June 27, 2013
31 mins read

የኃይል መቋረጥ እያሰከተለ ያለው ቀውስ

ተሻለ መንግሥቱ (teshalem1@gmail.com)
 ይህን ጦማር የምጽፈው፣ እንደልዩ ዕድል ወይም አጋጣሚ ሆኖ ከንፍሮ ውስጥ ጥሬ እንደሚገኝ ሁሉ በወያኔ መንደር ውስጥ ስለሀገራቸው የሚጨነቁ በጣት የሚቆጠሩ ባለሥልጣናትና የሥራ ኃላፊዎች ቢኖሩ “ሕዝቦቻቸው” በምን ዓይነት ችግር ውስጥ እንደሚገኙ ተረድተው ችግሩን ለመቅረፍ የተቻላቸውን ሁሉ እንዲያደርጉ ለመማጸን ነው፡፡ የገባንበት የችግር አዘቅት ተነግሮ የማያልቅ ቢሆንም በኤሌክትሪክ ኃይል ረገድ እየደረሰብን ያለው ጭቆናም ልበለው ረገጣ እጅግ የሚዘገንን ነው፡፡ እርግጥ ነው – ይህ ችግር የ‹ቅንጦተኞቹ› የከተማ ነዋሪዎችና መብራትና የኮረንቲ ኃይል በወሳኝነት ደረጃ ለሚያስፈልገን ዜጎች እንጂ አብዛኛውና ሌላውማ ዛሬ የሚቀምሳትን እንጂ የሚበራለትን መሻት ካቆመ ቆይቷል፡፡ ክትክታና ችቦም ቢሆን እያበራ የሚቀምሳት ቁራሽ እንጀራ ቢያገኝ – ያ ነው የጊዜው አንገብጋቢ ፍላጎቱ፡፡ ለብዙው ዜጋ የሚላስ የሚቀመስ ነገር ማግኘት ነው ቀዳሚ ፍላጎቱ፡፡ ዱሮ በ‹ክፉው› ዘመን ኩንታል በቆሎ ከአምስት ብር በታች በሆነ ዋጋ እንዳልተሸመተ ዛሬ በ‹ፀሐዩ› የወያኔ ‹ደግ› ዘመን አንዲት የተጠበሰች በቆሎ በአምስት ብር ተገዝታ ወስፋት የሚሸነገልባት ሀገር ተፈጥራለች፡፡

የኃይል አቅርቦት በአብዛኛው ከኤሌክትሪክ ጋር ይገናኛል፡፡ ሀገራችን በኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት በተለይ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ እየተሻሻለች እንደመጣች ይነገራል፡፡ ዱሮ ስንት ሜጋዋት ታመነጭ ነበር፣ አሁን ስንት ደርሳለች፣ የኤሌክትሪክ ተጠቃሚው ሕዝብስ በምን ያህል ምጣኔ አድጓል… የሚሉትን ጥያቄዎች ለባለሙያዎች ትነተና እንተወው፡፡ ግን አሁን ያለን ኃይል እንደሚባለው ለጎረቤት ሀገራት እስከመሸጥም ይድረስ ወይም በሺዎች የሚገመት ሜጋዋት ኮረንቲ በመጠባበቂያነት በየስቶሩ ይቀመጥ ዋናው ነገር ግና በ21ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ዜጎቿ በጨለማ ውስጥ የሚዳክሩባት ብቸኛ ሀገር ብትኖር ኢትዮጵያ ናት ማለት እንችላለን፡፡

አዲስ አበባም ሆነ የትም የኢትዮጵያ ክፍል በአሁኑ ወቅት መብራት የማይቋረጥበት ቦታ እንደሌለ ይታወቃል፡፡ መቋረጥ ሲባል ደግሞ ዓይነትና መጠን አለው፡፡ የኛ መቋረጥ በርካታ ሰዓቶችን አልፎ ሣምንታትንና ወራትንም ሊዘልቅ ይችላል፡፡ ይህ ደግሞ መቋረጥ ሳይሆን ሌላ ተስማሚ ቃል ሊፈለግለት ይገባል ባይ ነኝ፡፡ መቋረጥ ሲባል ለተወሰነ አጭር ጊዜና የተወሰነ ብልሽት ሲያጋጥም ያ እስኪስተካከል ድረስ እንጂ አንድን አካባቢ ለቀናትና ለወራት ዳፍንት ውስጥ መክተት የመብራት መቋረጥ በሚል የቁልምጫ ቃል ሊጠራ አይገባውም፡፡

