October 20, 2023
33 mins read

አደንዛዥ እጾችና የሚያሳብዱ ሱሶች!

በስዊድን የኢትዮጵያ አንድነት ራድዮ የስነጽሑፍ ክፍል የተዘጋጀ

ጥቅምት 4 ቀን 2016 ዓም(15-10-2023)

የአደንዛዥ እጾች ጉዳይ ሲነሳ በህሊናችን የጥቂት እጽዋት ብቻ መስሎ የሚታዬን ብዙዎች ነን።ግን ብዙ ከእጽዋት የተለዩ አደንዛዦችና የሚያሳብዱ ሱሶች እንዳሉ ከምናይበትና ከምንሰማበት ደረጃ ላይ ለመድረስ በመቻላችን በዚህ ጽሑፍ በጥቂቱም ቢሆን ለመተንተን እንወዳለን።

መደንዘዝ ማለት ስሜት አልባ መሆን፣ለምንም ነገር የማይጨነቅ፣ሕመምና ስቃይ የማይሰማው፣ የማይሞቀው ወይም የማይበርደው፣የሚንቀሳቀስ ግን በድን የሆነ ማለት ነው። ማደንዘዣ ለተለያዩ ተግባራት ሲውል የሁሉም ተግባር ግን ሰብአዊ ስሜትን የሚያርቅና ለሆነው ነገር ሁሉ ምላሽ ለመስጠት ከማይችሉበት ደረጃ ላይ የሚጥል ዘዴ ነው።

ማደንዘዣ በመልካም ወይም በጎጂ መልክ የሚታይ ይሆናል። አንድ በሽተኛ ለደረሰበት ጉዳት ወይም ሕመም የቀዶ ጥገና ሕክምና ቢያስፈልገው ሐኪሙ በሚወሰደው አካልን የመሰንጠቅ፣የመቀጠል ወይም የማሶገድ እርምጃ ሕመም ሳይሰማው ለተወሰነ ጊዜ በግማሽ ሞት ውስጥ ሆኖ የሚታከምበት ፣ ህይወትን ለማትረፍ ሲባል በመርፌ ወይም በጋዝ መልክ የሚሰጥ የማደንዘዣ ብልሃት ነው።እንዲህ አይነቱ ማደንዘዣ በክፋት የሚታይ ሳይሆን ለዕድሜ ቀጥል የሚደረግ የበጎ ውጤት መሳሪያ በመሆኑ የሚጠላና የሚወገዝ አይሆንም።

ከዚህ የተለዬ ዓላማ ላላቸው ውጤቶች መዳረሻ በመሆን በማደንዘዣነት የሚያገለግሉ እጽዋትና ጥንስሶች ብዙዎች ቢሆኑም ከታወቁት መካከል ብንጠቅስ ኮኬን፣ጫት፣አልክሆል፣ሃሽሽ በዓለም አቀፍ ደረጃ አደንዛዥ እጽዋት ተብለው ከታወቁት መካከል ዋናዎቹ ናቸው። በነዚህ እጾች ሱስ የተለከፉ የብዙ ሰዎች ህይወት ሲቀጠፍ፣ ኑሯቸው ሲናጋ፣የሰውነት ደረጃና ክብራቸው ወርዶ ከቁሻሻ በላይ ተንቀውና ተጠልተው እንደ ሰው ሳይኖሩ ለመሞት የሚበቁበት አሳዛኝ ክስተትን ለማዬት ብዙ ውጣ ውረድ፣እረጅም መንገድ ሳንሄድ፣በቅርብ እርቀት ላይ በገሃድ ከምናይበት ወቅት ላይ ደርሰናል።በዚህ አጥፊ የመደንዘዝ ሱስ ውስጥ ለመግባት ብዙ ምክንያቶች ቢኖሩም ዋናው ምክንያት ግን የማደንዘዣ ምንጩን የሚያደርቅና ለሰለባዎቹ የመከላከል እርምጃ ለመውሰድ የሚሻ ህብረተሰብ ወይም መንግሥት አለመኖሩ ነው።

