ጠ/ሚ አብይ አንድ ነገር ተናጋሩ፡፡ አዳጣቸው ልበል? ነገሩ፣ ምን ያህል የጦርነት አቅማቸው ከፍተኛ እንደሆነ በትጥቅ ትግል ላይ ያሉ ተቃዋሚዎቻቸውን ለማሸማቀቅ የተናገሩት ነው፡፡ የሃገሪቱን ፕሮጀክቶች በጀት አጥፈው በአስር ቢሊዮን የሚቆጠር ዶላር ለጦርነት ማዋል እንደሚችሉ ተናገሩ፡፡
አክለውም፣ ፋኖ ሆነ ሌላው ይህን ያክል ገንዘብ ከየት ያመጣል ሲሉ ጠየቁ፡፡ ገና ስልጣን ስንይዝ እንከፍለዋለን ቢሉ እንኴን ማን ይሄን ያህል ገንዘብ ይሰጣቸዋል ብለው እራሳቸው መልሱን መለሱልን፡፡ ይገርማል ይህን ከተናገሩ ገና ሳምንታቶች ነው ያለፉት፡፡ እዚህ ጋር ጉድ በል!
ሰውየው የሚያውቁት እኛ የማናውቀው ምስጢር አለ እንዴ? ከአስር ቢሊዮን ዶላር በታች ቃል ተገብቶላቸው ወይም ስልጣን ስንይዝ ገንዘቡን እንሰጣለን ተብለው ስልጣን ላይ ማውጣት የሚችሉ ኃይሎች አሉ እንዴ? እሳቸው ቢያውቁ ነው እንጂ እንደዛ ያሉት፡፡ እርሶስ በስንት ነበር የተደራደሩት? ይህ ሁሉ ከሃገር የሚወጣው ወርቅ መዳረሻው የት ይሆን? ማለትም ከአባዱላ ጀምሮ እስከ የእርሶ ሳተናው ጀነራሎቾ ድረስ ማለት ነው፡፡ ሂሳብ የሚያወራርድ ውጭ ያለ አካል አለ ማለት ነው፡፡ ምነው ነገሩን በደም የተለወሰ እንቁ አደረጉት( Blood Diamond)፡፡
እንግዲህ በሰለጠነው አለም ዲሞክራሲ ውስጥ ሎቢስት (Lobbyist or Interested Group) የሚባል ስብስብ አለ፡፡ ብዙ ግዜ ፖለቲከኞች የሃገራቸውን ጥቅም ለማስከበር እነዚህን ሰዎች ይቀጥሩና በሰሜን አሜሪካም ይሁን በአውሮፓ ፖለቲከኞች ላይ ተጽኖ በመሳረፍ ይረዷቸዋል፡፡ ጠ/ሚ አብይ ስልጣኑን እንደተረከቡ ሰሞን ለሎቢስት አስር ሚሊዮን ብር ከምከፍል ለሃገሬ ህዝብ ስንት ነገር እሰራበታለሁ እንዳሉ ትዝ ይለናል፡፡ ግና ምን ያደርጋል በዚሁ አፋቸው ምንጩን ለመጠየቅ ምን ያገባችኋል ባሉት አስር ቢሊዮን ዶላር ህዝብ በረሃብና ሰላም በማጣት በሚያልቅበት በአሁኑ ግዜ ቤተ መንግስታቸውን እየገነቡ ይገኛሉ እንጂ፡፡
የአፍሪካ መሪዎች ስልጣን ላይ ከመውጣታቸው በፊት በሎቢስት አማካኝነት የኃያላን ሀገር መሪዎችን አግኝተው እጅህ ከምን ተብለው ሳይጠየቁ እጄ ከዚህ ይላሉ፡፡ ለምሳሌ የሻቢያው መሪ አቶ ኢሳያስ አፈወርቂና የወያኔው መሪ አቶ መለስ ዜናዊ በኤርትራና ኢትዮጵያ ስልጣን ከመያዛቸው ከአመት በፊት በነጩ ቤተ መንግስት ከነ ጆርጅ ቡሽ ጋር ምሳ በልተው ነበር፡፡ ጠ/ሚ አብይ አህመድም ስልጣን ላይ ከመውጣታቸው በፊት ከኮንግረስ አባላት ጋር ይጸልዩ እንደነበር ሰምተናል፡፡