ለምን ይቋረጣል? ብለን መጠየቃችን አልቀረም፡፡ ለዚህ ጥያቄ ትክክለኛ መልስ ሊሰጠን የሚችል “ሕዝቤ ለሚጠይቀው ሕጋዊና ተገቢ ጥያቄ ተገቢና ትክክለኛ መልስ ያስፈልገዋል” ብሎ የሚያምን አገዛዝ ስለሌለን መልሶቻችን በአብዛኛው መላምቶችና ከውስጥ ዐዋቂ ሾልከው የሚወጡ ፍንጮች ናቸው፡፡ ከዚህ አኳያ መብራት የሚቋረጠው፡-

  1. ወደሀገር የሚገባው ዕቃ ከቻይናና ቻይናን ከመሰሉ ዓለምን በተለይም ኋላቀር የአፍሪካና መሰል ሀገሮችን ቆረጣጥመው ለመብላት ቆርጠው ከተነሱ ጅቦችና ዓሣማዎች በሻጥረኛ የዕቃ ግዢ ባለሥልጣናት አማካይነት በእከክልኝ ልከክልህ ተመሣጥሮ በመሆኑ የተቀየረው ዕቃ መብራት ከመለቀቁ ይፈነዳል ወይ ይቀልጣል፤ አካባቢውን ሳይቀር የጦርነት ቀጣና እያስመሰለ ሕዝብን ያስደነግጣል፡፡ አንድ ፊውዝ ከመቀየሩ በሴከንዶች ውስጥ የሚፈነዳው በኛዋ ምሥኪን ሀገር ውስጥ  ብቻ ሣይሆን አይቀርም፡፡ የሀገር ሀብት የውጪዎቹን ተባባሪ መዝባሪዎች ጨምሮ የማንም ወለፈንዴና ብሔራዊም ይሁን ሰብኣዊ ስሜት  የሌለው ጋጠወጥ ዜጋ መቀለጃና መጫወቻ ሆኗል፡፡ የሚገዛው ዕቃ ፎርጅድ ነው – ጀንዩን ዕቃ ወደኢትዮጵያ ከመጣ ሀገሪቱ በዕድገት የምትጎተት ይመስላቸዋል – ባለሥልጣኖቻችን፡፡ በሻጥር የዕቃ ግዢና ያም በሚያስከትለው የሥራ ውጥረት ምክንያት የተሠላቹት ሠራተኞች የመብራትን መቋረጥ ወዲያው ደርሰው ለመጠገን ወኔያቸው እንደሞተ ይነገራል፤ ‹ብንጠግነውም ወዲያው ይቃጠላል ወይ ይፈነዳል› ከሚል ትክክለኛ የሚመስለኝ ስሜት፡፡ ሰው ናቸውና ይሰለቻሉ መቼም፡፡ መፍትሔው ይህን የሙስና አሠራር በሀገር ወዳድ ዜጎች መተካትና ትክክለኛ አሠራርን መዘርጋት ነው፡፡
  2. የመሥሪያ ቤቱ ዕውቅ ሠራተኞችና ባለሙያዎች የግል ሥራ እየያዙና በጡረታ እየተገለሉ በአሁኑ ወቅት ያለው ሠራተኛ በአብዛኛው ለማጅና በቂ ዕውቀት የሌለው ነው ይባላል፤ ስለሆነም የባለሙያ ዕጥረት በመኖሩ ሥራው ከመብራት ኃይል መሥሪያ ቤት አቅም እየወጣ እንደሆነ ይወራል፡፡ ሠራተኛን በደንብ ተከባክቦ መያዝ በኢትዮጵያ ውስጥ እንደነውርና ኃጢኣት ስለሚቆጠር ባልረባ ኑሮ በችግር እየኮደኮዱ የሚያኖሩት ሠራተኛ የመንግሥትን ሥራ እየናቀ ወደግሉ ቢያማትር አይፈረድበትም፡፡ ሥራ ላይ ያለው ራሱም አብዛኛውን የሥራ ጊዜውን እየሠረቀ ከፍተኛ ጥቅም ለሚያስገኝለት የግል ሥራው ቢያውለውና ሲያውለው ቢገኝ ተቆጣጣሪ ያለው አይመስልም፡፡ ሙስና እንደባህል በሚቆጠርባት ሀገር ውስጥ መብትን በገንዘብ እንጂ በመብት ማግኘት አይታሰብምና መብራት ሲቋረጥብህ ወይም ሆን ተብሎ እንዲቋረጥብህ ሲደረግ በእጅ መሄድ የግድ ይሆንብሃል – አንዱን