የአደንዛዥ እጹ አምራቾችና አከፋፋዮች ከመንግሥት ተቋም ሃላፊዎችና ሠራተኞች ጋር የጥቅም ቁርኝት ስላላቸው ይህንን ዜጋ በተለይም ወጣቱን ትውልድ በሚቀጭ ልማድ ላይ የታይታ ካልሆነ በቀር ቆምጨጭ ያለ ዘላቂ እርምጃ ሲወስዱ አይታይም።ይባስ ብሎ የሚያስገኘው የገንዘብ ግብአት ከፍተኛ ስለሆነ መንግሥት እራሱ አምራችና አከፋፋይ የሆነባቸው አገራት አልጠፉም።የሚሰጡት ምክንያት ግን ጤናን የሚጎዳ መሆኑ እዬታወቀ ለጤና መንከባከቢያ የሚረዳ መድሃኒት ነው የሚል ፕሮፓጋንዳ በመንዛት ነው።

በዚህ የማደንዘዣ እጽ ብዙ የከበርቴ አገራት ዜጎች ተለክፈዋል።ከቱጃር እስከ ሙልጭ ያለው ድሃ በዚህ ሱስ ተይዟል።በዬቀኑና በየሰዓቱ ካላገኘ የቀን ተግባሩን ማከናወን ቀርቶ እንደሰው ማሰብ አይችልም። ሃብታሙ ለመዝናናት፣ወጣቱ ለጉራና ለዝና፣ለአብሮነት፣ሲል ሱሰኛ ሆኗል።የሱስ ደረጃው እያደገ ሲሄድ ግን የሁሉም እጣ ፈንታ ከነበሩበት ደረጃ ተከስክሰው፣ቤትና ቤተሰባቸውን አፍርሰው ወይም ጥለው መንገድ ዳር መውደቅና በተለያዩ በሽታዎች ተለክፈው አይሞቱ ሞትን የሚቀበሉ መሆን ነው።የደሃ አገር ዜጎችማ በዚህ ሱስ ከተለከፉ ህይወታቸው ወይም ኑሯቸው ከድጡ ወደማጡ ይሆንባቸዋል። ያንንም ታዝበናል።

ሌላው የማደንዘዣ ሱስ አይነት ደግሞ ከእጽዋት ጋር ያልተያያዘ ዝሙት(ሴሰኝነት)መጠጥ፣

ገንዘብ(ንብረት)ሥልጣን፣ፍርሃት፣ጎሰኝነት ወይም ዘረኝነትና አክራሪነት ናቸው።በእነዚህ ሱሶችና ከላይ በተጠቀሱት የእጽዋት ሱሶች የተለከፉ ሰዎች አድርጉ የተባሉትን ከማድረግ የማይመለሱ የጥፋት ማሽኖች በመሆን ሌሎች በተለይም በመንግሥት ሥልጣን ላይ ለተቀመጡ ሰዎች መገልገያ የወንጀል መልእክተኞች ይሆናሉ።ሌላውን በመሰለል፣በመግደልና በማስገደል ተልእኮ ይሳተፋሉ።በነዚህ ሱሰኞች ምክንያት አገራት በጠላቶች መዳፍ ውስጥ እንዲወድቁ የባንዳነት ተግባር ከመሰለፍ ባለፈም የአገር ምስጢር አሳልፎ በመስጠት፣አገር ወዳዱን በማጋለጥና በማጥቃት ግንባር ቀደም ሚና መጫወታቸውን ከብዙ የአገራት ትግልና ሕዝባዊ ንቅናቄ እንዲሁም አሁን አገራችን ከደረሰችበት ውድቀት ውድቀቶች ታዝበናል።

በዝሙት ሱስ የተለከፈ ለጠላት አስቸጋሪ የሆነ ወይም በወንጀል ሥራ ላይ አልተባበርም አሻፈረኝ ያለን ግለሰብ በደካማ ጎኑ በዝሙተኛነቱ በሚያማልሉ የሴት ሰላዮች በኩል ትጥቁንም ልቡንም እንዲፈታ ይደረጋል።ገንዘብና ንብረት የሚያሳሳው ሆዳም ደግሞ በዚያው ድክመቱ ለማይፈለግና ለጸረ ሕዝብ ተልእኮ የሚሰለፍ ይሆናል። በመጨረሻ ላይ ግን የሚሳሳለትን ገንዘብ ሃብትና ንብረት ሳይጠቀምበት የውሻ ሞት ይሞታል።ፍርሃት ደግሞ ሌላው ለባርነት የሚዳረጉበት ማደንዘዣ ነው።ለዚያም ነው

ጀግና ይሙት ፈሪ ይኑር ቢሻው

አተላ መሸከም ይችላል ትከሻው የተባለለት።አዎ ፈሪ ሰው እንኳንስ ለሌላው ይቅርና ለራሱም አይሆንም።ክብረቢስ ወራዳ ነው።በፍርሃቱ ሌላውን አሳልፎ ይሰጣል፣ለአምባገነኖች ሥርዓትም መሣሪያና አገልጋይ ይሆናል።ለእውነት አይቆምም፤ጀግኖች ሲዋደቁና ሲታገሉ በፍርሃት ይርዳል። የሚያሳዝነው ግን ፈርቶም ከመከራና ከስቃይ አለመዳኑ ነው።በቁሙ የሞተ ቢሆንም ለሁለተኛ ጊዜ ከዘለዓለማዊ ሞት አይተርፍም።በታሪኩም የሞተ ይሆናል።

ሥልጣንም አንዱ የማደንዘዣ መንገድ ነው። በሥልጣን ፍቅር የተለከፉ ሰዎች ከሥልጣን በላይ የሚወዱትና የሚሞቱለት ቁም ነገር የለም።አገራቸውን ቀርቶ እናታቸውን፣የወለዱትን ልጅም ሳይቀር አሳልፈው ይሰጣሉ።በዚህ ድክመት የተለከፉ ሰዎች ቢመከሩ አይሰሙም ፣ለነሱ አገር፣እናትና ልጅ ሁሉም ነገራቸው የብጣሽ ሥልጣን ባለቤት መሆን ነው።ነገርን ነገር ያነሳዋልና አንድ ነገር እናንሳና ሥልጣን እንዴት ከሰውነት የሚያወጣ የአረመኔ መንፈስ እንደሚያላብስ እንመልከት።

የዛሬ 50 ዓመት ሊሆነው ነው ፤በአገራችን ሕዝባዊ እንቅስቃሴውን ተከትሎ የወታደር ስብስብ አስተባባሪ ደርግ ተብሎ ሲመሠረት በወሬ ችሎታው የስብስቡ ሊቀመንበር የሆነው መንግሥቱ ሃ/ማርያም የተባለ እርኩስ ጨካኝ ሰው መመረጡን የሰማው የመጣበት በምሥራቅ ኢትዮጵያ ሐረር የሚገኘው ሦሥተኛ ክፍለጦር ስላልመረጥንህ ተመለስ ብሎ ተቃውሞ ሲያደርግና ወደ ጦሩ እንዲመለስ ሲጠይቀው እምቢ በማለቱ የጦሩ አባላት ካልመጣህ በቤተሰቦችህ(በሚስትህና በልጆችህ )ላይ እርምጃ እንወስዳለን ሲሉት ብትፈልጉ ቀቅላችሁ ብሏቸው እንጂ ከቦታዬ ንቅንቅ አልልም በማለት የሰጠው መልስ ሥልጣን ምን ያህል ጨካኝ እንደሚያደርግ ላቀረብነው ትንታኔ ማስረጃ ይሆናል።የጦሩ አባላት ከባህልና ተለምዷችን ተነስተው ምንም ጨካኝ ቢሆን የሰው ልጅ በሚስትና በልጆቹ ላይ አይጨክንም የሚል ሰብአዊ አስተሳሰብ ነበራቸው።መንግሥቱ ሃ/ ማርያም ግን ልጆቹም ቢቃወሙት ኑሮ እነሱንም ቢሆን እርሱ እራሱ ቀቅሎ ከመብላት እንደማይመለስ በፈጸመው ጭካኔ አሳይቶናል።ለመሆኑ ልጆቹ በነሱም ላይ የፈረደባቸው ጨካኝ አባት መሆኑን ያውቁ ይሆን?ካላወቁ በዚህ አጭር የታሪክ ምስክርነት ይወቁት እንላለን። በአገራችን አባባልማ ጎሽ ልልጇ ስትል ተወጋች ነበር፤ይህ አረመኔ ግን በጨካኞች እጅ ስላልወደቁ አልሞቱም እንጂ ልጆቹንና ሚስቱን ለእርድ አሳልፎ ሰጥቶ ነበር።

