(አሁንገና ዓለማየሁ)
በብሊንከን የሚመራውን ጸረ ኢትዮጵያና ጸረ አማራ የስቴት ዲፓርትመንት ስታፍ ሁላ ማባረሪያው ጊዜ አሁን ነው!!!
ኢትዮጵያ የህልውና አደጋ ተደቅኖባት እለት እለት ወደ መበታተን ጠርዝ እየተገፋች ትገኛለች። በዚህ ወቅት ኢትዮጵያዊ አሜሪካዊው መራጭ በአቅራቢያው ፖለቲካ ምቾት የሚሰጡትን ተመራጮች ከመምረጥ ይልቅ በምሥራቅ አፍሪካ ላይ ከፍተኛ አደጋ የማይደቅነውን የፖለቲካ ፓርቲ ቢመርጥ ለኢትዮጵያ ህልውና መጠበቅ የሚበጅ ሥራ ይሠራል። የአሜሪካ የውጭ ፖሊሲ በአሜሪካ ኢንተረስት ላይ ብቻ የተመሠረተ ነው የሚባለው ነገር ትክክል ቢሆንም ከዲሞክራቲክ ፓርቲና ከሪፐብሊካን ፓርቲ ጋር የተጣበቁ ኢንዱስትሪዎችና ፖለቲከኞች የተለያዩ ከመሆንም አልፈው የንግድና የፖለቲካ ፍልስፍናቸውና ትስስራቸውም የተለያየ ነው።
ዲሞክራቶች በአፍሪካ በተለይ እጅግ አውዳሚ ፖሊሲዎችን የተከተሉ መሆናቸው በመጽሐፍ የምናነበው ሳይሆን ራሱ የኛው ትውልድ ዋቢ የሆነበት አሳዛኝ ክሥተት ነው። የክሊንተን ዲሞክራት ቡድን ኤርትራን አስገንጥሎ፣ ሱማሊያን ብትንትኗን አውጥቶ፣ የሩዋንዳን ጭፍጨፋ አካሂዶ በተለይ በሱ ዘመን ኢትዮጵያ የመጡ እንቃቅላ የስቴት ዲፓርትመንትና የዲፕሎማሲው ክፍል ወጣቶች ከወያኔ ጋር እየተዳሩ፣ ከዝርፊያውና ዳንኪራው እየተሳተፉ በክሊንተን ስምነት አመት፣ በኦባማ ስምንት አመት፣ ጥርስና ጥፍር ቀንድ አውጥተው በባይደን ፕሬዚደንሲ ግዙፍ የሥልጣን ማማዎች ላይ የሚገኙ አማራ በጅምላ ቢፈጅ፣ በጅምላ ቢቀበር፣ በሚልዮናት አኅዝ ቢፈናቀል፣ መሠረተ ልማቱ ቢወድም ግድ የማይላቸውና እንዲያውም ያንሳል ብለው ያለው መንግስት ከአይ ኤም ኤፍና ወርልድ ባንክ ብድር እንዲያገኝ ያመቻቹ ጸረ ኢትዮጵያ መንጋ ለመሆን በቅተዋል። ብዙዎቹ ከወያኔ ባለሥልጣናት ጋር በአምቻ ጋብቻ፣ በጉዲፈቻ ጭምር የተቆራኙ ናቸው።
ሪፐብሊካን ፓርቲን በመምረጥ ቢያንስ እነዚህ መዥገሮች ለአራት አመት ከሀገራችን ቆዳ ላይ ተነቅለው መጠነኛ እፎይታ እናገኝ ዘንድ እመክራለሁ። “ከዝንጀሮ ቆንጆ ምን ይመራርጧል። ሁሉም ጸረ አፍሪካ ናቸው” የምትሉ ትኖራላችሁ። ከአንደኛው ግን አንደኛው ይብሳል። ዲሞክራቶች በዘመነ ካርተር ኢትዮጵያን ገንዘብ የተከፈለበት የጦር መሣሪያና የቴክኒክ ድጋፍ በመከልከል በሶማሊያ ወረራ ጭንቅ ውስጥ የገባው ደርግ ወደ ሩሲያ እቅፍ እንዲሄድ ያደረጉ በዚህም በኢትዮጵያ ለተከተለው ምስቅልቅል አንደኞቹ ተጠያቂዎች የሆኑ ናቸው። በክሊንተን ጊዜ የኤርትራን መገንጠል ሲያመቻቹ በተቃራኒው ነጻ መንግሥት የመሠረተችው ሶማሊላንድ እውቅና እንዳታገኝ አድርገዋል። በኢትዮጵያ ሰሜን እና ደቡብ ፍጹም ተቃራኒ ፖሊሲ በመከተል ጎጂ ሥራ ሠርተዋል። ዲሞክራቱ ክሊንተን የሩዋንዳን ጄኖሳይድ በአርምሞ ያስፈጸመ ብቻ ሳይሆን የጄኖሳይዱ እልቂት ያስከተለው የቀጠናውና የኮንጎ መፍረስ ቀጥታ ተጠቃሚ እና የማእድን ቱጃር ያደረገው ግለሰብ ነው። በኦባማ ስምንት አመት ዘመን ኦባማም የርሱ ኮልኮሌዎችም ኢትዮጵያ እየተመላለሱ በወያኔ የፉገራ ምርጫ ላይ የዲሚክራሲያዊነት ሰርተፊኬት ማኅተም ሲያደርጉ የነበሩ ወራዶች፣ ጸረ ዲሞክራሲና ጨካኞች ናቸው። ካርተርም ከመቃብር ተመልሶ የካርተር ማእከል በሚል የማጭበርበሪያ ድርጅቱ ጭምብልነት ኢትዮጵያ መጥቶ ያንኑ ጸረ ኢትዮጵያ የጥላቻ ሥራውን ደግሞ ለመሥራትና ዳግም ኢትዮጵያን ለመውጋት የወያኔን ምርጫ ዲሞክራሲያዊ ነው ብሎ የበየነ ሌላው ወራዳ አንጋፋ ዲሞክራት ነው። ብሊንከን የተባለው የባይደን ተሿሚ እና የርሱ ተላላኪ የበሬ ነጋዴ መሳዩ ማይክ ሃመር በወለጋ፣ መተከል፣ ሻሸመኔ፣ አርሲ፣ አዲስ አበባ ወዘተ በአማራ ላይ የሚደረገውን የዘር ማጥፋት ጭፍጨፋ ሳያወግዙ ከዚያ በኋላ በመጣው በትግራይ ጦርነት ጊዜ እጅግ የተወራጩ፣ የዘር ጨፍጫፊዎቹን ከተጠያቂነት አስመልጠው አቅፈው ያሸላለሙ ልክ እንደ ኸርማን ኮህን ከአሜሪካ መንግሥት ሌላ የበላይ አለቃ ያላቸው የሚመስሉ አስነዋሪ ዲሞክራቶች ናቸው። ምክንያቱም የሚጣረሰውን አቋምና ተግባራቸውን በምንም ዓይነት ከአሜሪካ ሕዝብ፣ የንግድ ድርጅቶች ወይም የመንግሥት ጥቅም አኳያ ትርጉም ለመስጠት ስለማይቻል።
ስለዚህ የአማራ ሕዝብ ከነዚህ በጸረ ኢትዮጵያ አቋም ሥር የሰደዱና ቀንድ ያወጡ የዲሞክራቲክ ፓርቲ ኮልኮሌዎች ቢያንስ የአራት አመት እፎይታ ያገኝ እና የህልውናውን አደጋ ለመቀልበስ ፋታ ይኖረው ዘንድ በዚህኛው ዙር ሪፐብሊካኖችን አንምረጥ። እዚህ ባለንበት ቦታ ፖሊሲያቸው የማይጥመን ይኖራሉ፣ በምሥራቅ አፍሪቃ ላይ ከተደቀነው አደጋ አኳያ ግን እነሱ ይሻሉናል በማለት ነው። የመን፣ ሊቢያ፣ ሶሪያ፣ ሱማሊያ፣ ሩዋንዳ የወደሙት በዲሞክራቶች የበላይነት ዘመን ነው። አሁንም ሱዳን እና ኢትዮጵያ በጦርነት ውስጥ የተዘፈቁት በዲሞክራቶች አስተዳደር ነው። አፍሪካ ውስጥ ከሚደርስ የጦርነት ውድመት ጋር የተለየ ቁርኝት አላቸው። በዚህስ አገር ቢሆን ኢትዮጵያውያን ካሉን የቤተሰብና የሃይማኖት እሴቶች ጋር ዲሞክራቶች ምን ያህል ተመሳሳይ ናቸው? በፖለቲካ የዋህነት ወይም በተጠቃሚነት ተገዝተው ተደራጅተው ዲሞክራቶችን ለማስመረጥ የሚንቀሳቀሱ ወገኖቻችን አሉ። ባለፉት አርባ አመታት ዲሞክራቶች በሀገራችን ላይ ያስከተሉትን እና እያስከተሉ ያሉትን አደጋ አጢነው በዚህ ታሪካዊ ወቅት ከተሳስተ አቋማቸው እንዲቀየሩ ጥሪ አቀርባለሁ። ባላፈው ምርጫ ትራምፕን በንግግሩና በብልግናው በመጥላት ከሥልጣን ለማውረድ ብዙዎች ተሯሩጠን፣ ጉዳዩ ተሳክቶ ለሥልጣን የበቁት ዲሞክራቶች ወራት ሳይሆናቸው ክፋታቸውን ተረድተን እነሱን ለመቃወም እንደገና ስንደራጅና ስንባዝን ከርመናል። ያንን መድገም የለብንም። ንግግርን ሳይሆን ተግባርን እንመልከት። የአቢይ አህመድ ሸፍጥ፣ ሽወዳና ክህደት በቂ አላስተማረንም? ስለ አንደበትና ስለተግባር?
“አንመርጥም፣ ሁሉም ያው ናቸው” ብለን እቤት አንቀመጥ። በእንግሊዝኛ “The lesser of two evils” እንደሚባለው አንዳንድ ጊዜ ከሁለት ክፉ በጣም ያልከፋውን ክፉ መምረጥ፣ መጋፈጥ ያለብን የሕይወት ግዴታ ይሆናል።
መልካም ምርጫ
የትኛው ፓርቲ ነው ለጥቁር ህዝቦች ደህንነትና ሰላም የሚያስበው? በአሜሪካ ያለፈ ታሪክ ውስጥ አሁን በምርጫው ሳቢያ እንዳለው አይነት ውጥረት ተፈጥሮ አያውቅም። ተሳዳቢና ዘላፊ፤ ጉረኛና ከእኔ በላይ ህግ የለም የሚልና ግራ ዘመም ህሳቤ የምታራምድ ምንም ዓይነት የሥራ ልምድ የሌላት ሴት ለእጩነት ቀርበዋል። ከ 300 ሚሊዪን ህዝብ ውስጥ እነዚህ ለውድድር መቅረባቸው በራሱ ታሪካዊነት አለው። ከታሪክም አልፎ የሁለቱን ፓርቲዎች የሻገተ አቋምና ለሃገር ሳይሆን ለፓርቲ ታማኝነትን ያሳያል። ለገባው አሜሪካ ውስጥ ዲሞክራሲ የለም። ዲሞክራሲ መሰል ጥሩንባ ነፊዎች እንጂ! ቀኑን ሙሉ በተገኘው ሚዲያ ሁሉ ሲሸራገድ መዋል የስልጣኔ ምልክት አይደለም። ድንቁርና እንጂ! ግራም ነፈሰ ቀኝ እሷም ተመረጠች እሱ ሃገሪቱ ሰላም አይኖራትም። በጥባጭ እያለ ማን ንጽህ ውሃ ይጠጣልና! ገና የምርጫው ውጤት ሳይታወቅ ለረብሻና ለብጥብጥ የታጠቁ ሰዎች አሉ። አይ መሰልጠን። ድንቄም ትሰልጥን!