ሲጠግኑ ሌላውንና በ‹እጅ› እንደሚመጣ የሚገምቱትን ሰው ለምሳሌ ኬክ ቤትና ወፍጮ ቤት ያለውን ሰው የኤሌክትሪክ መስመር አበላሽተው እንደሚሄዱ ይታማሉ – ለምሣ ዕረፍት ወደአንድ ሆቴል የገቡ ለቀስተኞች የመኪናቸው ዕቃ መጫኛ ላይ በክብር ያስቀመጡትን ለቀብር የሚጠበቅ ሬሣ ሠርቀው ‹የወሰደውን እናፈላልግላቸሁና እናስመልስላችሁ – ሦስት ሺህ ብር ክፈሉን› ብለው ለ‹አመርማሪ› የሚጠይቁና የተሰረቀን ሬሣ በውድ ዋጋ የሚሸጡ ዜጎች በሚኖሩባት ሀገር ይህ ዓይነቱ የኤልፓና የቴሌ ሠራተኞች ሻጥር እውነት አይሆንም አይባልም፡፡ ያም ሆነ ይህ የባለሙያ ዕጥረትና የደመወዝ ክፍያ ከሥራና ከኑሮ ውድነት ጋር አለመመጣጠንም አንዱ ችግር እንደሆነ በስፋት ይነገራል፡፡ ለዚህ መፍትሔው ሠራተኛን በበቂ ማሠልጠን፣ ክፍያንም ከወቅቱ ገበያ ጋር ማመጣጠን ይገባል፤ ‹እኔን ካልቸገረኝ ሌላው የራሱ ጉዳይ› ማለትም ከጤናማ አሠሪ አይጠበቅም፡፡ ችግር መጥፎ ነው፡፡ ብዙው ሰው በመኖርና አለመኖር አጣብቂኝ ውስጥ ሲገባ ‹ከነችግሬ እሞታለሁ› ብሎ እስከህቅታው ይጸናል ተብሎ አይገመትም – ወደስርቆትና ማጭበርበር ይገባል እንጂ፡፡
  3. በተለያዩ ቦታዎች የሚመረቱ የኃይል አቅርቦቶችን ወደማዕከላዊ የማዘዣ ጣቢያ ለማምጣት በሚደረግ ጥረት የኃይል መቋረጥ ይደርሳል፡፡ ይህ ችግር የዕውቀት ዕጥረት ጋር ሲደረብ የችግሩ ደረጃ ይወሳሰብና ምስቅልቅሉ ይወጣል፡፡ የትኛው ከየትኛው ጋር እንደሚቀላቀል በቅጡ የማያውቅ ሠራተኛ ሥራውን ከያዘው መስመሮች ሁሉ ይቀላቀሉና ብዙ አካባቢዎች ድንገት ወደተኩስ ወረዳነት ሊለወጡ ይችላሉ፡፡ በዚህ ሂደት ከጥቅም ውጭ የሆኑ ዕቃዎችን ለመቀየር በሚወስደው ጊዜ አንድ ክልል ወይ ከተማ ለሣምንታት ብቻ ሳይሆን ለወራትም መብራት ላያገኝ ይችላል፡፡ መፍትሔው ተገቢውን ሥራ ለተገቢው ሰው መስጠት ነው፡፡
  4. የወያኔ መንግሥት አንዱ መገለጫው ሀገሩን የማያውቅ ሌባና አጭበርባሪ ማፍራት በመሆኑ ብዙው ሌባ ምን ከማን መስረቅ ወይ መዝረፍ እንዳለበት አያውቅም፡፡ እርግጥ ነው – አንድን ሌባ “ይህን ስረቅ፤ ያን ግን አትስረቅ” ብሎ ሥልጠና መስጠት በኛ ሀገር አልተለመደም – (ዩጎዝላቪያ ውስጥ አንድ ዕውቅ የሥርቆት ማሰልጠኛ ተቋም እንዳለ ሰምቻለሁ)፡፡ የኛ ሀገር ሌቦች ግን  በተለይ ቀደምቱ ‹ፈሪሃ እግዚአብሄር ወባህል› ስለነበራቸው የሚሰረቅን ከማይሰረቅ ይለዩ እንደነበር የቅርብ ጊዜ ትዝታችን ነው፡፡ ለምሳሌ አእሩግን፣ ቤተ ክርስቲያንንና ካህናትን፣ የስልክና የመብራት ዕቃዎችን የመሰሉ የሀገር ሀብቶችን … አይሰርቁም ነበር፤ እንደነውር ይቆጠር ነበርና፡፡ ዛሬ ግን ዕድሜ ለሁሉንም ዘራፊ ወያኔ የሀገርም የሃይማኖትም ጽንሰ ሃሳቦች በመውደማቸው የቄሱን መስቀል ከእጁ ልፈው ሲሮጡ ብታይ በቄሱ ከርፋፋነት ከመሣቅ ውጪ የምትለው ወይ የምታደርገው ነገር የለም፡፡ ወያኔ መጥቶ ከጽላት ስርቆት እስከ ቅርስ ዘረፋና ሽያጭ በማኅበረሰቡ ውስጥ በማስተዋወቁ በሀገራችን ስርቆትና ውንብድና የደረሰበትን ከፍተኛ የሥልጣኔ ደረጃ መገመት አይከብድም፡፡ ዛሬ ዛሬ ሌብነት ቅጡን አጥቷል፤ ወግ ማዕረጉንም ተገፍፏል፡፡ ሌብነት ተልከሰከሰ፡፡ ሙያውን የሚያስንቁና የሚያዋርዱ ልክስክስ ዜጎች በመብዛታቸው ይሄውና ዛሬ የመብራት ሽቦና የስልክ ገመድ የሚሰርቁ ባለጌዎች ሞሉ፡፡ የተቀበረም ይሁን በአየር ላይ የተንጠለጠለና የቆመ የሕዝብ ንብረት በጠራራ ፀሐይ በግልም በቡድንም ይሰረቃል፡፡ የሬሣ ሣጥን ለቀስተኞች ቤት ከመድረሳቸው ይመነተፋል – ቆንጆ የአበባ ጉንጉን ጭምር፡፡ ከዚህ የባሰ የሞራልና የስርቆታዊ ግብረ ገብነት  ውድቀት የለም፡፡ በዚህ ሳቢያ የመብራትና የስልክ ምሰሶዎች፣ ገመዶችና የፋይበር  ግላስ ውድ የመገናኛ ዕቃዎች የሌብነት ሀሁ በማያውቁ ልቅላቂ ዜጎች እየተመነተፉ ብዙ ችግር እየተፈጠረ ነው፡፡ የሌቦ ሣህሉን ገድል ባጭሩ ላስታውሳችሁ ይሆን? ሌቦ ሣህሉ ታዋቂና ዝነኛ ሌባ ነበር – ማርካቶ ውስጥ፡፡ አንዲት ሴት ዕቃ ረስተው ኖሮ ‹እስክመለስ ድረስ እባክህን ይህን ዕቃ ጠብቅልኝ› ብለውት አንድ ገረወይና ቅቤ ፊቱ ላይ አስቀምጠው ይሄዳሉ፡፡ ሌቦ ሣህሉ ቢጠብቅ ቢጠብቅ ምሽቱ ለዐይን እስኪይዝ ሴትዮዋን የበላ ጅብ አልጮህ ይላል፡፡ እንደጠፉ አልቀሩም – መጡ፡፡ ‹ጎሽ ልጄ! አቆየሁህ አይደል?› ብለው አመስግነው ሊሄዱ ሲሉ ሌቦ ሣህሉ ቀበል አደረገና ‹ለመሆኑ እኔን አውቀውኛል? › ሲል ይጠይቃቸዋል – ፈገግ እያለ፡፡ እንደማያውቁት ይገልጻሉ፡፡ ቀጠለናም ‹ እኔ ሌቦ ሣህሉ እምባለው ነኝ፤ ግን ታማኝ ሌባ ነኝ› ሲላቸው በዝናው ያውቁት ስለነበር በድንጋጤ ምድር ተሰንጥቃ ብትውጣቸው በወደዱ፡፡ የዱሮ ሌባ ሩህሩህና ደርዝ ያለው፣ ሀገሩን እሚወድና ሙያውን የሚያከብር ነበር – ነገር በደረቁ ጥሩ አይደለም ብዬ ነው በቀልድ እያዋዛሁ እምጥፍላችሁ እንጂ አደራችሁን ሌላ ምስል እንዳትቀርጡብኝ፡፡ (ወያኔ ሥራየን ተሻማህ ብሎ ካልተቆጣ የሌብነት ኮሌጅ ልክፈት ይሆን? የሚያዋጣ ቢስነስ መሆኑ መቼም አያጠራጥርም፡፡ ) ለማንኛውም ይህን ችግር ለማስወገድ በወያኔ ጊዜ የሚቻል አይመስለኝም እንጂ ብሔራዊ ስሜትን መፍጠር፣ በዚህ ዓይነቱ ወንጀል የሚያዙ ሰዎችን አይቀጡ ቅጣት መቅጣትና ተጠርጣሪ ቦታዎችን በየጊዜውና በአሳቻ ወቅት መቃኘት… ለውጥ ሊያመጡ ይችላሉ፡፡