አሁንም በአንዳንድ ደካማ የሥልጣን ሱሰኞች በኩል በአገራችንና በወገናችን ላይ የሚደርሰው በደል የሚዘገንን ነው።ሥልጣን ይዘናል ባሉበት ቦታ የሚኖረውን ሕዝብ ለሥልጣናቸው ጭዳ በማድረግ ላይ ተሰልፈዋል።የፈነደቁበት መስክና ሜዳ፣የጠጡት ውሃ፣ያሳደጋቸው ማህበረሰብ ምን ይለናል አይሉም፤ ህሊናቸውን የሥልጣን ሱስ በውዞታል።በፓርቲና በሌላ አደረጃጀት የሥልጣን ባለቤት የሆኑት ከንቱዎች የሥልጣን ባለቤት መሆን የሚገባውን ሕዝብ እያሳደዱ በመግደል፣በማሰር፣በማፈናቀልና በማሳደድ ላይ ተሰማርተዋል።ይህን ሁሉ ወንጀል የሚፈጽሙት ግን በዛው ባልታደለውና በሚነገድበት ሕዝብ ስም ነው።አይምሮ ያለው ሰውማ ሥልጣን ባፍንጫዬ ይውጣ እንጂ የወንጀል ተባባሪ አልሆንም ብሎ እዬታገላቸው ነው። ይዋል ይደር እንጂ የውርደት ካባ የሚለብሱበት ጊዜው እሩቅ አይሆንም፤ አሁንም ጀንበር እዬጠለቀችባቸው ነው።

ሌላው የማይጠረጠረውና የማይጠበቀው የማደንዘዣ መንገድ ሃይማኖት ነው። የሰው ልጅ ለፈጣሪ ባለው ክብርና ፍቅር በሚመስለው የሃይማኖት መንገድ ይሰለፋል።የሃይማኖቱን አስተምሮ በማክበር ከክፉ ሥራና ድርጊት ለመራቅ ይሞክራል።ሃጢያትን ይጠዬፋል፣የፈጣሪን ትዕዛዝ በመቀበል በተግባር ለመተርጎም ይጥራል።በክርስቲያንም ሆነ በእስልምና ፣በቡድሃም ሆነ በአይሁድ—ወዘተ እምነቶች መግደል፣መስረቅ፣መዋሸት፣መክዳት፣መጥላት፣ምቀኝነት፣ዘረኝነት—ወዘተ የሚኮነኑና የተጠሉ መርህና አስተምሮ ናቸው። እነዚህን በፈጣሪ የተጠሉ ስነምግባሮች የሰው ልጅ እንዳይፈጽማቸው የዬሃይማኖት አባቶች ፊታውራሪ ሆነው እንዲከላከሉ ሃይማኖታዊ፣መለኮታዊና መንፈሳዊ አደራ ተጥሎባቸዋል።ስለሆነም ሁሉም የዬሃይማኖቱ ተከታይ ለሃይማኖት አባቶች ትልቅ አክብሮት አለው፤ ያሉትን ይሰማል፤ያዘዙትን ይፈጽማል።

በዚህ የመንፈሳዊ ሃላፊነት ቦታ ላይ የተቀመጡ ሰዎች ከሰይጣንና ከሥጋዊ ዓለም ብዙ ፈተና ይደርስባቸዋል፣ያንን ፈተና በጾምና በጸሎት ብሎም በጽናት የሚቋቋሙት በጣም ትንሽ ዕድለኞቹ ናቸው።አብዛኛዎቹ ሥጋዊ ድሎትና የዓለም ህይወት እያጓጓቸው ይሸነፋሉ።የተሰጣቸውን የክብር ቦታ ለሥጋዊ ድሎት መጠቀሚያ ያደርጉታል።የመንፈስ ልጆቻቸውን ክደው ከአምባገነኖች ጋር ይቆማሉ፣ ንጹሃን ሲገደሉና መከራ ሲያዩ በማውገዝና በመቃወም ፈንታ አይዟችሁ ይህንን አላፊ ምድራዊ ዓለም ሳይሆን የዘላለም ቤታችሁን የሰማዩን እያሰባችሁ ቻሉት ይላሉ።አልፈው ተርፈውም መንግሥትን ፈጣሪ መርጦ ያስቀምጣል፣ስዩመ እግዚአብሔር ስለሆነም በአምላክ ፈቃድና ምርጫ ሥልጣን ላይ የተቀመጠን አትቃወሙ፣ታዘዙ፣እንደሾማቸው ሁሉ ሊሽራቸውም የሚችለው ፈጣሪ ነውና የእርሱን ውሳኔ ጠብቁ!በሱ ሥራ አትግቡ!ይላሉ።ግራ ፊታችሁን ቢመቷችሁ ቀኙን ፊታችሁን ስጡ እንጂ ግብግብ አትግጠሙ የሚልም ትምህርት ይሰጣሉ። ይህ አስተምሯቸው ከዶግማና ቀኖና ውጭ መሆኑን አይቀበሉም።እንደውም ለሰላም የቆሙ መሆናቸውን የሚያሳዩበት አድርገው ይቆጥሩታል።ኦ! ሰላም ሆይ! በስምሽ ስንት ግፍ ተሠራ!

