ኤፍሬም ማዴቦ (emadebo@gmail.com )
አገራችን ኢትዮጵያ የተለያዩ መሪዎች በተለያየ ዘመን በሞከሩት የአገረ-መንግስት ግንባታ (Nation Building) ሂደት ውስጥ አልፋለች። አፄ ቴዎድሮስ ኢትዮጵያን ከግማሽ ምዕተ አመት በላይ ያለ ማዕከላዊ መንግስት ያስቀረውንና “ዘመነ መሳፍንት” በመባል የሚታወቀው አንድ የታሪካችን ምዕራፍ እንዲቆም አድርገው ኢትዮጵያን እንደገና በማዕከላዊ መንግስት የምትመራ አገር አድርገዋል። ቀኃስ በአገራችን ታሪክ የመጀመሪያውን ህገ መንግስት በመጻፍ፣የባህር ኃይልና የአየር ኃይል በማቋቋምና ኢትዮጵያን ፓርላማ ከሚባል ተቋም ጋር በማስተዋወቅ በዘመናዊው የኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ የራሳቸውን ሚና ተጫውተዋል። ኮ/ል መንግስቱ ኃ/ማሪያም ከቀዳማዊ ኃ/ሥላሴ የተረከበውን ኢትዮጵያን ሶሻሊስት አገር ለማድረግ 17 አመት ታግሏል። ከኮ/ል መንግስቱ በኋላ ኢትዮጵያን የመራው መለስ ዜናዊ መሰረቱን ብሔር ያደረገ የፖለቲካ ሥርዓትና የዛሬዋን ፌዴራል ዲሞክራሲያዊት ኢትዮጵያን ገንብቷል። እነዚህ ሁሉ የአገረ-መንግስት ግንባታ ጥረቶች እንዳሉ ሆኖ፣ ቀኃስ፣ ኮ/ል መንግስቱና መለስ ዜናዊ በተከታታይ ለ81 አመታት የመሯትንና ዛሬ ማዕበል እንደሚያንገላታው መርከብ በመንገዳገድ ላይ ያለችውን ትልቅ ኢትዮጵያ ፈጥረው የሰጡን ዳግማዊ ምኒልክ ናቸው።
ኢትዮጵያን በድምሩ ለ117 አመት የመሩት ከላይ ስማቸው የተጠቀሰው 5 መሪዎች፣ በኖሩበት ዘመን፣በነበራቸው የመንግስት ቅርፅ፣ኢትዮጵያን ጠንካራና የበለጸገች አገር ለማድረግ በተከተሏቸው ፖሊሲዎችና በግለሰብ ደረጃ በነበራቸው ባህሪያት በጣም ይለያያሉ። አፄ ቴዎድሮስ፣ሚኒልክና ቀኃስ ንጉሰ ነገስት ነበሩ። ወታደራዊ አምባገነኑ መንግስቱ ኃ/ማ በህዝብ ያልተመረጠ ፕሬዚደንት ነበር። መለስ ዜናዊ የብሔር አምባገነን ነበር። አምስቱም መሪዎች ኢትዮጵያን እንደፈለጉ የማድረግ ያልተገደበ ሥልጣን ነበራቸው፣ደግሞም ከነሱ የተለየ ሃሳብ ያለው የሌላ የማንም ሰው ወይም ቡድን ተሳትፎ ሳያስፈልጋቸው ኢትዮጵያን እነሱ ይበጃል ብለው ባመኑበት መንገድ ቀርጸዋታል።
የዚህ ጽሁፍ አላማ ካሁን በኋላ የምትኖረንን ወይም የወደፊቷን ሁላችንንም እኩል የምታቅፍ ኢትዮጵያን እንዴት በጋራ እንፍጠር፣ በተለይ አገርን እንደ ሙጫ አጣብቀው የሚይዙ ትላልቅ ተቋማትን እንዴት ነው መገንባት ያለብን የሚለውን ሃሳብ ከትላልቆቹ ተቋማት ውስጥ ከሰሞኑ ስሙ በየሜዲያው የሚነሳውን አንዱን እንደምሳሌ ወስዶ ለማሳየት ነው እንጂ፣ ከላይ የተጠቀሱትን 5 መሪዎች በሰሩት ስራ ለማወዳደር ወይም ድክመታቸውንና ጥንካሬያቸውን ለማሳየት አይደለም!
ከላይ በአጭሩ ለመግለጽ እንደተሞከረው የተለያዩ መሪዎች በተለያየ ዘመን ኢትዮጵያን በአዲስ መልክ ለመገንባት ሞክረዋል። ሆኖም በኢትዮጵያ ታሪክ በመጠኑም ቢሆን ህገመንግስታዊ ምህንድስናን (Constitutional Design) በተከተለ መንገድ የመንግስት መዋቅርን፣ የመንግስት ቅርፅንና የምርጫ ሥርዓትን በህገመንግስት ውስጥ አስቀምጦ አዲስ የፖለቲካ ሥርዓት የገነባው በህወሓቶች የሚዘወረውና በመለስ ዜናዊ የሚመራው የኢህአዴግ መንግስት ነው። የመንግስት መዋቅር ሲባል ፌዴራልዚምን፣ የመንግስት ቅርፅ ሲባል የፓርላማ ሥርዓትን፣ የምርጫ ሥርዓት ሲባል ደሞ አብዛኛ ድምፅ የምርጫ ሥርዓትን በህገመንግስት ደረጃ ቀርጾ የዛሬዋን በፓርላማ ሥርዓት የምትመራዋን ኢትዮዮጵያ የገነባው ኢሀዴግ ነው። በእርግጥ በቀኃሥ ዘመን በሰራቸው አንዳንድ አስገራሚ ስራዎቹ ፣በቅርጽና ይዘቱና በተለይ የታችኛው ምክር ቤት አባላት(House of Deputies) በሚመረጡበት መንገድ ባለፉት 32 አመታት ከነበረን ፓርላማ በጣም የሚሻል “ፓርላማ” የሚባል ተቋም ነበር። ሆኖም የቀኃሥ ሥርዓት ፍጹማዊ የንጉስ ሥርዓት እንጂ የፓርላማ ሥርዓት አልነበረም።
ከሰሞኑ የአዳዲስና ብዙ ግዜ ልብ የሚስብሩ አንዳንዴም ቀልብ የሚስቡ ዜናዎች ምንጭ ከሆነችው መዲናችን ከወደ አዲስ አበባ አንድ አዲስ ዜና ተሰምቷል። ይህ ከአዲስ አበባ የተሰማው ዜና የፓርላማ ሥርዓትን በፕሬዚደንታዊ ሥርዓት ለመተካት እየተሰራ ነው የሚል ነው። ለመሆኑ ማነው እየሰራ ያለው? ወይስ ከእነሱ በፊት ኢትዮጵያን በተከታታይ ከመሩ ሁለት ፓርቲዎች (ኢሠፓና ኢህአዴግ) መማር የተሳናቸው ብልፅግናዎች የወደፊቷን ኢትዮጵያ ቅርፅና ይዘት በከፍተኛ ደረጃ የሚወስነውን የመንግስት ቅርፅ ዲዛይን የማድረግ ስራን እራሳቸው ጀምረው እራሳቸው ሊጨርሱት ነው?
