ያለስም፣ ስም – ስጡኝ
ቅጡኝ፣ አስቀጡኝ፤
አግዙኝ፣ ወርውሩኝ፣…… በማጎሪያችሁ
እሰሩት…. እጀን፣…… በካቴናችሁ
‘ጠንዙት’…..እግሪን፣ …. በእግር ብረታችሁ
ቸንክሩት፣ ገንዙት፣ ….. ይደንዝዝላችሁ
ሽባ ሆኘ ልቅር፣ ‘’ልሰንከልላችሁ’’::…….
እንካችሁ …. ጀርባዬን
መጫሚያ፣ መዳፌን፤
ግረፉት፣ አቃጥሉት፣ …. በኮረንቲ ገመድ
የሰራ አከላቴ፣ ይክሰል፣ ይሁን ዓመድ::…….
ዝረፉት ……. ሀብቴን
ቤትና ንብረቴን፣ በምድር ያለኝን፤
ሰብስቡ፣ አከማቹት፣ ለዓለም ይሁናችሁ
ለማይጠረቃው፣ ለከርስ ዓላማችሁ
ለማፍረስ፣ ለመናድ፣ ለጥፋት ግባችሁ ::……….
እንካችሁ…… ደረቴን
እንካችሁ…… ግ’ባሪን፤
ለታንክ፣ ለመትረጊስ፣ ለጥይታችሁ
አፍስሱት ደሜን፣……. እስኪከረፋችሁ
አድቅቁት አጥንቴን፣……. እስኪወጋችሁ::…………
እንካችሁ……… እንካችሁ
ሥጋ – ሰውነቴን፣ ለጉድጓዳችሁ
ለመቃብራችሁ::…….
እንካችሁ……… እንካችሁ
ሁሉንም ……… እንካችሁ፤…….
…….. ግን “የእፍኝት ልጆች”…….
………. የሀገር እስስቶች ………….
………… እናንተ እኩያኖች፤……….
ምድር ሰማይ ሆኖ፣ ሰማይ ቢሆን ምድር፣ ቢፋለስ ተፈጥሮ
በጨረቃ ቦታ፣ ብትወጣ ጸሀይ፣ ዘመን ተቀይሮ፤
ቢተባበራችሁ፣ የዓለም ኃይል በአንድነት
እኔ እማልሰጣችሁ፣ እናንተ እማትወስዱት፤……
የሰው ልጅነቴን፣ ኢትዮጵያዊነቴን!
አረንጓዴ – ቢጫ – ቀይ፣ ሰንደቅ ዓላማዬን!
ከዓምላክ ያገኘሁት፣ ፍጹም ነጻነቴን!
—–//—-
ፊልጶስ/ ግንቦት 2005