እስካለፈው ሃሙስ ድረስ የአውራምባ ታይምስ ድረገጽ አዘጋጅ አቶ ዳዊት ከበደ ጋዜጠኛ ነው ብዬ አምን ነበር። ባለፈው ሃሙስ በአቶ ዳዊት ድረገጽ ላይ ስለ ዶ/ር ብርሃኑ ነጋ የተለጠፈውን የድምጽ ቅጂ አዳመጥኩኝ ፤ የተጻፈውንም አጭር ጽሁፍ አነበብኩ። አቶ ዳዊት የሚሰራው የጋዜጠኛ ስራ ሳይሆን ፡ የካድሬና ፕሮፓጋንዳ ስራ መሆኑን አምኜበታለሁ። ላብራራ። የድምጽ ቅጂውን ያዳመጠ ሰው በቀላሉ እንደሚረዳው ዶ/ር ብርሃኑ ተሰጠን ያሉትን ገንዘብ ከግብጽ ለመሆኑ በቅጂው ላይ ምንም መረጃ የለም። ለምነድን ነው ታዲያ አቶ ዳዊት በጽሁፍ “ምንጮቻችን” ገንዘቡ ከግብጽ እንደሆነ ነግረውናል ያለው? እዚህ ላይ አቶ ዳዊት ተራ የካድሬነት ስህተት ፈጽሟል።
ቅጂው በዩ-ቱዩብ ላይ የተለጠፈበት ጊዜ
(ረቡዕ ጁን 19) የአሜሪካው ምክር ቤት የዉጭ ጉዳይ ኮሚቴ “ድህረ መለስ ኢትዮጵያ” በሚል ያደረገውን ጉባዔ ለማጥቃት የተደረገ ይመስላል ፤ ምክንያቱም ዶ/ር ብርሃኑ ተጋባዥ መሆናቸው ቀድሞ ስለታወቀ።
አቶ ዳዊት በድረ-ገጹ ላይ የድምጽ ቅጂውን ከዩ-ቱዩብ የለጠፈው ሃሙስ ጁን 20 ነበር። ሃሙስ ጁን 20 የአሜሪካው ምክርቤት ጉባዔ የተደረገበት ቀን ነው። ዳዊት ምን ነካው? ከምር! ምን ነካው? እኔ የግንቦት-7 ደጋፊ አይደለሁም ፤ ግን ግንቦት-7 የእኔ ችግር አይደለም ፡ የኢህአዴግ እንጂ። አቶ ዳዊት ይሄ አልገባው ይሆን? ግንቦት-7 እንኳን 500 ሺ ዶላር ፤ 500 ሚሊዮን ዶላር ቢሰጠው ይገባዋል። ግንቦት-7 የቆመለት አላማ በኢትዮጵያ ውስጥ ፍትህ ፡ ነጻነት እና ዴሞክራሲ ለማምጣት እንጂ እንደ ኢህአዴግ በሙስና የነቀዘ ፡ በሰብዓዊ መብት ረገጣ የሰለጠነ ፡ የኮሮጆ ሌባ መንግስት ለመመስረት አይደለም። ታዲያ አቶ ዳዊት ዳግማዊ-አይጋ-ፎረም ለመፍጠር ነው ሙከራቸው? ዳዊት ከአይጋው አቶ ኢሳያስ አጽብሃ በጣም የተሻለ ግብረግብ እና የጋዜጠኝነት መርህ ያለው ሰው ይመስለኝ ነበር።
ድርጊቱ ስህተት ከሆነ አቶ ዳዊት የይቅርታ ደብዳቤ ቢጽፉ የባለሙያ እጣፈንታቸውን ሊያድኑ ይችሉ ይሆናል።
ካልሆነ ግን አውራምባ የአውሬ-አምባ ሆኖ ይቀራል።
– – – – – –
ጸሃፊውን ለመጠርነፍ ፡ ለማስፈራራት ወይም በኮንዶ ለመደደል በዚህ ይጻፉለት፦ yared_to_the_point@yahoo.com