ላለፉት ዓመታት ሳይሆን ዘመናት በእምነት ተቋሞቻችን ያዬነው ድክመትና የአባቶቻችን አድርባይነት ተቆጥሮ አያልቅም።ከመጣ ከሄደው ሥርዓት ጋር እጅና ጓንት ሆነው በሕዝቡና በአገራችን ላይ ወንጀል ፈጽመዋል።ቤተእምነቶቻችን ሲረክሱ በዝምታ አልፈዋል፣ባህልና እሴቶቻችን ሲደፈሩ በአርምሞት ተቀምጠዋል።ከሃይማኖታዊው መመሪያ ይልቅ ለቤተመንግሥት ትእዛዝ ጆሯቸውን ሰጥተዋል፣ አስፈጻሚም ሆነዋል።በአክራሪዎች ቤተመቅደስና መስጊድ ሲደፈር፣ሲቃጠል፣ምእመናን ሲታረዱ በንስሃና በትዕግሥት ስም፣ክፉን በክፉ አትቃወመው በሚል ሽፋን ለወንጀለኞቹና ወንጀሉን ላስፈጸመው ሥርዓት ጥብቅና ቆመዋል።ክርስቶስ ሳይቀር ቤተ መቅደሱን የንግድ መናኸሪያ ሊያደርጉ የሞከሩትን ፈሪሳውያንን፣የአባቴ ቤት የናንተ ሸቀጥ ማረገፊያና መደርደሪያ አይሆንም ብሎ በጅራፍ ገርፎ ያባረረውን በምሳሌነት አልተጠቀሙበትም።በሥልጣን ላይ ያለው አገር አጥፊ ሃይማኖት ከላሽ ቡድን ኑ እሺ፣ሂዱ እሺ፣ተኙ እሺ፣ተነሱ እሺ ሲላቸው ሳያቅማሙ ሁሉንም እሺ ለማለት የሚሯሯጡ ሆነዋል።በአቡነጴጥሮስ አገር ተወልደው አድገው ማዕረገ ክህነት ይዘው የአቡነ ጴጥሮስን አንድ ግራም ታህል ለአገርና ለሃይማኖት የመቆም ወኔ የማይታይባቸው ሆነዋል።በሚነዱት መኪናና በሚኖሩበት ቪላ፣በሚከፈላቸው ደመወዝ፣አንዳንዶቹማ የሕንጻ ባለቤቶች መሆናቸው፣እንደ ቁንጅና ተወዳዳሪ የማሳጅና የውበት ሳሎን ደንበኞች የሆኑ መኖራቸው ይነገራል። በምድራዊ ጥቅም ደንዝዘው ምእመናኑንም ያደነዝዛሉ።በሙስናና በግዥ ዲያቆን፣ቄስና ጳጳስ የሚሆኑበት አገር እነዚህን ለማብቀል ምን ይገደዋል?እነዚሁ ጉደኞች በተጥለቀለቁበት ዘመን ተጠምቆ ክርስቲያን የሆነ ደሃ ነፍስ አባት የለውም፣ ቢሞት ፍትሓት አይደረግለትም።እምነትና አገልግሎት በገንዘብ የሚሸምቱt ሸቀጥ ሆኗል። ቄስና ደብተራው ለነፍስ አባትነት የሚሯሯጠው በከበርቴና በቪላ ሰፈር ነው።በዬወሩ ብቅ ብሎ ጠበል ሲረጭ ለታክሲ ተብሎ የሚሰጠው ገንዘብ ቀላል አይደለም።በደሳሳ ሰፈር የሚኖር፣ጦሙን ውሎ የሚያድር ደሃ ከዬት አምጥቶ ይችለዋል? በቤተክርስትያኒቱም ውስጥ ለውጥ ያስፈልጋል።ወደነበረችበት ክብሯ መመለስ አንዱ የአገራዊ ትግሉ አካል መሆን አለበት።