መብራት በምንም ይቋረጥ በምንም አሉታዊ ውጤቱ ግን የሀገር ኅልውናን እስከመፈታተን የሚደርስ ነው፡፡

ሆስፒታሎች፣ ክሊኒኮች፣ ፋርማሲዎች፣ ሆቴሎች፣ ሱፐርማርኬቶች፣ ቢሮዎች፣ መኖሪያ ቤቶች፣… ካለመብራት ብዙም ዋጋ የላቸውም ቢባል እውነት ነው፡፡ ይታያችሁ – ቀድዶ ህክምና እየተደረገለት ያለ ሰው ላልተወሰነ ረጂም ጊዜ መብራት ‹ቢ› ሳይሆን ‹ሲ›ቋረጥበት ምን ይፈጠራል? ‹ቢ›ን ያልተጠቀምኩት መቋረጡ እርግጠኛ ስለሆነ ነው፡፡ ቢቋረጥ ብሎ ነገር አሁን አሁን የለም – በየቀኑ የማይቋረጥበት አካባቢ ከስንት አንድ ነውና፡፡ ምናልባት ከ‹ኃይል አሰላለፍ› አኳያ ቤተ መንግሥት፣ የጦሩ አካላት፣ የፖሊስና ደኅንነት ማዕከላት በኃይላቸው መብራት እንዳይቋረጥባቸው ያደርጉ ከሆነ እንጃ፡፡ አለበለዚያ በየትም ሥፍራ በየቀኑ ይቋረጣል፡፡ እርግጥ ነው አንዳንድ ተቋማት የራሳቸው ጄኔሬተር አላቸው፡፡ አዲስ አበባን ብትዞሩ በብዙ ቦታዎች በየደጁ ትናንሽ ጄኔሬተሮች ሲንደቀደቁና በኅብረት በሚያቀናጁት የድምፅ ሁከት አካባቢን ሲበክሉ ታያላችሁ፤ ይህ ዓይነቱ የድምፅና የጪስ ብክለትም አንዱ የመብራት መቋረጥ ጉዳት ነው፡፡(ይህችን ጽሑፍ በማዘጋጅበት በዚህች ዕለት ግን ቢያንስ ከጧት አሁን ድረስ – አምስት ሰዓት ሊጠጋ ነው- አልጠፋብኝም፤ ተመስገን ነው – ሌላ ጊዜ ግን እስካሁን ቢያንስ አራቴ ተቋርጧል፡፡ ዛሬ ጧት ኤዲት እያደረግሁ እያለሁ ግና መብራት ሄደ፣ እንደተለመደው ከ15 ሰዓታት በኋላ በተኛንበት መንፈቀ ሌሊት አካባቢ መጣና መጻፍ ከመጀመሬ ትንሽ ቆይቶ እንደገና ሄደና ግማሽ ሰዓት ጠፍቶ አሁን መጣ – ምሥጋናየም ሳይጠና ውሃ በላው፡፡) በእውነት ፀጉር የሚያስነጭ ሁኔታ ውስጥ ነው ያለነው፤ አንድ ነገር በስሜት እየሠራህ ሳለ ብዙውን ጊዜ ደግሞ ‹ሴቭ› ሳታደርግ ድርግም ይልብሃል፡፡

 