ታሪክን ወደኋላ መለስ ብሎ ለተመለከተ የጀርመኑ ሂትለር በምርጫ ወደ ስልጣን እንደመጣ መረዳት ይችላል። ዓለማችን አሁን ላይ መቆም ተስኗት በመንገዳገድ ላይ ትገኛለች። ትላንት ከዚህ ግቡ የማይባሉ ሃገሮች ዛሬ ሮኬት አስወንጫፊና ኑና ግጠሙን የሚሉ ሆነዋል። የዚህ ሁሉ የመከራ ዝናብ ምንጩን ስንመለከት ሁለት ናቸው። የመጀመሪያው ሃይማኖት ነው። ሌላው የእቃ እቃ ክፍፍል የእኔ ሽልጦ ከአንተ አነሰ አይነት ነው። ባጭሩ የሃብት ምዝበራና ክፍፍል የሚያስከትለው ግጭት! ከዚህ ውጭ ለነጻነት ለህዝቦች እኩልነት ገለ መሌ የሚባለው ቱልቱላ ሁሉ ማላበሻ ሃሳብ እንጂ እውነትነት የለውም። የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ፓሊሲም ለራሱ ሲቆርስ የማያሳንስ ለመሆኑ በአሜሪካና በወያኔ መካከል የነበረውንና ያለውን ወዳጅነት ልብ ማለት ተገቢ ይመስለኛል። ወያኔ ጦርነት የከፈተው በአሜሪካ አይዞህ ባይነት እንደነበረ የወያኔ አመራሮች የተናገሩት እውነት ነው። ጦርነቱ የሰው ቁጥር ቅነሳ እንጂ ለትግራይ ህዝብ ሰላም የሚያመጣ እንዳልሆነ ነጭ አምላኪዎችና ተመላኪዎቹ ነጮችም ልባቸው ያውቃል። ስንቱ ሞተ፤ ስንቶች አካለ ጎደሎ ሆነ። ግን ማን ገዶት ለጥቁር ህዝብ።
ባጭሩ የአሜሪካ የምርጫ ሂደትም ፊዝ እንጂ ሌላ ፍሬ የለውም። ዲሞክራቶችም ሆኑ ሪፕብሊካኖች ስልጣን መያዝ የሚለውጠው አንድም ነገር አይኖርም። በወረፋ ይህንም ያንም አተራምሰው ከአራት አመት በህዋላ ደግሞ ጡሩንባው እንደገና ይነፋና የአየር ሞገድ ሁሉ በውስልትና ይሞላል። እስከዚያው ግን ስለ አለፈው ምርጫ ጉዳይ ሲያመነዥኩ ይከርማሉ። ውሃ ወቀጣ ይሉሃል ይሄ ነው። ስለሆነም ለአፍሪቃ የሚጠቅም አሜሪካዊ መንግስት ድሮም አሁንም ወደፊትም አይኖርም። የጥቁር ህዝቦች ሰቆቃ በሁለት ጉዳዪች የተፈተለ ነውና። የመጀመሪያው እኛው ራሳችን የምናዘንበው የመከራ ዶፍ ነው። የተላላኪ መንጋ በዚህም በዚያም እያሳበበ ዝንተ ዓለም ህዝብ እያሰቃየ ይኖራል። ሁለተኛ ነጩ አለም በአንድ በኩል ቆዳውን ለጸሃይ እያስመታ መልካም መስሎ በመቅረብ ተንኮልን እየጋቱና እያስጋቱ በዚህም በዚያም በእርዳታና በአስታራቂነት ስም እየገቡ ጸባችን እንዳይቆም ከአረቦች ጋር በመመሳጠር ሲያፋጅን ኑረዋል። አሁንም እየሆነ ያለው የኽው ነው። አሁንም እየተፋጀን ነው። ማብቂያ የሌለው የመከራ ዶፍ!
ስለሆነም ሰው በመሰለው መንገድ ተሰልፎ መምረጡ መልካም ነው። ግን ድምጻችን የሰጠነው ሰው አጥፊ ሆኖ ሲገኝ ግን ራስን በሃላፊነት አብሮ ማሰለፍም እውቀት ነው። ይህን ታሳቢ አድርጎ መረጣ ማድረጉ ማለፊያ ነው። አንድ ነገር ግን ግልጽ ይሁን። There is no such thing as a lesser of two evils. There is only evil. The one we perceived to be a lesser evil can be more harmful than we thought. Taking a chance on a lesser evil is not a mathematical outcome. It is a guesswork at best. መልካም ምርጫ!
This article was written before the result of the election is known. However, the web site was not taking any comments.