ኢትዮጵያ የሚያስፈልጋት ፕሬዚደንታዊ ሥርዓት ነው የሚለው ሃሳብ በራሱ አዲስ ሃሳብ አይደለም።ከ2010 ዓም በፊት የአርበኞች ግንቦት 7 ንቅናቄ፣ ባለፉት አምስት አመታት ደግሞ የኢዜማና የብልፅግና ፓርቲ መሪዎችና ሌሎችም ተፅዕኖ ፈጣሪ ግለሰቦች ኢትዮጵያ የሚያስፈልጋት ፕሬዚደንታዊ የመንግስት ቅርፅ ነው ሲሉ በተደጋጋሚ ተደምጠዋል። ደግሞም ኢትዮጵያ ውስጥ ፕሬዚደንታዊ ሥርዓት ባይኖርም ኮ/ል መንግስቱና መለስ ዜናዊ “ፕሬዚደንት” የሚል ስያሜ ይዘው ኢትዮጵያን መርተዋል።
የዚህ ጽሁፍ አላማ ለምን ፕሬዚደንታዊ ሥርዓት ተፈለገ የሚል ተቃውሞ ማንሳት አይደለም፣የምትሰሩትን ስራ አታውቁም የሚል ወቀሳም አይደለም። ይህንን ጽሁፍ እንድጽፍ የገፋፉኝ የሚከተሉት ሃሳቦች ናቸው – የወደፊቷን ኢትዮጵያ በተመለከተ ብዙ ስራዎችን እንዲሰራ በአዋጅ የተቋቋመ አገራዊ የምክክር ኮሚሺን እያለ፣ በሁለቱ የአገራችን ትልልቅ ክልሎች ውስጥ ጦርነት እየተካሄደ፣ አገሪቷ ውስጥ አፈና፣ ግዲያ፣ቂሚያና ዝርፊያ የየቀኑ ዜና በሆነበት ባሁኑ ወቅት እንዲህ አይነቱ የብዙ ባለድርሻዎች ቀጥተኛ ተሳትፎ የሚያስፈለግውና የብሔር ኃይሎች “አይነኬ” ነው የሚሉትን ህገ መንግስት የሚነካ ጉዳይ እንዲነሳ የተደረገው ለምንድነው?
የፓርላማ ሥርዓት ለኢትዮጵያ የማይመቹ የትኞቹ ባህሪያት ስላሉት ነው በፕሬዚደንታዊ ሥርዓት እንዲተካ የተፈለገው? ፕሬዚደንታዊ ሥርዓትስ በየትኞቹ ጠንካራ ጎኖቹ ተመዝኖ ነው ከፓርላማ ሥርዓት የተሻለ ነው ተቦሎ የተመረጠው? ከሁለቱ የመንግስት ቅርጾች ውጭ ያሉት ሌሎች አማራጮችስ ታይተዋል ወይ? ኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን ማህበራዊ አደረጃጀት፣ የኢትዮጵያን ባህል፣ታሪክ፣የዲሞክራሲ ልምድና የፖለቲካ ባህል በሚገባ አይቶ፣ መርምሮ፣ የተለያዩ የመንግስት ቅርጾችን ከአነዚህ እሴቶች ጋር ጎን ለጎን አስቀምጦ፣ አወዳድሮና መዝኖ ለኢትዮጵያ የሚሻለው ፕሬዚደንታዊ ሥርዓት ነው የሚል ድምዳሜ ላይ የደረሰ ጥናታዊ ስራ አለ?
ለመሆኑ ኢትዮጵያ የሚያስፈልጋት የፓርላማ ሥርዓት ነው ወይስ የፕሬዚደንት ሥርዓት? እነዚህን ሁለት ሥርዓቶች ደባልቀን ድብልቁን ሥርዓት እንደ ሶስተኛ አማራጭ ለምን አልተመለከትንም? ድብልቅ ሥርዓቶች ወይም ግማሽ-ፕሬዚደንታዊ ስርዓት በሚል ስያሜ ከሁለተኛው የአለም ጦርነት በኋላ የተፈጠሩት ሁለት የመንግስት ቅርጾች የፓርላማና የፕሬዚደንት ሥርዓቶችን ደካማ ጎኖች ያስወግዳሉ ተብሎ ነው። ሆኖም የፓርላማና የፕሬዚደንት ሥርዓቶችን ደካማ ጎኖች አስወግዶ ጠንካራ ጎናቸውን ብቻ ይዞልን የሚመጣ የመንግስት ቅርፅ የለም። ከፓርላማ፣ ከፕሬዚደንትና ከግማሽ- ፕሬዘደንታዊ ሥርዓቶች ውስጥ አንዱን መምረጥ ማለት ከሦስት ትልልቅ ሳጥኖች አንዱን እንደ መምረጥ ማለት ነው። አንደኛው ሳጥን ውስጥ ያለውን ሌላኛው ሳጥን ውስጥ ላናገኝ እንችላለን፣ ወይም ከመረጥነው ሳጥን ውስጥ አንፈልገውምና ይቅርብን ብለን አውጥተን የምንወረውረው ነገር የለም። ከሦስቱ ትልልቅ ሳጥኖች አንዱን ስንመረጥ ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት የምንገነባበትን ጡቦች ነው የምንመርጠው። ስለዚህ ጡቦቹን ከላይ ከተጠቀሱት ከአገራችን ተጨባጭ ሁኔታዎች ጋር እያመቻቸን ጠርበን መገንባት ነው ያለብን እንጂ የምንፈልገውን ጡብ እየተጠቀምንበት የማንፈልገውን መጣል አንችልም።
በዚህ ጽሁፍ ውስጥ የ”መንግሥት ቅርፅ” እና የ”መንግሥት መዋቅር” የሚባሉ ጽንሰ ሃሳቦች በተደጋጋሚ ተገልጸዋል፣ እነዚህ ጽንሰ ሃሳቦች ስማቸው እየተጠቀሰ ሲነገር የሚመሳሰሉ ፅንሰ ሃሳቦች ይመስላሉ። ነገር ግን የመንግሥት ቅርፅና የመንግሥት መዋቅር በጣም የሚለያዩ ፅንሰ ሃሳቦች ናቸው። የመንግሥት ቅርፅ ስንል ፓርላማዊ፣ ፕሬዚደንታዊ፣ግማሽ-ፕሬዚደንታዊ የመንግሥት ዓይነቶች ወይም ከንጉሳዊ ሥርዓት ውስጥ አንዱን ማለታችን ነው። የመንግሥት መዋቅር ስንል ግን ፌዴራል ወይም (የኛ አገር የብሔር ዕብዶች “አሃዳዊ” የሚለውን ቃል እንደ መጥፎ ቢያቀርቡትም) አሃዳዊ የመንግሥት መዋቅር ማለታችን ነው(Unitary State)። በአንድ አገር ውስጥ ያለው የመንግሥት መዋቅር አሃዳዊ ሆኖ አብሮት የሚሄደው የመንግሥት ቅርፅ ፓርላማዊ፣ ፕሬዚደንታዊ ወይም ግማሽ-ፕሬዚደንታዊ ሊሆን ይችላል። ለምሳሌ፣ ፈረንሳይ በአንድ በኩል ጠ/ ሚኒስትር -ፕሬዚደንት የሚባለውን ድብልቅ የመንግሥት ቅርፅ የምትከተል አገር ናት፣ በሌላ በኩል ደግሞ ፈረንሳይ ውስጥ ያለው የመንግሥት መዋቅር አሃዳዊ ነው። አሜሪካንን ብንመለከት አሜሪካ ፌዴራል የመንግሥት መዋቅር ያላት አገር ስትሆን አሜሪካ ውስጥ ያለው የመንግሥት ቅርፅ ደግሞ‹‹ፕሬዚደንታዊ›› የመንግሥት ቅርፅ ነው። የፈረንሳይ ጎረቤት የሆነቸውን ጀርመንን ብንመለከት ደግሞ ጀርመን ፌዴራል የመንግስት መዋቅርና ፓርላማዊ የመንግስት ቅርፅ ያሉባት አገር ናት።
