዴግም ውሎ አድሮ ሲበጣጠስ፤ ይኼኑ ያሳየናል።
ውሃ ቢያጥቡት
ሥር የሰደደ ቂም ካለው የትግራይ ታሪክ የተያያዘ መነሻ ያለው የትግሬዎች ነፃ አውጪ ድርጅት፤*1 ኢትዮጵያን ማፈራረስ ዋና ዓላማው ነው። እንደ ኢትዮጵያዊያ ሳይሆን፤ የተገነጣጠልን ሆነን ራሳችንን እንድንመለከት ነው መርሁ። አንዳንድ የአካባቢ የፖለቲካ ድርጅቶች፤ ለምን ሀገር አቀፍ የሆነ ድርጅት እንዳልመሠረቱ ወይንም ሀገር አቀፍ ከሆኑ ድርጅቶች እንዳልተቀላቀሉ ሲጠየቁ፤ የሠጡት መልስ ወንዝ አያሻግርም። ዶክተር መራራ መልሳቸው፤ “እኛ ለኦሮሞ ሕዝብ የቆመ ድርጅት ይዘን ካልተገኘን፤ ሕዝቡ ወደ ኦነግ (የኦሮሞ ነፃነት ግንባር) ይነጉዳል።” ነበር። እንግዲህ የዶክተር መራራ ድርጅት የሚፎካከረው ኦሮሞዎችን ከኦነግ ጋር እንዳይሠለፉ ገንጥሎ፤ በሥሩ ለማድረግ ብቻ ነው። አቶ ገብሩ አሥራትም በበኩላቸው፤ “የትግራይ ሕዝብ የራሱ የሆነ ድርጅት ካላቀረብንለት የትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባር ብቸኛ ወኪላቸው በመሆን ያጠቃልላቸዋል።” ይላሉ። በዕርግጥ ቃል በቃል አልተጠቀሱም። መልሳቸው ግን ማንነታቸውን በግልፅ ያሳያል። የአቶ ገብሩ አሥራት አረና የሚፎካከረው ትግሬዎችን በሥሩ ለማድረግ ከትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባር ጋር ነው። የዶክተር አረጋዊ በርሄና የአቶ ግደይ ዘርዓፂዮን ታንድም እንዲሁ።
የግለሰብ መብትና የቡድን መብት – በግልፅ ከተነጋገርን
በግለሰብና በቡድን መብቶች ዙሪያ ብዙ ስለተጻፈ እዚህ ላይ መተንተኑ አስፈላጊ አይደለም። እግረ መንገዴን ግን የቡድን የምንለው መብት በግለሰብ መብት ውስጥ ሙሉ በሙሉ የተጠቃለለና በትክክለኛ የዴሞክራሲያዊ ሂደት ብቻውን መቆም የማይችል መሆኑን ማስታወስ እወዳለሁ። አቶ ገብሩ አሥራት፣ ዶክተር አረጋዊ በርሄና አቶ ግደይ ዘርዓፂዮን ትግሬዎችን ከትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባር ለመውሰድ ከሆነ የሚታገሉት ለምን የትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባር መንግሥት በከለለው በትግራይ ምድር ብቻ ተመዝግበው አይታገሉም? በእውነት ለመናገር፤ ለትግሬዎች ከሀገር አቀፍ በርዕዩተ ዓለም የተመሠረተ የፖለቲካ ድርጅት ሌላ፤ ከትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባር የበለጠ አረናና ታንድ ይጠቅማሉ? ይኼ ያጠራጥራል። ይልቁንም የትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባር መንግሥት ሲወድቅ፤ ትግሬዎች በደል እንዳይደርስባቸው ቦታ መያዣ የተቋቋሙ ድርጅቶች ናቸው። ዶክተር መራራም ሀገራዊ ፍቅር ኖሯቸው ሳይሆን፤ ለሥልጣን ሊያቀርባቸው የሚችለው፤ የአካባቢ የፖለቲካ ድርጅት በመመሥረት ስለሆነ ነው። በተመሳሳይ መልኩ ዶክተር በየነ ጴጥሮስም የዚሁ አባዜ ተጠቂ ናቸው። ታዲያ ዶክተር መራራም ሆኑ ዶክተር በየነ ለምን የትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባር መንግሥት በከለለው የኦሮሚያና የደቡብ ክፍል ተመዝግበው አይታገሉም? ይህ እንግዲህ በግልፅ እንነጋገር ከተባለ ነው። ታዲያ ለኔ፤ በመድረክ ውስጥ የታዬው ድራማ ከዚህ በላይ የተገለፀው ነው። በኢትዮጵያ የፖለቲካ ማኅደር የሚሳተፍና በሕዝቡ ላይ እምነት ያለው ግለሰብም ሆነ የፖለቲካ ድርጅት፤ በኢትዮጵያ ሕዝብ ፊት ቀርቦ ሃሳቡን መግለፅና አሳምኖ ተከታዮችን ማግኘት እንጂ፤ በአንድ የተለዬ አካባቢ ቀርቦ፤ ለዚያ አካባቢ ተከላካይና የዚያ አካባቢ ጠባቂ ለመሆን አያስብም።
የመገንጠል ግብ
መገንዘብ ያለብን፤ በሥልጣን ላይ ያለውን የትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባር መንግሥት መጣል ብቻ ሳይሆን፤ ኢትዮጵያን ለመገነጣጠል ዓላማቸው አድርገው የሚታገሉ የአካባቢ ድርጅቶች እንዳሉ ነው። እነኚህን ለይቶ ማስቀመጥና ከነዚህ ጋር ሊኖር የሚችለውን ግንኙነት ማጥናት ግዴታ ነው። በዕውነት ግን ከነዚህ ጋር ምን ዓይነት ቅርርብ ሊደረግ ይቻላል? ኢትዮጵያን ለማፍረስ ከተነሱ ድርጅቶች ጋር የትግሬዎችን ነፃ አውጪ ግንባር መንግሥት ለማስወገድ መሠለፍ፤ የራስን አንገት ለማስቆረጥ፤ ከጎራዴ መዛዡ ጋር መስማማት ነው።
(ክፍል ሁለት ይቀጥላል)
*1 የዶክተር አረጋዊ በርሄን የማስተርስና የዶርትሬት ጽሑፍና መጽሐፋቸውን ይመልከቱ። በአፄ ሚኒሊክ ላይ ያስቀመጡት ውንጀላ በግልፅ ተቀምጧል።