ከራሳቸው አልፈው ተርፈው ሕዝቡን ለወንጀለኛው ሥርዓት ጸጥ ሰጥ ብሎ እንዲገዛ በሽምግልና ስም በመላላክ ትግሉን ለማዳከምና እጁን አሳልፎ ለመስጠት ያላሰለሰ ሙከራ ካደረጉት መካከል ዋናዎቹ የቤተክህነት አባቶች ናቸው።በማህበረሰባችን አመለካከት ቄስና ጳጳስ ትልቅ ክብርና ተሰሚነት ስላለው ያንን በመጠቀም ለሥርዓቱ እንዲያጎበድድ እምቢ ብሎ መሣሪያ አንስቶ ለአገሩ አንድነትና ክብር ለራሱም ህልውና የሚታገለውን ሕዝብ ትጥቁን ለማስፈታት ተላላኪ የሆኑት እነዚሁ የሃይማኖት አባቶች ናቸው።በተግባራቸው የሃይማኖት አባቶች ከማለት ይልቅ የሞት መልእክተኞች፣የባርነት ጠበቆች ማለቱ ይቀላል።የዚህ አይነቱ የሃይማኖት አባቶች የሥርዓት አገልጋይነት በእኛ አገር ብቻ ዬታዬና የተጀመረ አይደለም።በሌሎቹም አገራት ለለውጥ በተደረገ ሕዝባዊ ትግልና በሥርዓቱ ላይ በተነሱ አመጾች ወቅት የተንጸባረቀ ችግር ነው፣ለዚያም ነው የግራ ፖለቲካ ፈላስፋ፣የምጣኔ ሃብትና የማህበረሰብ ሊቅ የሆነው ካርል ማርክስ በአውሮፓ በተካሄደው የሕዝብ ትግል ወቅት የሃይማኖት አባቶች ከሥርዓቱ ጎን ሆነው ትግሉንና ታጋዩን በመገዘትና በመርገም ከትግሉ እንዲያፈገፍግ ሲያደርጉ ተመልክቶ የሃይማኖት አባቶችን የማደንዘዣ ኪኒኖች(Opium of society) በማለት የገለጸው።በእኛ አገር ቀሳውስቱና ጳጳሳቱ ለአገራቸውና ለእምነታቸው ብሎም ለሕዝባቸው የማይቆረቆሩ ከሆነና ከሥርዓቱ ጋር እንከፍ እንከፍ እንላለን ካሉ ያለው ምርጫ እነሱንም ከሥርዓቱ ጋር አብሮ ማሶገድ ይሆናል።ጅብ ከሚበላህ ይልቅ በልተኸው ተቀደስ ተብሏልና!

ሌሎቹ ማደንዘዣዎች ደግሞ በምሑር ስም የትምህርት ደረጃቸውን መከታ አድርገው ለሥርዓቱ ጠበቃ በመሆን የሕዝቡን ትግል በጽሁፍም በስብሰባም ለማዳከም እላይ እታች የሚሉት ናቸው። በሚወረወርላቸው የሥልጣን ቁራጭ፣በቤትና መሬት እንዲሁም የገንዘብ ተፋሰስ የሥርዓቱ አርበኛ የሆኑ በምሑር ስም የሚነግዱ ብዙ ናቸው።እነዚሁ ጉደኞች ሰሞኑን ይዘው ብቅ ያሉት ካርታ የሰላምና ድርድር የሚል ጨዋታ ነው።ከመምህርነት ወደ አባ ሰላማነት ተቀይረው መጥተዋል።እርግጥ ነው ሰላምን የሚጠላ የለም፤ለሕዝቡም ትግል ምክንያት የሆነው ሰላምን ለማስፈን ሌላ ዘዴ ተሞክሮ ስላልተሳካ ነው።ሰላምን ያናጋ ስርዓት በመስፈኑ ነው።ለዘላቂ ሰላም የሰፈነው ስርዓት መወገድ ሲሆን ስርዓቱ ሳይወገድ አጥፊና ጠፊ ተቻችሎ ይኑር ማለት ትርጉም የለሽ ሰላም ይሆናል።ስለሆነም በዚህ መልኩ የሕዝቡን የትግል ስሜት ለማቀዝቀዝና ለማዳከም የሥርዓቱ አደንዛዥ ኪኒን የሆናችሁ ምሑራን ከአድራጎታችሁ ታቀቡ እንላለን።

