ከይገርማል ታሪኩ
ሻለቃ ሀይለየሱስ እጅጉ መዐሕድን ሲቀላቀሉ ድርጅቱ በአማራው ክልል እግሩን አልሰደደም ነበር:: ችግሩ ፋታ የሚሰጥ አይደለም:: አማሮች ካለአለሁ ባይ: ካለአይዟችሁ ባይ እየተጨፈጨፉ ነው:: በቀልን ሰንቆ ከበረሀ የተነሳውና ስልጣኑን ሙሉ በሙሉ በእጁ ያደረገው ወያኔ ሀላፊነት በጎደለው የጭካኔ ተግባር በአማራው ህዝብ ላይ ሽብር ነዛ- ሞት አወጀ:: መዐሕድን በሁለት እግሩ እንዲቆም ለማድረግ በሰውሀይል ማጠናከር ያስፈልጋል:: ህዝብን የማደራጀትና የማንቃት ስራ ገንዘብ ያስፈልገዋል:: የወገን ጩኸት ያባነናቸው አማሮች በከተሞች አካባቢ በቁጭት ድርጅቱን ለማጠናከር ደፋ ቀና ማለት ጀመሩ::
ብዙሀኑ ገበሬ ምን እየተደረገ እንደሆነ እንኳ አያውቅም:: መንግስት ይመጣል መንግስት ይሄዳል:: “ሽህ ቢታለብ ያው በገሌ” እንዳለችው ድመት ማንም መጣ ማን ያው አርሶ አደር ነውና ሁሉም የእለት ጉርሱን የአመት ልብሱን ያሟላ ዘንድ ደፋ ቀና ይላል:: ሌሊት ወጥቶ ሌሊት ይገባል:: ጠብ ለማይል ኑሮ ነጋ ጠባ ደፋ ቀና እንዳለ ይኖራል:: ወሬ የሚያዳምጥበት ጊዜ የለውም:: ብቻ ይሰራል- ሰርቶ ከሚያገኘው ይገብራል:: ገበሬው የሚፈቀደው የግብር ጊዜ ወይም የተለየ መዋጮ እንዲያደርግ ሲፈለግ: አሊያም ለውትድርና:: ከዚያ ውጭ የት ወደቀ የሚለው የለም:: እርሱም የቤቱን ገበና ለመሸፈን ላይ ታች ከማለት ውጪ ስለፖለቲካ የሚያውቀው ነገር የለውም:: መንግስት- አስተዳዳሪ: የህዝብን ሰላም የሀገርን ዳር ድንበር አስጠባቂ: መሰረት ልማት (መንገድ: አስኳላ ትምህርት: የጤና ተቋም…) አስፋፊ መሆኑን ያውቃል:: የመንግስት ዘር መኖሩን ግን አያውቅም:: አንዱን ህዝብ ጎድቶ ሌላውን ለመጥቀም እንደሚያልምም አያውቅም:: በርግጥ በዘር ወይም በቀረቤታ የሚሰሩ ባለስልጣኖች እንደነበሩ: አሁንም እንደማይጠፉ ያውቃል:: የማያውቀው ነገር ቢኖር መንግስት ለአንዱ ወላጅ አባት ለሌላው ደግሞ የእንጀራ አባት መሆን ስለመቻሉ ነው::
ከተሜው የገበሬውን ያህል ለፖለቲካ ሩቅ አይደለም:: ለሚዲያወች የተሻለ ቀረቤታ ስላለው ምን እየተካሄደ እንዳለ መጠነኛም ቢሆን ግንዛቤው አለው:: ስለዚህ ይህንን የህብረተሰብ ክፍል ማደራጀት ብዙም አይከብድም:: ግን እንዴት? ሰላምና መረጋጋት ብሎ መንግስት ያደራጃቸውና የኮር አባል ተብለው የሚታወቁት ምልምል ካድሬወች ህዝቡን ሰላሙን ነሱት:: በኮር አባላት ስብሰባ ላይ የመጀመሪያው ክፍል ኢንፎርሜሽን ማቀበል ነው:: ስለዚህ የኮር አባላቱ አይደለም የሚወራውን የሚበላውንና የሚጠጣውን ሳይቀር እያነሱ እገሌ እንዲህ አለ: እገሊት ከገሊት ቤት ቡና ጠጣች በማለት በየተሰጣቸው