የኢትዮጵያን የፖለቲካ ታሪክ አንድ መቶ ሃምሳ ዓመት ወደኋላ ዞር ብለን ስንመለከት የኢትዮጵያን ህዝብ የአጭርና የረጂም ጊዜ ህይወት የሚዳስሱ ትላልቅ ውሳኔዎች የተወሰኑት በአንድ ሰው አንዳንዴም በአንድ ቡድን ብቻ ነው። በህወሓት ዘመን መለስ ዜናዊና ጓደኞቹ፣ በደርግ ዘመን መንግሥቱ ኃ/ማርያምና ኢሠፓ ከዚያ በፊት ደግሞ ነገሥታቱ በኢትዮጵያ ጉዳዮች ላይ ፈላጭ ቆራጮች ነበሩ። የሚቀጥለው ታሪካችን የዚህ ተቃራኒ መሆን አለበት። እንዲህ ሲባል ደሞ የጠሚ አቢይ አህመድ መንግስት ወይም ብልፅግና ፓርቲ የኢትዮጵያን የወደፊት በሚወስኑና አሻሚ በሆኑ ቁልፍ ተቋሞች ግንባታ ሂደት ውስጥ ብቸኛ ተዋናይ አለመሆኑን ማወቅ አለበት ማለት ነው። ለምሳሌ፣ አሁን በስራ ላይ ያለውን የፓርላማ ሥርዓት በፕሬዚደንታዊ ሥርዓት የመተካቱ ዉሳኔ መንግስትን ጨምሮ የሌሎችም የተለያዩ ባለድርሻዎች የጋራ ውሳኔ ነው መሆን ያለበት እንጂ የጠሚ አቢይ አህመድ መንግስት ብቻውን የሚወስነው ውሳኔ መሆን የለበትም።
ኢትዮጵያ ምን አይነት የመንግስት ቅርፅ ያስፈልጋታል የሚለው ጥያቄ መልስ ከገዢው ፓርቲ ወይም ከጥቂት ቡድኖች መምጣት የለበትም። በእርግጥ ጥያቄው መልስ ማግኘት አለበት፣ ግን መልሱ ብቻ በቂ አይደለም። የዚህ በሚገባ ታስቦበትና የተለያዩ ባለድርሻዎችን አካትቶ ካልተሰራ መዘዙ ለሚቀጥለው ትውልድ የሚተላለፍ ጥያቄ መልስ የተገኘበት መንገድም ወይም ይህንን ጥያቄ የመለሰው አካል ብዛትና ጥንቅርም የመልሱን ያክል ለወደፊቷ ኢትዮጵያ ሰላምና መረጋጋት እጅግ በጣም አስፈላጊ ነው። ኢትዮጵያ ምን አይነት የመንግስት ቅርፅ ያስፈልጋታል የሚለው ጥያቄ መልስ ከምሁሩ፣ከልህቃኑ፣ከወጣቶች፣ ከሴቶች፣ ከሲቪክ ማህበራትና ከተለያዩ ማህበረሰብ ተወካዮች በአገር አቀፍ ደረጃ ከሚደረግ የምክክር ሂደት ውስጥ ነው መምጣት ያለበት።
ምን አይነት የመንግስት ቅርፅ ያስፈልገናል የሚለው ጥያቄ ውስብስብ ጥያቄ ነው፣ መልሱ እንደየአገሩ ማህበራዊ አደረጃጀት፣የእድገት ደረጃ፣ የዲሞክራሲ ልምድና የፖለቲካ ባህል ይለያያል። የመንግሥት ቅርፅ፣ የምርጫ ሥርዓትና የመንግሥት መዋቅር እጅግ በጣም የተወሳሰቡና እርስ በርስ የተቆላለፉ የዲሞክራሲ ተቋሞች ናቸው። ደግሞም እነዚህ ግዙፍ የዲሞክራሲ ተቋሞች እንደ ኢትዮጵያ ከረጂም ግዜ ግጭትና የርስ በርስ ጦርነት ተገላግለው ዲሞክራሲያዊ ሽግግር በሚያደርጉ አገሮች ውስጥ ምን ግዜም ቅድሚያ የሚሰጣቸው ተቋሞች ናቸው። ከእነዚህ ሦስት የዲሞክራሲ ተቋሞች ውስጥ አንዱን ስንመርጥ ምርጫው በተቀሩት ሁለቱ ምርጫዎቻችን ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖ ያደርጋል። ይህ ማለት ደግሞ የመጀመሪያው ምርጫችን ከተበላሸ የተቀሩት ሁለት ምርጫዎቻችን ገና ከጅምሩ የተበላሹ ሊሆኑ ይችላሉ ማለት ነው። ስለዚህ ለኢትዮጵያ ይበጃል ብለን የምንመርጠውን የመንግስት ቅርፅ ስንመርጥ፣ ምርጫችን የፌዴራል ሥርዓታችን የተዋቀረበት መንገድ እንዴት መሻሻል አለበት ከሚለውና ምን አይነት የምርጫ ሥርዓት ያስፈለገናል ከሚለው ጥያቄ ጋር አብሮ መታየት አለበት።