ፍሪጅ ውስጥ መቀመጥ የሚገባቸው ብዙ መድሓኒቶች አሉ፡፡ ምን ይሁኑ? ፍሪጅ ውስጥ መቀመጥ የሚገባቸው የበሰሉም ሆኑ ያልበሰሉ፣ የታሸጉም ሆኑ ያልታሸጉ ብዙ ምግቦች አሉ፡፡ ምን ይብቃቸው? ለሠራተኛ ደመወዝ፣ ለቤት ኪራይ፣ ለግብር፣ ለዕቃ ዲፕሪሼሽን፣ ለቀረጥ፣ ለኅልውና … ብዙ ወጪ ዐይኑን እያጉረጠረጠ የሚጠብቃቸው ሥራቸው በኤሌክትሪክ ፍጆታ ላይ የተመሠረተ ፋብሪካዎችና ኢንዱስትሪዎች፣ ኢንተርኔት ቤቶችና የጽሕፈት አገልግሎት የሚሰጡ ድርጅቶች፣ የኮምፒውተር ማስተማርያ ድርጅቶች፣ የማታ ትምህርት የሚያካሂዱ የትምህርት ተቋማት፣ ባንኮችና ኢንሹራንሶች፣ ምኖችና ምናምኖች ባጠቃላይ ምን ይዋጣቸው? በየመኖሪያና ንግድ ቤቶች ሰዎች እንጀራና ዳቦ ሊጋግሩ ተዘጋጅተው፣ ወጥ ሊሠሩ ሽንኩርት ጥደው … ሳለ ድንገት ይጠፋል፤ ያኔ ያዘጋጁት የእንጀራና የዳቦ ቡኮ ይሾመጥርና ሰዎች ኪሣራ ላይ ይወድቃሉ – ሰዎችም በተለይም ሕጻናትና ልጆች በርሀብ ይሰቃያሉ፡፡ ደመወዝ ከፋዮችን ስናይ በችግር ጊዜ በተለይ ወሩ ዕለት ነው – ወዲያው ከች ይላል፡፡ ምን ከየት አምጥተው ይክፈሉ? ቴክሎጂ እንደምታውቁት አስናፊ ነው – ያማርጣል ማለትም ያሰንፋል -‹ማ›ን አላሏት፡፡ ዛሬ ዛሬ ከኤሌክትሪክ ርዳታ ውጪ የሚከናወን ነገር ብዙም የለም፡፡ አደጉ በተባሉ ሀገሮችማ ከገበታ አንስቶ ወደአፍ የሚያጎርሰውም ኮረንቲው ራሱ ሳይሆን አይቀርም፡፡ እነሱ ከኛ በባሰ ሳይማርጡ አይቀሩም፡፡ በነገራችን ላይ ባደጉ ሀገሮች ለሴከንዶች ኤሌክትሪክ ቢቋረጥ በሣተና የሕግ ጠበቃቸው አማካኝነት ተከራክረው በዚያች ቅጽበት ለደረሰባቸው ማንኛውም ዓይነት ኪሣራና የደንበኞቻቸው  መጉላላት የሞራል ካሣ ጭምር የመብራት አከፋፋዩን ብዙ ገንዘብ ያስቆነድዱታል አሉ፤ እሰይ! እንዲህ ነው የዜግነት መብት መከበር ማለት፡፡ እንዲህ ነው እንደሰው መቆጠርና እንደሰው መታየት ማለት፡፡ በዚህን ዓይነት ማኅበረሰብ ውስጥ መፈጠር መታደል ነው፡፡ እኛ እኮ አይደለም ይህን መሰል የቅንጦት ኪሣራ መጠየቅና በፍርድ ቤት ማስፈረድ፣ የተገደልንበትን ጥይት ዋጋ በወቅቱ ገበያ ተተምኖ እንድንከፍል እንገደዳለን፡፡ እኛ እኮ ሃያ ዓመት ያለጥፋት ታስረን ስናበቃ ጥፋት አለመፈጸማችን ሲታወቅ ይቅርታ ጠይቁና እንፍታችሁ የምንባል ከዐይጥና ከዕንቁራሪት የማንሻል ፍጡራን ነን፡፡ እኛ እኮ ‹አንገታችሁ ተነቀሰ፣ ግንባራችሁ ተከሰከሰ› ተብለን ካለምንም ጥፋት የምንታሰርና የምንገደል አሳዛኝ ፍጡራን ነን፡፡