ከጸሎት በኋላ ደግሞ ስልጣን ብትይዝ ምን ታደርጋለህ? ጥቅማችንን እንዴት ታሰከብራለህ የሚል ጥያቄ ይከተላል፡፡ ከዚያ ከስለላ መዋቅሩ ጋር አብሮ መስራት ይጀመራል፡፡ እንግዲህ ብልጦቹ የአፍሪካ መሪዎች ኃይሌን እንዳጠናክርና ጥቅማችሁን እንዳሰከብር ከገንዘብ ቋታችሁ ክፈቱልኝ፣ የመሳሪያ እርዳታም አድረጉልኝ ይላሉ፡፡ ሁሉም ፐሮቶኮሉን ተከትሎ ይፈጸማል፡፡ ስልጣን ላይ ከተወጣ በኋላ ደግሞ የሳንቲም እንጥፍጣፊው እንኴን ሳይቀር ይከፈላል፣ ሂሳብ ይወራረዳል፡፡ ጠ/ሚ አብይ አዳልጧቸው የነገሩን ይሄን ነው፡፡ እንግዲህ የአፍሪካ መሪዎች በኢንተረስትድ ግሩፕ ስም የሚነቀሳቀሱ የማይታወቁ አካላት ፐሮጀክቶች ናቸው ማለት ነው፡፡ ፕሮጀክት ደግሞ ማብቂያ ግዜ (Termination Time) አለው፡፡
አፍሪካ ውስጥ በአንጎላ፣ኮንጎ ስራሊዮን…ያሉና የነበሩ ጦርነቶችን ስናነሳ የጦር መሳሪ ነጋዴዎቹና የፖለቲካ ደላሎቹ አፍጥጠው ይመጣሉ፡፡ መችና የቱን ሴራሊዮን ላይ ያደረገው ብለድ ዳይሞንድ የሚለው ፊልም ይህንን ነው የሚያትተው፡፡ አውሮጳውያኑ በኮሎናሊዝም ግዜ በኮሎኒያል ጸ/ቤት በኩል አፍሪካ ውስጥ ህዝብን ይከፋፍሉና አጋድለው ይገዙ ነበር፡፡ አውሮፓውያን ቀኝ ገዢዎች በካሄዱት ከፋፍለህ ግዛ መርሆ እርስ በራሳችን ባተረፍነው ጥላቻ እስካሁን አፍሪካውያን እየተጋደልን ነው፡፡
በየብሔሩ ውስጥ የተደበቀው ስሩን ቀኝ ገዢዎች ውስጥ ያደረገው ዛር ይኸው እስከአሁን ያስጓራናል፣ ግብሩም ደም ነው፡፡ አውሮፓውያኑ እኛን ከፋፍለው መያዝ ከጀመሩ ቆይተዋል፡፡ አፄ ቴውድሮስን እንግሊዞች በጦርነት ከስልጣን ከማስወገዳቸው በፊት ፈረንሳዮች የትግሬውን ንጉስ በዝብዝ ካሳን፣ እንግሊዞች ደግሞ የሸዋውን ንጉስ ሚኒሊክን ያባብሉ ነበር፡፡
አፄ ቴውድሮስ ከእንግሊዝ ጋር ጥልቅ ወዳጅነት ይፈልጉ ነበር፡፡ ይህን የሚያበስር ደብዳቤ ይጠብቁ የነበሩት ቴውድሮስ ግን ከታላቋ ብሪታኒያ ዘንድ አንድ ኮረንስ በተባለ ሰው እጅ ስጦታ ይደርሳቸዋል፡፡ ነገሩ የኢራን ምንጣፍ ነበር፡፡ እላዩ ላይ አንድን አንበሳ የአውሮፓውያን ድጋፍ ያለው አንድ አረብ ሲገድል ያሳያል፡፡ ከዚያም ቴውድሮስ አንበሳው እኔ ነኝ፡፡ ከአረቡ በላይ የሰፈረው ወታደር ፈረንሰዮች ናቸው ብለው በመደምደም እንግሊዝ አንበሳውን ለመረዳት የተ አለች ሲሉ ጠየቁ፡፡ ከዚያም ሴራ አለ በማለት ፈረንጆቹን ሁሉ አሰሯቸው፡፡ ይሄንን ተከትሎ በመጣው ጦርነት እሳቸውም ተሰዉ፡፡
ልጅ እያሱ በአንደኛው የአለም ጦረነት ወቅት በተከተለው ቱርክና ጀርመንን የመደገፍ አዝማሚያ ውድቀቱን ለማፋጠን የቀኝ ግዛት ሚኒሰተሩ ሰራተኛ ሸዋ ድረስ መጥቶ ነበር፡፡ ይህን ያክል ያልኩት ኢትዮጵያ በቀጥታ የቅኝ ግዛት ተጠቂ መሆኗን ለማሳየት ነው፡፡ ዛሬም ቢሆን ያው የነበረው ጣልቃ ገብነት መንግስታት ገለል ብለው በኢንተረስትድ ግሩፕ ስም እንደቀጠለ ነው፡፡ መንግስታትም ግን በቀጥታ ስረአት መቀየር (Regime change) ላይ የሚሳተፉበት ግዜ አለ፡፡
አሁን ደግሞ የልዕለ ኃያላኑ ሃገራት ጥቅም በየቦታው ነው ያለው፡፡ ለምሳሌ የአሜሪካንን ጥቅም ምስራቅ አፍሪካ ላይ ከነካህ ለተቃዋሚዎችህ የድል ችቦ አቀበልክ ማለት ነው፡፡ በሶቬይት ህብረት እርዳታ በሰሜን ኢትዮጵያ ለአስርት አመታት ያህል ጦርነት ሲያካሂድ የነበረው ደርግ የሶይቨት ህብረትን መፈራረስ ተከትሎ እርዳታ እየቆመበት ሲመጣ አሜሪካኖቹ ሻብያንና ወያኔን በመደገፍ ለስልጣን አበቋቸው፡፡
ያም ሁሉ ሆኖ ግን ሃገሪቱ ከጦርነት አዙሪት መውጣት አልቻለችም፡፡ ሻቢያና ወያኔ (ኢህአዲግ) ከሃያ አመት በፊት ለአስከፊ ጦርነት ተዳረጉ፡፡ ያንን ተከትሎ 1993 ዓ.ም. ላይ የኢህአዲግ ክፍፍልና መፈንቅለ መንግስት ተካሄደ፡፡ የዚያን ሰሞን አንድ የቴላቪቨ ዩንቨርስቲ ሙሁር የሆኑ ኤርሊች ሃጋይ የተባሉ ፕሮፌሰር ለነ ስዬ አብርሃ ቡድን ማስጠንቀቂያ የሚመስል ቃለ መጠይቅ ጋዜጣ ላይ ሰጡ፡፡ ነገሩ በቀጥታ ወያኔ(ኢህአዲግ)ን የሚመለከት ሳይሆን ኃይለ ስላሴን የሚመለከት ነበር፡፡
ፕሮፌሰር ኤርሊቸ “የአፄ ኃይለስላሴ መነሳትና መውደቅ” በሚል ርእስ ያሳተሙትን መጽሐፍ ነበር በግዜው በቀጥታ ያንፀባረቁት፡፡ በቃለ መጠይቁ ላይ የገለጹት በመጽሐፋቸውም ላይ የሰፈረው ሃሳብ እንዲህ ይላል፡፡ አፄ ኃይለስላሴ ከስልጣን የተገለበጡት እስራኤላውይንን ከኢትዮጵያ ባባረሩ አመት ባለሞላ ግዜ ውስጥ ነው፡፡