በመጨረሻው ላይ በአደንዛዥ እጽነት የምናነሳው ለሥርዓቱ አገልጋይ የሆኑትን በሚድያና በጋዜጠኝነት ሙያ የተሰለፉትን የሚመለከት ይሆናል።ጦር ከፈታው ወሬ የፈታው ይባላልና አምባ ገነን ሥርዓቶች ሕዝቡን ለማወናበድና ለማደንዘዝ ከሚጠቀሙበት አንዱ ዘርፍ የጋዜጣና የሚድያ ዘርፍ ነው።ሙያው የተከበረና ብዙ ጠቃሚ የሆኑ ሥራዎችን ለመሥራት የሚረዳ፣አስተማሪና የእውቀት ምንጭ የሕዝብ ልሳን በመሆን የሚያገለግል መሆን የሚገባውና ለዚያም ዓላማ ተብሎ የተፈጠረ ተቋም ነው።ይህንን የተቀደሰ ተግባርና ሃላፊነት ለአምባገነን ስርዓት ሲውል ማዬቱ ልብ ይሰብራል። በአገራችን ይህ ተስፋ የሚጣልበት ተቋም ለዓላማና ለሚድያ ስነምግባር ያደሩ ሳይሆኑ ለሆዳቸው ሲሉ ሌት ተቀን የሚዳክሩ፣ሰዎች የሚርመሰመሱበት ከሆነ ውሎ አድሯል።አምባገነኖች ሲገሉ አዳኑ፣ ሲያፈርሱ ሰሩ፣ሲቀሙ ሰጡ፣ሲዘርፉ አስገቡ—ወዘተ በሚል ፕሮፓጋንዳ ሽፋን የሚሰጡ ጋዜጠኞች ከማለት ይልቅ አፈ ንጉሶች ማለት ይቀላል። በሕዝባችንና በአገራችን ላይ የተጫወቱትና የሚጫወቱት ሚና ቀላል አይደለም።በሁሉም ዘርፍ የደረሰውን ስብራትና ድክመት፣የሕዝብ እልቂት፣የሥርዓቱን ወንጀል በመሸፋፈን የጥቂቶችን ስኬትና የተዝናና ኑሮ በማሳዬት፣በዘፈንና አስረሽምችው ጫጫታ ትኩረት በማስለወጥ ከፖለቲካው እስከመዝናኛው መድረክ የማደንዘዣ ሚና የሚጫወቱት እነዚሁ አድርባይ የሚዲያ ባለሟሎች ናቸው። በዚህም የባለብዙ ሚሊዬን ብርና ንብረት ባለቤቶች ሆነዋል። ውድድራቸውና የሚከተሉት የኑሮ ዘይቤ ከአሜሪካና ከአውሮፓውያን የኪነትና የጋዜጣ ተዋንያኖች ጋር እንጂ ከአገር በቀሉ ደክሞ ወጥቶና ወርዶ ሃብት ካፈራው ጋር አይደለም።ማነው ማር ከሸጠ ወሬ የሸጠ ያለው?እውነተኛ አባባል ነው።በተለይም የመንግሥትን አደንዛዥ ወሬ የሚነዛ በንብ ተነድፎ ለሰዎች የሚጠቅም ማር ከሰበሰበ፣አርሶ ካመረተ፣በሽተኞችን አክሞ ካዳነ ሃኪም ይበልጥ ወሬኞች የሃብት ባለቤት የሆነበት አገር ቢኖር አንዷ ኢትዮጵያ ነች።

በርእሱ የተሰጠውን ለማጠቃለል

በየስርዓቱና በዬጊዜው ሕዝብን ለማወናበድ የተፈጠሩ፣አሳሳችና አደንዛዥ ሰዎች መኖራቸው የማይካድ ክስተት ስለሆነ ምንም እንኳን ለመጨረሻው ማሶገድና ነጻ መሆን ባይቻልም ብቅ ሲሉ ፊት እዬነሱና ፣ ለሚሉትም ጆሮ ሳይከፍቱ እያዋረዱ መመለስ ይመረጣል።ጎን ለጎንም የጋዜጠኝነትንና የሚዲያን ስነምግባር የሚያከብሩትን በመደገፍና በማጠናከር ሙያውን የባለሙያዎች ንብረት ማድረግ ከሁሉም እውነት ወዳድ ይጠበቃል።