በአውሮፓና አሜሪካ እባብና እንሽላሊት የእንስሳነት መብታቸው ተጠብቆ ማንም እንዳያንገላታቸው በሕገ መንግሥት ሳይቀር ሲደነገግላቸው፣ የእንስሳት መብት አስጠባቂ ድርጅትም ሲቋቋምላቸው በእኛ ሀገር እኮ ምግብ ሊያቃምሰን የሚቋቋም የረድኤት ድርጅት ሳይቀር በአሸባሪነት እየተከሰሰ እንዲፈርስ ይደረጋል፡፡ በእኛ ሀገር እኮ … ኤዲያ የመርገምት ሀገር፡፡ ለምን አንድያውን እሳቱን አያነድባትም፡፡ ሰብኣዊነት የሌላቸው አውሬዎች ሥልጣን እየያዙ ሚሊዮኖችን እንዲህ በምድራዊ ገሃነም የተንተረከከ የእሳት ፍም ላይ ጥደው ከሚያንጨረጭሩን ሁላችንም እንጥፋና ምድሪቱ የአውሬ መፍንጪያ ትሁን፤ ወደምድረ በዳነትም ትለወጥ፤ ፈቃዱ ከሆነም አዲስ የሰው ፍል አፍልቶ በተሻለ ስብዕና እንደሰው የሚንቀሳቀስ ትውልድ ከእንደገና ያብቅልባት፡፡ እግዚአብሔር በመንበሩ ካለ ይህን ጸሎቴን ይስማ፡፡ የሀገራችንን ነገር ቁጭ ብላቸሁ ስታስቡት ይህ እርግማን በጣም ትንሽ ነው፡፡ ሰው መሆን ካቃተን የሚቀረን ብቸኛ ምርጫ ሰው አለመሆን ነውና ኢትዮጵያ ሰው ማፍራት እንደተሳናት የምትቀጥል ከሆነ መጥፋት በርሷ አልተጀመረምና  ለይቶላት ትጥፋ፡፡ ወደውጭ ስደት፣ የውስጥ ፍልሰትና እንግልት፣ ሞትና መከራ፣ እሥራትና ግርፋት፣ ጭቆናና ብዝበዛ፣ ዘረኝነትና ጎጠኝነት፣ በይና ተበይ፣ በላተኛና የበይ ተመልካች፣ ሻጭና ተሻጭ… ዕጣ ክፍላችን ሆነው እስከወዲያኛው የሚቀሩ ከሆነ አሁኑኑ ኢትዮጵያ የምትባል ሀገር ከምድረ ገጽ ትጥፋ፡፡ በቃ፡፡ መግቢያየና መውጫየ በመለያየቱ አዝናለሁ – የተነሱበትን ሃሳብ ተከትሎ መጨረስ ዱሮ ቀረ፤ አሁን ሁሉም ነገር ተመሰቃቅሎ ሀገርና ሕዝብ ጣር ላይ እያሉ በሥርዓቱ መጻፍ ይቅርና በወጉ መኖርም አልተቻለም – ከሁሉም ሰብኣዊ ሥርዓት ወጥተን አየር ላይ እየተንሳፍፈን የምንገኝ ሕዝብና ሀገር ሆነናል፡፡ ያልተነካ ግልግል ያውቃል ይባላል፤ በዚህች ሀገር ላይ እየወረደ ባለው ሁለንተናዊ ግፍና በደል ስሜታችሁ ያልተነካ ወገኖች በዚህ ደብዳቤ ልባችሁ ሊነካ እንደሚችል ይገባኛል፤ እርግማናችሁን እንደምታወርዱብኝም ይሰማኛል – ማንኛውንም በፀጋ ለመቀበል ዝግጁ ነኝ፡፡ ቢሆንም ከሁልጊዜ ምንትስ የአንድ ቀን ምንትስ ይሻላል እንላለንና እንዲህ አንዳችን አንዳችንን እያረድንና እየበለትን በአንድ ኢትዮጵያዊ ዓለም ውስጥ የገነትና የሲዖል ተምሣሌት የሆኑ ሁለት ተቃራኒ ዓለማትን ፈጥረን አልቃሽና አስለቃሽ ከምንሆን ሁላችንም እኩል የምንሆንበት የመከራ ዐውድማ ይለቅለቅና ሁላችንም እኩል እየተወቃን እናልቅስ፤ ምቀኝነት አይደለም – ለሁሉም የምትሆን ኢትዮጵያን መፍጠር ካልቻልን ለሁሉም የሚሆን አንድ ዓይነት ሁኔታ እንዲመቻች ካለኝ በጎ ምኞት እንጂ፤ ደግሞም ሞኝ አንሁን – ክርስቶስ ራሱ በመሣም አሣልፎ የሚሠጠውን የወፍጮ መጅ በአንገቱ ታስሮ ወደጥልቁ ባህር ቢወረወር እንደሚሻለው ተናግሯልና እንኳንስ ደካማው እኔን መሰሉ ሰው አንድያው የአምላክ ልጅም በጨካኞች ላይ ቆራጥ ብያኔውን ሰጥቷል፡፡ ሰውማ ጠላቱን እንዴቱን ያህል አስበልጦ አይራገም? እናም እላለሁ – እኔም የምመኘው ይሁንልኝ፤ አብረን መኖር ካቃተን፣ አንዳችን የአንዳችንን ጉድጓድ የምንቆፍር ከሆነ፣ በጌቶች ጉሮሮ ጠጅ በድሆች ጉሮሮ መርዝ የሚንቆረቆር ከሆነ – አትታዘቡኝ – አብረን ድራሻችን ይጥፋ፤ ሃሌ ሉያ፡፡

