ከያሬድ አይቼህ – ጁን 28፥2013
የኦሮሞ-አማራ ምሰሶነት ንድፈ-ሃሳብ በቀረበበት በዚህ ሰሞን ፡ አቶ ጃዋር መሃመድ በአልጀዚራ ቲሌቪዥን ላይ “መጀመሪያ ኦሮሞ ነኝ … ኢትዮጵያዊነት ያለፈቃዳችን ተጭኖብን ነው” ማለቱ ለሁለቱ መሰሶዎች ሊሂቃን አብሮ መስራት ፍላጎት የመጀመሪያው የአደባባይ ፈተና ሆኗል። ሁለቱ ምሰሶዎች አብረው መስራት የሚችሉት ለሁሉም ብሄሮች የሚበቃ ምህዳር ያለው ‘ኢትዮጵያዊነት’ ሲቃኝ ብቻ ነው። ሌላ አቋራጭ መንገድ የለውም።
– ኢትዮጵያዊነት እና አማራነት –
አማራዎች አንድ መሰረታዊ ችግር አለብን። እኛ አማራዎች ኢትዮጵያዊነትን እና አማራነትን ለይተን ማየት ተስኖናል። በተለይ አሮጌው ትውልድ በፍጹም ኢትዮጵያዊነትን ከአማራነት ፡ አማራነትን ከኢትዮጵያዊነት ለያይቶ ማየት የማይችል የአስተሳሰብ መካኖችን በብዛት አሉበት።
እኛ አማራዎች ‘አንድነት’ ስንል ‘አንድ አይነትነት’ ማለታችን መሆኑ ተነቅቶብናል። አሃዳዊት ኢትዮጵያ ለሁሉም ኢትዮጵያዊ ያልጠቀመች ኢትዮጵያ ነበረች። አሁን ብዙአዊት ኢትዮጵያ ነግሳለች። ብዙአዊት ኢትዮጵያ የጃዋር መሃመድ ኢትዮጵያ ናት። ብዙአዊት ኢትዮጵያ የሌንጮ ባቲ ኢትዮጵያ ናት። ብዙአዊት ኢትዮጵያ የዋለልኝ መኮንን ኢትዮጵያ ናት።
አማራዎች ሆይ! የዱሮዋ ኢትዮጵያ ተመልሳ አትመጣም። አማርኛ ቋንቋ ሁሉም የሚናገርባት ፡ ኦርቶዶክስ ክርስትና የተንሰራፋባት ፡ አርንጓዴ-ቢጫ-ቀይ ብቻ የሚውለወለብባት ያች ኢትዮጵያ በታሪክ መጽሃፍት እና በቪዲዮ እንጂ ወደፊት ልትመለስ አትችልም። የአሃዳዊ ስርዓት ናፋቂዎች እርማችንን እናውጣ!
– አዲስ ኢትዮጵያዊነት –
ባለፉት 22 አመታት ኢትዮጵያዊነት እንደገና ተቀርጿል ፤ አዲስ መልክ ተላብሷል። ኢትዮጵያዊነት የአማራዎች ሶፋ መሆኑ ቀርቶ ለሁሉም የሚበቃ ሰፊ አግዳሚ ወንበር ሆኗል። “መጀመሪያ ብሄሬን ነኝ ፡ ቀጥሎ ኢትዮጵያዊ ነኝ” የሚለው አስተሳሰብ በትግሬዎች ሲነገር ሃሰት ቢሆንም ፤ በምስራቅ ፡ ምዕራብና ደቡብ ኢትዮጵያዊያን ቢነገር ግን ሃቅ ነው።
ትግራያን የሚዘነጉት እውነታ ቢሆር አማርኛን ቋንቋ የኢትዮጵያ መንግስት ቋንቋ ያደረጉት አጼ ዮሃንስ መሆናቸውን ነው። ይሄን እውነታ እያወቁ የትግራይ ሊሂቃን ክህደት ውስጥ የገቡት ህወሃት በኦሮሞዎች እና በአማራዎች ላይ የፓለቲካ የበላይነት ለመያዝ ብሎ ነው።
በአዲሱ ኢትዮጵያዊነት ፡ ኢትዮጵያውያን ብዙ አይነት ማንነት አላቸው። ዜጎች አንድ አይነትነትን እንደ ኢትዮጵያዊነት አይቀበሉም። አቶ ጃዋር እንደገለጸው ፡ አንድ አይነትነት በግዴታ የሚጫን ማንነት ነው። በሰፊው ኢትዮጵያዊነት ግን ብዙ አይነትነትን የሚያስተናግዱ ፡ በፈቃደኝነት ላይ የተመሰረቱ ማንነቶች ተንሰራፍተዋል።
– የጃዋር ቁንጥጫ –
ጃዋር የቀድሞው ስርዓት ናፋቂዎችን ትዝታና የፓለቲካ ቱሪስትነት በንግግሩ ቆንጥጦታል። የትዝታ ፓለቲካ ለምንወድ የጃዋር ንግግር ያበሳጫል ፤ ንግግሩ ግን ታሪካዊ ጭብጥ ነው። የአገራችን የፓለቲካ ውጥረት በትዝታና በፓለቲካ ቱሪስትነት የሚፈታ አይደለም።
ለሁለቱ ምሰሶዎች አብሮ መስራት የአማራ ሊሂቃን የጃዋር መሃመድን ንግግር ያለምንም ቅድመ ሁኔታ መቀበላቸው የመጀመሪያ ፈተና ነው። ይሄን ማድረግ ያቃታችሁ የአማራ ሊሂቃን ፡ በተለይ በቀድሞው የአሃዳዊ ስርዓቶች ነፍስ ያወቅን ፡ ከትግሉ ጡረታ ውጡ። እናንተ ለሁለቱ ምሰሶዎች አብሮ መስራት ዋና እንቅፋትና ፡ መርዝ ናችሁና ገለል በሉ። መርዛችሁ ለኢትዮጵያዊነት መስፋፋት ፡ መዳበር እና እመርታ እንቅፋት ነውና ዞር በሉ:: አዎ! ዞር በሉ!!
ክብር ለጃዋር መሃመድ!
ቪቫ ኦሮሚያ! ቪቫ ኢትዮጵያ!
– – – –
የጸሃፊው አድራሻ፦ yared_to_the_point@yahoo.com