አቶ ታዬ ደንደዓ ዛሬ ህዳር 25 ቀን 2017 ዓ.ም. አመሻሹን ከማረሚያ ቤት ብለቀቁም ቤተሰቦቻቸውን ሳይቀላቀሉ ከማረሚያ ቤቱ በራፍ በጸጥታ ኃይሎች መወሰዳቸውን ቤተሰቦቻቸው ለዶይቼ ቬለ ገለጹ፡፡ ክስ ተመስርቶባቸው በእስር ላይ የሚገኙት አቶ ታዬ ደንደዓ ከትናንት በስቲያ ሰኞ ህዳር 23 ቀን 2017 ዓ.ም. የዋስትና መብት ተጠብቆላቸው ከእስር እንዲለቀቁ በፌዴራሉ ሰበር ሰሚ ችሎት መወሰኑ ይታወሳል፡፡
በተወሰነላቸውም መሰረት ቤተሰቦቻቸው በፍርድ ቤቱ ትዕዛዝ መሰረት የሕግ ሂደቶቹን ባለፉት ሁለት ቀናት አጠናቀው አቶ ታዬ ዛሬ በኢትዮጵያ ሰዓት አቆጣጠር አመሻሹን 11 ሰዓት ላይ ከቂሊንጦ ማረሚያ ቤት ብለቀቁም የፀጥታ ኃይሎች የማረሚያ ቤቱ በራፍ ላይ ጠብቀው ወዳልታወቀ ስፍራ እንደወሰዱዋቸው ባለቤታቸው ወ/ሮ ስንታየሁ ዓለማየሁ ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል፡፡
“ወደ ቂሊንጦ ማረሚያ ቤት ስንመጣ ፊትለፊቱ ሁለት ፓትሮሎች ነበሩ” ያሉት ወ/ሮ ስንታየሁ “ማስክ ያደረጉ የደህንነት ሰዎች የሚመስሉ ሲቪል የለበሱና የታጠቁ አካላት ልክ አቶ ታዬ ከማረሚያ ቤቱ ወጥተው ደጅ ላይ ልንቀበለው ስንሄድበት መኪና አዘጋጅተሃል ወይ አሉትና ከዚያም አስቀድሞም እንደተጠራጠርነው ለሌላ ጉዳይ ትፈለጋለህ ብለውት ያዙት” ብለዋል፡፡
የአቶ ታዬ ባለቤት ወ/ሮ ስንታየሁ አክለው እንዳሉት ባለፈው ሰኞ የፌዴራል ሰበር ሰሚ ችሎት አቶ ታዬ እስካሁንም የዋስትና መብታቸው “በጠባብ የህግ ትርጉም ሳይጠበቅ መቆየቱን” አስረድቶ በ20 ሺህ ብር ዋስትና ክሳቸውን ከውጪ መከታተል እንዲችሉ ነበር ያለው፡፡ በዚሁ መሰረት ትናንትና የአቶ ታዬ ቤተሰቦች ወደ ቂሊንጦ ማረሚያ ቤት ስያቀኑ በፍርድ ቤቱ የተላለፈላቸው ትዕዛዝ የቀንና የቁጥር ስህተት ያለው በመሆኑ እንዲስተካከል በተባለው መሰረት ዛሬ ከፍርድ ቤቱ ያንኑን አስተካክለው ወደ ማረሚያ ቤት ተመልሰው ሂደቱን አጠናቀው ማረሚያ ቤቱ በፍርድ ቤቱ ትዕዛዝ መሰረት ብለቃቸውም ከወጡ በኋላ መወሰዳቸውን አሳዛኝ ሲሉ ገልጸውታልም፡፡
“ችሎቱ የተቻለውን ብያደርግም የምናየው ነገር በጣም ያሳዝናል” ያሉት ወ/ሮ ስንታየሁ “ደብዳቤው ታርሞ በመምጣቱ ማረሚያ ቤት ብለቃቸውም በውሉ ሰላምታ እንኳ ሳንባባል ነው ውጪው ላይ ከመሃላችን ነጥቀው የወሰዱት” በማለት የት እንደሚወስዱዋቸውም እንዳልተነገራቸው አስረድተዋል፡፡ አመሻሹን በዶይቼ ስለጉዳዩ የተጠየቁት የፌዴራል ፖሊስ ቃል አቀባይ አቶ ጀኢላን አብዲ መረጃ እንደሌላቸውና እስከ ነገ እንደሚያጣሩ አስረድተዋል፡፡
የቀድሞ የሰላም ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታና የገዢው ብልጽግና ፓርቲ ከፍተኛ ባለስልጣን የነበሩት አቶ ታዬ ደንደዓ ከተከሰሱባቸው ሶስት ክሶች ሁለቱ ውድቅ ተደርጎላቸው “ከህግ አግባብ ውጪ የጦር መሳሪያ ይዘው ተገኝተዋል” በሚል የተመሰረተባቸውን አንዱን ክስ በፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ችሎት በመከላከል ሂደት ላይ እንደነበሩ ዶቼ ቬለ ነው የዘገበው።
መረጃው – የፋስት መረጃ ነው