በቅርቡ ከጠ/ሚ አቢይ አህመድ መንግስት አካባቢ የተሰማው ኢትዮጵያን ፕሬዚደንታዊ አገር እናደርጋታለን የሚለው ዜና መልካም ዜና ነው፣ ግን አጨብጭበን የምንቀበለው ዜና አይደለም። ይህ አጋጣሚ ከብዙ ጥያቄዎች ጋር ጠ/ሚኒስትሩንና ፓርቲያቸውን የምንሞግትበት አጋጣሚ መሆን አለበት። ለምሳሌ፣ ፕሬዚደንታዊ የመንግስት ቅርፅን የምንከተል ከሆነ ከዚህ አዲስ የመንግስት ቅርፅ ጋር አብረን ዲዛይን የምናደርገው የምርጫ ሥርዓት የቱ ነው የሚለውን ጥያቄ መጠየቅ አለብን፣ ከዚህ በተጨማሪ ህገመንግስቱን አሻሽለን የፓርላማ ሥርዓትን በፕሬዚደንታዊ ሥርዓት ስንቀይር ይህንን ትልቅ ውሳኔ የሚወስነው ማነው የሚል ጥያቄም መጠየቅ አለብን። ከሁሉም በላይ ደሞ የኢትዮጵያ ህዝብ ላለፉት 29 አመታት ህገ መንግስቱ ይሻሻል ብሎ የጠየቀው ጥያቄ ጠቅላይ ሚኒስትር አቢይና ፓርቲያቸው ብልፅግና ለሚፈልጉት ጉዳይ ብቻ ነው ወይ መሻሻል ያለበት የሚል ጥያቄም መጠየቅ አለብን።
ኢትዮጵያ በብሔር የተከፋፈለችና በተለያዩ ብሔሮቿ በተለይ በሶስቱ (ኦሮሞ፣ትግሬና አማራ) ብሔሮች መካከል በመሳሪያ የታገዘ ከፍተኛ የሥልጣን ፉክክር የሚታይባት አገር ስለሆነች ዛሬ በስራ ላይ ያለውን የምርጫ ሥርዓት ሳንቀይር የፓርላማ ሥርዓቱን በፕሬዚደንታዊ ሥርዓት ብንተካው፣ ላለፉት ሰላሳ አመታት በዘር ግድግዳ ለያይቶ ያኖረንና በተለይ ባለፉት አምስት አመታት ደሞ አላስቆም አላስቀምጥ ያለንን፣ ያዋጋንን እና ሰላም የነሳንን የብሔር ፖለቲካ ጭራሽ እናባብሰዋልን እንጂ የናፈቀንን ሠላምና መረጋጋት አንፈጥርም!
እንከን የሌለበት ወይም ፍጹም የሆነ የመንግስት መዋቅር፣የመንግስት ቅርፅና የምርጫ ሥርዓት የለም። የትኛውንም የመንግስት ቅርፅ ከየትኛውም የምርጫ ሥርዓት ጋር አያይዘን ዲዛይን ብናደርግና አዲስ የፖለቲካ ሥርዓት ብንገነባ ችግር የለሽ የፖለቲካ ሥርዓት ገነባን ማለት አይደለም። የትኛውንም ተቋም ብንመርጥ የመንግንስት ቅርፅ፣ የመንግስት መዋቅርና የምርጫ ሥርዓት የየራሳቸው ደካማ ጎን አላቸው። ትልቁ ቁም ነገርና ውሳኔ የትኛውን ተቋም ነው ከነደካማ ጎኑ መቀበል ያለብን የሚለው ጥያቄ ነው፣ ወይም የምንመርጠው የመንግስት መዋቅር፣የመንግስት ቅርፅና የምርጫ ሥርዓት ምን እንዲያስወግዱልን ነው የምንፈልገው፣ ምንስ አዲስ ነገር ይዘውልን እንዲመጡ ነው የምንፈልገው የሚለው ጥያቄ ነው።