Latest from Blog

ጥር 2 ቀን 2017 ዓ/ም   January 10, 2025  በኢትዮጵያዊነታችሁ፡ በኦርቶዶክሳዊ እምነታችሁ፡ በአማራነታችሁ፡ በአማረኛተናጋሪነታችሁ፡ በተሰነዘረባችሁ ብትር፡ ቤተ ሰብ፡ ወዳጅ ዘመዶቻችሁን ያጣችሁ: ልጆቻችሁን የቀበራችሁ፡ አካልችሁን ያጣችሁ፡ የተሰነዘረውን ብትር በመከላከል ላይ ያላችሁ፡ያለፈቃዳችሁ በመንግሥት ተጽእኖ ወደመግደልና

በኢትዮጵያዊነታችሁ፡ በኦርቶዶክሳዊ እምነታችሁ፡ በአማራነታችሁ፡ በአማረኛተናጋሪነታችሁ፡ በተሰነዘረባችሁ ብትር፡

January 10, 2025
መኮንን ሻውል ወልደጊዮርጊስ ¹⁵ የምድርም ነገሥታትና መኳንንት ሻለቃዎችም ባለ ጠጋዎችም ኃይለኛዎችም ባሪያዎችም ጌቶችም ሁሉ በዋሾችና በተራራዎች ዓለቶች ተሰወሩ ፥ ¹⁶ ተራራዎችንና   በላያችን ውደቁ በዙፋንም ከተቀመጠው ፊት ከበጉም ቍጣ ሰውሩን ፤ ¹⁷ ታላቁ የቁጣው ቀን  መጥቶአልና ፥ ማንስ ሊቆም ይችላል ? አሉአቸው ። ራእይ 6 ፤  15_17 ይኽ የመጽሐፍ ቅዱስ ቃል ። የኢየሱስን ልደት ሰናከብር የየሐንስ ራእይን ማንበብ ጠቃሚ ይመስለኛል ። ምክንያቱም በመጨረሻው ዘመን

ከኢየሱስ የፍርድ ቀን በፊት በህሊናችን ውስጥ ፍቅርን ለማንገስ እንጣር 

የምጣኔ ሀብታዊ ፍጥ፣ የፖለቲካ፣ የእውነትና የሰብአዊ መብት ታጋይ፣ የአመኑበትን ነገር ለመናገር እንደ ፖለቲከኛ በቃላት ሳያሽሞነሙኑ ቀጥታ የሚናገሩት የሀገሬ ኢትዮጵያ ታላቅ ሰው ነበሩ “ዘር ቆጠራውን ተዉት፤ የአባቶቻችሁን ሀገር ኢትዮጵያን አክብሩ!”  አቶ ቡልቻ ደመቅሳ

ሀገር ወዳዱ አቶ ቡልቻ ደመቅሳ ከዚህ አለም በሞት ተለዩ

January 6, 2025
ግን ይህ ሁሉ ወጣት የት ገባ? ግን ይህ ሁሉ ወጣት የት ገባ? ዛሬ፣ 2025 ዓ/ም ላይ ብንገኝም በዝንጋታ ገመድ ወደ ሞት እየተጎተትን እንደሆነ አናውቅም። (ሁል ጊዜ የሚሞተው የገነዝነው ይመስለናል። ) “ገብርዬ ነበረ

ግን ይህ ሁሉ ወጣት የት ገባ?

January 3, 2025
መኮንን ሻውል ወልደጊዮርጊስ ዛሬ እንደ አውሮፓዊያኑ አቆጣጠር ጥር 1ቀን 2025 ዓ/ም ነው ። አውሮፓውያኑ አዲስ ዓመትን “ሀ” ብለው ጀምረዋል ። አዲሱን ዓመት ሲጀምሩም ከልክ ባለፈ ፈንጠዚያ ነው ። ርቺቱ ፣ ምጉቡና መጠጡ

ዛሬ፣ 2025 ዓ/ም ላይ ብንገኝም በዝንጋታ ገመድ ወደ ሞት እየተጎተትን እንደሆነ አናውቅም። (ሁል ጊዜ የሚሞተው የገነዝነው ይመስለናል። )

Go toTop