እ.ኤ.አ. 1973 ዓ.ም. ግንቦት ወር ላይ አዲስ አበባ ውስጥ የአፍሪካ አንድነት ድርጅትን አስረኛ አመት ለመዘከር ስብሰባ ተካሂዶ ነበር፡፡ ነገሩ በሶማሊያና ኢትዮጵያ ሁኔታ ላይ ምክክር ላመድረግ አጀንዳ የያዘም ነበር፡፡ ነገር ግን በስብሰባ ላይ የተገኙት የሊቢያው መሪ ሞሃመድ ጋዳፊ ሁኔታዎችን ቀያየሩ፡፡ ቀደም ባሉት አመታተ በእስራኤልና አረቦች መካከል የተደረገው የስድስቱ ቀን ጦርነት በእስራኤል አሸናፊነት መጠናቀቁ ይታወቃል፡፡
በንጉሱ ግዜ የነበረችው ኢትዮጵያ ከእስራኤል ጋር ጥሩ ግንኙነት የነበራትና ብዙ እሰራኤላውያን በወታደራዊ ጉዳዮች ላይ በአማካሪነት እንዲሁም በተለያዩ የስራ መስኮች ላይ ተሰማርተው ይገኙ ነበር፡፡ ሰላዮች የነበሩም ነበሩ፡፡
የግብጹ መሪ ሳዳት አስራኤል ከያዘቻቸው የሲና መሬት መውጣት አለባት የሚለው ሃሳብ በአፍሪካ አንድነት ድርጅት ደረጃ እንዲሰተጋባላቸው ይፈልጉ ነበር፡፡ ይህም በእስራኤልና ግብጽ መሃል ለሚደረገው የሰላም ስምምነት ቅድመ ሁኔታ ሆኖ ይቀመጥ ከሚል ሃሳበ የመነጨ ነው፡፡፡፡ ኃይለ ስላሴ እነደ አፍሪካ ህብረት መስራችና አባት ይህን እንዲያረጋግጡ ይጠበቅ ነበር፡፡
ጋዳፊ በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን በቀጥታ ከአፍሪካ ህብረት አዳራሽ በተላለፈ ንግግሩ ኢትዮጵያና ንጉሱን ዘረኞች የሆኑትን የደቡብ አፍሪካ አፓርታይድና የሮዶሺያን መንግሰታት በመደገፍ የቀኝ ገዢዎች ተባበሪ በማድረግና ለአሜሪካና እስራኤል ማረፊ በመሆን ከሰሳቸው፡፡ አዲስ አበባም በእስራኤልና አሜሪካ ሰላዮች የተሞላች ከተማ መሆኗን ገለጸ፡፡ ጋዳፊ የአፍሪካ አንድነትን ድርጅት ከኃይለ ስላሴ የመንጠቅ አለማ አንጸባረቀ፣ አልተሳከለትም እንጂ፡፡ ይህን ስብሰባ ተከትሎ እስራኤል በሁሉም ተሰብሳቢ ሃገራት ተወገዘች፡፡
አፄ ኃይለ ስላሴ በስብሰባው ላይ በኢትዮጵያና እስራኤል መካከል ያለው ግንኙነት ጥንታዊ መሆኑን ገልጸው በግብጽና እስራኤል መካከል ለሚኖረው የሰላም ስምምነት መሰረቱ እስራኤል ሳይናን ለቃ መውጣት ነው ሲሉ ተናገሩ፡፡ በዛው አመት መስከረም ላይ የግብጹ መሪ ሳዳት፣ የሳውዲው ንጉስ ፈይሰል እና አፄ ኃይለ ስላሴ አልጄሪያ ውስጥ ተገናኙ፡፡
በስበስባቸው ላይ ንጉስ ፈይሰል ኢትዮጵያ ከእስራኤል ጋር ያላትን ግንኙነት ካቋረጠች ግማሹ ለወታደራዊ አቅም ግንባታ የሚውል፣ ግማሹ ደግም ለሃገር ግንባታ የሚውል 200 ሚሊዮን ዶላር ለንጉሱ እንደሚሰጥ ቃል ገባላቸው፡፡