አሜሪካና ኢትዮጵያ እጅግ በጣም የተለያዩ አገሮች ናቸው፣ ስለዚህ አሜሪካ ውስጥ የሰራው ፕሬዚደንታዊ የመንግስት ቅርፅ ኢትዮጵያ ውስጥም ይሰራል ማለት አይደለም። በእርግጥ አሜሪካ የዲሞክራሲ አገር እንደሆነች ኢትዮጵያም የዲሞክራሲ አገር መሆን አለባት፣ ኢትዮጵያ ውስጥ የምንገነባው ዲሞክራሲ ግን ኢትዮጵያን እንጂ አሜሪካንን መምሰል የለበትም። ስለዚህ ይህ ከሰሞኑ የተጀመረውን ኢትዮጵያን ፕሬዚደንታዊ ዲሞክራሲ እናደርጋታለን የሚለውን ሩጫ ጋብ አድርገን፣ለኢትዮጵያ የሚያስፈልጋት የትኛው የመንግስት ቅርፅ ነው (የአሜሪካኖቹ አይነት ፕሬዚደንታዊ ሥርዓት ነው፣የፈረንሳዩ አይነት ጠቅላይ ሚኒስትር-ፕሬዚደንት ሥርዓት ነው፣የሩሲያው አይነት ፕሬዚደንት-ፓርላማ ሥርዓት ነው ወይስ ዛሬ በስራ ላይ ያለውን ፓርላማዊ ሥርዓት ኢትዮጵያን እንዲመስል አድርገን እንደገና በአዲስ መልክ ማዋቀር ነው ያለብን) የሚለውን ጥያቄ በጥሞና አይተን በጥናትና ምርምር ላይ የተመሰረተ አጥጋቢ መልስ መመለስ አለብን። ያለምንም ጥናትና ምርምር እኛ በግላችን የምንፈለገውን የመንግስት ቅርፅ በመላ መርጠን ችግር ውስጥ ያለችውን አገራችንን ሌላ ተጨማሪ ችግር ውስጥ ከምንከት፣ግዜ ወስደን መልሱን የተለያዩ የማህበረሰብ ክፍሎችን ባካተተ፣ ነጻና ግልጽ በሆነ አገራዊ ምክክር መድረክ ላይ ብናገኝ ይሻላል። ደግሞም እራሳችንን ብቻ ከምናዳምጥ አይናችንን እና አዕምሯችንን ከፍተን ወደ ውስጥም ወደ ውጭም መመልከቱ በጣም ይጠቅማል። ባለፉት 35 አመታት በተለይ ከሶቪየት ህብረት መፈራረስ በኋላ ዲሞክራሲን ከገነቡና ከረጂም ግዜ ግጭትና የርስበርስ ጦርነት ተላቀው ዲሞክራሲያዊ ሽግግር ያደረጉ አገሮችን ልምድ ጠጋ ብሎ መመልከቱ አገራችንን ቤተ ሙከራ ከማድረግና በአገርና በህዝብ ላይ በቀላሉ የማይታረም ስህተት ከመስራት ያድነናል።
በመጨረሻም ለጠሚ አቢይ አህመድ ያለኝ ምክር- ፕሬዚደንታዊ የመንግስት ቅርፅን ለኢትዮጵያ ይበጃል የምንለው ከላይ በተጠቀሰው መንገድ መጓዝ ያለብንን ጉዞ ሁሉ ከተጓዝን በኋላ ነው እንጂ የኢትዮጵያ የመጀመሪያው በህዝብ የተመረጠ ፕሬዚደንት እሆናለሁ ከሚል ህልም ተነስተን አይደለምና፣ከልጅነትዎ ጀምሮ በቤተሰብ ደረጃ የተነገሮትን ትንቢት አፈጽማለሁ ብለው አገራችን ላይ ትልቅ የታሪክ ጠባሳ ጥለው እንዳያልፉ አደራ እላለሁ። ኢትዮጵያ የሁላችንም አገር ናት፣የምንገነባትም የምንጠብቃትም ሁላችንም ነን እና፣ እንደ አንድ አገር ህዝብ ሁላችንንም የሚመለከቱ ወይም በሁላችንም ላይ ተፅዕኖ ይዘው የሚመጡ ጥያቄዎችን በጋራ መመለስ አለብን። በሚቀጥለው ጽሁፌ ፕሬዚደንታዊ፣ ፓርላማዊና ግማሽ ፕሬዚደንታዊ የመንግስት ቅርፅ ሲባል ምን ማለት ነው? የእነዚህ የመንግስት ቅርጾች ጠንካራና ደካማ ጎን ምን ይመስላል የሚለውን ይዤ እስክመጣ በቸር እንሰንብት!