የሕዝቡ ትግል መልክ እዬያዘና የጠላት ጎራ ሲናጥ ልማደኞቹ አድርባዮች ሰፈራቸውን ለቀው በሕዝባዊ ጎራ ሰርጎ ለመግባት በመሯሯጥ ላይ ይታያሉ።በጥቅም ሲክቡትና ሲያወድሱት የኖሩትን ሥርዓት በአንድ ጀንበር ሲያወግዙትና ሲቃወሙት ይሰማሉ።ይህንን ማድረጋቸውና የጠላት ጎራ እዬተመናመነ መምጣቱ የሚፈለግ ቢሆንም ሕዝባዊው ጎራ እጁን ዘርግቶ ሊቀበላቸው አይገባም ፣የስርዓቱ አፈ ቀላጤና ተባባሪ ሆነው ፣ከሕዝብ ተቀምቶ የተሰጣቸውን ገንዘብና መሬት ቸብችበው የፈረጠጡ የወንጀል ተባባሪዎች በሕግ ፊት ሊጠዬቁ ይገባል።በጥቅም የሚገዙና በመገለባበጥ በሽታ የተለከፉ ስለሆነ ነገ ደግሞ ከመጣው ጋር ለማጨብጨብ አይቸገሩም።ስለሆነም ሳያቀርቧቸው በርቀት መጠባበቁ ይጠቅማል።ትግሉ ደም የሚያፈሱበትና ሕይወት የሚገብሩበት እንጂ ማንም ገብቶ የሚያጨበጭብበት ሆያ ሆዬ አይደለም።በርና ባለቤት የሌለውም ወና ቤት አይደለም።በማይናወጥ ዓላማና ዲስፕሊን መመራት ይኖርበታል።

ለአደንዛዥ እጾችና፣ሱሶች ለሥርዓቱ ተላላኪዎች የተመቸን አንሁን፣

ኢትዮጵያ በነጻነትና በአንድነት ለዘለዓለም ትኑር!!

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Latest from Blog

መኮንን ሻውል ወልደጊዮርጊስ ¹⁵ የምድርም ነገሥታትና መኳንንት ሻለቃዎችም ባለ ጠጋዎችም ኃይለኛዎችም ባሪያዎችም ጌቶችም ሁሉ በዋሾችና በተራራዎች ዓለቶች ተሰወሩ ፥ ¹⁶ ተራራዎችንና   በላያችን ውደቁ በዙፋንም ከተቀመጠው ፊት ከበጉም ቍጣ ሰውሩን ፤ ¹⁷ ታላቁ የቁጣው ቀን  መጥቶአልና ፥ ማንስ ሊቆም ይችላል ? አሉአቸው ። ራእይ 6 ፤  15_17 ይኽ የመጽሐፍ ቅዱስ ቃል ። የኢየሱስን ልደት ሰናከብር የየሐንስ ራእይን ማንበብ ጠቃሚ ይመስለኛል ። ምክንያቱም በመጨረሻው ዘመን

ከኢየሱስ የፍርድ ቀን በፊት በህሊናችን ውስጥ ፍቅርን ለማንገስ እንጣር 

የምጣኔ ሀብታዊ ፍጥ፣ የፖለቲካ፣ የእውነትና የሰብአዊ መብት ታጋይ፣ የአመኑበትን ነገር ለመናገር እንደ ፖለቲከኛ በቃላት ሳያሽሞነሙኑ ቀጥታ የሚናገሩት የሀገሬ ኢትዮጵያ ታላቅ ሰው ነበሩ “ዘር ቆጠራውን ተዉት፤ የአባቶቻችሁን ሀገር ኢትዮጵያን አክብሩ!”  አቶ ቡልቻ ደመቅሳ

ሀገር ወዳዱ አቶ ቡልቻ ደመቅሳ ከዚህ አለም በሞት ተለዩ

January 6, 2025
ግን ይህ ሁሉ ወጣት የት ገባ? ግን ይህ ሁሉ ወጣት የት ገባ? ዛሬ፣ 2025 ዓ/ም ላይ ብንገኝም በዝንጋታ ገመድ ወደ ሞት እየተጎተትን እንደሆነ አናውቅም። (ሁል ጊዜ የሚሞተው የገነዝነው ይመስለናል። ) “ገብርዬ ነበረ

ግን ይህ ሁሉ ወጣት የት ገባ?

January 3, 2025
መኮንን ሻውል ወልደጊዮርጊስ ዛሬ እንደ አውሮፓዊያኑ አቆጣጠር ጥር 1ቀን 2025 ዓ/ም ነው ። አውሮፓውያኑ አዲስ ዓመትን “ሀ” ብለው ጀምረዋል ። አዲሱን ዓመት ሲጀምሩም ከልክ ባለፈ ፈንጠዚያ ነው ። ርቺቱ ፣ ምጉቡና መጠጡ

ዛሬ፣ 2025 ዓ/ም ላይ ብንገኝም በዝንጋታ ገመድ ወደ ሞት እየተጎተትን እንደሆነ አናውቅም። (ሁል ጊዜ የሚሞተው የገነዝነው ይመስለናል። )

Go toTop