በሚቀጥለው ጥቅምት ወር ላይ በአረብና እስራኤል መካከል ጦርነት ፈነዳ፡፡ ሃያ የአፍሪካ ሃገራት ከእስራኤል ጋር የነበራቸውን ግንኙነት አቋረጡ፡፡ አፄ ኃይለ ስላሴም ባለስልጣናቶቻቸውን ይዘው መከሩ፡፡ እነ ጀነራል አስፋው አያናና ከተማ ይፍሩን የመሳሰሉ ሰዎች ከእስራኤል ጋር ያለው ግንኙነት ይቅጥል ሲሉ ምክረ ሃሳብ አቀረቡ፡፡
ጠ/ሚ እንዳለካቸው ግን ኢትዮጵያ ከሌሎቹ አፍሪካ ሃገራት የምትለይበት ምክነያት የለም ብለው ከእስራኤል ጋር የነበረው ግንኙነት እንዲቋረጥ ተከራከሩ፡፡ ውጤቱም ለእስራኤሉ አምባሳደር በአንድ ሳምንት ውስጥ እስራኤል ዜጎቿን ከኢትዮጵያ እንድታስወጣ ተነገረው፡፡ የእስራኤልና ኢትዮጵያ ግንኙነት በዚህ ሁኔታ ተቋረጠ፡፡
ጀነራል አስፋው አያና ግን የእስራኤል አማካሪዎች ከኢትዮጵያ ከወጡ ወታደሩ ውስጥ አለመረጋጋት እንደሚፈጠር አስጠንቅቀው ነበር፡፡ የእሳቸው ትንቢት አልቀረም ደርግ ንጉሱን ከእንደ አመት ከትንሽ ወራት ባነሰ ግዜ ውስጥ ከስልጣን አስወገዳቸው፡፡
አፄ ኃይለ ስላሴ እ.ኤ.አ. ጥር ወር 1974ዓ.ም. ላይ ሪያድ ሄደው ነበር፡፡ ንጉስ ፈይሰልን የት አለ 200 ሚሊዮን ዶላሩ ቢሉት፣ ስለ ሁለት መቶ ሚሊዮን ዶላር መናገሩ ትዝ እንደማይለውና 35 ሚሊዮን ዶላር ግማሹ በአዲስ አበባ ለእስልምና ተቋማት ምስረታ የሚሆን ገንዘብ ሊሰጣቸው እንደሚችል ብቻ ነገራቸው፡፡
ኤርሊች ሃጋይ !993 ዓ.ም. ላይ ቃለመጠይቅ ባደረገበት ግዜ ብዙ ሰዎች ተቃውመውት እንደ ሪፖርተር በመሳሰሉ ጋዜጦች ላይ ጽሑፍ አቅርበውበታል፡፡ በግዜው ይህን ቀለ መጠይቅ ያደረገው እሱ በትግሬ ታሪክ ላይ መጽሐፍቶች ይጽፍ ስለነበር፣ አዲስ ለሚነሱት ለነ ስዬ ቡድን ማስጠንቀቂያ ነበር የሚሉም አሉ፡፡ እነ ስዬ አብርሃ አንደ አክራሪ (hardliner) ይታዩ ስለነበር የአለምአቀፉ ተቋማት ለዘብተኞቹን እነ መለስን መምረጣቸው ያሳያል ሲሉም የተነተኑ አሉ፡፡
በቅርቡ እ.ኤ.አ. ሚያዚያ 7፣ 2024 ዓ.ም. የርዋንዳ ቱሲዎችን ጭፍጨፋ ሰላሳኛ አመት ለመዘከር የኢትዮጵያው ጠ/ሚ አብይ አህመድ ኪጋሊ ሄደው ነበር፡፡ እንዲሁም በእርሳቸው የፕሬዝደንትነት ዘመን የሩዋንዳውን ዘር ማጥፋት ወንጀል ለማስቆም ምንም አላደረጉም ተብለው የሚወቀሱት የቀድሞው አሜሪካ ፕሬዚደንት ቢል ከሊንተንም እዛው ተገኘተዋል፡፡
የሚገርመው ነገር ሰው(አማራ) ተገደለ ሲሏቸው፣ ለአስከሬኑ ጥላ ይሆን ዘንድ ዛፍ እየተከልኩ ነው የሚሉት፣ አንድ ሺህ ሰው በዘሩ ምክነያት ወለጋ ላይ አለቀ ሲሏቸው፣ አሜሪካ ውስጥ ስንት ሰው በአመት እንደሚሞት ታውቃላችሁ ሲሉ የሚሞግቱት፣ ምን ይሄን ብቻ እኔን ከነካችሁ በመቶ ሺህ የሚቆጠር ሰው ያልቃል ሲሉ በዘር ጭፍጨፋ ሟርት የሚያስፈራሩት ጠ/ሚ አብይ ከከሊንተን ጋር ተገናኝተው ምክክር ቢጤ አደረጉ አሉ፡፡
ምን እንደተነጋገሩ አንድዬ ብቻ ነው የሚያውቀው፡፡ እንደው ለመገመት ያህል ቢል ክሊንተን ነጩ ቤተ መንግስትን ለቀው ከወጡ በኋላ ምን እያደረጉ ነው ብለን እንጠይቅ፡፡ መጽሐፍ ጽፈው ለሽልማት በቅተዋል፡፡ ክሊንተን ፋውንዴሽን የተባለ በቢሊዮን ዶላር የሚንቀሳቀስ በጎ አድራጎት ድረጅትም አቋቁመዋል፡፡
ድርጅታቸው አለምአቀፍ ችግሮችን ለመፍታት፣ በአፍሪካ ሃገሮች ድህነት ላይ፣ በአየር ንብረት ለውጥ ፣በኤች፣አይ. ቪ. ኤድስ ላይ…ይሰራል፡፡ ድርጅቱን ከመካከለኛው ምስራቅ እንደ ሳውዲ አረብያና የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ የገንዘብ ድጋፍ ያገኛል፡፡
ክሊንተን እስከ አሁን ድረስ በደህንነት መስሪያ ቤት የሚጠበቁ የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዚደንት ናቸው፡፡ በፕሬዚደንትነት ዘመናቸው የሚያውቁትን የአሜሪካ ምስጢር ለሌላ ወገን አሳልፈው መስጠት ወይም ማጋራት አንዳይችሉ በህግ የተከለከሉ ሰው ናቸው፡፡ ሆኖም ግን የሎቢስትነትን ስራ ሆነ የማመከር አገልግሎት በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መስራት ይችላሉ፡፡ አሁን አሜሪካ ላይ በስልጣን የሚገኘው ፓርቲ የእሳቸው ዲሞክራቲክ ፓርቲ መሆኑንም አንዘንጋ፡፡
የእኛው አብይ ግን አንዴ ለግንቦት ሰባት፣ ሌላ ግዜ ደግሞ ለኦነግ እሰልል ነበር ብለው ሲናገሩ የማያፍሩ ናቸው፡፡ እሳቸው ኢንተረቪው አድረጎ የኒወርከሩ ጋዜጠኛ ጆን ሊ አንድርሶን እ.ኤ.አ. መስከረም 26፣ 2022 ዓ.ም. በጻፈው ጽሑፍ፣ ጠ/ሚ አብይ በኢራቅ ጦርነት ግዜ ከአሜሪካኖቹ ጋር አብረው እንደተዋጉ፣ ለአሜሪካ ብሔራዊ ደህንነት ድርጅት ሶማሊያ፣ሱዳንና የመንን በተመለከት መረጃ ያቀብሉ እንደነበርና ቢሮውም ስራቸውና እሳቸውን አንደሚያውቅ፣ ለአሜሪካም እንደሚሞቱ እንደነገሩት ጽፏል፡፡ ይህ ጽሑፍ እንግዲህ የዛሬ አንድ አመት ከሰባት ወር ገደማ የወጣ ነው፡፡