ቀጠና ያዩትንና የሰሙትን እያጋነኑ ያቀርቡ ጀመር:: ኢንፎርሜሽን ያላመጣ የኮር አባል ስለሚገመገም ግምገማውን ለማለፍ አይደለም የታየውና የተሰማው ያልታየና ያልተደረገው ሁሉ በንጹሀን ላይ መወራት ጀመረ:: የኮር አባላቱ በግላጭ አይታወቁ ስለነበር አንዱ አንዱን ማመን እየከበደው መጣ:: ፍርሀትና ጥርጣሬ ነገሰ:: የመንግስትን ፖሊሲ ይነቅፋሉ የተባሉ ሰዎች የተነፈሱት ሳይቀር እየተነገራቸው ከድርጊታቸው እንዲታቀቡ ምክርና ማስፈራሪ ይሰጣቸው ጀመር:: ምክርና ማስጠንቀቂያውን የጣሱ ሰዎች ሰርቀው ሊያመልጡ ሲሉ ተገደሉ: ወይም መጠጥ ቤት በተነሳ ግጭት ክፉኛ ተደብድበው ሞቱ: ወይም ባላንጣ ጊዜ ጠብቆ ገደላቸው እየተባሉ ተወገዱ:: የደርግ የቀይ ሽብር በድብቅ መተግበር ጀመረ:: ይህን ዘመን ለማለፍ ከተሜው ኮረንቲና ፖለቲካን በሩቁ አለ::
ድርጅት ለመመስረት የሚደረገው ትግል ግን በምንም መልኩ ሊደናቀፍ አይችልም:: መከፈል የሚያስፈልገው መስዋእትነት ተከፍሎ መዐሕድ እውን መሆን አለበት:: ድርጅቱ ስር እስኪሰድ ድረስ ለየት ያለ አካሄድ መከተል እንደሚገባ በመታመኑ በአንዳንድ አካባቢ ዱሮ በኢሕአፓ ጊዜ በነበረው የአደረጃጀት ስርአት መሰረት እምነት የሚጣልባቸውን በተለይ ደግሞ በዚህ መንግስት ደስተኛ ያልሆኑትን ሰዎች ሁለትና ሶስት በአንድ ላይ በማደራጀት ግንዛቤ ማስጨበጥና የአባልነት ፎርም ማስሞላት ተጀመረ:: በዚህ መልክ ውስጥ ውስጡን መዐሕድ ስር መስደድ ጀመረ:: በርግጥ የመጣውን ሁሉ በጸጋ ለመቀበል የግንባር ስጋ ሆነው ፈጥጠው የወጡ በርካታ ሰዎች ነበሩ:: መዐሕድ የሰላም ታጋይ ድርጅት ነው:: ሰላማዊ ትግል ማለት ቅሬታን ሰላማዊ በሆነ መንገድ መግለጽ ማለት ነው:: ቅሬታ መፍትሄ ካላስገኘ ትግሉ በመንፈስና በአካል እስከመሸፈት ያደርሳል:: ይህም ማለት ከሀይል ርምጃ በመለስ ያሉትን ሁሉ መጠቀም: እምቢ አልታዘዝም አላደርግም በማለት ተቃውሞን መግለጽን ያጠቃልላል:: አዎ! ሰላማዊ ትግል ማለት ከመንግስት በኩል የሚሰነዘረውን ማንኛውም ጥቃት በሰላም መቀበል ማለት ነው:: ሳያቆስሉና ሳይገድሉ እየቆሰሉና እየሞቱ ማሸነፍ ማለት ነው:: ይህ የትግል ባህሪ በለየላቸው የወያኔ አይነት አምባገነን መንግስታት ዘንድ በእጅጉ ጎጅ ነው:: የህዝብ እምቢ ማለት አያስደነግጣቸውም:: ራሳቸውን መለስ ብለው ለመመርመር አያስችላቸውም:: ይልቁኑ በተደፈርኩ መንፈስ ያወራጫቸዋል:: ለበቀል ጦራቸውን ይሰብቁና ያገኙትን ሁሉ ማጥቃት ይጀምራሉ:: በዚህ መልኩ ሰላማዊ ትግል መስዋእትነቱን ያከፋዋል:: ኋላቀር በሆኑ አምባገነኖች በሚመሯቸው አገሮች ዘንድ ሰላማዊ ትግል የሽምቅ ውጊያ ያህል ያስቀጣል:: ሰላማዊ ታጋይ ማለት ለመንግስት አመራር አልመችም የሚል አጉራ ዘለል ነውና የሸማቂውን ያህል ይቀጣል:: አምባገነኖች አይደለም የተቃወማቸውን ኮከባቸው ያልፈቀደውን ሰው ሁሉ ቢገሉ ይችላሉ:: ወያኔወች ደግሞ ሰላማዊ ታጋይ ያውም የአማራ ማየት ቀርቶ መስማትም አይፈልጉም:: ሆኖም በአግባቡ ከተጠቀሙበት ሰላማዊ ትግል በአጭር ጊዜ ውጤታማ ያደርጋል:: ውጤታማነት ከጠንካራ አደረጃጀትና ከበሳል አመራር ውጭ አይገኝም:: መዐሕድ አመሰራረቱ ለፖለቲካ የስልጣን ፉክክር አይደለም:: አላማው በአማራው ላይ እየደረሰ ያለውን ዘርፈ ብዙ ጭቆናና ግድያ ለአለም መንግስታትና ለሰብአዊ ድርጅቶች ለማሰማት ነው:: ግን ሁሉም ትግል ያስፈልገዋል:: በዚህ ሂደት ወያኔ መራሹ መንግስት መውደቅ ከቻለ እሰየው ነው- በደምና በአጥንት የሚያምኑት እኩዮች ከጠፉ አማራውን ለይቶ የሚያሳድድ አይኖርም ማለት ነው:: ከዚያ በኋላ ለኢትዮጵያ የሚበጅ የህዝብ አስተዳደር ለመመስረት ተፎካካሪ ሆኖ መቅረብ ይቻላል:: ለሁሉም የህዝብን መንፈስ መማረክ የሚያስችል ሁለንተናዊ ብቃት መጎናጸፍ ያስፈልጋል::
የልጆች ማስፈራሪያ “አባ ዳውሎ” ተብሎ ይጠራል:: አባ ዳውሎን አይቶ የሚያውቅ ልጅ የለም:: ግን አባ ዳውሎን ይፈራል:: ሲያለቅስ የነበረን ልጅ “አባ ዳውሎ መጣብህ” ካሉት ልቅሶውን ይውጣል:: ሻእቢያና ወያኔ ደግሞ ብሄር ብሄረሰቦችንና ህዝቦችን የሚያስፈራሩት “አማራ መጣልህ” ብለው ነው:: በሻእቢያና በወያኔ የተሰበከ የዋህ ይህንን ተቀብሎ አስተጋብቷል:: በኤርትራ እናቶች ልጆቻቸው ሲያስቸግሯቸው “አማራ መጣልህ” ይሏቸው ነበር:: አማራ አፉ እንደአዞ አፍ 180 ዲግሪ የሚዘረጋ ጆሮው እንደዝሆን የሰፋ: አስፈሪ የሆነ ፍጡር እንደሆነ ተደርጎ እየተነገራቸው ያደጉት ልጆች ታዲያ አማራ መጣብህ ሲባሉ ቱር ብለው የትም ይጠፋሉ- እናቶችም ከህጻናቱ ብጥበጣ ተንፈስ ይላሉ:: ይህ በኤርትራ የልጆች ማስፈራሪያ የነበረው አማራ አሁን ከልጆች አልፎ የብሄር ብሄረሰቦች ማስፈራሪያ ሆኗል:: “ነፍጠኛ” የአማራ ተለዋጭ ስም ነው:: እና ነፍጠኞች ከተባለ አማሮች ማለት ነው:: “ነፍጠኞች የብሄር ብሄረሰቦች ጠላቶች ናቸው- ኢትዮጵያ ደግሞ እስር ቤታቸው:: ነፍጠኞች አንገታቸውን ቀና ሊያደርጉ አይገባም:: አንገታቸውን ቀና ካደረጉ መሬትህን ይወስዳሉ: ነጻነትህን ይነጥቃሉ” ነቅተህ ጠብቅ ተብለው ይቀሰቀሳሉ:: የኢትዮጵያ ብሄር ብሄረሰቦች አማሮችን ጠንቅቀው ያውቋቸዋል:: አማሮች በያሉበት ላባቸውን አንጠፍጥፈው ሰርተው የሚኖሩ እንደሆኑ አሳምረው ያውቃሉ:: አሁን አማራ ክልል ተብሎ በሚታወቀው ክልል የሚኖሩ አማሮችም ቢሆኑ የእግር ጫማ እንኳ የሌላቸው ለፍቶ አዳሪወች መሆናቸውን ይረዳሉ:: አማሮች ጠላቶቻችሁ ናቸው ሲባሉ ግራ ተጋብተዋል:: የትኞች አማሮች ናቸው የእኛ ጠላቶች ብለው መጠየቅ አይችሉም:: እንዲህ ያለ ሰው “የነፍጠኛ ሎሌ” ሊባል ይችላል:: አማሮች በየቦታው ሲታደኑ ብሄር ብሄረሰቦች ውስጣቸው በሀዘን ተኮማትሯል:: በየቦታው ተበትነው ባሉት አማሮች ላይ ጥቃት ለመፈጸም በወያኔና በአጋሮቹ ከተዘጋጁት ገዳይ ስኳዶች ግን ሊታደጓቸው አልቻሉም:: እና የብሄር ብሄረሰቦች አባ ዳውሎ (አማራ) ዘሩ እንዳይጠፋ ተደራጅቶ ድምጽን ከፍ አድርጎ መጮህ: ቀሪውን ወንድም ኢትዮጵያዊ ሀቁን ማስጨበጥና የትግል አጋር ማድረግ ያስፈልጋል::
ሻለቃ ሀይለየሱስ በባህርዳር ልዩ ዞንና በምእራብ ጎጃም ዞን ከፍተኛ ሀላፊነት ተጥሎባቸዋል:: አባላትን መመልመል: ማደራጀት: የአባላት መዋጮ ማሰባሰብና ቢሮ መክፈት ይኖርባቸዋል:: ሰው የመቅረብ ልዩ ችሎታቸው ወሳኝ የሆኑ ሰዎችን ለማግኘት ረድቷቸዋል:: በጥቂት ወራቶች ውስጥ ምእራብ ጎጃምን እስከቀበሌ ድረስ ወርደው ማደራጀት ቻሉ:: ቢሮወች በበርካታ የወረዳ ከተሞች ተከፈቱ:: ቀስ በቀስ የህቡእ እንቅስቃሴው ገሀድ መውጣት ጀመረ:: የባህር ዳር ቢሮ በማእከልነት ያገለግል ጀመር:: ምንም እንኳ ሀይለየሱስ የምእራብ ጎጃምና የባህርዳር ልዩ ዞን አስተባባሪ ቢሆኑም በክልሉ ዋና ከተማ ተቀማጭ ስለሆኑ የአማራውን ችግር ከየዞኖች እየተቀበሉ ለበላይ የማሳወቅ ስራ በመስራት: መግለጫ በማውጣትና ህዝባዊ ስብሰባወችን በማካሄድ ግዙፍ ስራ ሰርተዋል:: በሰሜን ጎንደር: በደቡብ ጎንደር: በአዊና በምስራቅ ጎጃም ዞኖች ከአቶ አባይነህ ብርሀኑ ጋር በመሆን የዞን አስተባባሪወችን መልምለዋል- ቢሮወችን ከፍተዋል::
የት ይደርሳሉ ብለው በንቀት ይመለከቷቸው የነበሩ የየደረጃው የወያኔ አንጋቾች ህዝቡ ቀስ በቀስ ከእጃቸው እያፈተለከ ወደ መዐሕድ እቅፍ መሰባሰቡን ሲያዩ መበራገግ ጀመሩ:: በሻለቃ ላይ ፈተናወች በዙ:: መጀመሪያ ምክር ቢጤ ተሰጣቸው:: “ምንህ ተነካ- ለምን አርፈህ አትቀመጥም” ተባሉ:: ቀጠሉ የወያኔ ተስፈኞች- ” ብታርፍ ይሻልሀል:: አሊያ አወዳደቅህ ይከፋል” አሏቸው:: አልገባቸውም እንጅ ሀይለየሱስ አይደለም ለዛቻ ለጥይትም አይንበረከኩ:: ይህን ትግል ሲቀላቀሉ ብዙ ነገር ሊደርስባቸው እንደሚችል ተረድተው ነው የወሰኑት:: እና ሀይለየሱስ ይበልጥ ቀበቷቸውን ጠበቅ አድርገው ህዝብ የማደራጀቱን ስራ ገፉበት:: ፖሊሶችና የደህንነት ሀይሎች በየሄዱበት ይከታተሏቸዋል:: ሻለቃ ክፉ አይወጣቸውም:: ብቻ “እንዲያው ልፉ ብሏችሁ እኮ ነው” ይላሉ: ምንም ስህተት እንደማይገኝባቸው ለመግለጽ::