እግዲህ ጠቅላዩ ለክሊንተን የናንተ ሰላይ የነበርኩ ስለሆነ ኪሰሴን ይሙሉሉኝ ጥያቄ እንዳቀረቡላቸው መገመት አይከብድም፡፡ ለዚህ ደግሞ የሰለላ ኮድ ስማቸው “ሬድ ጃካል” እንደነበረም ሳይነግሯቸው አይቀርም፡፡ ቢል ክሊንተን እነሱ ናቸው ያወጡልህ ወይንስ አንተ መረጥከው ብለው ከጠየቁ፣ እብይ በምርጫዬ ያገኘሁት ስም ነው ይላሉ፡፡
ለምን ከተባሉ ደግሞ፣ በረጅሙ ይተነፍሱና ታሪኩ ብዙ ነው ብለው ሃተታቸውን ይጀምራሉ፡፡ አዩ ቀዩ ጃካል (ቀበሮ) ብልጥ ነው፡፡ ብዙ ግዜ አናብስቱን ይከተላል፣ ለምን ቢባል አናብስቱ ግጣይ ሲጥሉ ትርፍራፊያቸውን ለመበላት ማለት ነው፡፡… ወገን ይገርማል እኮ! ድሮስ ቢሆን በአደባባይ ሳያፍሩ “ልመና ስጦታዬ ነው” ካሉ ጠ/ሚ ከዚህ የተሸለ ንግግር መቼ ይጠበቃልና፡፡ አብይም ሰጦታዬ ነው ያሉትን ታለንታቸውን ነው የሚጠቀሙበት፡፡
ቢል ክሊንተን ትንሽ ፊት ከሰጧቸው ደግሞ እስኪ አረብ-ፍልስጤም ግጭት ውስጥ ለመፍተሄነት የኢትዮጵያን የመካከለኛ ዘመን ትርክት እኔን ጨምረው ያስገቡኝ ከማለት ወደ ኋላ አይሉም፡፡ ከዚያማ ምኑ ቅጡ…”መልአክት ሊረግጡ የሚፈሩትን ስፍራ ጅሎች ይጠቀጥቁታል” አይደል የሚለው ተረቱ፡፡ የዚህ አባባል ምስጢር መፍቻው ቁልፍ፣ በቅርብ ግዜ የምናየው ” አሳ ጎርጓሪ ዘንዶ ያወጣል” የሚለው ተረትና ምሳሌ ነው፡፡
በደራሲ ሰርቀ ዳንኤል “ቆንጆዎቹ” በሚል ርእስ ተዛማች ትርጉም የተሰራለት በጋናው ደራሲ አዪ ከዌ አርማህ የተደረሰው “ዘ ቢዩቲፉል ዋንስ አርኖት የት ቦርን” (The Beautiful Ones are not Yet Born) የሚለው ልብወለድ የነቁ ሙስናን የሚጠየፉ አፍሪካውያን ፖለቲከኞችን ይናፍቃል፡፡
ብልጽግና ፓርቲ ደግሞ ፍኖቴ ቢጫ በአፍሪካ ደረጃ የነቀሁ ውብና ቆንጆ እኔ ነኝ ይላል፡፡ የአማርኛ መዝገበ ቃላት ትርጉም እንደሚያሳየዉ “ወሸኔ” ማለት ውብ፣ ቆንጆ ማለት ነው፡፡ ታዲያ ቆነጆዎቹን እመራለሁ የሚሉት ጠ/ሚ አብይ በተዘረዘረው ታሪካቸው እንዳየናቸው፣ እንደሚሉት ወሸኔ አይደሉም፡፡ ታዲያ ምንድን ናቸው? ፊደል “ወ”ን እንግደፋታ!
አስቻለው ከበደ አበበ
ሜትሮ ቫንኩቨር፣ ካናዳ