“ማሸማቀቅ” የወያኔ አንዱ የትግል ስልት ነው:: አንድ ሰው ከሚፈጽመው ተግባር እንዲታቀብ ለማድረግ ሲፈለግ በስብሰባ ላይ የማስደንገጥ: በፖሊስና በደህንነት ክትትል የማስበርገግ ድርጊት ነው- ማሸማቀቅ:: ይህ ግን ሀይለየሱስ ዘንድ ሊሰራ አልቻለም:: ራሳቸው ሀይለየሱስም ሆኑ ቤተሰቦቻቸው በሌሉበት ቤታቸው በተደጋጋሚ ተፈትሿል:: ምን ይገኝባቸዋል? ምንም:: እርሳቸው እንደሆኑ የሰላም አርበኛ::
ወያኔ መዐሕድን ለማጥቃት ሲንቀሳቀስ ብአዴኖች ግዳይ ጥለው ሊሾሙ ሊሸለሙ ተቁነጠነጡ:: በወቅቱ የተከሰቱ ችግሮች ሁሉ የመዐሕድ አፍራሽ እንቅስቃሴ ውጤቶች ተደርገው በመንግስት ሜዲያወች ይናፈሱ ጀመር:: መዐሕድ “ካለወቅቱ የመጣው ዝናብ በእኛ እንዳይሳበብ እየሰጋን ነው” ሲል ወያኔ እየፈጠረበት ያለውን ልብ ወለድ ክስ ነቀፈ:: ወያኔ ግን ሰቅጠጥም አላለ:: ይባስ ብሎ በፈጠራ ክስ የድርጅቱን መስራችና የአማራ ጠበቃ የነበሩትን ፕሮፌሰር አስራት ወ/የስን አሰረ:: የወያኔ አላማ መሪው ከጨዋታ ውጪ ከሆነ ተከታዩ ይበተናል የሚል የተሳሳተ አላማ ነበር:: ያ ዱሮ ቀረ:: ዱሮ የጦር መሪ ሲሞት ሰራዊቱ ትጥቁን ይፈታ ነበር አሉ:: “ንጉስህ ወይም መሪህ ተማርኳልና እጅህን ስጥ” ተብሎ ይለፈፋል:: በቃ በዚያው ጦርነቱ ያበቃል:: ያ ጊዜ አሁን አይደለም:: ሰላማዊ ፍልሚያው ይበልጥ ተጧጡፏል:: አባላት ይመዘገባሉ: ቢሮወች ይከፈታሉ: የፖለቲካ ትምህርት ይሰጣል::
የመዐሕድ ጩኸት ፍሬ አሳየ:: አማሮችን በአማራነታቸው ብቻ ሰብስቦ መግደል ጋብ አለ:: ስለዚህ አሁን መዐሕድ ከአማራው አልፎ ለመላው ኢትዮጵያዊ ሊቆም የግድ ይላል የሚሉ ወገኖች ተበራከቱ:: እውነት ነው:: መጀመሪያምኮ ቢሆን መዐሕድ የተመሰረተው አማራ ተኮር የሆነ ግድያ በመስፋፋቱ ብቻ ነው:: ይህ ችግር ተንፈስ ካለ የሚቀጥለው ተግባር በኢትዮጵያ ላይ በጉልበቱ ነግሦ በዘርና በቋንቋ ህዝቡን እየከፋፈለ ያለውን ጸረ ህዝብና ጸረ ኢትዮጵያዊ ድርጅት ከኢትዮጵያውያን ጫንቃ ላይ አሽቀንሮ መጣል ይሆናል:: ይህ ውጤት ሊመጣ የሚችለው መላው ኢትዮጵያውያን በአንድ ላይ ተሰባስበው ለአንድ አላማ መሰለፍ ሲችሉ ብቻ ነው:: መዐሕድ ግቡን አሳክቷል:: ቀጣዩ ትግል ሁሉንም ኢትዮጵያዊ በእኩልነት የሚያሳትፍ ድርጅት መስርቶ በዚያው የሚካሄድ ይሆናል:: በዚህ መልኩ መኢአድ ተመሰረተ::
ሻለቃ ሀይለየሱስ እጅጉ ኢትዮጵያዊ ወታደር ነበሩ:: ሲያደሙና ሲደሙ የነበሩት ለሀገራቸውና ለህዝባቸው ነው:: ሀገራቸው ኢትዮጵያ ህዝባቸውም ኢትዮጵያውያን ናቸው:: ቀዳሚ አላማቸውን ከመዐሕድ ጋር ያሳኩት ሀይለየሱስ ለቀጣይ ግዳጅ ከመኢአድ ጋር ተሰለፉ::
ይቀጥላል